ሰበር ዜና – ከብር 4 ሚልዮን በላይ የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የመዘበሩት የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ሒሳብ ሹም እና ገንዘብ ያዥዋ ቃሊቲ ወረዱ!

Addis Ababa Lideta LeMariam Church

  • ለደብሩ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና ለሰንበት ት/ቤቱ ታላቅ ድል፤ በየአጥቢያው ለተጋጋለው የፀረ ሙስና እና ፀረ ኑፋቄ ንቅናቄ ታላቅ የምሥራች፤ የንቅናቄውን ኃይሎች በነፍስ ግድያ ዛቻዎች ጭምር ለማዳከም ለሚሯሯጡት አማሳኞች ከባድ ድንጋጤ እና መርዶ ኾኗል !!!

ginbot-12005-in-lideta-le-mariam

  • በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ ችሎት ባለፈው ሳምንት ዓርብ ረፋድ ባሳለፈው የቅጣት ውሳኔ፣ በሰነድ ማጭበርበር በፈጸሙት የእምነት ማጉደል ወንጀል የደብሩ ዋና ሒሳብ ሹም ዲያቆን ተስፋዬ በቀለ የአንድ ዓመት ከስምንት ወራት፤ የደብሩ ዋና ገንዘብ ያዥ ወ/ሮ አብረኸት ተክሉ በኹለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ፈርዶባቸዋል፡፡ መዝባሪዎቹ ውሳኔው ከተላለፈበት ካለፈው ሳምንት ዓርብ ረፋድ ጀምሮ ቀጨኔ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ቆይተው የቅጣት ጊዜአቸውን ለመፈጸም በዛሬው ዕለት ወደ ቃሊቲ ወኅኒ ቤት መውረዳቸው ታውቋል! ! !
  • በተመሳሳይ መዝገብ ሌሎች ሦስት ግብረ አበሮቻቸው የኹለት ዓመት እስር በገደብ እና የአምስት ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት የተላለፈባቸው ሲኾን እነርሱም÷ በተለያየ ጊዜ የደብሩ ጸሐፊ የነበሩት መ/ር ኃይለ ማርያም ኣብርሃ(ለአጭር ጊዜ የሀገረ ስብከቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ)፣ መ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ዕዝራ እና አቶ ዮሐንስ በርሄ ናቸው፡፡ ጉዳዩን የያዘው ዐቃቤ ሕግ፣ ‹‹ቅጣቱ አንሷል፤ አስተማሪም አይኾንም›› በሚል በኹሉም ተከሣሾች ላይ ከብዶ እንዲወሰን ይግባኝ እንደሚጠይቅበት ተመልክቷል፡፡
  • ከማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ያለተጠያቂነት ተዛውረው በአኹኑ ወቅት የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጸሐፊ ኾነው የሚሠሩት መ/ር ኃይለ ጊዮርጊስ ዕዝራከየካቲት እስከ ነሐሴ 2006 ዓ.ም. ባሉት ሰባት ወራት ብቻ ገዳሟ ለተመዘበረችው ከብር 1.5 ሚልዮን በላይ ገንዘብ ከሒሳብ ሹሙ፣ ከገንዘብ ያዡ፣ ከቁጥጥሩ እና ከቀድሞው አስተዳዳሪ ጋር ተጠያቂ እንደኾኑ ሰበካ ጉባኤው ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ በአድራሻ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በግልባጭ ለበላይ ጠባቂዋ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ለፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ያቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡

*          *          *

  • የወቅቱ የሀገረ ስብከቱ የሒሳብ እና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ እና የሰበካ ጉባኤ ማዳራጃ ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ መዘምራን ብርሃኑ ጌጡ÷ ከሐምሌ1/2004 – ኅዳር 20/2005 ዓ.ም. ያለውን የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የገቢ እና የወጪ ሒሳብ አጣርተው እንዲያቀርቡ በ2005 ኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ በደቡብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በታዘዙበት ወቅት በሰነድ ማጭበርበር የተፈጸመውን ከፍተኛ የገንዘብ ዘረፋ ለማድበስበስ እያንዳንዳቸው ብር 50‚000 ተቀብለዋል፡፡
  • የጥንቆላ እስረኛው፣ የፐርሰንት ፈሰስ፣ የሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እና የአበል ክፍያዎች ቀበኛውሊቀ ጠበብት ኤልያስም ‹‹እንዴት እኩል ይሰጠኛል›› በሚል በዋና ሒሳብ ሹሙ እና በዋና ገንዘብ ያዡዋ ላይ አቂመው ቆይተዋል፡፡ ጉዳዩን የደረሰበት የደብሩ ሰበካ ጉባኤም ለወቅቱ የደቡብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በወቅቱ በማሳወቅ ኅዳር 26 ቀን 2005 ዓ.ም በተላለፈለት መመሪያ መሠረት ዋና ሒሳብ ሹሙ፣ ዋና ገንዘብ ያዡዋ እና ዋና ተቆጣጣሪው በከፍተኛ የገንዘብ ብክነት እና የሰነድ ማጭበርበር ወንጀል በሕግ አግባብ እንዲጠየቁና በእልክ አስጨራሽ ክትትል የፍትሕ ብትር እንዲያርፍባቸው ለማድረግ ችሏል!!!
  • ከመጪው ሰኔ 30 ቀን ጀምሮ በየአድባራቱ የኦዲት ምርመራ ለማካሔድ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በአኹኑ ወቅት÷ ከማኔጅመንት የሰው ኃይል እንቅስቃሴ መርሖዎች ውጭ በአማሳኝ የአድባራት አለቆች እና በሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች የጥቅም ትስስር ያለተጠያቂነት የሚፈጸመው የአጥቢያ ልዩ ልዩ ሠራተኞች ዝውውር እንደቀጠለ ነው፤ በትላንትናው ዕለት ያለአስተዳደር ጉባኤው ዕውቅና በዋና ሥራ አስኪያጁ ና ጥቂት ተባባሪዎቻቸው ውሳኔ በበርካታ አጥቢያዎች የሒሳብ ሹሞችና ጸሐፊዎች መካከል የተደረጉት ዝውውሮች÷ በብልሹ አሠራር ላይ ጥያቄ ያቀረቡ የተጠቁበት፤ በምትኩ ለቀጣይ ምዝበራዎች ኹኔታዎች እየተመቻቹ እንዳሉ የሚጠቁም እንደኾነ እየተገለጸ ነው፡፡

*          *          *

በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ ከሚያዝያ 2002 ዓ.ም ጀምሮ ተመርጦ በሥራ ላይ የነበረው ሰበካ ጉባኤ በነሐሴ 2005 ዓ.ም. ለማኅበረ ካህናት፣ ለማኅበረ ምእመናንና ለየሰንበት ት/ቤቱ ያቀረበው ሪፖርት ዐበይት ነጥቦች፤

Lideta LeMariam Church77

  • ‹‹ቃለ ዐዋዲው÷ የደብሩ ሒሳብ ሹም በየወሩ፣ ቁጥጥሩ ደግሞ በየሦስት ወሩ ለሰበካ ጉባኤው ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያደርጉ ቢያዝም ድንጋጌውን በደብራችን ለመተግበር አስቸጋሪ ኾኖ ቆይቷል፤
  • ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኅዳር 28/2003 ዓ.ም. ለአጥቢያችን በተጻፈ ደብዳቤ የ10 ዓመት ያልተከፈለ 20% ዕዳ ብር 4‚181‚189.76 ስላለባችኹ እስከ ታኅሣሥ 30/2003 ዓ.ም. ገቢ እንድታደርጉ የሚል ደብዳቤ ደርሶን ነበር፡፡ …ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩበት ወቅት በቀየሱት የጥፋት እና የብክነት ስትራተጂ ከሙዳይ ምጽዋት ገንዘብ ከሚገኘው ገቢ ላይ ለሀገረ ስብከቱ ሊከፈል የሚገባው የ20% ድርሻ እየተቀነሰ ሰነድ ሳይነካው በአየር ላይ ወደ ሀገረ ስብከቱ እንዲላክ በቃል በማዘዛቸው በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተበልቷል
  • …በየወሩ በከፍተኛ መጠን የሚገባና ለብክነት የተጋለጠ የገንዘብ ምንጭ ቢኖር የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ ገንዘብ ነው፤ የቆጠራው ሥርዐት ምን እንደሚመስል ለመመልከት፣ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ካሉም ለማሻሻል እና የቁጥጥር ሥርዐቱን አጠናክረን ለመቀጠል የሰበካ ጉባኤው አባላት በሙሉ በመገኘታችን በወቅቱ የነበረው አስተዳደር፣ ለምን ተሰብስባችኹ ትገባላችኹ? ይህን እንድታደርጉ ማን ፈቀደላችኹ? በሚል በጣም ተቆጣ፤ አባላቱን በማስፈራራትና የቆጠራ ቀናትን በመደበቅ እንዳይገኙ ጥረት ቢያደርግም ሰበካ ጉባኤው ጉዳዩን አጠናክሮ ቀጠለበት
  • …በብዙ ሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በሚያንቀሳቅስ ቤተ ክርስቲያን የዚኽ ዓይነት ብልሹ የሒሳብ አሠራር በዘመናችን የለም፤ የሞዴል 64 ሰነዶች እየተደለዙ ከፍተኛ የማጭበርበር ተግባር ተፈጽሟል፤ 17 የሞዴል 64 ቅጠሎች በሓላፊዎቹ ተዘርፈዋል፤ ከሐምሌ1/2004 ዓ.ም. ጀምሮ የሒሳብ ምርመራው እስከተካሔደበት ድረስ የተወራረደ ሒሳብ የለም፤ ከሙዳይ ምጽዋት ተቆጥሮ በሞዴል 64 የገባ ብዙ መቶ ሺሕ ብር ተሰርዞ እና ተደልዞ መጭበርበሩን /በ2003 ዓ.ም. ከብር 591‚965.25 ባንክ አለመግባቱን/ ከባንክ ባስመጣነው የገቢ እና የወጪ ማስረጃ /Bank statement/ አረጋግጠናል፤
  • የሕንፃው ክፍሎች የኪራይ ክፍያ ወቅቱንና የአካባቢውን የገበያ ኹኔታ ያገናዘበ ሳይኾን ለተከራዩ የሚያደላና ከፍተኛ ችግር ያለበት ነው፤ ማኅበረ ምእመናን፣ ማኅበረ ካህናት እና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ገንዘባቸውን እያዋጡ ያሠሩትን የቅድስት ልደታ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ውጤት ለማየት ባለመቻላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፤ ኮሌጁ በሰበካ ጉባኤው እንዲተዳደር በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀው መተዳደርያ ደንብ ተጥሶ ደብሩ የማያዝበትና የማይጠቀምበት፣ ባለቤቱ በውል ያልታወቀ ተቋም በመኾኑ የገቢና ወጪ ሒሳቡን ለመቆጣጠር አልተቻለም፤ በ2003 እና በ2004 ዓ.ም. ለደብሩ የሚገባውን ፈሰስ አልከፈለም
  • በአጠቃላይ ከሐምሌ 1/2002 – ሰኔ 30/2005 ዓ.ም. ባሉት ሦስት የበጀት ዓመታት በውጭ ኦዲተር በተደረገ የሒሳብ ምርመራ ከብር 4‚606‚301.50(አራት ሚልዮን ስድስት መቶ ስድስት ሺሕ ሦስት መቶ አንድ ብር ከኃምሳ ሳንቲም) የቤተ ክርስቲያናችን ገንዘብ በዋና ሒሳብ ሹሙ፣ በዋና ገንዘብ ያዡዋ እና በዋና ተቆጣጣሪው ተመዝብሯል፡፡››

*          *          *

  • ‹‹[የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም] የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር በሰጡት መግለጫ÷ የደብሩ ሒሳብ በቃለ ዐዋዲው በተደነገገው መሠረት የጊዜ ሰሌዳውን ጠብቆ በአግባቡ እንዲመረመር ሰበካ ጉባኤው ለሚመለከተው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያለሟቋረጥ አቤቱታ ሲያቀርብ ቢቆይም ሰሚ ዦሮ በማጣት ወይም ዦሮ ዳባ ልበስ ተብሎ በመቆየቱ የተገለጸው ከፍተኛ የገንዘብ ምዝበራ በደብሩ ሊፈጸም የቻለ መኾኑን አሥምረውበታል፡፡
  • …ከካህናቱ እና ከምእመናኑ ከቀረቡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች መካከል፡- ሒሳብ ሹም፣ ገንዘብ ያዥ፣ ቁጥጥር በማን እንደሚላኩ እናውቃለን፡፡ ከዚኽ ከደብራችን የሥራ ብቃት ያላቸው ልጆች እያሉን ከላይ መመደባቸው ያሳዝናል፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተጠያቂዎች መኾናቸውን ሕዝበ ክርስቲያኑ ሊያውቀው ይገባል፡፡ለዚኽ ኹሉ ጥፋት ዋና መነሻ ከዚያው የሚላኩት ኦዲተሮች ናቸው፡፡ እነርሱ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ በእነርሱ ላይ የምንወስደው ርምጃ ምንድን ነው? የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡››

/የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፣ ‹‹የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ በደብሩ የተፈጸመውን ከፍተኛ የገንዘብ ምዝበራ አጋለጠ›› በሚል ርእስ በነሐሴ ወር ፳፻፭ ዓ.ም. ካሰፈረው ዘገባ/

14 thoughts on “ሰበር ዜና – ከብር 4 ሚልዮን በላይ የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የመዘበሩት የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ሒሳብ ሹም እና ገንዘብ ያዥዋ ቃሊቲ ወረዱ!

  1. Anonymous June 30, 2015 at 5:20 pm Reply

    BeEwunet Talak Mastemariya Ketat New! ! !

  2. ገብረ ማርያም June 30, 2015 at 6:08 pm Reply

    የወንድሞች ከሳሾች፤ መቼም ሀሰቱን እውነት ማለት ስራችሁ ነው ሀሰተኛ የሐሰት አባት የሆነው ዲያብሎስ አስመስሎ የወለደችሁ!!!

