ጊዜ ይፈጅ ይኾናል እንጂ ለውጡ አይቀሬ ነው

(አዲስ ጉዳይ፤ ቅጽ ፰ ቁጥር ፻፰፤ መጋቢት ፳፻፮ ዓ.ም.)

 • ሃይማኖት ከአስተዳደሩ የተለየ በጣም ጥልቅ ነገር ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት ከአንድ ግለሰብ ኾነ ከጥቂት ሰዎች አመራር የተለየና የራሱ ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት፣ ባህልና ሥርዓት ያለው መኾኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
 • በሥነ ምግባር ደረጃ እኔን ጨምሮ ኹሉም ሰው ችግር ሊኖርብን ይችላል፡፡ ይኹንና ይኼ የሥነ ምግባር ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በመነጋገርና ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ ነው፡፡ ስለ አስተዳደር ጉዳዮች ሲነሣ ነገሩ የሃይማኖት ሳይኾን የሥነ ምግባር መኾኑ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚኽ ለእኔ አስተዳደሩን ከሃይማኖቱ ጋራ ማቀላቀል ተገቢ አይኾንም፡፡
 • ዘመኑን ካልዋጀን ሌላው ቀርቶ የዘመኑ ትውልድ አብሮን ሊሔድ አይችልም፡፡ ትውልዱን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋራ ለማስቀጠል ከፈለግን አስተዳደራዊ ሥርዓታችንን የግድ ዘመናዊ ማድረግ አለብን፡፡ ሃይማኖት አንዴ ተሰጥቶ ያለቀ ስለኾነ የምንጨምርበት ኾነ የምንቀንስበት ነገር አይኖርም፡፡ አስተዳደራችን ግን በየጊዜው ከሚሻሻለው ዕውቀት ጋራ ተዘምዶ መሻሻል አለበት፡፡
 • የአንድ ደብር ጸሐፊ የኾነ ሰው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከኹለት ሺሕ ብር በማይበልጥ ደመወዝ ኹለት ሦስት መኪና፣ ኹለት የመኖሪያ ቤቶች በፍጹም ሊኖረው አይችልም፡፡ የአንድ ወር ደመወዛቸው ለመኪና ነዳጅ ወጭ የማይሸፍንላቸው አገልጋዮች መኪና እየለዋወጡ ሲይዙ በድሎት ሲኖሩ፣ የልጆችን ይኹን የራሳቸውን ወጭዎች ያለችግር ሲሸፍኑ ይኼ ነገር ከየት መጣ ያሰኛል፡፡
 • ቤተ ክርስቲያን አኹን እየተጠቀመችበት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ዓለም በ፲፯ኛው መ/ክ/ዘ የተወውንና የነጠላ ሒሳብ አሠራር (single entry) የሚባለውንና በሞዴል የሚሠራ የሒሳብ አሠራር ነው፡፡ በዓለም ላይ እንዲኽ ዓይነት የሒሳብ አሠራር የሚከተል ምንም ተቋም የለም፡፡
 • የነጠላ ሒሳብ አሠራር ወጪን ወጪ ይላል እንጂ ምክንያቱን አይናገርም፡፡ ስለዚኽ ወጪን ከነምክንያቱ ገቢን ከነምንጩ የሚጠቅሰው የኹለትዮሽ(ደብል) ሒሳብ አሠራር ሥርዓት የላትም፡፡ በመኾኑም ይኼን ተረድቶ የፋይናንስ ሥርዓቱን በአፋጣኝ ማዘመን ይገባል፡፡
 • ካሽ ሬጅስተር በመጠቀም እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ያለውን አቅም የላይኛው አስተዳደር አካል በሚገባ ለማወቅና ከፍተኛ ብክነትን ለማስወገድ ይችላል፡፡ አኹን እየጠፋ ያለውኮ ብሩ ብቻ ሳይኾን ሰነዱም ጭምር ነው፡፡ የካሽ ሬጅስተርን መረጃ ግን ማጥፋት ስለማይቻል የቁጥጥር ሥርዓትን ማጉላትና ተጠያቂነትን ማስፈን ይቻላል፡፡
 • የተጀመሩትን የለውጥ እንቅስቃሴዎች የሚቃወሙት በአስተዳደር ላይ ያሉ ጥቂት ሰዎች ናቸው፤ አስተዳደር ላይ ኾነውም ለውጡን የሚደግፉ አሉ፡፡ ምናልባት ጊዜ ይፈጅ ይኾናል እንጂ ችግሩ መፈታቱ አይቀሬ ነው፡፡

