ቋሚ ሲኖዶስ የሰንበት ት/ቤቶችን የፀረ ሙስና እና የፀረ ኑፋቄ ንቅናቄ እንደሚደግፍና ርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ፤ ፓትርያርኩ ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች መመሪያ ሰጡ

Holy Synod Miyaziya 13 Meglecha

ቋሚ ሲኖዶስ (ፎቶ ፋይል)

  • ቋሚ ሲኖዶሱ የሀ/ስብከቱን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር በማነጋገር ትእዛዝ ሰጥቷል
  • መዋቅሩ ችግሮችን በየደረጃው የሚፈታበት ፍትሐዊነት እና ተአማኒነት መፈተሽ ይኖርበታል
  • ከቤተ ክህነቱ በላይ የሚያሾሙና የሚያሽሩ አማሳኝ አለቆች እንዳሉ መግባባት ላይ ተደርሷል
  • በፓትርያርኩ ዙሪያ ያሉትን ጨምሮ በፀረ ሙስና እየተመረመሩ በሕግ እንዲዳኙ ተጠይቋል

*          *          *

  • ዋ/ሥ/አስኪያጅ የማነ÷ ‹‹በፀረ ሙስና አብሬ እሠራለኹ፤ በፀረ ተሐድሶ አቋምም እንግባባለን››
  • የሙዳይ ምጽዋት ቆጠራው በካሽ ካውንተር መከናወኑ የመቶ ሺሕዎች ልዩነት እያመጣ ነው ብለዋል
  • የካህናት የምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮችን ያሟሉ ሰ/ጉባኤያት ጥቂት እንደኾኑ ተመልክቷል
  • በማስታወቂያ በተቋቋመው የሰሚ/መድኃኔዓለም ሰ/ት/ቤት የደብሩ ሠራተኞች አመራሮች ኾነዋል

*         *         *

  • ትላንት፣ ሰኔ ፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋር ለአራት ሰዓታት (ከጠዋቱ 4፡00 – 8፡00) በተደረገው ውይይት፣ የሀገረ ስብከቱን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮችን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተገኝተዋል፡፡
  • ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከሰንበት ት/ቤቶቹ አንድነት አመራር ጋር የዕለቱን ጨምሮ ለሦስተኛ ጊዜ መገናኘታቸውን ቢገልጹም፣ ጥያቄዎቻቸውን በተመለከተ የቀረበላቸው እና የደረሳቸው ነገር እንደሌለ፤ አንድነቱም ስለመኖሩ እንኳ እንደማያውቁ መናገራቸው አግራሞትን አጭሯል፡፡
  • በሰንበት ት/ቤቶቹ እንቅስቃሴ እንዳይናገሩ እየታፈኑ መሥራት እንዳልቻሉና እየተዘመተባቸው እንዳለ ጠቅሰው፣ ‹‹ከሀስብከቱ ጋር በመነጋገር ሳይኾን በራሳቸው እየተጓዙ ነው፤ የአገልግሎት መስጫውን ዩኒፎርም ለብሰው እየወጡ አድማ መቀስቀሻ አድርገውታል›› ሲሉም ከሠዋል፡፡
  • የሰንበት ት/ቤቶቹ በርክበ ካህናት የቅ/ሲኖዶስ መክፈቻ ጸሎት በብዙ መቶዎች የአባላት ፊርማ አስደግፈው ያቀረቡትን አካሔዱን የጠበቀ አቤቱታ እና ጥያቄ ‹‹ፊርማ እና ባለቤት የለውም›› ያሉት ልዩ ጸሐፊው አሠራራቸው መፈተሽ እንዳለበት በሚገልጽ ቀጥተኛ ምላሽ ተሸንቁጠዋል፡፡

*         *         *

  • ለማንም በመወገን በማንም በመቀስቀስ ሳይኾን የራሳቸውን ጥያቄ ይዘው እንደመጡ የተናገሩት አመራሮቹ÷ ‹‹ፍትሕ ቢኖር፣ ችግሮች ደረጃቸውን ጠብቀው ቢፈቱ እዚኽ አንመጣም፤›› ካሉ በኋላ በአካሔዳቸው ስሕተቶች ካሉ ለመታረምና ለመመከር ዝግጁ መኾናቸውን በመግለጽ ከአጥቢያ እስከ ልዩ ጽ/ቤቱ በረዘመው የአማሳኞች ሰንሰለት የተጠለፈው መዋቅር ተአማኒነት እና ፍትሐዊ አሠራር መፈተሽ እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡
  • የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች በማስከበር ልዕልናውን ለማስጠበቅ እንደቆሙ የገለጹት አመራሮቹ፣ ውሳኔዎቹ እንዳይተገበሩ የሚሹ አማሳኞች እና በውግዘት ከተለዩ በኋላ ወደ መዋቅሩ የሰረጉ የተሐድሶ መናፍቃን በየአጥቢያው በአስተዳደር ሓላፊነት እየተቀመጡ ትምህርተ ሃይማኖት እና ሥርዐተ እምነት እንዳይጠበቅ፣ መልካም አስተዳደር እና ፍትሕ እንዳይሰፍን ስለሚፈጥሩት ችግር በስፋት አብራርተዋል፡፡
  • በአራት እና አምስት ሺሕ ብር ደመወዝተኞች የ1ነጥብ8 ሚልዮን ብር መኪና ይነዳል፤ ቪላ ቤቶች እና ሕንፃዎች ይሠራሉ፤ ፈሰስ እንዲከፈል ወጪ ከተደረገ በኋላ አየር ባየር እየተበላ አጥቢያዎች ባለዕዳ ኾነዋል፤ በሙዳይ ምጽዋት ቆጠራ እና በጨረታ ሽያጭ የምዝበራ ድርሻቸው የቢሯቸው ጠረጴዛ ላይ የሚመጣላቸው የሀገረ ስብከት ሓላፊዎች አሉ፤ ሰንሰለቱ ሲበጠስ ጠጋኙ ያለው እዚኹ በዙሪያዎ ነው፤ ዛሬ ፉክክሩ ኤሮትራከር ለማስመጣት ነው፡፡
  • የሚሾሙ የሚሽሩ አለቆች አሉ፤ የማኅበረ ካህናት፣ የማኅበረ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች ተሟልተው የሚገኙባቸው ሰበካ ጉባኤያት ስንት ናቸው? ጥያቄ የሚያነሡና ብልሹ አሠራር እንዲታረም የሚጠይቁ አመራሮች ይታሰራሉ፤ ይባረራሉ፤ ተረጋግቶ መሥራት አልተቻለም፡፡
  • ‹‹የሰረቁ ጣቶች ባለመቆረጣቸው ሌሎች እንዲሰርቁ በር ከፍቶላቸዋል፤›› ያሉት አመራሮቹ በአንዳንድ አጥቢያዎች ምእመኑ ፍትሕ በማጣቱ አለቆችን እስከማባረር መድረሱን ጠቅሰዋል፤ ከገቢያቸው በላይ ሀብት ያካበቱ አለቆች ለሌላ ተግባር እያዋሉት ስለኾነ ያለተጠያቂነት በየአጥቢያው እያዘዋወሩ ለዘረፋ ማበረታታቱ ቆሞ በፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲመረመሩና በአገሪቱ ሕግ እንዲዳኙ አመልክተዋል‹‹በእኛ እጅ ማስረጃው አለ፤ እናንተ ወስኑ፤ በዚኽ እንርዳችኹ፡፡››

*         *         *

  • ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት አንዱ የምሥራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ እና የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መመሪያ የበላይ ሓላፊ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮች የሰጡት ማብራሪያ ችግሩ ሥር መስደዱን እንዳስገነዘባቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹እውነት ነው፤ ትክክል ነው፤ አንዳንድ አለቆች ከቤተ ክህነቱም በላይ ኾነዋል፤ ማን እንደሚያሾም ማን እንደሚያሽር ይታወቃል›› ያሉት ብፁዕነታቸው ማስረጃው ከቀረበ በሚመለከተው አካል ታይቶ እንደሚወሰንበት ጠቁመዋል – ‹‹በእኛ ደረጃ ብቻ የሚያልቅ አይመስለኝም፤ ወደሚቀጥለው አካልም የሚደርስ ነው፤ ቦዩን እኛ ጋር ብቻ ባንገድበው››
  • በዕለቱ ውይይት የአንድነት አመራሮቹን መግለጫ በጥሞና ሲያዳምጡ እና መልእክቱንም መውሰዳቸውን በአካላዊ ኹኔታዎች ሲያረጋግጡ የተስተዋሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በሙስና እና በመልካም አስተዳደር ላይ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የእርሳቸው መመሪያ ውጤት መኾኑን ያወሱት፣ ‹‹ከገባኹ ጀምሮ ሙስናን በሕጉና በአግባቡ እንድንዋጋው አግዙኝ ብዬ ያወጅኹት እኔው ነኝ›› በማለት ነበር፡፡
  • በሒደት ሲፈጠር የቆየው ችግር በአንድ ጊዜ ስለማይስተካከል ቀጣይ ጥረት እንደሚጠይቅ ያስገነዘቡት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ልጆቻችን እኛም እንደግፋችኋለን›› ሲሉ ማስረጃቸው ተጠናቅሮ ሲቀርብ ርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል – ‹‹በሙስናም በተሐድሶም ረገድ ያሉትን ማስረጃዎች አቅርቡ፤ ርምጃ እንወስዳለን፤ ሲኖዶስ ታዲያ ምን ሊሠራ ነው የተቀመጠው፤ ይህን ሊሠራ አይደለም ወይ፤ ይህ ሲኾን ግን ሕጉን፣ መዋቅሩንና አሠራሩን በጠበቀ መንገድ ይኹን፡፡››
  • ከዕለቱ ውይይት መጠናቀቅ በኋላ ፓትርያርኩ ኹለቱን የሀገረ ስብከት ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች ወደ ኋላ አስቀርተው ጥብቅ የተባለ ነው አጠቃላይ መመሪያ መስጠታቸው ተሰምቷል – ‹‹ልጆቹን ስሜታዊ እያደረጋችኹ ያላችኹት እናንተ ናችኹ፤ በሚያቀርቡት ነገር አንዳች ነገር የለባቸውም፤ ሁከት እየተነሣ ነው እየተባለ ከየአቅጣጫው እየተወጠርን ነው፤ የሚጠይቋችኹን አዳምጧቸው፤ ትኩረት መሰጠት ያለበትን ትኩረት ስጡ፤ አብራችኹ መሥራት አለባችኹ፡፡››
  • ቋሚ ሲኖዶሱ የሰንበት ት/ቤቶቹ አንድነት አመራሮችን ጠርቶ የማነጋገሩ እና ፓትርያርኩ ለሰንበት ት/ቤቶች የሰጡትን የፀረ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ተጋድሎ መመሪያ ባስረገጠ አኳኋን በውይይቱ የተደረሰበት መግባባት ብፁዓን አባቶችን ያስደሰተና ለንቅናቄው ድጋፍን ያጎረፈ ቢኾንም በአማሳኝ አለቆች ዘንድ ብስጭትም ድንጋጤም መፍጠሩ ተሰምቷል፡፡
  • መነጋገሩ መግባባቱ የሚፈለግ እና የሚበረታታ ቢኾንም አኹንም ጥያቄው ተግባር ተግባር ተግባር የሚል ነውና አመራሮቹ እንዳሉት የዕቅበተ እምነት፣ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሕ ንቅናቄው ሰላማዊ ይዘቱንና ግለቱን እንደጠበቀ ይቀጥላል….

5 thoughts on “ቋሚ ሲኖዶስ የሰንበት ት/ቤቶችን የፀረ ሙስና እና የፀረ ኑፋቄ ንቅናቄ እንደሚደግፍና ርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ፤ ፓትርያርኩ ለሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች መመሪያ ሰጡ

  1. mr alemu June 17, 2015 at 6:36 am Reply

    This is a pity.We should not have discussed such kind of issue currently if it was solved earlier.Now the issue should be how we could reach the ones which are not part of our socitey and we should devise ways to improve our people’s christianity But now this church is behind 50 years regarding adminstrative issues. Our fathers should be commited to such dreadful acts forever.They should establish a system to monitor financial revenues.

  2. Anonymous June 17, 2015 at 7:30 am Reply

    ሐራዎች /ወታደሮች/
    በእውነትም እንደ ስማችሁ ወታደሮች ናችሁ፡፡ ያውም ከጠብመንጃ በስተቀር ሌላ ትውክልት እንደሌለው ወታደር ናችሁ፡፡

    የትላንቱን ስብሰባ በተመለከተ ምነው ይህን ያህል ውሸት….. ቅንዓተ ቤተ ክርስቲያን የሚያቃጥላቸው መቅደስ የሌላቸው “ወጣቶቹ ቀሳውስት” በብጹዕ አቡነ ማርቆስና በብጹዕ አቡነ ሉቃስ የወረደባቸውን ግሳጼ ዘለላችሁት? ለአንባብያን “ቀሲስ” ኄኖክ ብሎ የነበረው “ከኋላችን የሚከተሉን 25 ሺኅ ወጣቶች አሉ እነሱን ይዘን እንወጣለን” ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ተሐድሶ ከየት ይምጣ ሐራዎች/ወታደሮች/

    በነገራችን ላይ በሊቢያ ስለ እምነታቸው ሲሉ ሰማዕትነት የተቀበሉ ወንድሞቻን ለዚያ ክብር የበቁት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ባላቸው ጥብዐት እንጂ እንደ እናንተ በትዕቢት አይደለም፤ ስለዚህ እነርሱን ለመሆን መንግሥትንና አባቶችን መተነኳኰስ ሳይሆን መማር፣ መንፈሳዊ ሕይወትን መለማድ ነው፡፡

    ለመሆኑ ቅዱስ ፓትርያርኩ ፊት እና ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፊት የምትናገሩበትን ቋንቋ የማትመርጡ አጉራ ዘለሎች፤ አሁን ላይ በበርካታ የአ/አ ሰንበት ት/ቤቶች ስር የሚደረገውን የትምህርት እንቅስቃሴ ወጨፎው ያልነካችሁ ባልጩቶች ናችሁ፡፡ በአጠቃላይ አንድነቱ በብዙ የሰከኑ ወንድሞች የተመላውን የአዲስ አበባን ሰንበት ት/ቤቶች እንደማይወክሉ ነው፡፡

  3. Anonymous June 17, 2015 at 7:37 am Reply

    ከዕለቱ ውይይት መጠናቀቅ በኋላ ፓትርያርኩ ኹለቱን የሀገረ ስብከት ዋና እና ምክትል ሥራ አስኪያጆች ወደ ኋላ አስቀርተው ጥብቅ የተባለ ነው አጠቃላይ መመሪያ መስጠታቸው ተሰምቷል – ‹‹ልጆቹን ስሜታዊ እያደረጋችኹ ያላችኹት እናንተ ናችኹ፤ በሚያቀርቡት ነገር አንዳች ነገር የለባቸውም፤ ሁከት እየተነሣ ነው እየተባለ ከየአቅጣጫው እየተወጠርን ነው፤ የሚጠይቋችኹን አዳምጧቸው፤ ትኩረት መሰጠት ያለበትን ትኩረት ስጡ፤ አብራችኹ መሥራት አለባችኹ፡፡›› አላችሁን፡፡

    2ቱን ብቻ ወደ ኋላ አስቀርተው ከሆነ የተናገሯቸው እናንተ እንዴት የተባባሉትን አወቃችሁ?ወይስ ከየማነ ወይም ከእመረ አንዳቸው የእናንተ ሽርካ ናቸው?መቼም ድርሰት አትጽፉም!!

    ለማንኛውም ለወሬ ያህል ሀ/ስብከቱ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን በተጠሩ ሰዎች አማካኝነት ለአለቃ፣ፀሐፊና ሂሳብ ሹም ስልጠና(ማስጠንቀቂያም ሊባል ይችላል) ለመስጠት ማቀዱን ጨምራችሁ ዘግቡት፡፡

    የዛሬው አቀራረባችሁ ከቀደሙ ሚሊቴሪያዊ አቀራረቦች ለዘብ ማለቱን ወድጀዋለሁ፡፡ ስድብና ፍረጃውን በጥቂት በጥቂት እያላችሁ ወደ ኦርቶዶክሳዊው ሥነ-ምግባር በገቢር እንድትመለሱ እንጸልያለን፡፡

  4. Shitahun Minwyelet June 17, 2015 at 2:03 pm Reply

    Thank you very much for your valuable information. Let GOD Be with you & keep up your service.
    Shitahun Minwyelet

Leave a comment