የሰዓሊተ ምሕረት ምእመናን አማሳኞችን በማባረር ካቴድራሉን ተቆጣጠሩ፤ቢሮ አሸጉ፤ለቀጣዩ እየመከሩ ነው

 • ግብረ አበሩ የሰበካ ጉባኤ ም/ል ሊቀ መንበር፣ጸሐፊውና ሒሳብ ሹሙ ታግተው ነበር
 • በፖሊስ ጥበቃ ከእገታ አመለጡ፤ሒሳብ ሹሙ በሽጉጥ ቢያስፈራራም አልተሳካለትም
 • ቤተ ክህነቱን ለ6 ዓመታት ጠይቀናል፤አሁን ምላሽ የምንጠበቀው ከመንግሥት ነው
 • “መፍትሔ ካላገኘን አንወጣም፤” ያሉት ምእመናኑ፣በሰሜናዊ አንቀጽ እየመከሩ ነው

†††

 • አቤቱታውን አጣርቶ ምላሽ ለመስጠት ያልደፈረው ሀ/ስብከቱ ፈራ ተባ ሲል ሰንብቷል
 • ዘግይቶም የመደባቸው፣ እነማሙዬ ሸዋፈራውን መኾኑ፣የአያያዙን ደካማነት ያሳያል
 • የታገደውን የሰንበት ት/ቤት አመራርና የታሸገ ጽ/ቤቱን ለማስከፈት እንኳን ተስኖታል
 • አቤቱታው፥አማሳኞቹ ተወግደው ለሕግ እንዲቀርቡና የኦዲት ምርመራን ይጠይቃል

†††

ላለፉት ስድስት ዓመታት በአማሳኙ መልአከ ብርሃን ቀሲስ ሩፋኤል የማነ ብርሃንና ግብረ አበሮቹ ዓምባገነንነት፣ ሀብቱ በልማት ስም ሲመዘበርና ይዞታው ሲጠፋ የቆየው የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል፣ ምላሽ ከተነፈገው አቤቱታና ምጥንታ በኋላ፣ ዛሬ ዓርብ፣ ታኅሣሥ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠዋት በማኅበረ ምእመናኑ ፍጹም ቁጥጥር ሥር እንዲኾን ተደረገ፡፡

የአካባቢው ወጣቶች፣ የሰንበት ት/ቤት አባላትና ማኅበረ ምእመናኑ በአንድነት በመተባበር በወሰዱት መብረቃዊ ርምጃ፣ ዛሬ ከጠዋቱ 3፡00 ላይ የካቴድራሉን ጽ/ቤት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል፡፡

በሰዓቱ፣ በልማት ክፍሉ ቢሮ ተሰብስበው ሲመክሩ የነበሩት፦ ዋና ጸሐፊው ሊቀ አእላፍ ዕፁብ የማነ ብርሃን፣ ሒሳብ ሹሙ ሊቀ ትጉሃን ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃ እና ሕጋዊ ውክልና በሌለው ሰበካ ጉባኤ ስም በምክትል ሊቀ መንበርነት ተመድቦ የአማሳኞቹ አጋር በመኾን የግል ጥቅሙን ሲያካብት የቆየው ቀሲስ ካሳሁን ገብረ ሕይወት፣ እስከ 6፡00 ድረስ እንዳይወጡ ተከልክለውና ታግተው መቆየታቸው ታውቋል፡፡

ድንገቴው ርምጃ፣ አማሳኞቹ ሰነድና ንብረት እንዳያሸሹም የተደረገ በመኾኑ ባሉበት ማቆየትና መቆጣጠር አስፈላጊ እንደነበር የተናገሩት ምእመናኑ፣ በስም የተጠቀሱት ሓላፊዎች የቢሮውን በር ከውስጥ ቆልፈው አንወጣም፤ በማለታቸው በስፍራው በደረሰው የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ኃይል አማካይነት ንግግር እየተደረገ እስከ ቀኑ 6፡00 እንደ ቆዩ ገልጸዋል፡፡

የጸሎተ ቅዳሴው ሰዓት ደርሶ ምእመናኑ ትኩረታቸውን ወደ ሥነ ሥርዐቱ ሲያደርጉ ወጥተው ለማምለጥ ሲሞክሩ፣ “በሕግ አምላክ፣ እንዳይወጡብን” ብሎ ምእመኑ በመቃወሙ ለተወሰነ ጊዜ እዚያው በፖሊስ እንዲጠበቁ ለማድረግ ተችሎ የነበረ ቢኾንም፣ ከቆይታ በኋላ በፖሊስ መኪና ካቴድራሉን እንዲለቁ እንደተደረጉ የዐይን እማኞች አስረድተዋል፡፡

ሒሳብ ሹሙ፣ በማኅበረ ምእመናኑ ላይ ሽጉጥ በማውጣት ለማስፈራራት ቢሞክርም በገጠመው ጥብዓት የተመላበት መቋቋም እንዳልተሳካለት ተገልጿል፡፡ “ከዚህ ቀደምም ልማድ አለው፤” ይላሉ ምእመናኑ፡፡

ላለፉት ስድስት ዓመታት ከሀገረ ስብከቱ እና ከመንበረ ፓትርያርኩ መፍትሔ ለማግኘት በትዕግሥትና በተስፋ አቤቱታቸውን እያቀረቡ ሲጠብቁ መቆየታቸውን በምሬት ያወሱት ማኅበረ ምእመናኑ፣ ኹነኛ ምላሽና መፍትሔ ካላገኙ ካቴድራላቸውን በመቆጣጠራቸው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡“መፍትሔና ምላሽ ሳናገኝ ከካቴድራሉ አንወጣም፤ የምንጠብቀውም ከፍትሕና ከጸጥታ አካሉ ነው፤” ብለዋል ምእመናኑ፡፡ ዜናው በሚጠናቀርበት ሰዓትም፣ በካቴድራሉ ሰሜናዊ በር ተሰብስበው በቀጣዩ ርምጃዎቻቸው ላይ እየመከሩ እንዳሉ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዓምባገነንነት ሕግና አሠራር እየተጣሰ የሚፈጸም የቀኖና ቤተ ክርስቲያን መተላለፍን፣ የመልካም አስተዳደር በደልን፣ ልማትን ሽፋን ያደረገ ምዝበራንና ውድመትን በመንሥኤነት ያስቀመጠው የማኅበረ ምእመናኑና የሰንበት ት/ቤቱ አቤቱታ፤ ሦስት ዐበይት ጥያቄዎችን፣ ልዩ ሀገረ ስብከቱን በበላይነት ለሚመሩት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የቀረበበት ነው፡፡ እኒህም፡-

 • ዋና አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣ ዋና ጸሐፊው ዕፁብ የማነ ብርሃን፣ የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር ካሳሁን ገብረ ሕይወት እና ሒሳብ ሹሙ ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡ፤
 • በሕገ ወጥ መንገድ ያለምእመን ተሳትፎ በዝግ አዳራሽ የተመረጠውና በቀሲስ ካሳሁን ገብረ ሕይወት የሚመራው ሰበካ ጉባኤ ፈርሶ በቃለ ዐዋዲው መሠረት ምእመኑንና የካቴድራሉን አገልጋዮች የሚወክል ሰበካ ጉባኤ እንዲመረጥ፤
 • በቀጣይም በካቴድራሉ አስተዳደር ላይ የቀረቡትን አቤቱታዎች አጣርቶ ለሕግ የሚያቀርብ ኮሚቴ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከሀገረ ስብከት፣ ከወረዳ ቤተ ክህነትና ከአጥቢያው ምእመናን እንዲዋቀር፤
 • የውጭ ኦዲተር ተመድቦ የካቴድራሉ ገቢና ወጪ ኦዲት እንዲደረግ የሚሉ ናቸው፡፡

ጥያቄዎቹ፣ የዋና አስተዳዳሪውን የአፈና ሙከራ አልፈው በፓትርያርኩ ከተሰሙና ተጣርተው በሪፖርት እንዲቀርቡላቸው ለሥራ አስኪያጁ ጎይትኦም ያይኑ ከተመሩ ሳምንታት ቢቆጠሩም፣ ጣልቃ ገብተዋል በተባሉ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት ያልተገባ ምልጃ፣ “ወቅቱ አይደለም” የሚለው ሥራ አስኪያጁ ፈራ ተባ በማለቱ የረባ ሥራ ሳይሠራ በእንጥልጥል ተይዞ ሰንብቷል፡፡ በዚሁ የተደፋፈረው ዋና አስተዳዳሪውም፣ የሰንበት ት/ቤቱን ጽ/ቤት በማሸግና የሥራ አመራሩንም በማገድ ማናለብኝነቱን አሳይቷል፡፡ እግዱን እንዲያነሣና ያሸገውን እንዲከፍት በክፍለ ከተማው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ልኡካን ሲጠየቅም፣ ዋስትና ካልተሰጠኝ በማለት ከመገዳደሩም በላይ እንደ ሕገ ወጡ ሰበካ ጉባኤ ሁሉ የሰንበት ት/ቤቱንም አመራር በሚመቸው አኳኋን ለማዋቀር ዝቷል፡፡

ሀገረ ስብከቱ፣ አማሳኞቹ፣ ምዝበራቸውን ሕጋዊ ልባስ ከሚሰጡበትና “የጎማ ማኅተም” ካደረጉት ሕገ ወጡ ሰበካ ጉባኤ አሠራር በመነሣትና በአቤቱታው የተጠቆሙ ዐበይት ችግሮችን ለይቶና አጣርቶ ኹነኛ የመፍትሔ ሐሳብ ማቅረብ ሲገባው፣ የችግሮቹ መገለጫ በኾነው የሰንበት ት/ቤቱ መታሸግ መለስተኛ ጉዳይ ተጠምዶ ከርሟል፡፡ ያም ኾኖ ውጤት የለም፡፡ ይብሱኑ፣ አቤቱታውን አጥንተው እንዲያቀርቡ በሚል መሠሪውን አማሳኝ ማሙዬ ሸዋፈራውንና ለከፋ ሙስና እየተሟሟቀ ያለን ሌላ ዋና ሓላፊ በአስተዳደር ጉባኤ መመደቡ፣ ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኝነት እንዳነሰውና ደካማ አያያዙን አረጋግጧል፡፡

በሌለው ምግባር የሀ/ስብከቱ የምግባረ ሠናይ ዋና ክፍል ሓላፊ ኾኖ ሳለ፣ የሰው ኃይል አስተዳደሩንና የልማትና ዕቅድ ዋና ክፍሎችንም ሥራዎች ደራርቦ በመያዝ ያለአቅሙና ያለሞያው የሚያተራምሰው ማሙዬ ሸዋፈራሁ፣ በአኹኑ ወቅት የሕገ ወጥ ቅጥርና ዝውውር ገበያውን በኔትወርኮቹ በማድራት ግንባር ቀደም ተጠቃሚ በመኾኑ፣ “እንደ ሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራሉ ባሉ አብያተ ክርስቲያን የሚፈጠሩ ውዝግቦች ሠርግና ምላሹ ናቸው፤” ይላሉ የጽ/ቤቱ ምንጮች፡፡

ከጨቋኞቹና መዝባሪዎቹ አማሳኞች ጋራ በእጅ መንሻ እየተደራደረ አቤቱታዎችን ማድበስበስ የለመደው መፍቀሬ መተትና ጥንቆላ ማሙዬ ሸዋፈራው፣ የካህናቱንና የምእመናኑን ምሬት “ከፈ* አልቆጥረውም፤” ባይ በመኾኑ፣ የሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት በሐቅና በቅንዓት ያቀረቡትን አቤቱታ በቀጥታና በቅንነት አጥንቶ የሚያቀርብበት ሞራላዊ ብቃትና ሥልጣን የሌለው በመኾኑ ለጥናት መመደቡ በአስቸኳይ ሊጤን ያስፈልጋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ፣ የልዩ ልዩ አጥቢያዎችን ውዝግብ አጣርተው እንዲያቀርቡ እስከ አኹን ከሚመድባቸው ልኡካን ጥቂት የማይባሉት እንደ ማሙዬ፣ ለቤተ ክርስቲያን መብትና ለሕዝብ ሰላም ሳይኾን አጋጣሚውን ለግላቸው ለመጠቀም ያሰፈሰፉ ተደራዳሪዎች እንደኾኑ በተደጋጋሚ እንደታዘበ የተገለጸው ሥራ አስኪያጁ ጎይትኦም ያይኑ፣ የራሱን የመረጃ ምንጮች እየተጠቀመ የሚመሰገኑ ርምጃዎችን መወሰዱ የሚካድ ባይኾንም፣ በሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል ጉዳይ ፈራ ተባ ማለቱና መለሳለሱ እያስወቀሰውና ትዝብት ላይ እየጣለው ይገኛል፡፡

ይልቁንም፣ ሰሞኑን ከኢኢተቤ-ቴቪ ጋራ ባካሔደው ቃለ ምልልስ፣ ምእመኑ በፍትሕ ዕጦት ተመርሮ የቤተ ክርስቲያኑን መብቶችና ጥቅሞች ለማስከበር የሚወስደውን ርምጃ አላግባብ ሲኮንን ተደምጧል፡፡ ዛሬ ጠዋት በሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል እንደታየው፣ የአካባቢ ወጣቶችና ማኅበረ ምእመናን፣ አማሳኝ ሓላፊዎችን እስከ ማገት፣ የተሽከርካሪዎቻቸውን ጎማ እስከ ማስተንፈስና ጽ/ቤቶችን በይደው እስከ ማሸግ የሚደርሱት፣ ሥራ አስኪያጁ በዚያው ቃለ ምልልሱ እንደተናገረው፣ በቃለ ዐዋዲው መሠረት የካህናቱና፣ የምእመናኑንና የሰንበት ት/ቤቱን ውክልና አረጋግጦ የተመረጠና ሓላፊዎቹን በደንቡ ተቆጣጥሮ ማሠራት የሚችል ሕጋዊ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ባለመኖሩ ነውኮ፡፡

አኹን በሥራ ላይ ያለው ‘ሰበካ ጉባኤ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ያለምእመኑና ያለሰንበት ት/ቤቱ ተሳትፎ በዝግ አዳራሽ የተመረጠ ሲኾን፣ በምክትል ሊቀ መንበርነት የተመደበውም፣ ከጧት እስከ ማታ በቢሮ እየዋለ የአማሳኞቹን ፍላጎትና ዓላማ በማስፈጸም በእጅጉ የሚወቀስ ነው፡፡ ቀደም ሲል በልማት ክፍል ሓላፊነት የሠራ ሲኾን፤ በምክትል ሊቀ መንበርነት ከተመረጠ በኋላ ለክስረት ከተዳረገ ኑሮው ተርፎ የግል ኑሮውን ማደላደሉ ተጠቁሟል፤

