የአጠቃላይ ስብሰባው የውይይት መርሐ ግብር መራዘም ጉባኤተኛውን አሳዘነ፤ ከወዲሁ የመሰላቸት መንፈስ እየታየ ነው

IMG-20181015-WA0001

  • መርሐ ግብሩ ወደ ጉባኤው መጠናቀቂያ ዕለት መራዘሙ ሲገለጽ አዳራሹን ለቀው የወጡ አሉ፤
  • ቀጣይ ህልውናችንን በሚወስኑ ጉዳዮች ውይይት እንደሚኖር በሊቃነ መናብርቱ ተጠቁሞ ነበር፤
  • አጠቃላይ ስብሰባ እንደመኾኑ፣ ከሪፖርት ባሻገር በዐቢይ አጀንዳ የምር መነጋገር ይጠበቅበታል
  • ገና ለገና፣“እነእገሌ ያደራጁት ቡድን አለ” በሚል ውይይትን መሸሽ ጉባኤተኛውን መናቅ ነው፤
  • “ያለውይይት እርባና የለውም፤በዝግ አዳራሽ ውስጥ ከፈሩት በዐደባባይ ይጋቱታል፤”/ልኡካኑ/

***

የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 37ኛ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ ለቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ ለውጥና ለተጋረጠባት ወቅታዊ አደጋ ትኩረት ሰጥቶና በጥብቅ ተወያይቶ የጋራ አቋም እንደሚይዝና ለቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ ቢጠበቅም፣ የውይይት መርሐ ግብሩ ወደ ጉባኤው መጠናቀቂያ ዕለት መራዘሙ ብዙዎቹን ተሳታፊ ልኡካን በእጅጉ አሳዛነ፡፡ዓመታዊ ስብሰባው፣ ትላንት ሰኞ፣ ጥቅምት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ሲከፈት፣ የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ርእሰ መንበር በኾኑት በቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ምክትል ሰብሳቢ በኾኑት በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ እና በፕሮግራም አስተዋዋቂው፣ ውይይት እንደሚኖርና መወያየት የሚያስፈልግባቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች በንግግሮቻቸው በመጠቆማቸው፣ ተሳታፊ ልኡካኑ መርሐ ግብሩን በጉጉት እየተጠባበቁ ነበር፡፡

ኾኖም ጉባኤው ከምሳ ዕረፍት ሲመለስ፣ የውይይት መርሐ ግብሩ ስብሰባው ወደሚጠናቀቅበት ዕለት እንደተራዘመ በምክትል ሰብሳቢው ሲገለጽ፣ ጥቂቶች ሲያጨበጭቡ የሚበዙት ተሳታፊ ልኡካን የተቃውሞ መልክ ሲያሳዩና ሲያሰሙ ተስተውለዋል፡፡ በተለይም የምእመናን ተወካዮች፣ አስተያየት ለመስጠት እጃቸውን ቢያወጡም ዕድል ባለማግኘታቸውና የተለመደው የሪፖርት ማቅረብ መርሐ ግብር በመቀጠሉ አዳራሹን እየለቀቁ ሲወጡ ታይተዋል፡፡

ጉባኤተኛው ከምሳ ዕረፍት ሲመለስ፣ በርእሰ መንበሩ የጉባኤ መክፈቻ ቃለ በረከትና በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አጠቃላይ ሪፖርት ላይ እንደሚወያይ የተጠቆመና ይህም በተሠራጨው መርሐ ግብር ላይ ቢጠቀስም አልተከናወነም፡፡ ምክትል ሰብሳቢው፣ የመርሐ ግብሩን መራዘም ሲገልጹ ሐሳባቸውን ለመናገር ለፈለጉ ጉባኤተኞች ምንም ዕድል ባለመስጠታቸው የአፈና አካሔድ ኾኖ ተወስዷል፡፡ አንድ የጉባኤው ተሳታፊ፣ እጃቸውን ካወጡት ልኡካን ከዐሥር ያላነሱት ወዲያው ከአዳራሹ ሲወጡ መመልከቱን ተናግሯል፡፡ ለአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ትኩረት በመንፈግ ፌስቡክንና ሌሎች ጉዳዮችን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ የሚመለከቱ ልኡካንም ጥቂት እንዳልኾኑ ጠቅሷል፡፡

የአጠቃላይ ጉባኤው የውይይት ክፍለ ጊዜ፣ አስቀድሞ በተቀመጠው ፕሮግራም መሠረት ተጠብቆለት መርሐ ግብሩ ሊከናወን እንደሚገባ ያሳሰቡት ተሳታፊዎቹ፣ ገና ለገና፣“እነእገሌ ያደራጁት ቡድን አለ፤” በሚል የውይይት መድረክን መሸሽ ጉባኤተኛውን ከመናቅ ተለይቶ እንደማይታይ ተናግረዋል፡፡ መርሐ ግብሩ ወደ መጠናቀቂያው ዕለት የተገፋውም፣ከተሳታፊዎች ጉጉት አንጻር አዳራሹ ባዶ እንዳይቀር በተስፋ ለመያዝ እንጅ ውይይቱ ለይስሙላ አልያም ጨርሶ እንዳይካሔድ ሊደረግ እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ርእሰ መንበሩ፣ በጉባኤው መክፈቻ ቃለ በረከታቸው እንደገለጹት፣ ዓለም አቀፋዊ የኾነው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሚመሠረተው፣ የካህናትና የምእመናን አንድነት/ኅብረት/ ነው፡፡ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ በቃለ ዐዋዲው የሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያት አደረጃጀት ከፍተኛው አካል ሲኾን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ስብሰባ ተደርጎ የሚታይ ነው፤ በአባልነት የሚሳተፉበትም፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና የአህጉረ ስብከት ስብከት ሥራ አስኪያጆች ብቻ ሳይኾኑ፣ ከየመንበረ ጵጵስናው የተወከሉ የካህናት፣ የምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች እንደመኾናቸው ሐሳባቸው፣ ጥያቄያቸውና ተቃውሟቸው በሰብሳቢዎቹና በአዘጋጆቹ በአግባቡ ሊደመጥና ሊያዝ ይገባል፡፡

