የአእላፋት ድምፅ ኅብረቱ: የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለውጥ አቋሙን ለቅዱስ ሲኖዶስ አስረዳ፤ “መክረን እናስታውቃችኋለን” /ቅዱስ ፓትርያርኩ/

YeAelafat Dimitse after Synod briefing

  • ኹለንተናዊ ለውጥ ያመጣል የተባለ መሪ ዕቅድ እንዲተገበር ተወስኗል፤
  • ከፍተኛ ባለሞያዎችን በማስተባበር በትግበራ ሒደቱ ለመሳተፍ ዐቅዷል፤
  • የለውጡ ተስፋና ምልክት እስከ ግንቦት መታየት እንዲጀምር ጠይቋል፤
  • የምእመናን ተሳትፎ የሚያድግበት ሥርዓት እንዲዘረጋ አመልክቷል፤

***

(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ ጥቅምት ፲፯ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.)

YeAelafat Dimtse

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመዋቅርና የአሠራር ችግሮች ኹነኛ መፍትሔ በመስጠት ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውና በአምባሳደር ዶ/ር ካሳ ከበደ የሚመራው የአእላፋት ድምፅ የካህናትና ምእመናን ኅብረት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ፊት ቀርቦ የአስተዳደር ለውጥ አቋሙን አስረዳ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱም በጥያቄዎቹ ላይ መክሮ ምላሽ እንደሚሰጥ ለኅብረቱ ተወካዮች አስታውቋል፡፡

የብዙ ሺሕ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ የአገር ሽምግሌዎችና ታዋቂ ምእመናን ተወካዮች የኾኑና በአምባሳደር ካሳ ከበደ የሚመሩ 9 የኅብረቱ ልኡካን፣ ትላንት ዓርብ፣ ጥቅምት 16 ቀን ረፋድ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመሪ ዕቅድ በመመራትና የምእመናንን ከፍተኛ ተሳትፎ በማረጋገጥ ማምጣት ስላለባት አስተዳደራዊ ለውጥ ያላቸውን አቋም በመካሔድ ላይ በሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ፊት ቀርበው ማስረዳታቸውን፣ ምክትል ሰብሳቢው አርክቴክት ዮሐንስ መኰንን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡

“ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ለውጥ የካህናትንና የምእመናንን አቤቱታ ስለማቅረብ” በሚል ርእስ በንባብ በተሰማው ጽሑፍ፣ ለቤተ ክርስቲያን ችግሮች በጥናት የተደገፈ አስቸኳይ እርምት አለመስጠት፣ ተግባራዊ እንዲኾኑ ውሳኔ የተላለፈባቸው ጥናቶች አስፈጻሚ ማጣትና በስፋት አለመታወቅ፣ ሐዋርያዊ ተልእኮዋንና አገራዊ ሚናዋን በአግባቡ እንዳትወጣ፣ ሁከትና ብጥብጥን እያስፋፋ ለጠቅላላ ህልውናዋ ቀጣይነት አደጋ እያስከተለ እንደኾነ ተጠቅሷል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአሁኑ ስብሰባው፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ የኾነው የመሪ ዕቅድ ጥናት፣ የትግበራ ጽ/ቤት ተቋቁሞለት ወደ ሥራ እንዲገባ መወሰኑና የ2.5 ሚሊዮን ብር መነሻ መመደቡን ኅብረቱ አድንቆ፣ በትግበራው ሒደት ቅዱስ ሲኖዶሱ መመሪያ ሊሰጥባቸው ያስፈልጋል ያላቸውን አምስት ዋና ዋና ጥያቄዎቹን ማቅረቡን አርክቴክት ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡

የመሪ ዕቅድ ትግበራ ጽ/ቤቱ መቋቋሙን የሚከታተልና የሚያስፈጽም አካል፣ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ከባለሞያ ምእመናን ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚሁ ስብሰባው እንዲሠይም፤ ጽ/ቤቱ ከሚቀጠሩለት መደበኛ ባለሞያዎች ባሻገር አስፈላጊውን የሰው ኃይል ማሟላት እንዲችልና ተግባሩን በአግባቡ እንዲወጣ ሙሉ ነፃነትና ሥልጣን እንዲሰጠው፤ አባላቱም እንደ ሞያቸው በባለቤትነት መሳተፍ እንዲችሉ ኅብረቱ ጠይቋል፡፡

መሪ ዕቅዱ ቢያንስ፣ በግንቦት ወር እስከሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ድረስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ርእስና ማእከል በኾነው በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና የአህጉረ ስብከት ማዕከልና መንበረ ፓትርያርክ በኾነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደረጃ ተተግብሮ የለውጡ ተስፋና ምልክት መታየት እንዲጀምር ኅብረቱ አመልክቷል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በየዓመቱ በሚካሔደው አጠቃላይ ጉባኤ ላይ የምእመናን ውክልና በሕጉ መሠረት እንዲጠበቅና ተሳትፏቸው በከፍተኛ ደረጃ የሚረጋገጥበት ሥርዐትና አሠራር በሚዘረጋበት ኹኔታ ላይም ቅዱስ ሲኖዶሱ ትኩረት ሰጥቶ እንዲመክር ኅብረቱ ጠይቋል፡፡

የኅብረቱን ጥያቄዎች፣ ምልዓተ ጉባኤው በጥሞና እንደሰማ የገለጹት ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ መክሮበት ውሳኔውን እንደሚያስታውቃቸው መናገራቸውን አርክቴክት ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

ከ2006 እስከ 2009 ዓ.ም፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ለውጥ የሚገዳቸው ከፍተኛ ኤክስፐርቶች፣ በሦስት የተለያዩ ጥራዞች አጥንተው ያቀረቡት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ሥራዋን የምትመራበት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ እና ኹለንተናዊ ለውጥ ጥናቶች፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነት አግኝቶ ተግባራዊ እንዲኾኑ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ እንዳይተገበሩ ለውጡን በማይፈልጉ አካላት ተሰናክሎ መቆየቱን የኅብረቱ ምክትል ሰብሳቢ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡

YeAelafat Dimtse3

ኅብረቱ እንቅስቃሴውን ከጀመረበት ካለፈው መስከረም ወር አጋማሽ አንሥቶ፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ለውጥን በመሪ ዕቅድ ትግበራና በከፍተኛ የምእመናን ተሳትፎ የማረጋገጥ አስፈላጊነትን በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እያከናወነ ይገኛል፡፡

YeAelafat Dimtse1

ከትላንቱ የምልዓተ ጉባኤው ማብራሪያ አስቀድሞ፣ በዮድ አቢሲኒያ ሆቴል 300 የተለያዩ ባለድርሻዎች የተሳተፉበት የግማሽ ቀን ውይይት አካሒዷል፤ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቅስቀሳውንና የጥያቁዎቹን ዐበይት ነጥቦች ሲያስረዳ መቆየቱ ታውቋል፡፡

 

Leave a comment