የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ለዴር ሡልጣን እድሳት በፈጠረችው ዕንቅፋት የእኅትማማች ግንኙነቱ እየተበላሸ ነው፤“ጸጸትና ርኅራኄ የላቸውም” /ፓትርያርኩ/

deir-sultan

  • ገዳሙን ለማደስ የእስራኤል መንግሥት ቃል ቢገባም፣ ኮፕቶቹ ዕንቅፋት ኾነዋል፤
  • “ልቀቁና በራሳችን እናድሰው” ያሉትን፣ መንግሥትም ቤተ ክርስቲያንም ተቃወሙ፤
  • ፖፑ፥ “ጠቅላላ ገዳሙ የእኛ ነው፤ መመለስ አለባችሁ፤” በማለት ለፓትርያርኩ ጻፉ፤
  • ፓትርያርኩ፥ “በእድሳቱ አያገባችሁም፤ አንጡራ ሀብታችን ነው፤” ሲሉ መለሱላቸው፤
  • በውጭ ቢኾንም በኢትዮጵያ ቅርስነቱ መንግሥት ሊጠብቀው ይገባል፤”ሲሉ አሳሰቡ፤
  • ኮፕቶቹ፥ “መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ግፊት ያድርግልን፤” ቢሉም አልተቀበለም፤
  • ንብረታችን እንደኾነና የእኛ እናድሰው ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደሌለው አሳወቃቸው፤
  • በውዝግቡ መሀል፣ ከአብያተ መቅደሱ አንዱ የኾነው የቅዱስ ሚካኤል ጣሪያ ተሸንቁሯል፤
  • ከሺሕዎች የተሳላሚዎች ጉዞ ባሻገር፣ Save Der Sultanየተደራጀ ሉላዊ እንቅስቃሴ!!

†††

pat on der sultan

በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የታሪክና የቅድስና ይዞታችን የኾነውን የዴር ሡልጣን ገዳማችንንና የአገልጋይ መነኰሳትን ማረፊያ ቤት ለማደስ የእስራኤል መንግሥት ቃል ቢገባም፣ የባለቤትነት ጥያቄ የምታነሣው የግብጽ – ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እየፈጠረች ባለችው ውዝግብ የእኅትማማች ግንኙነታችን እየተበላሸ መኾኑን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡

ቅዱስነታቸው፣ የካቲት 24 ቀን ከተከበረው አምስተኛ ዓመት የፕትርክና በዓለ ሢመታቸው ጋራ በተያያዘ ከኢኦተቤ ቴቪ/EOTC Tv/ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በጥገና ዕጦት እየፈራረሰ የሚገኘውን የዴር ሡልጣን ገዳምና የመነኰሳቱ ማረፊያ ቤት እንዳይታደስ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ዕንቅፋት በመፍጠሯና ከዚያም አልፋ ጠቅላላ ይዞታውን ለመንጠቅ እየቃጣች በመኾኑ፣ የኹለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እየተበላሸ ነው፤ ብለዋል፡፡

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ፣ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ገዳሙን ለማደስ ቃል መግባታቸውንና በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የእስራኤል ጉብኝት ወቅት ይህንኑ ቃላቸውን ቢያረጋግጡም፤ ኮፕቶቹ ግን፣ “መንግሥት የሚላችሁን ትታችሁ እኛ እናድስላችሁ፤ በገንዘባችን፣ በመሐንዲሶቻችን እኛ በራሳችን እናድሰው፤” በማለት እድሳቱ በአፋጣኝ እንዳይከናወን ዕንቅፋት እየፈጠሩ እንደኾነ ፓትርያርኩ ተናግረዋል፡፡

“ዴር ሡልጣንን ለመጎብኘት ሔደን የእናንተ መነኰሳት ሊደበድቡን ቃጡብን፤ አናስገባም፤ አናሳልፍም አሉን፤ ፖሊስ ይዘን ብንመለስም ተከለከልን፤ ተባረርን፤” የሚል ስሞታ ይዘው ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ከመጡ ኹለት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጋራ በጉዳዩ ላይ እንደተወያዩ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ “በእኛ ሥር ኹነው እንዲቀመጡ ንገሩልን፤ ንገሯቸውና መቆያ ቦታም እንሰጣችኋለን፤ ገዳሙን ልቀቁልንና እኛ እናድሰው፤” የሚል ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው ጠቁመዋል፡፡

ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደሌለው የገለጹላቸው ፓትርያርኩ በበኩላቸው፣ “ያለፈው ይበቃችኋል፤” ቢሏቸውም ግብጻውያኑ ጳጳሳት፣ “ሳንወያይበት እድሳት የሚባል ነገር እንዳይደረግ” በማለት ለማስጠንቀቅ ሞክረዋል፡፡ የፓትርያርኩን ምላሽ ለፖፕ አባ ታዎድሮስ ማሳወቃቸውንና ፖፑም፣ የጳጳሳቱን አቋም በማጠናከር እድሳቱን ከመከልከላቸውም በላይ፣ “ጠቅላላው ገዳሙ የእኛ ነው፤ መመለስ አለባችሁ፤” የሚል ደብዳቤ ለቤተ ክርስቲያናችን እንደ ጻፉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በቃለ ምልልሱ አውስተዋል፡፡

“መነኰሳቱ እኛን አምነው በእኛ ሥር ኹነው ቢቀመጡኮ ይህ ሁሉ መከራ አይኖርም ነበር፤ እንረዳቸው ነበር፤ አኹንም ቢኾን እኛ እናድሰው፤ እናድስላችሁ፤ ይኼ መንግሥት የሚላችሁን ትታችሁ እኛ እናድስላችሁ፤ በገንዘባችን፣ በመሐንዲሶቻችን በራሳችን እኛ እናድሰው፤ ንገሯቸውና ቦታም እንሰጣችኋለን መቆያ፤እኛ እናድሰው፤ ገዳሙን ልቀቁልንና፤”


“ዴር ሡልጣን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታሪክና የቅድስና አንጡራ ሀብታችን ነው፤” ያሉት ፓትርያርኩ፣ እድሳት ከባለቤትነት ጋራ የሚያያዝ እንደኾነ ጠቅሰው፣ በቱሪስትነት እንጅ በባለቤትነት ታሪክ የማያውቃት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በእድሳቱም ጉዳይ የሚያገባት ነገር እንደሌለ ለፖፑ ደብዳቤ በአጸፌታው በላኩት የጽሑፍ ምላሽ መግለጻቸውን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የትምህርተ ሃይማኖት አንድነት ያላቸውና የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ቤተሰብ የኾኑት የኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት እኅትማማች ግንኙነት እየተበላሸ እንደኾነ ተናግረዋል – “በዚህ ኹኔታ ነው ያለው፤ ግንኙነታችን እየተበላሸ ነው ያለው በዚህ በኩል፡፡”

ኢትዮጵያውያን የቅድስት ሀገር ተሳላሚዎች የሲናይን በረሓ በእግራቸው እያቋረጡ በጥንታዊቷ ኢየሩሳሌም በርካታ ቦታዎችን ይዘውና በሕዝቡ ታወቀው ሲጸልዩ ለዘመናት በኖሩባቸው ቦታዎች፣ “የሃይማኖት ወንድሞቻችሁ ነን፤” በሚል በእንግድነት የገቡት ኮፕቶቹ፣ ቀስ በቀስ በየዋህነት ያስጠጓቸውን አባቶቻችንን እየገፉ ከገዳሙ በማስወጣትና የታሪክ ሰነዶቻችንን በማጥፋት የፈጸሙትን በደል ፓትርያርኩ በቃለ ምልልሱ በስፋት አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የታሪክና የቅድስና ይዞታ የኾነው የዴር ሡልጣን ገዳም የሚገኝበት ሥፍራ፣ አብርሃም ልጁን ይሥሓቅን ሊሠዋበት የነበረው ሲኾን፣ ጌታችንም መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ ሲጓዝ፣ ለሦስተኛ ጊዜ የወደቀበት “ዘጠነኛው ምዕራፍ” መኾኑ አያጠያይቅም፡፡ ከቆብጦቹ በፊት በኹለት የጸሎት ቤቶችና በቅዱስ ጎልጎታ ቤተ ክርስቲያን ጣሪያ ላይ በሚገኙ ክፍሎች ታሪካዊ መብቶች ነበሩን፡፡ግብጾቹ ሰፊውን የገዳሙን ክፍል ከወሰዱ በኋላ የተጀመረው ውዝግብ 240 ዓመታትን ማስቆጠሩን ያስረዱት ፓትርያርኩ፣ “ያችንም የያዝናትን የቅድስት እሌኒ ገዳም/ፍሎር/ የምትባለዋንና ኹለት ትንንሽ ቤተ መቅደሶችም ለመውሰድ እየቃጡ ይገኛሉ፤” ብለዋል፡፡

በጣሪያው ላይ የሚታዩት ጎጆ(መቃብር) መሰል ቤቶች፣ቦታችንን እናስመልሳለን በሚል ተስፋ በኮፕቶቹ የተገፉት ኢትዮጵያውያን በጊዜያዊ መጠለያነት የሠሯቸው እንደኾኑና አስከሬን ለማስወጣት እንኳ የተከለከሉበትን ወቅት በመጥቀስ የግብጻውያኑን ቀማኛነትና ጭካኔ አስገንዝበዋል፡፡ በሊቀ ጵጵስና ተመድበው ገዳማቱን ከዐሥር ዓመት በላይ ሲያስተዳድሩ እንደቆዩና ኮፕቶቹን በሚገባ እንደሚያወቋቸው ጠቅሰው፣ “ምንም ዐይነት ጸጸትና ርኅራኄ የላቸውም፤” ሲሉ ወቅሰዋቸዋል፡፡ በኢየሩሳሌም ይዞታ ባላቸው ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በዴር ሡልጣን ገዳም መደበኛ ባለቤትነት የሚታወቁትና ማስረጃም ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንደኾኑና ግብጻውያኑ በታሪክ የሚጠሩት፣ “ጎብኚዎች” /tourists/ ተብለው እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

“ደግሞኮ የሚገርመው ነገር ኹሉም ያውቃቸዋል፤ የግሪክ ኦርቶዶክስም ሌሎችም… እኛ ማስረጃ አለንኮ፤ እነርሱ በታሪክ የሚጠሩት ጎብኚዎች ተብለው ነው፤ እኛ መደበኞች ነን፤ ከጥንቶቹ ሡልጣኖችና ግሪኮች ጋራ አብሮ ነው ታሪካችን የሚነበበው በኢየሩሳሌም ታሪክ፤ እነርሱ ቱሪስትስ ነው የሚባሉት፤ ቱሪስቶች ናቸው ይሏቸዋል፤ ግሪኮችም ሌሎችም ኹሉ፤”


ገዳሙንና የመነኰሳቱን ማረፊያ ቤት ለማደስ፣ የእስራኤል መንግሥት በተደጋጋሚ የገባው ቃል በአጀንዳ ተይዞ እንዳለ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በውጭ የሚገኝ ቢኾንም፣ ቅርስነቱ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ሀገራዊም እንደመኾኑ መጠን መንግሥት ሊጠብቀው እንደሚገባ በቃለ ምልልሳቸው አሳስበዋል፡፡

Presidentr Rivlin with the Ethiopian Orthodox Patriarch in Jerusalem

ፓትርያርኩ ከሁለት ዓመት በፊት እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት፣ “ምንም ቢኾን መነጋገር የማይፈታው ነገር የለምና እንነጋገርበታለን፤ ጉዳዩን እንፈታዋለን፤” የሚል ተስፋ ከሀገሪቷ ፕሬዝዳንት የተሰጣቸው ሲኾን፤ አምባሳደሩ አቶ ህላዌ ዮሴፍ ደግሞ፣ በኤምባሲው ዓመታዊ ዕቅድ ውስጥ የዴር ሡልጣን ጉዳይ ከዋነኛ ተግባራት አንዱ ኾኖ ተቀምጦ፣ ዋና መሥሪያ ቤቱም ክትትል እንደሚያደርግበት መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡

ወደ አዲስ አበባ አምርተው ከፓትርያርኩ ጋራ ከተወያዩት ኹለቱ ግብጻውን ጳጳሳት በተጨማሪ በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደርም ቅዱስነታቸውን ማነጋገራቸው ታውቋል፡፡ ጳጳሳቱ የፓትርያርኩን አቋም ካደመጡ በኋላ ከመንግሥት ባለሥልጣናትም ጋራ የተገናኙ ሲኾን፣ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከተስማማች የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ገዳሙን ታድሳለች፤” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ አያይዘውም “ፓትርያርኩ ሊያናግሩን አልፈለጉም፤” ሲሉ ለባለሥልጣናቱ ስሞታ አቅርበዋል፤ “መንግሥት ግፊት ያድርግልን፤” ሲሉም ጠይቀዋል፤ ተብሏል፡፡

ኾኖም በባለቤትነቱም በእድሳቱም ጉዳይ ከባለሥልጣናቱ የተለየ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተገልጿል – “ንብረትነቱ የኢትዮጵያ ነው፤ የምናድሰውም ራሳችን ነን፤ የማደስም አቅም አለን፤ የሚያድስልን አንፈልግም፡፡”

የኮፕቶቹ አካሔድ፣ “ወይ እኛ እናድሰዋለን፤ አልያም ይፍረስ፤” እንደማለት መኾኑን የጉዳዩ ተከታታዮች ያስረዳሉ፡፡ የእስራኤል መንግሥት ለእድሳቱ ቃል ቢገባም፣ በአካባቢው ከሚከተለው ለግብጽ ያደላ አያያዝ አኳያ በተጨባጭ ይረዳናል ተብሎ የማይታሰብ በመኾኑ፣ በተለይ ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ ክፉኛ እየተጎዳ ያለውን ቅርሳችንን ለማትረፍና ይዞታችንን ለማስከበር መላው ኢትዮጵያውያን የተደራጀና ኹሉን አቀፍ ሉላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በተለያዩ አህጉረ ዓለም የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን፣ የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌምን መካናት ተሳልመው የልደት እና የትንሣኤ በዓላትን በታሪክና በቅድስና ይዞታቸው ለማክበር በየዓመቱ በሺሕዎች የሚያደርጉት ጉዞ በቀላሉ የማይገመትና ለመፍትሔውም ዋስትና የሚሰጥ በመኾኑ አስፋፍቶ ከማስቀጠል ባሻገር፣ ታላላቅ ብዙኃን መገናኛዎችንና ማኅበራዊ ሚዲያውን ያካተተ ተከታታይና ከፍተኛ ጫና የምናሳድርበት “ዴር ሡልጣንን እናድን”/Save Der El Sultan/የተጠናከረ እንቅስቃሴ መካሔድ እንዳለበት ጥሪ ቀርቧል፡፡

2 thoughts on “የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ለዴር ሡልጣን እድሳት በፈጠረችው ዕንቅፋት የእኅትማማች ግንኙነቱ እየተበላሸ ነው፤“ጸጸትና ርኅራኄ የላቸውም” /ፓትርያርኩ/

  1. Anonymous March 16, 2018 at 2:34 pm Reply

    እንኳን የውጪውን የአገር ውስጡንም መፍታት አልቻሉም ያሳዝናል አይ አባ ማትያስ

  2. Amanuel March 17, 2018 at 3:31 am Reply

    የኮፕት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ድርጊቷ ቀጥላ እዚህ መድረሷ ብዙም አይገርምም፤ ምክንያቱም ቀደም ብላም በተጠና እና በተጠናከረ መልኩ ታሪክ እና ቅርሱን ጠቅልላ የራሷ የማድረግ ምኞቷ የፈጠረው ለራስ የማድላት ጠንቋ ውጤት ነውና ።

    96 ዓ ም ላይም የግብጹ መነኩሴ “ፀሐይ ልሙቅ” በሚል ፈሊጥ የዋኃኑን ኢትዮጵያውያን መነኮሳትን በማታለል በየዕለቱ ፀሐይ በወጣች ቁጥር እርሳቸውም ፀሐይ በመሞቅ ሰበብ ጣራ ላይ በመውጣት በድብቅ ፎቶ እያነሱና የኢትዮጵያን ቅርሶች በሙሉ የፅብጽ (የኮፕት) ቤተ ክርስቲያን ቅርስ እና ይዞታ ነው በማለት ለዓለም ሲያስተዋዉቁ ማንም የጠረጠረ አልነበረም ።

    ኋላ ግን ይህ ድርጊት ሲ ነ ቃ መነኮሳቶቻችን ያንን ተንኮለኛ ግብጻዊ መነኩሴ በፀሐይ በመሞቅ ሰበብ በጠራራ ፀሀይ ቅርሳችንን ሊቀማ የቃጣ ቀበኛ መሆኑን በመግለጽ ዳግመኛ እዚያች ቦታ ላይ ፀሐይ መሞቅ እንደማይችል ሲነግሩት እሞቃለሁ አትሞቅም በሚል በተፈጠረ እሰጥ አገባ ጠቡ ተባብሶ ድብድብ በመጀመሩ ፈርጠምጠም ያሉት የግብፃውያን መነኮሳት ጡጫና ጥቃት በማየሉ የኛ መነኮስያይትም ይጠቅመናል ያሉትን ስልት በመንደፍ እና በርበሬ በማውጣት የግብጻውያኑ ዓይን ላይ በመበተን ዓይናቸው የተለበለበው (የተቃጠለው) ግብጻውያን እየተደነባበሩ በማፈግፈጋቸው ድሉን የኛ ለማድረግ ችለው ነበር ።

    ይህ በመሆኑም”” ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ግብጻውያኑን በበርበሬ አጠቁ”” በሚል በወቅቱ ይታተም የነበረው ኢትዮጵ ጋዜጣ በፊት ገጹ አስነብቦ ነበር።

    ዛሬ የቅርሳችን የባለቤትነት ጉዳይ አደጋ ላይ መሆኑ አይጠረጠርም አባቶቻችን ይህንን ታላቅ ቅርስ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ምቾት ሳይሰለጥንባቸው በአካባቢውም ባላቸው መወደድ እና ሞገስ ይዞታውን በማስከበር እድሜ ዘመናቸውን በብዙ መከራ ውስጥ አልፈው እዚህ አድርሰውልናል ።

    አሁን ቅርሱን ለማስጠበቅ በርበሬ ሳይሆን ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ትግል ያስፈልጋል፤ ከዚህ በተያያዥ ለቅርሱ ታላቅነት በቂ ግንዛቤ ያላቸው ወገኖቻችን ጉዳዩን እንዲይዙት ማድረግ ያስፈልጋል እነርሱም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ጊዜው ሳይቀድመን ቅርሳችንን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ መትጋት ይጠበቅባቸዋል እንጂ የኪስ ቦርሳ እንኳ የጠፋበት ሰው የሚቆጨውን ያህል ቁጭት ሳይኖር “ምንም ዓይነት ጸጸትና ርህራሄ የላቸውም” ብሎ ጉዳዩን አቅልሎ ማየቱ ተገቢ አይሆንም፤ ለርሱ ለርሱማ ከቅዱስ አባታችን በላይ ጸጸትና ርህራሄ የሌለው አለ እንዴ? ይሄን ስብዕና ይዞ መደራደርም ከባድ እኮ ነው። እርስዎ የሆኑትን እኮ ነው ሰዎቹም የሚሆኑብዎ!!

Leave a comment