በሲኖዶሳዊ መዋሐድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ አንድነት በተመለሰበት ማግሥት የሚካሔደው ይኸው ዓመታዊ ስብሰባ፣ ከ62 አህጉረ ስብከት የተውጣጡ ከአንድ ሺሕ ያላነሱ ልኡካን የሚሳተፉበት እንደኾነ ተገልጿል፡፡ ይህን ያህል ስብስብ ተይዞ በቂ የውይይት መድረክ እንዳይኖር መንፈግ፣`የውይይት ፎቢያ’ ካልኾነ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡ ምክትል ሰብሳቢው እንዳሉት፦ በሰፊ መሪ ዕቅድ፣ በፖሊሲዎችና አሠራር ለውጦች ዝግጅት ጉዳይ አጥብቆ መወያየቱ ይቅርና የተለመዱ የአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች እንኳን፥ ምእመናን በገፍ እንደተፈናቀሉ፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት እንደተቃጠሉ፣ አስተዳደራዊና ሌሎችም በደሎች እየተፈጸሙ መኾናቸውን እየጠቆሙ ባለበት፣አደጋውን በመከላከሉና በመቋቋሙ ስልት ላይ አለመምከር፣ የአዳራሹ አጀንዳና ትችት ወደ ዐደባባይ እንዲወጣ መግፋት ይኾናል፡፡

በፕሮግራሙ እንደተጠቀሰው፣ ትላንት ከቀትር በኋላ ከነበረውና ከባከነው የ55 ደቂቃ የውይይት ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ፣ ነገ ረቡዕ፣ ጥቅምት 7 ቀን ከምሳ ዕረፍት መልስ(ከሻይ ዕረፍት በፊትና በኋላ) በድምሩ የአንድ ሰዓት ከ35 ደቂቃ የውይይት መርሐ ግብር ተይዟልና ተከብሮ ሊከናወን ይገባል፤ “አጠቃላይ ጉባኤው፣ ቤተ ክርስቲያን ስለሚያስፈልጋት አስተዳደራዊ ለውጥ የመነጋገርያ ርእስ ለይቶ ከምር መወያየት ካልቻለ እርባና የለውም፤ ሰብሳቢዎቹም በዝግ አዳራሽ የፈሩትን አጀንዳና ትችት በዐደባባይ ሊጋፈጡት ይገደዳሉ፤” ይላሉ የመርሐ ግብሩ መገፋት ያሳዘናቸው ተሳታፊዎች፡፡

የሦስት ዓመት የዋና ሥራ አስኪያጅነት ዘመናቸውን ዘንድሮ የሚያጠናቅቁት የጉባኤው ምክትል ሰብሳቢ፣ በውይይቱ አስፈላጊነት ላይ ከጉባኤው አዘጋጆች ጋራ አስቀድመው በመከሩበት አኳኋን መድረኩን ለውይይት ክፍት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ትላንት የውይይቱን መራዘም በገለጹበት ወቅት፣ ከዚሁ ጋራ እንደተያያዘ በተገመተ መልኩ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና ከፕሮግራም አስተዋዋቂው ጋራ ሲመላለሱ የታዩበት ኹኔታ መደገም የለበትም፤ በሥራ ዘመናቸው መጨረሻ ሞገስ የተመላበት መውጫና የለውጥ አንድ ማሳያ ይኾናቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ሪፖርታቸው እንዳሳሰቡት፣“በአጽንዖትና አጥብቆ መወያየት ያስፈልጋል፤”ማለታቸው ብቻ በቂ አይኾንም፡፡

በሌላ በኩል፣“ተናጋሪዎች ናቸው፤” የተባሉ አንዳንድ ተሳታፊዎች እየተለዩ፣ “አትናገሩ፤ ምንም ጥቅም የለውም፤ ጥርስ ውስጥ ከመግባት ውጭ ምንም አታተርፉም፤” በሚሉ ወትዋቾች ማዳከሙ ግን ተገቢነት አይኖረውም፡፡

2 thoughts on “የአጠቃላይ ስብሰባው የውይይት መርሐ ግብር መራዘም ጉባኤተኛውን አሳዘነ፤ ከወዲሁ የመሰላቸት መንፈስ እየታየ ነው

  1. Anonymous October 17, 2018 at 1:54 am Reply

    what is the camera woman is doing there with pants infront of all monks

  2. Senait Temesgen October 18, 2018 at 3:43 am Reply

    How is the Camera woman on the the photo wore? I expect a lady who is working in front of our Church Fathers to wear Netela and a descent dress. The holly meeting worths respect. I think the problem is the event organizers.

Leave a comment