መምህር ምሐባው ዓለሙምሐባው ዓለሙ ተወልደው ያደጉት በቀድሞው አጠራር በጎጃም ክፍለ ሀገር በደጋ ዳሞት ወረዳ ሲኾን እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ያለውን ትምህርታቸውን በትውልድ አካባቢያቸው ተከታትለዋል፡፡ ከዚኽ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአካውንቲንግ ዘርፍ አጠናቀዋል፡፡ በተለያዩ ተቋማት በድምሩ የ12 ዓመታት የሥራ ልምድ ያላቸው አቶ ምሐባው ዓለሙ በማስተማር፣ በኦዲተርነትና በሌሎችም ዘርፎች በተማሩበት መስክ የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ከልጅነታቸው አንሥቶ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት በመማር ካደጉ በኋላም በሰንበት ት/ቤት እና በተለያዩ ሓላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ከማገልገላቸው ጋራ በተያያዘ ያላቸውን ዕውቀት መሠረት በማድረግ በተለይ በማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ ልዩ ትኩረት ያደረገ ‹‹የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች›› በሚል ርእስ የተዘጋጀ መጽሐፍ በማሳተም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ይስተዋላል ያሉትን በርካታ የአስተዳደር፣ የፋይናንስና የሰው ኃይል አስተዳደር ችግሮች ጠቁመዋል፡፡

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰፊ ትኩረት ከተቸረው የመዋቅርና የአስተዳደራዊ ለውጥ እንቅስቃሴ ጋራ በተያያዘ በቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ የአካውንቲንግ መምህር ከኾኑትና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ከኾኑት አቶ ምሐባው ዓለሙ ጋራ ቀጣዩን ቆይታ አድርገናል፡፡

*                                *                               *

አዲስ ጉዳይ፡- ‹‹የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች›› የሚለውን መጽሐፍ ለምን አዘጋጁት?

በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ገብተኽ ስትመለከተው የምታየው እውነት አለ፡፡ እኔም የሰበካ ጉባኤ ተመራጭ ኾኜ ስሠራ ከዚያ በፊት በፍጹም በቤተ ክርስቲያን ይደረጋል ብዬ የማላስበውን ነገር ታዝቤያለኹ፡፡ እኔ አስቀድሞ በነበረኝ ግምትና እምነት የሚዋሽ አንድ የቤተ ክርስቲያን አባት አለ ብዬ በፍጹም አላምንም ነበር፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ገቢ የሚሰርቅ አገልጋይ ይኖራል ብዬ በጭራሽ አላምንም ነበር፡፡ ይኹን እንጂ በአገልግሎት ላይ ሳለኹ ከዚኽ እምነቴ ጋራ የሚቃረኑ ብዙ ነገሮች ሲፈጸሙ ተመለከትኹ፡፡ በወቅቱ ያጋጠሙኝ በጣም የሚያበሳጩ ነገሮች ስለነበሩ አንዳንዴ እንዲያውም መተኛት ኹሉ ያቅተኛል፡፡

በነገራችን ላይ ጥፋቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ይኹንና የዚኽ ጥፋት ተካፋዮች ጥቂት ናቸው፡፡ ድርጊቱ ግን የብዙ አባቶችን ስም የሚያጠፋ፣ ለቤተ ክርስቲያናችንም ከባድ ችግርን የሚያመጣ በመኾኑ በተለይ ያሉትን ችግሮች የሚፈጽሙት ጥቂቶች እንጂ ብዙዎች ባለመኾናቸው ይኼ ነገር ለውጥ ያስፈልገዋል፤ የግድ መጽሐፍ መዘጋጀት አለበት ከሚል ውሳኔ ላይ በመድረሴ ነው መጽሐፉን ያዘጋጀኹት፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ከመጽሐፉ መውጣት በኋላ ያገኙት ምላሽ ምን ይመስላል?

በመጽሐፌ ዙሪያ ያገኘኹትን ምላሽ በዝርዝር መግለጹ ያስቸግራል፡፡ ይኹን እንጂ በደፈናው በአንድ በኩል ‹‹ጥሩ ነው፤ ይኼ የአንተ መጽሐፍ እንደመነሻ ኾኖ ወደፊት ለሚወሰዱት እርምቶች ማስተካከያ የሚወሰድባቸውን መንገዶች ዕድል ይፈጥራል›› በማለት ከታላላቅ አባቶች አንሥቶ የእኔን መጽሐፍ የደገፉና ያበረታቱኝ ነበሩ፡፡ ከዚኽ ተቃራኒው ደግሞ እርምቱ ሲወሰድ ጥቅማችን ይነካብናል ያሉት አካላት ግን በጣም ተቆጥተውና ተበሳጭተው ነበር፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- መጽሐፍዎ ለምን የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ አተኮረ?

እኔ በግሌ እንደማስበው ከኾነ እውነታው በተለይ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ተጨባጭ ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን እንዲኽ ያለ ነገር ሲጻፍ የግድ ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡ እኔም በእጄ ያለኝ ተጨባጭ ማስረጃ የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን በመኾኑ ጉዳዩን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋራ ያያዝኹት ለዚኹ ነው፤ ደግሞም ጉዳዩ ሊያስከሥሥና ኾነ ተብሎ የተለያዩ ስሞች ሊያሰጥ እንደሚችል ዐውቃለኹ፡፡ በዚኽ የተነሣ ድንገት ይኼ ዓይነቱ ክሥ ቢቀርብብኝ ራሴን ነፃ ለማውጣት ይኹን ለቀረበልኝ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የምችለው እጄ ላይ በሚገኝ ተጨባጭ ማስረጃ በመኾኑ ጉዳዩ በአንድ አጥቢያ ዙሪያ እንዲያተኩር አድርጌያለኹ፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- በሌሎች አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትስ ችግሩ ለመኖሩ ርግጠኛ ነዎት?

በሚገባ! በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የተለያዩ ጥናቶችን አድርጌ ነበር፡፡ ይኹን እንጂ የያዝኋቸው መረጃዎችን እንጂ ማስረጃዎቹ እጄ ስላልገቡ ነው መጽሐፉ ላይ ያልተካተቱት፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ማስረጃ አለኝ ባሉት አንድ አጥቢያ ላይ ማተኮርዎ ጥያቄ እንዳይነሣብዎ አድርጓል?

በርግጥ መጽሐፉ እንደወጣ ታስሬያለኹ፡፡ በይፋ ከሣሽ እኛ ነን ያሉ ሰዎች በፍጹም ራሳቸውን ግልጽ ባያደርጉም እኔ ግን ለቀናት ታስሬ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በእስር ቤት ረጅም ጊዜ እንዳልታሰር የኾንኩት እጄ ላይ ተጨባጭ ማስረጃ በመኖሩ የተነሣ ነው፡፡ በፖሊስ በታሰርኹ በአራተኛው ቀን ጉዳዩ የማያሳስር በመኾኑ ውጣ አሉኝ፡፡ እኔ ግን ‹‹አይ ፍ/ቤት ቀጠሮ ሰጥቶኛል፣ አልወጣም፡፡ ቀድሞስ ምን ብላችኹ አሠራችኹኝ? አኹንስ ምን ብላችኹ ትለቁኛላችኹ?›› ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ እነርሱ ግን የለም፣ ብትወጣ ይሻላል ብለው አንዳንድ ነገር ለማስረዳት ከሞካከሩ በኋላ የፍ/ቤት ቀጠሮ ከመድረሱ አስቀድሞ እንድወጣ አድርገዋል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ችግር ሲነሣ ሃይማኖቱ እንደተነካ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፡፡ ከዚኽ ጋራ በተያይዘ የገጠምዎ ነገር አለ?

