ማኅበረ ቅዱሳን: “ማንም በቋንቋው እንዳይማር ዕንቅፋት አይፈጥርም”፤ የቴቪ መርሐ ግብርን የሚያካትት “የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት” አቋቁሞ እየሠራ ነው

 • “በቋንቋችን እንዳንማር ማኅበረ ቅዱሳን በደል አድርሶብናል” የሚለው ክሥ እንዲጣራ ይሻል
 • ቅዱስ ሲኖዶስ፥ አህጉረ ስብከት አጣርተው መፍትሔ እንዲሰጡና ውጤቱን እንዲያቀርቡ አዟል
 • ቤተ ክርስቲያኒቱን “የሰሜን ብቻ የሚያስመስሉ ፀራውያን ሤራ እንዳይኾን፣ “መጣራቱ ይበጃል”
 • ፀራውያኑ፥ ለተማሪዎቹ ያሰቡና ለምእመናኑ የተቆረቆሩ በመምሰል ለመለያየት የሚሠሩ ናቸው
 • ማኅበሩ፥ በቋንቋው እንዳይማሩ ዕንቅፋት አይፈጥርም፤ መከልከል የሚችልበት አሠራርም የለም

*          *         *

በግቢ ጉባኤያት የአፋን ኦሮሞ መርሐ ግብራት

 • በ38 ማእከላቱ፣ የአፋን ኦሮሞ ግቢ ጉባኤያት መርሐ ግብራትን በማቋቋም ኮርሶችን ያስተምራል
 • ኮርሶቹ፥ ለግቢ ጉባኤያት ሥርዓተ ትምህርት በተዘጋጁ የ11 ሞጁሎች ትርጉም የተደገፉ ናቸው
 • በቋንቋው፥ የጽዋና የጸሎት መርሐ ግብራት እንዲካሔዱ፤ መዝሙራት እንዲቀርቡ እያደረገ ነው
 • በየ3 ወሩ ለግቢ ጉባኤያት የምትዘጋጀውን ጉባኤ ቃና መጽሔት፣ ተርጉሞና አሳትሞ ያሰራጫል
 • በምረቃ መጽሔት፥ ትምህርታዊ ጽሑፎችና መልእክቶች፣ በአፋን ኦሮሞ እየተዘጋጁ ይተላለፋሉ

*         *        *

ከመደበኛ አገልግሎት የአፋን ኦሮሞ ሥራዎቹ፡-

 • የጸሎት፣ የታሪክ እና ማጠቀሻዎችን ጨምሮ 20 መጻሕፍትን፣ አዘጋጅቶ አሰራጭቷል
 • የሊቀ ጉባኤ – ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት እና ሌሎች 2 መጻሕፍት ዝግጅት ተጠናቋል
 • 5 የመዝሙር አልበሞችና አንድ ጥራዝ አሰራጭቷል፤ 6ኛውን በመቅረጽ ሥራ ላይ ነው
 • የተለያዩ መልእክታትን የያዙ በራሪ ወረቀቶችን፣ በበዓላትና በየጊዜው እያዘጋጀ ያሰራጫል
 • ጥናቶች ታትመዋል፤ ወርኃዊ ጉባኤ ይካሔዳል፤ የመምህራኑ ሥልጠና 13ኛ ዙር ደርሷል
 • የአብነት ት/ቤቶችን አቋቁሞ ካህናትንና ሰባክያንን እያሠለጠነ ያሰማራል፤ የተዘጉትን አስከፍቷል

*          *         *

በ2007 ዓ.ም. በተቋቋመው፣ “የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት”

 • Dhangaa Lubbuu(ዳንጋ ልቡ) መጽሔት እያዘጋጀ ያሰራጫል
 • የአፋን ኦሮሞ መካነ ድር በመክፈት፣ በማስተማር ላይ ይገኛል
 • በኦቢኤስ ቴሌቭዥን፥ ሳምንታዊ መርሐ ግብር ሲያቀርብ ቆይቷል
 • ዕለታዊ የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቋል
 • መርሐ ግብሩ ለማይደርሳቸው የቴክኖሎጂ አማራጮችን ይጠቀማል

*          *        *

 

 

 

ማኅበሩ በአፋን ኦሮሞ አዘጋጅቶ ካሰራጫቸው 20 መጻሕፍት ጥቂቱ

ምእመናን በማይሰሙት ቋንቋ እንዲማሩ የማትፈቅደው ቤተ ክርስቲያናችን፣ ልዩ ልዩ የሐዋርያዊ ተልእኮ ተግባራትን ከመፈጸም ጎን ለጎን መጽሐፈ ቅዳሴን በአፋን ኦሮሞ አስተርጉማ እያገለገለችበት ትገኛለች፡፡ ከዚኽ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ የተለየ አካሔድ እንደሌለው የገለጸው ማኅበረ ቅዱሳን፤ አቅሙ እስከቻለ ድረስ፣ ለሕዝቡ በየቋንቋው ወንጌልን ለማስተማር ሲተጋ እንደቆየና ወደፊትም ይህንኑ አስፋፍቶና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡

ማኅበሩ፣ በየ15 ቀኑ የሚያሳትመው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ ትላንት ባወጣውና የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔን ባሰፈረበት እትሙ፣ በኦሮሚያ ክልል በሰባት ዞኖች በሚገኙ  ዩኒቨርስቲዎች፣ ትምህርት በቋንቋችን እንዳንማር በደል አድርሶብናል፤” በሚል ከቀረበበት አቤቱታ ጋራ በተያያዘ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ምልአተ ጉባኤው፥ አቤቱታው፣ ዩኒቨርስቲዎቹ ባሉበት አህጉረ ስብከት ተጣርቶ መፍትሔ እንዲሰጠው ያሳሰበ ሲኾን፤ ውጤቱንም ለቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርቡ አዝዟል፡፡ “የጉዳዩን መጣራት ማኅበረ ቅዱሳን የሚፈልገው ነው፤” ያለው ጋዜጣው፤ ይኸውም፣ በማኅበሩ የዕቅበተ እምነት አገልግሎት፣ መሠሪ አካሔዳቸው የከሸፈባቸው ፀራውያን፡- ለቤተ ክርስቲያን የተቆረቆሩ፣ ለምእመናን ሕይወት የተጨነቁ፣ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያሰቡ መስለው፣ ርትዕት ከኾነችው ሃይማኖት ለመለየት የሸረቡት ሤራ እንዳይኾን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጿል፡፡

 

ከማኅበሩ የአፋን ኦሮሞ ስብከት ቪሲዲዎች


በተለያዩ ቋንቋዎች ሐዋርያዊ ተልእኮን ለማስፋፋትና ለማጠናከር የሚወስነው ነገር ቢኖር የሀብት ውስንነት ብቻ እንደኾነ ጠቅሶ፤ ኹኔታዎች በተመቻቹበትና ፍላጎቱ በታየበት ኹሉ፣ በዐማርኛ የጀመረውን አገልግሎቱን በሌሎችም ልሳናት እየሰጠ እንደሚገኝ ዘግቧል፡፡ በዚኽ መሠረት፣ በመደበኛ አገልግሎቱ በግቢ ጉባኤያት እንዲኹም ከሦስት ዓመታት በፊት በጀመረው የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ያከናወናቸውንና እያከናወናቸው ያሉትን ተግባራት ዘርዝሯል፡፡

የማኅበሩ የአፋን ኦሮሞ ቪሲዲ መዝሙር


ይህም ማኅበሩ፣ ተማሪዎቹንም ኾነ ምእመናንን በቋንቋው ሲያስተምር እንደቆየ በተጨባጭ እንደሚያሳይ አስረድቷል፡፡ ማንም በቋንቋው እንዳይማር መከልከል የሚችልበት አሠራርም እንደሌለ በማብራሪያው ያመለከተው ማኅበሩ፤ ወደፊትም አቅሙ እስከቻለ ድረስ ለሕዝቡ በየቋንቋው ወንጌልን የማስተማሩን ትጋት አስፋፍቶና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ የማብራሪያው ሙሉ ቃል እንደሚቀከተለው ቀርቧል፡፡


(ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፤ ፳፬ኛ ዓመት ቁ. ፲፯፤ ከግንቦት ፲፮ – ፴ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)

ማሳሰቢያ፡- የተከበራችኹ አንባብያን፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዐት እምነትና ክርስቲያናዊ ትውፊት፣ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ፣ ነገረ ማርያምንና ነገረ ቅዱሳንን በተመለከተ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው ሓላፊነት መሠረት ሲያስተምር፤ ላላወቁት ሲያሳውቅ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡

ማኅበሩ አገልግሎቱን ሲጀምር፣ በአማርኛ ቋንቋ፥ በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በበራሪ ወረቀት፣ በመጻሕፍት፣ በካሴት፣ በምስል ወድምፅ የሚችለውን ኹሉ ሲያከናውን ቢቆይም፤ በሰው ኃይል ሲጠናከርና የምእመናን ፍላጎት ሲጨምር ደግሞ፥ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ፣ በወላይትኛ፣ በእንግሊዝኛ በማስተማር ላይ መኾኑ ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ተግባሩ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ባስተላለፈው የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ውሳኔው፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ሰባት ዞኖች ሥር በተቋቋሙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች በቋንቋቸው መንፈሳዊ ትምህርት እንዳይማሩ ማኅበረ ቅዱሳን በደል ያደረሰባቸው መኾኑን የሚገልጥና ጉዳዩ እንዲጣራ የሚያሳስብ ውሳኔ አሳልፏል፤ የጉዳዩን መጣራት ማኅበረ ቅዱሳን የሚፈልገው ነው፡፡

መንፈሳዊ ፊልም በአፋን ኦሮሞ

ወንጌለ መንግሥትን በመላው ዓለም እንዲያዳርስ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት የሰጠችው ማኅበር፣ በአቅም ማነስ ምክንያት ጠያቂዎቹ ያላቸውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ አሟልቻለኹ ብሎ ለመናገር ባይደፍርም፣ በቋንቋቸው እንዳይማሩ ግን አላደረገም፤ ወደፊትም አያደርግም፡፡

