የሀ/ስብከቱ ጳጳስ: በወልድያ የበዓለ ጥምቀት ግጭትና ግድያ የጸጥታ ኃይሉን ወቀሱ፤“የእነርሱ መዘዝ ነው፤ወጣቱ አበላሸ የምንለው ነገር የለም”

His Grace Abune Ermias speaks on the Woldias massacre

ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፤ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ

  • መከላከያዎቹ እንዳይመጡ ቀድመን አሳስበናል፤ከዞኑም ጋር ተናበን እየሠራን ነበር፤
  • “በሰላም ሊጠናቀቅ ባለበት ሰዓት መጥተው ግጥም አሉ፤ ይኸው ወጣቱን አሳበዱት፤”
  • “ወጣቱን ሌላ የፖሊቲካ አካል ቀሰቀሰው አሉ፤ ወታደሮቹን ማን ነው የቀሰቀሳቸው?”
  • “የበቀል ነው የሚመስለው፤እንደው ከራሳቸው መካከልም የሚያጠፋ ያለ ይመስለኛል፤”
  • “ታቦቱን ያከበሩት ካህናት፣በጎናቸው ባሉት ካህናት ተገድፈው ነው እንጅ ወድቀዋል፤”
  • ተዉ ብሎ ይህን ማስተካከል እና መሥመር ማስያዝ ያለበት መንፈሳዊ አባት ነው፤
  • ቤተ ክርስቲያኗን ወጣቱ ሰምቶልናል፤ታቦቱ ከገባ በኋላ ሁሉም እንሙት እያለ ነበረ፤

†††

  • “ተረጋግቶ እያለ ድኻ የሚረዳ ልጅ ገድለው ዳግም በእነርሱ ስሕተት ግጭቱ ቀጠለ፤”
  • “ሕንፃ እግዚአብሔር እያፈረሳችሁ ፎቅ ትጠብቃላችሁ፤”ብሎ ሕዝቡ በጣም ተቆጨ፤
  • “ስንቱስ ንብረት ወደመ? የእነርሱ መዘዝ ነው፤ ወጣቱ አበላሸ የምንለው ነገር የለም፤”
  • “መከላከያ ይውጣ፤ ወጣቱ ከከተማው ፖሊስ ጋር ይጠብቀዋል፤” በሚል ተስማማን፤
  • ርእሰ መስተዳድሩም፣ “ሠራዊቱን አስወጣለሁ፤ አጣሪ እልካለሁ፤ አጥፊው ለሕግ ይቀርባል፤ ይፋም አደርጋለሁ፤” ብለዋል፤ ልቅሶ ቤትም ገብተው አብረው እያለቀሱ አጽናንተዋል፤
  • ከኹለት ዙር ውይይት በኋላ፣ ወጣቱን በየአቅጣጫው የሚመሩ ካህናት መድበን ወደየቤቱ እንዲገባ አድርገናል፤ በሰላም እየዘመረም ወደየቤቱ ተመልሷል፤”
  • እኛም በየሐዘን ቤቱ እየዞርን ስናጽናና ውለናል፤ ርእሰ መስተዳድሩ ከተመለሱ በኋላ ከላኳቸው ልኡካን ጋራ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተካትተን እየመከርን ነው፤

†††

በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ፣ በጥምቀት እና በቃና ዘገሊላ በዓል አከባበር ወቅት የተቀሰቀሰው ግጭትና የተፈጸመው ግድያ፣ በጸጥታ ኃይሉ ስሕተት የደረሰ ነው፤ ያሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ረዳት፣ ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፣ ለጠፋው የዜጎች ሕይወት እና ለወደመው ንብረት ወቀሱት፡፡

የቃና ዘገሊላ በዓል፣ እንደ በዓለ ጥምቀት ኹሉ በሥርዐቱ እየተከበረ በሰላም ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት የመጣው የጸጥታ ኃይል “ያልተጠራ” እንደነበር የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ ከመጣ ችግር እንደሚፈጠር ስለታመነ እንዳይመጣ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ቀድመው አሳስበው እንደነበር አውስተዋል፡፡

his-grace-abune-qerlos

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ፤ የሰሜን ወሎ እና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ለበዓሉ አከባበር፣ ሀገረ ስብከቱ ከዞኑ ሓላፊዎች ጋራ እየተናበበ በመሥራቱ የተጠየቀ ተጨማሪ ኃይል እንዳልነበርና “እነርሱ አይምጡ፤ እኛው በእኛው ፕሮግራማችንን እንመራለን፤” በማለት ቀድሞ እንዳሳወቀ ብፁዕነታቸው ጠቁመዋል፡፡

ይኹንና በመምጣታቸው ወጣቱን ለተቃውሞ እንዳነሣሡ ተናግረዋል፤ “ወጣቱን አሳበዱት፤ የተሳደበም ይመስለኛል፤ ድንጋይም ሳይወረውር አይቀርም፤ በጥይት ለቀሙት፤” በማለት የርምጃውን ኢፍትሐዊነት አስረድተዋል፡፡ በማግሥቱም ቀጥሎ የነበረው ግጭትና የንብረት ውድመት መንሥኤ የጸጥታ ኃይሉ እንደኾነ የተናገሩት ብፁዕነታቸው፣ “የእነርሱ መዘዝ ነው፤ እኛ ወጣቱ አበላሸ የምንለው ምንም ነገር የለም፤” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል፡፡

በሞትና መቁሰል ስለደረሰው ጉዳትም፣ “ብዙ ሰው ነው የተጎዳብን፤ ያላወቅነውም ይኖራል፤” ብለዋል ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ፡፡ ግጭቱ በተከሠተበት ወቅት ከመርሳ ከተማ ወደ ወልዲያ ተመልሰው በዚያው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማር በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ገልጸው፣ የጸጥታ ኃይሎቹ ለብተና በተጠቀሙበት አስለቃሽ ጢስ ታቦቱን ያከበሩት ካህናት፣ “በጎናቸው ባሉ ካህናት ተገድፈው ነው እንጅ ወድቀዋል፤” ብለዋል ጥልቅ ቅሬታ በሚደመጥበት አነጋገር፡፡

የጸጥታ ኃይሉን ለምን ማሠማራት እንዳስፈለገ እንደማያውቁ ብፁዕነታቸው ጠቅሰው፣ ኾነ ተብሎ የታቀደ እንደሚመስላቸው ሳይገልጹ አላለፉም – “ለምን እንደመጡ አናውቅም፤ ኾን ብለው ለመምታት ይመስላል፤ ከራሳቸው መካከልም የሚያጠፋ ያለ ይመስለኛል፤” ብለዋል፡፡ አያይዘውም፣ “ወጣቱን ሌላ የፖሊቲካ አካል ቀሰቀሰው ይባል፤ እነርሱን ወታደሮቹን ማን ነው የቀሰቀሳቸው? ሰላም እንዳይኾን!” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጋራ በኹለት ዙሮች በተካሔደው ውይይት፣ ወጣቱ በአጠፌታ ተሠማርቶበት ከነበረው የንብረት ማቃጠልና ማውደም አረጋግተው ወደ አዳራሽ እንዲገባ በማድረግ ከሌሎች የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ጋራ የተሳካ ሥራ እንደሠሩ ብፁዕነታቸው ይገልጻሉ፡፡ ቀደም ሲል ከእግር ኳስ ጨዋታ ጋራ ተያይዞ ተከሥቶ በነበረው የከተማዋ ግጭት በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የማረጋጋት አባታዊ ሚና እንደነበራቸው በማውሳት፣ቤተ ክርስቲያኗን ወጣቱ ሰምቶልናል፤” ሲሉ አመስግነዋል፡፡

ባለፈው ሰኞ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር በተገኙበት በተደረገው ውይይት፣ የመንግሥት ጥፋት በግልጽና በዝርዝር መቅረቡን፤ ለከተማው ሰላምና ጸጥታ በሚረዱ አጠቃላይ መፍትሔዎች ላይም ስምምነት እንደተደረሰ አስታውቀዋል፡፡ ሠራዊቱን ከከተማው እንደሚያስወጡ ርእሰ መስተዳድሩ የገለጹ ሲኾን፣ ለሰላሙና ጸጥታው ወጣቱ ከፖሊስ ተባብሮ እንደሚሠራም አረጋግጧል፡፡ ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ “ስለተፈጸመው ነገር የሚያጣራ አካል እልካለሁ፤ አጥፊው ለሕግ ይቀርባል፤ ለእናንተም ይፋ አደርጋለሁ፤” ማለታቸው ታውቋል፡፡

ከውይይቱ በኋላ አቶ ገዱ፣ ሐዘንተኞችን በየቤታቸው ተገኝተው በማጽናናታቸው ያመሰገኑት ብፁዕነታቸው፣ በቤተ ክርስቲያንም በኩል ካህናትን መድቦ ወጣቱ በሰላም ወደየቤቱ እንዲገባ ከማድረግ ባሻገር፣ እስከ ትላንት ድረስ ሐዘንተኞችን ሲያጽናኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ በአኹኑ ወቅትም በክልሉ መንግሥት ተሠይሞ ከተላከው ልኡካን ቡድን ጋራ፣ እርሳቸውን ጨምሮ የከተማው የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የተካተቱበት ምክክር እየተካሔደ እንዳለ አስታውቀዋል፡፡

እየተከሠተ ያለው የግፍና የጥፋት ድርጊት፣ ሕዝብን ከሕዝብ እያለያየ መኾኑ በእጅጉ እንደሚያሳዝናቸው ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡ ተዉ ማለት ያለበት፣ ይህን ማስተካከልና መሥመር ማስያዝ ያለበት መንፈሳዊ አባት ነው፤” ሲሉ ቤተ ክርስቲያን ጥፋትን የመከላከል፣ አጥፊውን የማውገዝና የመገሠጽ፣ የተበደለው እንዲካስና እንዲጽናና የማድረግ በአጠቃላይ የአገርን ሰላምና የሕዝብን አንድነት የማስጠበቅ ከባድ መንፈሳዊና ታሪካዊ ሓላፊነት እንዳለባት አመልክተዋል፡፡

አባቶችና መንበረ ፓትርያርኩ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብር በመዳፈርና ሥርዐቷን በመጣስ ጭምር ስለተፈጸመው የወልዲያው ግፍ፣ አቋማቸውን እንዲያሳውቁና ኖላዊነታቸውን እንዲያረጋግጡ በብዙኃን መገናኛዎችና በመግለጫዎች የሚሰነዘሩት ጥያቄዎችና ወቀሳዎች እንደቀጠሉ ናቸው፡፡

መኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች፣ ከትላንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓልን ለማክበር በወጡ የወልዲያ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ የተመለከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ድርጊቱን አለማውገዟ ያስተዛዝበናል፤ ብለዋል፡፡

ለተነሣው ግጭትና ለተወሰደው የግድያ ርምጃ የቀረበው ምክንያት፣ “መንግሥትን የሚቃወም ዜማ አሰማችሁ፤” የሚል እንደኾነ በመግለጫቸው የጠቀሱት ፓርቲዎቹ፣ “ይህ ደግሞ መብት መጣስ ነው፤” ብለዋል፡፡

አክለውም፣ “የጸጥታ ኃይሎች ቅዱስ ታቦትን ባከበሩ ቀሳውስት ላይ አስለቃሽ ጭስ መተኮሳቸው ሃይማኖቱን መዳፈር በመኾኑ መንግሥት ድርጊቱን በማውገዝ የእምነቱን ተከታዮች በዐደባባይ ይቅርታ ይጠይቅ፤ ለሟች ቤተ ሰዎች የደም ካሳ እንዲከፍል፤ ግድያው እንዲፈጸም ትእዛዝ የሰጡም ኾነ ጉዳዩን በቸልተኝነት የተመለከቱ የዞኑ ባለሥልጣናት በሕግ እንዲጠየቁ፤ ግድያውን የፈጸሙ የመንግሥት ታጣቂዎች ለሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን፤” ሲሉ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን በመወከል በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ርእሰ መንበርነት አመራር የሚሰጠው ቋሚ ሲኖዶስ፣ ከልደት ጀምሮ በነበሩት ዐበይት ክብረ በዓላት ሳቢያ የተመደቡት ተለዋጭ አባላቱ ብፁዓን አባቶች በየአህጉረ ስብከታቸው በመኾናቸው አለመሰብሰቡ ተጠቁሟል፡፡ ሰሞኑን እስከ ግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ድረስ በተለዋጭነት በተመደቡት አራት ብፁዓን አባቶች አባላቱ በሚቀጥለው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው፣ ጉዳዩን ይመለከተው እንደኾነም ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

 

4 thoughts on “የሀ/ስብከቱ ጳጳስ: በወልድያ የበዓለ ጥምቀት ግጭትና ግድያ የጸጥታ ኃይሉን ወቀሱ፤“የእነርሱ መዘዝ ነው፤ወጣቱ አበላሸ የምንለው ነገር የለም”

  1. Kebede Bogale January 25, 2018 at 10:43 pm Reply

    ይድረስ በውጭም ሆነ በሀገር ውሥጥ ላላችሁ ለቤተ ክርስቲያን ካህናት ==
    ሕዝብ መከራ ሲደርስበት የካህናትና ‘የቅዱሳን ማኅበር” ነን የሚሉት ሚና ምን መሆን ነበረበት ?
    ካህናት ወይም የሃይማኖት መሪዎች በግል ሕይዎታቸው ግፈኞች የሚያደርሱባቸውን ግፍና መከራ ነው በፀጋ መቀበል የሚገባቸው እንጅ፣ በሌሎች የሚደርሠሰውን ግፍ መቃወምና ማውገዝ ይገባቸዋል። ይህን ማድረግ ምንም የሚከለክል የቀኖናም ሆነ የዶግማ ሕግ የለም። መጥምቁ ዮሐንስና እውነተኛው ካህን ዮሐንስ አፈወርቅ በግፈኛ ገዝዎች ግፍ ሲፈጸምባቸው ከነበሩት ከደካማወች ጋር ቁመው ነበር ግፈኞችን ሲያውግዙ የነበሩትና፥ በዚያም ምክንያት ሥጋዊ ሕይዎታቸውን የሰውት። ዛሬ የእኛ ካህናትና ‘’የቅዱሳን ማኅበር አባላት’ ነን የሚሉት ግን፥ ሕዝብን እየፈጀ አገር እያፈረሰ ያለውውን ግፈኛ ገዥ የጨለማ ኃይልን ማውገዝና መገሠጽ ‘’ፖለቲካ’’ ነው በሚል ሺፋን በዝምታ ያልፉታል። እንዲያውም በዚህ ‘’ፖለቲካ ነው’’ በሚል ምክንያት ግፈኛውን ከመገሠጽ ይልቅ፣ ግፍ የሚፈጸምባቸውን ነቅፈው ‘በሰላም ስም’ ከግፈኛው አገዛዝ ጋር መቆምን ይመርጣሉ። እግዚአብሔር ግን በዘመነ ብሉይም በነብያቱ አድሮ እንዲህ ሲል ነበር። አምላክ ቃሉ የማይለወጥ ዘለዓለማዊ ስለሆነ ዛሬም ለእኛ ካህናት እንዲህ እያለ ነው። ’’ የጭቆናን ሰንሰለትና የፍትሕ መጓደልን ቀንበር አስወግዱ፣ የተጨቆኑትንም ነፃ አውጡ !’’ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ፣ ‘’ እነሆ እናንተ በምትጾሙበት ጊዜ ሁሉ የልባችሁን ፈቃድ ትፈጽማላችሁ፣ ሠራተኞቻችሁንም በመጨቆን ትበዘብዛላችሁ። የጾማችሁም መጨረሻው ጠብና ክርክር ስለሆነ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ትማታላችሁ። ታዲያ እንደዚህ ዐይነቱ ጾም ጸሎታችሁን እንድሰማ የሚያደርግ ይመስላችኋዋልን? በምትጾሙበት ጊዜ ሰውነታችሁን ታጎሳቁላላችሁ። ራሳችሁንም እንደ ሙጃ ሳር ዝቅ ታደርጋላችሁ። ዐመድ ነስንሳችሁ ፥ ማቅ አንጥፋችሁም ትተኛላችሁ፤ ታዲያ እናንተ ጾም የምትሉት ይህን ነውን? እኔ በዚህ ደስ የሚለኝ ይመስላችኋልን? እኔ የምፈልገው ጾም ይህ ነው ፣’ የጭቆናን ሰንሰለትና የፍትሕ መጓደልን ቀንበር አስወግዱ፣ የተጨቆኑትንም ነፃ አውጡ ! ካላችሁ ምግብ ለረሀብተኞች አካፍሉ፣ መጠለያ የሌላቸውን ድኾች በቤታችሁ ተቀበሉ፣ የተራቆቱትን አልብሱ፣ ዕርዳታ የሚፈልጉ ዘመዶቻችሁንም ፊት አትንሡ። “ ይህን ብታደርጉ የእኔ ፀጋ እንደ ንጋት ፀሐይ ይበራላችኋል፣ ከቁስላችሁም ፈጥናችሁ ትፈወሳላችሁ። አድናችሁ ዘንድ እኔ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ። እኔም ለእናንተ የምገልጥበት ክብር እንደ ደጀን ሁኖ በሁሉም አቅጣጫ ይጠብቃችኋል፣ በምትጸልዩበት ጊዜም ጸሎታችሁን እሰማለሁ። በምትጠሩኝም ጊዜ መልስ እሠጣለሁ። የጭቆናን ቀንበር፥ የትዕቢትን ፌዝና ክፉ ንግግርን ሁሉ ብታስወግዱ፥ ምግብ በመሥጠት የተራቡ ችግረኞች እንዲጠግቡ ብታደርጉ የከበባችሁ ጨለማ ወደ ቀትር ብርሃን ይለወጣል። እኔ ሁልጊዜ እመራችኋለሁ፣ ሕይወታችሁንም በበረከት እሞላዋለሁ፣ ጤንነትንና ብርታትን በመሥጠት እጠብቃችኋለሁ። ምንጊዜም ከማይደርቅ ምንጭ በቂ ውሃ እንደሚያገኝ የአትክልት ቦታ ትሆናላችሁ። ሕዝባችሁ ቀድሞ ፈራርሰው የነበሩትን ሁሉ እንደ ገና መልሶ በጥንቱ መሠረት ላይ ይሠራል። ስለዚህም እናንተ ቅጽሮችን መልሶ የሚያንጽና ፈራርሰው የነበሩ ቤቶችን የሚያድስ ሕዝብ ተብላችሁ ትጠራላችሁ !! “ ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 58 ፣ ቁጥ. 4-13። ታዲያ እኛስ ዛሬ የምንጾመው ጾም እግዚአብሔር ለነቢዩ ኢሳይያስ ከነገረው ጋር ይመሳሰላል ወይስ አይመሳሰልም ? በተለይ ባገር ውሥጥ ሕዝባችን በግፍ እየጨፈጭፈ ካለው ዘረኛ የግፍ አገዛዝ ጋር እጅና ጉኣንት ሁነው የሚሠሩ ‘የቤተ ክርስቲያን መሪዎች’ና አጃቢዎቻቸው፥ ይህን እግዚአብሔር ለነቢዩ ኢሳይያስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስምንተኛው ምዕት ዓመት መጨረሻ አካባቢ የተናገውን ነገረ እግዚአብሔር ዛሬ እንዴት ያዩት ይሆን ? እንዲህም ይላል፣ “ እንደገናም በዓለም ላይ የፍርድ መጓደልንና ግፍ ተመለከትሁ፣ የተገፉ ጭቁኖች የሚያጽናናቸው አጥተው ያለቅሱ ነበር። የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣን በገዥዎቻቸው እጅ ስለሆነ የሚረዳቸው አላገኙም። ስለዚህም እኔ ‘ በዚህ ሁኔታ ላይ በሕይዎት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱት ይሻላሉ ‘ አልሁ። በተለይም ከነዚህ ከሁለቱ ወገኖች ይልቅ ከቶውኑ ያልተወለዱትና በዚህ ዓለም (በዚች ኢትዮጵያችን) የሚፈጸመውን ግፍና ጭቆና ያላዩ ዕድለኞች ናቸው። “ መጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ 4 ፥ 1-4።
    ከበደ .አ. ቦጋለ

  2. Misrak January 26, 2018 at 5:38 am Reply

    አሳዛኝና አሳፋሪ በደል ነው። መንግስትን ከሚቃወም ዜማና ንጹሃንን ከታቦተ ህጉ ፊት በጥይት ከመድፋት የቱ ይከብዳል? እነኝህ ሰወች አእምሯቸውን ስተዋል ልበል? እንደ ምክንያት ሲያነሱት አያፍሩም? ምንም ችግር ያልፈጠረን ህዝብ በሰላም ሊጠናቀቅ የነበረ በዓል ገብቶ ማሸበር ይሄ ከIsis በምን ይለያል?

  3. Amanuel January 27, 2018 at 3:49 am Reply

    አዎን ብጹዕ አባታችን ትክክል ነዎት ሰዎቹ ሊወቀሱም ሊገሰጹም ይገባቸዋል እግዚአብሔር በደሙ የዋጀውን መንጋ ያለከልካይ ሲገድሉ ኖረዋል ፣ አይከሰሱ እንዲሁ በጥይት አረር ዜጎችን እያነደዱ በበደል ላይ በደል ሲፈፅሙ እንጂ ከጥፋታቸው ሲታረሙ ተሰምተው አያውቁም የዚያ ልብም የላቸውም በእርግጥም የሰዎቹ ልብ ከፈርዖንም በላይ ደንድኗል ።

    አባቶች በተናጥልም ብቻ ሳይብቻ ሳይሆን በብሕረት (በሲኖዶስም) ደረጃ ይህን እኩይ ተግባር በእውነት እና በእምነት ሊያወግዙት ይገባል ። የተሾማችሁበት ትልቁ ዓላማም ይህ ነውና !
    ቀድሞም ሃይ ባይ ቢኖር ሰዎቹ በእግዚአብሔር ላይ እስከመገዳደር ባልደረሱም ነበር አንድ እና ሁለት ሰው ሲገድሉ ዝም ስላላችኋቸው እና ስላላወገዛችኋቸው ይኸው ወደ ጅምላ ግድያ ተሸጋገሩ ።

    በደለኞችን ዝም ብሎ ማየት በበደል እንዲበረቱ ያደርጋልና ዝምታችሁ ለብዙ ጥፋታቸው ምክንያት ስለሆነ እና ስለሚሆን አባቶች መንጋውን እንድትጠብቁ በሾማችሁ በልዑል አምላክ ፊት ከተጠያቂነት ትድኑ ይሆን ???

    አባቶቼ ፍርሃትም ከተባለ ልክ እና መጠን አለው የእናንተ ግን መለኪያ አጣኮ! !
    ለመሆኑ የሚያስፈራችሁ ምን ይሆን? እናንተ የተሰጣችሁን ስልጣን የሚያህል በምድር ላይ ማን ስልጣን አለው? በምድር የምታስሩት በሰማይም የሚታሰር በምድር የምትፈቱትም በሰማይ የሚፈታላችሁ ድንቅ ባለስልጣኖች! !

    ሲያሻችሁ በእምነት ከተጠቀማችሁበት ነፍስን ከስጋ የመለየት ስልጣኑ የተሰጣችሁ የስልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ተካፋዮች! በእነ ሃናንያ እና ሰጲራ ላይ ብቻ የማይቆም ፍርድ ባለቤቶች!

    ታድያን የዚህ ሁሉ ስልጣን ባለቤቶች አባቶቼ ስጋን የሚገድሉ እነኚህ እንዴት ያሸብሯችኋል?
    ስለዚህ ሁላችሁ በሕብረት ገዳዮችን አውግዙ በጎቻችሁን በጠራራ ፀሐይ እየነጠቁ ዝምታው ይብቃችሁ! ሞገስ እና ክብራችሁም ይኸው ነውኮ!

    በነተበ ከስክስ ጫማ መቅደስ እስከመግባትና በዚያም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በቅጥቀጣ ማሰቃየት ለእነርሱ ጀግንነት ይመስላቸው ይሆናል አላወቁት እንጂ ለሞታቸው መጣጣር የለውም ልብ ቢኖራቸው ከፈርዖን ይማሩ ነበር ግን ልቡ ከየት ይምጣ እንጂ!

    ብጹዕ አባታችን መልዕክትዎ አግባብነት ያለው ነውና ክብር ይገባዎታል በረከትዎ ትደርብን የሞቱትን ወገኖቻችንን ነፍስ እግዚአብሔር ብርሃን ያጎናፅፍልን
    ገዳዮችንም እግዚአብሔር ይበቀልልን ኢትዮጵያን ሃገራችንን እናታችንን ቤተክርስቲያንን ጌታችን በቸርነቱ ከጠላቶቿ ይጠብቅልን!!!

Leave a comment