    • Anonymous July 1, 2015 at 8:30 am Reply

      አንተ ውዕቱ አቡሃ ለሀሰት

  3. samuel July 1, 2015 at 6:46 am Reply

    temesgen new yemibalew

  4. adis July 1, 2015 at 7:11 am Reply

    LEWNETEGNOCH DES YEMIL ZENANEW GIN TIRU NEGER ATISERUM TIRU TARIK LERASACHIHU LEMADREG GIN WISHET AYTEKMACHIHUM LEBOCHU LEFIRD ENDIKERBU BEMIRMERA ATABIKIGN YASGEBACHE LIKETEBEBT Elias New LEZIHM Tesasitachihu kehone Yedebru seek GUBAENA SENDEBET TIMHIRT BET WETATOCH BEGINBAR ANAGIRU GIN ENANATE MECHE LEHAK KOMACHIHUNA TEZAZBENAL TEWAWIKENAL FIRDU LEGZIABHER SETITNAL

  5. ታዛቢው July 1, 2015 at 8:19 am Reply

    1.ተው፡፡ተው፡፡የበሬውም ምስጋና ለፈረሱ አትስጡ፡፡ሐራዎችም እነዚህን ፍርድ የተላለፈባቸው ሰዎች ስማቸውን ስትጠሩት ሰምተን አናውቅም፡፡ይሕ ፍትሕ የተገኘው ምሀባው ዓለሙ ከበደ የተባለ የቀድሞ የማኅደረስብሐት ቅድስት ልደታ ሰ/ት/ቤት ሰብሳቢና የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባል በነበረ ልጅ እጅግ ቆራጥና በማስተዋል የተሞላ ርምጃ መነሻነት ነው፡፡በሰሞነኛው የነኄኖክ አስራት ከማስረጃ ስብሰባ በፊት ዛቻንና መፈክርን ባስቀደመ ዘመቻ አይደለም፡፡ቢሮ በማሸግና በመሳደብም አይደለም፡፡ቁልጭ ያለ የሰነድ ማስረጃ ሰበሰበ፡፡የፍትሑ ጎማ ቀስ ብሎ ሲሽከረከር ቆይቶ መድረስ ባለበት ጊዜ ደረሰ፡፡ማስረጃ ከፈለጋችሁ ሩቅ ሳንሄይድ ይሄው ሐራ ከዚህ ቀደም ያወጣችውhttps://haratewahido.wordpress.com/2014/03/23/%E1%8C%8A%E1%8B%9C-%E1%8B%AD%E1%8D%88%E1%8C%85-%E1%8B%AD%E1%8A%BE%E1%8A%93%E1%88%8D-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8C%82-%E1%88%88%E1%8B%8D%E1%8C%A1-%E1%8A%A0%E1%8B%AD%E1%89%80%E1%88%AC-%E1%8A%90%E1%8B%8D/

    ከሐራ የወቅቱ ዘገባ(ከአዲስ ጉዳይ የመጋቢት 2006 እትም የተወሰደ) የምሀባው ንግግር ለመጥቀስ ያህል
    • ሃይማኖት ከአስተዳደሩ የተለየ በጣም ጥልቅ ነገር ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት ከአንድ ግለሰብ ኾነ ከጥቂት ሰዎች አመራር የተለየና የራሱ ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት፣ ባህልና ሥርዓት ያለው መኾኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
    • በሥነ ምግባር ደረጃ እኔን ጨምሮ ኹሉም ሰው ችግር ሊኖርብን ይችላል፡፡ ይኹንና ይኼ የሥነ ምግባር ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በመነጋገርና ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ ነው፡፡ ስለ አስተዳደር ጉዳዮች ሲነሣ ነገሩ የሃይማኖት ሳይኾን የሥነ ምግባር መኾኑ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚኽ ለእኔ አስተዳደሩን ከሃይማኖቱ ጋራ ማቀላቀል ተገቢ አይኾንም፡፡
    ዘመኑን ካልዋጀን ሌላው ቀርቶ የዘመኑ ትውልድ አብሮን ሊሔድ አይችልም፡፡ ትውልዱን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋራ ለማስቀጠል ከፈለግን አስተዳደራዊ ሥርዓታችንን የግድ ዘመናዊ ማድረግ አለብን፡፡ ሃይማኖት አንዴ ተሰጥቶ ያለቀ ስለኾነ የምንጨምርበት ኾነ የምንቀንስበት ነገር አይኖርም፡፡ አስተዳደራችን ግን በየጊዜው ከሚሻሻለው ዕውቀት ጋራ ተዘምዶ መሻሻል አለበት፡፡
    የአንድ ደብር ጸሐፊ የኾነ ሰው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከኹለት ሺሕ ብር በማይበልጥ ደመወዝ ኹለት ሦስት መኪና፣ ኹለት የመኖሪያ ቤቶች በፍጹም ሊኖረው አይችልም፡፡ የአንድ ወር ደመወዛቸው ለመኪና ነዳጅ ወጭ የማይሸፍንላቸው አገልጋዮች መኪና እየለዋወጡ ሲይዙ በድሎት ሲኖሩ፣ የልጆችን ይኹን የራሳቸውን ወጭዎች ያለችግር ሲሸፍኑ ይኼ ነገር ከየት መጣ ያሰኛል፡፡
    ቤተ ክርስቲያን አኹን እየተጠቀመችበት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ዓለም በ፲፯ኛው መ/ክ/ዘ የተወውንና የነጠላ ሒሳብ አሠራር (single entry) የሚባለውንና በሞዴል የሚሠራ የሒሳብ አሠራር ነው፡፡ በዓለም ላይ እንዲኽ ዓይነት የሒሳብ አሠራር የሚከተል ምንም ተቋም የለም፡፡የነጠላ ሒሳብ አሠራር ወጪን ወጪ ይላል እንጂ ምክንያቱን አይናገርም፡፡ ስለዚኽ ወጪን ከነምክንያቱ ገቢን ከነምንጩ የሚጠቅሰው የኹለትዮሽ(ደብል) ሒሳብ አሠራር ሥርዓት የላትም፡፡ በመኾኑም ይኼን ተረድቶ የፋይናንስ ሥርዓቱን በአፋጣኝ ማዘመን ይገባል፡፡
    ካሽ ሬጅስተር በመጠቀም እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ያለውን አቅም የላይኛው አስተዳደር አካል በሚገባ ለማወቅና ከፍተኛ ብክነትን ለማስወገድ ይችላል፡፡ አኹን እየጠፋ ያለውኮ ብሩ ብቻ ሳይኾን ሰነዱም ጭምር ነው፡፡ የካሽ ሬጅስተርን መረጃ ግን ማጥፋት ስለማይቻል የቁጥጥር ሥርዓትን ማጉላትና ተጠያቂነትን ማስፈን ይቻላል፡፡

    2.ሌላ ሊታወቅ የሚገባው ይሕ ችግር ሲከሰት የነበረው አመራር የአሁኑ የነ ሊቀማዕምራን የማነ እና የነ መጋቤ ብሉይ አእመረ አይደለም፡፡

    3.ከዚህ መዝገብ ሁሉም ሰው ሊማርበት ይገባል፡፡ሀ/ስብከቱ የሞዴል 64 ያላግባብ ከነ ቃለጉባኤ በጸሐፊ እጅ እየሆነ ቀሪና በራሪው በስርዝ ድልዝ የሚጨማለቅበትን ሥርዓት ቢያንስ ከቆጠራ በኋላ በግልጽ በሚነበብ ቃለጉባኤ መዝግቦ ሞዴሉን ወደ ጸሐፊ ሳይሆን ወደመዝገብ ቤት የማስገባትና የሰ/ጉባኤ አባላትም ሆነ የበላይ ኦዲተሮች በማንኛውም ጊዜ ሲመጡ እንዲያገኙት የሚያደርግ ሥርዓት ይዘርጋ፡፡ይሕ ጅምር በንቡረዕድ አባ ገብረማርያም ተጀምሮ ባጭር የተቀጨ ነው፡፡የቦታ ኪራዮች ለምሳሌ 2ሺህ ካሬ ተከራየ ይባልና ተከራዩ ተመሳጥሮ የሚያጥረው ግን 7ሺህ ሊሆን ይችላል፡፡የንብረት ሺያጭ ነገር እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ምንም ሥርዓት የሌለውና በጥቂት ሞኖፖሊስቶች ኔትወርክ የተተበተበ ነው፡፡የ50ሺህ ብር የይስሙላ ጨረታ ይወጣል ሲሸጥ ግን የ150ሺህ ብር ንብረት ሆኖ ይገኛል፡፡አስተዳደሩ ይሄን ሁሉ ማየት ይጠበቅበታል፡፡የጨረታው ይስሙላ ይፈተሸ፡፡

    4.ይህን ድርጊት ለማስቆም ቅን ልቦና ያላችሁ ምዕመናን፣ሰ/ተማሪዎችና ካሕናት ጉዳዩን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር፣አስቀድሞ ስም ከመለጠፍና በመደዳ ከተሐድሶ ጋር እያያዛችሁ ኮንስፓይሬሲ ከመቀመር ማስረጃ ሰብስቡ፡፡ተጨባጭ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ሰብስቡ፡፡በተለይ ሰበካ ጉባኤ አባላት ሰ/ተማሪዎችና ምዕመናን ወ ካሕናት እናንተ ተቀናጅታችሁ ከሰራችሁ ብዙ ዘረፋና ንጥቂያ ማቆም ትችላላችሁ፡፡ችግሩ አጀንዳውን አስቀድማችሁ ወሬ በማጮህ በቀሳጥያኑ ወጥመድ ራሳችሁን ትከታላችሁ እነ አጅሬም ሰነድ አጥፍተው ቁጭ ይላሉ፣አልፎ ተርፎም ሀቃችሁን በበለው ፍለጠው ኃይል ተሞላበት አካሄድ ትቀጩታላችሁ፡፡ ከሚገባችሁ ጊዜና የእድሜ ገደብ በላይ የሰ/ት/ቤቱን አመራር ሙጭጭ ያላችሁበት ጎልማሶች ደግሞ ራሳችሁ በካሕናት ማኅል ግሩፕ ፈጥራችሁ ያልተጣላችሁ ሰው ቢመዘብር አይሰማችሁም፤ሱቃችሁ ኢዲት ይደረግ ካልተባለ በቀር የቤ/ክ ህመም አይሰማችሁም፤አልፎ ተርፎም ራሳችሁን በጣም በማጋነን ተራውን ካሕን ወደ ማቃለልና ችላ ወደማለት ስለምታዘነብሉ ካሕኑ ከእናንተ ጋር ለመሰለፍ አይደፍርም፡፡ስለዚህ ይሕን የቸከ አመራር ፈትሾ በማስረጃ የተሞላ አቤቱታ በመያዝ፣ግንኙነትን ጤናማ በማድረግ፣አካሄድን ካልተገባ አነጋገርና ከኃይል ተግባር በማራቅ ከተሄደ የቤ/ከ መዋቅር መፍትሄ ባይሰጥ እንኳ ድርጊቱ ደረቅ ወንጀል ስለሆነ እንዲህ እንዳሁኑ በዳዮችን በፍርድ አደባባይ ማቆም ይቻላል፡፡

    5.አሁን ሰዎቹ በወንጀል ተፈርዶባቸዋል፡፡ያ ማለት ግን የወሰዱትን ገንዘብ መልሰዋል ማለት አይደለም፡፡ስለዚህ ቤ/ክ ልታገኝ የሚገባትን የመጨረሻ ፍትሕ ገና አላገኘችም ማለት ነው፡፡በቀጣይ በወንጀል መዝገብ የተላለፈባቸውን ፍርድ እንደ አንድ አባሪ የሰነድ ማስረጃ አድርጎ፣ስርዝ ድልዞችን ሰነዶች አያይዞና የሰው ማስረጃም ቆጥሮ ገንዘቡን የፍትሐብሔር ክስ ከፍቶ ማስመለስ ግድ ነው፡፡የደብሩና የሀ/ስብከቱ የሕግ ክፍሎች ይሐየን ካላደረጉ የነ የማነ አስተዳደር ቁርጠኝነት ላይ ጥያቄ ልናነሳ እንገደዳለን፡፡በሙዳየ-ምጽዋት ቆጠራ፣በፉካ እና በካሕናት አስተዳደር ያየነውን አዎንታዊ ለውጥ በዚህ አስተማሪ ውሳኔ መሰረት የቤ/ክ ገንዘብ ተመልሶ በማየት ጭምር ማየትን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡በነገራችን ላይ በሴኩላሪዝም መርህ የተነሳ በቤ/ክ ውስጥ የሚፈጸም ሙስና በሙስና አዋጅ ሳይሆን በተራ የማጭበርበርና የማታለል ወንጀል አናቅጽ ስለሚዳኝ ነው ቅጣቱ ያነሰው፡፡በአዋጁ ቢሆን በእርግጠኝነት ቅጣቱ ከ10 አመት ያላነሰ ይሆን ነበር–እንደ ብሩ በሚሊዮን መቆጠር!

    6. ወደ ችግሩ ስንመለስ በ10 አመትና በ5 አመት ገደብ እጅግ በወረደ ዋጋ እየተከራዩ ያሉ፤ያውም በጥቂት ከደብር ደብር በሚሸከረከሩ የቤ/ክ ቦታ ቀበኛ ባለጋራዦች፣ባለሱቆች፣መቃብር ቆፋሪዎች(ሰሪዎች) ጋር የሚደረጉ ውሎች ላይ ጥብቅ ፍተሻ፣የኪራይ ቦታ ልኬት፣የውል ፍትሐዊነት፣የበላይ አካል እውቅና፣ያገልግሎት ተገቢነት ላይ ክለሳ ሊደረግ ይገባል፡፡አሳፋሪ ነው፡፡ባዶ ቦታዎች ጥቂት ጊዜ አከራይቶ የተሻለ እና ከቤ/ክ አገልግሎት ጋር የማይጣረስ ግንባታና ኪራይ እንደማካሄድ በነ ነፍሰ-ኄር አቡነ ጳውሎስ ብልህነት በወጣ ካርታ የተገኙ ይዞታዎች እድሜ ልካቸውን ጋራዥ ሆነው ሲቀሩ ማየት ያማል፡፡ባዶ ቦታ አማራጭ ጠፍቶ ቢከራይ እንኳ መሸጋገሪያ እንጅ እንደቋሚ ገቢ ማስገኛ መወሰድ የለበትም፡፡እነ የማነ ይሕን ነገር አጢኑት፡፡አጥቢያዎችም እንደዚያው፡፡ለምሳሌ ጃቲ ኪ/ምሕረት በዚህ መንገድ 10 አመት ሊሆናት ነው፡፡እነ ቡልቡላ መድኃኔዓለም በአሳፋሪ መንገድ ቦታ እየሸነሸኑ ባልረባ ገንዘብ ማከራየትን ገፍተውበታል፡፡ያሳፍራል!

  6. ታዛቢው July 1, 2015 at 8:33 am Reply

    ምሀባው ከሰጠው ቃለምልልስ ለማስታወስ ያሕል…
    አዲስ ጉዳይ፡- ‹‹የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች›› የሚለውን መጽሐፍ ለምን አዘጋጁት?
    በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ገብተኽ ስትመለከተው የምታየው እውነት አለ፡፡ እኔም የሰበካ ጉባኤ ተመራጭ ኾኜ ስሠራ ከዚያ በፊት በፍጹም በቤተ ክርስቲያን ይደረጋል ብዬ የማላስበውን ነገር ታዝቤያለኹ፡፡ እኔ አስቀድሞ በነበረኝ ግምትና እምነት የሚዋሽ አንድ የቤተ ክርስቲያን አባት አለ ብዬ በፍጹም አላምንም ነበር፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ገቢ የሚሰርቅ አገልጋይ ይኖራል ብዬ በጭራሽ አላምንም ነበር፡፡ ይኹን እንጂ በአገልግሎት ላይ ሳለኹ ከዚኽ እምነቴ ጋራ የሚቃረኑ ብዙ ነገሮች ሲፈጸሙ ተመለከትኹ፡፡ በወቅቱ ያጋጠሙኝ በጣም የሚያበሳጩ ነገሮች ስለነበሩ አንዳንዴ እንዲያውም መተኛት ኹሉ ያቅተኛል፡፡
    በነገራችን ላይ ጥፋቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ይኹንና የዚኽ ጥፋት ተካፋዮች ጥቂት ናቸው፡፡ ድርጊቱ ግን የብዙ አባቶችን ስም የሚያጠፋ፣ ለቤተ ክርስቲያናችንም ከባድ ችግርን የሚያመጣ በመኾኑ በተለይ ያሉትን ችግሮች የሚፈጽሙት ጥቂቶች እንጂ ብዙዎች ባለመኾናቸው ይኼ ነገር ለውጥ ያስፈልገዋል፤ የግድ መጽሐፍ መዘጋጀት አለበት ከሚል ውሳኔ ላይ በመድረሴ ነው መጽሐፉን ያዘጋጀኹት፡፡

    አዲስ ጉዳይ፡- ከመጽሐፉ መውጣት በኋላ ያገኙት ምላሽ ምን ይመስላል?

    በመጽሐፌ ዙሪያ ያገኘኹትን ምላሽ በዝርዝር መግለጹ ያስቸግራል፡፡ ይኹን እንጂ በደፈናው በአንድ በኩል ‹‹ጥሩ ነው፤ ይኼ የአንተ መጽሐፍ እንደመነሻ ኾኖ ወደፊት ለሚወሰዱት እርምቶች ማስተካከያ የሚወሰድባቸውን መንገዶች ዕድል ይፈጥራል›› በማለት ከታላላቅ አባቶች አንሥቶ የእኔን መጽሐፍ የደገፉና ያበረታቱኝ ነበሩ፡፡ ከዚኽ ተቃራኒው ደግሞ እርምቱ ሲወሰድ ጥቅማችን ይነካብናል ያሉት አካላት ግን በጣም ተቆጥተውና ተበሳጭተው ነበር፡፡

    አዲስ ጉዳይ፡- መጽሐፍዎ ለምን የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ አተኮረ?

    እኔ በግሌ እንደማስበው ከኾነ እውነታው በተለይ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ተጨባጭ ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን እንዲኽ ያለ ነገር ሲጻፍ የግድ ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡ እኔም በእጄ ያለኝ ተጨባጭ ማስረጃ የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በመኾኑ ጉዳዩን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋራ ያያዝኹት ለዚኹ ነው፤ ደግሞም ጉዳዩ ሊያስከሥሥና ኾነ ተብሎ የተለያዩ ስሞች ሊያሰጥ እንደሚችል ዐውቃለኹ፡፡ በዚኽ የተነሣ ድንገት ይኼ ዓይነቱ ክሥ ቢቀርብብኝ ራሴን ነፃ ለማውጣት ይኹን ለቀረበልኝ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የምችለው እጄ ላይ በሚገኝ ተጨባጭ ማስረጃ በመኾኑ ጉዳዩ በአንድ አጥቢያ ዙሪያ እንዲያተኩር አድርጌያለኹ፡፡

    አዲስ ጉዳይ፡- በሌሎች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትስ ችግሩ ለመኖሩ ርግጠኛ ነዎት?

    በሚገባ! በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የተለያዩ ጥናቶችን አድርጌ ነበር፡፡ ይኹን እንጂ የያዝኋቸው መረጃዎችን እንጂ ማስረጃዎቹ እጄ ስላልገቡ ነው መጽሐፉ ላይ ያልተካተቱት፡፡
    አዲስ ጉዳይ፡- ማስረጃ አለኝ ባሉት አንድ አጥቢያ ላይ ማተኮርዎ ጥያቄ እንዳይነሣብዎ አድርጓል?
    በርግጥ መጽሐፉ እንደወጣ ታስሬያለኹ፡፡ በይፋ ከሣሽ እኛ ነን ያሉ ሰዎች በፍጹም ራሳቸውን ግልጽ ባያደርጉም እኔ ግን ለቀናት ታስሬ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በእስር ቤት ረጅም ጊዜ እንዳልታሰር የኾንኩት እጄ ላይ ተጨባጭ ማስረጃ በመኖሩ የተነሣ ነው፡፡ በፖሊስ በታሰርኹ በአራተኛው ቀን ጉዳዩ የማያሳስር በመኾኑ ውጣ አሉኝ፡፡ እኔ ግን ‹‹አይ ፍ/ቤት ቀጠሮ ሰጥቶኛል፣ አልወጣም፡፡ ቀድሞስ ምን ብላችኹ አሠራችኹኝ? አኹንስ ምን ብላችኹ ትለቁኛላችኹ?›› ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ እነርሱ ግን የለም፣ ብትወጣ ይሻላል ብለው አንዳንድ ነገር ለማስረዳት ከሞካከሩ በኋላ የፍ/ቤት ቀጠሮ ከመድረሱ አስቀድሞ እንድወጣ አድርገዋል፡፡

    አዲስ ጉዳይ፡- የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ችግር ሲነሣ ሃይማኖቱ እንደተነካ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፡፡ ከዚኽ ጋራ በተያይዘ የገጠምዎ ነገር አለ?

    ምን አለ መሰለኽ፣ እኔ በዋናነት የጻፍኹት የአስተዳደሩን ጉዳይ የተመለከተ ነው፡፡ ይኹን እንጂ መጽሐፉን ሳያነቡ እንዲኹ በስማ በለው ተነሣስተው ደውለው ለምን እንዲኽ ታደርጋለኽ ብለው የተናገሩኝ አሉ፡፡ በርካቶች ግን እኔ የጻፍኹት ኹሉም የሚያውቀው በመኾኑ መጽሐፍኽ ለለውጥ እንደመነሻ ያገለግላል በማለት በተለያዩ መንገዶች ምስጋናቸውን ገልጸውልኛል፡፡

    አዲስ ጉዳይ፡- አስተዳደሩን መውቀስ ሃይማኖቱን ከመተቸት የተለየ መኾኑን ለሰዎች በምን መንገድ ሊያስረዱ ይችላሉ?

    ሃይማኖት ማለት ከኹሉ አስቀድሞ በኾነ ወቅት ወይም በአንድ አስተዳደር ብቻ የሚገለጽ አለመኾኑ መታወቅ አለበት፡፡ ሃይማኖት ከአስተዳደሩ የተለየ በጣም ጥልቅ ነገር ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት ከአንድ ግለሰብ ኾነ ከጥቂት ሰዎች አመራር የተለየና የራሱ የኾነ ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት፣ ባህልና ሥርዓት ያለው መኾኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በሥነ ምግባር ደረጃ እኔን ጨምሮ ኹሉም ሰው ችግር ሊኖርብን ይችላል፡፡ ይኹንና ይኼ የሥነ ምግባር ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በመነጋገርና ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ ነው፡፡ በመኾኑም ስለ አስተዳደር ጉዳዮች ሲነሣ ነገሩ የሃይማኖት ሳይኾን የሥነ ምግባር መኾኑ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚኽ ውጭ ግን አኹን እኔ ባየኋቸው የተለያዩ ነገሮች ተካፋይ በነበሩ አባቶች ላይ ምንም ዓይነት የሃይማኖት ችግር በፍጹም አላየኹም፡፡
    በርግጥ በተወሰነ ደረጃ አንዳንዶቹ ሃይማኖት አላቸው ወይም ሌሎቹን ደግሞ በርግጥ ክህነት የተቀበሉ ናቸው ወይ? በሚል ጥያቄ ያነሣኹበት ኹኔታ አለ፡፡ የኾነው ኾኖ ግን አብዛኞቹ በሃይማኖታቸው ችግር የሌለባቸው ካህናት ናቸው፤ እውነተኛ አገልጋዮችም አሉ፡፡ ይኹን እንጂ በአስተዳደሩ ላይ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች የሥነ ምግባር ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ ይህን ችግር መፍታት አለብን፡፡ ይህን የሥነ ምግባር ችግር ደግሞ አንዳንዶቹ ወደውት ሳይኾን ተገደው የገቡበት ሊኾን ይችላል፡፡ የነበረው ሥርዐት እነርሱ በፈለጉት መንገድ አላስኬድ ብሏቸው ወደዚኽ መንገድ ተገደው የገቡበት ሰዎችም አሉ፡፡
    ስለዚኽ ለእኔ አስተዳደሩን ከሃይማኖቱ ጋራ ማቀላቀል ተገቢ አይኾንም፡፡ በተለይ ደግሞ አንድ አባት አስተዳደር ላይ ስለተቀመጡ ብቻ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴያቸውንና የሚያስተላልፏቸውን ውሳኔዎች በሙሉ የሃይማኖቱ አካል ተደርጎ መታሰብ አይኖርበትም፡፡
    ምንጭ፡- https://haratewahido.wordpress.com/2014/03/23/%E1%8C%8A%E1%8B%9C-%E1%8B%AD%E1%8D%88%E1%8C%85-%E1%8B%AD%E1%8A%BE%E1%8A%93%E1%88%8D-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8C%82-%E1%88%88%E1%8B%8D%E1%8C%A1-%E1%8A%A0%E1%8B%AD%E1%89%80%E1%88%AC-%E1%8A%90%E1%8B%8D/

    ይሄ ቀዝቃዛ ወላፈን የሆነ ዳሞቴ እንዴት አኮራኝ!!የሚያናድደው ምሀባውንና አቡነ ቶማስን ያፈራችውን “ዳሞት” መጠሪያው አድርጎ ዘወትር በየብሎጉ ወጭና ወራጁን በጭፍንነት እና በረጃጃም ዓረፍተ-ነገር የሚሞልጭ ልጅ በቅሎ ያበሳጨኛል፡፡

    • ዳሞት July 1, 2015 at 7:07 pm Reply

      ለታዛቢው
      አስቀድሜ የኔን ግንዛቤ ስለመረጃና ማስረጃ ልናገር።
      መረጃ ከሰውም ይሁን ከሚዲያ የሚገኝ ነው። መረጃን ተመርኩዞ የራስን እይታ መናገርም ይሁን መፃፍ ይቻላል። ማስረጃ መረጃን ካቀረበው አካል የሚገኝ ወይም ድርጊቱ ከተፈፀመበት ወይም ከተከናወነበት ቦታ ያለ ነው። ማስረጃን ምንም እንሿን ስለሚናገሩት እውነታ ወይም ስለሚፅፉት ታሪክ ትክክለኛነት ለማስረገጥ አያይዘው ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም ዋናው አሥፈላጊነቱ ግን በህግአንፃር ስለሚደረግ እንቅስቃሴ ነው የድርጊቱን መፈፀም ለማሳየትና ብይን ለመሥጠት ነው።
      ማስረጃ ከሌለ በመረጃ መናገር፣ አሥተያየት መሥጠትና መጻፍ አይቻልም የሚለው ግን ትክክል አይደለም ለኔ። እንዲህ የሚሉ አካላት በራሳቸው ችግር ያለባቸውና የተፈፀመው ድርጊት መረጃን ተመርኩዙ እውነታው እንዳይገለፅ የሚፈልጉና በመረጃው አንጻር የሚመጣን ወቀሳም ይሁን አመለካከት ለማጨለምና ላለመቀበል ነው።
      መረጃው የቀረበበት አካልም ይሁን ክፍል መረጃው ትክክል አይደለም ካለ መናገርና የመረጃውን ትክክል አለመሆን መግለፅ ተገቢ ነው። ስለ መረጃና ማስረጃ ይህን ካልኩኝ ወደ ሌላው ልሻገር፦
      ታዛቢው ወጭ ወራጂ የሚል ገለፃ ተናግሯል። ማን ወጭ፤ ማን ደግሞ ወራጅ እንደሆነ የሚያውቀው እሱ ስለሆነ ለሱ ልተወው። ነጀር ግን “ወጭ ወራጁን በጭፍን ይሞልጫል” የሚል ነው የእኔን የእይታ ፅሐፌን የተቸውና በእኔም የተበሳጨው።
      በመጀመሪያ ጭፍን የሚለውን ቃል የትና እንዴት መጠቀም እንዳለበት ያወቀውም አይመስለኝም። ጭፍንነት እየታየበት ያለውበእኔ ግንዛቤ ታዛቢው እራሱ ነው። ምክንያቱም አንድ ግለሰብ በቤተክርስቲያኗ አገልግሎት ውስጥ በነበረበት ጊዜ የተመለከተው በመጽሐፍ በመጻፉ በዘራፊዎቹ ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነት ብይን የእሱ ውጤት ነው ይልና ሌሎችን ግን ያገላል። ቃለመጠየቅ ያደረገው ብሎ ያያዘው ላይም የመጽሐፉ ፀሐፊ ፃፍኩ አለ እንጂ ወደ ሀግ ወሰድሿቸውም ሆነ ከሌሎች ጋር ጥፋተኞች እንዲጠየቁ ሰራሁ አላለም። በእርግጥ በመጽሐፍ መረጃውን ማውጣቱ ጉዳዮን ወደ ህግ ለመውሰድ የራሱን አስተዋጽዎ እንዳለው ይታመናል።ሆኖም የእሱ ውጤት ብቻ ነው ብሎ ወገብን መያዝ ጭፍንነት ነው። ሌላም ልጨምር፦ ስለ ዘራፊዎችና ስለ መልካም አስተዳደር ችግሮች ሲነገር ዘረፋውም ችግሩም የድሮ ነው በሚል ቢሒል የአሁኖቹ ንፁህ ናቸው ለማለት ይሞክራል። ሌላውን እንተወውና የአሁኖቹ የአስዳደር ሐላፊዎች የተሾሙበት አሿሿም እንሿን የቤተክርስቲያኗን ህግ የጣሰ ነው። ይህን ትክክል ብሎ ጥብቅና መቆም በራሱ ጭፍንነት ነው።
      ዘረፋውም ሆነ የአስተዳደር ችግሩ የተጀመረው ቀድሞ ቢሆንም ዘራፊዎቹም የአስተዳደር ችግሩም እንዳይወገዱ እንቅፋት የሆኑት ጊዜው የኛ ነው ባዮች ናቸው። ካሁን የነበሩት የአስተዳደር ሐላፊዎች ስራቸውን እንዳይሰሩ ከዛቻ ጀምሮ የተለያዮ መሰናክሎች ሲጋረጡባቸው የነበረና ጊዜ የኛነው በሚሉት ካለ አግባብ ከሐላፊነታቸው ሲነሰ ነው ያለፉት። ታዲያ ይህን ሁሉ የቤተክርስቲያኗን ህግ የጣሰ አካሔድ ትክክል ነው ማለትና ዘራፊዎቹን ከማንቆለጳጰስ በላይ ጭፍንነት አለ እንዴ።
      በነገራችን ላይ ከቤተክርስቲያኗ አሰራር ውጭ በህገወጥ መንገድ የተሾሙት አካላት እየሰሩ ያሉት ከትናንት ጀምሮ እስከ ዛሬ በመዝረፍና ቤተክርስቲያንን በማስነቀፍ ካሉት ጋር በዋናነት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
      ሌላኛው ሙለጫ ነው። እውነቱ ሲነገር ሙለጫ ዘረኝነቱ ሲንቆለጳጰስና ሲፎከርበት ግን ጽድቅና የበጎ ሥራ ትሩፋት ማድረግ በራሱ ጭፍንነትና የክፉ ድርጊት ተባባሪነት ነው። እኔ የታባቱ ወይም ሽንታም ብዬ አባት እንደሌለው ወይም ሰው ሆኖ የማይሸና ያለ በማስመሰል አልዘለፍኩም። ለክርስቲያን መመኪያቸው እግዚአብሔ፤ ሐይላቸውም እሱ ነው። መወለዳቸው መምጣታቸውም ከእግዚአብሔር ነው። ነገር ግን ክርስቲያን በሰው በጉልበተኛ፣ በዘሩ፣ በመሳሪያ ብቻ በምድራዊ ነገር ሲታበይና ሲመካ ጥፋቱ ሊነገረውና ሊገሰፅ ይገባዋል። ካል ሰማና በማናለብኘቱ ከቀጠለ ተግባሩ ክርስቶስን ከሰቀሉት ሐዋርያትን አሳደው ከገደሉት የተለየ አይደለምና መምህር መምህር ወይም አለቃ አለቃ ልለው አልችልም።
      በመጨረሻ እንደምትበሳጭም ተናግረሃል ደግሞ በሌላ ቦታ ካህን ነኝ ለዛውም ትሁት ካህን ነኝ ብለህ ሥለ ራስህ እየመሰከርህም ስታስታውቅ ነበር። ታዲያ ትሁት ካህን ይበሳጫል እንዴ? ካህን እኮ ልጅ ሲያጠፋ እየታገሰ ከጥፋት እንዲመለሱ ይመክር፣ ይገስፅና ያስተምራ። ነው መገሰፅ ማለት መበሳጨት ነው እንዴ ላንተ ለታዛቢው? ለእኔ ግን መገሰፅ ማለት መበሳጨት አይደለም እያልኩ ላብቃ።

  7. ታዛቢው July 1, 2015 at 10:07 am Reply

    Dear administrator of hara, please, respect our comment as usual
    1.ተው፡፡ተው፡፡የበሬውም ምስጋና ለፈረሱ አትስጡ፡፡ሐራዎችም እነዚህን ፍርድ የተላለፈባቸው ሰዎች ስማቸውን ስትጠሩት ሰምተን አናውቅም፡፡ይሕ ፍትሕ የተገኘው ምሀባው ዓለሙ ከበደ የተባለ የቀድሞ የማኅደረስብሐት ቅድስት ልደታ ሰ/ት/ቤት ሰብሳቢና የደብሩ ሰበካ ጉባኤ አባል በነበረ ልጅ እጅግ ቆራጥና በማስተዋል የተሞላ ርምጃ መነሻነት ነው፡፡ ቁልጭ ያለ የሰነድ ማስረጃ ሰበሰበ፡፡ የፍትሑ ጎማ ቀስ ብሎ ሲሽከረከር ቆይቶ መድረስ ባለበት ጊዜ ደረሰ፡፡

    2.ሌላ ሊታወቅ የሚገባው ይሕ ችግር ሲከሰት የነበረው አመራር የአሁኑ የነ ሊቀማዕምራን የማነ እና የነ መጋቤ ብሉይ አእመረ አይደለም፡፡

    3.ከዚህ መዝገብ ሁሉም ሰው ሊማርበት ይገባል፡፡ሀ/ስብከቱ የሞዴል 64 ያላግባብ ከነ ቃለጉባኤ በጸሐፊ እጅ እየሆነ ቀሪና በራሪው በስርዝ ድልዝ የሚጨማለቅበትን ሥርዓት ቢያንስ ከቆጠራ በኋላ በግልጽ በሚነበብ ቃለጉባኤ መዝግቦ ሞዴሉን ወደ ጸሐፊ ሳይሆን ወደመዝገብ ቤት የማስገባትና የሰ/ጉባኤ አባላትም ሆነ የበላይ ኦዲተሮች በማንኛውም ጊዜ ሲመጡ እንዲያገኙት የሚያደርግ ሥርዓት ይዘርጋ፡፡ይሕ ጅምር በንቡረዕድ አባ ገብረማርያም ተጀምሮ ባጭር የተቀጨ ነው፡፡የቦታ ኪራዮች ለምሳሌ 2ሺህ ካሬ ተከራየ ይባልና ተከራዩ ተመሳጥሮ የሚያጥረው ግን 7ሺህ ሊሆን ይችላል፡፡የንብረት ሺያጭ ነገር እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ምንም ሥርዓት የሌለውና በጥቂት ሞኖፖሊስቶች ኔትወርክ የተተበተበ ነው፡፡የ50ሺህ ብር የይስሙላ ጨረታ ይወጣል ሲሸጥ ግን የ150ሺህ ብር ንብረት ሆኖ ይገኛል፡፡አስተዳደሩ ይሄን ሁሉ ማየት ይጠበቅበታል፡፡የጨረታው ይስሙላ ይፈተሸ፡፡

    4.ይህን ድርጊት ለማስቆም ቅን ልቦና ያላችሁ ምዕመናን፣ሰ/ተማሪዎችና ካሕናት ጉዳዩን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር፣አስቀድሞ ስም ከመለጠፍና በመደዳ ከተሐድሶ ጋር እያያዛችሁ ኮንስፓይሬሲ ከመቀመር ማስረጃ ሰብስቡ፡፡ተጨባጭ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ሰብስቡ፡፡በተለይ ሰበካ ጉባኤ አባላት ሰ/ተማሪዎችና ምዕመናን ወካሕናት እናንተ ተቀናጅታችሁ ከሰራችሁ ብዙ ዘረፋና ንጥቂያ ማቆም ትችላላችሁ፡፡ችግሩ አጀንዳውን አስቀድማችሁ ወሬ በማጮህ በቀሳጥያኑ ወጥመድ ራሳችሁን ትከታላችሁ እነ አጅሬም ሰነድ አጥፍተው ቁጭ ይላሉ፣ አልፎ ተርፎም ሀቃችሁን በበለው ፍለጠው ኃይል ተሞላበት አካሄድ ትቀጩታላችሁ፡፡ ከሚገባችሁ ጊዜና የእድሜ ገደብ በላይ የሰ/ት/ቤቱን አመራር ሙጭጭ ያላችሁበት ጎልማሶች ደግሞ ራሳችሁ በካሕናት ማኅል ግሩፕ ፈጥራችሁ ያልተጣላችሁ ሰው ቢመዘብር አይሰማችሁም፤ሱቃችሁ ኢዲት ይደረግ ካልተባለ በቀር የቤ/ክ ህመም አይሰማችሁም፤አልፎ ተርፎም ራሳችሁን በጣም በማጋነን ተራውን ካሕን ወደ ማቃለልና ችላ ወደማለት ስለምታዘነብሉ ካሕኑ ከእናንተ ጋር ለመሰለፍ አይደፍርም፡፡ስለዚህ ይሕን የቸከ አመራር ፈትሾ በማስረጃ የተሞላ አቤቱታ በመያዝ፣ግንኙነትን ጤናማ በማድረግ፣አካሄድን ካልተገባ አነጋገርና ከኃይል ተግባር በማራቅ ከተሄደ የቤ/ከ መዋቅር መፍትሄ ባይሰጥ እንኳ ድርጊቱ ደረቅ ወንጀል ስለሆነ እንዲህ እንዳሁኑ በዳዮችን በፍርድ አደባባይ ማቆም ይቻላል፡፡

    5.አሁን ሰዎቹ በወንጀል ተፈርዶባቸዋል፡፡ያ ማለት ግን የወሰዱትን ገንዘብ መልሰዋል ማለት አይደለም፡፡ስለዚህ ቤ/ክ ልታገኝ የሚገባትን የመጨረሻ ፍትሕ ገና አላገኘችም ማለት ነው፡፡በቀጣይ በወንጀል መዝገብ የተላለፈባቸውን ፍርድ እንደ አንድ አባሪ የሰነድ ማስረጃ አድርጎ፣ስርዝ ድልዞችን ሰነዶች አያይዞና የሰው ማስረጃም ቆጥሮ ገንዘቡን የፍትሐብሔር ክስ ከፍቶ ማስመለስ ግድ ነው፡፡የደብሩና የሀ/ስብከቱ የሕግ ክፍሎች ይሐየን ካላደረጉ የነ የማነ አስተዳደር ቁርጠኝነት ላይ ጥያቄ ልናነሳ እንገደዳለን፡፡ በሙዳየ-ምጽዋት ቆጠራ፣በፉካ እና በካሕናት አስተዳደር ያየነውን አዎንታዊ ለውጥ በዚህ አስተማሪ ውሳኔ መሰረት የቤ/ክ ገንዘብ ተመልሶ በማየት ጭምር ማየትን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡

    በነገራችን ላይ በሴኩላሪዝም መርህ የተነሳ በቤ/ክ ውስጥ የሚፈጸም ሙስና በሙስና አዋጅ ሳይሆን በተራ የማጭበርበርና የማታለል ወንጀል አናቅጽ ስለሚዳኝ ነው ቅጣቱ ያነሰው፡፡ በአዋጁ ቢሆን በእርግጠኝነት ቅጣቱ ከ10 አመት ያላነሰ ይሆን ነበር–እንደ ብሩ በሚሊዮን መቆጠር!

    6. ወደ ችግሩ ስንመለስ በ10 አመትና በ5 አመት ገደብ እጅግ በወረደ ዋጋ እየተከራዩ ያሉ፤ያውም በጥቂት ከደብር ደብር በሚሸከረከሩ የቤ/ክ ቦታ ቀበኛ ባለጋራዦች፣ባለሱቆች፣መቃብር ቆፋሪዎች(ሰሪዎች) ጋር የሚደረጉ ውሎች ላይ ጥብቅ ፍተሻ፣የኪራይ ቦታ ልኬት፣የውል ፍትሐዊነት፣የበላይ አካል እውቅና፣ያገልግሎት ተገቢነት ላይ ክለሳ ሊደረግ ይገባል፡፡አሳፋሪ ነው፡፡ባዶ ቦታዎች ጥቂት ጊዜ አከራይቶ የተሻለ እና ከቤ/ክ አገልግሎት ጋር የማይጣረስ ግንባታና ኪራይ እንደማካሄድ በነ ነፍሰ-ኄር አቡነ ጳውሎስ ብልህነት በወጣ ካርታ የተገኙ ይዞታዎች እድሜ ልካቸውን ጋራዥ ሆነው ሲቀሩ ማየት ያማል፡፡ባዶ ቦታ አማራጭ ጠፍቶ ቢከራይ እንኳ መሸጋገሪያ እንጅ እንደቋሚ ገቢ ማስገኛ መወሰድ የለበትም፡፡እነ የማነ ይሕን ነገር አጢኑት፡፡አጥቢያዎችም እንደዚያው፡፡ለምሳሌ ጃቲ ኪ/ምሕረት በዚህ መንገድ 10 አመት ሊሆናት ነው፡፡እነ ቡልቡላ መድኃኔዓለም በአሳፋሪ መንገድ ቦታ እየሸነሸኑ ባልረባ ገንዘብ ማከራየትን ገፍተውበታል፡፡ያሳፍራል!

    7. ሐራዎች ደግሞ ወደ አንድ ወገን አዘንብላችሁ ምን ቢያጠፉ ስማቸውን የማታነሷቸው ሰዎች አሉ፡፡ በዚያው ልክ በሌሉበት ቦታ ሳይቀር ስማቸውን የምታብጠለጥሏቸው አሉ፡፡ ለእውነት የቆምን የቤ/ክ ወታደሮች ነን ካላችሁ ጎጥና ብሔር ሳትለዩ የሁሉንም አቅርቡ፡፡ ከሙስና የጸዳ ብሔር የለም፡፡ ሁሉም በድሏል፡፡ የምትጠቀሙዋቸው ቃላት ወደ ጽርፈት ስለሚያዘነብሉ ነገራችሁን ግለሰባዊ ጥላቻ አስመስሎ ሐቃችሁን እየበላባችሁ ነው፡፡አስቡበት፡፡ፍትሀዊ ሁኑ፡፡

  8. Anonymous July 1, 2015 at 1:31 pm Reply

    የመውጊያውን ብረት ቢቃወሙ በእራሳቸው ይብሳል።

  9. Anonymous July 2, 2015 at 4:06 pm Reply

    በእውኑ ጌታችን መድሃኒታችን ሐወርያትን ሲሾም ሁለት ጫማ ሁለት ልብስ እንዳይኖረቸው ነበር የዘመኑ ሐወርያ ግን ሆዱ አምላኩ፣ እንቅልፋም ስብከቱ ፣ውድመት ልማቱ ያሳዝናል

  10. Shitahun Minwyelet July 8, 2015 at 3:47 pm Reply

    እግዚአብሔር አገልገግሎታችሁን ይባርክ !!!.

    ከገ/ስላሴ

  11. Anonymous June 29, 2016 at 11:45 pm Reply

    ኡኡኡ ምን ጉድ ነው

Leave a comment