Category Archives: Uncategorized

ብፁዕ አቡነ አብርሃም: ጠቅ/ሚኒስትሩ ስለኢትዮጵያዊነት በተናገሩት እንዲጸኑ አበረታቱ፤በቤተ ክርስቲያን ላይ ስለሚፈጸመው በደል አሳሰቡ-“ስምን ፈረሰኛ አይቀድመውምና ልጄ ተጠንቀቅ”

 • ተቀባይነትን ያስገኘላቸውና ተደናቂነትን ያተረፈላቸው፣ ከበዓለ ሢመታቸው ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረግ የሚገልጹባቸው ውብና ወርቃማ ቃላት በመኾናቸው፣ ስለ ተግባራዊነታቸው ዘወትር ሊያስቡበት ይገባል
 • ኢትዮጵያን የማያውቅ ትውልድ እየተፈጠረ በመኾኑ፣ በአስተዳደር ዘመናቸው፣ የአንዲት እናት ሀገር ልጆች፣ የጠላት መሣሪያዎች ኹነን፣ በጎጥና በድንበር ተከላለን ዐይንህ ላፈር የምንባባልበት የጎጣጎጥ ጉዳይ ሊያበቃና ትውልዱ አንድ በሚኾንበት ጉዳይ ላይ መሥራት ያስፈልጋል፤
 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ የኢትዮጵያ ባለአደራ፣ ጥንታዊት፣ አንጋፋና እናት ቤተ ክርስቲያን መኾኗ የማይካድ ሐቅ ቢኾንም፣ ውለታዋ ተዘንግቶ፣ በሃይማኖት እኩልነትና ነፃነት ስም እንርገጥሽ የተባለችበት ዘመን ኾኗል፡፡
 • ዛሬም የኢትዮጵያን ታሪክ ለማሳየት የምትጥረዋን እናት ቤተ ክርስቲያን፣ ትውልዱ ማክበር ለምን ተሳነው? በምሥራቁና በደቡቡ፣ መንግሥታዊ አደራን ረግጠው ራሳቸውን የሃይማኖት መሪ ባደረጉ ባለሥልጣናት ጣጣው እየበዛባት፣ ፈተናው እየከበዳት ነው፤
 • እባክዎ ክቡርነትዎ፣ በአስተዳደር ዘመንዎ፡-እኩልነት፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መቻቻል በቃል ሳይኾን በተግባር ሰፍኖ፤ አልይህ፣ አልይህ መባባል ቀርቶ፣ በትምህርት እንጅ በሰይፍና በጥቅምጥቅም፣ በዱላና በአባርርሃለሁ ባይነት ያልተመሠረተ፣ ሰላማዊነት እንዲሰፋና እንዲሰፍን አደራ እልዎታለሁ
 • አባቶቻችን፥ ስምን ፈረሰኛ አይቀድመውምና ልጄ ተጠንቀቅ ይላሉ፤ በበጎ ጀምረውታል፤ በበጎ እንዲደመድሙት፤ በጎ በጎውን ምክር የሚመክርዎትን፣ በጎ በጎ ሐሳብ የሚያመጡልዎትን ተከትለው ይምሩን፤
 • እንዲህ እስከመሩን ድረስ፣ ሹመትዎ ከእግዚአብሔር ነውና፣ እጅግ ውብ በኾነ ዐረፍተ ነገር የመሰከሩላት ኢትዮጵያ፣ ከቃል ወደ ተግባር ተለውጣ፣ ሺሕ ዓመት ያንግሥዎት እንድንል እንገደዳለን፤ እንደ ጥንቱ፡፡  

†††

 • ኢትዮጵያዊነት ሲሸረሸር እንደቆየና እየተካደም እንዳለ ለባሕር ዳርና አካባቢው ነዋሪዎች የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ መጠገንና መታከም እንዳለበት አሳስበው፣ ለዚህም ቀና ቀናውን ማሰብ፣ ያሰብነውን መናገር፣ የተናገርነውንም ተደምረን መተግበር እንዳለብን አስገንዝበዋል፤
 • መደመር በአንድ ጀንበር እንደማይመጣና ጊዜና መደጋገፍ እንደሚፈልግ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ፣ ቂምን ከመቁጠር ይልቅ በይቅርታ ልብ ተደጋግፈን፣ ከትላንቱ ተምረን መልካሙን በመያዝ፣ ክፋቱ አይበጅም፤ አይደገምም ተባብለን ኢትዮጵያን ማስቀጠል እንዳለብን መክረዋል፤
 • “በኦሮሞ ኮታ አታስቡኝ፤ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የአፋር፣ የሶማሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ፤ እኩል ነው የማገለግላችሁ፤” በማለት አስታውቀው፣ የሃይማኖት አባቶች፥ በጸሎትና በምክርም እንድታግዙኝ እጠይቃለሁ፤” ብለዋል፡፡
 • የሃይማኖት አባቶችም፥ትሕትናን፣ አክብሮተ ሰብእን፣ ግብረ ገብነትን፣ ክፉ ሥር የኾነውን ሌብነትን መጸየፍን ለትውልዱ በማስተማር ድርሻቸውን እንዲወጡና እንዲደግጠይቀዋል፤
 •  አገራዊ ዕውቀት እንዲያብብ ጥንታውያኑ ጣና ቂርቆስ፣ደብረ ኤልያስ እና ዲማ ጊዮርጊስ የመሳሰሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት፤ ከእነርሱም የተገኙ ሊቃውንትና አይተኬ አስተምህሮዎች፣ በኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ ሐሳቦችን በማመንጨትና ትውልድን በመቅረጽ መሠረታቸውን ያኖሩ ባለውለታዎች እንደኾኑ ጠቅሰዋል፤
 • አራት ዐይና ጎሹና መምህር አካለ ወልድ፣ ከሊቅነታቸው ባሻገር በማኅበራዊ የሽምግልና ሚናቸውና ምክራቸው እንደሚታወቁ፤ አለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፣ ወለጋ ቢወለዱም ጎጃም-ደብረ ኤልያስ ተምረው በጎንደርም እንዳስተማሩ አንሥተዋል፤
 • ዘመናዊ ትምህርት ባልተጀመረበት የአገራችን ታሪክ፣ የአስተዳደሩ መዋቅር ይሸፈን የነበረው ከአብነት ት/ቤት ተመርቀው በሚወጡ ምሁራን እንደነበር አውስተው፤ ዛሬም የባህል፣ የጥበብና የዕውቀት ገድሉን በማስቀጠልና የላቀ ትውልድ ለማፍራት ብዙ መጣር ይጠበቅብናል፤ ብለዋል፤

†††

የብፁዕነታቸው ንግግር ሙሉ ቃል፡-

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን

 • ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር
 • ክቡር ፕሬዝዳንት
 • ክቡር ከንቲባ
 • ክቡራን ሚኒስትሮችና በዚህ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ
His Grace Abune Abreham2

ብፁዕ አቡነ አብርሃም: የባሕር ዳር እና ምዕራብ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ከሁሉ አስቀድሞ ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ኾኖ በዚህ ዕለት ከልዩ ልዩ ነገር፣ እኛ ከማናውቀው እርሱ ከሚያውቀው ፈተና ሰውሮ ከመሪያችን ጋራ በአንድነት ስለ ሀገራችን እንድንወያይ፣ እንድንመካከር፤ ከአዲሱ መሪያችንም መመሪያ እንድንቀበል፣ ጊዜውን ፈቅዶና ወዶ በዕድሜያችንም ላይ ተጨማሪ አድርጎ የሰጠን እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ምንም እንኳ እንግዳ ባይኾኑም ወደሚመሩት ሕዝብዎ በመምጣትዎ ቤት ለእንግዳ የምትለው ሀገር እንኳን ደኅና መጡ፤ ትላለች፡፡ ዘመንዎ ኹሉ፥ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመግባባት፣ የብልጽግና ይኾን ዘንድ ምኞትዋንም ትገልጻለች፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እኔ ልናገር የምፈልገው ክቡርነትዎን በተመለከተ ነው የሚኾነው፡፡ በድፍረት ሳይኾን በታላቅ ትሕትና፡፡

ያለእግዚአብሔር ፈቃድ ማንም ማን አይሾምም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርታችን፣ ማንኛውም ሰው በታላቅም ደረጃ ይኹን በቤተሰብ አስተዳደር ከታች ጀምሮ እግዚአብሔር የፈቀደለት ይሾማል፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶልዎትም በመራጮችዎ አድሮ ሹሞታል፡፡ ያከበርዎትና የሾሞት እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይኹን፡፡

እግዚአብሔር ሲሾም ግን፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ ኹለት ዐይነት አሿሿሞች አሉ፡፡ የክቡርነትዎ የትኛው ነው? በጎው እንደሚኾን ሙሉ ተስፋ አለኝ፤ አኹን ከሚታየው፡፡ እግዚአብሔር፥ አንዱን ለጅራፍነት፣ ለአለጋነት ይሾማል፡፡ ሕዝብ ሲበድል፣ ሕዝብ ሲያምፅ፣ እግዚአብሔርነቱን ሲረሳ፣ አልታዘዝም ባይነት ሲገን፤ የሚገርፍበትን፥ ጨንገሩን፣ አለጋውን፣ ጅራፉን፣ እሾሁን ይሾማል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ፣ ሕዝብ ሰላማዊ ሲኾን፣ በአምልኮቱ ሲጸና፣ ፍቅርና መከባበር ሲኖረው ደግሞ የሚያከብረውን፣ የሚያለማለትን፣ የሚቆረቆርለትን፣ አለሁ የሚለውን ይሾማል፡፡

በእኔ እምነት እስከ አሁን ድረስ፣ ከበዓለ ሢመትዎ ጀምሮ በሚያስተላልፏቸው ወርቃማ ቃላት፣ ኅብረ ቀለማትን የተላበሱ፣ ሰንሰለት በሰንሰለት ተሳስረው እንደ ሐረግ እየተመዘዙ በሚወርዱ ውብ ዐረፍተ ነገሮች፤ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው እጅግ ደስ በሚያሰኝ መልኩ እናትነትን የመሳሰሉትን ዝርዝር ሳልገባ ሲገልጹ ሰንብተዋል፡፡ በእኒህ የአጭር ጊዜ የሹመት ሳምንታትም፣ ዳር እስከ ዳር፣ ካህን ነኝና “ወጥን ማን ያውቃል ቢሉ ቀለዋጭ” እንዲሉ እንደ ካህንነቴ ብዙ ስለምሰማ፣ ተደናቂነትን አትርፈዋል፡፡ በዚህ እግዚአብሔርን እናመሰግነዋለን፡፡