ምን አለ መሰለኽ፣ እኔ በዋናነት የጻፍኹት የአስተዳደሩን ጉዳይ የተመለከተ ነው፡፡ ይኹን እንጂ መጽሐፉን ሳያነቡ እንዲኹ በስማ በለው ተነሣስተው ደውለው ለምን እንዲኽ ታደርጋለኽ ብለው የተናገሩኝ አሉ፡፡ በርካቶች ግን እኔ የጻፍኹት ኹሉም የሚያውቀው በመኾኑ መጽሐፍኽ ለለውጥ እንደመነሻ ያገለግላል በማለት በተለያዩ መንገዶች ምስጋናቸውን ገልጸውልኛል፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- አስተዳደሩን መውቀስ ሃይማኖቱን ከመተቸት የተለየ መኾኑን ለሰዎች በምን መንገድ ሊያስረዱ ይችላሉ?

ሃይማኖት ማለት ከኹሉ አስቀድሞ በኾነ ወቅት ወይም በአንድ አስተዳደር ብቻ የሚገለጽ አለመኾኑ መታወቅ አለበት፡፡ ሃይማኖት ከአስተዳደሩ የተለየ በጣም ጥልቅ ነገር ነው፡፡ ሃይማኖት ማለት ከአንድ ግለሰብ ኾነ ከጥቂት ሰዎች አመራር የተለየና የራሱ የኾነ ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት፣ ባህልና ሥርዓት ያለው መኾኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በሥነ ምግባር ደረጃ እኔን ጨምሮ ኹሉም ሰው ችግር ሊኖርብን ይችላል፡፡ ይኹንና ይኼ የሥነ ምግባር ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በመነጋገርና ተገቢውን ርምጃ በመውሰድ ነው፡፡ በመኾኑም ስለ አስተዳደር ጉዳዮች ሲነሣ ነገሩ የሃይማኖት ሳይኾን የሥነ ምግባር መኾኑ መታወቅ አለበት፡፡ ከዚኽ ውጭ ግን አኹን እኔ ባየኋቸው የተለያዩ ነገሮች ተካፋይ በነበሩ አባቶች ላይ ምንም ዓይነት የሃይማኖት ችግር በፍጹም አላየኹም፡፡

በርግጥ በተወሰነ ደረጃ አንዳንዶቹ ሃይማኖት አላቸው ወይም ሌሎቹን ደግሞ በርግጥ ክህነት የተቀበሉ ናቸው ወይ? በሚል ጥያቄ ያነሣኹበት ኹኔታ አለ፡፡ የኾነው ኾኖ ግን አብዛኞቹ በሃይማኖታቸው ችግር የሌለባቸው ካህናት ናቸው፤ እውነተኛ አገልጋዮችም አሉ፡፡ ይኹን እንጂ በአስተዳደሩ ላይ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች የሥነ ምግባር ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ ይህን ችግር መፍታት አለብን፡፡ ይህን የሥነ ምግባር ችግር ደግሞ አንዳንዶቹ ወደውት ሳይኾን ተገደው የገቡበት ሊኾን ይችላል፡፡ የነበረው ሥርዐት እነርሱ በፈለጉት መንገድ አላስኬድ ብሏቸው ወደዚኽ መንገድ ተገደው የገቡበት ሰዎችም አሉ፡፡

