ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያኒቷን አስተዳደር የማሻሻል አቋሜ ‹‹አልተበረዘም፤ አልተከለሰም›› አሉ

  • ‹‹የፀረ ሙስና አቋማቸው ራሳቸውን ከማስተዋወቅ ያለፈ ውጤት አላመጣም›› /ተቺዎች/

(ሰንደቅ፤ የካቲት ፳፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)

Sendek front pageየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፍትሕ፣ ርትዕና እኩልነት የሞላባት፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት ለማድረግ በዕለተ ሢመተ ፕትርክናቸው የተናገሩት ቃል ኹሉ እንደጸና መኾኑንና ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከምእመናን ጋር በመኾን እንደሚያጠናክሩት ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ ስድስተኛ ፓትርያርክ ኾነው የተሾሙበት አንደኛ ዓመት ከትላንት በስቲያ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተከበረበት ወቅት ‹‹ሙስና ካልጠፋ ሕይወት አይኖርም›› ሲሉ የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚሰበሰበው ገንዘብ ከድኾች የተገኘ ሀብት ስለኾነ የድኾችን ገንዘብ በከንቱ የሚያማስነውን እግዚአብሔር እንደሚፈርድበት፣ በዚኽም እግዚአብሔርን ማታለልና በእግዚአብሔር ላይ መቀለድ እንደማይቻል አስጠንቅቀዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእውነትና የሐቅ መገኛ ትኾን ዘንድ መንፈሳዊ ባሕርይዋ የሚያስገድዳትና አገልግሎትዋም በእግዚአብሔር ስም የሚሠራ በመኾኑ አሠራርዋ ከአድሏዊነትና ወገንተኝነት መጽዳት፣ ታማኝነትንና ፍትሐዊነትን መጎናጸፍ ይኖርበታል ብለዋል ፓትርያርኩ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ሲባል ሕንፃ ቤተ መቅደሱ ብቻ ሳይኾን የካህናትና የምእመናን አንድነትም መኾኑን ያስረዱት አቡነ ማትያስ፣ በይበልጥም ቤተ ክርስቲያኒቷን በሓላፊነት ለመጠበቅ ጥሪው ያላቸው ካህናት በአበው ሥርዐት በተደነገገው መሠረት÷ ቀኖናዋንና ትውፊቷን መጠበቅና ማስጠበቅ፣ ምእመኖቿን በስብከተ ወንጌል ማርካትና በግብረ ገብነት እንዲታነፁ ማድረግ የዉሉደ ክህነት ሓላፊነት ነው፤ ከዚኽ አንጻር ዉሉደ ክህነት የቤተ ክርስቲያኒቱ ተልእኮ ፈሩን ሳይስት እንዲፈጸም የማድረግ መንፈሳዊ ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በዓለ ሢመቱ የአንድ መሪ ግለሰብ በዓል እንዳልኾነ ያስገነዘቡት ፓትርያርኩ፣ በዓሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ኹለንተናዊ ልዕልናና ክብር በፊት እንዴት እንደነበር፣ አኹን ምን ላይ እንዳለና በቀጣይ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በስኬት ለማከናወን ምን መደረግ እንዳለበት እየታሰበ እንደሚከበር አብራርተዋል፡፡ ከሥርዐተ ሢመታቸው ወዲህ ባለፈው የአንድ ዓመቱ ጉዞ ውስጥ ተከናውነዋል ያሏቸውን ተግባራት ፓትርያርኩ በንግግራቸው ዘርዝረዋል፡፡

‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ እየተሻሻለ ነው፤ በመልካም አስተዳደር፣ በመሪ ዕቅድ እንድትመራ ጥረት እየተደረገ ነው፤›› በማለት ክንውኑን የጠቀሱት ፓትርያርኩ፣ ‹‹ችግሩ ለዘመናት የተከማቸና በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማምጣት ስለሚያዳግት በትዕግሥት መጠባበቁ መልካም ይኾናል፤›› ብለዋል፡፡ በበዓለ ሢመታቸው ቀን የአስተዳደር መዋቅር ማሻሻያን አስመልክቶ ተናግረዋቸው የነበሩ ቃላት ኹሉ ‹‹እንደጸኑ ናቸው፤ አልተበረዙም፤ አልተከለሱም፤ እንዲያውም ከሲኖዶስ አባላት፣ ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከምእመናን ጋር በመኾን አጠናክራቸዋለኹ›› ያሉት አቡነ ማትያስ፣ ለመልካም አስተዳደር መረጋገጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለድርሻ አካላት ኹሉ መነሣት እንደሚኖርባቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፤ ‹‹ይህ ግዴታ ነው›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መዋቅር እንዲሁም አደረጃጀትና አሠራር ከመሠረታዊ ክህነታዊና የስብከተ ወንጌል ተልእኮዋ ጋራ እንዲጣጣም፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር እንዲወገድ የተደረጉ የሙከራ ትግበራዎችና በመደረግ ላይ ያሉ ጥረቶች፣ ‹‹ይኹንታ ካገኙበት የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ በተፃራሪ ዕንቅፋት ገጥሟቸዋል፤›› የሚሉ የቅርብ ታዛቢዎች በበኩላቸው÷ ፓትርያርኩ ሙስናን በየአጋጣሚው በመቃወምና ስለመልካም አስተዳደር ደጋግሞ በመናገር ራሳቸውን አስተዋውቀው እንደኾነ እንጂ ያመጡት ተስፋ ሰጭ ውጤት የለም፤ እንዲያውም በደሉና ጥፋቱ መልኩን ለውጡ እየረቀቀና እየተባባሰ መምጣቱን በምሬት ይናገራሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ ሥር ሰዷል ያሉት ጎሰኝነት ከቀድሞም ጀምሮ ስማቸው ሲጠቀስ በቆዩና በተለይ በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ዙሪያ በተሰባሰቡ ግለሰቦች ተጽዕኖ እየገዘፈ መምጣቱን ታዛቢዎቹ ከማስረዳታቸውም በላይ፣ ፓትርያርኩ ‹‹እንደ ጸና ነው›› የሚሉት አቋማቸው በላቀ አመራርና የውሳኔ ሰጭነት አቅም ተፈትኖና በተግባር ተገልጦ ማየት እንደሚሹ ለሰንደቅ ገልጸዋል፡፡

3 thoughts on “ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያኒቷን አስተዳደር የማሻሻል አቋሜ ‹‹አልተበረዘም፤ አልተከለሰም›› አሉ

  1. በአማን ነጸረ March 6, 2014 at 9:45 am Reply

    1. እረ እናንተ የስመ – ነጻ ጋዜጦች ምን ይሻላችሁዋል?? አሁን አምስት ኪሎ ሩቅ ነው?? እስኪ ያለውን ለውጥም ሆነ መባባስ እንደ ደራሲ ቁጭ ብሎ በስማበለው ከመተረክ ገብታችሁ ዘግቡ፡፡ ሰራተኛውን ጠይቁ፡፡ ምንድነው ይሄ አሉሽ… አሉሽ!! ጠቅላይ ቤተክህነትም ሆነ መንበረፓትርያርክ ከቅድስት ማርያም ጀርባ ነው ሂዱና ከሁለቱም ወገን አጣርታችሁ ጻፉ፡፡ የአንድ ወገን አስተያየት አታንጸባርቁ፡፡
    2. ያ ሁሉ ወከባ የነበረበት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በጸጥታ መስራት የሚገባውን እየሰራ ነው፡፡ ለዚህ ከፓትርያርኩ ጀምሮ ምስጋናውን የሚወስዱ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ለጊዜው ከንቱ ውዳሴ እንዳይሆንባቸው ስማቸውን አንጠራም፡፡ ምስጋናውን ግን አናስቀርባቸውም – አመስግነናል፡፡ ብዙ ግፉአንን በሽግግር ስም ከተቁዋቁዋሙ ይሉኝታ የለሽ ስ/አስኪያጅ ቀሳጥያን ካህኑን ስላዳናችሁት፡፡ አሁንም በቦታው አቆይቶዋችሁ ብዙ እንድትሰሩ እጸልያለሁ፡፡ እንደተመኘነው ሆናችሁ በፍቅረንዋይ ሳትሰነካከሉ ባጭር ጊዜ ውስጥ ላሳለፋችሁዋቸው ፍትሀዊ ውሳኔዎች ምስጋና ሲያንሳችሁ ነው፡፡ እሰይ ውሉደ ክህነት!!አውቃለሁ አንዳንዶች እነሱ ቡራኬ ያልሰጡት ካልሆነ በቀር ሙትም ቢያስነሳ ለሰው መልካም ምግባር እውቅና መስጠት አይፈልጉም፡፡ግዴለም ስራችሁን አምላከ – ተዋህዶ እያየው ነው፡፡ዕሴተ ጻማችሁ አይቀርም፡፡
    3. የጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ ጸጥታው ደስ ይላል፡፡ ብዙ ወከባ የለም፡፡ በፓትርያርኩ ዙሪያ በማንዣበብ እሳቸውን እያሞጋገሱ ያለፉትን እየነቀፉ በሲመቱ ማግስት አዳዲስ አፋሽ-አጎንባሽ መሆን የፈለጉ ሰዎች ቦታ አላገኙም፡፡ ስለዚህ ቢጮሁ አይገርምም፡፡ ለቅዱስ ፓትርያርኩ አማካሪ የሚሆን ሰው እነሱ ካልመረጡ በቀር ሰዎቹ ስለማይረኩ ለጊዜው እናልፋቸዋለን፡፡ በቃ፡፡ በራሱ አእምሮ የሚመራ ሰው ሳይሆን ለእነሱ መሳሪያ የሚሆን ሰው ካላገኙ በቀር እንቅልፍ ስለማይወስዳቸው ከነቅዠታቸው መተው ነው፡፡ የነቁ ቀን ይነቃሉ፡፡እስከዚያው ከሰሙን ለፓትርያርኩ አማካሪ የመምረጥ መብት እንደሌላቸውና ፓትርያርኩ ከልጅነት እስከ ሽበት ባደጉባት ቤ/ክ ማን ለምን እንደሚያማክራቸው ጠንቅቀው ለማወቅ የሚያስችል መንፈሳዊ ብቃት እንዳላቸው እንነግራቸዋልን፡፡
    4. አሁን ግን ድባቡን ሁሉ ወደነዋል፡፡ የለውጥ አየር እየነፈሰ ስለመሆኑ አንጠራጠርም፡፡ በላይኛው ቤተክህነት ያለው ተነሳሽነትና ቅዱስ ፓ/ርኩን ለማገዝ ያለው እንቅስቃሴም ተስፋ ይሰጣል፡፡ ለውጥ ከሌሎች የሚጫን ሳይሆን ከውስጥ መመንጨት እንዳለበት ሁሉም የተገነዘቡ ይመስላል፡፡ አንዳንዶች አለቦታው ጠቅሰውት የነበረው…ዘልህቀ ውስቴታ የአምር ስርዓታ…እዚህ ላይ ቢጠቀስ ልክክ ይላል፡፡ እኛም… ኦ ቤተክህነት… ንቃህ እምንዋም…እያልን ነው፡፡በዚህ የመልካም አስተዳደርና የቤ/ክንን ሉዐሌ በሁሉም መስክ ከፍ የማድረግ እንቅስቃሴ የመላውን ውሉደ – ጥምቀት ምዕመናን የማይነጥፍ ልግስናና የሚንተከተክ ቀናኢነት ላፍታም አንዘነጋውም፡፡ማንን ይዞ ጉዞ!!በስማቸው ታዝለው መንበር የሚነቀንቁትን ግን በርዕትዕት ሃይማኖት ስላለን አንድነት ብናዝንላቸውም ተግሳጻችንን አንተውም፡፡አኮ ከመዝ…እንላቸዋለን!!
    5. ያለፈውን አንድ አመት እንደሽግግር ጊዜ እንጅ እንደስራ ወቅት ለመገምገም ይከብዳል፡፡ ሆኖም ቅ/አባታችን በዚህ ጊዜ ውስጥ (ሀ)ሂደቱ፣ ይዘቱና ህጋዊነቱ ላይ ቅሬታ ቢኖረኝም መዋቅራዊ ጥናት እንዲጠና ማስጀመራቸው፣(ለ)ባጭር ጊዜ ውስጥ በብዙ የገጠሪቱዋ ቤ/ክ በመዘዋወር ቡራኬ በመስጠት ልጆቻቸውን በማጽናናታቸው፣(ሐ)የአክሱምን ግዙፍ የ300ሚሊዮን ብር ሙዚየም ግንባታ በማፋጠናቸው፣(መ)ትንሽ፣ትልቅ፣ከዚህ ወገን-ከዚያ ወገን ሳይሉ ባለጉዳዮችን ሁሉ በትህትና ያለአድልዎ ተቀብሎ በማነጋገር፣(ሠ)በሄዱበት ሁሉ ስለሙስና አስከፊነት በመስበክ ጆሮ ላለው ሁሉ በማሰማት ቀሳጥያን እጃቸውን ሰብሰብ እንዲያደርጉ በማስቻላቸው፣(ረ)የካህናት ኑሮ እንዲሻሻል ከ40 በመቶ በላይ የደሞዝ ጭማሪ በማድረግ አቡነ ጳውሎስ 2ሺህ ያደረሱትን የካህናት ደሞዝ ወደ 3ሺህ በማምዘግዘግ የከተማ ኑሮ ውድነት ያደቀቀው ካህን የደጀሰላም መክፈልት መጣ-አልመጣ ሳይል፣ ለእለት ምግቡ ሳያስብ እንዲያገለግል በማድረጋቸው….ወዘተ አመቱ የስኬት ሆኖ አልፉዋል፡፡

    6. እኚህን አባት መላው ምዕመንና ካህን በጸሎትም በተግባርም ሊራዳቸው ይገባል!! እንዳለፈው ዘመን የቤተክህነትን ገመና ለቤ/ክ አንድነት ሀላፊነት በማይሰማቸውና በአንድ ግለሰብ ስሜት ከመሽከርከር ባለፈ ብዙም ተቄዋማዊ መልክ በሌላቸው ዓለማዊ የፖለቲካ ጋዜጦች እንዳንወሰድ፡፡የግብጽ ኮፕቲክን ተመልከቱ፡፡አባቶቻቸውን በመራዳት በፍጹም አንድነት ይቆማሉ እንጅ እንደ እኛ የጋዜጣ ሲሳይ አያደርጉዋቸውም፡፡ለዚህም ነው ሁሌም ኃያላን አባቶችን የሚያፈሩት – በቅንነት ሚራመድ ምዕመንና ካህን ስላለ!!እኛኮ በዚች የ60 አመት የመንበረ ፓትርያርክ ልምዳችን…ለሙሴ ቤ/ክህነት ቀበርዎ በህይወቱ…እያልን ታላላቅ አባቶችን ለደርግ ግዞትና ገመድ የሰጠን ሰዎች ነን፡፡እንመለስ እንጅ ወንድሞች!!እስካሁን አባቶችን ከማወከብ ምንም አላገኘንም!!ስለዚህ እስኪ አግዘናቸው ደግሞ እንሞክረው!!

    ሁላችንንም ከበቅ/ቤ/ክ ደጅ አይነጥለን!!

    • Anonymous March 7, 2014 at 8:46 am Reply

      ሰናይ ውእቱ፡፡

  2. Anonymous March 8, 2014 at 1:32 am Reply

    በአማን ነጸረ በሚል አጠራር ራስህን የምታስተዋውቀው ግለሰብ የምታቀርበውን አስተያየት አሁን ስመለከተው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በአጠቃላይ የሃሳብህ ዋና ዓላማ ማቅ ላይ ያነጣጠረ እንጅ ምንም በቃላት ድርደራ ብታሳምረውም ቁም ነገሩ ከዚህ አልፎ ተርፎ ያየሁት ነገር የለም። ይህንን ስል ግን አንድ ሰው ሀሳቡን በየትኛውም መንገድ የመግለጽ መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አንተ እንደምታወራው ግን በምንም ይሁን በምን ማኅበሩን ለማቃለል የምታደርገው የጥላቻ ወይም የቅናት መንፈስ እንጂ የአንተን ለቤተ ክርስቲያን ቀናኢነት የሚያሳይ አንድም ፋይዳ ያለው ነገር አያሳይምና እንዲሁ ሥራ ፈትነትህን ትተህ ባይሆን ወኔው ካለህ እውነትን ለመናገር መልካም ነገርን ለማሰብ ሞክር። የማኅበሩን በጎ ጎን ለማየት አባል መሆን አያስፈልግም የቤተ ክርስቲያን ልጅ መሆን በቂ ነው። ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን የሚያደርገውን አስተዋጸኦ በቅርብ ስለማውቀው የአንተ አባባል በስምም ባትጥቅሰውም ከጥቅም ፈላጊዎች ወገን ወይንም ለወሬ ጊዜ ከተረፈው ስለሚመድብህ እንዲሁ እንዳወራህ ትቀራለህ እንጂ አንተም ሆንክ መሰሎችህ የምታመጡት ምንም ለውጥ የለም ወደፈት እናየዋልን። የሆኖ ሆኖ አንተም ወደ ልብህ ተመልሰህ ትችትም ቢሆን ለመሻሻል የሚጠቅመውን እየመረጥክ ብታስነብብ ይመረጣልና ተለማመደው።

Leave a comment