ክቡርነትዎን ግን አደራ የምለው፣ መናገር ቀላል ነው፤ ማድረግ ግን ከባድ ነው፡፡ ማውራት ይቻላል፤ በአንድ ቀን ሀገርን መገንባት፣ ማልማት ይቻላል – በወሬ ደረጃ፤ መሥራት ግን ፈታኝ ነው፡፡ ፈታኝ የሚያደርገው፣ ውስብስብ እየኾነ በተለያየ መልኩ የሚቀርበው ጣጣ ነው፡፡ ስለዚህ ከተለያየ አቅጣጫ የሚቀርበው ውስብስብ ነገር፣ የተናሯቸውን ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ የጋራነትን፤ አሁንኮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ትልቁ ችግር፣ እኔነት የሚል ራስ ወዳድነት ሠልጥኖ እኮ ነው፡፡ ለእኔ ከሚል ይልቅ ለወንድሜ፣ ለእኅቴ፣ ለጎረቤቴ፣ ለሀገሬ፣ ለወገኔ የሚለው ስሜትኮ በእያንዳንዳችን ቢሠርጽ ሌላ ችግር አይኖርም፤ ነገር ግን በእያንዳንዱ አእምሮ የሠረጸው የእኔነት ጠባይዕ ነው፤ ራስ ወዳድነት ነው፡፡ እንደ እንስሳዊ አባባል፣ “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” የሚል አስተሳሰብ በመፈጠሩ ነው፡፡

ስለዚህ፣ ይህን ችግር ለመናድ፣ ይህን ችግር ለማስወገድ በተዋቡ ዐረፍተ ነገሮች የሚያስተላልፏቸው ቃላት እንደው ዘወትር እንደ መስተዋት ልበል፣ እንደ ግል ማስታወሻ ከፊትዎ ሰቅለው፥ ምን ተናግሬ ነበረ፤ የቱን ሠራሁት፤ የትኛው ይቀረኛል የሚል የዘወትር ተግባር እንዲኖርዎ፣ በቤተ ክርስቲያን ስም በታላቅ ትሕትና እገልጽልዎታለሁ፡፡ ምክንያቱም ይህን ዕድል ያገኘሁት ዛሬ ስለኾነ፣ ነገ ብቻዎን ስለማላገኘዎት አሁኑኑ ልናገር ብዬ ነው፡፡

ብዙ ታሪክ አሳልፈናል፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት መቼም፣ አሰብ ስለነበርኩ በአካል የማውቃቸው የአፋሩ ታላቅ አዛውንት መሪ የነበሩት በአንድ ወቅት እንደተናገሩት፣ “ኢትዮጵያን እንኳን እኛ ግመሎቻችን ያውቋታል[ከነባንዴራዋ]” ነው ያሉት አይደል፡፡ ግመሎች ያውቋታል፤ ነው ያሉት፤ አስታውሳለሁ፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያን የማያውቅ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡ ክቡርነትዎ ተደናቂነትን እያተረፉ ያሉት፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹባቸው ቋንቋዎች፣ እጅግ የተዋቡ በመኾናቸው ነው፡፡

ሰሞኑን ኢየሩሳሌም ነበርኩ፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ፡፡ ከተለያየ አቅጣጫ ያልመጣ አልነበረም፤ ብዙ ሰው የሚያወራው ግን ትልቅ የምሥራች ነው፤ “እግዚአብሔር በርግጥም ይህችን ሀገር ከጥፋት ሊታደጋት ይኾን?” የሚል ጥያቄ ነው ያለው፡፡ አዎ፣ ያንዣበበው ፈተና፣ የደፈረሰውና የታጣው ሰላም አስጊ ነበር፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በቅዱስ ፓትርያርኩ መልእክት አስተላላፊነት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ጮኻለች ወደ እግዚአብሔር፡፡የሰላም አምላክ ሆይ፣ ሰላምህን ስጣት፤ አንድነትን ስጥ ለልጆችህ፤ እያለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ወሰን ስለሌላት፤ ቤተ ክርስቲያን ሁሉም ልጆቿ ስለኾኑ፣ ከልጆቿ አንዱም ማንም ማን እንዳይጎዳ ስለምትፈልግ፣ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለሀገራችን ሰላምን ስጣት፤ እያለች ጸሎቷን ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አሰምታለች፡፡ ወደፊትም ታሰማለች፡፡

ስለዚህ ክቡርነትዎ፣ ይኼን የጎጣጎጡን ጉዳይ፣ የዚያ ማዶ የዚህ ማዶ የመባባሉን ጉዳይ ወደ ጎን ይተዉትና አልጀመሩትም፤ ይጀምሩታልም ብዬ አላስብም፤ ትውልዱ አንድ የሚኾንበትን ጉዳይ፣ ላለመደፈር፤ አባቶቻችንኮ ያልተደፈሩት አንድ ስለኾኑ ነው፡፡ ልዩነት ስለሌላቸው ነው፤ ከዚህ ቀደምም ተናግሬዋለሁ፤ በላይ በበራሪ በምድር በተሽከርካሪ የመጣውንኮ በኋላ ቀር መሣሪያ ያሸነፉትና ያንበረከኩት፣ በየትኛውም ዓለም ብንሔድ፣ ኢትዮጵያዊ አትዮጵያዊ ነኝ ብሎ በሙሉ ወኔ በየትኛውም ቦታ ገብቶ የመናገር፣ የመቀመጥ ዕድሉን ያገኙት በአንድነታቸው ነው፡፡ የእገሌ ወእገሌ መባባል ስለሌለባቸው፡፡

አሁን ግን ወዳጆቻችን በሰጡን የቤት ሥራ፣ እዚሁ ተቀምጠን እንኳ በአሁን ሰዓት የእገሌ የቤት ሥራ፣ የእገሌ፣ የእገሌ እየተባባልን ነው፡፡ መቼ ነው ከዚህ ሸክም የምንላቀቀው ወገኖቼ? መቼ ነው ከጎጠኝነት የምንላቀቀው? መቼ ነው፣ በኢትዮጵያዊነት አምነን፣ አንች ትብሽ አንተ ትብስ ተባብለን እግዚአብሔር በሰጠን የነፃነት ምድር፣ አባቶቻችን የደም ዋጋ በከፈሉባት ምድር፣ አባቶቻችን አጥንታቸውን በከሠከሱባት ምድር፣ አባቶቻችን ዕንቁ የኾነውን ታሪካቸውን ለእኛ አሻራ አድርገው ትተውባት በሔዱት ምድር በእፎይታ የማንኖረው እስከ መቼ ነው? የአንድ እናት ልጆች፣ የአንዲት ሀገር ልጆች የጠላት መሣሪያዎች ኹነን፣ በጎጥና በድንበር ተከላለን ዐይንህ ላፈር የምንባባለው እስከ መቼ ነው? ስለዚህ በክቡርነትዎ ዘመን ይኼ እንዲበቃ ምኞቴም ነው፤ ጸሎቴም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን እላለሁ፡፡

ሌላው ሳልጠቁም የማላልፈው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ክቡርነትዎ እንደሚያውቁት፣ የታሪክም ሰው እንደመኾንዎ፣ ቅድምም ሲናገሩ ዐይናማ የኾኑትን አራት ዐይናማ ሊቃውንት፣ ከየአቅጣጫው ኢትዮጵያዊነትን የሚገልጹትን በሙሉ እየጠቃቀሱ እንዳስረዱን ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ትልቅ ባለውለታ፣ አንጋፋ እናት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ይኼ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ ርግጠኛ ነኝ፣ ሼኹም ይመስክሩ ሌላውም ይመስክር፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እገሌ ወእገሌ ሳትል ሁሉንም በየእምነቱ ፊደል ያስቆጠረች፣ ያስነበበች፤ ለሀገር መሪነት ያበቃች አንጋፋ እናት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ የእኔ ስለኾነች አይደለም የምመሰክረው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ የእምነቱ ተከታዮች አይኾኑ፤ እናከብራቸዋለን፤ እንዲያከብሩን እንፈልጋለን፡፡ ግን ለባለውለታ፣ ሀገርን ዛሬም በሰንሰለቶቿ አስራ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማሳየት የምትጥረዋን እናት ቤተ ክርስቲያን፣ ትውልዱ ማክበር ለምን ተሳነው? በሃይማኖት እኩልነት፣ በሃይማኖት ነፃነት እንርገጥሽ እየተባለች ያለችበት ዘመን ቢኖር ግን ዛሬ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያንኮ ባለአደራ ናት፡፡ ክቡርነትዎ ጊዜ ቢኖርዎት፣ ክቡር ፕሬዝዳንት ጊዜ ኖሯቸው ቢያስጎበኙልኝ እስኪ እነዳጋ እስጢፋኖስን ይጎብኟቸው፤ የነገሥታቱን የእነዐፄ ሱስንዮስን የእነዐፄ ዳዊትን የእነዐፄ ፋሲለደስን የእነዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን አዕፅምት ይዛ የምትገኝ፣ ባለአደራ ጥንታዊት እናት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ዛሬ ዛሬ በምሥራቁ ስንሔድ፣ በደቡቡ ስንሔድ፤ እዚህ አካባቢ ያው ጎላ በርከት ብሎ የኦርቶዶክሱ ተከታይ ስላለ ተቻችለን እንኖራለን፤ ወደ ሌላው ስንሔድ ግን ጣጣው እየበዛባት ነው ቤተ ክርስቲያን፤ ፈተናው እየከበዳት ነው ቤተ ክርስቲያን፤ መጀመሪያዎች ኋለኞች፣ ኋለኞች ፊተኞች ይኾናሉ፤ የተባለው ቃል እየተፈጸመባት ነው፡፡

በሥልጣን ክፍፍልም ኾነ በአካባቢው ያሉ ሥልጣን ላይ ይቀመጣሉ፣ የመንግሥት ሓላፊነታቸውን ትተው፣ የተሰጣቸውን አደራ ረስተውና ረግጠው፣ ራሳቸውን የሃይማኖት መሪ እያደረጉ ይህችን እናት አንጋፋ ቤተ ክርስቲያን በዋለችበት እንዳታድር፤ ባደረችበት እንዳትውል እንደ ጥንቱ እንደ ሮማውያን ዘመን እየኾነ ያለበትም ቦታ አለና እባክዎ ክቡርነትዎ በአስተዳደር ዘመንዎ፡- እኩልነት፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መቻቻል ሰፍኖ፤ ይኼ በቃል፣ በቋንቋ የምንናገረው ሳይኾን ተግባራዊ በኾነ መልኩ አንተን አልይህ፣ አንተን አልይህ መባባል ቀርቶ እምነትም ከኾነ በትምህርት ላይ የተመሠረተ እንጅ በሰይፍና በጥቅምጥቅም፣ በዱላና በአባርርሃለሁ ባይነት ያልተመሠረተ፣ ሰላማዊ የኾነ ነገር እንዲሰፋ እንዲሰፍን አደራ እልዎታለሁ፡፡

PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ከዚህ በተረፈ፣ ዘመንዎ ሁሉ፣ አጀማመርዎ ጥሩ ነው፤ አካሔዱን አይቶ ስንቁን ይቀሙታል፤ ይላሉ አባቶቻችን፤ በዚህ አካሔድዎ፣ እጅግ ደስ የሚልና በእያንዳንዱ አእምሮ ተቀባይነትን እያገኙ እንደሚቀጥሉ፡፡

አባቶቻችን የሚሉት አንድ ነገር አለ፤ ስምን ፈረሰኛ አይቀድመውምና ልጄ ተጠንቀቅ፤ ይላሉ፤ እንደ ዛሬ አየር አይቀድመውም፤ እንደ ጥንቱ ግን ፈረሰኛ አይቀድመውም፤ አንድ ስም አንድ ጊዜ በክፉ ከወጣ አለቀ፤ አንድ ስም አንድ ጊዜ በበጎ ከወጣ ደግሞ አለቀ፤ ስለዚህ በበጎ ጀምረውታል፤ በበጎ እንዲደመድሙት፤ የእርስዎና የእርስዎ የቤት ሥራ ኹኖ እግዚአብሔር ከእርስዎ ጋራ ኹኖ፣ የትላንትናዋ ምልዕት ኢትዮጵያ፣ ቅድስት ኢትዮጵያ፣ አንድነት የሰፈነባት፣ መለያየት የሌለባት፣ ሁሉም በሔደበት ቤት ለእንግዳ ተብሎ የሚያልፍባት፤ አንተ እገሌ ነህ፣ አንተ እገሌ ነህ የማይባባልባት አገር ትኾን ዘንድ እግዚአብሔርን በመለመን፣ አማካሪዎችዎንም በማማከር፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ምክረ ኵይሲ እንለዋለን…ይኼ አላስፈላጊ ምክር የሚመክሩ እንደ ምክረ አሦር አሉ፤ ስለዚህ በጎ በጎውን ምክር የሚመክርዎትን፣ በጎ በጎ ሐሳብ የሚያመጡልዎትን ተከትለው እስከመሩ ድረስ፣ አዎ ርግጠኛ ነኝ፤ የተናገሩላት፣ እጅግ ውብ በኾነ ዐረፍተ ነገር የመሰከሩላት ኢትዮጵያ፣ ከቃል ወደ ተግባር ተለውጣ፣ ሺሕ ዓመት ያንግሥዎት እንድንል እንገደዳለን ማለት ነው፤ እንደ ጥንቱ፡፡ እግዚአብሔር ይስጥልን፤ እግዚአብሔር ይባርክልን፡፡

ከዚህ በተረፈ፣ በመጨረሻ መቸም አንዳንድ ጊዜ የእኛ ልማድ፣ ከይቅርታ ጋራ ነው የምናገረው፣ አዲስ ባለሥልጣን መጣ ሲባል፣ እንግዳ መጣ ሲባል፣ ስሜታችንን መናገር የተለመደ ጠባያችን ስለኾነ ይቅርታ እየጠየቅሁኝ፣ እንደ እኛ እንደ እኛ እንደ ባሕር ዳር፣ ያለአድልዎ፣ በሚገባ፣ እኔም በማውቀው እኔም አንድ ጠያቂና ተመላላሽ ስለኾንኩ፣ የሚያስተናግዱንን ክቡር ከንቲባችንንም ኾነ ክቡር ፕሬዝዳንቱን፣ አጠቃላይ መሥሪያ ቤቱን ሳላመሰግን ባልፍ ኅሊናዬ ስለሚወቅሰኝ እግዚአብሔር ያክብርልኝ፤ እላለሁ፤ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

Advertisements

በዴር ሡልጣን ጉዳይ፡ ኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች በኢየሩሳሌም ሰልፍ አካሔዱ፤ የቅ/ሚካኤል ቤተ መቅደስ እድሳት እንዲፈቀድ ጠየቁ

_45118367_monastery_466

 • የገዳሙ አስተዳደርና በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ክትትል እንዲጠናከር አሳሰቡ
 • የቅ/ሚካኤል ቤተ መቅደስ፣ ጣሪያው ተነድሎ አገልግሎት ካቆመ 8 ወራትን አስቆጠረ
 • ግሪኮቹ እናድስ አሉ፤ ግብፆቹ አይታድስም አሉ፤ መንግሥት፥ እስኪጣራ ብሎ አሸገው
 • ማን ይሥራው? ከእኛም ሰዎች እንቅስቃሴ የለም፤ ከመንግሥትም እንቅስቃሴ የለም
 • እንደታሸገ ከቆየ ወይ ግብፅ ይጸናላታል ወይ ግሪኮቹ ያድሱትና የራሳችን ነው፤ይላሉ

†††

 • የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ተወካይ፣ ምላሹን በቅርቡ እንደሚያሳውቁ አስታውቀዋል
 • ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ነው! እድሳቱ ይፈቀድ! የግብፅ ሁከት ይገታ!– ሰልፈኛው
 • በዘንድሮው ትንሣኤ፣ ከ11ሺ ያላነሱ ተሳላሚዎች ቢገኙም ሰልፈኞቹ በመቶዎች ናቸው
 • ቁጥራቸው የጨመረው አስጎብኚዎች፣ ተሳላሚውን በማንቃት ተባብረው ሊሠሩ ይገባል
 • ሰልፉን ውጤታማ ያደረገው፣ በእስራኤል የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ፣ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡

†††

 (ሰንደቅ፤ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 10 ቀን 2010 ዓ.ም.)

የዘንድሮን የትንሣኤን በዓል ለማክበር፣ ከመላው ዓለም በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን፣ በዴር ሡልጣን ገዳም ባለቤትነትና እድሳት ጉዳይ ሰላማዊ ሰልፍ አካሔዱ።

በእስራኤል የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ እና የዴር ሡልጣን ገዳም አስተዳደር ባስተባበሩት በዚሁ ሰልፍ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተጓዦች፤ በዳግም ትንሣኤ እሑድ፣ ሚያዝያ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጸሎተ ቅዳሴ በኋላ (ከጠዋቱ 4፡30)፣ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ቢሮ በማምራት አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

ሰልፈኞቹ በአቤቱታቸው፥ ጣሪያው በመሸንቆሩ ላለፉት ስምንት ወራት ተዘግቶ የቆየው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ በአስቸኳይ ታድሶ አገልግሎቱ እንዲቀጥል እንዲደረግ፤ በማኅበረ መነኰሳቱ ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖና አድልዎ እንዲቆም በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታሪክና የቅድስና ይዞታ በኾነው የዴር ሡልጣን ገዳም ላይ፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይገባኛል በማለት እየፈጠረችው የምትገኘው ዕንቅፋት እንዲገታ ጠይቀዋል፤ ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ነው! እድሳቱ ይፈቀድ! የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይገባኛል በማለት የምትፈጥረው ሁከት ይገታ! የሚሉና በዕብራይስጥ፤ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋዎች የተጻፉ መፈክሮችንና መዝሙራትን በጋለ ስሜትና በከፍተኛ ድምፅ አስተጋብተዋል።

Jerusalem piligrims rally1

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወካይ፣ በሰልፈኞቹ የተመረጡ ሦስት ልኡካንን ካነጋገሩ በኋላ በጽሑፍ የተዘጋጀውን አቤቱታ ተቀብለዋል፤ ምላሹንም በቅርቡ እንደሚያሳውቁ ለተወካዮቹ ቃል ገብተዋል።

ጉዳዩን በመከታተል በኩል፣ በገዳሙ አስተዳደር አቅምና ንቃት እንዲሁም በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትብብር ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ለሰንደቅ አስተያየታቸውን የሰጡ የሰልፉ ተሳታፊዎች፤በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት በጥቃቅን ምክንያቶች ከመለያየት ይልቅ በዋናው የገዳሙ ባለቤትነትና እድሳት ጉዳይ የዜጎችንና ተቆርቋሪዎችን አቋም አስተባብረው ክትትላቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

Israel-Palestinians-E_Horo-1-e1492187029403-640x400

በዘንድሮው ክብረ በዓል ከአሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓ እና በዋናነትም ከኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ11ሺሕ ያላነሱ ተሳላሚ ምእመናን በተለያዩ አስጎብኚ ድርጅቶች በኩልና በግላቸው ጭምር ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዙ ሲኾን፤ ሰልፈኞቹም ከተጓዦቹና በእስራኤል ነዋሪ ከኾኑ ኢትዮጵያውያን የተውጣጡ እንደኾኑ ተገልጿል፤ በቁጥር 350 ያህል ሰልፈኞች እንደኾኑ የዐይን እማኞች አረጋግጠዋል።

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ይዞታ ከኾነው የዴር ሱልጣን ገዳም ባለቤትነት ጋራ በተያያዘ ግብፅ የይገባኛል ጥያቄ በተደጋጋሚ በማንሣት፣ የእድሳት ሒደቱንም በማደናቀፍ እየተከሠቱ ባሉ አለመግባባቶች ሳቢያ፣ የኹለቱ ሀገሮች እኅት ኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ግንኙነት እየሻገረ እንደሚገኝ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በቅርቡ ለኢኦተቤ ቴቪ/EOTC Tv/ የተናገሩትን ጠቅሰን መዘገባችን የሚታወስ ነው። 

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

በሰልፉ የተሳተፉ ተሳላሚዎች በዝርዝር እንዳስረዱት

የዳግም ትንሣኤ ዕለት፣ ለአክብሮ በዓል ከተለያዩ አህጉረ ዓለም በኢየሩሳሌም የተሰበሰቡ ኢትዮጵያውያን ሰልፍ የወጡበት የቅርብ ምክንያት፣ በዴር ኤል ሡልጣን ገዳም ካሉን ኹለቱ አብያተ መቃድስ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ መታሸጉና መተላለፊያውም መዘጋቱ ነው፡፡ ስምንት ወራትን አስቆጥሯል፤ መቅደሱ ከመስከረም ጀምሮ ተዘግቶ እድሳቱም ተከልክሎ አገልግሎት ማቆሙ ነው፡፡

በርግጥ ጉዳቱን በዐይን ለማየት አልቻልንም፤ ከዚያም ከዚህም ተዘግቷል፤ ግሪኮቹ ከላይ እናድሳለን ብለው በድንጋይ እየገነቡ በመቦርቦሪያ ሲቦረቡሩ የቅዱስ ሚካኤልን ቤተ መቅደስ ጣራ ወደታች ነደሉት፤ ስለበሱት አቧራና ፍሪፋሪ ወደ ውስጥ እያስገባ ነው፤ ግሪኮቹ እናድስ አሉ፤ ግብፆቹ ደግሞ ማንም አያድስም አሉ፤ በዚህ አተካራ መሀል የእስራኤል መንግሥት፥ “ማንም አያድስም፤ ነገሩ እስኪጣራ ይዘጋ” ብሎ አሸገው፡፡ ቤተ መቅደሱ ምንም አገልግሎት ስለማይሰጥ በዚያ በኩል ማንም አይተላለፍም፡፡ ጸሎተ ቅዳሴው የተከናወነው በአርባዕቱ እንስሳ ቤተ መቅደስ ውስጥና ሕዝቡም በውጭ ድንኳን ተጥሎ ነው፡፡

easter in Jerusalem

አሁን መተላለፊያውን ዘግተውና ቤተ መቅደሱን አሽገው ቀስ ብለው ደግሞ በዚያው ወደ ይዞታቸው እንዳያካትቱት ያሰጋል፡፡ የሕዝቡ ዋና ብሶት፣ ጉዳዩ ስምንት ወራትን አስቆጠረ፤ ማን ይሥራው? ከእኛም ሰዎች እንቅስቃሴ የለም፤ ከመንግሥትም እንቅስቃሴ የለም፤ እንደታሸገ ከቆየ ነገ ወይ ግብፅ ይጸናላታል ወይም ደግሞ ግሪኮቹ ያድሱትና የራሳችን ነው፤ ይላሉ፤ እዚያ ሀገር የሚያድስ አካል የእኔ ነው የማለት ታሪክና መብት አለው፤ የሚል ስጋት ሕዝቡ አንሥቷል፡፡ ግሪኮች ጠላት አይደሉም፤ እናድስ ካሉ ግን የሀገሪቱ ሕግ ሊያግዛቸው ይችላል፤ ካደሱና ገንዘብ ካወጡ የእኛ ነው የሚል ጥያቄ ማንሣት ይችላሉ፤ የሚያድስ ባለቤት ነው፡፡

በቅርቡ ፓትርያርኩ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ስለ ዴር ሡልጣን የሰጡት መግለጫ የፈጠረው ተጽዕኖ የለም፡፡ እንዲያውም ተቃውሞ ነው ያለው፡፡ ቅዱስነታቸው የገዳማቱ ሊቀ ጳጳስ እያሉ ያበላሹት ነገር አለ፤ ግሪኮቹ ግንባታ እንዲፈጽሙ ድሮ የጻፉት ደብዳቤ አለ፤ የሚል ጥቆማና ተቃውሞ አለ፡፡ ይህን እናቆየውና በዳግም ትንሣኤ ዕለት ሰላማዊ ሰልፉ ከቅዳሴ ውጭ ረፋድ 4፡30 በኋላ ነው የተደረገው፡፡ ሰልፉን በዋናነት ያስተባበረው በእስራኤል የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲና የገዳሙ አስተዳደር ነው፡፡ ከጸሎተ ኀሙስ ጀምሮ ቅስቀሳ አድርገዋል፤ በዚህም መሠረት ለሰልፉ ትኩረት ሰጥተው የተባበሩ አስጎብኚ ድርጅቶችና የተገኙ ተጓዦች አሉ፤ ያልተገኙም አሉ፡፡

በርግጥ ዘንድሮ የተሳላሚው አጠቃላይ ቁጥር በብዙዎቹ የጉዞና አስጎብኚ ወኪሎች ቀንሶ ታይቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዦችን የሚወስዱ አስጎብኚ ድርጅቶች ቁጥር ወደ 13 ደርሷል፡፡ ከአውሮፓ – ከጀርመን የሚመጣ ሁለት ቡድን አለ፤ እነመ/ር ጥበበ ሥላሴ ከእንግሊዝ ሁለት የተጓዥ ቡድን ይዘው መጥተዋል፤ከአሜሪካ እነቀሲስ በለጠ ይረፉ ጋራ ኹለት ቡድን፣ ከካናዳም አንድ የተጓዥ ቡድን መጥቷል፤ በየግላቸው የመጡም አሉ፤ በአጠቃላይ ከ11ሺሕ ያላነሱ ኢትዮጵያውያን ተሳላሚዎች ተገኝተዋል፤ ባለፈው ዓመት ከ14ሺሕ በላይ ነበሩ፤ በዘንድሮው ቀንሷል፤ ዋናው መንሥኤ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የሆቴል ወጪ ጨምሯል፤ ትኬት ተወዷል የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ በኢየሩሳሌም ድርጅት የሔደው ተጓዥ ከ400 ወደ 220 ዝቅ ብሏል፡፡

yod_abyssinia_tour

ምእመናን በዕርገት፣ በጾመ ፍልሰታ ይሔዳሉ፤ በዓለ ትንሣኤ ግን ከምንም በላይ ብዙ ተሳላሚ ይገኝበታል ተብሎ የሚጠበቅ ቢኾንም በሰልፉ ትኩረት ሰጥተው የተገኙት 350 ያህል ናቸው፡፡፡ የተሔደበት መሥሪያ ቤት የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዋና ጽ/ቤት ነው፡፡ ሰልፉ የተደረገበት የዳግም ትንሣኤ እሑድ እዚያ ሀገር ሥራ ክፍት ነው፡፡ መነሻው ከደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በዕለቱ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ቀደሱ፤ ሥርዐቱ እንደተፈጸመ የመንግሥት ተቃዋሚና ደጋፊ፣ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ ሳይለያይ የሚችል ኹሉ በአውቶቡስ እየተሳፈረ ወደ ጽ/ቤቱ አመራ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ከደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ቢያንስ 9 ኪ.ሜ ይርቃል፡፡ ከ4፡00 ጀምሮ ተፈቅዶልን ነበር በፖሊስ፡፡ በፖሊስ መንገዱ ተዘግቶ፣ ሕዝቡ እየጮኸ፣ እሪ እያለ ተመመ፤ በሀገሩ መንገድ ማዘጋት ትልቅ ተቃውሞ ነው፡፡ መዝሙራት፣ በአማርኛ የተጻፈ የገዳሙ ስብከተ ወንጌል ሓላፊ ያነበቡት የገዳሙ ታሪክ፤ በዕብራይስጥ፣ በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ የተጻፉ መፈክሮች ቢያንስ ከሠላሳ ደቂቃ በላይ በከፍተኛ ድምፅና በጋለ ስሜት ተስተጋብተዋል፡፡ መፈክሮቹ፡- ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ነው! እድሳቱ ይፈቀድ! የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይገባኛል የምትለው ነገር ይነሣ! የሚሉ ናቸው፡፡

እኒህ መፈክሮች እየተስተጋቡ እያለ ለግብፅ የሚያዳላ የእስራኤል ፖሊስ ኮማንደር ነበር ሰልፉን እንዲያስተናግድና መንገድ እንዲዘጋ የተመደበው፡፡ ሰልፈኛ ኢትዮጵያውያኑ ኮማንደሩን ሲያዩት፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ በጣም ጮኹ፡፡ ስሙን እየጠሩ፣ “ይኼ ፖሊስ ሰልፉን አይወክልም፤ ለዚህ ሰልፍ መልእክት አይመጥንም፤ ሌላ አስተባባሪ ይመደብልን፤” ብለው ተቃወሙ፡፡ እርሱም ገለል ተደርጎ ሌላ ሓላፊ መጣ፡፡ ውጤቱ የሚገርም ነው፤ ሰልፉን የመራውንና ያስተባበረውን በእስራኤል የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ጥንካሬ ያሳያል፡፡

የዴር ሡልጣንና እንዳይታደስ የተከለከለው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ ምስሎች በትልቁ ይታያሉ፤ ሞንታርቦ ተይዟል፤ ይጮኻል፤ ይዘመራል፤ ይፈከራል፡፡ ከገዳሙ የጽሑፍ መልእክት ነው የተነበበው፡፡ በተለይ በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ፉከራዎችንና መፈክሮችን በዕብራይስጥ ቋንቋ አሰምተዋል፡፡ ከተለያየ አህጉረ ዓለም የመጡ ተጓዦች ቢኾኑም በኢትዮጵያዊ አንድነት የተስተጋባው አቋምና መልእክት ግን አንድ ነው – “ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ነው፤ ግብፅ እጇን ታንሣ!” የሚል ነው፡፡

በኮማንደሩ ተተክቶ የመጣው ሓላፊ፤ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ገብተው ጉዳዩን የሚያስረዱ ሦስት ሰዎች ምረጡ፤ አለ፡፡ አባ ሐረገ ወይን የሚባሉ ዕብራይስጥ የሚችሉ ከሕዝቡ መካከል የኾኑ አባት፣ ከኮሚኒቲው ደግሞ በእስራኤል ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ ወ/ሮ አልማዝ የሚባሉ እናት፤ ቤተ እስራኤላዊ የኾነ የገዳሙ ተቋርቋሪና የሰልፉ አስተባባሪ ከሰልፈኛው ተመርጠው፣ በእንግሊዝ እና በዕብራይስጥ የተጻፈ ደብዳቤ ይዘው ወደ ቢሮው ገቡ፡፡

በፖሊስ ታጅበውና ስማቸው ተመዝግቦ ከገቡ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወካይ ተቀበሏቸው፤ ጥያቄው የኢትዮጵያውያንና የቤተ ክርስቲያን ጥያቄ መኾኑን አስረድተው የጠቅላይ ሚኒስትሩን አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሹ አመለከቱ፡፡ ተወካዩ በበኩላቸው፣ አንድ ሰውም ኾነ ከዚያ በላይ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማናገር እንደሚችል ገለጹላቸው፤ ነገር ግን ፈቃዱ፣ ሰልፉን ለማድረግ እንጅ እርሳቸውን ለማናገር ባለመኾኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማናገር ባትችሉም ደብዳቤያችሁን አቀርብላችኋለሁ፤ አሏቸው፡፡ የኮሚዩኒቲው ተወካዮችና የገዳሙ አስተዳደር አካላት ምላሹን ይከታተሉ፤ ብለው አሰናበቷቸው፡፡

በእስራኤል የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ አውቶቡስ እያዘጋጁ፣ ታክሲ በራሳቸው እየከፈሉ ነው ሕዝቡን ወደ ሥፍራው ያጓጓዙት፡፡ ከአስጎብኚ ድርጅቶችም ተጓዡን በዕለቱ ወደ ሌላ ይዘው የሔዱ ቢኖሩም፣ በመጓጓዣ ክፍያውና በማስተባበሩ ያገዙ አሉ፤ በይበልጥ ከእንግሊዝ፣ ከጀርመንና ከአሜሪካ የመጡ፤ ከኢትዮጵያ ደግሞ የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅትና ሌሎች ኹለት አስጎብኚ ድርጅቶች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ሥራዬ ብለው ነው የተባበሩት፡፡

ኮሚዩኒቲው ጠንካራ ቢኾንም በሚመለከታቸው ሓላፊዎች ሊታገዝ ይገባል፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚለከታቸው አካላት፣ ነገሮችን ከወቅቱ ጋራ በማያያዝ ብቻ ወደ ኋላ የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ ይኼ  ነገሩ እንዳይፈጽም በማዳከም ለተቀናቃኞች ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ ግልጽ ለማድረግ ያህል፥ የሰልፉ ቀን ከሌላ አህጉረ ዓለም የመጡ ኢትዮጵያውያን በንቃትና ያገባኛል ስሜት ሲሳተፉ እንኳ ዋና ሓላፊዎች የሚባሉት አልተገኙም፤ የገዳማቱ ሊቀ ጳጳስም ምክትላቸውም ሲቀሰቅሱ ሲያስተባብሩ ቢሰነብቱም በሰልፉ ላይ መገኘት ሲገባቸው አልተገኙም፤ ገዳሙ ምን ያህል ጉዳዩን ይከታተለዋል፤ በሚለው ላይ ስጋት አለ፤ ንቁ አይደለም አስተዳደሩ፡፡

በቀጠሮ ቀን እንኳ ያለመገኘት ችግር አለባቸው፤ ለስሙ ከኤምባሲው ጋራ እንናበባለን፤ ይላሉ፤ ፕሮቶኮል እንጠብቅ እያሉ ይጨናነቃሉ፡፡ በዲፕሎማሲው፣ ሓላፊዎች በሰልፍ ላይ አይገኙም፤ የሚል ሕግ አለ፤ ይላሉ፡፡ በሌሎቹ ግን አምባሳደር ሳይቀር ከዜጋቸው ጋራ ባንዴራቸውን ይዘው ሲወጡ ታይተዋል በሀገሩ፡፡ አሁን ጩኸቱን ያሰማው ሕዝቡ ነው፡፡ ኾኖም የገዳማቱ አስተዳደር፣ ጉዳዩ የሚጠይቀውን ያህል የመከታተል አቅም አለው ወይ? በኤምባሲውም በኩል የባንዴራን ውዝግብ በመጥቀስ መተባበርን የማቀዝቀዝ ነገር እንዳይኖር ስጋቱ በመኖሩ፣ ለዋናው ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥቶ ክትትሉ ሊጠናከር ይገባል፡፡

 

ኹለቱ የዋልድባ መነኰሳት ስለ እስር ቆይታቸው

 • ተፈታን የምንለው፥በሀገርና በቤተ ክርስቲያን የተተበተበው ማነቆ ሲበጠስና ሲፈታ ነው
 • …የአገር ሰላምና አንድነት፣የመናገርና የመጻፍ መብት ሲረጋገጥ፤መልካም አስተዳደር ሲሰፍን
 • ቆብህን፣ የሃይማኖት ልብስህን አውልቅ” እያሉ መሬት ለመሬት እየጎተቱ ሥቃይ ደርሶብኛል
 • አይዟችሁ ብለው ለደገፉንና ለጠየቁን ኹሉ፣በዋልድባ ገዳም ስም በእጅጉ እናመሰግናለን

†††

VOAAmharic

በዛሬው ዕለት ከእስር የተፈቱት ኹለቱ የዋልድባ መነኰሳት፣ አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም እና አባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት፥ “ተፈታን የምንለው፣ አገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን ከታሰሩበት ማነቆ መፈታት ሲችሉ ነው፤ ብለዋል፡፡ አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ሲፈቱና የአገሪቱ ሰላም ሲረጋገጥ፣ ከእስር በመፈታታቸው እንደሚደሰቱ ነው የገለጹት፡፡ ጽዮን ግርማ አጠር ያለ ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡

አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም፡-

እንኳን ከእስር ተፈቱ፡፡ ዛሬ ነው ከእስር የወጡት፤ ስንት ሰዓት ላይ ነው?Aba Gebrayesus

እንኳን የአበው አምላክ ከእናንተ ጋራ አገናኘን፤ ዛሬ 5 ሰዓት አካባቢ ነው የወጣነው፤

የታሰራችሁበት ጊዜና የእስር ኹኔታችሁ ምን ይመስል ነበር? በፍ/ቤት የነበረው ኹኔታ በዘገባ ሲወጣ ነበር፤ በእናንተ አንደበት እንዴት ትገልጹታላችሁ?

እኛ የታሰርነው ታኅሣሥ 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡ የፍ/ቤት፣ የማዕከላዊ እና የቂሊንጦ ችግር፤ በእኔ አንደበት ብቻ ተገልጾ የሚዘለቅ አይደለም፡ ወደፊት ብዙ የምንነጋገርበት ይኾናል፡፡ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን፤ በእውነት የአባቶቻችን አምላክ ከብዙ ፈተናዎች አውጥቶ ለመነጋገር አብቅቶናል፤ ደካሞች ብንኾንም፣ በሕዝባችን ትግልና ጥረት፣ በአባቶቻችን አምላክ ኃይል የመጣብንን ፈተና አስወግዶ አሁን ከወገናችንንና ከሕዝባችን ጋራ እንድንቀላቀል አድርጎናል፡፡

ከነበረው ጊዜ ከባዱና ተገላገልነው የምትሉት የትኛው ነበር?

አሁን ተገላግለናል ማለት አይደለም፡፡ ከእስር ተፈታን የምንለው ሀገራችን፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከታሰሩበት ማነቆ፣ የተተበተበው ማነቆ ሲበጠስና ሲፈታ ነው፤ ከእስር ተፈታን ብለን የምንናገረው፡፡ አሁን ግን ታግተን ነበር፤ ተለቀን ወደ ማኅበረሰቡ፣ ብዙኃኑ ወደታሰረበት እስር ቤት ተገናኘን፣ አብረን በአንድ ላይ ተቀላቀልን ማለት እንጅ ከእስር ተፈታን ማለት አይደለም፡፡

ምክንያቱም፣ በብዙ ነገር ታስረን ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው፡፡ እዚያ ውስጥ አካላችን ነው የታሰረው፤ መንፈሳችን አይታሰርም፡፡ ብዙ ወገኖቻችን ታስረዋል፤ አሁንም እንደነ አሸናፊ አካሉ ያለ ያለምንም ፍርድ ለአምስት ዓመት ከሦስት ወር በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ያስቆጠሩ ወንድሞቻችን እንደታሰሩ ነው፡፡ እነኚህ እስካልተፈቱ ድረስ፣ ከእስር ተፈታን ብለን ደፍረን ልንናገር አንችልም፡፡ በእገታ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችን ሲፈቱና የአገራችን ሰላምና አንድነት ሲረጋገጥ፤ የመናገርና የመጻፍ መብት ሲጠበቅ፤ መልካም አስተዳደር ሲሰፍን፣… ያኔ ነው ከእስር ተፈታን ብለን የምንናገረው፡፡

ኹለተኛ፥ በማዕከላዊም ኾነ በቂሊንጦ የእኛን መታሰር፣ መቸገር፣ መንገላታት በተለያዩ ሚዲያዎች ሲተላለፍ በመስማት ለተባበሩን፣ ከቦታው ድረስ መጥተው ለጠየቁን ክርስቲያንና ሙስሊም የሌላም እምነት ተከታዮች፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ላሉ ኹሉ በዋልድባ ገዳም ስም እጅግ አድርገን እናመሰግናለን፡፡ በእነርሱ አይዟችሁ ባይነት፣ ሞራልና ድጋፍ ሰጭነት፣ ከታገትንበት ወጥተን ከወገኖቻችን ጋራ እንድንቀላቀል አድርገውናል፡፡

አባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት፡-

Aba Gebrasilassieየእስር ቆይታችሁን እንዴት ይገልጹታል? ዛሬ ከእስር በመውጣትዎ ያልዎት ስሜት ምንድን ነው?

ከእገታ ነው የወጣነው እንጅ ከእስር ተፈታን ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም፣ ብዙ ወንድሞቻችን በሥቃይና በመከራ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ እኛም ብዙ መከራና ሥቃይ አይተናል፡፡

ኹለታችሁም የምንኵስና ልብሳችሁን እንድታወልቁ ስትገደዱ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ መሬት ለመሬት ተጎትተዋል፤ የሚል ቀርቦ በዘገባችን አካተን ነበር፤ ጠበቃችሁም በወቅቱ ገልጸውልን ነበር፡፡ እርሱን ኹኔታ በእርስዎ አንደበት ደግሞ ቢገልጹልን?

ጠበቃችን ልክ ናቸው፤ እውነት ነው፡፡ ኅዳር 14 ቀን ሰው ወደሌለበት ጨለማ ቤት ይዘውኝ ሒደው፣ ቀጠሮ የሌለኝን ቀጠሮ አለህ ብለው አታለው አውጥተው አራት የጎማ ብትር የያዙ ባሉበት አንዱ መሬት ለመሬት እየጎተተ፣ ሌሎቹ ደግሞ በኋላ በኋላ እየተከተሉ፣ ከጠዋቱ 2 እስከ 4 ሰዓት ድረስ፣ “ቆብህን፣ የሃይማኖት ልብስህን አውልቅ” እያሉ እየተሳደቡ፤ የተወለድኩበትን አገርና ማንነቴን እየሰደቡ ብዙ መከራና ሥቃይ አድርሰውብኛል፡፡ እኔን ቢሰድቡኝ ጥሩ ነበር፡፡እኔም ብቻ ሳልኾን፣ እንደ ወንድምም እንደ አባትም የማያቸው አባ ገብረ ኢየሱስም ብዙ ሥቃይ አይተዋል፡፡

አባ ገብረ ሥላሴ፣ ኹለታችሁም ለሰጣችሁ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ሰፋ ባለ ማብራሪያ እመለሳለሁ፡፡

ኹለቱ የዋልድባ መነኰሳት ከእስር ተፈቱ

FB_IMG_1523529318111

በመጨረሻም፣ በዐቃቤ ሕግ የተመሠረተባቸው የ“ሽብር ክሥ” የተቋረጠላቸው ኹለቱ የዋልድባ መነኰሳት ከእስር ተፈቱ፡፡

received_646981535648903

ዐቃቤ ሕግ፣ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ክሡን ማቋረጡን፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ያስታወቀ ሲኾን፤ ተከሣሾቹ ለሚገኙበት ለቂሊንጦ እስር ቤት የመፍቻ ትእዛዝ እንዲጻፍለት በጠየቀው መሠረት ፍ/ቤቱ በሰጠው ትእዛዝ ኹለቱ አበው መነኰሳት ዛሬ፣ ሚያዝያ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ከእስር ተፈተዋል፡፡

received_646982172315506

ከአባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት ገብረ መድኅን ጋራ ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት በእስር የቆዩት አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም ካሴ(በፎቶው: በስተግራ የሚታዩት)፣ በዋልድባ አካባቢ የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ከ2004 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ፣ የገዳሙን ይዞታ ለማስከበር ማኅበረ መነኰሳቱን በመወከል ባደረጉት ጥረት ይታወቃሉ፡፡

ከኹለቱ አበው መነኰሳት ጋራ በአንድ መዝገብ የተከሠሠውና ከቃሊቲ እስር ቤት ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው፣ አቶ ነጋ ዘላለም መንግሥቴም ከእስር የመፈቻ ትእዛዝ እንደወጣለት ተረጋግጧል፡፡ ከትላንት ጀምሮ ተፈጻሚ በኾነው የፍ/ቤቱ የፍች ትእዛዝ፣ ክሣቸው የተቋረጠላቸው 114 ተከሣሾች ከእስር እንደሚለቀቁ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

 

የቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ፤ “ሓላፊነታቸውን የተወጡ ሙሉ አገልጋይና ታላቅ ሰው ነበሩ” – ፓትርያርኩ

Kesis Dr Mikre

 • ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕርግ ተሰጥቷቸዋል፤
 • በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የትርጉም ኤክስፐርት አማካሪነት ለ25 ዓመት ሠርተዋል፤
 • ለዓለም አቀፉ የፍትሕ ጥምረትበሀገር ውስጥ አስተባባሪነት በመሥራት ላይ ነበሩ፤
 • አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀዋል፤ አሳድሰዋል፤ የአረጋውያን መጦርያ አሠርተዋል፤
 • ለእመቤታችን ታላቅ ፍቅር ነበራቸው፣ በሰንበት እና በበዓላት ከደጇ አይለዩም ነበር፤
 • የእመቤታችን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ እንዳይቋረጥ አደራየፍጻሜ ቃላቸው

†††

በተወለዱ በ88 ዓመታቸው፣ ትላንት ሚያዝያ 2 ቀን ያረፉት፣ የነገረ መለኰት ሊቁና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ምሁሩ፣ የቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ፡፡

ዛሬ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ጽ/ቤት መምሪያዎችና ድርጅቶች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ሓላፊዎችና ሠራተኞች፣ ያገለገሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት ካህናትና ምእመናን፣ በሥራቸው የሚያውቋቸው ወዳጆቻቸውና ቤተ ሰዎቻቸው፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተገኝተው ሥርዐተ ቀብራቸውን በማስፈጸም በከፍተኛ ሐዘን ሸኝተዋቸዋል፡፡

ለቤተሰዎቻቸውና ለወዳጆቻቸው፣እግዚአብሔር ጽናቱንና መረጋጋቱን ይስጣችሁ፤ ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፤ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ ከቤተ ክርስቲያን ምሁራን ልጆች አንዱ እንደነበሩና ከልጅነት እስከ ዕለተ ዕረፍት፣ በክህነታቸውና በሞያቸው ረጅምና ብርቱ አገልግሎት የፈጸሙ “ደግና ታማኝ ገብርኄር” እንደኾኑ ቃል ወንጌሉን በመጥቀስ ተናግረዋል፡፡ ሓላፊነታቸውን የተወጡ ሙሉ አገልጋይና ታላቅ ሰው ናቸውና ዛሬ በሞተ ሥጋ ሲለዩን፣ ከዚህ ዓለም ድካምና መከራ ዐረፉ እንጅ ሞቱ የማይባል በመኾኑ፣ ዕረፍታቸው ክብራቸው ነው፤ “በጥቂቱ ታመነሃልና በብዙ እሾማሃለሁ” ከተባሉት የሚደመሩበት ጥሪ በመኾኑ፣ እግዚአብሔር በመንግሥቱ ይቀበላቸው ብለን ነው የምንሸኛቸው፤ ብለዋል፡፡

ለመርሐ ግብሩ የተዘጋጀውን ዜና ሕይወታቸውንና ሥራቸውን ከእንባ ጋራ በንባብ ያሰሙት የሥርዐተ ትምህርት ከፍተኛ ባለሞያው ቀሲስ መምህር ሰሎሞን ወንድሙ፤በዛሬው ዕለት የሸኘናቸው ታላቁ የነገረ መለኰት ምሁርና የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋይ፣ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል በዕረፍተ ሥጋ ከዚህ ዓለም ስለተለዩን፣“አንድ ትልቅ የቤተ ክርስቲያንና የሀገር ቅርስ እንደጠፋ ስለምንቆጥረው ሐዘናችን የከፋ ነው፤” ብለዋል፡፡

ከብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ሥልጣነ ቅስናን የተቀበሉት ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ፣ በቤተ ክርስቲያናችን የአብነት ትምህርት በገበዩት ቅኔና የጸዋትወ ዜማ፣ በመዘምርነት አገልግለዋል፡፡ በግሪክ፣ በአሜሪካ እና በእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች፥ ነገረ መለኰትን፣ የግሪክንና የዕብራይስጥ ቋንቋዎችን እንዲሁም እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ባጠኑት የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ሞያቸው፤ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ መምህርነት አንሥቶ በምክትል ዲንነት፣በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሬስ መምሪያ ተባባሪ አርታዒነት፤ በዓለም አቀፉ የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለምሥራቅ አፍሪቃ የትርጉም ሥራ ኤክስፐርት አማካሪ ኹነው ጡረታ እስከ ወጡበት እስከ 1999 ዓ.ም. ድረስ ለ25 ዓመታት ሲሠሩ እንደቆዩ በዜና ሕይወታቸው ተገልጿል፡፡

በዓለም አብያተ ክርስቲያናት እና በመላው አፍሪቃ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤቶች በልዩ ልዩ ኮሚሽኖች በአባልነት መሥራታቸውንና በሊቀ መንበርነት መምራታቸውን፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በቦርድ አባልነትና በምክትል ሊቀ መንበርነት ለአምስት ዓመታት ማገልገላቸውን ዜና ሕይወታቸው አትቷል፡፡

በዘመናዊ ትምህርት ባሳዩት ጉብዝና፣ ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በተደጋጋሚ ለመሸለም ከመብቃታቸው በተጨማሪ፣ ባደረጉት ጥናትና ምርምር መሠረት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕርግ ተሰጥቷቸዋል፤ ለኅትመት ካደረሷቸውና ካበቋቸው መጻሕፍትም አራት ያህሉ ተዘርዝረዋል፡፡

ምሁሩ፣ በሞያቸውና በአስተዳደር ሓላፊነት በብሔራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከአከናወኗቸው ተግባራት ባሻገር በበጎ ፈቃድም፣ ለብዙዎች መካሪና አስተማሪ፣ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው ያገለገሉ መንፈሳዊና የዋህ አባት እንደነበሩ ተወስቷል፡፡

የአረጋውያን መጦሪያ አሠርተዋል፤ ጥቂት የማይባሉ አብያተ ክርስቲያንን አሳንፀዋል፤ እንዲታደሱም አድርገዋል፡፡ ከእኒህም አንዱ እስከ ኅልፈታቸው የኖሩበትና በሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበርነት ያገለገሉበት የሐያት ደብረ በረከት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሲኾን፤ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነበራቸው ታላቅ ፍቅርም፣ ዘወትር በሰንበት እንዲሁም በበዓላት ቀን ከደጇ አይለዩም ነበር፡፡

ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ተጠናቆ ለማየት ከነበራቸው ጉጉት የተነሣ፣ ግንባታቸው የደረሰበትን ደረጃ በየጊዜው በቅርበት እየተገኙ ይከታተሉ ነበር፡፡ በሕመማቸው ወቅት በቅርብ የሚያውቋቸውን አባቶች አስጠርተው፣ “የእመቤታችን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ አደራ፤ እንዳይቋረጥ፤ በቅርበት ተከታትላችሁ ከፍጻሜ እንዲደርስ አድርጉ፤ አደራ፤ አደራ፤ አደራ” በማለት አስረክበዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ በሥርዐተ ተክሊልና ቅዱስ ቊርባን ካገቧቸው ባለቤታቸው ወ/ሮ ዕፀ ገነት ድረስ፣ አንድ ወንድ ልጅ ወልደው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡ በተጨማሪም በርካታ ልጆችን አስተምረው ለታላቅ ደረጃ አድርሰዋል፡፡

ልዑል እግዚአብሔር፣ የቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤልን ነፍስ፣ ከቅዱሳን አንድነት ይደምርልን፡፡ ኦ እግዚኦ አዕርፍ ነፍሰ አቡነ ምክረ ሥላሴ፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን ይስጥልን፡፡ አሜን፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

የቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል አጭር የሕይወት ታሪክ

Dr Mikre Silassie Gebra Ama

በዛሬው ዕለት የምንሸኛቸው ታላቁ የነገረ መለኰት ምሁርና የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋይ፣ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል ይባላሉ፡፡ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ በዕረፍተ ሥጋ፣ ከዚህ ዓለም በሥጋ ስለተለዩን፣ አንድ ትልቅ የቤተ ክርስቲያንና የሀገር ቅርስ እንደጠፋ ስለምንቆጥረው ሐዘናችን የከፋ ነው፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ ከአባታቸው ከቄሰ ገበዝ ገብረ ዐማኑኤል እንዳልካቸው እና ከእናታቸው ወ/ሮ ማዘንጊያ ገብረ ሥላሴ ባዩ፣ ዛሬ በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በሚገኘውና ቀድሞ ፉሪ ፈረስ ማሰሪያ ይባል በነበረ ቦታ፣ ጥር 7 ቀን 1923 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡

አባታቸው ቄሰ ገበዝ ገብረ ዐማኑኤል እንዳልካቸው፣ አጐታቸውን መምሬ ዘቁስቋምን ተከትለው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመንበረ መንግሥት(ግቢ) ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ተመድበው ያገለግሉ ነበር፡፡ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤልም ከወላጆቻቸው ሳይለዩ በፉሪ ጽርሐ ንግሥት ቅድስት ሐና ቤተ ክርስቲያን፣ የደብሩ አስተዳዳሪ ከነበሩት ከመምህር ገብረ ጻድቅ እና ከመሪጌታ ገብረ ሚካኤል፣ በኋላም ከግራ ጌታ ወልደ ሐና ዘንድ የንባብና የመጀመሪያ ዜማ ትምህርታቸውን ተምረዋል፡፡ በመቀጠልም በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም የአብነት ት/ቤት ገብተው በመማር ጸዋትወ ዜማ ማለት ጾመ ድጓ፣ ድጓ እና ምዕራፍ አጠናቅቀው ተምረዋል፡፡

በ1941 ዓ.ም. ወደ ደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም ሔደው ከታወቁት የቅኔ መምህር ከአለቃ( በኋላ መልአከ አርያም) ይትባረክ መርሻ ዘንድ ቅኔ ከነአገባቡ ተምረዋል፡፡ በተማሩትም የጸዋትወ ዜማ እና የቅኔ ሞያ በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመዘምርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ ከቅኔ ትምህርት ቤት ከተመለሱ በኋላ በ1943 ዓ.ም. ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ት/ቤት ገብተው የአንደኛ እና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በ1950 ዓ.ም. አጠናቀዋል፡፡ በአንደኛ እና በኹለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በሚማሩበት ወቅት፣ በትምህርታቸው አንደኛ ይወጡ ስለነበር ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ሦስት ጊዜ የወርቅ ብዕሮችንና የተለያዩ መጻሕፍትን ተሸልመዋል፡፡ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንደጨረሱም ለከፍተኛ ዘመናዊና መንፈሳዊ ትምህርት ወደ ግሪክ ተልከው በአቴንስ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛው የነገረ መለኰት ትምህርት በተጨማሪ የግሪክኛ የዕብራይስጥ ቋንቋዎችን አጥንተዋል፡፡

በ1955 ዓ.ም.፣ ከአቴንስ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ማዕርግ በማጠናቀቅ በነገረ መለኰት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን(Bachelor of Divinity) አግኝተዋል፡፡ በማስከተልም ከአሜሪካው ዬል ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ስኮላርሽፕ አግኝተው ከፍተኛ ትምህርታቸውን በመቀጠል፣ በአንድ ዓመት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የማስትሬት ዲግሪአቸውን አግኝተዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ 8 ዓመት በመምህርነትና በአካዳሚ አስተዳደር አገልግለዋል፡፡ በ1965 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለሦስተኛ ዲግሪ ወደ እንግሊዝ አገር ተልከው፣ በ1969 ዓ.ም. ከአበርዲን በታሪክ ትምህርት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር ይተዳደር በነበረው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፡- ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የሐዲስ ኪዳንና የግሪክኛ ቋንቋ መምህር ኾነው አገልግለዋል፡፡ የነገረ መለኰት ምሁሩ ባደረጉት ጥናትና ምርምር መሠረት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕርግ ተሰጥቷቸዋል፤ የኮሌጁም ምክትል ዲን ኹነው ተሾመዋል፡፡

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በሚያስተምሩበት ወቅት፣ ከጀግናው ደጃዝማች ድረስ ሺፈራው ልጅ ከወ/ሮ ዕፀገነት ድረስ ጋራ በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ በብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ጸሎተ ቡራኬ፣ በሥርዐተ ተክሊል እና ቅዱስ ቊርባን ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡ ጋብቻቸውንም እንዲፈጽሙ ያስተምሯቸው ለነበሩት የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች አርኣያ ለመኾን፣ ከብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ እጅ ሥልጣነ ክህነት ተቀብለዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን ለማሻሻል በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት መሠረት፣ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ገብረ ዐማኑኤልን፣ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ አድርገው ሾመዋቸው ነበር፡፡ ለዶክትሬት ትምህርት ወደ ውጭ አገር እስከ ሔዱ ድረስ፣ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ በአስተዳዳሪነት ሲያገለግሉና ሲያስገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተው ወደ ውድ አገራቸው ሲመለሱ፣ በኢትዮጵያ በተከሠተው የፖሊቲካ ለውጥ የተነሣ፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲዘጋ ተወስኖ ስለነበር፣ እርሳቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ(የሥነ ጽሑፍ ክፍል) ተባባሪ የመጽሐፍ አርታዒ(Associate Editor) ኾነው ተመድበው ሠርተዋል፡፡

ከዚያም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ኾነው እንዲሠሩ በመንግሥት ተሹመዋል፡፡ በሥራ አስኪያጅነትም ለአንድ ዓመት ከሦስት ወር ከሠሩ በኋላ፣ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው የዩኒቨርሲቲው ፕሬስ መምሪያ ተባባሪ የመጽሐፍ አርታዒ( Associate Editor) ኾነው ሠርተዋል፡፡ ይኹንና ምድብ ሥራቸው ከትምህርታቸውና ከእምነታቸው ጋራ ተቃራኒ ኹኖ ስላገኙትም በሥራቸው ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ስለዚህም ለእምነታቸውና ለትምህርታቸው ተስማሚ ሥራ እንዲሰጣቸው ለፈጣሪያቸው በጸሎት ያመለክቱ ነበር፡፡

ልዑል እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቷቸው፣ በዓለም አቀፉ የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለምሥራቅ አፍሪቃ የትርጉም ሥራ ኤክስፐርት አማካሪ ኹነው የሚሠሩበት ኹኔታ ስላገኙ፣ የቀረበላቸውን ጥሪ በደስታ ተቀብለው ሥራውን ጀምረዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ የነገረ መለኰት ሊቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈባቸውን የግሪክኛ እና የዕብራይስጥ ቋንቋዎችን አጣርተው የሚያውቁ ምሁር በመኾናቸው ሥራቸውን ለመጀመር ወደ ኬንያ-ናይሮቢ ሔደዋል፡፡ በዚያም በዓለም አቀፉ የተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለምሥራቅ አፍሪቃ የትርጉም ሥራ ኤክስፐርት አማካሪ ኹነው ጡረታ እስከ ወጡበት እስከ 1999 ዓ.ም. ድረስ ለ25 ዓመታት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ በነበራቸው ዕውቀትና ታዋቂነት፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል በመኾን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡ ለአብነት ያህል፡-

 1. ከ1960 እስከ 1968 ዓ.ም.፣ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር፣ የዓለም ሐዋርያዊ እና የወንጌል ተልእኮ ኮሚሽን አባል(Commission on World Mission and Evangelism)
 2. ከ1961 እስከ 1966 ዓ.ም.፣ በመላ አፍሪቃ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር፣ በኢትዮጵያ የከተማና የኢንዱስትሪ ሐዋርያዊ አገልግሎት ኮሚሽን(Urban and Industrial Mission of AACC) በአባልነትና በሊቀ መንበርነት፤
 3. ከ1970 እስከ 1974 ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በቦርድ አባልነትና በምክትል ሊቀ መንበርነት፤
 4. ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የዓለም የቅዱሳት መጻሕፍት ሥነ ጽሑፍ ማኅበር በአባልነት አገልግለዋል፤
 5. በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ በዓምደ ሃይማኖት የሰንበት ት/ቤት እየተገኙም ወጣቶችን ያስተምሩ ነበር፡፡
 6. በፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት የሮም ቤተ ክርስቲያን ላደረግችው ድጋፍ፣ የኢጣልያ መንግሥት ኢትዮጵያን ይቅርታ እንዲጠይቅና እንዲክስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥ አስተባባሪነት በመሥራት ላይ ነበሩ፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል በተዘጋጀው መድረክ ተገኝተው የተለያዩ ጥናቶችን በማቅረብ ወጣቶችን ያስተምሩ ነበር፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ ይማሩባቸውና ያስተምሩባቸው በነበሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የተለያዩ መጻሕፍትን በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አዘጋጅተዋል፡፡ ለአብነት ያህልም፡-

 • በ1964 ዓ.ም.፣ Cyril and Methodius and the Slavonic MIssion(ቄርሎስ እና ሜቶድዮስ በስላቭ አገሮች የፈጸሙት ሐዋርያዊ አገልግሎት)(ያልታተመ)፤
 • Western Christian Missions in Ethiopia since the 16th century(የምዕራብ አገሮች ሚስዮናውያን በኢትዮጵያ ከ16ኛው መ/ክ/ዘ ጀምሮ)(ያልታተመ በእንግሊዝኛ ቋንቋ)
 • በ1969 ዓ.ም.፣ Church and Missions in Ethiopia in Relation to the Ethio-Italian War and the Italian Occupation of Ethiopia and the Second World War(PhD thesis,1976) later published as Church and Missions in Ethiopia during the Italian Occupation(ቤተ ክርስቲያንና ሚስዮናውያን በኢትዮጵያ እና በኢጣልያ ጦርነት ጊዜና በኢጣልያ ወረራ ጊዜ እንዲሁም በኹለተኛው የዓለም ጦርነት)(ያልታተመና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለዶክትሬት ዲግሪ የቀረበ መጽሐፍ)
 • በ2000 ዓ.ም.፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በግእዝ ቋንቋ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ይጠቀሳሉ፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ የደብረ ጽጌ ቅድስት ማርያም ገዳም ቤተ ክርስቲያን ሙሉ እድሳት እንዲደረግለት እንዲሁም የአረጋውያን መጦርያ እንዲሠራለት፣ በኮሚቴ አባልነት መመሪያ በመስጠትና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ቤተሰቦቻቸውን በማስተባበርና ገንዘብ በመስጠት በቡልጋ አውራጃ በጠራ ወረዳ ልዩ ስሙ እረገት ማርያም የተባለችዋን ቤተ ክርስቲያን ሙሉ እድሳት እንዲደረግላት አድርገዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ በሚኖሩበት በሐያት መንደር አቅራቢያ፣ የሐያት ደብረ በረከት ቅድስት ማርያም (ገመናዬ ማርያም) ቤተ ክርስቲያን ከተተከለችበት ጊዜ ጀምሮ በነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት፣ በርካታ መንፈሳዊ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ መቃኞ ቤት በዘመናዊ ዐቅድ እንዲታነፅ፤ የዋናውም ቤተ ክርስቲያን ግንባታ በፍጥነት እንዲከናወን ባለሞያዎችን በማበረታታትና ምእመናንን በማስተባበር፣ በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ የሐያት ደብረ በረከት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር በመኾን አገልግለዋል፡፡ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነበራቸው ታላቅ ፍቅርም፣ ዘወትር በሰንበት እንዲሁም በበዓላት ቀን ከደጇ አይለዩም ነበር፡፡ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ተጠናቆ ለማየት ከነበራቸው ጉጉት የተነሣ፣ ግንባታቸው የደረሰበትን ደረጃ በየጊዜው በቅርበት እየተገኙ ይከታተሉ ነበር፡፡ በሕመማቸው ወቅት በቅርብ የሚያውቋቸውን አባቶች አስጠርተው፣ የእመቤታችን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታ አደራ፤ እንዳይቋረጥ፤ በቅርበት ተከታትላችሁ ከፍጻሜ እንዲደርስ አድርጉ፤ አደራ፤ አደራ፤ አደራ በማለት አስረክበዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ ለብዙዎች መካሪና አስተማሪ፣ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው ያገለገሉ መንፈሳዊ እና የዋህ አባት ነበሩ፡፡

ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ዕፀ ገነት ድረስ ጋራ የተረጋጋ ቤተሰብ መሥርተው፣ አንድ ወንድ ልጅ ወልደው አሳድገው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡ በተጨማሪም በርካታ ልጆችን አስተምረው ለታላቅ ደረጃ አድርሰዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል፣ በአደረባቸው ሕመም፣ በጸሎትና በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ክርስቶስ ተሰቅሎ፣ ተቀብሮ በትንሣኤው ዓለምን ባዳነበት በዓለ ትንሣኤ ማግሥት፣ ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በተወለዱ በ88 ዓመታቸው በዕረፍተ ሥጋ ተለይተውናል፡፡

ልዑል እግዚአብሔር፣ የአባታችንን የቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤልን ነፍስ፣ ከቅዱሳን አንድነት ይደምርልን፡፡ ኦ እግዚኦ አዕርፍ ነፍሰ አቡነ ምክረ ሥላሴ፡፡

የአባታችንን የቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤልን ሥርዐተ ቀብር ለማስፈጸም ከተለያየ ቦታ የመጣችሁ አባቶች፣ ዘመድ ወዳጆችና የአጥቢያችን ምእመናንና ምእመናናት፤ እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ፤ ያክብራችሁ፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን ይስጥልን፡፡ አሜን፡፡

ሰበር ዜና – የኹለቱ የዋልድባ መነኰሳት ክሥ ተቋረጠ

FB_IMG_1522058589440

 • ቃቤ ሕግ ለቂሊንጦ እስር ቤት የመፍቻ ትእዛዝ እንዲጻፍለት ጠይቋል

በእነተሻገር ወልደ ሚካኤል የክሥ መዝገብ፣ በ“ሽብር ወንጀል” የተከሠሡት ኹለቱ የዋልድባ መነኰሳት፥ አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም እና አባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት፣ ክሥ ተቋረጠ፡፡

ዐቃቤ ሕግ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ለፍ/ቤት ባቀረበው ማመልከቻ፣ ክሡ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸውን በፍ/ቤት በመከታተል ላይ በሚገኙት አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም ካሴ፣ አባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት ገብረ መድኅንና አቶ ነጋ ዘላለም መንግሥቴ ላይ የመሠረተውን ክሥ ማቋረጡን ያስታወቀ ሲኾን፤ ክሡን በማንሣቱ ከእስር እንዲፈቱ ለቂሊንጦ ማረፊያ ቤት የመፍቻ ትእዛዝ እንዲሰጥለት መጠየቁ ታውቋል፡፡

ፍ/ቤቱ፣ በዐቃቤ ሕግ የማመልከቻ ጥያቄ መሠረት ለእስር ቤቱ በሚጽፈው የመፍቻ ትእዛዝ፣ በእነተሻገር ወልደ ሚካኤል መዝገብ ከተከሠሡትና ቀደም ሲል ክሣቸው ተቋርጦ ከተለቀቁት 32 ሰዎች ተለይተው ሳይፈቱ የቀሩት ሦስቱ ማለትም አባ ገብረ ኢየሱስ ኪዳነ ማርያም፣ አባ ገብረ ሥላሴ ወልደ ሃይማኖት እና አቶ ነጋ ዘላለም ከነርሳቸውም ጋራ ክሣቸው የተቋረጠላቸው 114 ግለሰቦች ከዛሬ ጀምሮ እንደሚፈቱ ይጠበቃል፡፡

የነገረ መለኰት ምሁሩና ጸሐፊው ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል ዐረፉ

 • የቀብር ሥነ ሥርዐታቸው፣ ነገ ሚያዝያ 3፣ ከቀኑ በ9 ሰዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፤
 • የጣልያን መንግሥትና የሮም ካቶሊክ፥ ኢትዮጵያን ይቅርታ መጠየቅ፣ መካስና የዘረፏቸውን ቅርሶች መመለስ እንደሚገባቸው በጽሑፎቻቸው ከሚሟገቱት አንዱ ነበሩ፤
 • ለሩብ ምእት ዓመት፣ በተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ በትርጉም ሥራዎች ቤተ ክርስቲያንን በመወከል አገልግለዋል፤

†††

IMG_0729-300x253

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅነትን ጨምሮ ቤተ ክርስቲያንን በተለያዩ መድረኮች በመወከል ሲያገለግሉ የኖሩት ቴዎሎጅያኑና ጸሐፊው ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል ዐረፉ፡፡

ዛሬ ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ንጋት ላይ፣ በሕክምና እየተረዱ በነበረበት በአዲስ አበባ ሐያት ሆስፒታል ማረፋቸው ተሰምቷል፡፡

በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ ክህነት፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት ያገለገሉት ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ፡- በሊቃውንት ጉባኤ አባልነትም በርካታ የጥናት ጽሑፎችን በማዘጋጀትና መጻሕፍትንም በማረምና በማቅናት ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል፡፡

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ነገረ መለኰትን ያስተማሩ ሲኾን፣ በተባበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ለኻያ አምስት ዓመታት በትርጉም ሥራ፣ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ም/ቤትና በሌሎችም መድረኮች ቤተ ክርስቲያንን በመወከል በስፋትና በከፍተኛ ደረጃ ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡

ከአምስት ያላነሱ መጻሕፍትን ያበረከቱት ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ፡- በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ባተኮሩ ጽሑፎቻቸው ይታወቃሉ፡፡ ለኅትመት ያበቁት የዶክትሬት ጥናታቸውም፣ በአምስቱ ዓመት የፋሽስት ጣልያን ወረራ ዘመን የሚስዮናውያንን ተጽዕኖ የሚተነትን ነው፡፡

 

በቅዱሳት መጻሕፍት ማንነት ጉዳይ ከኢኦተቤ ቴቪ ጋራ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ

ፋሽስት ኢጣልያ፣ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ላይ ላደረሰው ቃጠሎ፤ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአባቶች ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና መነኰሳት እንደዚሁም በምእመናን ላይ በግፍ ላደረሰው ጭፍጨፋ፣ የጣልያን መንግሥት እና የሮም ካቶሊክ ኢትዮጵያን ይቅርታ መጠየቅ፤ ከየገዳማቱና አድባራቱ የዘረፋቸውን ንዋያተ ቅድሳት፣ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትንና አገራዊ ቅርሶቻችንን መመለስ እንደሚገባቸው በጽሑፎቻቸው ከሚከራከሩት የመብትና ፍትሕ ተሟጋቾችም አንዱ ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ ላይ የፋሽስት ኢጣልያ ወረራ እና የሮሙ ፖፕ ፒዮስ ፲፩ኛ አቋም” በሚል ርእስ በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል መድረክ ባቀረቡት ጽሑፍ በውይይት ላይ

ባደረባቸው ሕመም በ87 ዓመት ዕድሜአቸው ያረፉት የቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ ዐማኑኤል የቀብር ሥነ ሥርዐት፤ ነገ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 3 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ከቀኑ በ9 ሰዓት፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ብፁዓን አባቶችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት እንደሚፈጸም ተገልጿል፡፡