ስለዚኽ ለእኔ አስተዳደሩን ከሃይማኖቱ ጋራ ማቀላቀል ተገቢ አይኾንም፡፡ በተለይ ደግሞ አንድ አባት አስተዳደር ላይ ስለተቀመጡ ብቻ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴያቸውንና የሚያስተላልፏቸውን ውሳኔዎች በሙሉ የሃይማኖቱ አካል ተደርጎ መታሰብ አይኖርበትም፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ‹‹ለቤተ ክርስቲያን ዘመናዊ ሥርዐት አያሻትም፡፡ የነበረው ጥንታዊ የአስተዳደር ሥርዓት መቀጠል አለበት፤›› በማለት የሚከራከሩ ሰዎች ለቤተ ክርስቲያን የሚበጃት ይኼ ብቻ ነው የሚል መከራከርያ ያቀርባሉ…

እንዲያውም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ዘመኑን ዋጁ›› ብሎ እንደ መመሪያም እንደ ማስጠንቀቂያም የነገረው ለቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በመኾኑም በየጊዜው የሚኾነውን ነገር በሚገባ እያጤኑ ዘመኑን መቅደም ያስፈልጋል፡፡ ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር፣ የሥርዓት ኾነ የብዙ ነገር ምንጭ ናት፡፡ ይኼ ነገር በርግጥ አኹን እየተዳከመ ነው፡፡ ከዚኽ ቀደም የዕውቀት ምንጭ የኾኑ ብዙ የሃይማኖት ተቋማት ነበሩ፡፡ አሁን የሉም፡፡ ፊደል ቀርፃ፣ ቀለም በጥብጣ፣ ብራና ፍቃ ብዙ ታሪክና ቅርስ ለትውልድ ያበረከተች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይኼ ቀድሞ በነበረበት እየኼደ አይደለም፡፡ በአስተዳደሩ ዘርፍ የነበረው ቀደምት ሥልጠና አኹን የለም፡፡ በሕጉ በኩል ይሰጡ የነበሩ ሥልጠናዎች ቀርተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የነበራት አቅም እየጠፋ ነው፡፡

በመኾኑም እስከ አኹን የነበረውን የላቀ ውጤታማ ለማድረግ ያለንን አስተዳደራዊ ሥርዐት ዘመናዊ ማድረግ፣ ከዘመኑ ጋራ እያሻሻልን እየበለጸግን መሔድ እንጂ አስተዳደራዊ ሥርዓቱ መለወጥ የለበትም የሚለው አያስኬድም፡፡ እንዲያውም ይኼን የማናደርግ ከኾነ እኛ ልንኖር አንችልም፡፡ ዘመኑን ካልዋጀን ሌላው ቀርቶ የዘመኑ ትውልድ አብሮን ሊሔድ አይችልም፡፡ ትውልዱን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋራ ለማስቀጠል ከፈለግን አስተዳደራዊ ሥርዓታችንን የግድ ዘመናዊ ማድረግ አለብን፡፡ ሃይማኖት አንዴ ተሰጥቶ ያለቀ ስለኾነ የምንጨምርበት ኾነ የምንቀንስበት ነገር አይኖርም፡፡ አስተዳደራችን ግን በየጊዜው ከሚሻሻለው ዕውቀት ጋራ ተዘምዶ መሻሻል አለበት፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ‹‹ቤተ ክርስቲያን የካሽ ሬጅስተር ማሽን ያለቫት ትጠቀም›› የሚለው ሐሳብ እያወዛገበ ነው…

የእኔ መጽሐፍ ለንባብ ከበቃ በኋላ አባቶች በምን መልኩ ማሻሻያ ይደረግ ብለው ጠይቁኝ፡፡ እኔም በጉዳዩ ላይ የራሴን ጥናት በማድረግ ፕሮፖዛሉን አቅርቤያለኹ፡፡ ከተጠቃሚውና ከሰርቨሩ አንጻር ያለውን ዝርዝር የመረጃ ልውውጥ ኢትዮ ቴሌኮም በአካል ተገኝቼ በማጥናት በቤተ ክርስቲያናችን ካሽ ሬጅስተር ቢገባ በምን መልኩ ማስተዳደር ይቻላል የሚለውን ገምግሜያለኹ፡፡ ከዚያ በኋላ ሐሳቡ ጎልቶ የብዙዎች መነጋገርያ ኾነ፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ይኽን ፕሮፖዛል ወይም ምክረ ሐሳብ ለምን ማቅረብ መረጡ?

አንደኛው ትልቁ ነጥብ፣ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ያለውን አቅም የላይኛው አስተዳደር አካል በሚገባ ለማወቅ ይችላል፡፡ አኹን በጣም ከፍተኛ ብክነት በመኖሩ የላይኛው ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከታች ያለውን ትክክለኛ አቅም አላወቀውም፡፡ በመኾኑም በየአር ትራንስፖርት እንበለው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ካሽ ሬጅስተር በመጠቀም የገቢውን ትክክለኛ አኃዝ የላይኛው አስተዳደር ማወቅ የሚችልበት ዕድል ያመቻቻል፡፡

ኹለተኛው ትልቁ ጉዳይ ደግሞ ካሽ ሬጅስተር ለመጠቀም አኹን እየጠፋ ያለውን ከፍተኛ ገንዘብ በመዝገብ በመያዝ ዘመናዊ አሠራርን ማስፈን ይቻላል፡፡ አኹን እየጠፋ ያለውኮ ብሩ ብቻ ሳይኾን ሰነዱም ጭምር ነው፡፡ የካሽ ሬጅስተርን መረጃ ግን ማጥፋት ስለማይቻል የቁጥጥር ሥርዓትን ማጉላትና ተጠያቂነትን ማስፈን ይቻላል፡፡ በዚኽም ያለውን የፋይናንስ ሥርዓት ችግሮች በማስወገድ ቤተ ክርስቲያን ባላት አቅም የተለያዩ ልማቶችንና ሌሎች ሥራዎችን ማከናወን ይቻላታል ከሚል ሐሳብ በመነሣት ነው ፕሮፖዛሉን ያዘጋጀኹት፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- ካሽ ሬጅስተር መጠቀሙ ሃይማኖታዊ ትእዛዝን ያዛንፋል የሚሉ አሉ?

እዚኽ ላይ ግልጽ መኾን ያለበት ነገር ካሽ ሬጅስተሩ የአንድን ሰው ስጦታ ሳይኾን የቤተ ክርስቲያኒቱን ገቢ የሚያሳውቅ ብቻ መኾኑ ነው፡፡ ምእመኑ ልክ እንደ ቀድሞ ኹሉ አቅሙ የፈቀደውን ነው ማንም ሳያይበት ሙዳየ ምጽዋት ውስጥ የሚጨምረው፤ ነገር ግን ከሙዳየ ምጽዋት ውስጥ ገንዘቡ ወጥቶ ይቆጠራል፡፡ ይኼን የተቆጠረ ገንዘብ ነው ካሽ ሬጅስተሩ የሚመዘግበው፡፡ ከዚኽ ውጭ ግን ከተለያየ ቋሚ ይኹን የአገልግሎት ገቢ ሲገኝ ለወትሮም በደረሰኝ የሚሰበሰቡ በመኾናቸው ወዲያውኑ በካሽ ሬጅስተሩ እንደሚዘገብ ይደረጋሉ፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- በቤተ ክርስቲያን ያለውን የአስተዳደር ችግር ፈጽሞ ለማመን የሚከብዳቸው አሉ…

በነገርኽ ላይ እኔም ሰው ሲነግረኝ በፍጹም አላምንም ነበር፡፡ የሚሰርቅ ቀርቶ የሚዋሽ የአስተዳደር ሠራተኛ ይኖራል የሚል እምነት ፈጽሞ አልነበረኝም፡፡ ይኼ ግምቴ ግን ድሮ ሳይኾን አኹንም የዩኒቨርስቲ አስተማሪ እንኳ ኾኜ ነው፡፡ እኔ ራሴ የአስተዳደር ዝርክርክነቱ መኖሩን ያወቅኹት በሰበካ ጉባኤ መሳተፍ ከቻልኹ በኋላ ነው፡፡

ይኼ የአስተዳደር ችግር ባይኖር ኖሮ የአንድ ደብር ጸሐፊ የኾነ ሰው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከኹለት ሺሕ ብር በማይበልጥ ደመወዝ ኹለት ሦስት መኪና፣ ኹለት የመኖሪያ ቤቶች በፍጹም ሊኖረው አይችልም፡፡ የአንድ ወር ደመወዛቸው ለመኪና ነዳጅ ወጭ የማይሸፍንላቸው አገልጋዮች መኪና እየለዋወጡ ሲይዙ በድሎት ሲኖሩ፣ በርካታ የልጆች ኾነ የራሳቸው ወጭዎች ያለችግር ሲሸፍኑ ይኼ ነገር ከየት መጣ ያሰኛል፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ከተወለዱበት ዕለት አንሥቶ አኹን የሚያገኙበት ደመወዝ ተደምሮ ቢሰጣቸው ሊኖራቸው የማይችለውን ሰፊ ሀብት ለማካበት ኹሉ የቻሉ ናቸው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ቅርብ ለኾኑ ሰዎች ኹሉ ይኼ ግልጽ ነው፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- በአኃዛዊ ስሌት የገንዘብ ዘረፋው ምን ያኽል ይደርሳል?

እኔ በየዓመቱ ቤተ ክርስቲያን በመቶ ሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ትመዘበራለች ብዬ በመጽሐፌ ላይ ገልጩ ነበር፡፡ ይኹን እንጂ አኹን ከቀድሞ በተሻለ ጉዳዩን ስመለከተው ቤተ ክርስቲያን በምዝበራ የምታጣው ሀብት ከመቶ ሚልዮኖች የሚልቅ መኾኑን ለመረዳት ችያለኹ፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- የቤተ ክርስቲያኗ የፋይናንስ ሥርዓት ኋላቀር መኾኑ ይነገራል፡፡ እውነት ነው?

ስለ ፋይናንስ ሥርዓቱ ሲነሣ ብዙ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትጠቀምበት ዘመናዊ አሠራር (double entry) ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አኹን እየተጠቀመችበት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ዓለም በ፲፯ው መ/ክ/ዘ የተወውንና የነጠላ ሒሳብ አሠራር (single entry) የሚባለውንና በሞዴል የሚሠራ የሒሳብ አሠራር ነው፡፡ በዓለም ላይ እንዲኽ ዓይነት የሒሳብ አሠራር የሚከተል ምንም ተቋም የለም፡፡ በመኾኑም ይኼን ተረድቶ የፋይናንስ ሥርዓቱን ማዘመን ይገባል፡፡

ይኼ የሒሳብ አሠራር በፍጹም ምቹ አይደለም፡፡ የሒሳብ አሠራሩ በራሱ ነጠላ ነው፡፡ ወጪን ወጪ ይላል እንጂ ምክንያቱን አይናገርም፡፡ ስለዚኽ ወጪን ከነምክንያቱ ገቢን ከነምንጩ የሚጠቅሰው የኹለትዮሽ(ደብል) አሠራር ሥርዓት የላትም፡፡ ይኼ አሠራር ደግሞ በአፋጣኝ መለወጥ አለበት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ሲል ከጠቀስኹት ወጭ ዘርዝረን የማንጨርሳቸው በርካታ ሌሎችም ችግሮች ስላሉ ነው፡፡

አዲስ ጉዳይ፡- እርስዎ ያቀረቡት ሐሳብ ይኹን የተጀመረው የለውጥ ዝግጅት እንቅስቃሴ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ እንደዚኽም ኾኖ ያሉት የአስተዳደር ችግሮች ይፈታሉ ብለው ያስባሉ?

ትውልዱና ዘመኑ የሚፈልጉት በመኾኑ ያቀረብኹት ሐሳብ ይተገበራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዛሬ ላይ ባይኾን ነገ ይኼ ነገር ይተገበራል፡፡ በዚኽ ላይ የተጀመሩትን የለውጥ እንቅስቃሴዎች የሚቃወሙት በአስተዳደር ላይ ያሉ ጥቂት ሰዎች ናቸው፤ አስተዳደር ላይ ኾነውም ለውጡን የሚደግፉ አሉ፡፡ ምናልባት ጊዜ ይፈጅ ይኾናል እንጂ ችግሩ መፈታቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚያ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና ሌሎችም አባቶች ግልጽነቱ እንዲመጣ ጠንካራ አቋም ይዘው እየሠሩ በመኾኑ ለውጡ አይቀሬ ነው፡፡ ይኼም ኾኖ የአስተዳደር ችግር እንዲፈታ ኹሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፡፡

Advertisements

5 thoughts on “ጊዜ ይፈጅ ይኾናል እንጂ ለውጡ አይቀሬ ነው

 1. Anonymous March 23, 2014 at 6:28 am Reply

  ENDIH LEBETEKERSTIYAN YEMIYASEBU WENDMOCHEN EGZIABHERE YEBEZALEN….BETEKERESTIYANACHENEN YTENEKELENE

 2. Anonymous March 24, 2014 at 5:24 pm Reply

  Mehabaw, yor are starting fighting with fire, unlike the corrupts who are playing with fire. Your fight is for good. You strongly know and challenge with your practical knowledge. What message you are conveying to us, and to the corrupts is that <> You are saying we all need to further collaborate for our church’s administration reform through devoted and committed heart.

  Yes, Yes, no matter how late it may be, the administrative reform of the Church is inevitable. Unless masked by false and wrong information, or wrong mission, the government must, MUST support this unit-corruption campaign. I am saying, the Government not some government officials, like Dr. Shiferaw T/mariam, who are fighting the church under the mask of .

  Tekleegzi from A.A

 3. Anonymous March 25, 2014 at 6:01 am Reply

  በእውነት ለቤተክርስቲያን አስበህ ከሆነ መሆን የነበረበት በዚህ ምልኩ አይደለም ችግሮች አሉ እናውቃለን ግን እንዳንተ አይነት ማህበራትም ውስጥ ተመሽገው አባቶች ዻዻሳት፣አባቶች ካህናት፣ወንድሞች ዲያቆናትና ምዕመና ወምዕመናት ጭምር ኢህጋዊ የሆነ ሃብት ማካበት አስለመዳችሁት እና ቤተክርስቲያን መዝረፍ ጀመረ ። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ግን በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሔቶች እንዲሁም በኢ-ሚድያወች በተገላብጠሽ ይወራል ስለ እውነት እንነጋገር ከተባለ ተጠያቂዎቹ ሁሉም ነው። መፍትሔው ደግሞ የቤተክርስቲያን ገመና በማውጣት ሳይሆን ውስጥ ሆኖ ስለ እውነት በመስራትና በመፀለይ ነው። እግዚአብሔር አይነ ልቡናችን ያብራልን አሜን!

 4. Anonymous March 28, 2014 at 9:11 am Reply

  ስለ ፋይናንስ ሥርዓቱ ሲነሣ ብዙ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትጠቀምበት ዘመናዊ አሠራር (double entry) ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን አኹን እየተጠቀመችበት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት ዓለም በ፲፯ኛው መ/ክ/ዘ የተወውንና የነጠላ ሒሳብ አሠራር (single entry) የሚባለውንና በሞዴል የሚሠራ የሒሳብ አሠራር ነው፡፡ በዓለም ላይ እንዲኽ ዓይነት የሒሳብ አሠራር የሚከተል ምንም ተቋም የለም፡፡ በመኾኑም ይኼን ተረድቶ የፋይናንስ ሥርዓቱን ማዘመን ይገባል፡፡

 5. Amaregashu July 2, 2015 at 5:18 am Reply

  This is good try

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: