ሰበር ዜና – የሀገር አቀፍ አንድነት ጠቅላላ ጉባኤው ለአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ፀረ ሙስና እና ፀረ ኑፋቄ ንቅናቄ የጋለ ድጋፉን ሰጠ

eotc ssd 4th gen assembly

 • የንቅናቄው መነሻ የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ እና የፓትርያርኩ አባታዊ መመሪያ ነው
 • ከ25 በላይ አማሳኝ የአድባራት አለቆች እና ጸሐፊዎች ላይ በቂ ማስረጃዎች ተሰብስበዋል
 • የተሐድሶ አራማጅ ሰባክያንን የሚጋብዙ አለቆችና የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ተለይተዋል
 • የደብረ ናዝሬት ቅ/ዮሴፍ፣ የመካነ ሰማዕት ቅ/ቂርቆስ እና ጃቲ ኪዳነ ምሕረት ተጠቅሰዋል
 • የሀ/ስብከቱ ሥ/አስኪያጅ የሰንበት ት/ቤቶቹን አመራሮች ‹‹እኔ ራሴ አሳስራችኋለኹ›› አሏቸው
 • ‹‹እንቅስቃሴው ይቀጥላል፤ የመላው የአ/አ ሰንበት ት/ቤቶች እና የአንድነቱ የጸና አቋም ነው››

eotc ssd 4th gen assembly participants00
ሦስተኛ ቀኑን የያዘው ፬ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ት/ቤቶች ሀገር አቀፍ አንድነት ዓመታዊ ጉባኤ÷ አማሳኝ የአስተዳደር ሓላፊዎችን እና ሠራተኞችን በማረም ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ከቤተ ክርስቲያን ለማስወገድ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንን በማጋለጥ ከቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት እና ከመዋቅሯ ለማጥራት በአጠቃላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ተከብሮ ውሳኔዎቹ ተግባራዊ እንዲኾኑ ለመታገል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ለቀረበው የተግባራዊ ንቅናቄ ጥሪ የጋለ ድጋፍ ሰጠ፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተግባራዊ ንቅናቄ ጥሪ ለጠቅላላ ጉባኤው የተላለፈው፣ የአህጉረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጉባኤያትን የሥራ አፈጻጸም እና የበጀት አጠቃቀም ሪፖርቶችን ለማዳመጥ በተያዘው መርሐ ግብር በቀረበው የአንድነቱ ሪፖርት ነው፡፡

ከሚታወቀው ገቢያቸው በላይ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት መዝብረው መልሰው ሰላሟን በሚነሱ እና የተቋማዊ ለውጥ ጥረቷን በሚያደናቅፉ አማሳኞች እና የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አቀንቃኞች ላይ የተጀመረው ንቅናቄ በመላው የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች የጸና አቋም የተያዘበት መኾኑን በሪፖርቱ ያስታወቀው አንድነቱ፣ አህጉረ ስብከትም ንቅናቄውን በሙሉ ቁርጠኝነት በመደገፍ ለተግባራዊ ለውጥ በጋራ ለመታገል እንዲነሣሱ ጥሪውን ባቀረበበት ቅጽበት ኹሉም የጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ከመቀመጫቸው አፈፍ ብለው በመነሣት ለደቂቃዎች በዘለቀ ጭብጨባ ለንቅናቄው ያላቸውን የጋለ ድጋፍ ገልጸዋል፡፡

ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ከቤተ ክርስቲያን ማስወገድ፣ መናፍቃንን ከቤተ ክርስቲያን ማስወጣት፣ የቤተ ክርስቲያን የበላይ አመራር የኾነውን የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና በማስከበር ውሳኔዎቹን ማስፈጸም የአዲስ አበባ ብቻ ሳይኾን መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያን ሊጋደሉለት የሚገባ የጋራ ጉዳይ እንደኾነ በሪፖርቱ ተገልጧል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች የፀረ ሙስና እና የፀረ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ንቅናቄ በግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት ወቅት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተገኙበት በይፋ እንደተጀመረ ሪፖርቱ ለጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች አብሥሯል፡፡

አማሳኝ የአስተዳደር ሓላፊዎችን እና ሠራተኞችን የተመለከተው የንቅናቄው መሠረታዊ መነሻ ጥር ፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ‹‹ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ከቤተ ክርስቲያን ለማስወገድ በሚደረገው ከፍተኛ ጥረት ከጎኔ እንድትቆሙ›› በማለት ለጥምቀት በዓል ቅድመ ዝግጅት ቡራኬ ለመቀበል በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብሰባ አዳራሽ ለተገኙ መላው የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አባላት የሰጡት አባታዊ መመሪያ መኾኑን ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው በሰኔ ፳፻፮ ዓ.ም. ፫ኛው ሀገር አቀፍ አንድነት ዓመታዊ ስብሰባው፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከመናፍቃን ቅሰጣ ለመጠበቅ እና ማንነታቸውን ለማጋለጥ የሚያስችል ጥናት በየአህጉረ ስብከቱ ለማድረግ ቃል በመግባት የጋራ አቋም መያዙን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የሚያበቁ ስልቶችን በመንደፍ ይፋዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

እስከ አኹን በተደረገው እንቅስቃሴ፣ ከገቢያቸው በላይ ሕገ ወጥ ሀብት ባካበቱ ከ25 በላይ የገዳማት እና የአድባራት አስተዳዳሪዎች እና ጸሐፊዎች ላይ በቂ ማስረጃ መሰብሰቡ ተገልጧል፡፡ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶን እንደሚያራምዱ በግልጽ የሚታወቁ ‹ሰባክያንን እና ዘማርያንን› በየዐውደ ምሕረቱ በመጋበዝ ኑፋቄአቸውን እንዲያስፋፉ የሚተባበሩ አስተዳዳሪዎች እና የስብከተ ወንጌል ሓላፊዎች ድርጊታቸውን በሚቃወሟቸው ሰንበት ት/ቤቶች ላይ እንግልት እየፈጸሙ እንደሚገኙ ሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡

ለዚኽም የደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ተጠቃሽ ሲኾን የክፍለ ከተማው እና የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተላለፉ የመፍትሔ ሐሳቦች ተግባራዊነት ከማጣታቸው የተነሣ ለውጥ ባለማምጣታቸው ሰንበት ት/ቤቱ በመዳከም ላይ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡ በተመሳሳይ አኳኋን የደብረ ፍሥሓ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ እና የጃቲ መካነ ሕይወት አድባራት ሰንበት ት/ቤቶች ዕጣ የተለየ እንደማይኾን ጠቋሚ ምልክቶች ይታያሉ ብሏል፡፡

የሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ዓምባገነናዊ አስተዳደርን ጨምሮ በአንዳንድ አድባራት፣ የሰንበት ት/ቤት አባላትን ‹‹የሀብታም እና የድኻ ምእመናን›› እያሉ መከፋፈላቸው ፈታኝ ችግር መኾኑ ተጠቅሷል፡፡ በሰሚት መካነ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ ለሀብታም ምእመናን ልጆች ልዩ አዳራሽ ለሌላው ደግሞ የማይመች ቦታ በመስጠት አድልዎ መደረጉ አሳዛኝ ነው ብሏል፡፡ ጉዳዩ ለሀገረ ስብከቱ ቀርቦ አሠራሩ እንዲቆምና የተለያየው ጉባኤ በአንድ ተጠቃሎ አገልግሎቱ እንዲፈጸም መመሪያ ቢሰጥም ግብታዊው እና ማንአለብኝ ባዩ የደብሩ አስተዳደር፣ የሰንበት ት/ቤቱን የሥራ አመራር በማገድ ጽ/ቤቱን እና አዳራሹን አሽጓል፤ የቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ እና የተከበረ ማኅተም በመጠቀም አባላቱንም በአሸባሪነት በመሰየም እና በመፈረጅ ለእስር እና ለእንግልት ዳርጓል፡፡

የታገዱት የሰንበት ት/ቤቱ አመራሮች ከትላንት በስቲያ ዓርብ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጁን በግንባር ቢያነጋግሩም፣ ‹‹እንድትታገዱ እና እንዲታሸግ ያዘዝኹት እኔ ነኝ፤ በአባልነት መመዝገብ ያለባቸው ዕድሜአቸው እስከ 30 የኾኑት ብቻ ናቸው፤ ከእነዚኽ ውጭ ሌሎቹ መባረር አለባቸው፤ ከዚኽ በኋላ በዚኽ ውሳኔ ላይ አንድ እንቅስቃሴ ብታደርጉ እኔ ራሴ ነኝ የማሳስራችኹ›› የሚል እብሪት የተሞላበት ምላሽ አዝነው መመለሳቸው ታውቋል፤ ይኸውም በአንድነቱ ሪፖርት ተካትቶ ጠቅላላ ጉባኤው እንዲሰማው ተደርጓል፡፡

በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው፣ በሀገረ ስብከቱ በሰባቱ ክፍላተ ከተማ ጽ/ቤቶች የተመደቡ አብዛኞቹ የክፍል ሓላፊዎች የድርሻቸውን አይወጡም፤ የሰንበት ት/ቤቶችን ችግር ለመፍታት የአቅም ውስንነት አለባቸው፤ ከአንድነቱ ጋራ ለመሥራትም ፍላጎት የላቸውም፡፡ በመኾኑም ሰንበት ት/ቤቶች በሚደርስባቸው ችግር አፋጣኝ ምላሽ እና መፍትሔ አያገኙም፡፡

ይህም ኾኖ በአምስት ዓመቱ ሀገር አቀፋዊ ስትራተጅያዊ ዕቅድ መሠረት፣ በሀገረ ስብከቱ በኹሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ተቋቁመዋል፤ የሰንበት ት/ቤት አባላትን ቁጥር ወደ 11‚200 ለማሳደግ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር የተያዘው አፈጻጸም በመልካም ኹኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡ የሀገረ ስብከቱ የሰባቱ ክፍላተ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤያት የ156 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶችን የሚወክሉ ሲኾኑ 32‚000 መደበኛ አባላት፣ ከ90‚000 በላይ ሕፃናት እና አዳጊዎች እንዲኹም ከ50‚000 በላይ ተሳታፊ ጎልማሶች በአጠቃላይ ከ200‚000 በላይ አባላት ታቅፈውባቸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እና የማደራጃ መምሪያው የበላይ ሓላፊ በተገኙበት ከየሰንበት ት/ቤቱ ለተወከሉ ቁጥራቸው ከ750 በላይ ለሚኾኑ አመራር አባላት በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሰፊ ውይይት መደረጉ በሪፖርቱ ተነግሯል፡፡

ለሰንበት ት/ቤቶች በፍጥነት አለማደግ ኹለንተናዊ መንሥኤው በቤተ ክርስቲያን የተንሰራፋው ብልሹ አስተዳደር እንደኾነ በዋነኛ ችግርነት ተነሥቷል፡፡ ዲያቆን በለጠ ብርሃኑ ‹‹የሰው ኃይል አያያዝ በሰንበት ት/ቤት›› በሚል ርእስ ለጠቅላላ ጉባኤው ባቀረቡት ጽሑፍ ÷ ለሰው ልጅ አእምሯዊ እና መንፈሳዊ ዕድገት ሓላፊነት ያለባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋን ለመወጣት በሰንበት ት/ቤቶች የሰው ኃይል ማፍራት እንዳለባት ተናግረዋል፡፡ ይህም ወጣቶችን በመያዝ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባው የመከሩት ጽሑፍ አቅራቢው፣ በዘመናችን ወጣቶችን በክርስትና ለማጽናት የዓለምን እና የሀገር ቤትን ነባራዊ ኹኔታ ማወቅ እና መለየት፤ ዘመኑን የዋጀ የሰው ኃይል አያያዝ ስልቶችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ዲያቆን በለጠ ነባራዊ ኹኔታውን ለማሳየት የዘረዘሯቸው ችግሮች፡-

 • ከሃይማኖተኝነት ይልቅ ዓለማዊነት እያየለ መምጣቱ፣
 • የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጽዕኖ፣
 • የግዴለሽነት መስፋፋት፣
 • አርኣያነት ማጣት፣
 • በቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ችግሮች የተነሣ ተስፋ መቁረጥ፣
 • የወጣቱን ሃይማኖተኝነት ለማስጣል የሚተጉ አካላት(መናፍቅነት፣ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እና ሰዶማዊነት) እየተበራከቱ መሔድ ናቸው፡፡

ከእኒኽ የነባራዊ ኹኔታው መግለጫዎች መካከል፣ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እና የቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ ችግሮች በኾኑት የመልካም አስተዳደር ዕጦት የተነሣ በወጣቶች ላይ በሚታየው ተስፋ መቁረጥ ጉዳይ ጉባኤው አጽንዖት ሰጥቶ በስፋት ተወያይቶበታል፡፡

የሰንበት ት/ቤቶችን የኹለንተናዊ ዕድገት ማነቆዎች በመለየት አቅማችንን እያወደሙ ያሉ አሠራሮችን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ መምህር ምሐባው ዓለሙ ናቸው፡፡ መምህሩ፣ ‹‹ኢኮኖሚ እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች›› በሚል ርእስ ለጠቅላላ ጉባኤው ባቀረቡት ጽሑፍ፣ አጥፊዎች እንዲታረሙ እና ፋይናንሱ በማእከል እንዲመራ በማድረግ የፋይናንስ አስተዳደሩን ማስተካከል ይገባል፡፡

በማደራጃ መምሪያው ይኹን በአንድነቱ ሪፖርት ከዐበይት ችግሮች በቀዳሚነት ከተጠቀሱት መካከል የሰንበት ት/ቤቶች የበጀት እጥረት እና የአባሎቻቸው የገቢ አነስተኛነት ለአገልግሎቱ የፈጠረው ዕንቅፋት ነው፡፡ እንደ መምህር ምሐባው የኢኮኖሚ አቅም ማነስ ፈተናዎች፡- እምነትን ይፈትናል፤ እንደ ትውልድ መቀጠልን ይገዳደራል፤ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ እንዳንፈጽም ያደርጋል፤ ለስደት እና ለመከራ ይዳርጋል፤ ዕውቀትን እና ምርምርን ያጠፋል፤ ራስን ለመከላከል አለመቻልን ያስከትላል፤ በራስ መተማመንን ያጠፋል፤ እንደ አንዲት የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንዳናስብ ያደርጋል፡፡

በመኾኑም የኢኮኖሚ አቅማችንን በማጎልበት፡-

 • የመደመጥ
 • የመወሰን
 • የመተግበር

አቅሞቻቻችንን ለማጎልበት÷ አርቆ በማሰብ፣ ውጤታማ ተግባራትን በመምረጥ፣ ዐቅዶ በመሥራት፣ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም የመሪነት ሚናን በአግባቡ መወጣት ያስፈልጋል፤ መሥራት እና ለውጥ ማምጣት የምንችል መኾናችንን ማመን ይኖርብናል፤ ከመሳዮቻችን መማር፣ ኹላችንንም የኢኮኖሚው ተሳታፊ የሚያደርግ የፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር፣ ፍትሕ እንዲነግሥ መጣር፣ አንድነትን ማጠናከር እና ትስስርን ማጎልበት ይገባናል፡፡
His Grace Abune Kelemntos ssd gen assembly

የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በጉባኤው መክፈቻ ባስተላለፉት መልእክት÷ ሀገር አቀፉን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ማቋቋም ያስፈለገው የተናጠል ጉዞው ውጤታማ ባለመኾኑና በአንጻሩ አንድነቱ ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ጥቅም በቅዱስ ሲኖዶስ በማረጋገጥ ነው፡፡

የሰንበት ት/ቤትን ጥቅም ባልተረዱ ወገኖች ዘንድ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች መባል እንደ ነቀፋ ይቆጠር የነበረውን ስም ማስቀረት የሚቻለው በሥራ መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕነታቸው፣ የወጣቱን አእምሮ ለሃይማኖታዊ ልማት በማነሣሣት ረገድ የአንድነቱ መቋቋም ጉልሕ ሚና መጫወቱን አረጋግጠዋል፤ አባላቱም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጥቅም በማስቀደም ከቡድናዊ እና ጐሣዊ አስተሳሰብ በመራቅ የቤተ ክርስቲያንን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲተጉ አሳስበዋል፡፡

በአገራችን ተቆጥረው በሚታወቁት 37,332 አብያተ ክርስቲያን ከ20,000,000 በላይ ወጣቶች እንዳሉ ይገመታል፡፡ በሥርዐት ተመዝግበው አገልግሎት የሚሰጥባቸው አብያተ ክርስቲያን 8,610 ያኽሉ ሲኾኑ የአባሎቻቸው ብዛትም 2,701,253 ብቻ መኾኑን የሚጠቅሰው የማደራጃ መምሪያው ሪፖርት ገና ብዙ መሥራት እንደሚገባ አመላካች ነው ብሏል፡፡

Advertisements

9 thoughts on “ሰበር ዜና – የሀገር አቀፍ አንድነት ጠቅላላ ጉባኤው ለአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ፀረ ሙስና እና ፀረ ኑፋቄ ንቅናቄ የጋለ ድጋፉን ሰጠ

 1. dakon nati May 31, 2015 at 2:44 pm Reply

  tadsochi yewtu yeiyeu

 2. dakon nati May 31, 2015 at 2:45 pm Reply

  egzabher lbonan yadlachiew deglmaryam hasbachewn temlse

 3. EWNET GENZEBU May 31, 2015 at 8:09 pm Reply

  tewahedon krstos fekdo slemeseratat,
  fetena teleyitoat aiawkm,Esu befekedelachuw lijochuwa
  semayitne noralech Ahunm tabbalech begltswagan
  kefau nguse tigstna blhatun yadlachu;

 4. Anonymous June 1, 2015 at 5:22 am Reply

  yesenbet temariwechew lebelte tsega egiziabher yadilachu. Betekirsitiyan fetena teleyituat ayawikim. yewistim yewichim fetena benesabatim meseretua Kirstos newina yegehanem dejoch ayichiluatim. Enaten yekurit lijoch argo yasinesalatal. Tebarekuuuuu. Amen.

 5. Hilina June 2, 2015 at 11:06 am Reply

  Ewnet hoY Yemtgelechiw mechi yehone

 6. Anonymous August 24, 2015 at 7:41 am Reply

  እግዚአብሔር ይርዳችሁ ደስ ብሎናል

 7. እግዚአብሄር ከነንተ ጋር ይሁን አነመሰግነለን

 8. Anonymous September 4, 2016 at 1:30 pm Reply

  የአባቶቻችን አምላክ የተኩላዎችን ቀንድ ይስበር

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: