ቅ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ: “ጽኑ ሕመም” ላይ ነው! ደቀ መዛሙርቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ድጋፍ ጠየቁ፤ ትምህርት ካቋረጡ ከሳምንት በላይ ተቆጥሯል

 • እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ በተደጋጋሚ የቀረቡ አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ጥያቄዎቻቸው ሰሚ አጥተዋል፤
 • እንደ ሌሎች ኮሌጆች ኹሉ፣ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተጠሪ ኾኖ በበላይነት እንዲከታተለው አመለከቱ፤
 • አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ በክብር እንዲነሡና አቅመ ቢስ አመራሮች በአፋጣኝ እንዲወገዱ ደቀ መዛሙርቱ ጠየቁ
 • ከነገ ጀምሮ፣ጥቅመኛ ሓላፊዎችንና ሠራተኞችን በማገድ ቢሮዎችን የማሸግ ርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ

HTTC Dekmezamuret to PM

 • ጭቁን መምህራንና ሠራተኞች እንዲሁም የማታ ደቀ መዛሙርት፣ ጥያቄዎቻቸውን እንደሚደግፉ አረጋገጡ፤
 • ንግዳዊነት የተንሰራፋበት ኮሌጁ፣ ተጠቃሎ ከመሸጡ በፊት ተቆርቋሪ ወገኖች ኹሉ እንዲደርሱለት ተማፀኑ፤

***

 

 • ለክፍያ ሲሉ ኮርሶችን በሚያግበሰብሱ ሓላፊዎች ሳቢያ፣ የትምህርት ጥራቱ “ሙሉ በሙሉ ሞቷል፤ ወድቋል፤”
 • ከመምህራኑ ይልቅ ያለአግባብ የተሰገሰጉ ሠራተኞች፥በደመወዝ፣ በአበልና በበዓላት ቦነስ  በጀቱን ይቀራመታሉ፤
 • የተማሪዎች ማደሪያዎች ሳይቀሩ፣ለንግድ እና ለመኖርያ ተከራይተዋል፤ መጸዳጃ ቤቶቻቸው መጋዘን ኾነዋል፤

HTTC Hidar2011f

 • ነፃነት የታወጀበትና በቅርስነት መያዝ ያለበት የቀድሞ የሊቀ ጳጳሱ ቢሮ፣ጾም የሚሻርበት ናይት ክለብ ኾኗል፤”
 • የተከራዮች ማንነትና ተመኑ ተለይቶ ይታወቅ፤ገቢው በውጭ ኦዲተር ተመርምሮ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ይተዳደር፤
 • ለአንድ ትልቅ የትምህርት ተቋም ሕንፃ መገንባትና መነገድ የስኬት ጥግ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፤ በቤተ ክርስቲያንና በሕዝብ ሀብት ላይ እየደረሰ ያለውን ኪሳራ እናጋልጣለን፤ትክክለኛ ተቋማዊ ለውጥ እስኪፈጠር ድረስ እንዋጋለን፤ ጥያቄያችን አፋጣኝና ቁርጥ ተግባራዊ ምላሽ ሳያገኝ ወደ መማር ማስተማሩ አንመለስም፤

/ ኹሉም 150 ደቀ መዛሙርት/

***HTTC Dekmezamuret Hidar2011

Advertisements

ቤተ ክርስቲያን: አገር አቀፍ የሰላም እና ስብከተ ወንጌል ስምሪት ልታካሒድ ነው

pat office

 • ሥልጠናን፣ሕዝባዊ ውይይትንና ዕቅበተ እምነትን ያካተተ ስምሪት ነው፤
 • እስከ ታኅሣሥ መጨረሻ ድረስ፣52 አህጉረ ስብከትን ለማዳረስ ታቅዷል፤
 • በወቅቱ ፈተናዎች፥የካህናትና የወጣቶች መብትና ግዴታ ላይ ያተኩራል፤
 • በሰማዕትነትና በሚዲያ አጠቃቀም ረገድ ኦርቶዶክሳዊውን ወጣት ያነቃል፤

***

 • ከ9ሚ. ብር በላይ በጀት ተመድቧል፤250 ጠቅላላ ልኡካን ይሳማሩበታል፤
 • በእያንዳንዱ ስምሪት በሊቀ ጳጳስ የሚመሩ 5፣ 5 ልኡካን ይሳተፉበታል፤
 • ዓላማውን የሚያስፋፉ ንኡሳን ኮሚቴዎች በየአህጉረ ስብከቱ ይቋቁማሉ፤
 • ካህናትና ምእመናን ከአቀባበል ጀምሮ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል

***

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ ከነገ በስቲያ ኀሙስ፣ ታኅሣሥ 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል የሚዘልቅ የአገራዊ ሰላም እና የስብከተ ወንጌል ስምሪት ሊያካሔድ ነው፡፡

በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለውና በቀላሉ የሚገታ የማይመስለው የሰላም ዕጦት ችግር ያሳሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ባለፈው ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሔደው የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባው ባስተላለፈው መመሪያ መሠረት የተዘጋጀው ስምሪቱ፣ ቤተ ክርስቲያናችን በሰላም ዕጦት የሚገጥማትን ተግዳሮት የምትቋቋምበትና ለአገራዊ ዕርቅና ለሕዝብ አንድነት መጠበቅ ያላትን ታሪካዊና ብሔራዊ ሚና የምትወጣበት እንደኾነ ተገልጿል፡፡

ስምሪቱ፥ የሥልጠና፣ የሕዝባዊ ውይይትና የዕቅበተ እምነት መርሐ ግብሮችን ማካተቱ ተጠቅሷል፡፡ ካህናትን በሚያሳትፈው ሥልጠና፦ የካህናት ድርሻ በሀገር ሰላም፣ የካህናት መብት እና ግዴታ፣ የካህናት ኖላዊነት(እረኝነት)፣ የካህናት መሪነት እና ዕቅበተ እምነት በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚሠራ ተጠቁሟል፤ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች መብት እና ግዴታ፣ ወጣትነት እና ሰማዕትነት፣ ወጣትነት እና ወቅታዊ ፈተናዎች እንዲሁም መንፈሳዊ ወጣት እና የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በሚሉ ርእሶችም የሰንበት ት/ቤት እና የአካባቢ ወጣቶችን የሚያነቁና የሚያስገነዝቡ ዐውደ ትምህርቶች መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡

በአገር ሰላም እና በሕዝብ አንድነት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩት የውይይት መርሐ ግብሮች፣ ከቤተ ክርስቲያን ምእመናን ውጭ የኾኑ ዜጎች የሚሳተፉበት ሕዝባዊ አቀራረብና ይዘት እንዳላቸው ታውቋል፡፡

በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሰብሳቢነት የተቋቋመውና 6 ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያዎችና ድርጅቶች፣ ከሰንበት ት/ቤቶች አገር አቀፍ አንድነት፣ከማኅበረ ቅዱሳን፣ ከነገ መለኰት ምሩቃን ማኅበር እና ሌሎች መንፈሳውያን ማኅበራት እንዲሁም ከመንፈሳውያን ኮሌጆች ተውጣጥቶ የተቋቋመና 15 ጠቅላላ አባላትን ያቀፈ የሥራ አስፈጻሚ ዐቢይ ኮሚቴ፣ በአምስት ንኡሳን ኮሚቴዎች በመደራጀት፥ ተሳታፊ ልኡካንን የመመልመል፣ የስምሪት ቦታዎችን የመለየትና አስፈላጊውን በጀት አጥንቶ የማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱ ተነግሯል፡፡

250 ጠቅላላ ልኡካን የሚሳተፉበት ይኸው መርሐ ግብር፣ 52 የሀገር ውስጥ አህጉረ ስብከትን እንደሚሸፍንና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ወጪ የተደረገ 9 ሚሊዮን ብር የማስፈጸሚያ በጀት እንደተመደበለት ታውቋል፡፡ እያንዳንዱ ስምሪት 5፣ 5 ልኡካን የሚይዝና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ እንደሚኾን ተጠቅሷል፡፡ ስምሪቱን በአህጉረ ስብከት ደረጃ የሚያቀናጁ፣ ሥልጠናውንና ውይይቱን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ የሚያስፋፉ የማኅበረ ካህናት፣ የማኅበረ ምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የማኅበራት ተወካዮች፣ የመንግሥት አካላትና የአገር ሽማግሌዎች ንኡሳን ኮሚቴዎች በየክፍሎቹ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መሪነት ይቋቋማሉ፤ ተብሏል፡፡

ካህናት፣ ምእመናንና ወጣቶች፣ ለልኡካኑ አቀባበል ከማድረግ ጀምሮ የአካባቢያቸውን ችግሮች በማሳወቅ፣ በመወያየትና መፍትሔ በማስቀመጥ በሥልጠናውም በሕዝባዊ ውይይቱም በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ከነገ በስቲያ በይፋ የሚጀመረው የሀገራዊ ሰላምና ስብከተ ወንጌል ስምሪት ቀዳሚ ተሳታፊ ልኡካን፣ በነገው ዕለት በሥራ አስፈጻሚ ዐቢይ ኮሚቴው የተዘጋጀ ገለጻ/ኦሪየንቴሽን/ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንደሚሰጣቸው ታውቋል፡፡ ጠቅላላ የስምሪት መርሐ ግብሩን እስከ ታኅሣሥ 26 ድረስ በማጠናቀቅ፣ በውጭ አህጉረ ስብከት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመቀጠል መታቀዱ ተጠቁሟል፡፡

በደቡብ ክልል የቤተ ክርስቲያንን መብት የሚጋፉ ባለሥልጣናት ተጽዕኖ እንዲቆም ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አሳሰቡ፤“አማራጩ ራስን አጠናክሮ መገኘት ብቻ ነው”

 • ከባለሥልጣናቱ አንዳንዶቹ፣ የሃይማኖት ሰባክያን እና ሓላፊዎች ናቸው፤
 • በሆሳዕና እና በከምባታ፣ ሕጋዊ የባሕረ ጥምቀት ይዞታችንን እያወኩ ነው፤
 • “ጥቃትን የምንቋቋመው የመከላከል አቅምን በአንድነት በማጠናከር ብቻ ነው”
 • በ1.5 ሚ. ብር ወጪ የአብነት ት/ቤት ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ ነው፤

***

His Grace Abune Hiryakosበአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያናችን አገልጋይ ካህናት እና ምእመናን ላይ እየተሰነዘረ ያለውን ጥቃትና ጭፍጨፋ መቋቋም የምንችለው፣ የመከላከል አቅማችንን በአንድነት ስናጠናክር ብቻ እንደኾነ የሐድያና ስልጤ፣ ሀላባ ከምባታና ጠምባሮ አህጉረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ አሳሰቡ፡፡

በሶማሌ ክልል ከተሞች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያን ላይ ከደረሰው ውድመት፣ በካህናት እና በምእመናን ላይ ከተፈጸመው ግድያና ጭፍጨፋ ተምረን በቀጣይ በሌሎች ቦታዎችም ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይደገም ከተፈለገ ያለው አማራጭ፣ “ራስን አጠናክሮ መገኘት ብቻ ነው፤” ብለዋል ብፁዕነታቸው፡፡

በደቡብ የሀገራችን ክፍል፣ አንዳንድ ባለሥልጣናት፥ ሕገ መንግሥቱን በመፃረር፣ የቤተ ክርስቲያንን ይዞታ በመጋፋትና ሥርዐተ እምነትን በነፃነት የመፈጸም መብትን በመጋፋት ተፅዕኖ እያደረሱብን እንደሚገኙ ብፁዕነታቸው ለዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል፡፡ ከእኒህም ባለሥልጣናት አንዳንዶቹ፣ የአብያተ እምነት ሰባክያንና ሓላፊዎች ጭምር ኾነው የሚሠሩ እንዳሉበት ብፁዕነታቸው በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

የአህጉረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና በኾነው ሆሳዕና፣ ላለፉት 40 ዓመታት በቤተ ክርስቲያን ይዞታ ሥር ተጠብቆ የኖረው ባሕረ ጥምቀት፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ያለው ቢኾንም፣“ቦታው የገበያ ቦታ ነው፤ በሚል የቃና ዘገሊላ በዓል ቅዳሜ በሚውልበት ዕለት በቦታው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐት ማካሔድ አልቻልንም፤” የችግሩን ስፋት በምሬት ገልጸዋል፤ በከምባታም ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ከብፁዕነታቸው መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህም ኾኖ፣ የክርስትና ጉዞ በመስቀል ላይ በመኾኑ፣ በአህጉረ ስብከታቸው ስብከተ ወንጌልን በማጠናከር፣ ወጣቶችን በሰንበት ት/ቤቶች በማደራጀትና ምእመናንን በማስተማር አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ ብፁዕነታቸው አስታውቀዋል፡፡ ተተኪ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ለማፍራት እየተደረገ ባለው ጥረትም፣ ብፁዕነታቸው በውጭ ሀገራት ያሉ የመንፈስ ልጆቻቸውን በማስተባበር በሐወራ በ1.5ሚሊዮን ብር ወጪ የአብነት ት/ቤት ለመሥራት ዝግጅት እየተደረገ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ብፁዕነታቸው ገለጻ፣ ባለፈው በጀት ዓመት፣ በኹለቱም አህጉረ ስብከት፥ በቤቶች ግንባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት ማድለብ እና ወተት ፕሮጀክት በማዘጋጀት፣ የመሳሰሉት የልማት ዘርፎች አጥጋቢ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚያው በጀት ዓመት በተደረገው ሐዋርያዊ አገልግሎት፣ በገጠርና በከተማ፣ 2ሺሕ800 ሐዲሳን አማንያን ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያን አባል ኾነዋል፡፡

የግራኝ አሕመድ ጊዜ እንዳያገረሽ – ቤተ ክርስቲያናችን ዘመቻ ፊልጶስን ልታውጅ ይገባታል

(ዜና ቤተ ክርስቲያን፤ ርእሰ አንቀጽ፣ ጥቅምት እና ኅዳር ፳፻፲፩ ዓ.ም.)

 • በአሁኑ ጊዜ ኹሉም የራሱን እምነት በሰላም ማራመድ ሲገባው በተቃራኒው ፀረ ኦርቶዶክስ ዘመቻ በኹለት ግንባር በመካሔድ ላይ ይገኛል – የፀረ ክርስትናው ቡድን ውድመት እና የሐሳውያን መናፍስት የቅሠጣ ዘመቻ
 • በሰባክያነ ወንጌል እጥረትና በአባቶች ቸልተኝነት፣ በደቡብ እና በምዕራብ ኢትዮጵያ አህጉረ ስብከት የሚገኙት አብያተ ክርስቲያን እየተዘጉ ናቸው፤ ምእመናንንም በነጣቂ ተኩላዎች እየተበሉ ናቸው፤
 • አገር ናትና፣ መደፈርና ውድመት ቢያጋጥማትም ችግሮች የበለጠ ተባብሰው የከፋ አደጋ እንዳያመጡ በትዕግሥት፣ በአርምሞና በጽሞና ማሳለፍ ከጀመረች እነኾ ወደ ግማሽ ምእት ዓመት አጋማሽ ተጠግቷታል፤
 • ሀገረ አምላክ ኢትዮጵያ፣ የእነ ሬንሐርድ ቦንኬ ሠራዊት መፈንጫ አገር ከመኾኗም ባሻገር ኹለተኛዋ ሊብያ እንዳትኾንና የግራኝ አሕመድ ጊዜ እንደገና እንዳያገረሽ፣ ቤተ ክርስቲያናችን ዘመቻ ፊልጶስን ልታውጅ ይገባታል፤
 • ከጦርነት ኹሉ የሃይማኖት ጦርነት ስለሚከፋ፣ የከፋ ችግር ከመፈጠሩ በፊት በሀገሪቱ ምሥራቃዊ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች እየተፈጸመ ያለው ኢክርስቲያናዊ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲገታ መንግሥትን ጠይቃለች፤

***

 • በአዲስ አበባ በአንድ ደብር ብቻ እስከ 10 ሰባክያነ ወንጌል ታጉረው የሚገኙት፣ በዓመት አንድ ቀን እንኳን የቅዳሴ ተራ የማይደርሰው ዲያቆን 7፣ 8 ሺሕ ብር ደመወዝ ሲያገኝ የአብነት መምህራኑና የሰባክያነ ወንጌሉ ከእጅ ወደ አፍ የኾነው በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ድክመት የተነሣ ነው፤
 • ያንዣበበውን ጥምር አደጋ ለመቋቋም፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ ለግብረ ሙስና የሚውለውን ብዝኃ ንዋይ በመቆጣጠር ለስብከተ ወንጌል ሥራ ማስኬጃ ሰፊ በጀት ከፍቶ፣ በየደብሩ የታጎሩትንም ኾነ በአሰኛቸው ጊዜ ወደ ውጭ የሚፏልሉትን ሰባክያነ ወንጌል በማሠልጠን፣ በቂ ደመወዝ እየሰጠ፣ የስብከተ ወንጌል ቡድን እየቦደነ፣ ጥምር አደጋ እየደረሰባቸው ያሉትን ክልሎች ወይም አህጉረ ስብከት መታደግ ግዴታው ነው፤
 • መንግሥታዊ ሥርዓቱ በፈጠረው ዘረኝነትና ጎሠኝነት ምክንያት፣ በየክልሉ በሚጋጩት ሕዝቦች መካከል እየተገኙ በማስተማር ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ ከሃይማኖት አባት የሚጠበቅ ተልእኮ ነው
 • ብፁዓን አባቶች የስብከተ ወንጌል ቡድን መሪዎች በመኾን፣ ጥምር አደጋው በሚደርስባቸው አህጉረ ስብከት እየተዘዋወሩ የማስተማር፣ የተጎዱትን የማጽናናት፣ ካህናቱና ምእመናኑ የሚቀበሉትን የመከራ ጽዋዕ አብሮ የመቀበል አባታዊ ግዴታ አለባቸው፤
 • የውጭዎቹ ጳጳሳትም፣ የውጭ ተወላጆች ስለአልኾኑና ዲያስጶራዎች በመመለስ ላይ ስለሚገኙ፣ በተቸገሩት አህጉረ ስብከት ከመደበኞቹ ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ኾነው በማገዝ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን መታደግ ይጠበቅባቸዋል፤

***

Zena Bete Kirstian Editorial Tik Hidar2011

ጥንታዊቷ፣ ታሪካዊቷና ብሔራዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ አገር እንደኾነች፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እንደመሰከሩላት ኹሉ፣ የሥርዓተ መንግሥት ለውጥ በመጣ ቁጥር፣ ለቀጣዩ ትውልድ ዕንቅፋት ኾኖ ላለመገኘትና ከለውጡ ጋራ ተያይዘው በኅብረተሰቡ ላይ የሚከሠቱ ችግሮች የበለጠ እንዳይባባሱና የከፋ አደጋ እንዳያመጡ በመሥጋት፣ ለውጡን ተከትሎ ወይም ተገን አድርጎ የሚነሣ ፀረ ክርስትና ቡድን በሚወስደው ኢክርስቲያናዊ ርምጃ ምክንያት የአምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ የኾኑት አብያተ ክርስቲያን ሲደፈሩና ሲወድሙ፤ በአገልጋዮቿ ካህናትና በተከታዮቿ ምእመናንም ላይ እስከ ኅልፈተ ሕይወት ጉዳት ሲደርስ፣ ሌላ አቅም ባይኖራትም የተከታይ አቅም እያላት፣ “ዝም በሉ የእኔን እግር ነው የሚበላው” እንደተባለው ዐይነት ነገር የደረሰባትን ጉዳትና ችግር ኹሉ በትዕግሥት፣ በአርምሞና በጽሞና ማሳለፍ ከጀመረች እነኾ ወደ ግማሽ ምእት ዓመት አጋማሽ ተጠግቷታል፡፡

የሩቁን ለታሪክ እንለፈውና በቅርቡ የተደረገውን ስናስታውሰው፣ በ1997 ዓ.ም. በአርሲ ሀገረ ስብከት በኮፈሌ ወረዳ ውስጥ የምትገኘው የአይሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ በወቅቱ በተፈጠረው የምርጫ ግርግር ምክንያት፣ ፀረ ክርስትና አቋም ባለው ቡድን ስትቃጠልና አገልጋዮቿ ካህናት በቤተ መቅደስ ውስጥ ሲታረዱ ዝም ብላ አሳልፋለች፡፡ እንደገናም በ1999 ዓ.ም. በጅማ ሀገረ ስብከት የበሸሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ጥቅምት 5 ቀን በዕለተ በዓሉ በፀረ ክርስትና ኃይሎች ሲቃጠልና አገልጋዮቿ ካህናትና ተከታዮቿ ምእመናንም በቤተ መቅደሱ ውስጥ እንደ በግ ሲታረዱ አሁንም ለኅብረተሰቡ የከፋ እልቂት እንዳይደርስ በማሰብ በብዙኃን ተከታዮቿ ዘንድ እየታማች ጉዳቷን ጉዳት አድርጋ ድምፅዋን ሳታሰማ በትዕግሥት አሳልፋለች፡፡

አሁን ደግሞ በቅርቡ፣ ባሳለፍነው በ2010 ዓ.ም. መገባዳጃ ላይ፣ አገር የኾነችውን ወይም ኹለንተናዊ ጠቃሜታዋና ትሩፋቷ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታ የኾነችውን አንጋፋዋን ቤተ ክርስቲያን ከሌላው ነጥሎ ለመምታትና የተከታዮቿ ምእመናንን አሻራ ከገጸ ምድር ለማጥፋት ወይም አሳምኖ የራሱ ተከታዮች ለማድረግ፣ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ባለው የሱማሌ ክልል ፀረ ክርስትና ቡድን በፈጸመው ጥቃት፣ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያንን በሙሉ አውድሟቸዋል፤ ሀብታቸውን፣ ንብረታቸውንና ቅርሶቻቸውንም ዘርፏቸዋል፤ አገልጋዮቿ ካህናትንም እንደ ካህኑ ዘካርያስ በየቤተ መቅደሳቸው ውስጥ አርዷቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ በማነጣጠር በተከታታይ የተፈጸመው ይህ ዐይነቱ ጥቃት ወይም ኢክርስቲያናዊ ድርጊት ከትዕግሥት በላይ ቢኾንም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ አገር እንደ መኾኗ መጠን፣ አሁንም በቤተ ክርስቲያንም ኾነ በሕዝብ ላይ የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ በማሰብ ብዙ መጎዳቷንና መጠቃቷን ለመንግሥትና ለሕዝብ ይፋ ያደረገችው ከብዙ ጉዳትና ትዕግሥት በኋላ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ከዓመታት በፊት በሊቢያ በረሓ ላይ በአይኤስኤስ ፀረ ክርስትና ቡድን ለተሠዉት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሰማዕትነት ክብርና ማዕርግ እንደሰጠቻቸው ኹሉ ይልቁንም፣ በራሳቸው አገር በቤተ መቅደስ አገልግሎት ላይ እንዳሉ ለተሠዉት ለራሷ ካህናትና ምእመናን የሰማዕትነት ክብርና ማዕርግ መስጠት ነበረባት፤ ከአሁኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የሚጠበቀውም ይህ ውሳኔ ነበር፤ ወደፊትም ቢኾን የሰማዕትነት ክብርና ማዕርግ እንዲያገኙ ውሳኔ መስጠት ይገባታል፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ፣ ለኹሉም በተሰጠው ገደብ የለሽ የእምነት ነጻነት መሠረት፣ ኹሉም የራሱን እምነት በሰላም ማራመድ ሲገባው በተቃራኒው ፀረ ኦርቶዶክስ ዘመቻ በኹለት ግንባር በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡ በአንድ በኩል ቀደም ሲል በዝርዝር እንደተገለጸው፣ ፀረ ክርስትና አቋም ያለው ቡድን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙትን የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን እያቃጠለ ነው፤ ካህናትንና ምእመናንንም እያረደ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ እንደእነ ፓስተር ኢዩ ጬፋን የመሳሰሉት የእነ ሬንሐርድ ቦንኬ ደቀ መዛሙርት፣ በቡድን ተሰማርተው ሕዝቡን በወንጌል ሳይኾን በመናፍስት መንፈስ በማስገደድና በካራቴ በግድ በማሳመን የእነርሱ ተከታይ ለማድረግ እየተጣጣሩ ነው፡፡

ስለዚህ የብሉይ ኪዳን እምነትና የሐዲስ ኪዳን እምነት መሠረት የኾነችው ሀገረ አምላክ ኢትዮጵያ፣ የእነ ሬንሐርድ ቦንኬ ሠራዊት መፈንጫ አገር ከመኾኗም ባሻገር ኹለተኛዋ ሊብያ እንዳትኾንና የግራኝ አሕመድ ጊዜ እንደገና እንዳያገረሽ፣ ቤተ ክርስቲያናችን ዘመቻ ፊልጶስን ልታውጅ ይገባታል፡፡ በስሟ ተጠቃሚዎች የኾኑት አንጋፋ ማኅበራትም፣ ከቤተ ክርስቲያኒቷ ጋራ በአቻነት ለመሰለፍ የሚያደርጉትን ግብግብ ለጊዜው አቁመው በሚቻላቸው ኹሉ ሊያግዟት ይገባቸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ትዕግሥትዋ ያለቀ በመኾኑ፣ ከጥቅምት 11 እስከ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ባደረገችው ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ባሳለፈችው ውሳኔ፣ ከጦርነት ኹሉ የሃይማኖት ጦርነት ስለሚከፋ፣ የከፋ ችግር ከመፈጠሩ በፊት በሀገሪቱ ምሥራቃዊ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች እየተፈጸመ ያለው ኢክርስቲያናዊ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲገታ መንግሥት የራሱን አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ ያቀረበችው አቤቱታና ከኅዳር 1 እስከ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ለ7 ቀናት ያህል በመላ ኢትዮጵያ ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ የዐወጀችው ዐዋጅ የሚደገፍ ነው፡፡

እንዲሁም ችግር ባለባቸው ክልሎች ወይም አህጉረ ስብከት፣ የስብከተ ወንጌል ቡድን እንዲላክ ያሳለፈችው ውሳኔም ድጋፍ የሚቸረው ነው፤ ምክንያቱም፣ “ሰዎቹ ሲተኙ ጠላት መጥቶ በስንዴው ላይ እንክርዳድ ዘራበት” የሚለው ቃለ ወንጌል፣ በአሁኑ ጊዜ በቀጥታ በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ እየተፈጸመ ያለ ተግባር በመኾኑ፣ በ37ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ በሰባክያነ ወንጌል እጥረትና በሃይማኖት አባቶች ቸልተኝነት የመጤ እምነት አራማጆች በሚዘሩት ኑፋቄና ክሕደት፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ አህጉረ ስብከት የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን እየተዘጉ ናቸው፤ ምእመናንንም በነጣቂ ተኩላዎች እየተበሉ ናቸው፤ በፀረ ክርስትና ቡድን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚደርሰውም አደጋ፣ ከዚህ በላይ በመጠኑ እንደተገለጸው ነው፡፡

ከቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ድክመት የተነሣ፣ በአዲስ አበባ በአንድ ደብር ብቻ እስከ 10 የሚደርሱ ሰባክያነ ወንጌል ታጉረው ይገኛሉ፡፡ እንደዚያም ኾኖ ሕዝበ ክርስቲያኑ በቂ ትምህርት አያገኙም፤ ብቃት ያላቸውና አንደበተ ርቱዕ የኾኑ ሰባክያነ ወንጌልም፣ ወደ አውሮጳና ወደ አሜሪካ፣ ወደ ዐረብ አገሮችም ጭምር ለስብከት እየተጋበዙ የሚሔዱት፣ በደመወዝ እጥረት ያለባቸውን ችግር ለመሸፈን እንጂ አዲስ አማኝ ለማግኘት አይደለም፡፡ በጠቅላላው ችሎታ ያላቸው ሰባክያነ ወንጌል ኹሉ፣ በውጭም ኾነ በውስጥ ሲፍጨረጨሩ የሚስተዋሉት፣ ራሳቸውን ለማኖር ያህል እንጂ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማኖር አይደለም፡፡ የሀገር ውስጦቹም ቢኾኑ ራሳቸውን ከማኖር ባለፈ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያኖር ትምህርት ሲሰጡ አይስተዋሉም፡፡

ክብርና ምስጋና፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ራሳቸውን አስችለው ላለፉት አባቶች ይኹንና በአሁኑ ጊዜ የሌሎቹ እንደተከደነ ይብሰልና በዓመት አንድ ቀን እንኳን የቅዳሴ ተራ የማይደርሰው ዲያቆን፣ የወር ደመወዙ ሰባት፣ ስምንት ሺሕ ደርሷል፡፡ የአብነት መምህራንና የሰባክያነ ወንጌል ደመወዝ ግን፣ እስከ አሁንም ድረስ ከእጅ ወደ አፍ እንደኾነ ነው፡፡ በዚያም ኾነ በዚህ፣ በአሁን ሰዓት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ያንዣበበውን ጥምር አደጋ ለመቋቋም፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ በዋናው መሥሪያ ቤትም ኾነ በገዳማትና በአድባራት ለግብረ ሙስና የሚውለውን ብዝኃ ንዋይ በመቆጣጠር ለስብከተ ወንጌል ሥራ ማስኬጃ ሰፊ በጀት ከፍቶ፣ በየደብሩ የታጎሩትንም ኾነ በአሰኛቸው ጊዜ ወደ ውጭ የሚፏልሉትን ሰባክያ ወንጌል በማሠልጠን፣ በቂ ደመወዝ እየሰጠ፣ የስብከተ ወንጌል ቡድን እየቦደነ፣ ጥምር አደጋ እየደረሰባቸው ያሉትን ክልሎች ወይም አህጉረ ስብከት መታደግ ግዴታው ነው፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓቱ በፈጠረው ዘረኝነትና ጎሠኝነት ምክንያት፣ በየክልሉ የሚጋጩት ሕዝቦች መካከል እየተገኙ በማስተማር ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ ከሃይማኖት አባት የሚጠበቅ ተልእኮ ነው፡፡

በየአህጉረ ስብከቱ የተመደቡት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም፣ የስብከተ ወንጌል ቡድን መሪዎች በመኾን፣ ጥምር አደጋው በሚደርስባቸው አህጉረ ስብከት እየተዘዋወሩ እንዲያስተምሩና የተጎዱትን እንዲያጽናኑ ሓላፊነታቸው ያስገድዳቸዋል፤ ካህናቱና ምእመናኑ የሚቀበሉትን የመከራ ጽዋዕ አብሮ የመቀበል አባታዊ ግዴታም አለባቸው፡፡ የውጭዎቹ ጳጳሳትም ቢኾኑ፣ የውጭ ተወላጆች ስለአልኾኑና የኢትዮጵያውያን ዲያስጶራዎች ወደ አገራቸው በመመለስ ላይ ስለሚገኙ፣ ችግር በደረሰባቸው አህጉረ ስብከት ኹሉ ከመደበኞቹ ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ ተጨማሪ ኾነው በማገዝ በቅድሚያ በሀገር ውስጥ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን መታደግ ይገባቸው ነበር፡፡ ኹሉም ብፁዓን አባቶች፣ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ ሀገር ከአንዱ ሀገረ ስብከት አልመቻቸው ሲል ወደ ሌላው ሀገረ ስብከት እየተዘዋወሩ መኖር የሚችሉት ቤተ ክርስቲያን መኖር ስትችል ነውና፡፡ በሌላ አባባልም፣ “ፍሬ የሚያፈራውን ዛፍ ለመቁረጥ ምሳር በዛፎች ላይ ተቃጥቷል” ተብሎ በቅዱስ ወንጌል እንደተነገረው ኹሉ፣ በአሁኑ ጊዜም ፀረ ክርስትናው ኃይል በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ክፉኛ ስለ አነጣጠረ፣ የግራኝ ሙሐመድ ጊዜ እንደገና እንዳያገረሽ ያሠጋል፡፡

“የአንዳንድ አካባቢዎች የሰላም ዕጦት ለወደፊቱ ያሰጋል” ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ዐወጀ፤ ምልዓተ ጉባኤውን ባለ15 ነጥቦች መግለጫ በማውጣት አጠናቀቀ

EOTC Holy Synod

 • በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውና በቀላሉ የሚገታ የማይመስለው የሰላም ዕጦት ወደፊት አስቸጋሪ ኹኔታዎች እንዳያስከትል ስለሚያሰጋ፣ የወንጌል ሥምሪት ተዘጋጅቶ ትምህርተ ወንጌል ተጠናክሮ እንዲሰጥከዚህም ጋራ ከኅዳር 1 እስከ 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በመላው አብያተ ክርስቲያን ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ መመሪያ አስተላልፏል፤
 • የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ ለማስፋት ከላይ እስከ ታች የሚተገበር የኹለንተናዊ ለውጥ መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የቀረበ ስለኾነ፤በተከፈተው ጽ/ቤት ትግበራው እንዲቀጥል

የመግለጫውን ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲኾን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት፣ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሒድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ማኅበራዊና መንፈሳዊ አካሔዶች የሚበጁ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡ በዚሁ መሠረት፤

 1. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቀረበው አጀንዳ ተራ ቁጥር አንድ ላይ በተገለጸው የጉባኤ መክፈቻ ንግግር የተመዘገበው ፍሬ ሐሳብ የበጀት ዓመቱ መመሪያ ኾኖ ያገልግል ዘንድ ምልዓተ ጉባኤው ተቀብሎታል፤
 2. የብፁዓን አባቶች የሥራ ምደባና ዝውውር በማስፈለጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን ኹኔታ ከመረመረ በኋላ ዝውውሩን አከናውኗል፤ አዲስ የሥራ ምደባም ተካሒዷል፡፡
 3. በሀገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ ክልሎችና ዞኖች ተከሥቶ የነበረው ኅልፈተ ሕይወት፣ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠልና የንብረት መውደም የዜጎች መፈናቀል ይገታ ዘንድ በተደጋጋሚ የተላለፈው ጥያቄ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግሥት በኩል ተቀባይነትን ያገኘ ቢኾንም፤ አሁንም በሀገሪቱ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ እየተሰማ ነው፡፡ ስለዚህ ከየአቅጣጫው እየተሰማ ላለው ችግር አስቸኳይ መፍትሔ ተፈልጎ እንዲገታ ካልተደረገ እየሰፋና እያደገ ሊሔድ ስለሚችል መንግሥት ከአቅም በላይ እየኾነ ለሚታየው ችግር አጽንዖት ሰጥቶ አስፈላጊውን ሕጋዊ መፍትሔ እንዲገኝ በማድረግ ተገቢውን እንዲፈጸም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በድጋሚ ያሳስባል፡፡
 4. የዘንድሮውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ልዩ ታሪካዊ ጉባኤ ከሚያደርጉት መካከል፣ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ዐራተኛ ፓትርያርክ፣ አብረዋቸው ከነበሩት አባቶች ጋራ ወደ እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ የመመለሳቸው ጉዳይ አንዱ እንደኾነ አያጠያይቅም፤
 5. ለኢትዮጵያ ምእመናን ከኤርትራ ምእመናን፤ ለኤርትራ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም የኤርትራ ቤተ ክርስቲያን የመፈቃቀርና የአንድነት እንዲሁም የበለጠ የክፉ ቀን ደራሽ ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ስለዚህ በሁሉም መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ተቀራርቦ እየሠሩ መረዳዳት ይቻል ዘንድ ከወዲሁ ኹኔታዎችን የሚያመቻች የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
 6. በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የጸደቀው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ሠላሳ ሰባተኛው ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ የጋራ መግለጫ፣ በአፈጻጸም ዙሪያ የሚከሠት ችግር ካጋጠመው በቋሚ ሲኖዶስ እየተመረመረ ለውጤት ይበቃ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቶ መመሪያ አስተላልፏል፤
 7. በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለው የሰላም ዕጦት ችግር በቀላሉ የሚገታ ኾኖ ካልተገኘ ወደፊት አስቸጋሪ ኹኔታዎች ሊከሠቱ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ፡፡ ስለዚህ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዊ ሥርዓት የወንጌል ስምሪት ተዘጋጅቶ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትምህርተ ወንጌል ተጠናክሮ እንዲሰጥ ኾኖ ከዚህም ጋራ ከኅዳር 1 እስከ ኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መመሪያውን አስተላልፎአል፤
 8. በተቀረፀው አጀንዳ መሠረት አቤቱታ የቀረበባቸውን አህጉረ ስብከት በተመለከተ መርምሮና አጣርቶ መፍትሔን የሰጠ ሲኾን በአንጻሩ ከቅን አስተዳደር የሚጠበቅ ድርሻ ስለኾነ አስተዳደራዊ ችግር ያጋጠማቸው አህጉረ ስብከት ተመርምረው ውጤታቸው ተፋጥኖ ይቀርብ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል፡፡
 9. በበጀትና ሒሳብ መምሪያ በኩል የቀረበው የዘመኑ ገቢና ወጭ ሒሳብ ሪፖርት ከተሰማ በኋላ ገቢው በትክክል እንዲመዘገብ ኾኖ፤ የወጭው አርእስት ተጠብቆ በበጀት ዓመቱ እንዲሠራበት ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያን ሰጥቷል፡፡
 10. በጥንታዊት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በመንፈሳዊውም ኾነ በማኅበራዊው ረገድ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ገምግሟል፡፡ በቀጣይም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ ለማስፋት በቤተ ክርስቲያኒቱ ከላይ እስከታች የሚተገበር የቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ለውጥና መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ የቀረበ በመኾኑ ለዚሁ ተግባር በተከፈተው ጽ/ቤት ሥራው እንዲቀጥል፤

በውጭ አገር ለምትገኘውም ቤተ ክርስቲያናችን የየአገሮቹን ሕገ መንግሥት ባገናዘበ መልኩ ቃለ ዓዋዲ እንዲዘጋጅና ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በመዋቅራዊ አስተዳደር እንዲመራ ተወስኖአል፡፡

11. አሁን በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱስ ሲኖዶስ መካከል የተፈጠረው አንድነት ለቀጣይ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሥራችን መቃናት በር ከፋች በመኾኑ ከአሁን በኋላ በአገር ውስጥም ኾነ በውጭው ዓለም ያለችው ቤተ ክርስቲያን በአንዲት ቀኖናዊት ቤተ ክርስቲያን በማዕከል እንድትመራ ወስኗል፡፡

12. ከሐምሌ ወር በዋሽንግተን ዱሲ የሁለቱ ሲኖዶስ ልኡካን የስምምነቱን ሰነድ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተቀበሎ በማጽደቅ በሰነድነት እንዲቀመጥ ወስኗል፡፡

13. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በዴር ሡልጣን ገዳማችን ይዞታ ላይ እየታየ ያለው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመሔዱ የተነሣ ችግሩ ይፈታ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽሑፍም ኾነ በቃል ለሚመለከተው ሁሉ በአካል ቀርቦ ከማመልከት የተገታበት ጊዜ እንደሌለ ይታወቃል፤ ታሪካዊ እውነትን ለመሻር በማይገባ ኹኔታ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሌላት ርስትና መብት የዴር ሡልጣን ገዳማችን ባለቤትነታችንን ለማሳጣት ብዙ የፈጠራ ወሬዎችን በመንዛት የተሰማሩት ግብጻውያን ኮፕቲኮች ሊያውቁት የሚገባ ትልቁ ጉዳይ በማን ርስት ማን ያዝዛል? ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሕይወታቸውን ሳይቀር መሥዋዕት በማድረግ ሃይማኖታቸውንና ጥንታዊ ታሪካቸውን ጠብቀው ለእኛ አስረክበውናል፤ እኛም ጠብቀን ለትውልዱ የማስረከብ ሓላፊነታችንን እንወጣለን፡፡

የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ኾነ በማንኛውም የሰነድ መረጃ የሌለው የባለቤትነት ጥያቄ በማንሣት እየተፈጠረ ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ ማቆም አለባቸው፤ ዴር ሡልጣን ትላንትም ዛሬም ነገም የኢትዮጵያ ገዳም ነው፡፡

ዳሩ ግን መፍትሔውን ከማስገኘት ይልቅ እየደረሰ ያለው ተፅዕኖ እየሰፋና እየከበደ መጥቶ በአሁኑ ወቅት ገዳሙን በሚጠብቁና በሚቆጣጠሩ መነኰሳት ላይ በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ያልተጠበቀ ከፍተኛ ችግር እየደረሰ ስለኾነ የችግሩን አስገዳጅነት አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት የጉዳዩ ባለቤት እንደመኾኑ አስፈላጊውን መፍትሔ እንዲያስገኝልን እንጠይቃለን፡፡

14. የቦታቸው ታላቅነትና የታሪካቸው ስፋት ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ባስገኘላቸው በርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን እየተገነባ ላለው ሙዝየምና የመሰነጣጠቅ አደጋ ለሚታይበት ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለጥገናና ለግንባታ አገልግሎት የሚውል ገንዘብ ተፈቅዶዋል፤

በዚሁ መሠረት፤

 1. ለርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሥራ ማከናወኛ ብር 20,000,000.00/ኻያ ሚሊዮን ብር/
 2. ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ማስጠገኛ ብር 20,000,000.00/ኻያ ሚሊዮን ብር/ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ወጭ ኾኖ እንዲሰጥ ተወስኗል፤

15. አንዳንድ ግለሰዎች በግልና በቡድን በመደራጀት የቤተ ክርስቲያኗ መብትና ቀኖና እየተጋፉ መኾናቸውን ከቀረበው ሪፖርት ጉባኤው ተገንዝቧል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በዚህ ተግባር ላይ የተሠማሩትን የሕግ ከለላ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም ዓበይት ጉዳዮች ላይ ለ11 ቀናት ያህል በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች በስፋትና በጥልቀት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ጥቅምት 21 ቀን 2011 ..


EOTC Holy Synod Tik2011 Closing Meg

በቅ/ሲኖዶስ አዲስ የአህጉረ ስብከት አደረጃጀት በውጭና በአገር ቤት የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ስምና ምደባ ዝርዝር

Holy Synod Bishops placementBishops placement33

ማስታወሻ፡-
 • በቀደመው ዘገባ፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ፣ በመካከለኛው ካናዳ ሀገረ ስብከትም እንደተመደቡ የተገለጸው፣ ብፁዕነታቸው በሀገር ውስጥ ብቻ ለመመደብ ለምልዓተ ጉባኤው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት በመለወጡ የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብቻ ኾነው ተመድበዋል፤
 • በተጨማሪም፣ በቦልቲሞር የመካነ ሰላም ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ – የፐልስንቫንያ ስቴት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ – በሮቸስተር የኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ፤ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ – የሰሜን ካሊፎርኒያና አካባቢው ሀገረ ስብከት ጳጳስና የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሎሳንጀለስ የበላይ ጠባቂ፤ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ – የዩናይትድ ኪንግደም እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተሹመዋል፡፡

ኮፕቲኮች በፈጠራ መረጃ በዴር ሡልጣን ባለቤትነት ላይ ከሚያካሒዱት ትንኮሳ እንዲታቀቡ ቅ/ሲኖዶስ አሳሰበ

 • በዓለም ዙሪያ የሚገኙ መላው ኢትዮጵያውያን ትንኮሳውን ለመቃወምና ከግብጽ ያልተመለሱ ይዞታዎችን ለማስመለስ እንዲተባበሩ ጥሪ አቀረበ፤
 • የእስራኤል መንግሥት በቃሉ መሠረት፣ በቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ ላይ ጥገና በመጀመሩ አመሰገነ፤ ጥገናው ኹሉንም ይዞታዎች እንዲያካትት ጠየቀ፤
 • ዴር ሡልጣን፣ የኢትዮጵያ የነበረና ምንጊዜም የኢትዮጵያ ኾኖ የሚቆይ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሳችን ነው፤

***

የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት፣ ጥንታውያንና ታሪካውያን ይዞታችን በኾኑት የዴር ሡልጣን ገዳማት ላይ ማስረጃ በሌለው የፈጠራ መረጃ የባለቤትነት ጥያቄ በማንሣት የሚያካሒዱትን አላስፈላጊ ሁከት እንዲያቆሙ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥሪ አስተላለፈ፤ የእስራኤል መንግሥት ቃል በገባው መሠረት ከዴር ሡልጣን የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ የጀመረውን የእድሳት ሥራ አጠናክሮ በመቀጠል ኹሉንም የኢትዮጵያ የዴር ሡልጣን ይዞታዎች በአግባቡ እንዲጠግን ጠየቀ፡፡

Holy Synod Der Sultan resoration

የኢትዮጵያ ይዞታ በኾነው በዴር ሡልጣን ገዳም የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ እድሳት ላይ፣ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ያሳዩትን ሕገ ወጥ ተቃውሞ አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 ቀን በሰጠው መግለጫ፣ ግብጻውያኑ ከትንኮሳና ሁከት እንዲታቀቡ ጥሪ ያቀረበ ሲኾን፤ ቃል በገባው መሠረት፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ ጥቅምት 14 ቀን ጥገናውን ለጀመረው የእስራኤል መንግሥት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምስጋናቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ አያይዞም፤ የመድኀኔዓለም፣ የአርባእቱ እንስሳ እና የቅዱስ ሚካኤል ገዳማትን የያዘው ዴር ሡልጣን፣ የኢትዮጵያ የነበረና ምንጊዜም የኢትዮጵያ ኾኖ የሚቆይ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሳችን፣ የኢትዮጵያውን በኢየሩሳሌም ቅድስት ሀገር በኹሉም ዘመናት በቋሚነት ለመገኘታቸው ምስክር እንደኾነ አስገንዝቧል፡፡

Coptic monk arrested

“የግብጽ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የለሽ ክሥና ሁከት በመቃወምና ገዳማችሁን በመጠበቅ የበኩላችሁን እንድትወጡ፣ ወደፊትም ከግብጽ ያልተመለሱ ይዞታዎቻችንን ለማስመለስ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ እንድታደርጉ፤” በማለት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ መላው ኢትዮጵያውያን ለተቃውሞ እንዲተባበሩ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል ይመልከቱ የሚከተለው ነው

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

የኢትዮጵያውያን ይዞታ በኾነው በዴር ሡልጣን ገዳም የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ እድሳት ላይ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ያሳዩትን ሕገ ወጥ ተቃውሞ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ሁላችሁም እንደምታውቁት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም ካሏት ጥንታውያንና ታሪካውያን ቅዱሳት መካናት ውስጥ አንዱና ዋናው፣ በዴር ሡልጣን የሚገኘው የመድኀኔዓለም፣ የአርባዕቱ እንስሳ እና የቅዱስ ሚካኤል ገዳማት ናቸው፡፡

ከታሪክ እንደምንረዳው፣ ኢትዮጵያውያን በምድረ እስራኤል የነበራቸው ርስት ከሦስት ሺሕ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የአሁኗ ኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ መገኛዋን ከዓባይ ምንጭ ጋራ በማያያዝ ያለምንም መሳሳት ከአርባ ጊዜ በላይ የተመዘገበች፤ በታሪክ፣ በእምነት እና በማኅበራዊ ትስስር ከእስራኤል ጋራ የጸና ግንኙነት ያላት ሀገር ናት፡፡

ከንግሥት ሳባ የኢየሩሳሌም ጉብኝት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ወደ ቅድስት ሀገር ያለማቋረጥ በየዓመቱ በዓለ ፋሲካን ለማክበር፣ ዓመታዊ አምልኰተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም፣ በርስት የተሰጣቸውን ይዞታ ለማስከበርና በንግድ ሥራዎች ይጓዙ እንደነበር በታሪክም በቅዱሳት መጻሕፍትም የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡

ለዚህም በሐዲስ ኪዳን፣ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ለመግባቱ ምክንያት የኾነውና በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ከቁጥር 26 እስከ 40 የተጻፈው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ታሪክ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ወደ ኢየሩሳሌም በሚያደርጉት ጉዞ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ትስስርን ከማጠናከር ባሻገር በዴር ሡልጣን እና በብዙ መካናት ቋሚ ይዞታን በማቋቋም በርካታ ገዳማትንና አድባራትን መሥርተዋል፤ መንበረ ጵጵስናም አቋቁመዋል፡፡ ይህም ድርጊት፣ ኢትዮጵያ በኢየሩሳሌም የሕዝቦቿ ምልክትና መመኪያ እንድትኾን አድርጓታል፡፡

ይኹን እንጅ ነባሩን ታሪካዊ እውነት ለመሻርና በማይገባ ኹኔታ ግብጻውያን በሌላቸው መብትና ሕጋዊ ባልኾነ የፈጠራ መረጃ፣ ኢትዮጵያን ከኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን ገዳም ባለቤትነቷን ለማሳጣት ብዙ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆዩም፣ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ሳይቀር መሥዋዕት በማድረግ ሃይማኖታቸውንና ጥንታዊ ገዳማቸውን ጠብቀው እስከ አሁን ቆይተዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን የኢየሩሳሌም ይዞታ ከቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃነት በተጨማሪ ኢየሩሳሌምን ይገዙ በነበሩ መሪዎች የግብር እና የመንግሥት ዐዋጅ መዛግብት፣ ኢየሩሳሌም ድረስ ተጉዘው ታሪክ በጻፉ ምሁራን፣ በኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች የግል ማስታወሻ እና በዓለም አቀፍ መዛግብት ሳይቀር የተመዘገበ ሐቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህልም እንደነ አባ ጀሮም ያሉ የላቲን ታሪክ ጸሐፊዎች፣ እንደነ ከሊፋ ዑመር እና ሳላሐዲን ባሉ ገዥዎች፣ በኢየሩሳሌም ተመሳሳይ ይዞታ ባላቸው በአርመንና በሶርያ ኦሬንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ በግሪክ እና በራሽያ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ገዳማት መዛግብት የተመሰከረ ነው፡፡

ይኹን እንጅ፣ ግብጻውያን በሚፈጥሩት ግፍና ኢሰብአዊ ድርጊት በይዞታችን ያለውን ገዳም ከጉዳት ለመጠበቅና ለማደስ እንኳ ሳንችል በመቅረታችን እየፈራረሰ ይገኛል፡፡

በመኾኑም ቤተ ክርስቲያኒቱ ስታሰማ በነበረው ተደጋጋሚ አቤቱታና የኢትዮጵያ መንግሥት ባቀረበው ሕጋዊ የመብት ጥያቄ መሠረት፣ የእስራኤል መንግሥት ገዳሙን ለማደስ ቃል በመግባቱ እና በዚሁ መሠረት መንግሥት ቃሉን በመጠበቅ በቅርቡ ጉዳት ከደረሰበት ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ እድሳት በመጀመሩ የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እና በመላው ኢትዮጵያውያን ስም በመግለጽ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡

የተጀመረው እድሳት፣ በዴር ሡልጣን የሚገኙ እና እጅግ በአስከፊ ጉዳት ላይ ያሉ ሁሉንም የኢትዮጵያ ይዞታዎች በማዳረስ ገዳሙ ጥንታዊ ይዞታውን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚደረግልን እናምናለን፡፡

አሁን እየተደረገ ያለውን ጥገና አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥትም ኾነ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለእስራኤል መንግሥት ምስጋናችሁን እንድታቀርቡልን፤ የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት የለሽ ክሥና ሁከት በመቃወም ገዳማችሁን በመጠበቅ የበኩላችሁን እንድትወጡ፣ ወደፊትም ከግብጽ ያልተመለሱ ይዞታዎቻችንን ለማስመለስ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት፣ በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ኾነ በማንኛውም የሰነድ ማስረጃ መሠረት የሌለው የባለቤትነት ጥያቄ በማንሣት እየፈጠሩት ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ እንዲያቆሙ፤

ዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ገዳም፣ ምንጊዜም ቢኾን የኢትዮጵያ የነበረና ወደፊትም የኢትዮጵያ ኾኖ የሚቆይ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሳችን፤ የኢትዮጵያውያን በኢየሩሳሌም ቅድስት ሀገር በሁሉም ዘመን በቋሚነት ለመገኘታቸው ምስክር ስለኾነ፣ ከዚህ የተሳሳተ ትንኮሳና ሁከት እንዲታቀቡ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ በመጨረሻም የተጀመረው የእድሳት ሥራ ተጠናክሮ በመቀጠል ሁሉንም የኢትዮጵያ የዴር ሡልጣን ይዞታዎች በአግባቡ እንዲጠግኑልን፤ በኢትዮጵያ መንግሥትም ኾነ የሰው ልጅ ቅርስ ጥበቃ ለሚያሳስባቸው በጎ አድራጊዎች ሁሉ ጥሪያችንን እያስተላለፍን፣ እድሳቱ ያለምንም ዕንቅፋትና ሁከት ከፍጻሜ እንዲደርስ ጸሎታችንና ምኞታችን መኾኑን እናስታውቃለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን 

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም.