ዐሥራ አራቱን ቅዳሴያት በመስኮብኛ የተረጐሙት ብፁዕ ዶክተር አቡነ ጢሞቴዎስ ዐረፉ

  • ሥርዓተ ቀብራቸው፣ ነገ ረቡዕ ከጸሎተ ቅዳሴ በኋላ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል
  • ወደ ዩኒቨርሲቲ ያደገውን አንጋፋውን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ለ20 ዓመታት መርተዋል፤
  • ዐሥራ አራቱን ቅዳሴያት በመስኮብኛ(ሩሲያ ቋንቋ) ተርጉመዋል፤ ስንክሳርን በ800 ገጾች አትተዋል
  • የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንን ለ11 ዓመታት በበላይ ሓላፊነት መርተዋል፤

***

የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ እና የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂ ብፁዕ ዶክተር አቡነ ጢሞቴዎስ ዐረፉ፡፡

የ83 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የኾኑት አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ትላንት መጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ሌሊት፣ ከዚኽ ዓለም ድካም ማረፋቸውን፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የሐዋሳ እና ጌዴኦ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ዜና ዕረፍት እንደተሰማ፣ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት እና በቅርብ ያሉ ብፁዓን አባቶች፣ ዛሬ ጠዋት በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት መወያየታቸውንና የብፁዕነታቸውን ሽኝት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡

በዚኽም መሠረት፣ ዛሬ ማክሰኞ ከቀኑ በ11፡00፣ ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሓላፊዎች እና ሠራተኞች እንዲሁም የዐዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ለብፁዕነታቸው ጸሎት ይደረጋል፡፡

ከዚኹ ጋራ ተያይዞ፣ ነገ ረቡዕ፣ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ከረፋዱ በ4፡00 ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፤ ጸሎተ ቅዳሴውም እንዳበቃ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ለረጅም ጊዜ ባገለገሉበት በዚያው በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡

በመኾኑም፣ ቅዱሳን ፓትርያርኮች እና ብፁዓን አባቶች በተገኙበት ነገ ከቀትር በኋላ በሚፈጸመው የብፁዕነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ ካህናት እና ምእመናን እንዲሁም የብፁዕነታቸው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው እና ወዳጆች፣ በካቴድራሉ ተገኝተው ሽኝት እንዲያደርጉላቸው ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ጥሪ አስተላለፈዋል፡፡

#################

የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ዜና ሕይወት እና ሥራዎች በአጭሩ

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ከአባታቸው ከባላምባራስ ተስፋ ተኰላ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ካህሳ(ወለተ ዮሐንስ) ኃይሉ፣ በቀድሞ አጠራር በትግራይ ክፍለ ሀገር በዓድዋ አውራጃ በብዘት ወረዳ በፊልፈሎ መድኃኔዓለም ቀበሌ በ1930 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡

ዕድሜአቸው ለትምህርት እንደ ደረሰ፣ የቤተ ክርስቲያንን መሠረተ ትምህርት በመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከአጎታቸው ከመልአከ ሰላም ገብረ አረጋዊ ተማሩ፡፡ ትምህርታቸው ለማስፋፋት ወደ አኵስም ተጉዘው ሐለማት ከሚባለው ቦታ እና በአቡነ ጰንጠሌዎን ገዳም ከመምህር ገብረ ዮሐንስ፣ ለሙሉ ዲቁና የሚያበቃቸውን ትምህርት ከተማሩ በኋላ በ1942 ዓ.ም. ወደ አሥመራ ሔደው፣ የኤርትራ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ማዕርገ ዲቁና ተቀበሉ፡፡

ወደተወለዱበት ብዘት ወረዳ ተመልሰው ለጥቂት ዓመታት በፊልፈሎ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በዲቁና እንዳገለገሉ፣ በዓድዋ አውራጃ በዓዲ አርባዕተ ወረዳ ወደሚገኘው ደብረ ሃሌ ሉያ አቡነ ሳሙኤል ገዳም ገብተው፣ ጸዋትወ ዜማን ከመሪጌታ ይትባረክ፣ መዝገብ ቅዳሴን ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር ተምረዋል፤ ከትምህርታቸው ጋራም በረድእነት በኋላም በመጋቢነት እያገለገሉ ሥርዓተ ምንኵስናን በ15 ዓመታቸው በዚኹ ገዳም ፈጽመዋል፤ ኃይለ ሥላሴ ይባል የነበረው ዓለማዊ ስማቸውም አባ ሀብተ ሥላሴ በሚል ተተካ፡፡ በኋላም ማዕርገ ቅስናን ከኤርትራ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ በትምህርት ላይ እያሉ የአቡነ ሳሙኤል ገዳም የንብረት አስተዳደር ሓላፊ በመኾን፥ የዕቃ ግምጃ ቤት፣ የእህል ጐተራ እና የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳዎችን አሠርተዋል፡፡ በገዳሙ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ሴቶች፣ የወንዶች ገዳም በኾነው በአቡነ ሳሙኤል ገዳም መገልገል ባለመቻላቸው ችግራቸውን ተገንዝበው ሌሎች ረዳቶችን ይዘው በራሳቸው ጉልበት በገዳሙ አጠገብ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ሠርተው ለሴቶች አገልግሎት እንዲውል አድርገዋል፡፡

ከደብረ ሃሌ ሉያ የዓመታት ትምህርት እና ከፍተኛ አገልግሎት በኋላ የዘመናዊ ትምህርት ፍለጋ በ1950 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ በዐዲስ አበባ እያሉ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ወደ ትምህርት ቤት እንዲያስገባቸው ደጅ በመጥናት ላይ እያሉ፣ በቤተ ክህነቱ አዳሪ ት/ቤት ገብቶ ለመማር መስፈርቱ የቅኔ ችሎታ መኾኑን በመረዳታቸው ወደ ጎጃም አቅንተው በእነማይ ወረዳ በምትገኘው መንግሥቶ ኪዳነ ምሕረት ከመምህር ደጉ ቅኔን አጥንተዋል፡፡ በ1950 ዓ.ም. ወደ ዐዲስ አበባ ተመልሰው፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተቋቁሞ በነበረው የፈታኝ ኮሚቴ ከሌሎች ጋራ ተወዳድረው በከፍተኛ ውጤት በማለፋቸው፣ ሐረር ወደሚገኘው የራስ መኰንን የመምህራን ማሠልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተልከው በአዳሪነት በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሦስት ዓመታት ውስጥ አጠናቀዋል፡፡

መደበኛ አገልግሎታቸውን በሐረር ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በማድረግ፣ በየክብረ በዓላቱ በሌሎችም አብያተ ክርስቲያንም እያገለገሉ የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አልፈው፣ ወደ ዐዲስ አበባ በመመለስ፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመግባት የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አገልግለዋል፤ በመንፈሳዊ ኮሌጅ ወጣቶች ይካሔድ በነበረው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በብዙ ተሳትፈዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰጠችው የነፃ ትምህርት ዕድል መሠረት፣ ከአራት ቀሳውስት እና ዲያቆናት ጋራ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ወደ ሶቭየት ኅብረት ለከፍተኛ ትምህርት ተላኩ፡፡ በሌኒንግራድ አካዳሚ ለአራት ዓመታት የሚሰጠውን ትምህርት ከተከታሉ በኋላ፣ ዐሥራ አራቱን ቅዳሴያት ወደ ሩሲያ ቋንቋ በመተርጐም በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቃቸው፣ ለዶክትሬት ትምህርት እንዲቀጥሉ የነበሩበት የትምህርት ተቋም ዕድል ሰጣቸው፡፡ በዚህ መሠረት ለዶክትሬት ማዕርግ የሚያበቃቸውን ትምህርት ለአራት ዓመታት ተከታትለው፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ታሪክንና ስለ ስንክሳር በሩሲያ ቋንቁ 800 ገጽ ጽፈው ለአካዳሚው አቅርበው ጽሑፋቸው ተቀባይነት በማግኘቱ በዶክትሬት ማዕረግ ተመርቀዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ከሶቭየት ኅብረት ከተመለሱ በኋላ፣ የቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤት ዳይሬክተር በመኾን ነበር ሥራቸውን የጀመሩት፡፡ ከዚያም በኋላ፣ የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ሥልጣናት ኾነው ተሹመዋል፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የውጭ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ እና የገዳማት መምሪያ ሓላፊ ኾነው አገልግለዋል፤ ቤተ ክርስቲያንን በዐበይት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤያት በመወከል ተሳትፈዋል፡፡

በፊት ስማቸው ቆሞስ ዶክተር አባ ሀብተ ሥላሴ ተስፋ ይባሉ የነበሩት ብፁዕነታቸው፣ በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ጥር 4 ቀን 1972 ዓ.ም. ማዕርገ ጵጵስና ከተሾሙት ሦስት አባቶች አንዱ የነበሩ ሲኾን፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ተብለው፣ በከፋ ክፍለ ሀገር የጊሚራ እና የማጂ አውራጃ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስነት ተመድበዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ ኾነው በመሥራት ላይ እያሉ ከቅዱስነታቸው ጋራ በተፈጠረ አለመግባባት ከልማት ኮሚሽን ተነሥተው በጂማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስነት ተመድበው ለሰባት ዓመታት በቆዩበት ጊዜ፣ 11 አብያተ ክርስቲያንን ያሠሩ ሲኾን፣ በዘመን ብዛት የተጎዱ 31 ሕንፃ አብያተ ክርስቲያንን አሳድሰዋል፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የገቢ ምንጭ ለመፍጠር፣ ዘጠኝ ፕሮጀክቶችን አዘጋጅተው፥ መጋዝን፣ ልዩ ልዩ የጐጆ ኢንዱስትሪዎች፣ ሦስት የዕንጨት መሰንጠቂያ ማሽኖችንና የእህል ወፍጮዎችን ተክለዋል፡፡ ከጅማ ከተማ ውጪ 30ሺሕ ካሬ ሜትር የእርሻ መሬት ከመንግሥት አስፈቅደው አትክልት፣ ፍራፍሬ እና ልዩ ልዩ የምግብ ሰብሎችን አምርተዋል፡፡ ዛሬም በልማት ሐዋርያው ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የሚመራው ሀገረ ስብከቱ፣ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ የጀመሯቸውን የልማት ሥራዎች በማጠናከር ከእርሻ መሬቱ በማልማት ተጠቃሚ በመኾን ላይ ይገኛል፡፡

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዕረፍት በኋላ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን እንቅስቃሴ በመዳከሙ፣ ራብዓይ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ብፁዕነታቸውን ወደ ቀድሞ ሓላፊነታቸው መለሷቸው፡፡ በዚህ ወቅት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በመንግሥት እና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል የነበረው ጦርነት ተፋፍሞ ሰለነበረ፣ በመቶ ሺሕዎች ለስደት እና መፈናቀል ተዳርገው በአስከፊ ችግር ላይ ነበሩ፡፡ በወቅቱ ተከሥቶ የነበረው ድርቅም የሕዝቡን ችግር አባብሶት ነበር፡፡ በመኾኑም ብፁዕነታቸው፣ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት፣ ወንጌላዊት እና ከመካነ ኢየሱስ ተወካዮች ጋራ በመኾን፣ በአውሮጳ፣ በልዩ ልዩ አሜሪካ ግዛቶች እና በካናዳ በመዘዋወር ለተቸገረው ሕዝብ የነፍስ አድን ርዳታ በመጠየቅ፣ በጥሬ ገንዘብ እና በዓይነት በርካታ ርዳታ አስገኝተዋል፡፡ ይህም ሰብአዊ ረድኤት ከየቦታው የተፈናቀለውን ሕዝብም ሕይወት ለማዳን ችሏል፡፡

በ1983 ዓ.ም. የሥርዓተ መንግሥት ለውጥ ወቅት በእርስ በርስ ጦርነቱ የተፈናቀለውን ሕዝብ ለማቋቋም እና የአገራችንን የመልሶ ግንባታ ጥረት ለመደገፍ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ በብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ አባታዊ አመራር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡

የገጠር መንገዶችን በመሥራት፣ ለገበሬዎች የእርሻ በሬ እና የወተት ላሞችን በማደል፣ ምርጥ ዘር ለገበሬው በማሠራጨት፣ ት/ቤቶችን፣ ክሊኒኮችን፣ የጤና ኬላዎችን በመሥራት፣ የእህል ወፍጮ በመትከል፣ የንጹሕ ውኃ አገልግሎት በገጠር በማስፋፋት ለኅብረተሰቡ ከፍተኛ አገልግሎት አበርክቷል፡፡ ከተፈጥሮ ደን የተራቆተውን መሬቱ እንዲያገግም የዛፍ ችግኞችን በማፍላት እና ለገበሬዎች በማደል፣ የዛፍ ችግኞችን በማስተከል፣ መሬት እንዲያገግም ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲኾን በማድረግ፣ የዕርከን ሥራዎችን በማከናወን ኮሚሽኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት እና ስላጠቃቀሙ ተግባራዊ ሥልጠና በመስጠት የገጠሩን ሕዝብ ሕይወት ለመለወጥ በተደረገው ጥረት፣ ኮሚሽኑ በብፁዕነታቸው አመራር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከትም የገቢ ምንጭ ለመፍጠር ያካሒድ ለነበረው የገጠር ልማት ሥራ፣ በሐሳብ እና በገንዘብ ረድተዋል፡፡ ገዳማት የራስ አገዝ ልማት ሥራዎችን እንዲያካሒዱ በማገዝ በችግር እንዳይዘጉ እና መነኰሳትም እንዳይሰደዱ ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ በየአህጉረ ስብከቱም የካህናት ማሰልጠኛ ማዕከላትን በማቋቋም፣ ካህናትን በስብከተ ወንጌል እና በገጠር ልማት ሥራ አሠልጥነዋል፡፡ እያንዳንዱ ሀገረ ስብከትም በሥልጠናው ተጠቃሚ ኾኗል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ለዐሥራ አንድ ዓመት ካገለገሉበት ከልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ተነሥተው ለኹለት ዐሥርት ዓመታት ወዳገለገሉበት አንጋፋው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ኾነው የተመደቡት በ1991 ዓ.ም. ነበር፡፡ መንፈሳዊ ኮሌጁ ከነበረው የመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ የማታ ትምህርት መርሐ ግብር በመክፈት፣ አከታትሎም የርቀት ትምህርት እና ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ አበባ ካህናት በአማርኛ ልዩ ትምህርት እንዲያገኙ ዐዲስ የትምህርት ፕሮግራም አስከፍተዋል፡፡ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የኹለት ዓመት የድኅረ ምረቃ የትምህርት ፕሮግራም አስጀምረዋል፡፡ የመንፈሳዊ ኮሌጁ የትምህርት ፕሮግራም በመስፋፋቱ የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን፣ ባለአራት ፎቅ ሕንፃ በ2000 ዓ.ም. በ58 ሚሊዮን ብር አስገንብተዋል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማሳደግ በነበረው ዕቅድም፣ የማስተማሪያ እና ልዩ ልዩ የትምህርት መገልገያ ክፍሎች ያሉት ባለአራት ፎቅ ኹለገብ ሕንፃ በ133 ሚሊዮን ብር አስገንብተው አስመርቀዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ከመደበኛ ሓላፊነታቸው በተጨማሪ በልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን ተቋማት እየተመደቡ አገልግለዋል፡፡ የሰበታ ቤተ ደናግል ጠባባት የሴቶች ገዳን በመርዳት፣ የምስካየ ኅዙናን ገዳም የቦርድ አባል በመኾን፣ የሕፃናት እና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ በመኾን አገልግለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አሁን ያላቸው ምኞት የተጀመረውን የኮሌጁን ሕንፃ አጠናቀው ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት፣ ለዩኒቨርስቲው የሚመጥን የሰው ኃይል በማደራጀት እንዲሁም ለትምህርት የሚተጉ፣ በሥነምግባር የታነጹና ቤተ ክርስቲያን ፍጹም ታማኝ አገልጋዮችንና መሪዎችን ማስተማርና ማሰልጠን ነው፡፡ ከዚያም በኋላ፣ በልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንና በመጨረሻም ከ1992 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 2011 ዓ.ም.፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ኾነው ሰፊ አባታዊ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ በአንጋፋው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ለኻያ ዓመታት ያኽል የነበራቸው የበላይ ሓላፊነት ቆይታ፣ በበርካታ ክሦች እና ውዝግቦች የተመላውን ያኽል፣ መንፈሳዊ ኮሌጁ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለተሸጋገረበት ተቋማዊ ዕድገት እና መስፋፋት የነበራቸው አስተዋፅኦ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከአምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋራም የነበራቸውን ቅርበት ያኽል፣ ከሌሎች አባቶች ጋራ ከሓላፊነት እስከ መታገድ የደረሱበት እና “መርሐ ተዋሕዶ” የተሰኘ ጋዜጣ በማቋቋም ይፋ የወጣ ውዝግብ፣ በመጨረሻም በመንግሥት አካል ተሳትፎ ጭምር በተቋቋመው አጣሪ ኮሚሽን፣ መሠረታዊ አስተዳደራዊ ችግሮች የተፈተሹበትና ለሕገ ቤተ ክርስቲያን የ1991 ዓ.ም. ማሻሻያ አንድ ምክንያት የኾኑበት፣ አጋጣሚ ብፁዕነታቸው የሚታወሱበት ነው፡፡

Leave a comment