ቋንቋን እንደ መነሻ አድርገውና ጥንታዊት ታሪካዊትና ሐዋርያት የኾነችውን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን፣ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ነዋሪዎች ብቻ አስመስለው የሚያቀርቡ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንን፣ ማኅበረ ቅዱሳን ዓላማቸው እንዳይሳካ በማድረጉ፥ ለቤተ ክርስቲያን የተቆረቆሩ፣ ለምእመናን ሕይወት የተጨነቁ፣ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያሰቡ መስለው፣ ርትዕት ከኾነችው ሃይማኖት ለመለየት የሸረቡት ሤራ እንዳይኾን መጣራቱ መልካም ነው፡፡ ከዚኽ ውጭ ማኅበረ ቅዱሳን፣ ወጣቶቹ፣ በቋንቋቸው፣ በሥርዐተ ትምህርቱ መሠረት ትምህርተ ሃይማኖትን እንዲማሩ ሲያደርግ ለመቆየቱ ተጨባጭ ሥራዎቹ ምስክሮች ናቸው፡፡

ከዚኽ ቀደም በአፋን ኦሮሞ ከተሠሩ ሥራዎች ለማሳያ ያኽል ለመጥቀስ፡-
 • አዲስ መጻሕፍትን በቋንቋው አዘጋጅቶ አሠራጭቷል፤
 • በግእዝ እና በአማርኛ ተጽፈው የሚገኙትን መጻሕፍት ወደ አፋን ኦሮሞ ተርጉሟል፤
 • የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ውዳሴ አምላክ እና ሰይፈ ሥላሴ በኦሮምኛ ተርጉሞ አሰራጭቷል፤
 • በሦስት ወር አንድ ጊዜ፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ታስባ የምትዘጋጀውን ጉባኤ ቃና መጽሔት ተርጉሞና አሳትሞ አሰራጭቷል፤
 • Dhangaa Lubbuu(ዳንጋ ልቡ) መጽሔትን ለኹሉም ክርስቲያን በሚመጥን ዓምድ በየሦስት ወር አዘጋጅቶ እያሰራጨ ይገኛል፤
 • አምስት የመዝሙር አልበሞችን በአፋን ኦሮሞ አዘጋጅቶ አሰራጭቷል፤
 • ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ጥራዝ አዘጋጅቶ አሳትሟል፤
 • ልዩ ልዩ ቪሲዲ ስብከቶችንና መዝሙሮችን በቋንቋው አዘጋጅቶ ለምእመናን አሰራጭቷል፤
 • በክልሉ አህጉረ ስብከት ስላሉት አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎትና ታሪካዊነት የተመለከቱ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን አዘጋጅቶ እንዲታተሙ አድርጓል፤
 • በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ለሚያስተምሩ መምህራን የክረምት ሥልጠና በዐሥራ ሦስት ዙር፣ በዚኽም በዓመት ከዘጠና በላይ አገልጋዮችን ለማሠልጠን ዝግጅቱን አጠናቅቋል፤
 • በአፋን ኦሮሞ የሚተላለፍ ሳምንታዊ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ሲያቀርብ የቆየ ሲኾን፣ ይህንኑም አጠናክሮ የሚቀጥል ይኾናል፡፡
 • በአፋን ኦሮሞ መካነ ድር በመክፈት በማስተማር ላይ ይገኛል፤
 • በአፋን ኦሮሞ ትምህርት የሚሰጥበት የአፋን ኦሮሞ ወርኃዊ ጉባኤ በማካሔድ ላይ ይገኛል፤
 • በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙና ግቢ ጉባኤያት ካላቸው 47 ማእከላት በ38ቱ፣ የአፋን ኦሮሞ መርሐ ግብር እንዲኖርና ተማሪዎች በቋንቋቸው ኮርስ እንዲማሩ፣ የጽዋ እና ጸሎት መርሐ ግብራት እንዲያካሔዱ፣ መዝሙራትን እንዲያጠኑና እንዲያቀርቡ ተደርጓል፤ በመደረግም ላይ ነው፤
 • በተጠኑ የክልሉ ቦታዎች፣ አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመመሥረት፣ አፋን ኦሮሞ የሚችሉ ዲያቆናትንና ቀሳውስትን እንዲኹም ሰባክያንን አስተምሮ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በማሠማራት ላይ ነው፤ ለዚኽም በምዕራብ ወለጋ የሚገኘውን የቂልጡ ካራ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና በጅማ ሀገረ ስብከት ሥር ያለውን የአበልቲ ኪዳነ ምሕረት ገዳማት የአብነት ትምህርት ቤቶችን በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል፤
 • በግቢ ጉባኤያት የምረቃ መጽሔት ላይ የተለያዩ ትምህርታዊ ጽሑፎችንና መልእክቶችን በአፋን ኦሮሞ በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፤
 • በክልሉ ያሉ ገዳማት እና የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በመተግበር፣ መምህራንና ደቀ መዛሙርትን በመደጎም፣ ቋንቋውን የሚችሉ ዲያቆናትና ካህናት እንዲፈሩ በመደረጉ በርካታ የክልሉ ምእመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፤ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፤ (የባሌ፣ የምሥራቅ ሐረርጌ እና የነገሌ ቦረና አህጉረ ስብከት አብነት ትምህርት ቤቶችን መጥቀስ ይቻላል)፡፡

በአጠቃላይ ማኅበረ ቅዱሳን፣ በክልል ኦሮምያ ለሚገኙ ምእመናን በተለየ ትኩረት የበለጠ አገልግሎት ለመስጠት ካለው ቁርጠኝነት የተነሣ፣ የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት የሚል በይፋ አቋቁሞና በቢሮ ደረጃ ከፍቶ በተደራጀ መልኩ አገልግሎቱን በመፈጸም ላይ እንደኾነ፣ በዚኹ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል፡፡

ወደፊት ለመሥራት የታቀዱ 
 • ዕለታዊ አፋን ኦሮሞ የቴሌቭዥን መርሐ ግብር መጀመር፤
 • መንፈሳዊ የአፋን ኦሮሞ ራድዮ መርሐ ግብር መጀመር፤
 • ወርኃዊ የራድዮ መጽሔት ማዘጋጀት፤
 • ዕቅበተ እምነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን በአፋን ኦሮሞ ማዘጋጀት፤
 • ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ወደ አፋን ኦሮሞ የመተርጎሙን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል፣
 • የሕፃናት መጻሕፍት እና መንፈሳዊ ፊልሞችን በአፋን ኦሮሞ ማዘጋጀት፤
 • ወጣቶች፣ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ የሚያግዙ የማስተማሪያ አፕሊኬሽኖችን በቋንቋው ማዘጋጀት፤
 • የራዲዮና ቴሌቭዥን መርሐ ግብሮችን መከታተል ለማይችሉ የገጠር ምእመናን፣ ባሉበት፣ ቃለ እግዚአብሔርን ለማስተማር የሚያስችል ዕቅድ በማውጣት በዘመኑ ቴክኖሎጂ በቀላሉ እንዲደርሳቸው ማድረግ የሚሉትና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ቬነስያ መንፈሳዊ ልቦለድ ትረካ በአፋን ኦሮሞ

ማኅበረ ቅዱሳን ይህንና እንዲኽ ይሠራል፡፡ ማንም በቋንቋው እንዳይማር ዕንቅፋት አይፈጥርም፤ መከልከል የሚችልበት አሠራርም የለም፡፡ ወጣቶች በማይሰሙት ቋንቋ እንዲማሩ የማትፈቅደው ቤተ ክርስቲያናችን፣ ልዩ ልዩ ተግባራትን ከመፈጸም ጎን ለጎን መጽሐፈ ቅዳሴን በአፋን ኦሮሞ አስተርጉማ እያገለገለችበት ትገኛለች፤ ማኅበረ ቅዱሳንም ከቤተ ክርስቲያን የተለየ ዓላማ የለውም፡፡ አቅሙ እስከ ቻለ ድረስ ወንጌልን ላልተማሩ ለማስተማር ሲተጋ ቆይቷል፤ ወደፊትም ይህንኑ አስፋፍቶና አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ 

ማኅበረ ቅዱሳን: ከአራት ሺሕ በላይ ልኡካን የሚሳተፉበት ”የግቢ ጉባኤያት ሳምንት” ያካሒዳል

 • የግቢ ጉባኤያት እንቅስቃሴ፣ ለሀገር እና ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ፋይዳ ይዳስሳል
 • አገልግሎቱን በሚደግፉ፥ የገቢ ማሰባሰብ፤ የአጋርና ተባባሪ አካላት ፖሊሲ ላይ ይወያያል
 • የግቢ ጉባኤያት ምሩቃን ከ500ሺሕ በላይ ደርሰዋል፤ 250ሺሕ ያኽሉን እያስተማረ ነው

 *                      *                  *

(ሰንደቅ፤ ረቡዕ፣ ግንቦት 23 ቀን 2009 ዓ.ም.)


ኑ ነገን የሚረከብ ትውልድ ለማፍራት በጋራ እንሥራ
በሚል መሪ ቃል፣ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን የሚዳስስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤያትን ከአጋርና ባለድርሻ አካላት ጋራ በማስተዋወቅ አገልግሎታቸውን ለማጠናከር ያለመ፣“የግቢ ጉባኤያት ሳምንት” መርሐ ግብር፣ ከግንቦት 25 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በዋና ማዕከል ጽ/ቤቱ እንደሚያካሒድ ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ፡፡

በመንግሥትና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች የኾኑ ተማሪዎች የታቀፉባቸው ግቢ ጉባኤያቱ፦ ዘርፈ ብዙ ችግሮቻቸውን ተቋቁመው አገልግሎታቸውን ወጥነት ባለው መልኩ እንዲፈጽሙ የማድረግ ዐቢይ ዓላማ ያለው መርሐ ግብሩ፣ ዐውደ ጥናትንና ዐውደ ርእይን ያካተተ እንደኾነ ተገልጿል፡፡

በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ነባራዊ ሁኔታዎችና በአገልግሎት ውጤታቸው ላይ የሚያተኩረው ዐውደ ጥናቱ፥ የእኅት አብያተ ክርስቲያናትን ልምድ ጨምሮ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ሃይማኖታዊና ሳይንሳዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ ሲኾን፤ ግቢ ጉባኤያት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ያላቸውን ፋይዳ በተመለከተም በስፋት ይመክራል፤ ተብሏል፡፡


 • የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ምንነትና አኹን ያሉበት ነባራዊ ኹኔታዎች፤
 • የግቢ ጉባኤያት አገልግሎትን ለማጠናከር የምሩቃን ሚና፤
 • በግቢ ጉባኤያት ላይ መሥራት ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር ያለው ፋይዳ እና የእኛ ድርሻ፤
 • ሃይማኖት እና ሳይንስ፤
 • ኦርቶዶክሳዊ ወጣት እና የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት፤
 • የዐውደ ርእይ መርሐ ግብር፤

አገልግሎታቸውን በማጠናከርና ተማሪዎችን ባለተልእኮ በማድረግ ረገድ፥ የቀድሞ ምሩቃን፣ የተማሪዎች ወላጆች፣ የሰንበት ት/ቤቶች፣ መንፈሳውያን ማኅበራትና ድጋፍ አድራጊዎች/ተባባሪ አካላት/ የሚኖራቸው ሚና፣ ከማኅበሩ፥ የስድስት ዓመት የግቢ ጉባኤያት ስልታዊ ዕቅድ እንዲኹም ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ፖሊሲ አኳያ ውይይት እንደሚካሔድበት ተጠቁሟል፡፡

በመጪው ዓርብ፣ ግንቦት 25 ቀን ከሰዓት በኋላ የሚከፈተውና ለተከታታይ ዐሥር ቀናት የሚቆየው ዐውደ ርእዩ፣ የመርሐ ግብሩ አካል ሲኾን፤ ጎን ለጎንም የገቢ ማሰባሰብ ሥራዎች እንደሚኖሩ ከወጣው ፕሮግራም ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከአራት ሺሕ በላይ ልኡካን የሚሳተፉበት ይኸው የዐሥር ቀናት “የግቢ ጉባኤያት ሳምንት” መርሐ ግብር፣ ለኹለተኛ ዙር የተዘጋጀ ሲኾን፤ ከ500 በላይ የተማሪዎች ወላጆች፤ ከ1ሺሕ500 በላይ የቀድሞ ምሩቃን እንዲኹም፣ በመቶዎች ከሚቆጠሩ የአዲስ አበባና የክልል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተውጣጡና ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ከ2ሺሕ በላይ ተማሪዎች እንደሚሳተፉበት የዝግጅት ዐቢይ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን በማቀፍ አገልግሎቱን በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና ሲያከናውን በቆየባቸው ያለፉት ሩብ ምእት ዓመታት፣ ያስመረቃቸው ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች አጠቃላይ ቁጥር ከ500ሺሕ በላይ ደርሰዋል፤ በአኹኑ ወቅትም፣ በ407 ግቢ ጉባኤያት ከ250ሺሕ በላይ ለሚኾኑ ተማሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓተ እምነት ጨምሮ፣ በኹለንተናዊ መልኩ ብቁና ግብረ ገባዊ የኾኑ አገልጋዮችንና ዜጎችን ለማፍራት ስልታዊ ዕቅድ ቀርጾ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የቅድስት አርሴማን ቤተ ክርስቲያን ያፈረሱ የወረዳ ሓላፊዎች በእስራት ተቀጡ፤ ቅጣታቸውን ሳይፈጽሙ በማግሥቱ ተፈቱ!

 • መቃኞዋ እንድትፈርስ በተወሰነው ላይ የቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደረገ
 • የደብሩ አስተዳደር፣ ለሰበር ሰሚ ፍ/ቤት ይግባኝ እንደሚጠይቅ ተጠቆመ
 • ኪዳኑ እና ቅዳሴው በድንኳን እየተከናወነ፤ ጉባኤውም እንደቀጠለ ነው

*                        *                     *

(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ ግንቦት ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)


የፍርድ ቤት የእግድ ትእዛዝ በመጣስ፣ በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ፣ ልዩ ስሙ የካ አባዶ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የምትገኘውን የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን ያፈረሱ፣ የወረዳ 12 አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ሓላፊ፣ በ15 ቀን ቀላል እስራት እንዲቀጡ የከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍ/ቤት ወሰነ፤ ቤተ ክርስቲያንዋ እንድትፈርስ የሥር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ግን፣ “ይግባኝ አያስቀርብም” ብሏል፡፡

በይግባኝ ባይ፥ የደብረ ልዕልና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እና በመልስ ሰጪ፥ የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽ/ቤት መካከል ያለውን የይግባኝ ቅሬታ ሲመረምር መቆየቱን ከትላንት በስቲያው ውሳኔው ያስታወቀው ፍ/ቤቱ፤ መልስ ሰጪዎቹ፥ የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደመላሽ ጎሳ እና የደንብ ማስከበር ጽ/ቤቱ ሓላፊ አቶ ዳዊት ሙሉጌታ፤ የፍ/ቤትን የእግድ ትእዛዝ እያዩ፣ ክርክር የቀረበባትን መቃኞ ቤተ ክርስቲያን ማፍረሳቸው፣ የፍ/ቤትን ሥራ ማወክ በመኾኑ ጥፋተኛ ኾነው እንደተገኙ ገልጿል፡፡

በይግባኝ ባይ በኩል የቀረቡ አራት ምስክሮች፣ የደብሩ አስተዳዳሪ ሊቀ ካህናት በየነ አሰፋ“የፍ/ቤት የእግድ ትእዛዝ አለ፤ በሕግ አምላክ አታፍርሱ” እያሉ በስም ለተጠቀሱት ኹለት ሓላፊዎች እንዳሳዩዋቸው፤ እነርሱ ግን ለማቆም ፈቃደኛ እንዳልነበሩና በግብረ ኃይል እንዳስፈረሱ፣ በበቂ ኹኔታ እንዳስረዱ ፍ/ቤቱ በውሳኔው ጠቅሷል፡፡

በመልስ ሰጪዎች በኩል የቀረቡት ኹለት ምስክሮች፣ አፍራሽ ግብረ ኃይል ኾነው የማፍረስ ተግባር እንዳከናወኑና የምስክርነት ቃላቸውም እርስ በርሱ የሚጋጭ ኾኖ በመገኘቱ፣ “ገለልተኛ እና ተኣማኒነት ያለው ኾኖ አላገኘነውም፤” ብሏል – ችሎቱ፡፡

ስለኾነም መልስ ሰጪዎቹ፣ የቀረበባቸውን አቤቱታ እና ማስረጃ ለመከላከል ባለመቻላቸው፥ የፍ/ቤትን ሥራ በማወክ ጥፋተኛ ኾነው ተገኝተዋል፡፡ አስፈጻሚ አካላት ኾነው ሳለ የተጣለባቸውን ሓላፊነት ወደ ጎን በመተው፣ የፍ/ቤትን የእግድ ትእዛዝ በመጣሳቸው፣ ሊያስተምር የሚችል ቅጣት እንዲቀጡ፣ ይግባኝ ባይ በቅጣት አስተያየቱ ጠይቋል፡፡

የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ “የጣስነው ሕግ የለም፤ የወሰድነው ርምጃም ተቋሙን ወክለን ነው፤” በሚል የቅጣት ማቅለያ ቢያቀርቡም፣ ፍ/ቤቱ፥ “ጥፋተኞችንም ኾነ ሌሎች ግለሰቦችን ያስተምራል፤” በሚል በወንጀል ሕግ 449 መሠረት፣ አቶ ደመላሽ ጎሳ እና አቶ ዳዊት ሙሉጌታ፣ ውሳኔው ከተሰጠበት ከኃሙስ፣ ግንቦት 17 ቀን ጀምሮ በ15 ቀን ቀላል እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፤ እስራቱንም፣ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲያስፈጽም አዝዟል፡፡


በትእዛዙ መሠረት በዕለቱ፣ የልደታ ፖሊስ መምሪያ፣ ኹለቱን ሓላፊዎች አቆይቶ፣ ትላንት ዓርብ ለማረሚያ ቤት ማስረከብ ቢኖርበትም፣ የተወሰነባውን የ15 ቀናት የቅጣት ጊዜ ሳይፈጸሙ በማግሥቱ 
ማለትም ትላንት እንደተለቀቁ ነው፣ ዘግይቶ የተሰማው፡፡

በሌላ በኩል፣ የሥር ፍ/ቤት፣ “የቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታና ግንባታ ሕገ ወጥ ነው፤” በሚል መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. የሰጠው ውሳኔ፣ የሚነቀፍበት ምክንያት እንዳላገኘበት ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤቱ ጠቅሶ፤ “መልስ ሰጪን መጥራት ሳያስፈልግ፣ ይግባኙ አያስቀርብም” በማለት መዝገቡን መዝጋቱን በተጨማሪ ትእዛዙ አስታውቋል፡፡ የደብሩ አስተዳደር፣ በጉዳዩ ለሰበር ሰሚ ይግባኝ እንደሚጠይቅ ተጠቁሟል፡፡

ዛሬም በሸራ ድንኳን በቀጠለው የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት፣ ጸሎተ ቅዳሴ ይፈጸማል፤ ስብሐተ እግዚአብሔሩና ጸሎተ ኪዳኑ ይደርሳል፤ የአዘቦቱ የሠርክ ጉባኤም እየተደረገ ሲኾን፣ ከግንቦት 4 እስከ 6 ቀን፣ ልዩ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ እንደተካሔደ ተገልጿል፡፡

መናፍቁ አሰግድ ሣህሉ የተወገዘበት የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጠናቀቀ፤ ወጣቱ፥ ከሃይማኖት በራዥ ኃይሎች እንዲጠነቀቅ አሳሰበ

 • ባለዐሥራ አምስት ነጥቦች መግለጫ አወጣ

ቃለ ውግዘቱ የሰፈረበት የመግለጫው አንቀጽ 2፡-

 • ከቤተ ክርስቲያናችን እምነት እና ሥርዓት ውጭ በመደራጀት የኑፋቄ ትምህርት ሲያካሒድ የነበረው አሰግድ ሣህሉ የተባለ ግለሰብለበርካታ ዓመታት የኑፋቄ ትምህርት ሲያሰራጭ መኖሩ በመረጃ የተደረሰበትና የተረጋገጠ በመኾኑ፣ ከአኹን በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እንዳያስተምር፤ ምእመናንም እንዳይከተሉት፣ ምልአተ ጉባኤው ከግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ቃለ ውግዘት አስተላልፏል፡፡
 • ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ውጭ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳያገኙ፣ በተመሳሳይ ኹኔታ አዳራሽ ተከራይተው፣ በቤተ ክርስቲያናችን ስም፥ ወንጌል እናስተምራለን፤ ዝማሬ እናሰማለን፤ የሚሉ ሕገ ወጦች፣ ከእንዲኽ ዓይነት ድርጊታቸው እንዲታረሙ፤ ምእመናንንም በተለይ ወጣቱ ትውልድ፣ እንዲኽ ዓይነት ሕገ ወጦችን ከመከተልና ሃይማኖታችኹን ከሚበርዙ ኃይሎች እንድትጠበቁ ቅዱስ ሲኖዶሱ አበክሮ ያሳስባል፡፡

ሌሎች የመግለጫው ነጥቦች፡-

 • ለ16ቱ ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ሐምሌ 9 ቀን ሢመተ ጵጵስና ይፈጸማል፤
 • በጥቅምቱ ጉባኤ፣ ለውጭ አህጉረ ስብከት ተጨማሪ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንደሚኖር ጠቆመ፤
 • ሕገ ወጥ አጥማቂዎችንና ሰባክያንን የመቆጣጠሩ ሥራ ይጠናከራል፤
 • የስንክሳሩ ሚያዝያ 10 ወበዛቲ ከእንግዲህ እንዳይነበብ፤ የፍትሕ መንፈሳዊው “ኢይሢሙ” በቀጣይ ኅትመቶች እንዳይገባ አዘዘ፤ “ግብጻውያን አባቶች በሥርዋጽ ያስገቡት ሕገ ወጥ ጽሑፍ ነው፤ የአገራችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር የሚነካ ኾኖ ተገኝቷል፤”
 • የአስጎብኚ እና ሌሎች ማኅበራት ማደራጃ ደንብ ይወጣል፤
 • ለብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ(ኢኦተቤ-ቴቪ) የ2010 ዓ.ም.፣ 12 ሚ. ብር በጀት ፈቀደ፤
 • የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ የርዳታ ለጋሾችን በማነጋገርና በማስተባበር የድርቅ ርዳታውን ያጠናክራል፡፡

******************

የ2009 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔዎች ሙሉ ቃል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ፣ በዓመት ኹለት ጊዜያት እንዲኾን በፍትሕ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ የዘንድሮውን መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ፣ ከበዓሉ ዋዜማ፣ ከግንቦት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ ለ፲፬ ቀናት ያህል ሲወያይ ሰንብቷል፡፡

በምልአተ ጉባኤው የተደረገውን የመክፈቻ ንግግር በተመለከተ፡-

 • በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ዘርፍ ዙሪያ እየተሠሩ ያሉትን ማኅበራውያን ተግባራት የዳሰሰ፤
 • በአገራችን አንዳንድ አካባቢ፣ በዝናም እጥረት ምክንያት ድርቅ ባስከተለው ችግር ለተጎዱ ወገኖች ሊደረግ የሚገባውን ሰብአዊ አገልግሎት ያገናዘበ፤
 • በአገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን ዅለንተናዊ ዕድገት የሚበጀውን በማመቻቸት በዅሉም አቅጣጫ ያለው ኅብረተሰብ የሥራ ተነሣሽነቱን በበለጠ አጐልብቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል መልእክት መኾኑን ምልአተ ጉባኤው ተመልክቶ ለተላለፈው አጠቃላይ መመሪያ ትኵረት ሰጥቶ በቀረበው አጀንዳ ከተወያየ በኋላ በርከት ያሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል፤ ከውሳኔዎቹም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፤

፩. ከፍ ብሎ እንደ ተገለጸው ዅሉ፣ በአኹኑ ጊዜ በአገራችን በአንዳንድ አካባቢ በተከሠተው ድርቅ ለረኃብ የተጋለጡ ወገኖቻችንን ለመታደግ መንግሥት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት በመገንዘብ፣ የቤተ ክርስቲያናችን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሓላፊነቱን ወስዶ ከርዳታ ሰጪዎች ጋራ በመነጋገርና በማስተባበር የሚገኘውን ርዳታ ድርቁ የተከሠተባቸው የክልል መሪዎች በሚሰጡት አቅጣጫ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፪. ከቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓት ውጭ በመደራጀት የኑፋቄ ትምህርት ሲያካሒድ የበረው አሰግድ ሣህሉ የተባለ ግለሰብ ለበርካታ ዓመታት የኑፋቄ ትምህርት ሲያሠራጭ መኖሩ በመረጃ የተደረሰበትና የተረጋገጠበት በመኾኑ፤ ከአኹን በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እንዳያስተምር፤ ምእመናንም እንዳይከተሉት፤ ምልአተ ጉባኤው ከግንቦት ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ ቃለ ውግዘት አስተላልፏል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ውጭ፣ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳያገኙ በተመሳሳይ ኹኔታ አዳራሽ ተከራይተው በቤተ ክርስቲያናችን ስም፣ ‹‹ወንጌል እናስተምራለን፤ ዝማሬ እናሰማለን›› የሚሉ ሕገ ወጦች፣ ከእንዲህ ዓይነት ድርጊታቸው እንዲታረሙ፤ ምእመናንንም በተለይ ወጣቱ ትውልድ እንዲህ ዓይነት ሕገ ወጦችን ከመከተልና ሃይማኖታችሁን ከሚበርዙ ኃይሎች እንድትጠበቁ ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡

፫. የቤተ ክርስቱያኒቱ መገናኛ ብዙኃን ጉዳይን በተመለከተ የሚዲያ ድርጅቱ በሰው ኃይል እንዲጠናከር፤ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶችም ጥራት እንዲኖራቸው ማድረግ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተነጋግሮ፣ ለ፳፻፲ በጀት ዓመት ብር 12,000,000.00 (ዐሥራ ኹለት ሚሊዮን ብር) ተፈቅዶለት በበጀት ተጠናክሮ ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቷል፡፡

፬. በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ዴር ሡልጣን ገዳም ችግር ጉዳይ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ ችግሩን አስመልክቶ መፍትሔ ማግኘት እንዲቻል ለኢፊዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ለእስራኤል ኤምባሲ እና በእስራኤል ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ተወስኗል፡፡

፭. ሚያዝያ ፲ ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር እና በፍትሕ መንፈሳዊ መጽሐፍ ላይ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት ጳጳሳትን አይሹሙ›› የሚለው በ፯ተኛው መቶ ዓመት ግብጻውያን አባቶች በሥርዋጽ ያስገቡት ሕገ ወጥ ጽሑፍ ስለኾነ፣ ምልአተ ጉባኤው ተነጋግሮ ጽሑፉ የአገራችንና የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚነካ ኾኖ በመገኘቱ፣ ከአኹን በኋላ ጽሑፉ እንዳይነበብ፤ ከመጻሕፍቱም ውስጥ እንዲወጣ ወደፊትም በሚታተሙ መጻሕፍት እንዳይገባ ተወስኗል፡፡

፮. ሥርዓተ ምንኵስና እና ሥልጣነ ክህነት አሰጣጥን አስመልክቶ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት የተወሰኑ ውሳኔዎች በአብዛኛው አፈጻጸም ላይ ችግሮች እንዳሉ ስለሚታይ ወደፊት የሚወሰነው ተጠብቆ እንዲሠራበት ጉባኤው ተስማምቷል፡፡

፯. ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና አጥማቂዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አገልግሎት እንዳይሰጡ የተወሰነ ቢኾንም፣ ውሳኔው መከበር ስላልቻለ፤ ችግሮችም በስፋት የሚታዩ ስለኾነ፤ አኹንም በውሳኔው መሠረት የቁጥጥሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተስማምቷል፡፡

፰. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም፣ በአዲስ አበባም ኾነ በየአህጉረ ስብከቱ በማኅበር ተደራጅተው ገዳማትን በማስጐብኘትም ኾነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በልዩ ልዩ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትን መቆጣጠር የሚቻልበት የማኅበራት ማደራጃ ደንብ እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፱. የቤተ ክርስቲያኒቱ ዅለንተናዊው ችግር በባለሞያ ተጠንቶ እንዲቀርብ ቀደም ሲል በተወሰነው መሠረት፣ ጥናቱ ተጠናቆ ከቀረበ በኋላ ጉባኤው ተመልክቶ፣ የሕግ ባለሞያዎችና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ባሉበት ተመርምሮና ተስተካክሎ ለጥቅምቱ ፳፻፲ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡

፲. የስብከተ ወንጌል መስፋፋት፤ የሰንበት ት/ቤት እና የመንፈሳውያን ኮሌጆች መጠናከር፤ የአብነት ት/ቤቶች መደራጀት እና በበጀት እንዲደገፉ ማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓይነተኛ ተግባር መኾኑን ምልአተ ጉባኤው ተነጋግሮ፤ በስብከተ ወንጌል ትምህርት አሰጣጥ እና በመንፈሳውያን ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት አያያዝ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡

፲፩. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የኾነውን ሀብትና ቅርስ በባለቤትነት መጠበቅና ማስጠበቅ እንዲቻል ተዘጋጅቶ የቀረበውን ጥናት ቅዱስ ሲኖዶስ ካዳመጠና ከተወያየበት በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በቅድሚያ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲቀርብ ወስኗል፡፡

፲፪. ብፁዓን አበው በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ዕጩዎች ቆሞሳት ምርጫን በተመለከተ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ ቆሞሳትን በማወዳደር ፲፮ ቆሞሳት ለኤጲስ ቆጶስነት ተመርጠዋል፤ በዓለ ሢመታቸውም ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም እንዲፈጸም ተወስኗል፡፡

፲፫. ኤጲስ ቆጶሳት የሌሉባቸውን የውጭ አህጉረ ስብከት በተመለከተም፣ በጥቅምቱ ፳፻፲ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እየታየና እየተጠና ብፁዓን አበው እንዲመደቡባቸው ለማድረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡

፲፬. በኦሮምያ ክልል በሰባት ዞኖች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች፣ ‹‹መንፈሳዊውን ትምህርት በቋንቋችን እንዳንማር ማኅበረ ቅዱሳን በደል አድርሶብናል፤›› በሚል ባቀረቡት አቤቱታ፣ ዩንቨርሲቲዎቹ ያሉበት አህጉረ ስብከት ጉዳዩን ግራና ቀኝ አጣርተውና ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጡና ውጤቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚኽ በላይ በተገለጹት የውሳኔ ነጥቦችና በሌሎችም ዐበይት ጉዳዮች ላይ ለ፲፬ ቀናት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤
አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኤጲስ ቆጶስነት ተሿሚው ላይ የቀረበው አቤቱታ፥ “ለቤተ ክርስቲያን ክብርና የሕዝቡን አእምሮ ነጻ ለማድረግ ሲባል መጣራት አለበት”/ምልአተ ጉባኤው/

 • ፓትርያርኩ፥ሌላ ማስረጃ ካለ ይምጣ እንጅ ወደ ኋላ የሚመለስ ነገር የለም፤” ብለዋል
 • የአካሔድ ችግሩ፥ “አጣርቶ መምረጥ ወይስ መርጦ ማጣራት?!” የሚል ትችት ተሰንዝሮበታል
 • በሌሎችም ላይ ከበዓለ ሢመቱ በፊት ኹነኛ ነገር ከተገኘ፣ ከመመርመር ውጭ አማራጭ የለም
 • “ይገባዋል” ብለው ካጨበጨቡ በኋላ ተቃውሞ ቢነሣ፣ ያስታርቃሉ እንጅ ተቀባይነት የለውም

*                     *                 *


ዐዲስ ኤጲስ ቆጶሳት የሚሾሙት፣ አስፈላጊነቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሲታመንበትና ሲወሰን ነው፡፡ ለኤጲስ ቆጶስነት ብቁ የኾኑት ዕጩ ቆሞሳትና መነኮሳት ተገምግመውና ተመዝነው የሚቀርቡት
፣ ምልአተ ጉባኤው በሚያቋቁመው አስመራጭ ኮሚቴ ቢኾንም፤ ያገለገሉበትና የሚሾሙበት ሀገር ካህናትና ምእመናን ምርጫና ምስክርነት በመመዘኛነት ሊካተት እንደሚገባውበቀኖናውም በዕጩዎች መስፈርት ደንቡም ተደንግጓል፡፡

ካህናትና ሕዝቡ እንዲሾምላቸው፣ ኤጲስ ቆጶስ የሚኾነውን ቆሞስ መርጠው እንደሚያቀርቡ፣ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ረስጠብ 52 በግልጽ ሰፍሯል፡፡ ስለ ተመራጩ፥ ደግነትና ትሩፋት፤ ንጽሕና እና ከነውር ስለ መራቁ፣ በተደጋጋሚ እንደሚጠየቁና እነርሱም፥ “የሚባለው ነው” ብለው ሦስት ጊዜ መላልሰው እንደሚያረጋግጡ፤ በሦስተኛውም እጃቸውን አንሥተው፣ “ይገባዋል” እያሉ እንደሚያጨበጭቡ፣ ወይም አመልጥነው “አማን በአማን” እያሉ እንደሚያሸበሽቡ ተገልጿል፤ ካጨበጨቡ በኋላ ግን፣ ተቃውሞ ቢነሣ ያስታርቃሉ እንጅ ተቀባይነት እንደሌለው፣ አንቀጹ ያመለክታል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ክፍት በኾኑ መንበረ ጵጵስናዎችና አስተዳደራዊ መዋቅር በተዘረጋላቸው ዐዲስ አህጉረ ስብከት፣ 16 ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ምርጫ አካሒዷል፡፡ ከተሿሚዎቹ መካከል በተለይ ኹለቱ፣ ከምርጫው አስቀድሞ፣ ከፍተኛ ጥያቄና ተቃውሞ ተነሥቶባቸው የነበረ ቢኾንም፤ አንዱ፥ በዕጣ ሌላው ደግሞ፣ ድምፅ ሳይሰጥባቸው ያለተወዳዳሪ በብቸኛነት ተመርጠዋል፡፡ ኾኖም፣ ጸሎተ ሢመቱ ተፈጽሞ ካህናቱና ምእመናኑ “ይደልዎ፤ ይደልዎ” ከማለታቸው በፊት፣ የኤጲስ ቆጶስ ሢመተ ክህነት ሥርዓቱ እንደሚለው፣ ጥያቄና ተቃውሞ ማንሣቱ፣ የሚጠበቅና ተቀባይነት ያለው ነው፡፡

ከግንቦት 2 ቀን ጀምሮ ሲካሔድ የቆየው የ፳፻፱ ዓ.ም. ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ፣ ዛሬ ሰኞ፣ ግንቦት 14 ቀን ረፋድ፣ ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ከመጠናቀቁ አስቀድሞ፣ ሊደመጡ የሚገባቸው ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች እንዳሉ፥ በማኅበራዊ ሚዲያው የሚተላለፉ መልእክቶች፤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለብፁዓን አባቶች በጽሑፍና በስልክ የሚጎርፉ አቤቱታዎችና ምሬቶች ይጠቁማሉ፡፡ ምልአተ ጉባኤው፣ ምርጫውን ባካሔደበት ባለፈው ኃሙስ የቀትር በኋላ ውሎው፣ ከ16 ተሿሚዎች አንዱ የኾኑትን ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰን ጠርቶ በጠየቀበት ጉዳይ፣ የማጣራት ትእዛዝና ጊዜአዊ እገዳ ያሳለፈበት ውሳኔ፣ሥርዓተ ሢመቱ መሠረት የሕዝቡ አቤቱታ መደመጡን ያሳያል፡፡

በርግጥ፣ ውሳኔውና ትእዛዙ፥ “አጣርቶ መምረጥ ወይስ መርጦ ማጣራት?!” በሚል፣ የቅደም ተከተል ችግር እንዳለበት የሚያመለክት ትችት ተሰንዝሮበታል፡፡ ምልአተ ጉባኤው፣ ወደ ምርጫው ከመግባቱ አስቀድሞ፣ “በተነበበው የዕጩዎች ግለ ታሪክ መሠረት ማን ምንድን ነው? የሚለውን እንፈትሽ፤” የሚል ጥያቄ ከኹለት ብፁዓን አባቶች ቢነሣም፣ “ትላንት ሰምተነዋል፤ አንወያይም፤ ወደ ድምፅ እንሒድ፤” በሚሉ አንጋፋ አባቶች ጫና፣ የምእመናኑ አቤቱታ አስቀድሞ ሊደመጥ የሚችልበት ዕድል ተዘግቶ ነበር፡፡ የጋምቤላው ሥራ አስኪያጅ አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱና በገለልተኛ አካል ያልተረጋገጠው የውሸት ዶሴአቸው፥ ‘ሐዋርያዊ ስኬት’ ተብሎ ያለተወዳዳሪም ያለድምፅም እንዲመረጡ፤ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያምም፣ “በማስረጃ የተደገፉ፣ ሃይማኖታዊና የሕግ ይዘት ያላቸው ክሦች አሉባቸው፤ እናጥራቸው፤” ቢባልም፥ “የአባ ዕዝራ ደጋፊዎች ለማሸነፍ ሲሉ ፈጥረው በኢንተርኔት የለቀቁት ስም ማጥፋት ነው፤” በሚል የጅምላ ማሸማቀቅ ካርዱ ተጣለ፤ ዕጣውም ወጣ፡፡

ምልአተ ጉባኤው መርጦ ከወጣና የተሿሚዎቹ ማንነት ከታወቀ በኋላ ግን፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ነጻነትና ክብር እንዲኹም የቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነትና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ፣ ጥያቄ ውስጥ መግባቱን የሚያሳስቡ ቁጣዎችና ምሬቶች ወደ ብፁዓን አባቶች ጎረፉ፤ የጡመራ መድረካችንም፣ የምርጫውን ውጤት ባስታወቀበት የቀትር ሰበር ዜናው፥ የምእመናኑ ተቃውሞና ጥያቄ በዋዛ እንደማይታለፍና ቤተ ክርስቲያን እንደተቋም አልያም ተሿሚው በግል ማብራሪያ ሊሰጡበት እንደሚገባ አሳሰበ፡፡

በምልአተ ጉባኤው የቀትር በኋላ ክፍለ ጊዜ፣ ኹለት ብፁዓን አባቶች ጥያቄ አነሡ፤ የምልአተ ጉባኤው የመጀመሪያ ተግባርም፦ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰን በመጥራት፣ ምእመናን ተቃውሞ ባነሡበትና ከሦስት ወራት በፊት፣ በአዲስ አበባ ደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ስለተከናወነው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት “የጸሎት ሥነ ሥርዓት”  እንዲኹም እርሳቸው ስለነበራቸው ተሳትፎ እንዲያብራሩ መጠየቅ ኾነ፡፡

መርሐ ግብሩን የመምራት ሚና የነበራቸውና በደቡብ ኮሪያ – ቡሳን በተካሔደው የኅብረቱ ፲ኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ በሥራ አስፈጻሚ አባልነት የተመረጡት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ መርሐ ግብሩን እንዲያስተባብሩ ከቤተ ክርስቲያን መወከላቸውን አውስተው፣ ፓትርያርኩና ሌሎችም አባቶች የተገኙበት እንደነበር በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል፤ “ውኃ ለኹሉም ፍትሐዊ በኾነ መንገድ” የሚል ዋና ጭብጥና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተውጣጣ እንጅ የተለየ ጸሎት እንዳልነበር አስረድተዋል፡፡ ከሀገራችን ትውፊት በመነሣትም፣ ከውኃ ጋራ በተያያዘ፣ ጠበልና እምነት ፈዋሽ መኾኑን ለማሳየት ተበጥብጦ እንደቀረበና ቅብዓ ቅዱስም ሜሮንም እንዳልነበረ ተናግረዋል፤ “እነርሱም ቅብዓ ቅዱስ አልቀቡኝም፤ እኔም አልቀባኋቸውም፤” ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

ጉባኤውን በርእሰ መንበርነት የሚመሩት ፓትርያርኩም የሰጡት ገለጻና ያላቸው ግንዛቤ፣ ከዚኹ የዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም ማብራሪያና ምላሽ ጋራ የሚስማማ ነው፡፡ የእምነት አልያም ሌላ መሠረታዊ ችግርን የሚመለከት ማስረጃ በአባ ኃይለ ማርያም ላይ እስካልመጣ ድረስ፣ የቀረበባቸው አቤቱታ፣ መመረጣቸውን የሚያስቀርና ሒደቱንም ወደ ኋላ ለመመለስ የሚያበቃ እንዳልኾነ ነው፣ በአቋም ደረጃ ያንጸባረቁት፡፡

እኛ የሔድነው ጸሎት ይደረጋል ተብሎ ነው፤ ስንደርስ ውኃና ዘይት ቀርቦ ጠበቀን፤ እዚያው ነው ያወቅነው፤ እኔም፣ ጸሎት ብቻ እናደርጋለን፤ ቦታ ስጡን አይደለም ወይ ያላችሁት፤ ምንድን ነው ይኼ ነገር? ብዬ ጠይቄአቸዋለኹ፤ እነርሱም፣ ‘ceremonial’ ነው፤ የጋራ ፍቅር መገለጫችን ነው፤ ኅብረታችንን ለማሳየት ነው፤ በሌሎችም አገሮች የምናደርገው ነው፤ አሉኝ፡፡ የእምነት መገለጫ ተደርጎ መቅረብ የለበትም፡፡

“እዚያ ቦታ እንዲኽ ዓይነት ሥርዓት መፈጸም አልነበረበትም፤” ከተባለ ስሕተቱ የጋራ ነው፤ እኔንም ይጨምራል፤ የጋራ ጥፋት አድርገን እንቀበለው፤ እርሳቸው[ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም] ምንም ማድረግ አይችሉም፤ ከእርሳቸው በላይ ያለነው እኛ ነን፤ ለማዘዙም ለምኑም፤ ከመመረጣቸው ጋራ በተያያዘ ግን የሚከለክላቸው የእምነት ችግር አለ ከተባለ በማስረጃ ተደግፎ ይምጣ፤ ከሢመት ብቻ አይደለም ከሌላም የሚያስቀር ይኾናል፤

… የክርክራችን ጉዳይ፥ ተቀብተዋል ወይስ አልተቀቡም የሚለው ከኾነ፣ ‘ceremonial’ ስለኾነና የኅብረት መገለጫ ነው፣ በሚል የትም ቦታ ይደረጋል፤ ይኼ መሠረታዊ ‘concept’ መታወቅ አለበት፤ እና በእኔ በኩል ከምርጫው ጋራ በተያያዘ ወደ ኋላ የምንመለስበት አንዳችም ምክንያት የለም፤

…ኮሚቴው ባቀረበው ብቻ እንድንመርጥ ተስማማን፤ ያን ጊዜ አኹን አለ የተባለው የሃይማኖት ችግር አልተሰማም፤ በድምፅ ብቻ አይደለም፤ ዕጣምኮ ስንጥል ወደ እርሳቸው ሔደ፤ ይህ ኹሉ ከኾነ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ፣ ላለመቀበልና ሌላውን ለማሳለፍ ብቻ የታሰበ ያስመስላል፤ በእኔ በኩል ጨርሻለኹ፤ ወደ ኋላ የመመለስ ዓላማ ካለ፣ ጥያቄ የሚነሣው በእርሳቸው ብቻ አይኾንም፡፡


ምልአተ ጉባኤው በመጨረሻ፣ ሢመተ ጵጵስናው ከመፈጸሙ በፊት፣ ጉዳዩ መጣራት እንዳለበት ወስኗል፡፡ የዕለቱን ሥነ ሥርዓት፣ በተሟላና ጎላ አድርጎ የሚያሳዩ የምስል ወድምፅ ማስረጃዎች፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት በኩል ቀርበው፣ በብፁዓን አባቶችና በሊቃውንት ጉባኤ ከታዩ በኋላ ውሳኔ እንዲያገኝ ቋሚ ሲኖዶሱን አዝዟል፡፡

ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም ተጠርተው እንዲጠየቁ ስለተወሰነበት ኹኔታ ያስረዱ አንድ የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል፥ “ምእመኑ እጅ ላይ የገቡትና በማኅበራዊ ሚዲያው የተለቀቁት ምስሎች፣ “ሲኖዶሱ እንዴት አለፈው?” የሚል ጥያቄ ይመጣል፤ ለአገልግሎት በሔዱበት ኹሉ ይከተላቸዋል፤ ሕዝቡስ እንዴት ይቀበላቸዋል? ይኼ ግልጽልጽ ብሎ መውጣት አለበት፤” በማለት ተጠያቂው ከመቅረባቸው አስቀድሞ ምልአተ ጉባኤው መወያየቱን ገልጸዋል፡፡  

“እርሳቸውን ሾመን ወዴት ይሔዳሉ?” ሲሉ የሚጠይቁት ሌላው አባት፣ “ተመልሰው ቤተ ክርስቲያንንና ሕዝቡን ነው የሚያገለግሉት፤” ይላሉ፡፡ ለቤተ ክርስቲያንና ለቅዱስ ሲኖዶሱ ክብር እንዲኹም፣ የሕዝቡን አእምሮ ነጻ ለማድረግ ሲባል፣ ጉዳዩ ግልጽ መኾን እንዳለበት፣ ምልአተ ጉባኤው ማስማማቱን ያስረዳሉ፡፡

መመረጣቸውና መሾማቸው፣ እርሳቸውን የሚያስተችና ለሕዝቡም ቅር የሚያሰኝ እንዳይኾን ጥያቄው መመለስ አለበት፡፡ እየተባለ ያለው እውነት ነው፣ ውሸት ነው መታወቅ አለበት፡፡ ተግበስብሶና ተሸፋፍኖ መሔድ የለበትም፡፡ ሓላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት አለብን፡፡


ማጣራቱ፣ የ‘መቀባባት’ ጉዳይን ብቻ ሳይኾን፣ ከሹመት የሚከለክል ሌላም ሕጸጽ አለባቸው፤ በሚል የሚቀርብ ማስረጃንም እንደሚያካትት የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ያሳያል፡፡ በ1965 ዓ.ም. በሰሜን ጎንደር ደብረ ሰላም ሎዛ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መወለዳቸው የተነገረው ተሿሚው፦ ከአባት ስም እና የትውልድ ዘመን መቀያየር፤ ከ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት እና በከፍተኛ ትምህርትም በተለይ ከዶክትሬት ዲግሪ መመረቂያቸው ጋራ በተያያዘ የሚነሡባቸው ጥያቄዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡

የዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም ጉዳይ ትኩረት ያገኘው፣ ማስረጃው በይፋ በመቅረቡ እንደኾነና በሌሎችም ተሿሚዎች ላይ ከበዓለ ሢመቱ በፊት ኹነኛ ነገር ከተገኘ፣ ከመመርመር ውጭ አማራጭ እንደሌለ ተመልክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ፣ በሰዓሊተ ምሕረቱ “የጸሎት ሥነ ሥርዓት” የቀረበባቸውን አቤቱታ በተመለከተ፣ ከትላንት በስቲያ ዓርብ፣ ከኢኦተቤ-ቴቪ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ማብራሪያና ማስተባበያ ሰጥተዋል፡፡ ከፓትርያርኩ በተላለፈላቸው አስቸኳይ ትእዛዝ የሰጡትን ማስተባበያ መነሻ በማድረግ፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ተከታዩን ዘገባ ይዞ ወጥቷል፡፡


የኤጲስ ቆጶስ ተሿሚው ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ የቀረበባቸውን አቤቱታ አስተባበሉ

 

 • እምነትና ውኃ እንጂ ቅብዐ ቅዱስም ሜሮንም አልነበረም፤ ሰውዬውም አልቀባኝም
 • ቅዱስ ሲኖዶሱ ከሢመተ ጵጵስናው አስቀድሞ ጉዳዩ እንዲጣራ አዝዟል
 • ቤተ ክርስቲያኒቱ በመጪው ሐምሌ፣ 16 ኤጲስ ቆጶሳትን ትሾማለች
 • ተሿሚዎቹ ከሢመተ ጵጵስናው በፊት የወር ሥልጠና ይሰጣቸዋል

*                    *                 *

(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ ግንቦት 12 ቀን 2009 ዓ.ም.)


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በመጪው ሐምሌ ወር ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾሙ 16 መነኰሳትንና ቆሞሳትን የመረጠ ሲሆን፤ ከተሿሚዎቹ አንዱ የኾኑት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ፣ በቤተ መቅደስ ውስጥ ከሃይማኖቱ ውጭ ከኾኑ ሌሎች የእምነት መሪዎች ጋራ “ቅብዓ ቅዱስ ተቀባብተዋል” በሚል የቀረበባቸውን አቤቱታ፥ ድርጊቱን አልፈጸምኩም፤ ሲሉ አስተባበሉ፡፡

የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባላት የኾኑ የመካነ ኢየሱስና የወንጌላውያን አብያተ እምነት መሪዎች በተገኙበት፣ ባለፈው የካቲት 22 ቀን፣ በአዲስ አበባ ደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል የተካሔደው መርሐ ግብር፣ በሚያሳስቡ የጋራ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ለመመካከር የተዘጋጀ የጸሎት ሥነ ሥርዓት እንጂ፣ የቡራኬና ቀኖናዊ እንዳልነበረ፣ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሳተላይት ቴሌቭዥን ጣቢያ(ኢኦተቤ-ቴቪ) በሰጡት ማስተባበያ ተናግረዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ ጭብጥ፥ “ውኃ ለኹሉም ፍትሐዊ በኾነ መንገድ” በሚል በወርኃ ጾሙ፣ ንጹሕ ውኃ በተለይ ከሰሃራ በታች ላለው ክፍለ አህጉር፣ በፍትሐዊ መንገድ እንዲዳረስና ውኃ ወለድ በሽታዎች እንዲወገዱ ለማሰብ እንደተዘጋጀና ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱም መገኘታቸውን ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም በማስተባበያቸው ጠቅሰዋል፤ ሥነ ሥርዓቱን የመሩትም፣ መርሐ ግብሩን እንዲያስተባብሩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ በመወከላቸውና ኅብረቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም አገሮች በሚያካሒደው የሰባት ሳምንታት ተከታታይ መርሐ ግብር፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተረኛ በመኾኗ እንደነበር አስረድተዋል፡፡


“ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክዬ፣ ውኃ በእጅጉ አስፈላጊ የእግዚአብሔር ስጦታ ስለመኾኑ በመጽሐፍ ቅዱስ የሰፈረውንና በሀገራችን ክርስቲያናዊ ትውፊት በጠበልና በእምነት የሚሰጠውን ፈውስ ተናግሬአለሁ፤”
ያሉት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፤ “የጸሎት ሥነ ሥርዓቱን የምትመራው የኅብረቱ አባል ቤተ ክርስቲያን፣ በመነካካትና በተግባር የምትፈጽማቸው ምልክታዊ መገለጫዎች(symbolic action) አሉ፤ እኔም ተበጥብጦ ከቀረበው ውኃና እምነት በጣቴ ጠቅሼ በተሳታፊዎቹ ግንባር ላይ በትእምርተ መስቀል ምልክት አድርጌያለሁ፤ ይህም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በእምነትና በሥርዓት የሚመስሏት ሌሎች እኅት አብያተ ክርስቲያናትም፣ በመሰል መርሐ ግብሮች ላይ የሚያደርጉትና የተለመደ ነው፤” ብለዋል፡፡

ለሥነ ሥርዓቱ የቀረበው፣ “ቅብዓ ቅዱስ እና ሜሮን ነው፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት ደግሞ በእምነት ከተለዩና ከተወገዙ ሰዎች ጋራ ይህ አይደረግም፤ መርሐ ግብሩም በቤተ መቅደስ ውስጥ መከናወን አልነበረበትም፤” በሚል ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም እንደቀቡና እንደተቀቡ የሚያሳዩ ምስሎችና ትችቶች በማኅበራዊ ድረ ገጽ በስፋት መሰራጨታቸውን በተመለከተ የተጠየቁት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ “ሰውዬው ጣቱን አስጠጋ እንጅ በፍጹም አልቀባኝም” ሲሉ ተቀብተዋል መባሉን አስተባብለዋል፡፡


“ቅብዓ ቅዱስም ቅብዓ ሜሮንም አልነበረም፤ እነርሱም አይቀበሉም፤ አይፈልጉም፤” ያሉት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ በምስሉ ላይ የሚታየው ሰው ጣቱን ወደ ግንባራቸው ሲያስጠጋ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት የተሾመ ካህን ሌላ ሰው ሊነካውና ሊባርከው እንደማይችል በሹክሹክታ እንደነገሩትና ጣቱን እንደመለሰ ገልጸዋል፡፡

ሥነ ሥርዓቱ ከተካሔደ ወራት ማስቆጠሩን ያስታወሱት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ ምስሉን በማኅበራዊ ድረ ገጽ ያሰራጩት ሰዎች፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚቆረቆሩ ከኾነ፣ በወቅቱ እንዲብራራላቸው ሊጠይቋቸው ይችሉ እንደነበር ጠቅሰው፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳትን እስከሚመርጥበት ሳምንት በማዘግየትና ከሢመተ ጵጵስናው ጋራ በማገናኘት በድረ ገጽ ማስፋፋታቸው፥ “ግላዊ ጥቅምና ተልእኮ እንዳላቸው ያሳያል፤ እኔን ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንን ክብር ነው የነኩት፤“ ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፤ ለሹመቱም የተመረጡት፣ በቅርበትና በሓላፊነት ላይ ስላሉ ሳይሆን በፈቃደ እግዚአብሔር እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

የኤጲስ ቆጶስ ተሿሚው ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም ይህን ይበሉ እንጂ፣ የጸሎቱን መርሐ ግብር ሙሉ በሙሉ የሚያሳይ ቪዲዮ፣ ለሊቃነ ጳጳሳት እና ለሊቃውንት ቀርቦ እንዲጣራ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ከትላንት በስቲያ አዝዟል፡፡ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም በኤጲስ ቆጶስነት ቢሾሙም፣ ተመልሰው የሚያገልግሉት ምእመኑን እንደኾነና፣ ለቅዱስ ሲኖዶሱና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ክብር እንዲሁም የሕዝቡን ኅሊና ነጻ ለማድረግ ሲባል፣ የተነሣው ጥያቄ ከበዓለ ሢመቱ በፊት ምላሽ ማግኘት እንዳለበት፣ ጉዳዩ ያሳሰባቸው ሊቃነ ጳጳሳት ተናግረዋል፡፡ አስተያየታቸውን በፌስቡክ የሰጡ ምእመናንም፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ዘግይቶም ቢኾን እንዲጣራ ማዘዙ ቢያስደስታቸውም፣ “አጣርቶ መምረጥ ወይስ መርጦ ማጣራት?” በማለት፣ በዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መመረጥ ታይቷል ያሉትን የቅደም ተከተል ግድፈት ተችተዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ የአራቱ ጉባኤያት መምህርነት ከሚታወቁት ሌላው ዕጩ፣ ሊቀ ሊቃውንት አባ ዕዝራ ሐዲስ ጋራ ጎንደርን በመወከል ተወዳድረው፣ ሁለቱም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትን እኩል 18 ድምፅ በማግኘታቸው በተጣለው ዕጣ ለኤጲስ ቆጶስነት ተመርጠዋል፤ የተባሉት ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ በነገረ መለኰት የዶክትሬት ዲግሪ እንዳላቸውና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንደኾኑ ተገልጿል፡፡

ግንቦት 2 ቀን የጀመረውን የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤውን በትላንትናው ዕለት ያጠናቀቀው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ክፍት በኾኑ መንበረ ጵጵስናዎች የሚሾሙ 16 ኤጲስ ቆጶሳትን ከትላንት በስቲያ ኃሙስ የመረጠ ሲኾን፤ ሢመተ ጵጵስናው፣ በመጪው ሐምሌ 9 ቀን እንደሚፈጸም ተጠቁሟል፡፡ ተሿሚዎቹ፣ ከ31 ተጠቋሚ መነኰሳትና ቆሞሳት መካከል፣ በክህነትና በምንኵስና ሕይወት፥ በትምህርት ዝግጅትና በአገልግሎት ልምድ በአስመራጭ ኮሚቴ ተለይተው ለቅዱስ ሲኖዶሱ እንደቀረቡና በምልአተ ጉባኤው አባላት ምሥጢራዊ የድምፅ አሰጣጥ እንደተመረጡ ታውቋል፡፡

ተሿሚዎቹ ኤጲስ ቆጶሳት፣ የቤተ ክርስቲያን አመራርና አስተዳደር እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱን እየፈተኗት በሚገኙ ዐበይት ወቅታዊ ጉዳዮችና እንደ አባትነታቸው የሚጠበቅባቸውን በተመለከተ፣ ከሢመተ ጵጵስናው በፊት የአንድ ወር ሥልጠና እንደሚሰጣቸው፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ የአኹኑ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የራሷን ጳጳሳት ማሾምና መሾም ከጀመረችበት ከ1921 ዓ.ም. ጀምሮ ያሉትን አባቶች ጠቅላላ ሊቃነ ጳጳሳት ቁጥር 136 ያደርሰዋል፡፡

የኤጲስ ቆጶስነት ተሿሚዎች የአንድ ወር ሥልጠና ይሰጣቸዋል

 • የቤተ ክርስቲያን ዐበይት ችግሮች እና ተግዳሮቶች የኾኑ ወቅታዊ ጉዳዮችም አሉበት
 • ከጠባብነት፣ ጥቅማጥቅምና መሀል ሰፋሪነት የተጠበቁ የኹሉ አባት መኾን አለባቸው
 • በመጪዎቹ ኹሉት ሳምንታት ውስጥ፣ ወደ ማእከል ተጠቃለው እንዲገቡ ይጠራሉ

  *                    *                  *

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት

በመጪው ሐምሌ ወር፣ ሢመተ ኤጲስ ቆጶስነት የሚፈጽምላቸው፣ ተሿሚ ቆሞሳትና መነኰሳት፣ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እና አመራርን ጨምሮ፣ በዐበይት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የወር ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ተጠቆመ፡፡

ስለ ተመራጭ ቆሞሳትና መነኰሳት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. ባወጣው የመመዘኛ ደንብ ቁጥር 16 መሠረት የተዘጋጀው ይኸው ሥልጠና፣ በሦስት ሳምንት ጊዜ እንደሚጀመርና የኤጲስ ቆጶስነት ተሿሚዎቹ፥ በመጪዎቹ ኹለት ሳምንታት፣ ከያሉበት አህጉረ ስብከት ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ተጠቃለው እንዲገቡ፣ በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይጠራሉ፤ ተብሏል፡፡

ሥልጠናውን፣ የቋሚ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የሚያስተባብረው ሲኾን፤ በተመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምሁራን እንደሚሰጥ ተመልክቷል፡፡

ደንቡ የሦስት ወራት የሥልጠና ጊዜ ቢያስቀምጥም፣ በተባለው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ፡- ቀኖና ቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያን አመራርና አስተዳደር፤ በተሐድሶ መናፍቃን ሤራና በሌሎችም ዐበይት ወቅታዊ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሐዋርያዊ ተልእኮ ችግሮችና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እንደሚሰጧቸው ተጠቁሟል፡፡

ተሿሚዎቹ ቆሞሳትና መነኰሳት፣ ከሥልጠናው፦ በከፍተኛው ሥልጣነ ክህነት አባትነታቸው ለኹሉም እንደኾነ፤ ቤተ ክርስቲያን እየተጎዳችባቸው ያሉ ኹለንተናዊ ችግሮችንና የኖላዊነት አገልግሎታቸውን፥ ከጠባብነት፣ ጥቅማጥቅምና መሀል ሰፋሪነት ተጠብቀው መፍትሔ መስጠት እንደሚገባቸው በቂ ግንዛቤ ይጨብጣሉ፤ ተብሎ ታስቧል፡፡

ስለ ሥርዓተ ገዳምና ሥርዓተ ምንኵስና በቂ ግንዛቤ በመያዝ ለምንኵስና ሕይወት ትክክለኛ ማስረጃ ማቅረብ፤ በሥርዓተ ክህነት በመቀደስና በማስተማር እስከ ቆሞስነት ደረጃ መድረስ፤ የቤተ ክርስቲያንን ነገረ መለኰትና ሥርዓተ ቀኖና ጠንቅቆ የማወቅና የመግለጽ አቅም፤ ከአብነት ትምህርቶች ቢያንስ በአንድ ጉባኤ መመረቅ፤ ግእዝን ጨምሮ በሚሾሙበት ሥፍራ ለማገልገል የሚያስችል የዘመናዊ ትምህርት ዝግጅትና የቋንቋ ችሎታ፤ በመንፈሳዊ ሕይወትና በግብረ ገብነት፣ በሥራ አመራርና ልምድ የአገለገለበት ሀገረ ስብከት ወይም ቦታ ካህናትና ምእመናን ምስክርነት፤ በአጠቃላይ፥ የምእመናንና የካህናትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ችግሮች የመረዳትና የመፍታት ልምድና ችሎታ፤ ተመራጮቹ በዕጩነት ሲቀርቡ ሊያሟላቸው ይገባሉ፤ ተብሎ፣ በመመዘኛው የተዘረዘሩ መስፈርቶች በመኾናቸው፣ የሥልጠናውን አድማስና ጥልቀት ለመወሰን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተመደቡ፤ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም በኢኦተቤ-ቴቪ አስተባበሉ

 • የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የገዳማት አስተዳደር መምሪያ፣ በበላይ ሓላፊነት ይመራሉ
 • የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጠናቀቀ፤ በመጪው ሰኞ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል
 • ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ በቀረበባቸው አቤቱታ፣ ለኢኦተቤ-ቴቪ ማስተባበያ ሰጡ

  *                      *                    *

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ

የወላይታ እና ዳውሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ወደ ሶማሌ/ጅግጅጋ/ ሀገረ ስብከት ተዛውረው እንዲሠሩና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያን፣ በበላይ ሓላፊነት እንዲመሩ በምልአተ ጉባኤው ተመደቡ፡፡

በምደባው መሠረት፣ ብፁዕነታቸው በተዛወሩበት ሀገረ ስብከት ሥራቸውን የሚጀምሩት፣ የተመረጡት ኤጲስ ቆጶሳት ሢመተ ጵጵስና ከተፈጸመ በኋላ እንደሚኾንና እስከዚያው ድረስ አኹን ባሉበት ሀገረ ስብከት እንደሚቆዩ ተገልጿል፡፡

የጅግጅጋ ሀገረ ስብከትን ሲመሩ የቆዩት ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ ከብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዕረፍት በኋላ ደርበው የያዙትን ሰፊውን የአርሲ ሀገረ ስብከት መምራታቸውን የሚቀጥሉ ሲኾን፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን በበላይ ሓላፊነት እንደሚመሩም የሚታወቅ ነው፡፡ 

ላለፉት ዐሥራ አንድ ቀናት ሲካሔድ የቆየው፣ የ፳፻፱ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በዛሬው ዕለት ቃለ ጉባኤዎችን በመፈራረም ተጠናቋል፤ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት፣ በቋሚ ሲኖዶሱ የሚሠሩ ተለዋጭ አባላትንም መርጧል፡፡

እስከ ሐምሌ 30 ቀን ባሉት ቀጣዮቹ ሦስት ወራት፣ የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ኾነው የሚሠሩት አራት ብፁዓን አባቶች፥ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እና ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ሲኾኑ፤ በምልአተ ጉባኤው የጸደቁትን ሕግጋት፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች በሥራ ላይ መተርጐማቸውን መከታተልና መቆጣጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከምልአተ ጉባኤው ዐበይት ውሳኔዎች አንዱ፣ በቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ችግሮች ላይ የተጠናውንና የቤተ ክህነቱን መዋቅር፣ ሕግና የአሠራር ሥርዓት መልሶ ማደራጀትና ማሻሻል እንደሚያስፈልግ የሚያሳስበውን ጥናታዊ ሪፖርት የሚመለከት ነው፡፡ የአጥኚ ቡድኑን ማብራሪያ በማዳመጥ በጥናታዊ ሪፖርቱ ላይ የተወያየው ምልአተ ጉባኤው፣ በተጨማሪ ባለሞያ ተመርምሮ ለቋሚ ሲኖዶሱ እንዲቀርብ በመወሰኑ፣ መልክና ቅርጽ ይዞ እንዲተገበር ኹኔታዎችን በማመቻቸት ረገድ የተጣለበትን ከፍተኛ ሓላፊነት እንደሚወጣ ተስፋ ይደረጋል፡፡

የምልአተ ጉባኤውን ሒደትና ውሳኔዎች በተመለከተ፣ በመጪው ሰኞ ረፋድ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡


በተያያዘ ዜና፣
ከ16ቱ ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ ኾነው በዕጣ የተመረጡት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ አባ ኃይለ ማርያም መለሰ(ዶ/ር)፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ለተሠራጨባቸውና ምልአተ ጉባኤው እንዲጣራ ባዘዘው የ”መቀባባት” አቤቱታ፤ ዛሬ፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን(EOTC-Tv) ማስተባበያ መስጠታቸው ተሰማ፡፡

በቃለ ምልልስ መልክ በተሰጠው ማስተባበያቸው፦ የካቲት 22 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተከናወነው፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት “የጸሎት ሥነ ሥርዓት” በጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረና በግልጽ የተካሔደ እንጅ የቡራኬ እንዳልነበረ፤ እርሳቸውም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው እንዲያስተባብሩ በታዘዙት መሠረት መርሐ ግብሩን መምራታቸውን፤ ውኃና እምነት ተበጥብጦ እንደቀረበና እርሱን በጣታቸው ጠቅሰው በትእምርተ መስቀል መቀባታቸውንና እርሳቸው ግን በፍጹም እንዳልተቀቡ፤ ቅብዓ ቅዱስ እና ሜሮን እንዳልነበረ፤ ለተሿሚነትም የተመረጡት በፈቃደ እግዚአብሔር እንደኾነ፤ ማስረጃው በወቅቱ ቢቀርብ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይችሉ እንደነበርና የኤጲስ ቆጶስ ምርጫና ሢመት ወቅት ተጠብቆ መሠራጨቱ ተገቢ እንዳልኾነ በመጥቀስ ቅሬታቸውን መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በትላንት የቀትር በኋላ ውሎው፣ አባ ኃይለ ማርያምን(ዶ/ር) በመጥራት፣ ስለ መርሐ ግብሩ እንዲያብራሩ የጠየቃቸው ሲኾን፤ “እኔም ቅብዓ ቅዱስ አልቀባኋቸውም፤ እነርሱም አቀልቀቡምኝም” ሲሉ ለቀረበባቸው አቤቱታ መልሰዋል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱም፣ ሥነ ሥርዓቱን በተሟላና በጉልሕ የሚያሳይ የምስል ወድምፅ እንዲኹም እርሳቸውን የተመለከቱ ሌሎችም ማስረጃዎች በጽ/ቤቱ በኩል ቀርበው፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በሊቃውንት፣ ከበዓለ ሢመቱ በፊት ተጣርቶ ውሳኔ እንዲያገኝ ማዘዙ ተዘግቧል፡፡

ዛሬ፣ ቀትር ላይ የተቀረጸው የማስተባበያና የማብራሪያ ቃለ ምልልሱ፣ ነገ እሑድ ረፋድ በጣቢያው እንደሚተላለፍ ተጠቄሟል፡፡