“ቢሮ የሚገባው እንደ መደበኛ ሠራተኛ ጠዋት 2፡00 ነው፤ አስተዳዳሪው እንደ ቋሚ ሠራተኛ ያዝዘዋል፤ የአካባቢው ተወላጅ ነኝ፤ በሰንበት ት/ቤት ያደግሁ ነኝ፤ እያለ ስለ ምእመናኑ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት አስተዳዳሪውን በዓምባገነንነቱ ያደፋፍረዋል፤ ከነባር የሰንበት ት/ቤት አባላት ጋራ ያጋጫል፤ የተመረቀው በሰርቬይንግ ቢኾንም ኢንጅነር ነኝ እያለ ግንባታዎችን ይከታተላል፤ አንዳንዶቹንም በጨረታ ስም ራሱ ይዞ ይጠቀምባቸዋል፤ በባንክ ዕዳ ምክንያት በሐራጅ ሊሸጥ የነበረ ቤቱን አስመልሶ ኑሮውን አደላድሏል፤” ይላሉ ማኅበረ ምእመናኑ፡፡

ይልቁንም በአቤቱታቸው እንዳሰፈሩት፣ አባቶቻችን የእርሻ መሬታቸውን ሰጥተው በድህነት አቅማችን ያለንን ኹሉ መሥዋዕት አድርገን እዚህ ባደረስናት ቤተ ክርስቲያናችን ተገቢውን አምልኮ መፈጸም ስላልቻልንና በመልካም አስተዳደር አለመስፈን ከፍተኛ በደል እየደረሰብን ስለኾነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ሀገረ ስብከቱ ተገንዝቦ ለአስተማሪና ኹነኛ የጋራ መፍትሔ ሊተጋ ይገባል፡፡

የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል ማኅበረ ምእመናንና የዕውቀት ብርሃን ሰንበት ት/ቤት ለፓትርያርኩ ያቀረቧቸው መፍትሔና ምላሽ የሚሹ አቤቱታዎች፤

የማኅበረ ምእመናኑ አቤቱታ፡-

የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል፣ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙና ረጅም ዕድሜ ካስቆጠሩ አድባራት መካከል የምትጠቀስ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ የአጥቢያው ምእመናን ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን መሥዋዕት በማድረግ በሰበካ ጉባኤ አባልነት፣ በሕንጻ አሠሪ ኮሚቴነት፣ በአስተባባሪነትና በሌሎችም ዘርፈ ብዙ አገልግሎች ላይ በመሳተፍ ቤተ ክርስቲያኒቱ አሁን ያለችበት የዕድገት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ግንባር ቀደም በመኾን ጉልሕ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ የቤተ ክርስቲያኗን የቦታ ይዞታ ለማስከበርና የተጀመረው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተጠናቆ አገልግሎት እንዲጀምር እንዲሁም፣ በደብሩ ውስጥ ትልልቅ መሠረተ ልማቶች እንዲከናወኑና የአምልኮ ሥርዐቱ እንዲስፋፋ በተደረገው ጥረት ውስጥ የአጥቢያው ምእመናን፣ የአካባቢው ወጣቶች፣ የደብሩ ካህናትና የሰንበት ት/ቤት በጋራ በመኾን ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን፣ አመጣጣቸው ሌላ አጀንዳ ያለው እስኪመስል በቡድን ከሳሪስ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን የመጡት የአሁኑ አስተዳዳሪ የቀድሞው ጸሐፊ፣ የአሁኑ ዋና ጸሐፊ የቀድሞው ም/ጸሐፊ፣ የሒሳብ ሹም፣ የእነርሱን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ ከሦስት በላይ ካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም በሕዝብ ሳይመረጡ ራሳቸውን የሰበካ ጉባኤና የልማት ኮሚቴ አድርገው በተሾሙ ግለሰቦች አማካይነት ከላይ የተጠቀሰውን የምእመኑንና የወጣቶችን ተሳትፎ ችላ በማለትና የቤተ ክርስቲያኒቱን መተዳደሪያ ሕግ(ቃለ ዓዋዲ) በመጣስ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሕግና በምእመናን ተሳትፎ የምትመራ መኾንዋ ቀርቶ በጥቂት ጥቅመኛ ግለሰቦች እንድትመራ ተደርጋለች፡፡

ለዚህም ማሳያ የሚኾኑና ካለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ወዲህ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ እየተፈጠረ ያለውን የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሕገ ወጥ አሠራሮች የሚያሳዩ ዋና ዋና ነጥቦች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፡፡

 1. ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያን ባወጣው ሕግ መሠረት፣ አንድ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚመራው ከምእመናን፣ ከካህናት፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ተውጣጥቶ በተመረጠ ሰበካ ጉባኤ ኾኖ ሳለ የደብሩ የአስተዳደር አካላት ይህን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጎን በመተውና በሕዝብ ተሳትፎ የተመረጠን ሰበካ ጉባኤ በማፍረስ ከ2006 – 2008 ዓ.ም ለሁለት ዓመት ያህል ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለሰበካ ጉባኤ የጥቅም ተጋሪያቸው በኾነው ምክትል ሊቀ መንበር ቀሲስ ካሳሁን ገብረ ሕይወት ተባባሪነት ብቻ ስትመራ ቆይታለች፡፡
 2. በአሁኑ ወቅት አለ የሚባለው ሰበካ ጉባኤ አመራረጡ ፍጹም ከቃለ ዐዋዲው መመሪያ ውጪ አስተዳደር ክፍሉ ለራሱ ዓላማ ማስፈጸሚያ ይኾኑ ዘንድ አጋር ይኾኑኛል፣ በአስተዳደር ክፍሉ ቀድሞ የሚዘጋጅላቸውን ቃለ ጉባኤ ከመፈረም የዘለለ መብት አይኖራቸውም፤ ያሏቸውን እጩ ተመራጮች አዘጋጅተው ለማጸደቅ ያህል ብቻ ያለ ቅስቀሳና ያለማስታወቂያ አግባብ ባልኾነ መንገድ ያለምንም የምእመናን ተሳትፎ የካቴድራሉ የአስተዳደር አካላት የራሳቸውን ውስን ደጋፊዎችና ምእመኑን የማይወክሉ ጥቂት ግለሰቦችን ብቻ በማሳተፍ በዝግ አዳራሽ ውስጥ የብዙኃኑን ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ባላሳተፈ መልኩ በተጽዕኖ በተሰበሰቡ የካቴድራሉ ካህናትና የአብነት ተማሪዎች እንዲሁም የአካባቢውን ሕዝበ ክርስቲያን በማይወክሉ ጥቂት ወዳጆቻቸው ተሳትፎ የተመረጠ ነው፡፡ በመኾኑም የአጥቢያውን ምእመናን የሚወክል ሰበካ ጉባኤ የለም፡፡
 3. የቤተ ክርስቲያኒቱ የገንዘብ አጠቃቀም ግልጽነት የጎደለው ከመኾኑም ባሻገር ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ምንም ዓይነት የሥራና የሒሳብ ሪፖርት ቀርቦ አያውቅም፡፡ የካቴድራሉ የአስተዳደር ክፍልም ሪፖርት ለማቅረብም ፈቃደኝነት የሌለው በመኾኑ ቃለ ዐዋዲውን የሚፃረር ከመኾኑም በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ ለከፍተኛ ምዝበራ እየተጋለጠ መኾኑ አያጠያይቅም፡፡ (የሰው ምስክር አለ እንዲሁም በሚመለከተው አካል የሚጣራ)
 4. በቤተ ክርስቲያኒቱ እየተከናወነ ያለው የልማት ሥራ፣ በቃለ ዓዋዲው መሠረት የልማት ኮሚቴ ተዋቅሮ በዕቅድና በሥርዐት ሊመራ ይገባል፡፡ ምንም እንኳን ለስሙ የልማት ኮሚቴ ተዋቀረ ቢባልም ያለዕቅድና ያለበቂ ጥናት በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ሓላፊነት ላይ በሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች የግል ፍላጎትና ሐሳብ ብቻ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍተኛ ለኾነ የገንዘብና የይዞታ ብክነት ውስጥ እንድትገባና በልማት ስም በሚወጣ የገንዘብ ወጪ የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ የግለሰቦች መጠቀሚያ እንዲኾን በር ከፋች ኾኗል፡፡
 5. በደብሩ እየተከናወኑ ያሉ ግንባታዎች፥ሕገ ወጥና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማስተር ፕላን ውጪ ከመኾናቸውም በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገጽ{ እያበላሹ ያሉ ግንባታዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነው በቅርቡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ የተገነቡ ሕገ ወጥ የንግድ ሱቆች፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዲዛይን ባላገናዘበ ኹኔታ በስሜ{ዊነት የተሠራው ዐውደ ምሕረት ተጠቃሽ ነው፤በቀጣይም ይኸው ዐውደ ምሕረት የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን እይታ የሸፈነ በመኾኑ ይህን ታሪካዊ ስሕተት ለመሸፈን፣“የቤተ ክርስቲያኑ ጣሪያ አፍስሷል፤” በሚል ምክንያት በሚሊዮኖች የሚገመተውን ዋና ጉልላት(ዶም) ለማፍረስ እየተሯሯጡ ይገኛሉ፡፡ (የሰነድና የሰው ማስረጃ አለ)
 6. የቤተ ክርስቲያኒቱን የቦታ ይዞታ፣ ሰበካ ጉባኤ በሌለበትና ግልጽነት በጎደለውና ሕገ ወጥ በኾነ መንገድ በድብቅ ለግለሰቦችና ለተለያዩ ድርጅቶች ለረጅም ዓመት በኪራይ መልክ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ (በሚመለከተው አካል የሚጣራ)
 7. የካቴድራሉ የአስተዳደር አካላት ቦታ በሚያከራዩበት ወቅት ውል ያጭበረብራሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚኾነው፣ የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ዋና ጸሐፊ በነበሩበት ወቅት ከሰበካ ጉባኤው ዕውቅና ውጪ ለካቴድራሉ አገልግሎት የተረከቡትን ማኅተም ሕገ ወጥ ለኾነ ተግባር በመጠቀም/ሰነድ በማጭበርበር/፣ «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» እንዲሉ የቀድሞው የሰበካ ጉባኤ የአገልግሎት ዘመን እየተጠናቀቀ ባለበት ወቅት የጊዜ ገደቡ ያላለቀውን የቦታ ኪራይ ውል ሦስት ወር አስቀድሞ እና የውል ቀኑን ወደፊት ውሉ ወደፊት በሚጠናቀቅበት ቀን ማለትም ታኅሣሥ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ለሚታደስ ውል ጳጉሜን 5 ቀን 2005 ዓ.ም በማዘጋጀት የእድሳት ውል በመፈጸም የእምነት ማጉደልና የሰነድ ማጭበርበር ፈጽመዋል፡፡ (የሰነድ ማስረጃ ተያይዟል፤ የሰው ምስክር አለ)
 8. የደብሩ አስተዳዳሪ እና የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር፣ ሰበካ ጉባኤ በሌለበት በቃለ ዐዋዲው ላይ ከተቀመጠላቸው ሥልጣን ውጪ፣ ከሀገረ ስብከቱ ምንም ዐይነት የተለየ መመሪያ ሳይሰጣቸው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በውርስ ያገኘችውንና በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ካርታ የወጣለትን ጉርድ ሾላ አካባቢ የሚገኝ ስፋቱ 169 ሜ.ካሬ የኾነ ቦታን በጨረታ አወዳድሮ በመሸጥ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት አባክነዋል፡፡ (የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃ አለ)
 9. በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተገነቡት ሱቆች በሕጋዊ መንገድ ሊከራዩና ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን ገቢ ሊያስገኙ ሲገባ፣ በደብሩ የአስተዳደር ሓላፊነት ላይ የሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች ሱቆቹን በቤተሰዎቻቸውና በወዳጆቻቸው ስም በመቀራመትና የተከራየ በማስመሰል ለግል ጥቅማቸው እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡
 10. የቦታ ኪራይን በተመለከተ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለአድባራትና ገዳማት በ2007 ዓ.ም. ባወጣው መመሪያ መሠረት፣ ገዳማትና አድባራት ቦታን ማከራየት የሚችሉት ለአንድ ዓመት ብቻ ኾኖ ሳለ ይህን መመሪያ ወደ ጎን በመተውና ከሰበካ ጉባኤ ዕውቅና ውጭ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቦታ ተፈዘር ለተሰኘ አክሲዮን ማኅበር እና ለስሪ ኤፍ(3F) የግል ድርጅት በራሳቸው ወጪ ሱቅ ሠርተው እንዲጠቀሙበት ለ10 ዓመት ቦታው በኪራይ መልክ እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የካቴድራሉ የአስተዳደር ክፍል፣ ሱቆቹ የተገነቡት በሰበካ ጉባኤው አማካይነትና በቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ እንደኾነ አስመስለው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና የሀገረ ስብከት ሓላፊዎች በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ በማኖርና የሚመለከታቸውን አካላት በማሳሳት ትልቅ ድፍረት የተሞላበት ስሕተት ፈጽመዋል፡፡ በተጨማሪም ቦታውን ተከራይተው የራሳቸውን ግንባታ ያከናወኑት የግል ድርጅቶች ተገቢውን የቦታ ኪራይ ክፍያ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ገቢ እያደረጉ ለመኾኑ አጠራጣሪ ነው፡፡ ከባለሀብቶቹ በግል ጉርሻ በመቀበል የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም እያስቀሩ ይገኛሉ፡፡ (የሰነድና የምስል ማስረጃ)
 11. በቤተ ክርስቲያኒቱ ማስተር ፕላንና መንግሥት ለቤተ ክርስቲያኒቱ በሰጣት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መሠረት፣ለቀብር አገልግሎት የሚውል ራሱን የቻለ የቦታ ይዞታ እያለ ቦታውን ያለአግባብ በመጠቀም የአካባቢው ምእመናን ተገቢውን የቀብር ቦታ በማጣት ከፍተኛ ችግር እየገጠመን ከመኾኑም በላይ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ የሚለዩ ምእመናን መቀበሪያ አጥተው በአኹኑ ሰዓት ወንዝ ዳርና ምልስ አፈር ላይ እንዲቀበሩ መደረጉ አስከሬኖቹ በውኃ ያለመወሰዳቸውና በአውሬ አለመነጠቃቸው መተማመኛ የሌለው በመኾኑ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ጥሎናል፡፡ (የሰው ማስረጃና በሚመለከተው አካል የሚታይ)
 12. በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የምንገኝ ምእመናን ያለአግባብ ለልማት በሚል ሰበብ ከአቅም በላይ የኾነ ገንዘብ እንድንከፍል ጫና እየተደረገብን ይገኛል፡፡ (የሰነድ ማስረጃ ተያይዟል)
 13. በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ታቅፈው የሚገኙ የሰንበቴ ማኅበራትን ያለአግባብ ለልማት በሚል ሰበብ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲከፍሉ ጫና እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡
 14. የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታዊነት የሚዘክሩ ነባር ቅርሶችና ከቤተ ክርስቲያኒቱ ምሥረታ ጋራ አብረው የተተከሉ ሀገር በቀልና ዕድሜ ጠገብ ዝግባዎች፣ የሐበሻ ጥዶች፣ ሾላዎች፣ ወይራዎች እና ሌሎችም ዐጸዶች ከልማት ጋራ ምንም በማይገናኝ ኹኔታ ያለምንም በቂ ምክንያት ተጨፍጭፈው እንዲጠፉ እየተደረገ ነው፡፡ (የሰው ምስክር አለ)
 15. የአካባቢው ምዕመን ተገቢውን ሥርዐተ አምልኮ እንዳይፈጽም በዕለተ ሰንበት ከሌሊቱ 9 እና 10 ሰዓት ቅዳሴ እየገቡ ቅዳሴውን ኾን ተብሎ ምእመኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት የማይችልበት ሰዓት ላይ በማድረግ፣ ምእመኑ ተገቢውን አምልኮ እንዳይፈጽም እየተደረገ ሲሆን ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል የሚመጡ ምእመናንም ሥርዓቱን ጠብቀው እንዳይቆርብ እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቅዳሴ ሰዓቱ ሌሊት በመኾኑ ምክንያት የአጥቢያው ምእመናን ለስርቆትና ለድብደባ እየተጋለጥን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አብዛኛው ምእመን ወደ ሌሎች በአቅራቢያችን ወደሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሔደን ለማስቀደስ እየተገደድን ነው፡፡
 16. ነባር የካቴድራሉ ካህናትና አገልጋዮች ያለአግባብ ወደ ሌላ ደብር እንዲዘዋወሩና በምትኩ ለአካባቢው ምእመናን እንግዳ የኾኑ ካህናት እንዲመጡ በማድረግ በምእመናኑና በደብሩ አገልጋይ ካህናት መካከል ያለው ማኅበራዊ ትስስር አናሳ እንዲኾን ከማድረግ ባሻገር አዲስ ተዘዋውረው የሚመጡት ካህናት የአጥቢያውን ምእመን በንስሐ አባትነት እንዳያገለግሉ ሕገ ወጥ መመሪያ በመስጠት የአካባቢው ምእመን ከካህናት አባቶች ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኝ እየተደረገ ነው፡፡ ይህም የአካባቢው ምእመን ለከፍተኛ የመንፈሳዊ ሕይወት ቀውስ እንዲዳረግና ለኑፋቄ እንዲጋለጥ ምክንያት ኾኗል፡፡
 17. ከሀገረ ስብከቱ እውቅና ውጭ ያለአግባብ የካህናት ቅጥር ይካሔዳል፡፡
 18. የካቴድራሉ አስተዳዳሪ የቤተ ክርስቲያኒቱ መደበኛ አገልጋይ ኾነው ሳለ ዘወትር በሥራ ገበታቸው ላይ ተገኝተው ተገቢውን አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን መስጠት ሲገባቸው በተደጋጋሚ ለረጅም ወራት ከሥራ ገበታቸው በመራቅና “ለግል ጉዳይ ወደ ሰሜን አሜሪካን ሔደዋል፤” እየተባለ በርካታ ምእመናን የጋብቻ፣ የቀብር፣ የልደት ማስረጃዎችን በወቅቱ ለማግኘት እየተቸገሩና አላስፈላጊ እንግልት እየደረሰባቸው ከመኾኑም ባሻገር በቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ አስተዳደር ላይ በርካታ ክፍተቶች እየተፈጠሩ ይገኛል፡፡(የሰው ምስክር አለ)
 19. የካቴድራሉን ዋና አስተዳዳሪ ጨምሮ ሌሎች የአስተዳደር አካላት ምእመኑንና የካቴድራሉን አገልጋዮች በፍቅርና በሥርዐት ከመምራት ይልቅ ከአንድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የማይጠበቅ ነውር የተሞሉ ቃላትን በመጠቀምና ጸያፍ ስድቦችን በመሳደብ በርካታ የካቴድራሉ አገልጋዮች ከመንፈሳዊ አገልግሎትና ከቤተክርስቲያን እንዲርቁ ምክንያት ኾነዋል፡፡
 20. በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ የአጥቢያውን ምእመናን «ከአንድ ጧፍ የማያልፍ የጉርድ ሾላ ሕዝብ አሁን ለሰዓሊተ ምሕረት አይጠቅማትም፤ የሚያስፈልጓት በገንዘብ የሚደግፏት ከሲኤምሲና ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ባለሀብቶች ናቸው፤» ብሎ የአካባቢውን ምእመን በመዝለፍና በማንቋሸሽ በርካታ ምእመናን አዝነው ከቤተ ክርስቲያን እንዲርቁ እየተደረገ ነው፡፡ (የሰው ምስክር አለ)
 21. ለመንፈሳዊ ትምህርት ከጋምቤላ ክልል ወደ ካቴድራሉ መጥተው መንፈሳዊ ትምህርት ሲከታተሉ የነበሩትን 30 ደቀ መዛሙርት፣ “ለቤተ ክርስቲያን አያስፈልጉም” በሚል ከትምህርት ገበታቸው በማፈናቀል ከቤተ ክርስቲያን እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡
 22. ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የኾኑ የተለያዩ ድርጊቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይከናወናሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ፣ ከጥቂት ወራት በፊት በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ስብሰባ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተ መቅደስ ውስጥ ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ የተከናወነው ድርጊት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በተጨማሪ ከጥቂት ዓመት በፊት በተመሳሳይ መንገድ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ዋና አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ ካቴድራሉ ራሱን የቻለ የማጥመቂያ ስፍራ(ክርስትና ቤት) እያለው ልጃቸውን ቤተ መቅደስ ውስጥ በማስገባት በቤተ መቅደስ ውስጥ ክርስትና እንድትነሣ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በድንግልና ተወስነው ያልኖሩ ምእመናን በመዓስባን ሥርዐት ጋብቻ ለመፈጸም ሲመጡ፣ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን በመጣስ ሥርዐተ ተክሊል እንዲፈጽሙ ይደረጋሉ፡፡
 23. ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ፣ ዋና አስተዳዳሪው ቅዳሴ ቀድሰው ምእመኑን ሳያቆርቡ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው ይቀመጣሉ፤ ቅዳሴ ያልቀደሰ ካህን እንዲያቆርብ ይደረጋል፤ በዐበይት በዓላት ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቱን ትውፊት ባልጠበቀ ኹኔታ የምዕራባውያንን ባህል በሚያንፀባርቁ ጌጣጌጦች ቤተ መቅደሱ ዲኮር(እንዲያሸበርቅ) ይደረጋል ወዘተ…
 24. የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ ከዚህ በፊት በየትም ቤተ ክርስቲያን ታይቶ በማይታወቅ ኹኔታ በቤተ መቅደስ ውስጥ ለምእመናን መታደል ያለበት የኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ብቻ ኾኖ ሳለ ይህን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ወደ ጎን በመተው ከየት እንደመጣ በማይታወቅ ሥርዐት፣ ካህናቱን ከቅዳሴ ፍጻሜ በኋላ በሦስቱም የቤተ መቅደሱ መንበር ትይዩ በመመደብና ምእመናኑን ዕጣን እንዲያበሉ በማዘዝ በቅዳሴ ላይ የተሳተፉትንና ቅዱስ ቁርባን የተቀበሉትን ምእመናን ዕጣን እንዲበሉ በማድረግ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ አሳዛኝ ተግባር በተደጋጋሚ ፈጽመዋል፡፡ (የሰው ምስክር አለ)
 25. ከሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ በማን አለብኝነት አገልጋዮች በ40 ቀን ውስጥ ትዳር እንዲይዙ አግባብ ያልኾነ መመሪያ በማስተላለፍና የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ በመመሪያው መሠረት፣ በ40 ቀን ውስጥ የትዳር አጋር ፈልጎ ትዳር የማይዝ አገልጋይ ርምጃ እንደሚወሰድበት በመግለጽ አገልጋዮች አላስፈላጊ ጭንቀት ውስጥ ከመግባታቸውም ባሻገር አንዳንዶች ካለ ፍላጎታቸው ወደ ምንኵስና ሕይወት የገቡበት ኹኔታም አለ፡፡ (የሰነድ ማስረጃ ተያይዟል)
 26. የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ ቤተ ክርስቲያኒቱ የአምልኮ ስፍራ መኾኗን ችላ በማለትና ለግል ምቾት በመጨነቅ በሕዝብና በቤተ ክርስቲያን ገንዘብ በቤተ ክርስቲኒቱ ቅጽር ውስጥ እጅግ ዘመናዊና ቅንጦት የበዛበት ማረፊያ ክፍል በማስገንባት፤ ለአንድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሲባል አስፈላጊ ያልኾኑና እጅግ ውድ ቁሳቁሶችን በማሟላትና በማረፊያ ክፍሉ ውስጥ ግምቱ ኹለት መቶ ሰማንያ አምስት ሺሕ ብር/285,000 ብር/ የሚያወጣ ዘመናዊ ጃኩዚ በማስገጠም ቤተ ክርስቲያኒቱን ከአምልኮ ስፍራነት ወደ ግል መኖሪያነት ቀይረዋታል፤ የግል ፍላጎታቸውን ለመሸፈን «ይህን ያደረኩት ለራሴ ሳይኾን ቅዱስ ፓትርያርኩ ሲመጡ እንዲያርፉበት ነው፤» በማለት በመንፈሳዊነታቸው የምናውቃቸውን ቅዱስ ፓትርያርካችንንና በጾምና በጸሎት ሥጋዊ ፈቃዳቸውን ጎስመው የሚኖሩ ብፁዓን አባቶቻችንን ለሥጋዊ ምቾታቸው የሚጨነቁና በቅንጦት የሚኖሩ በማስመሰል የአባቶቻችን ገጽታ እያበላሹ ይገኛል፡፡   

በአጠቃላይ የካቴድራሉ የአስተዳደር ክፍል፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ችግር ዙሪያ ቅሬታዎችን በሚያሰሙበት ወቅት ጉዳዩን ከፖሊቲካ ጋር በማያያዝና መንግሥት ለምእመናኑ ጥያቄ የተሳሳተ ምልከታ እንዲኖረው በማድረግ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር ለማድረግ እየሞከሩ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ዋና አስተዳዳሪው በቤተ ክርስቲያኒቱ ክብረ በዓላት ላይ ለመሳተፍና በክብር እንግድነት ተጋብዘው የሚመጡ የአንዳንድ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ስም በመጥቀስ፣ «እነ እገሌ የተባሉት ባለሥልጣናት ወዳጆቼ ናቸው፤ ማንም ምንም ሊያደርገኝ አይችልም፤» በማለት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሚያነሡ አገልጋዮችንና ምእመናንን የማስፈራራት ሥራ ይሠራሉ፡፡

ይህ ብቻ ሳይኾን የአጥቢያው ምእመናን በተደጋጋሚ እየተፈጠሩ ያሉት የአስተዳደር ክፍተቶች እንዲታረሙ ለዋና አስተዳዳሪው ለማሳወቅ በምንሞክርበትና “ክፍተቶቹ የማይታረሙ ከኾነ ለቅዱስ ሲኖዶሱና ለቅዱስ ፓትርያርኩ እናሳውቃለን፤” በምንልበት ወቅት ዋና አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣ «ሲኖዶስ ማለት እኛ ነን፤ እነዚህ የቆብ ተስካራቸውን ያልጨረሱ ሽማግሌ ጳጳሳት እኔን አያዙኝም፡፡ ፓትርያርኩም ቢኾኑ ከኔ ፈቃድ አይወጡም፡፡ አሜሪካን ሀገር በነበሩበት ወቅት ብዙ ውለታ የዋሉላቸው የሚስቴ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን ለሕክምናና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አሜሪካን ሲሔዱ ወጪያቸውን ሸፍኜ፣ ማረፊያ አዘጋጅቼ፣ መኪና መድቤ የምንከባከባቸው እኔ ነኝ፤ የሚስማማቸውን ምግብ እያዘጋጀኹ ወጪያቸውን የምሸፍነው እኔ ነኝ፤» በማለት ምእመናን ቅሬታ ይዘን ወደ ወደ ቅዱስ ሲኖዶሱ እና ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ እንዳንሔድ ተስፋ ለማስቆረጥና ለብፁዓን አባቶቻችን የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረን ለማድረግ በተደጋጋሚ ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን እኛ ምእመናን የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን በይሉኝታና በውለታ የሚታሰሩ ናቸው ብለን ስለማናምንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ለቅዱስ ፓትርያርካችን የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት አቅቷት ቅዱስ ፓትርያርካችን ግለሰብ ላይ ጥገኛ ይኾናሉ ብለን ስለማናምን፣ በድፍረት ይህን አቤቱታ አቅርበናል፡፡                                                 

በመኾኑም ከላይ ለተዘረዘሩት መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮችና ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት መንሥኤው የመልካም አስተዳደር ዕጦት በመኾኑ የዚህ ችግር ምክንያት የኾኑት ደግሞ የካቴድራሉ የአስተዳደር አካላትና በሕገ ወጥ መንገድ የተመረጠው ሰበካ ጉባኤ በመኾኑ፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱና ሀገረ ስብከቱ ይህን ችግር በመገንዘብና የምእመኑን የመልካም አስተዳደር ጥያቄና ቅሬታ በመቀበል በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከተሉትን ውሳኔዎች እንዲያስተላልፍልን እንጠየቃለን፡፡

 • የካቴድራሉ ዋና አስተዳዳሪ የኾኑትን መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃንን፣ ዋና ጸሐፊው ዕፁብ የማነ ብርሃን፣ የሰበካ ጉባኤው ም/ሊቀ መንበር ካሳሁን ገ/ሕይወት እና የደብሩን ሒሳብ ሹም ዘርዐ ብሩክ ኣብርሃን ከሓላፊነታቸው እንዲያነሣልን፤
 • በሕገ ወጥ መንገድ ያለሕዝብ(ምእመን) ተሳትፎ በዝግ አዳራሽ የተመረጠውና በቀሲስ ካሳሁን ገብረ ሕይወት የሚመራው ሰበካ ጉባኤ ፈርሶ በቃለ ዐዋዲው መሠረት ዐዲስ ምእመኑንና የካቴድራሉን አገልጋዮች የሚወክል ሰበካ ጉባኤ እንዲያስመርጥልን፤
 • በቀጣይም በካቴድራሉ አስተዳደር ላይ የቀረቡትን አቤቱታዎች አጣርቶ ለሕግ የሚያቀርብ ኮሚቴ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከሀገረ ስብከት፣ ከወረዳ ቤተ ክህነትና ከአጥቢያው ምእመናን እንዲዋቀርልን
 • የውጪ ኦዲተር ተመድቦ የቤተ ክርስቲያኒቱ ገቢና ወጪ ኦዲት እንዲደረግልን በማለት ጥያቄያችንን በአክብሮት እናቀርባለን፡፡

በአጠቃላይ፣ የአጥቢያው ምእመናን የሃይማኖት ነጻነታችንንና በሕገ መንግሥቱ የተደነገገልንን በነጻነት አምልኮ የመፈጸም፣ ሃይማኖታችንን የመጠበቅና የማስጠበቅ እንዲሁም የማስፋፋት መብት በጥቂት ጥቅመኛ ግለሰቦች እየተነፈግን ስለኾነና አባቶቻችን የእርሻ መሬታቸውን ሰጥተው በድህነት አቅማችን ያለንን ኹሉ መሥዋዕት አድርገን እዚህ ባደረስናት ቤተ ክርስቲያናችን ተገቢውን አምልኮ መፈጸም ስላልቻልንና በመልካም አስተዳደር አለመስፈን ከፍተኛ በደል እየደረሰብን ስለኾነ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ሀገረ ስብከቱ እና ቅዱስ ሲኖዶሱ ለዚህ ሕዝባዊ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲሰጡን ስንል ከታላቅ አክብሮትና ትሕትና ጋራ እንጠይቃለን፡፡

የአባቶቻችን ጸሎትና ቡራኬ ይድረሰን!

ማስታወሻ፡-

በእያንዳንዱ ነጥቦች ላይ ያቀረብናቸው ማስረጃዎች እንደተጠበቁ ኾነው ጉዳዩ የሚመለከተው አካል የራሱን ምርመራና ክትትል በሚያደርግበት ወቅት ሌሎች ተጨባጭ ማስረጃዎችን ማግኘት እንደሚችል እያሳወቅን፣ የቀረበው አቤቱታ የሕዝበ ክርስቲያኑ ጥያቄ ለመኾኑ ከአራት ሺሕ/4,000/ በላይ ፊርማና በአጥቢያው ዙሪያ የሚገኙ ኅብረተሰቡን በደስታም ይኹን በሐዘንና በልማት ጭምር ተደራሽ የኾኑ እድሮች ጥያቄ ጭምር ስለኾነ የእነዚኹኑ እድሮች አቤቱታና ድጋፍ የሚያሳይ ደብዳቤ አያይዘን አቅርበናል፡፡

ግልባጭ

 • ለቋሚ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
 • ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ
 • ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት
 • ለካቴድራሉ ሰበካ ጉባኤ አስተዳደር ጽ/ቤት
 • ለካቴድራሉ ሰንበት ት/ቤት
 • ለአዲስ አበባ ወጣቶችና ጎልማሶች መንፈሳዊ ማኅበራት ኅብረት
 • ለአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽ/ቤት
 • ለፍትሕ ቢሮ የጸጥታ ጉዳዮች ጽ/ቤት
 • ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
 • ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
 • ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጽ/ቤት
 • ለፌዴራል የሃይማኖት ጉዳዮች ጽ/ቤት
 • ለሕዝብ ደኅንነት ጽ/ቤት
 • ለቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
 • ለቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ
 • በቦሌ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 7 አስተዳደር ጽ/ቤት
 • በቦሌ ክፍለ ከተማ ለሲኤምሲ ፖሊስ ማዘዣ ጣቢያ
 • በካቴድራሉ ለሚገኙ ዐሥራ አንድ የሰንበቴ ማኅበራት በአየድራሻቸው፤

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

የሰንበት ት/ቤቱ አቤቱታ፡-

ቀን፡ 11/03/2010

ለ፡- አዲስ አበባ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት

ጉዳዩ፡- ሰንበት ትምህርት ቤቱ በካቴድራሉ የአስተዳደር ጽ/ቤት እየደረሰበት ያለውን አስተዳደራዊ በደልና ጫና ስለማሳወቅ፤

የሰንበት ት/ቤቱ ሥራ አመራር፣ በካቴድራሉ ጽ/ቤት በኩል በሰንበት ት/ቤቱ ላይ እያደረሰ ያለውን የአስተዳደር በደል ለማስተካከል በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም፣ ጉዳዩ ከሰንበት ት/ቤቱ አቅም በላይ በመኾኑ መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በመኾኑም የአዲስ አበባ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ተገቢውን መፍትሔ ይሰጠን ዘንድ ሰንበት ትምህርት ቤቱ እየገጠመው ያለውን ችግር እንደሚከተለው ዘርዝረን አቅርበናል፡፡

 1. የካቴድራሉ ጽ/ቤት በቃለ ዐዋዲው ላይ ከተቀመጠለት ሥልጣንና መመሪያ እንዲሁም ከሰንበት ት/ቤቱ ዕውቅና ውጪ ያለአግባብ በሰንበት ት/ቤቱ አባላት ላይ የእግድ ቅጣት በማስተላለፍ አንዳንድ የሰንበት ት/ቤት አባላት ከአገልግሎት እንዲርቁ እየተደረገ ነው፡፡
 2. በሰንበት ት/ቤቱ የውስጥ አስተዳደር ላይ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት በመፈጸም፣ ሰንበት ት/ቤቱ በራሱ መንገድ አባላትን በሓላፊነት እንዳይመድብና በአገልግሎት እንዳያሳትፍ ጫና እየተደረገበት ነው፡፡
 3. ለሰንበት ት/ቤቱ መገልገያ ተብሎ እየተገነባ ያለው ሕንጻ የሰንበት ት/ቤቱ መኾኑን የሚገልጽ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ለመስጠት ካቴድራሉ ፈቃደኛ ካለመኾኑም ባሻገር የሕንጻው መጠንና ዲዛይን ምን እንደኾነ የሚገልጽ ፕላን ባለመኖሩ የሚገነባው ሕንጻ የሰንበት ት/ቤቱ ለመኾኑ ምንም ዋስትና የለም፡፡
 4. የሰንበት ት/ቤቱ የሰበካ ጉባኤ ተወካይ፣ ሓላፊነቱን አስረክቦ ከሀገር የወጣ ሲኾን በምትኩ ሰንበት ት/ቤቱ የሚፈልገውን ተወካይ እንዲተካ ካቴድራሉ ፈቃደኛ ባለመኾኑ የሰንበት ት/ቤቱን ወክሎ በሰበካ ጉባኤ አባልነት የሚያገለግል ተወካይ የለም፡፡
 5. የካቴድራሉ የአስተዳደር ጽ/ቤት በማን አለብኝነት የሰንበት ትምህርት ቤቱን አባላት የግል ማኅደርና ተያያዥ ሰነዶችን ከሰንበት ት/ቤቱ ቢሮ በመውሰድ በሰንበት ት/ቤቱ ላይ ከፍተኛ በደል እየፈጸመ ይገኛል፡፡
 6. የሰንበት ት/ቤቱ ጽ/ቤት የተለያዩ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ወደ ካቴድራሉ ጽ/ቤት በሚሔድበት ወቅት ተገቢውን ትብብር እያገኘ አይደለም፡፡
 7. የካቴድራሉ ጽ/ቤት ሰንበት ት/ቤቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ቀጥታ ከሰንበት ት/ቤቱ ጽ/ቤት ጋራ መነጋገር ሲገባው ያለአግባብ ሰንበት ት/ቤቱ ካልወካላቸውና ምንም ዐይነት የሓላፊነት ድርሻ ከሌላቸው የሰንበት ት/ቤት አባላት ጋራ ያልተገባ ግንኙነት በማድረግ የሰንበት ት/ቤቱን ገጽታ ከማበላሸትም በዘለለ ሰንበት ት/ቤቱ ከካቴድራሉ ጋራ ጤናማ ግንኙነት እንዳይኖረው እንቅፋት ኾኗል፡፡
 8. በሰንበት ት/ቤት ውስጥ፣ በተሐድሶ ኑፋቄ የሚጠረጠሩ አባላትን በተመለከተ ጥቆማ በሚሰጥበት ወቅት፣ ጉዳዩን በአግባቡ አጣርቶ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ በጉዳዩ ላይ ጥቆማ የሚሰጡ አባላትን ያለአግባብ በመቅጣት ሰንበት ት/ቤቱ ራሱን ከኑፋቄ እንዳይከላከልና ተገቢውን ክትትል እንዳያደርግ ካቴድራሉ ትልቅ እንቅፋት እየኾነ ይገኛል፡፡
 9. የደብሩ ዋና አስተዳዳሪ፣ ከአንድ የቤተ ክርስቲያን አባት በማይጠበቅና ፍጹም ኢ-ክርስቲያናዊ በኾነ መንገድ የሰንበት ት/ቤቱን አባላት በመሳደብና በመዝለፍ የሰንበት ት/ቤቱ ወጣቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
 10. ከሰንበት ት/ቤቱ ቢሮ ላይ ቆርቆሮ ተገንጥሎ የስርቆት ወንጀል የተፈጸመና ንብረት የጠፋ ሲኾን፣ ጉዳዩን ለካቴድራሉ ብናመለክትም መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም፡፡

በመኾኑም የአዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት፣ ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንዲሰጠን በማለት በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡

4 thoughts on “የሰዓሊተ ምሕረት ምእመናን አማሳኞችን በማባረር ካቴድራሉን ተቆጣጠሩ፤ቢሮ አሸጉ፤ለቀጣዩ እየመከሩ ነው

 1. Anonymous December 29, 2017 at 8:08 pm Reply

  Please keep going to clean up the dirty leadership of Aba Mattiyas. Our mother and beloved church is surrounded by the corrupters

 2. Amanuel December 29, 2017 at 8:31 pm Reply

  +++ስለ ዓለም ሠላም እና ስለ ህዝብም ፍቅር ምልጃ በሚቀርባትና የበደሉም በንስሃ ከቅጽሯ ወድቀው ምህረትን በሚለማመኑባትለቅቡጻን ተስፋ በሆነች በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ እንደነዚህ ዓይነት ሆድ አደር አረሞች መብቀላቸው ምንኛ ያማል?

  +++ስለ ሰዓሊተ ምሕረት አስተዳዳሪ ብዙ ተብሏልና ያንኑ መድገም አያሻም ግን ሰውየው ስልተኛ በመሆኑ አልፎ አልፎ ጉባዔያትን በማያዘጋጀት በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው የተመሰከረላቸውን እውነተኛ አገልጋዮችን እንኳ በመቅረብና በማቅረብ ለአገልግሎት እንዲያስተምሩና እንዲዘምሩም ከሀገር ውስጥም፣ ከውጭም ጭምር እየጋበዘ….. እርሱ በዚያ ቦታ በመምጣቱና በማልማቱ በርካታ ገቢ እያስገኘና ቤተክርስቲያንን እየጠቀመ እንዳለ… ጉዱን እና ለግሉ የሚያጋብሰውን እኩይ ግብሩን ደብቆ ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለራሱ የሚጠቀምበትን ሱቃ ሱቅ በማስጎብኘት ፅድቁ እንዲመዘገብለትና ለዚህ የጭንቅ ቀኑ ዝክር፣ ምሥክር፣ አማላጅም ይሆኑት ዘንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችንም ለማታለል ብዙ ደክሟል ። ስልቱ አልያዘለትም እንጂ!

  እንግዲህ አሁን አሁን በየቦታው ምዕመኑ እና አገልጋዩ ተናበው አርአያነት ያለው ስራ እየሰሩ ነውና።ተመስገን ነው።

  አሁን ግን የትግል ስልቱም ከፍ ብሎ ከስራ ማሳገድ ብቻ ሳይሆን የበሉትን ወደማስተፋት ሊያድግም ይገባል። ምክንያቱም ሰዎቹ በተዓምር ሺህ ዘመን እንኳ ቢኖሩ ሰርተው ሊያጠራቅሙ የማይችሉትን ገንዘብ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያጋብሳሉ። ቤተ ክርስቲያን ለትውልድ ልታስተላልፍ የምትችለው በርካታ ሀብት በእነዚህ የማይጠግቡና በማይጠረቁ ከርሳሞች እጅ ገብቷል።

  ይሄ የእነርሱ ጠንቅ ለሀገርም ለትውልድም የሚተርፍ ነው፤ የግብረገብነት ማዕከል በሆነች ቅድስት ሥፍራ እንደነዚህ ያሉ ውሽልሽሎች መራባታቸው አደጋ አለው። ስለዚህ መፍትሄው እነርሱን ከማገድ ባሻገር በየስርቻው የወሻሸቁትን በርካታ ንብረት ለባለንብረቷ ቤተክርስቲያን መመለስ ይገባል ።

  እነርሱ ባጋበሱት ሳይረኩ ቁንጣን ይዞ እያስጨነቃቸው ሌላም ሊጨምሩበት ሲንቆራጠጡ በየገጠራ ገጠሩ ግን በበጀት እጥረት ምክንያት ወንጌል ባለመድረሱ አውሬው እንክርዳዱን ለመዝራት እድል አግኝቷል ።

  ታድያ እኒህን ለጥፋት ምክንያት የሚሆኑ ከርሳሞችን ችላ ማለቱ ይበጃል ትላላችሁ?
  ስለዚህ እንደ ሰዓሊተ ምህረት፣ እንደ ደ /ጽ /ቅ/ዑራኤል፣ እንደ በዓታ ለማርያም እና ሌሎችም ትጉሃን እና ጥቡአን አገልጋዮች እና ምዕመናን ሌሎቻችንም የሚጠበቅብንን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንድንሰራ ፈጣሪ ይርዳን !የዘመኑ አንዱ ታላቅ አገልግሎትም ነው እና እንበርታ ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን!!!

  • Anonymous December 30, 2017 at 2:49 pm Reply

   I definitely agreed with You Amanuel.
   Our church schlars are suffering of lack of shelters and food and our monasteries are vanished because of this evil leadership of Aba Mattias. Lets wake up and stand together in order to protect our church and to change this awful leadership.

 3. […] ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።በወቅቱ የቀረበው ጥያቄ ዋና ጭብጥ ሐራ ዘተዋህዶበድረ ገፁ እንደዘገበው የሚከተሉትን ነጥቦች የያዘ ነበር። […]

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: