ኢሕአዴግ እና የሃይማኖት ነጻነት

FACT Magazine Cover 02(ፋክት መጽሔት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፲፱ ጥቅምት ፳፻፮ ዓ.ም.)

ተመስገን ደሳለኝ

… ኢሠፓ መራሹ መንግሥት በኢሕአዴግ ከተተካ ጥቂት ወራት ቢያልፈውም፣ የተራዘመው የእርስ በርስ ጦርነት ያልደረሰባቸው በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አንዳንድ ከተሞችን ገና በቅጡ አልተቆጣጠራቸውም፤ በአናቱም በኢሠፓ መንግሥት ሽንፈት ሳቢያ እንዲበተን ከተገደደው የአገሪቱ መደበኛ ወታደር አብዛኛው ከእነትጥቁ የትውልድ መንደሩንና ቤተሰቡን መቀላቀሉ በአገሪቱ ላይ ከባድ ፍርሃት አንብሯል፡፡ በሰላም ወጥቶ ለመመለስ ርግጠኛ መኾን የማይቻልበት ከባቢያዊ አየርም አስፍኗል፡፡ በበርካታ ቦታዎች ተጠንተውና ታቅደው የሚፈጸሙ ወንጀሎችም ከአምስት እስከ ዐሥራ አምስት በሚደርሱ ወታደሮች የተደራጁ ልዩ ልዩ ሕገ ወጥ ቡድኖች በየማዕዘኑ እያቆጠቆጡ መኾኑን አመላክትዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የዐዲስ አበባ ቆዳ ስፋትና የነዋሮዎቿ የአኗኗር ዘይቤን በቀላሉ ለመልመድ የተቸገሩ ተጋዳላዮች ለትንሽ ለትልቁ ግርግር ጠመንጃን እንደ መፍትሔ መምረጣቸው ችግሩን አባብሶታል፡፡ ጉዳዩ እያሳሰባቸው የሄደው የኢሕአዴግ ዋነኛ መሪዎችም እንዲህ ዐይነቱን አለመረጋጋትና ሥርዐተ አልበኝነት ለመቆጣጠር የመንፈሳዊ መሪዎች አስተዋፅኦ ወሳኝ ስለ መኾኑ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል(እንደ ቀደሙት ሥርዐቶች ኹሉ ለቅቡልነት ከሚጠቀሙበት በተጨማሪ ማለት ነው)፡፡ ይኹንና በመንበሩ ላይ የነበሩት ፓትርያርኩ አቡነ መርቆሬዎስ አገር ለቀው እንዲወጡ በመደረጉ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡

ይህ ጊዜ ነው ከ፲፱፻፸፬ ዓ.ም. ጀምሮ [ከኢየሩሳሌም ተሰደው] መኖርያቸውን አሜሪካን አገር ያደረጉ አንድ መንፈሳዊ አባት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የተወሰነው፤ በጥሪው መሠረትም ወደ አገራቸው ሲገቡ መንግሥት የክብር አቀባበል አደረገላቸው፡፡ እኚኽ አባት ዛሬ በመንበረ ፕትርክናው የተሠየሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ነበሩ፡፡ ኾኖም ከሳምንት ሽር ጉድ በኋላ አቡነ ‹‹የኢዲዩ አባል ነበሩ›› የሚል ወሬ በአመራሩ አካባቢ በስፋት መሰራጨቱ ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ አስከተለ፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ኢሕአዴግ እና ኢዲዩ በ፲፱፻፸ዎቹ መጀመርያ ትግራይ እና ጎንደር ውስጥ በርካታ መሥዋዕትነት ያስከፈለ ውጊያ ማድረጋቸው ብቻ አልነበረም፡፡ የመጀመርያዎቹ ሊቀ መንበሮች ስሁል ገሰሰ እና መሐሪ ተኽሌ(ሙሴ) ‹‹የተገደሉት በኢዲዩ ነው›› የሚለው ወሬ በድርጅቱ ውስጥ ከጫፍ ጫፍ የተናኘና የታመነበት ጉዳይ መኾኑ ነበር፡፡ በዚህም ላይ የህ.ወ.ሓ.ት መሪዎች ግራ ዘመምነት ተደማምሮ አቡነ ማትያስ በወቅቱ ወደ ታሪክነት ከተቀየረ ዓመታትን ባስቆጠረው ኢዲዩ ተፈርጀው ከታጩበት የፕትርክና መንበር ተገፈተሩ፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር አብላጫውን የትጥቅ ትግል ዘመን በአሜሪካ ያሳለፉት አሰፋ ማሞ እና ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ‹‹ዉድብ›› የሰጠቻቸውን ተልእኮ ተቀብለው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ያመሩት፤ እናም ቀድሞም ትውውቅ ወደነበራቸው ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ዘንድ ሄደው ለፕትርክና ወንበር መታጨታቸውን አበሠሯቸው፡፡ በእንዲህ ያለ መንገድ መንግሥት የቀባቸው አቡነ ጳውሎስም እስከ ኅልፈታቸው ድረስ አወዛጋቢ መሪ ኾነው ዘልቀዋል፡፡

(በነገራችን ላይ በአሜሪካ ለመጀመርያ ጊዜ ከሲኖዶሱ ተነጥሎ የቆመ ቤተ ክርስቲያን የመሠረቱት አቡነ ጳውሎስ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ አቡኑ ደርግ ለጥቂት ዓመታት አስሮ ከለቀቃቸው በኋላ ወደ አሜሪካ ሄደው የፈጣሪያቸውን ሰማያዊ መንግሥት ሲሰብኩ ቆይተው የህወሓት ሠራዊት ክንዱ እየበረታ በቁጥጥሩ ሥር ያዋላቸው ከተሞችም እየበዙ ሲሄዱ እርሳቸውም ስብከታቸውን ወደ ትግርኛ ቋንቋ ከመቀየራቸውም በላይ ለ‹ነጻ አውጭ›ው ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ ያሰባስቡ ጀመር፡፡ የሥርዐት ለውጥ መደረጉን ተከትሎም በፖሊቲከኞች በተቀነባበረ ሤራ ከአቡነ ጳውሎስ ጋራ ቦታ የተለዋወጡት አቡነ መርቆሬዎስም፣ እዚያው አሜሪካ ‹ተተኪ›ያቸው የጀመሩትን ብሔር ተኮርና ከሲኖዶሱ የተገነጠለ ቤተ ክርስቲያን አስፋፍተው ዛሬ ለደረሰበት ‹የጎንደሬ ማርያም›፣ ‹የትግሬ ገብርኤል›. . .ለተሰኘ አሳፋሪ ክፍፍል ዳርገውታል፡፡ በርግጥ ለአቡኑ[አቡነ መርቆሬዎስ] ከአገር መውጣት የኢሕአዴግ እጅ እንዳለበት እንድናምን የሚያስገድደን በቅርቡ ታምራት ላይኔ ‹‹በእኔ ፊርማ ነው ያባረርናቸው›› ማለቱን ዊኪሊክስ ካደረሰን መረጃ በተጨማሪ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ህወሓት በተቆጣጠራቸው በትግራይና ወሎ ነጻ መሬቶች በሚገኙ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎችን ቀስቅሶና አደራጅቶ ፓትርያርኩ ላይ ‹‹ሽጉጥ ታጣቂ ጳጳስ››፣ ‹‹ቀይ ደብተር ያለው/ለኢሠፓ አባላት የሚሰጥ/ የሸንጎ ተወካይ››. . .የመሳሰሉትን መፈክሮች እያሰሙ በተቃውሞ ሰልፍ እንዲያወግዟቸው ማስተባበሩን ስናስታውስ ነው)፡፡

ዛሬስ የሃይማኖት ነጻነት የት ድረስ ነው?

ከላይ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብዬ በደምሳሳው ለመጠቃቀስ እንደሞከርኹት፣ ኢሕአዴግ በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ጣልቃ ማስገባት የጀመረው ክንዱ ሳይፈረጥም ገና በረሓ ላይ ሳለ ነበር፡፡ በዚህ ኹኔታ የተጀመረው ጣልቃ ገብነት ዛሬም ድረስ ተባብሶ ቀጥሏል፤ ምንም እንኳ በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገባ በደፈናው ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፲፩ን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ለማስተባበል ቢሞክርም ያለፉት ዓመታት ተጨባጭ ተግባሮቹ የሚመሰክሩት ግልባጩን ነው፡፡ ድርጅቱ ራሱም ቢኾን ጥያቄው በተነሣ ቁጥር ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፲፩ን የሚጠቅሰው ለስሙ እንጂ ሕጉ ተግባራዊ አለመኾኑን ሳይረዳ ቀርቶ አይደለም፤ አቶ ተፈራ ዋልዋም በ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. ኅዳር/ታኅሣሥ ወር ከታተመችው ሐመር መጽሔት ጋራ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ጉዳዩን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት የኢሕአዴግን አጭበርባሪነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡-

‹‹ኢሕአዴግ እኮ የሚመራው መንግሥት በደርግም ጊዜ፣ በኃይለ ሥላሴም ጊዜ እንደሚታወቀው ‹የቤተ ክርስቲያን ሥራ አስኪያጅ ሹምልን› ተብሎ ተጠይቆ ‹የለም ራስዋ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትሾማለች እንጂ እንደ ቀድሞው መንግሥት አይሾምላችኁም› የሚል መልስ የሰጠ መንግሥት ነው፡፡››

በሕዝበ ሙስሊሙ ተመርጦ ለእስር የተዳረጉት የኮሚቴ አባላትም በአንድ ወቅት ለሚመለከተው የመንግሥት ባለሥልጣን የጻፉት ደብዳቤ ጣልቃ ገብነቱን በግልጽ ያሳያል፡-

‹‹መንግሥት እንደ መንግሥት ሕዝቡ ተበድዬአለኹ፤ ምርጫ ይካሔድ፤ የመጅሊሱን አመራር አላመንኹበትም፤ ውክልና የለውምና ሕገ ወጥ ነው ያለውን አካል ሕገ ወጥነቱ እንዲረዝም ምርጫውን እርሱው እንዲያካሒድ መወሰን ሕዝብን ግራ አጋቢ ነው፡፡››

ሥርዐቱ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ እንደማይገባ ለማሳመን ይህን ያህል ቢዳክርም በቅርቡ ‹‹የፀረ አክራሪነት ትግል የወቅቱ ኹኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች›› በሚል ርእስ የተዘጋጀው ባለ 44 ገጽ ሰነድ፣ መንግሥት በዘወርዋራ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ሙሉ በሙሉ የሚያምን ኾኖ አግኝቸዋለኹ፤

‹‹የመንግሥት መዋቅራትን ሴኩላር መንግሥት መኾናችንን ዐውቆ የመንግሥትን መዋቅር ተጠቅሞ የራሱን ሃይማኖት መሠረት ያደረገ አገልግሎት ከመስጠት ሙሉ በሙሉ ያልጸዳ መኾኑን የተለያዩ ጥቂት የማይባሉ ገሃድ የወጡ መገለጫዎች አሉ፡፡ እንዲያውም የትኛውም አክራሪ ኃይል ከመዋቅር(ከመንግሥት) አካል በርታ ሳይባልና ሽፋን ሳይሰጠው የሚንቀሳቀስ እንደሌለ አማኞቹ በገሃድ ይገልጻሉ፡፡››

መቼም ይህን ያነበበ ዜጋ መረጃው የተገኘው በመንግሥት ከተዘጋጀ ሰነድ ሳይኾን በኒዮሊበራሊስት›ነት ከተፈረጁት እነ‹‹ሂዩማን ራይትስዎች›› እና ‹‹አምንስቲ ኢንተርናሽናል›› ቢመስለው አይደንቅም፡፡ ሐቁ ግን ይኸው ነው፡፡ አገዛዙ ላለፉት ኻያ ሁለት ዓመታት መንግሥት እና ሃይማኖት እንዲለያዩ ማድረጉን ሲለፍፍ ከመቆየቱም በላይ በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን የዘገቡ ጋዜጠኞችን ከሥሦ ዛሬም ድረስ ፍርድ ቤት እያመላለሳቸው እንደኾነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ይመስለኛል ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በእስር ላይ የሚገኙት የእነ አቡበበከር መሐመድ ክሥ፣ የሼኽ ኑር ሑሴን ግድያ፣ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ውንጀላዎችንና መሰል ፍረጃዎችን አምኖ ለመቀበል የተቸገሩት፡፡

ያም ኾነ ይህ ሃይማኖትን ብቻ ሳይኾን ዕድርና ዕቁብንም ሳይቀር ‹ካልተቆጣጠርኹ ሞቼ እገኛለኹ› በሚል የቁጥጥር ልክፍት የተያዘው ኢሕአዴግ፣ በተለይም 99.6 ድምፅ አግኝቼ አሸንፌአለኹ ብሎ ካወጀበት ከምርጫ ፳፻፪ ማግሥት ጀምሮ ‹‹አናት ላይ ከተቀመጡ መሪዎቻቸው በቀር ሙሉ በሙሉ አልተቆጣጠርናቸውም›› የሚላቸውን የኦርቶዶክስ ክርስትና እና የእስልምና እምነቶችን ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ እየሠራ ለመኾኑ በርካታ መረጃዎች አሉ፡፡

በ፳፻፫ ዓ.ም. ኅዳር ወር ‹‹የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና የኢትዮጵያ ሕዳሴ›› በሚል ርእስ በአቶ መለስ ዜናዊ ተሰናድቶ የተሰራጨው ጥራዝ፣ የሥርዐቱን ቀጣይ አካሔድና ይህን ኹናቴ የሚያሳይ ከመኾኑም በተጨማሪ ዛሬም ድረስ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ መንግሥት የሚያዘጋጃቸው ሥልጠናዎችም ኾኑ ጥናታዊ ጽሑፎች መነሻ ሐሳባቸው ይኸው ዳጎስ ያለ ጥራዝ እንደኾነ ይነገራል፡፡

ጥራዙ የእምነት ተቋማትን በተመለከተ ከገጽ 128 – 132 ያካተተው ሐሳብ፣ ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛው ምክንያት ‹‹የሃይማኖት አክራሪነት›› መኾኑን ከጠቃቀሰ በኋላ ችግሩን ‹‹ተኪ የኾነ ልማታዊ አስተሳሰብ›› በማምጣት ማስወገድ እንደሚቻል ይመክራል፡፡ ይህን ከግብ ለማድረስ ደግሞ ሚዲያዎችንና ተያያዥነት ያላቸውን ማኅበራት መጠቀሙ አዋጭ እንደኾነ ይተነትናል፡፡ የኢሕአዴግ አባላት በየእምነት ተቋሞቻቸው ያሉ ማኅበራትን በዐይነ ቁራኛ መከታተል እንዳለባቸውም ያሳስባል፡- ‹‹[የግንባሩ አባላት] ከእምነት ተቋማት ውጭ ባላቸው አደረጃጀት አማካይነት በሰፊው መሥራት አለብን››፡፡ በርግጥም የእስልምና እምነት ተከታዮች ‹‹የሃይማኖት ነጻነት ይከበር›› የሚል ተቃውሟቸውን ባጠናከሩበት ሰሞን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ሙስሊም አባላቱን ለብቻ እየሰበሰበ እንቅስቃሴውን የማክሸፍ ሥራ መሥራት ግዴታቸው መኾኑን የሰበከው ከዚኹ አቶ መለስ ዜናዊ አዘጋጅተውት ከነበረው ጥራዝ ነው ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡

ከጣልቃ ገብነት ወደ ጠቅላይ ተቆጣጣሪነት

በዘወርዋራም ቢኾን በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ሙሉ በሙሉ የሚያምነው ከላይ የተጠቀሰው ሰነድ በአገሪቱ ‹‹የሃይማኖት አክራሪነት›› መከሠቱን ካተተ በኋላ ዋነኛ ተጠያቂዎች አድርጎ ያቀረበው እንደወትሮው ኹሉ ለተደጋጋሚ መሸማቀቅ የተዳረጉትን መንፈሳዊ መሪዎችንና ማኅበራትን ሳይኾን የመንግሥት መዋቅርን ነው፡-

‹‹የመንግሥት መዋቅራችን አካል ኾነው አክራሪነቱን በድብቅም በገሃድም የሚደግፍ አካል በፌዴራልም በክልልም ከሞላ ጎደል የሚታወቁ ናቸው፡፡ እነዚኹ አካላት በተቻላቸው ኹሉ በመድረክ ጤናማ እየመሰሉ የሚኖሩ ናቸው፡፡ የፀረ አክራሪነቱን ትግል ማጧጧፍ የሚፈልገውን መዋቅር አካልም ይኹን የሕዝብ አካል በተደራጀና በመረባቸው አማካይነት ከፍተኛ ጫና የሚያሳድሩ፣ የተቋማቸውን ምቹ ኹኔታ ተጠቅመው በፀረ አክራሪነት የሚንቀሳቀሱትን አካል የሚቀጡ፣ አሉባልታ እየፈጠሩ የሚያሸማቅቁ፣ ኾን ብለው ድጋፍ የሚነፍጉና በሐሰት ምስክርም ጭምር ዜጎችን የሚያሳስሩ ናቸው፡፡ የመንግሥትን አቅሞች ተጠቅመው አክራሪነትን የሚያስፋፉና ከአክራሪነት እንቅስቃሴ ጋራ በተለያዩ ጥቅሞች የተሳሰሩ ናቸው፡፡››

እነኾም በእንዲህ ዐይነቱ የውንብድና ተግባር የተሠማሩ ባለሥልጣናት የተሰባሰቡበት፣ ውንብድናው መኖሩንም የሚያምን መንግሥት አንድም ተጠያቂዎቹን ለሕግ አሳልፎ አለመስጠቱ፣ አልያም ሥልጣኑን በፈቃዱ አለመልቀቁ በአገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመረዳት ነቢይነትን አይጠይቅም፡፡ በአናቱም ሥርዐቱ ለሕግ የበላይነት ተገዥ አለመኾኑን የሚያሳየው በዚህ ደረጃ ‹‹ችግሩን ተረድቸዋለኹ›› እያለም እንኳ፣ ዛሬም የቅጣት ብትሩን ያሳረፈው ከመዋቅሩ ጋራ አንዳችም ንክኪ በሌላቸው መንፈሳዊ መሪዎች ላይ መኾኑ ነው፡፡ በርግጥም ይህ ዐይነቱ አሠራር ከዐምባገነን አስተዳደር መገለጫዎች አንዱ ነው፡፡ ኢሕአዴግም ያለፉትን አራት ምርጫዎች ጨምሮ በተለያየ ጊዜ የዴሞክራሲም ኾነ የሰብአዊ መብትን በዐደባባይ መጣስ፣ የሐሰት ክሦችንና ፍረጃዎችን እንደ ምክንያት መጠቀም ነባር ስልቱ እንደኾነ ይታወቃል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እየዘረዘረ ያለው የፈጠራ ውንጀላ እና ለሙስሊሙ ‹‹መፍትሔ አፈላላጊ›› ተብለው በተመረጡት የኮሚቴ አባላት ላይ የወሰደው ዕመቃ መግፍኤ ይኸው ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ ከዚህ ቀደም በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ስለሚፈጸመው የግፍ ግድያዎች ይሰጥ የነበረውን ምክንያት በመንፈሳዊ ሰዎችም ላይ ያለአንዳች የይዘት ለውጥ ለመጠቀም አላመነታም፡፡ እንደሚታወሰው በድኅረ ምርጫ – ፺፯ በአምቦና በኢተያ በታጣቂዎች የተገደሉትን የኦሕኮ አባላት ከተፈጥሮ ሕመም ጋራ አያይዞት ነበር፡፡ በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጀመርያ ላይ በተካሔደው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ደግሞ የምዕራብ ወለጋና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኄኖክ ‹‹ቤጊ›› ወረዳ በመንግሥት ባለሥልጣናት ተፈጸመ ያሉትን ግድያ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ተወካይ፡-

‹‹በቤተ ክርስቲያን 70 ሜትር ርቀት ላይ የሌላ እምነት ተከታዮች የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ መፈቀዱን ከተቃወሙት መካከል አንድ ዲያቆን ተደብድቦ በሦስተኛው ቀን ሕይወቱ ሲያልፍ ‹በወባ በሽታ ነው የሞተው› ተብሎ ለፍርድ ቤቱ የሐሰት ማስረጃ ከዶክተሩ እንዲቀርብ ታዘዘ›› ማለታቸውን መጥቀሱ ለጉዳዩ አስረጅነት በቂ ይመስለኛል፡፡

የኾነው ኾኖ አገዛዙ በዘረጋው ግዙፍ መዋቅሩ ውስጥ ያልታቀፉ ማኅበራትንም ኾነ የሃይማኖት ተቋማትን የስጋት ምንጭ አድርጎ ማየቱ፣ በእምነት ነጻነት ላይ ጣልቃ ለመግባትም ኾነ ምንም ዐይነት ገለልተኛ ተቋማት እንዳይኖሩ ዕንቅልፍ ዐጥቶ መሥራቱን ያሳያል ብዬ አስባለኹ፤ በሚቆጣጠራቸው የኤሌክትሮኒክስና የኅትመት ሚዲያዎች ቀን ከሌት የፕሮፓጋንዳ ከበሮ የሚመታበት የ‹አክራሪነት› ፍረጃም መነሾው ይኸው ይመስለኛል፡፡ ሰነዱን ከዚህ ቀደም ካየናቸው ለየት የሚያደርገው፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ አሉ ከሚላቸው ወንበዴዎች በተጨማሪ የሚከሥሣቸውን መንፈሳውያን ማኅበራት በደፈናው ‹‹በክርስትና እምነት ውስጥ ያሉ›› ብሎ አለማለፉ ነው፤ ቃል በቃል እንዲህ ይላልና፡-

‹‹በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ የመሸጉ የትምክህት ኃይሎች ጽንፈኛ የፖሊቲካ ኃይሎች አካል በመኾን በጋዜጣና በመጽሔት ሕዝባችንን ለዐመፅና ለሁከት ለማነሣሣት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡. . .በራሳችንም ኃይል እንደሌላው ሰልፍ ልንወጣ ይገባል በሚል የዐመፅና የሁከት ቅስቀሳ ለማድረግ ይፈልጋሉ፡፡››

ይህ ኹኔታ መንግሥት መንፈሳውያን ማኅበራትን ጠቅልሎ ለመቆጣጠር በመፈለጉ ለተቃዋሚዎች ያሠመረውን ‹ቀይ መሥመር› መጣሱን ያሳያል፡፡ አስገራሚው ጉዳይ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማትን የፖሊቲካ መሣርያ አድርጎ መጠቀሙ አልበቃ ብሎት ወደ መንፈሳውያን ማኅበራቱ መዞሩ ነው፡፡

በገሃድ እንደሚታወቀው የክርስትና ይኹን የእስልምና እምነት መሪዎች በተለያየ ጊዜ ከሥርዐቱ ጎን ተሰልፈው ‹ናዳን ለመግታት› ያደረጉት አበርክቶ በቀላሉ የሚገመት አለመኾኑ ነው፡፡ በርግጥም ‹‹የቄሣርን ለቄሣር›› በሚል አስተምህሮ የሚያድሩ፣ ደመወዛቸው በምድር ያልኾኑት መንፈሳውያን አባቶች በድኅረ ምርጫ – ፺፯ ሕፃናትን ሳይቀር በጥይት የፈጀውን ሥርዐት ማውገዝ ቀርቶ መምከር ያለመፈለጋቸው ምክንያት ፍርሃት ብቻ ሳይኾን የግል ጥቅምን ታሳቢ ያደረገው ግንኙነታቸው ያሳደረው ተጽዕኖ ይመስለኛል፡፡ ከቅዱሳን መጻሕፍት ይልቅ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ‹አዳኝ› አድርገው የመቀበላቸው መግፍኤ ይኸው ነው፡፡ ኢሕአዴግም ‹ነገረ መለኰት›ን ለሲኖዶሱና ለመጅሊሱ እስከ ማስተማር ድረስ የደፈረው የእነርሱ ለሁለት ጌታ መገዛት ነው – ለገንዘብ እና ለጌታ፡፡

የሲኖዶሱ እና የመንግሥት ፍጥጫ

በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ከፍተኛውን ሥልጣን የሚይዝ ሲኾን ፓትርያርክንም የመሾምና የመሻር ሥልጣን አለው፡፡ ኾኖም ይህ የላዕላይ መዋቅር እስከ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት ድረስ ለእርሳቸውም ኾነ ለሥርዐቱ ሰጥ ለጥ ብሎ የሚገዛ ጥርስ የሌለው አንበሳ በመኾኑ ለትችት ከመዳረጉም በላይ በምእመናን ዘንድ ለመንፈሳውያን አባቶች የሚሰጠው ክብርም ተነስቶት ቆይቷል፡፡

ይኹንና በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጀመርያ በተካሄደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ፴፪ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከመንግሥት የተወከሉ ሓላፊዎች÷ ‹‹የብዝኃነት አያያዝ አክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌዎቹና መፍትሔዎቹ›› በሚል ርእስ ያቀረቡትን ጥናት ተከትሎ ስድስት ጳጳሳት ቀድሞ ባልታየ መልኩ ጠንካራ ተቃውሞ ማቅረባቸው፣ በብዙዎች ዘንድ የሃይማኖት መሪዎች ለመንፈስ ልዕልና ሊገዙ ይኾን? ከምድራዊው ይልቅ ሰማያዊውን ሊመርጡ ይኾን? ‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› የሚለውን አስተምህሮአቸውን ሊተገብሩ ይኾን? የሚል ጥያቄ አጭሯል፡፡

በዕለቱ የመጀመርያው ተናጋሪ የነበሩት የሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በጥናቱ ላይ መቻቻል አስመልክቶ የቀረበውን ድምዳሜ እንዲህ ሲሉ ነበር ያጣጣሉት፡-

‹‹ይኼ አክራሪነት፣ ጽንፈኝነት የሚለውን ቋንቋ እናንተው ናችኹ ያሰማችኹን፤ ከዚህ በፊትም አይታወቅም፣ በደርግም ይኹን በሌላ፡፡ እንደገና ደግሞ ብዙ ጊዜ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት እያላችኹ ዕድሜ ሰጥታችኹ ያበለጸጋችኋቸው እናንተው ናችኹ፡፡››

በርግጥም አቡኑ የተቹት ሥርዐቱ የፕሮፓጋንዳው ፋሽን ያደረገውን ‹‹መቻቻል››ን ብቻ አይደለም፤ ‹‹በመቃብሬ ላይ ነው የሚሻሻለው›› የሚለውን የመሬት ፖሊሲንም ነው፡፡. . . ‹‹በፊት መሬትም ሕዝብም የነገሥታቱ ነበር፤ አሁንስ የማን ነው? ይልቁንም ከአንድ ቤት ‹ግድግዳው የቤቱ ባለቤት ነው፤ ሳሎኑ የመንግሥት ነው› የሚለው ዐዋጅ የአሁን አይደለም እንዴ? ለኢትዮጵያዊነቱ ዋስትና የለውም፤ ይኼ የእኔ ነው የሚለው ከሌለ ምንድን ነው? ይህች የእኔ የኢትዮጵያዊነቴ መገለጫ ናት ካላለ ምንድን ነው ኢትዮጵያዊነት? አሁንም መሬቱም ሕዝቡም የእናንተው ኹኖ ሳለ ለፊቱ፣ ለነገሥታቱ መስጠታችኹ በምን ተመልክተውት ነው?››

የደቡብ ጎንደር ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ እንድርያስም በሚያስተዳድሩት አካባቢ ያለውን የመንግሥት ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖን ከዘረዘሩ በኋላ ለተሰነዘረው ፍረጃና ማሸማቀቂያ እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡-

‹‹የተበደለ ሰው ሲናገር ‹ፖሊቲካ ተናገረ› እየተባለ የውሸት ውሸት ሲያተራምሱን የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡. . .እንዴ! የመንግሥት ሥልጣን የተረከቡ ወንድሞች የእኛን አፍ፣ የእኛን አንደበት ብቻ ነው እንዴ የሚጠብቁት፤ ለሌሎች ሞራል ይሰጣሉ ማለት ነው?. . .ለምንድን ነው ግን በሽፋንነት የምትጠቀሙብን? መንግሥት እኛን ሽፋን አድርጎ ነው ሲበዘብዘን የምንኖረው፡፡ ሌባውም ቀጣፊውም ሰርጎ ገቡም ሲያጭበረብረን ሲያታኩሰን መንግሥትን ሽፋን አድርጎ ነው፡፡››

የወላይታ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅም በተመሳሳይ መልኩ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ቤተ ክርስቲያኗ ስትቃወም ጉዳዩን ወደ ፖሊቲካ እየቀየሩ ማስፈራራቱ እንደተለመደና ለቀብር ማስፈጸሚያ የሚኾን መሬት ከመስተዳድሩ በሚጠየቅበት ጊዜ የሚሰጠው መልስ በሐሰት መወንጀል እንደኾነ ከገለጹ በኋላ ጉዳዩ መፍትሔ ካላገኘ ሊከተል ስለሚችለው ስጋታቸውን ተናግረዋል፡-

‹‹ ‹የፖሊቲካ ጉዳይ ነው፤ ሕዝብን በሃይማኖት ሽፋን ታንቀሳቅሳላችኹ› እየተባልን እየተሸማቀቅን ያለንበት ኹኔታ ነው ያለው፡፡ ይህን እንዴት ታዩታላችኹ? መቻቻልስ የሚመጣው ከምን አኳያ ነው? ዝም ብለን የምንቀመጥ ከኾነ ምናልባት ሓላፊነት ለመውሰድ ስለሚከብደን ይህን ወርዳችኹ እንድትፈትሹ ለማለት ነው፡፡››

(በነገራችን ላይ የአጠቃላይ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ በተጠናቀቀ ማግሥት ከማኅበረ ቅዱሳን አመራር ሦስት አባላት ወደ ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተጠርተው ዶ/ር ሽፈራውን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ሓላፊዎች ጋራ ውይይት ማድረጋቸውን ከመሥሪያ ቤቱ ምንጮቼ ሰምቻለኹ፡፡ ሚኒስትሩ ከማኅበሩ አመራሮች ጋራ ለመወያየት የተገደዱት ካልተጠበቀው የሲኖዶሱ አባላት ድፍረት ጀርባ ‹የማኅበረ ቅዱሳን እጅ አለበት› የሚል ጥርጣሬ በመያዙ ነው፡፡ በውይይቱም ላይ የተንጸባረቀው የአባላቱ መለሳለስ፣ ማኅበሩን አክራሪ ብለው እንደማያምኑና ከዚህ ቀደም የተሰራጩት ወንጃይ ሰነዶችን ሳይቀር ‹አናውቃቸውም› እስከማለት የደረሰ እንደነበር አረጋግጫለኹ፡፡ ይኹንና ይህ እሳት ማጥፊያ ስልት ከሥርዐቱ ጋራ የቆየ መኾኑ ይታወቃል፤ የማኅበሩ አመራርም ይህ ይጠፋዋል ብዬ ባላስብም፤. . .)

የኾነው ኾኖ [በአጠቃላይ ጉባኤው ዓመታዊ ስብሰባ] ከፌዴራል ጉዳዮች ከመጡት ሦስት ተወካዮች መካከል አቶ ገዛኽኝ ጥላሁን አብዛኛውን ጥያቄ በተመለከተ የሰጡት ምላሽ የወከሉት መንግሥት ዛሬም በተሳሳተ ታሪክ ንባብ እያሸማቀቀ፣ እያስፈራራ፣ ሕግን እየጠመዘዘ፣ እስር ቤት እየከተተ. . . የፖሊቲካ ጥቅሙን ማስከበር ላይ ያተኮረ መኾኑን ያሳያል፡፡ ሓላፊው ማስጠንቀቂያውን ያስተላለፉት እንዲህ በማለት ነው፡-

‹‹መጀመርያ ግንዛቤ ላይ እንሥራ በሚል ርምጃ አልወሰድንም፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር ወደ ቃሊቲ መፍትሔ አይኾንም፡፡››

. . .‹ቃሊቲ›ን ምን አመጣው? መቼም ለጣልቃ ገብነቱ ከዚህ የበለጠ ማሳያ መፈለግ ‹ዐውቆ የተኛን. . .› እንደመኾን ነው፡፡ ‹‹መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው›› ብሎ መከራከሩም ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ ይመስለኛል፡፡ እናም የተሻለው መንገድ ከላይ በጠቀስኹት ሰነድ ‹‹በየማእከላዊ ኮሚቴው በሚካሄደው የስምሪት ተግባር በፀረ አክራሪነት ትግል ላይ ያለው የእያንዳንዱ ግለሰብ ቁመና መፈተሽ አለበት›› ተብሎ የተገለጸውን ማሳሰቢያ በፍጥነት በመተግበር፣ በቅድሚያ ራስን ከአክራሪነትና አሸባሪነት ማራቅ ነው፡፡ ማረጋገጫ የማይቀርብበትን አፈ ታሪክንም እየለቃቀሙ በአንድ ሃይማኖት ላይ መለጠፉ አስተማሪ አይመስለኝም፡፡

ከዚህ ባለፈ ‹‹የሃይማኖት ኮማንድ ፖስት አቋቁመን ለችግሩ እልባት እንሰጣለን›› የምትሉት ጉዳይ በቀጥታ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ማስገባቱን በዐደባባይ ከማመን ያለፈ የፖሊቲካ ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡ ጳጳሳቱም ኾኑ ሼኾቹ ሓላፊነትና ግዴታቸው ሰማያዊውን መንግሥት መስበክ እንጂ ከሰላይ አለቆችና ከፖሊስ አዛዦች ጋራ ቢሮ ዘግተው የመንፈስ ልጆቻቸውን ‹‹ትምክህተኛ››፣ ‹‹አሸባሪ››፣ ‹‹አክራሪ››. . .እያሉ እንዲፈርጁ መፈታተኑ ያልታሰበ ሕዝባዊ ቁጣ መቀስቀሱ አይቀርም፡፡

11 thoughts on “ኢሕአዴግ እና የሃይማኖት ነጻነት

  1. Anonymous November 11, 2013 at 7:04 am Reply

    ይቅርታ በመጀመሪያ ሃራ ተዋህዶ ፖለተካ ነክ ፅሁፍ ያዋጣል ብየ አላስብም ነበር፡፡ ተመሰገን ከፃፈው ውስጥ ምን አዲስ ነገር ጨመረበት?ይህን ፅሁፍ እኮ የትም ቦታ ማነበብ የምትችለው ነው ነገር ግን እንደ ትልቅ ነገር በዝህ ድህረ ገፅ መውጣቱ አሳፍሮኝል፡፡ ወይንስ ለኔ የተደበቀብኝ ኦርቶዶክሳዊ ፅሁፍ ይኖው ይሆን !አይመስለኝም፡፡ወይስ ተመስገን እንደሚለው እንደ ሌሎች እምነቶች ግጭትን እንድንፈልግ ነው? ወይንስ ደግሞ ተመስገን የትኛው የሃይማኖት ጥንካሬው ነው እንደ መልካም ነገር በሃራ ተዋህዶ ዌብሳይት የወጣው? በፀሎት ሃይል ሁሉን ማድረግ እንደምንችል ፈፅሞ አምናለሁ፡፡ ከተመስገንስ እናንተ በተሻለ ሁኔታ መፃፍ አትችሉምን? ለማንኛውም መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ፡፡

  2. ms November 11, 2013 at 7:58 am Reply

    ኣቶ ተመስገን የተቃዋሚው ጎራ ተስፋ ቢያጣበት የ ቤተ ክርስትያኒቱ ጠበቃ በመምሰል እዛው ያጣውን ኪሳራ ባባቶች ስም ለማካካስ ይፈልጋል! ዳሩ ግን ኣሁንንም መታወቅ ያለበት ኣክራሪነት በዚች ኣገር ቦታ ሊኖረው ኣይገባም! ኣቶ ተመስገን ቢያንስ ቢያንስ በኣክራሪነት ዙርያ መንግስትን ደግፎ መቆም ነበረበት የፖሎቲካ ልዩነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን “የትም ፍጪው ሰልጣኑን ኣምጪው” የሚለውን መርህ መከተል የትም ኣያደርስም! ይህ የሚያሳየው ባገር ጉዳይና ደኅንነት ምንም እንደማያስጨንቀው ነው! ኣሁንም ኣክራሪው እስልምና እንዳለ ሆኖ በማኅበረ ቅዱሳን የመሸጉ የትምክህት ኃይሎች በስፋት መኖራቸው ያደባባይ ምስጢር ነው! ማኅበሩ የቤተክርስትያኒቱ ኣጀንዳ ብቻ ኣድርጎ ቢንቀሳቀስ ያዋጣዋል የሚል እምነት ነው ያለኝ ካልሆነ ግን በቤተ ክርስትያኒቱ ታሪክ ጠባሳ ነገር ትቶ ማለፉ የማይቀረ ነው!

    • Anonymous November 12, 2013 at 12:41 am Reply

      ms በስባሳ ስለ ስብከትህ ገደል ልትገባ ትችላለህ ዳሩ የት ይገባሃል ?

    • Anonymous November 12, 2013 at 12:49 pm Reply

      woyane

  3. tm November 12, 2013 at 6:48 am Reply

    Dear ms
    I apologize for not using Amarigna.
    I do respect your opinion however, when one criticize somebody’s idea he has to differentiate the individual from the his argument. Thus, my advise for you is to forget Ato Temesgen and focus his arguments. This is i think a rational and fair way of giving a feedback. He has explained his ideas based on evidences and he has cited references for his argument, therefor you are expected to defend this by a similar way. Bring your evidences let’s see them so that our decision will not be skewed. Otherwise blaming somebody because of his argument even by Mentioning his name is unacceptable and in any means will not be justifiable.

    The other point i want to kindly request you is that you have mentioned about ” በማኅበረ ቅዱሳን የመሸጉ የትምክህት ኃይሎች በስፋት መኖራቸው ያደባባይ ምስጢር ነው” I appreciate that you are one of the person to witness it is a revealed truth! Let me ask you simple questions

    As a person who criticizes an argument in public,
    Do you relay know who mahiberekidusan (mk) is?
    How and how it is established, its role and responsibility?
    What is your evidence to reach on to the above conclusion?
    Mk has a head quarter office at the middle of Addis, did you ever get the chance to visit and see the living operation conducted for not less than 18 hrs a day.? I do recommend you to visit if you don’t do it so far , no body will ask you who you are, where are you from, which language your speaking, from which region or tribe you are, what life status you are in and etc.., if may be you are out of Addis, MK has 44 regional offices across the country even out side the country, then you will be able to give criticism.

    Don’t you know that leave alone a tangible evidence, a simple public rumour is enough for the government to take mk to the court, but that is not the case. Besides, it is the holy synod who has absolute authority even not the government over MK, so don’t forget that when you blame or criticize mk, you are indirectly pushing the synod’s authority that is against the constitution. But I’m not saying mk shouldn’t be criticized, but it should be based on real and tangible evidence, by then you may provide your evidence to the synod and even to the public.
    I hope it is clear. Sorry for my jargon words.
    Selam!

  4. kokeb November 12, 2013 at 7:27 am Reply

    ” በማኅበረ ቅዱሳን የመሸጉ የትምክህት ኃይሎች በስፋት መኖራቸው ያደባባይ ምስጢር ነው” can you please list their names with clear evidence of their membership to MK. otherwise same BORING baseless accusations.

  5. TEGEHAS November 13, 2013 at 10:27 am Reply

    ስለ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሁሉም ህትመቶች ላይ ሲጻፍ በፍጥነት ብታወጡልን ደስታየ ነው ፡፡ግን በማላውቀው ምክንያት የምታወጡዋቸው ከመንግስት በተቃራኒ ከቆሙ ሚዲያዎች የሚሰነዘሩ ትችቶችን ብቻ ነው፡፡ለምን?? ለምን???

    በተመስገን ሀተታ ላይ የሚታዩኝ ጉድፎች

    1. ማስረጃ ሳይጠቅሱ መጻፍ፡ ስለ አቡነ ማትያስ ኢዲዩ ተብሎ በህወሃት መገፍተር፣አሰፋ ማሞና ብርሃነ ገ/ክርስቶስ አቡነ ጳውሎስን ለማግባባት ወደ አሜሪካ ስለመላካቸው፣አቡነ ጳውሎስ የህወሃትን ትግል በገንዘብ ስለመርዳታቸው፣ህወሀት በአቡነ መርቆሬዎስ ላይ ስላደረገችው አሉታዊ ቅስቀሳ በድፍረት ሲጽፍ ለአንባብያን አንዳችም ማስረጃ አላቀረበም፡፡ወይም ማስረጃ የሚያስፈልገው ስለ ተቃዋሚ ሲጻፍ ብቻ ነው ብሎ ደምድሙዋል፡፡

    2. አንድ ወገንን ብቻ ለማጥቃት መጻፍ፡ አቡነ ጳውሎስም ሆነ አቡነ ማትያስ በ1974 ዓ.ም ለምን እንደተሰደዱ እንኩዋ መጻፍ አይፈልግም፡፡ከዛ ይልቅ በደርግ የተሸሙት የአቡነ መርቆሬዎስ ስም መጥፋቱና እሱ እንኩዋ አለማዊ ሆኖ ሳለ የተቁዋቁዋመውን ወከባ ፈርተው ሀገር ለለቀቁት አቡን በብእሩ የአዞ እንባ ያለቅሳል፡፡አያይዞም የአቡነ መርቆሬዎስን ከስርዓት ውጭ 2ኛ ሲኖዶስ በማቁዋቁዋም በኢኦተቤክ ላይ የተፈጸመ ሀጢአትን በአቡነ ጳውሎስ በማሳበብ ሊያጥብ ይፈልጋል!!!

    3. ጽሁፉ ትምክህተኝነት ያለበት ነው፡ ተመስገን ማስረጃ ባይጠቅስም አቡነ ጳውሎስ በ”ትግርኛ” ወንጌል ማስተማራቸውን ትልቅ ጉድለት አድርጎ ጽፎታል፡፡እንዴት ነው ወንጌል በትግረኛ አታስተምሩ የሚል ቀኖና አለ እንዴ!!ቅዳሴ በኦሮምኛ መተርጎሙን ሰሞኑን ሰምተን በምንደሰትበት ወቅት የትግረኛ የወንጌል ማስተማሪያ መሆን የሚያመው ጋዜጠኛ ማየት ትምክህተኝነት ከመባል በቀር ምን ይባላል!!በዚህ ላይ በተመስገን ብእር የሚቀጠቀጡት ሁሉም የአንድ ብሄር አባላት ናቸው፡፡በሀገራችን ጋዜጠኝነትም ምሁርነትም ዘረኝነትን(ትምክህተኝነትን) ቅቡል(justify) ማድረጊያ ከመሆን አልፈው ለሀቅኝነት መቆሙን ትተውታልና አይገርመኝም!!

    4. ለመደምደም ፈጥኑዋል፡ ተመስገን መንግስትን ለመወንጀል ብቻ በሚመስል መልኩ ስለሚጽፍ ግራቀኙን ለማየት አልታደለም፡፡ ለምሳሌ፡ወንበዴው መንግስት ነው ለማለት “…..የትኛውም አክራሪ ሀይል ከመዋቅር(ከመንግስት) አካል በርታ ሳይባልና ሽፋን ሳይሰጠው የሚንቀሳቀስ እንደሌለ አማኞቹ በገሀድ ይገልጻሉ….” የሚለውን የመንግስት አሳብ እንደ ትልቅ ማሳያ አድርጎ ያጮኸዋል፡፡በዚህም ማህበረ-ቅዱሳንን ጨምሮ የአክራሪነት ክስ የሚቀርብባቸውን አካላት ነጻ ለማውጣት ይታትራል፡፡መቼም ከስንት ብሄሮችና ሃይማኖቶች በተገነባ መንግስት ውስጥ የአንድ ወይም የሁለት ባለስልጣናት ለራሳቸው ሃይማኖት ድጋፍ መስጠት መገለጹ ጠቅላላውን የመንግስት አስተዳደር የአክራሪዎች ስብስብ ያሰኛል ማለት ተገቢ አይሆንም፡፡እነዲያውም ይችን የመንግስት ሀሳብ ቀደም ሲል የማ/ቅዱሳን ዋ/ጸሀፊ የነበረው ሙሉጌታ ሃ/ማርያም “አብዛኞቹ የማህበሩ አባላት የኢህአዴግ አባላት እና ደጋፊዎች ናቸው” ሲል ለእንቁ መጽሄት የሰጠውን ቃለምልልስ ተመስገን ቢያይ የመንግስትን “የአክራሪዎች የመዋቅር ሽፋን የማግኘት” ስጋትና መንግስት(ኢህአዴግ) በአብዛኛው አባላቱ ስላሉበት ማህበረ-ቅዱሳን ያለውን የትምክህት ሀይሎች መሸሸጊያነት መረጃ ባደነቀ ነበር!!!

    • ms November 16, 2013 at 8:49 am Reply

      TEGEHSA ተባረክ እኔ ሌላ መልስ መስጠት ኣያስፈልገኝም!

      • kk November 18, 2013 at 6:45 am

        @ms, have you read ‘tm’s’ response particularly addressing you above?

  6. Anonymous November 15, 2013 at 7:51 am Reply

    In the Name of the Father, the Son and Holy Sprit, One GOD Amen
    Although you have been feeding important information. You are trying to prove what His Excellency Ato Shifrawe said ” Promoting politics in name of religion”. We know those who were working hard for the heavenly Kingdom of God can be short circuited by Satan (emotion, sentiment) and end-up fighting for earthly kingdom. The Jews did not believe in our Lord and Savior Jesus Christ because He told them he will no return the Kingdom of Israel. Although you pretend to defend MK , you must be one of few ex-members of MK that joined the quest for earthly kingdom. Some religiously partisan government official use you and other sentimental website run by few individuals as the proof the necessity of closing MK and weaken Sunday schools. Hence, you and these officials work for some goal. The same agent of satan stir you emotion and make you blend information about EOTC with politics and true or fabricated sin of some father and then indicate this to those official. The goal of this agent of satan is prevent to the flow of the youth to serve GOD in the unrevised Apostolic Church.

    Please repent and stop blending religion with politics and posting true and fabricated sins of individual. Post only information that brings Unity and Institutional Change of EOTC!

    Amen

  7. kk November 18, 2013 at 6:34 am Reply

    ስለ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሁሉም ህትመቶች ላይ ሲጻፍ በፍጥነት ብታወጡልን ደስታየ ነው ፡፡

Leave a comment