የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት አስተዳደራዊ ችግሮቹን እየፈታ ነው፤ ለሶማሌ ተጎጅዎች 100ሺሕ ብር ረዳ፤ ተጨማሪ ለማሰባሰብ ኮሚቴ አቋቋመ

his grace abune ephrem and his grace abune Kelemntos

አባቴ፤ ልጄ የሚባባሉት ሁለቱ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት አባቶች፤ አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም(ግራ)፤ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ሊቀ ጳጳስ(ቀኝ)

  • የቤተሰባዊ ትስስርና የዘመድ አዝማድ መሳሳብ ችግርን የማስተካከል ርምጃ ወሰደ፤
  • ሞያዊ ግምገማና ሥልጠና በማካሔድ፣ ሁሉንም ወረዳዎች ያማከለ ምደባ አደረገ፤
  • አንጋፋና በዕድሜ ለጡረታ የደረሱ 32 የጽ/ቤት እና የወረዳ ሠራተኞችን አሰናበተ፤
  • በችሎታ፣ በሥራ ልምድና በሥነ ምግባር ላይ በተመሠረተ ምደባና ዝውውር ተካ፤
  • ሀ/ስብከቱን በዕቅድ የመምራቱ ሥራ፣የጽ/ቤቱን ተግባርና በጀት በማዘጋጀት ጀመረ፤
  • ስብከተ ወንጌልንና ዕቅበተ እምነትን በሥልጠናዎች በማጠናከር ቅሬቶችን ያጸዳል፤

†††

  • የአረጋዊው ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የሕይወት ታሪክ ዝግጅት እንዲቀጥል አዝዟል፤
  • “ለዝግጅቱ ሕጋዊ ውክልና ሰጥተውኛል፤”ባዩ ግለሰብ ከጽ/ቤቱጋ እየተወዛገበ ነው፤
  • ከ250 እስከ 450ሺ ብር እንዲከፈለው ቢጠይቅም ለማስገምገም ፈቃደኛ አይደለም፤
  • ውሉና ክፍያው ክብራቸውን ጠብቆና ሕግን ተከትሎ እንዲፈጸም ጽ/ቤቱ አሳስቧል፤
  • የአረጋዊውን አባትና የብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን ወዳጅነት ለማናጋት እየሠራ ነው፤
  • “ዝቅ የተደረጉ መዝባሪዎችንና የመናፍቃን ተላላኪዎችን ቢያሰለፍም አይሳካለትም፤”

†††

በአድሏዊ አመራርና አሠራር ሳቢያ በሚቀርቡ አቤቱታዎች ሲታመስ የቆየው የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ችግሮቹን ለመቅረፍ በወሰዳቸው ተከታታይ የመልካም አስተዳደር ርምጃዎች አመርቂ ለውጦች ማስመዝገብ መጀመሩን አስታወቀ፤ በሶማሌ ክልል አሠቃቂ ጥቃት ለተጎዱ ወገኖችና አብያተ ክርስቲያን መልሶ ማቋቋሚያ ከጽ/ቤቱ ወጪ ያደረገውን 100ሺሕ ብር በተከፈተው የባንክ አካውንት ማስገባቱንና ከኹሉም ወረዳዎች ተጨማሪ ርዳታ የሚያሰባስብ ኮሚቴ መሠየሙን ገለጸ፡፡

የአስተዳደራዊ ችግሮቹ ዋነኛ መንሥኤ፣ በቤተሰባዊ ትስስርና በዘመድ አዝማድ መሳሳብ በግልጽም በስውርም ለዓመታት ሲፈጸም የቆየው የሠራተኛ ምደባ፣ዕድገትና ዝውውር እንደነበር ጽ/ቤቱ ጠቅሷል፡፡ ካለፈው ጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ግን፥ ግልጽነትን፣ አሳታፊነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ አሠራሮችን ተከተሎ በወሰዳቸው የማስተካከያ ርምጃዎች አበረታች ለውጦች እየታዩ ነው፤ ከወረዳ አብያተ ክህነት፣ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያንና ከመንግሥታዊ አስተዳደሩ ጋራ መዋቅሩን የጠበቀና በመተጋገዝ ላይ የተመሠረተ የውሳኔ ሰጭነትና መላሽነት አዎንታዊ ግንኙነት እየታየ ነው፤ ብሏል፡፡

እኒህ የለውጥ ርምጃዎች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር የካህናትንና የምእመናንን አቤቱታ በማጣራት ያሳለፋቸው ውሳኔዎችና የሰጣቸው መመሪያዎች ተግባራዊ የተደረገባቸው በመኾናቸው፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሀገረ ስብከቱን ማመስገኑን ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡ ከውሳኔዎቹና መመሪያዎቹ መካከል የሚከተሉት ዐበይት እንደነበሩ ጽ/ቤቱ አስታውሷል፤

  • በዕድሜ የበለጸጉት አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፣ ዞሮ በማስተማርና በመባረክ ችግር ባይኖርባቸውም፣ በዕድሜ መግፋትና በጤና እክል ምክንያት ደብዳቤዎችን በብፁዕነታቸው ማስፈረሙ የተወሳሰበ የአመራር ሒደት ስለሚፈጥር የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ተገቢውን ክትትልና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ለሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎችም መመሪያ እንዲሰጡ፤
  • ለቤተሰባዊ ትስስሩ እልባት ለመስጠት፣ በርካታ ሥራዎችን ደራርበው በመያዝ ለአስተዳደር ጉባኤው አሳታፊነትና ለክትትል ዕንቅፋት የፈጠሩት መጋቤ ሠናያት ፈቃደ ደመሳ፣ ከሓላፊነታቸው ተዛውረው በተመደቡበት ተወስነው እንዲሠሩ፤ በቡድናዊነት የምዝበራ ኔትወርክ በመዘርጋት የሀገረ ስብከቱን ሰላም የሚንጡት መ/ር አስቻለው ፍቅሬ፣ ከቦታቸው ተዛውረውና ከደረጃ ዝቅ ተደርገው እንዲሠሩ የተወሰነው እንዲፈጸም፤ በጋብቻና በዝምድና ቁርኝት ያላቸው ግለሰቦች ለሥራው ጥራትና መተማመን ለመፍጠር ካሉበት የሥራ መደብ ወይም ክፍል እንዲለያዩ እንዲደረግ፤
  • አንጋፋ የሀገረ ስብከትና የወረዳ ሠራተኞች፣ ዕድሜያቸው ለጡረታ ደርሶ እያለ እንዲወጡ አለማድረጉ የትውልድ ቅብብሎሽን ከማደናቀፉም በላይ እየተለዋወጠ ያለውን አስቸጋሪ ኹኔታ ለመምራትና ለማስተካከል በሚያስችል አቅም ላይ ባለመኾናቸው በሕጉ መሠረት በጡረታ እንዲገለሉና የመተካካቱ ሥራ እንዲሠራ
  • በሀገረ ስብከቱ ጎልተው ከሚታዩት ችግሮች መካከል ዕውቀትን፣ ልምድንና ዕድሜን ያገናዘበ የሥራ ድልድልና ሓላፊነትን ከወቅታዊ ኹኔታ አንጻር አጥንቶ አለመስጠት ተጠቃሹ ነው፡፡ የሠራተኛ ዝውውርና የዕድገት አሰጣጥ ሥርዐቱና ሒደቱ፥ የትምህርት ዝግጅትን፣ የሥራ ችሎታንና ልምድንና መሠረት አድርጎ ያልተተገበረና ቤተሰባዊነት ያለበት በመኾኑ በሥራቸው የተመሰገኑትን ቅር አሰኝቷል፡፡ በመኾኑም፣አፈጻጸሙ ሁሉንም ወረዳዎች ያማከለ እንዲኾንና ይህም በአስተዳደር ጉባኤ እየተወሰነ በግልጽነት እንዲከናወን
  • የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ፥ ለምእመኑ የሚመጥን ትምህርተ ወንጌል በማቅረብ ጊዜውን ለመዋጀት የሚችሉ፣ የመናፍቃንን ወረራ ለመመከት የሚበቁ፣ ተኣማኒነትና ምሳሌነት ያላቸውን መምህራን እያወዳደሩ በመመደብ እንዲመራ እንዲደረግ፤
  • በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን በኅቡእ ሠልጥነው የሚያሠለጥኑና ኅትመቶቻቸውን የሚያሰራጩ፣ ለሀገረ ስብከቱ ሰላም መጥፋት ምክንያት የኾኑና የለውጥ ርምጃውን የሚያደናቅፉ በአጠቃላይ በሃይማኖታዊ አቋማቸው የሚጠረጠሩ የሀገረ ስብከትና የወረዳ ሠራተኞች አሉ፤በመኾኑም ሀገረ ስብከቱ በፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ አማካይነት ተገቢውን ማጣራት አድርጎ አፈጻጸሙን ለዋናው መሥሪያ ቤት እንዲያሳውቅ፤
  • መደበኛ ሥራቸውን እየተዉ በአድመኝነትና ጥቅመኝነት ተግባር የተሠማሩ የወረዳ ሊቃነ ካህናት፣ ከተልእኳቸው አንጻር ነቀፋን የሚያስከትል በመኾኑ በተመደቡበት ወረዳ በሕግ በተደነገገው የሠራተኞች የሥራ ሰዓት መግቢያና መውጫ መሠረት ሥራቸውን እንዲሠሩ ሀገረ ስብከቱ ጥብቅ የጽሑፍ መመሪያ በመስጠት እንዲያስከበር፤
  • በ1981 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ የተመሠረተው ሀገረ ስብከቱ፣ 29 ወረዳዎችንና 2ሺሕ አብያተ ክርስቲያንን የያዘ ሰፊ በመኾኑ፣ ከፍተኛ የሰበካ ጉባኤ ገቢ ያገኛል፤በሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጎበኙ ታላላቅ ቅዱሳት መካናትም አሉት፤ ከዚሁ ጋራ በተያያዘ ሥራው ሰፊና ለተጽዕኖ ተጋላጭ በመኾኑ በአቅም ግንባታና በግጭት አፈታት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች በሊቃውንትና በምሁራን የሚሰጥበት ሒደት እንዲመቻች፤ የሚሉ ናቸው፡፡

የእነኚህ ውሳኔዎችና መመሪያዎች አፈጻጸም፣ በአረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የእገዛ ጥያቄና በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ከመጡበት ሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. አንሥቶ እንደተጀመረና ሥራ አስኪያጁ መ/ር ሣህለ ማርያም ወዳጆ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከተዛወሩበት ጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. በኋላም እንደተጠናከረ ተገልጿል፡፡

የሀገረ ስብከቱ የመልካም አስተዳደር ተግዳሮት የኾኑትን የቤተሰብ አስተዳደር፣ ሙሰኝነትና ስም ማጥፋት ችግሮችን ለመፍታት፣ በዕቅድ መመራት እንደሚያስፈልግ ታምኖበት የጽ/ቤቱ ዓመታዊ የተግባርና የበጀት ዕቅድ፣ ሁሉም ክፍሎች በተሳተፉበትና ግልጽነትን በተላበሰ አካሔድ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በተግባር ዕቅዱ በቀዳሚነት የሰፈረው በባለሞያ የታገዘ ግምገማዊ ሥልጠና አንዱ ሲኾን፤ በተሻሻለው ቃለ ዐዋዲ አተገባበር፣ በፋይናንስና ንብረት አያያዝና አጠቃቀም፣ በመልካም አስተዳደርና ግጭት አፈታት እንዲሁም በዕቅበተ እምነት የፀረ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

ይኸው ሥልጠና በኅዳር ወር መከናወኑን ተከትሎ በሒደቱ ለተገመገሙ ሠራተኞች አዲስ ምደባና በዕድሜያቸው ለጡረታ የደረሱት ደግሞ በሕጉ መሠረት እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ ከትምህርት ዝግጅታቸው፣ ከሥራ ልምዳቸውና ከሥነ ምግባራቸው አንጻር ብቁ ኾነው የተገኙት በወረዳ ቤተ ክህነትና በሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በዕድገት ተዛውረዋል፤ የአቅም ማነስ የታየባቸው ከደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ ተደርጓል፤ ዕድገቱም ኾነ ዝውውሩ፣ የቤተሰባዊ ትስስሩ ማሳያ የነበረውን የደብረ ብርሃን ዙሪያ ባሶ ወረዳ ቤተ ክህነትን ጨምሮ ሁሉንም ወረዳዎች ባማከለ ኹኔታ መከናወኑ ተጠቅሷል፡፡

ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትና ከወረዳዎች በአጠቃላይ 32 ሓላፊዎችና ሠራተኞች በጡረታ ተሰናብተዋል፡፡ ብዙዎቹ፥ በረዥም ጊዜ አገልግሎታቸው፣ በዕውቀታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ቢኾኑም፤ የጡረታ ጊዜያቸው አልፏቸው ሳለ፣ የሚያገኙት ደመወዝ ከአገልግሎት ዘመናቸው ጋራ አይመጣጠንም፤ በሚል ከ7 እስከ 10 ዓመት ድረስ ሳይሰናበቱ የዘገዩ መኾናቸው ታውቋል፡፡

በቡድናዊ ትስስር የሀገረ ስብከቱን ሰላማዊ አሠራር በማወክ፣ በሌብነትና በአቅም ማነስ ከደረጃ ዝቅ ብለው ወደ ሀገረ ማርያም ወረዳ ጸሐፊነትና ሒሳብ ሹምነት እንዲዛወሩ የተላለፈው ትእዛዝ ቀደም ሲል ከተፈጸመባቸው መ/ር አስቻለው ፍቅሬ በተጨማሪ፣ የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ ሊቀ አእላፍ ሁሉም ይፈር እና የቤተሰባዊ ትስስሩ ማሳያ የኾኑት መጋቤ ሠናያት ፈቃደ ደመሳ ተመሳሳይ ርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

አረጋዊውን ሊቀ ጳጳስ በመዘወርና ጫና በመፍጠር ፍላጎታቸውን ሲያስፈጽሙ የኖሩትና በአቅም ማነስ(ሞያ ቢስነት) የተገመገሙት ሊቀ አእላፍ ሁሉም ይፈር፣ ወደ ሞረትና ጅሩ ወረዳ(እነዋሪ) ቤተ ክህነት ተዛውረዋል፤ መጋቤ ሠናያት ፈቃደ ደመሳም፣ ከልማት ክፍል ሓላፊነት እንዲነሡ ቀድሞ የተሰጠው ትእዛዝ ቢፈጸምም፣በየወረዳው በዘረጉት የምዝበራ ሰንሰለት እየተጠቀሙ ዕንቅፋት ከመፍጠር ባለመቆጠባቸው ደመወዛቸውን እያገኙ ከሥራ ታግደው ነበር፤ በኋላ በአረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ጥያቄ በልማት ክፍሉ ምክትል ሓላፊነት ዝቅ ተደርገው እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡

መጋቤ ሠናያት ፈቃደ፣ ደራርበው በቆዩዋቸው የተለያዩ ሓላፊነቶች፥ በአስተዳደር ጉባኤው እንዳይወሰን፣ ሠራተኛውም በልማቱ እንዳይሳተፍና ባለቤትነት እንዳይሰማው ከማድረጋቸውም በላይ፣ ሥራዎች ተጀምረው እንደማያልቁና የክትትል እጥረትም እንዳለባቸው ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ በከተማው ሦስት ቦታዎች አሏቸው የሚባሉት ሕንፃዎችና የኮንዶሚኒየም ቤት እንዲሁም ሁለት ባጃጆችና ታታ መኪና ምንጮች መነጋገሪያዎች ናቸው፡፡ ‘የግል ሕንፃዎቻቸውን’ ሲያሠሩ በየወረዳው በዘረጉት ቡድናዊ ትስስር፥ ፌሮ ብረት፣ አሸዋ፣ ሲሚንቶና ጠጠር ሲገለበጥላቸው፤ የወይራ ዘይት፣ የአጃና የሽሮ እህል፣ ጤፍና ማርም በየምድቡ ይጫንላቸው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

አሁን እርሳቸውና መሰሎቻቸው ከሓላፊነት መሥመር ገሸሽ ቢደረጉም፣ በሌሎች ተሸፍነው ቅራኔዎችን በማራገብ የሀገረ ስብከቱን ሰላማዊ አሠራር ለማወክና ቀረብን የሚሉትን ጥቅም ለማስጠበቅ በአድማና አሉባልታዎችን በመንዛት እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ በጸሎትና ቡራኬ ባሉት አረጋዊው ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም እና ሀገረ ስብከቱን በሚመሩት ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ መካከል አለመግባባት ፈጥሮ ምእመናኑን ማደናገርና መከፋፈል አንዱ ስልታቸው ነው፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሁለት ቶዮታ ላንድ ክሩዘር መኪኖች ለጥገና በገቡበት የዐቢይ ጾም ወቅት፣ አረጋዊው አባት መኪኖቹን እንዳይጠቀሙና እንደተከለከሉ አድርገው እያጋነኑ አስወርተዋል፡፡ ቤተሰብና ዘመድ ነን በሚል አንዳቸው ባጃጅ አቅራቢ ሌላቸው ቪዲዮ ቀራጭ ኾነው አረጋዊውን አባት ወደ ቤተ ክርስቲያን በማመላለስ ምስሉን በከተማው አሰራጭተዋል፡፡ በግል ተሽከርካሪያቸው ብፁዕነታቸውን ለማገልገል የጠየቁ ምእመናን ቢኖሩም ክፉ ውጥናቸውን ያሰናክላልና ተከላክለዋል፡፡

እውነታው ግን፣ መኪኖቹ በጥገና ላይ የቆዩት ለአጭር ጊዜ እንደኾነና ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስም በእግራቸው ይንቀሳቀሱ እንደነበር ነው የሀገረ ስብከቱ ምንጮች የሚያስረዱት፡፡ “በአንድ መቅደስ ሲገናኙ የኔ ልጅ፣ አባቴ እየተባባሉ ያገለግላሉ፤ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስም፣ ሁለት ጳጳስ በአንድ መኪና አይሔድም፤ ብለው ቅድሚያውን ለአረጋዊው አባት ነው የሚሰጡት፤” ይላሉ ምንጮቹ፡፡

ሀገረ ስብከቱን ለዘመናት ለመሩት አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፣ ሕክምናና ለሚያስፈልጓቸው ወጪዎች ሁሉ ጽ/ቤቱ የበጀት ርእስ አውጥቶ 50ሺሕ ብር መድቧል፤ ካነሰም እየታየ እንዲጨመር ከመወሰኑም በላይ፤ የግል ሐኪም፣ ነርስ፣ ልዩ ረዳትና አብሳይ ለመመደብ ቢያቅድም “ለደኅንነታቸው እንሰጋለን፤” ባዮቹ እነመጋቤ ሠናያት ፈቃደ ደመሳ፣ ሊቀ አእላፍ ሁሉም ይፈርና አስቻለው ፍቅረ፣ አረጋዊውን ሊቀ ጳጳስ በቤተሰብ አጥረው ሰው እንዳይጠይቃቸው ተከላካይ ኾነዋል፡፡

ኹኔታው ያሳሰባቸው ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ማረፊያ ቤታቸውን በድንገት ሲጎበኙ የተጋለጠው እውነታ ግን፣ ቤተ ዘመድ/ቤተሰብ ነን ባዮቹ፣ ከግል ንጽሕና ጀምሮ ምንም ዐይነት ክብካቤ እንደማያደርጉላቸው ነው፡፡ ወዲያው፣ ፎቅ ላይ የነበረውን ማረፊያቸውን ለዕርግናቸው ወደሚመችና አስፈላጊው ነገር ወደተሟላለት ምድር ቤት እንዲዛወር፣ ጽዳቱም እንዲጠበቅ መመሪያ ሰጥተው ተፈጻሚ ኾኗል፤ ቤተ ዘመድ ነን ባዮቹ ግን፣ “ለሕክምና ወጪ ተከልክለው፣ያለረዳት አገልጋይ ተጥለው በጠባብ ክፍል ውስጥ ኩርምት ብለው እንባቸውን ይረጫሉ፤” በማለት በለመዱት ከፋፋይነትና ስም አጥፊነት ሐሰት ለማሰራጨት አላፈሩም፡፡

ሰሞኑን ደግሞ፣ አረጋዊው አባት የጓጉለት የሕይወት ታሪካቸውን የያዘ መጽሐፍ እንዳይታተም ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱና ሥራ አስኪያጃቸው ዕንቅፋት ኾነዋል፤ የሚል አሉባልታ ማናፈስ ይዘዋል፡፡ መጽሐፉን አዘጋጅቼ ለኅትመት አድርሻለሁ፤ የሚሉት በኵረ ጠቢባን ወሰን ደበበ ማንደፍሮ ከአረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ጋራ በተወሰነ ደረጃ የሥጋ ዝምድና ያላቸው ሲኾኑ፤ እነመጋቤ ሠናያት ፈቃደ ደመሳ እና መ/ር አስቻለው ፍቅረ ደግሞ አማካሪና ሽፋን ሰጪዎች እንደኾኑ ተነግሯል፡፡ የምንጃር፣ የቀይት፣ የጫጫ እና የባሶ ወረዳዎች ሊቃነ ካህናትን ሲያሳድሙ፤ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ለመኾን ሞክረው ያልተሳካላቸውንና ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የኾኑ ሁለት የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶአውያን የውስጥ አርበኞችንና ኅትመት አሰራጮችንም በአጋርነት አሰልፈዋል፡፡

wossen debebe mandefroደራሲ ነኝ ባዩ ወሰን ደበበ፣ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ዝግጅቱን ምክረ ሐሳብ፣ በግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. ለሀገረ ስብከቱ አቅርበው ከአረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ሕጋዊ ውክልና መቀበላቸውን ቢናገሩም፣ በዞኑ ፍትሕ ጽ/ቤት ተፈጽሟል ከሚሉት ውል ውጭ፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ስምምነቱን የሚገልጽ ሰነድ አለማግኘቱ ተጠቅሷል፡፡ የሥራውና አሠራሩ ስምምነት በወረቀት ቢሰፍርም ሳይፈረምበት፣ መጽሐፉን በዐሥር ወራት ውስጥ አዘጋጅተው ማጠናቀቃቸውን ወሰን ደበበ ገልጸዋል፡፡ ያልተፈረመበትም፣ “በአዲሱ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ወደ ሀገረ ስብከቱ መምጣት ነው፤” በማለት ምደባቸውን ለመተቸት ይሞክራሉ፡፡

ይህም ኾኖ ከሊቀ ጳጳሱ ምደባ በፊት የቤተሰብ ትስስሩን ተጠቅመው፣ በመጀመሪያ፣ በሰነድ ያልሰፈረ 40ሺሕ ብር፣ በኋላም በቀድሞው ሥራ አስኪያጅ ላይ ጫና በመፍጠር ለሁለተኛ ጊዜ 30ሺሕ ብር ክፍያ እንደወሰዱ ተጠቁሟል፡፡ በዚሁ ልማድ፣ 100ሺሕ ብር እንዲከፈላቸው በጠየቁበት ወቅት ሊቀ ጳጳስ ኾነው የተመደቡት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ከክፍያው በፊት መታየት ያለባቸውን ነገሮች በመዘርዘር መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በጸሎት፣ ዞረው በማስተማርና በቡራኬ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት ያገለገሉት የአረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ማዘጋጀቱ መልካም መኾኑን የገለጹት ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ሥራው ሳይቆም እንዲቀጥል ኮሚቴ አቋቁመው መመሪያ ሰጥተዋል፤ የተጠየቀውን ክፍያ ለመፈጸም ግን፣ ደራሲው አዘጋጀሁት ያሉት ሥራ መገምገም እንዳለበት አዝዘዋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ መ/ር ሣህለ ማርያምም፣ ደራሲ ነኝ ባዩ ለዝግጅቱ የተመረጡበት የሞያና የሥራ ልምድ አግባብነትና ሕጋዊነት እንዲፈተሸ፤ የመጽሐፉ ቋንቋና ይዘትም እንዲመረመር ገልጸው ለማግባባት ጥረዋል፡፡

እንዴት ተመረጡ ለሚለው ጥያቄ፣ ጋዜጠኛ ነኝ፤ የሚል ምላሽ ቢሰጡም ማስረጃና ልምድ የላቸውም፡፡ የአረጋዊው አባት የሕይወት ታሪክም፣ከዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተለይቶ ስለማይታይ፤ ይዘቱና አስተማሪነቱ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክልና ለትውልድ የሚተላለፍ መኾን ስላለበት ሀገረ ስብከቱ እንዲገመግመው ሲጠየቁ፣ የደራሲ ነኝ ባዩ ምላሽ የሚያግባባ አልነበረም፡፡ “መጽሐፉ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የታረመ ስለኾነ ምንም ዐይነት እርማት አያስፈልገውም፤ ሀገረ ስብከቱ፣ ከደራሲው ጋራ በመነጋገር የማስተካከያ ሐሳብ የመስጠት እንጅ የመጨመርና የመቀነስ መብት የለውም፤” ነው ያሉት፡፡

wossen debebe appeal

ደራሲ ወይስ አሰባሳቢ/አስተጋባኢ የሚለውም በራሱ መታየት የሚገባው ጥያቄ ነው የሚለው ጽ/ቤቱ፣ የግለሰቡ ሚና አስተጋባኢነት እንደኾነ ገልጿል፤ የመጽሐፍ ረቂቁን ለማስረከብ ከፈቀዱም፣ ክፍያው በቀን አበልና በሚያቀርቡት የወጪ ሰነድ መሠረት እንደሚፈጸምላቸው ጠቁሟል፡፡ ሀገረ ስብከቱ መጽሐፉን ከተረከበ በኋላ በሚመለከታቸው ሊቃውንት አስገምግሞ በማሳተም በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ ለምእመናን በነጻ እንደሚያሠራጨውና ለሽያጭ እንደማያውለው አስታውቋል፡፡ በቤተሰባዊ ትስስሩ ተሸፍነው ዳጎስ ያለ ጥቅም ለማካበት ያሰሉት ወሰን ደበበ ግን፣ ለአጠቃላይ ዝግጅቱ 250ሺሕ ብር እንዲከፈላቸው፣ ታትሞ ሲሸጥም የ10ሺሕ ኮፒ ሽያጭ ገቢ ኃምሳ ፐርሰንት(250ሺሕ ብር) ጠይቀዋል፡፡ መጽሐፉ ታትሞ በነጻ የሚሠራጭ ከኾነም፣ ከተለያዩ የስፖንሰር ገቢ አገኘዋለሁ ያሉት 250ሺሕ ብር ተጨምሮላቸው በአጠቃላይ 450ሺሕ ብር እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል፡፡

ጉዳዩ፣ በአንድ በኩል፣ በሀገረ ስብከቱ የሕጋዊነትና አግባብነት ጥያቄ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በታየ ጥቅመኝነት መካከል የሚነሣ ኾኖ ሳለ፣ እነወሰን ደበበና ቤተ ዘመድ ነን ባዮች፣ በአረጋዊው አባት ስም የምእመኑን ስሜት በሐሰት ለመኮርኮር የጀመሩት የአሉባልታ ዘመቻ መዝባሪነታቸውን ከማጋለጥ በቀር የሚያምናቸውና የሚቀበላቸው እንደማይኖር ጽ/ቤቱ ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል የደብረ ብርሃን ፖሊስ የነበሩት ደራሲ ነኝ ባዩ በሥነ ምግባር ጉድለት ተገምግመው መባረራቸው እንደሚታወቅ ተጠቅሷል፤ ከዓመት በፊትም በሀገረ ማርያም ወረዳ ካለችው የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ገዳም፣“ገድሏን አግኝቻለሁ፤ አሳትማለሁ፤” ብለው ዘርፈው እንደሔዱ ተሰምቷል፤ አሁንም በሌላቸው ሞያና ልምድ፣ ብፁዕ አቡነ ኤፍሬምን ያህል አንጋፋ አባት፣ እንደተራ ግለሰብ ወስደው የሕይወት ታሪኬን ጻፍልኝ ያሰኙበትን አካሔድ እንደሚያጤነው ተችቷል፡፡

የአረጋዊውን ሊቀ ጳጳስ የሕይወት ታሪክ ማዘጋጀት የሚደገፍ ቢኾንም፣ የዕድሜ ባለጸግነታቸውንና ቤተሰባዊ ትስስሩን ተጠቅመው በጫና በማስፈረም ጥቅም ለማጋበስ ያሰቡበት አካሔድ እንደኾነ ጽ/ቤቱ በተለያዩ ማሳያዎች አረጋግጧል፡፡ ደራሲ ነኝ ባዩ፣ በመጽሐፉ ዝግጅት ስም ከሀገረ ስብከቱ ያለሰነድ ከወሰዳቸው ክፍያዎች በተጨማሪ፣ አዲስ አበባ ቃሊቲ አካባቢ ካሉ የአረጋዊው አባት ወዳጅ፣ 150ሺሕ ብር መቀበላቸውን ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የነገሯቸው ራሳቸው ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ናቸው፡፡ “ዘመዶቼ ጋራ እየሔደ በስሜ ብር ይወስዳል፤ ሲያጭበረብረኝ የኖረ ሌባ ነው፤” ያሉት አረጋዊው አባት፣ “እኔን ይጦሩኛል ብዬ የማምንብዎትን ከእርስዎ ጋራ ሊያጣሉኝ፤” በማለት የሁለቱን አባቶች የማደፍረስ ዓላማቸውን አጋልጠዋል፤ “እኔን አይወክለኝም፤” ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

በሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስም ኾነ በሥራ አስኪያጁ መ/ር ሣህለ ማርያም ወዳጆ የተወሰደው አሠራሩን የማስተካከል አቋም፣ መሰል የማጭበርበር ችግሮችን ለመቅረፍ ተገቢው ጥንቃቄና ክትትል እንዲደረግ፣ ለሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎችም መመሪያ እንዲሰጥ የተላለፈው የጠቅላይ ጽ/ቤቱ መመሪያ በተግባር የተፈጸመበት እንደኾነ ጽ/ቤቱ አስረድቷል፡፡

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፣ ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ወደ ሀገረ ስብከቱ ሲመጡ በተደረገላቸው አቀባበል ላይ፣ ምደባቸው፣ በአረጋዊው አባት ጥሪና በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነ የመንፈሳዊ አገልግሎት ርክክብ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም፣ በትምህርታቸው፣ በአስተዳደራቸው፣ በልማታቸው፣ በሐቀኝነታቸው፣ በለጋስነታቸውና በትሑትነታቸው ከቤተ ክርስቲያን ተጠቃሽ አባቶች ግንባር ቀደም አባት ናቸው፤ ብለዋል፡፡ ያሳደጓቸውና ለደረሱበት ማዕርግ ያደረሷቸው የብፁዕነታቸው ፍሬ እንደኾኑና ከእርሳቸው ጋራ ለመሥራት፣ እርሳቸውን ለመርዳትና ለማገዝ መታጨት፣ መልካም አርኣያቸውን በመከተል ለሚያበረክቱት ክርስቲያናዊ ተጋድሎ ትልቅ መንፈሳዊ ኃይልና ጉልበት እንደሚኾናቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱንና የዕቅበተ እምነት ተጋድሎውን አስመልክቶ፣ የዘመኑ መናፍቃን በምእመናን ጉያ በመሸጎጥና በመደበቅ፣ የቤተ ክርስቲያንን ንዋያት በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን እየተገዳደሯት እንደኾኑ አስገንዝበዋል፤ ቸልተኝነት፣ መዘናጋትና መፋዘዝ ሳይወረን ሃይማኖትን በንቃትና በጽናት መጠበቅ የሁሉም መንፈሳዊ ግዴታ እንደኾነ አሳስበዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፈው በጀት ዓመት፣ የአብነት መምህራንና ተማሪዎችን ትኩረት ሰጥቶ በማሠልጠን የተጀመረው እንቅስቃሴ በተጠናከረ አያያዝ እንደሚቀጥል ጽ/ቤቱ ጠቁሟል፡፡

ብፁዕነታቸው፣ ከ29 ወረዳዎች በ25ቱ በኪደተ እግር ጭምር ሐዋርያዊ ጉዞ በማድረግ፥ ካህናትን መሾማቸውን፣ በሥልጠናዎች መሳተፋቸውን፣ በበዓላት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ መስጠታቸውንና የልማት ሥራዎችን መመረቃቸውን የሀገረ ስብከቱ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

በአጠቃላይ፣ በሀገረ ስብከቱ የተጀመረው የመልካም አስተዳደር ጅማሮ በጥናት ላይ ተመሥርቶ በቁርጠኝነት እንደሚቀጥል ጽ/ቤቱ አረጋግጧል፤ የአረጋዊው አባት፥ ወዳጅ ነን፤ ዘመድ ነን፤ ቀራቢ ነን፤ በማለት ሀገረ ስብከቱ በሕግና መርሕ እንዳይመራ በጣልቃ ገብነት አቅጣጫ ለማስለወጥ የሚያሳድሙ ሰዎችን የማስተካከልና የመናፍቃን ቅሬቶችን የማጽዳት ሥራ እንደሚሠራ ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ወደ መንበረ ፓትርያርክ የሚልከው የፈሰስ ገቢ በየዓመቱ ዕድገት የሚታይበት ሲኾን፣ ዘንድሮም ከአምናው ከፍተኛ ልዩነት ያሳየ ውጤት(3 ሚሊዮን ብር ያህል) ማስመዝገቡን ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ ለሶማሌ ክልል አሠቃቂ ጥቃት ተጎጂዎችና አብያተ ክርስቲያን መልሶ ማቋቋሚያ፣ የ100ሺሕ ብር ድጋፍ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዐቢይ ኮሚቴ በተከፈተው የንግድ ባንክ አካውንት አስገብቷል፤ 29ኙም ወረዳዎች የሚሳተፉበት ተጨማሪ ርዳታ ለማሰባሰብ ከሁሉም አካላት የተውጣጣ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡

የርዳታ አሳባሳቢ ኮሚቴው፥ ከሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ ከመንፈሳዊ ወጣቶች ኅብረት፣ ከማኅበረ ቅዱሳንና ከሀገር ሽማግሌዎች የተውጣጡ 14 አባላትን እንዳካተተና በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እንደሚመራ አስታውቋል፤ በቅርቡ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዐደባባይ የሚያካሒደው የገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴ ከዕቅዶቹ አንዱ እንደኾነ ጠቁሟል፡፡

4 thoughts on “የሰሜን ሸዋ ሀ/ስብከት አስተዳደራዊ ችግሮቹን እየፈታ ነው፤ ለሶማሌ ተጎጅዎች 100ሺሕ ብር ረዳ፤ ተጨማሪ ለማሰባሰብ ኮሚቴ አቋቋመ

  1. nwdg August 27, 2018 at 7:11 am Reply

    ለመሆኑ ሐራ በቅ/ሥ/ካቴድራል በጎላጎል አካባቢ እያሰራ ባለው ሕንጻ እየተፈጸመ ስላለው ሕገ ወጥ የኪራይ አፈጻጸም ሰምታችኀል?

  2. Anonymous August 29, 2018 at 9:02 am Reply

    melkam

  3. Anonymous August 30, 2018 at 8:02 am Reply

    Le Betekrstanachn tilk ye astedadrawi tadso yasfeligatal.Sefi Limat,menfesawi agelglot yitebekbnal.Gn gizew gar meramed yalchal astedaderoch rist adrgewu yizewal.Beteley ye IluAbabor Hageresbket yerasun astedader be afatagn kaladese b/yanachn mnm tesfa yelatm.

  4. ananimos September 7, 2018 at 3:24 am Reply

    melkam new. betegbar entebikalen

Leave a comment