የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የተቃወሙት ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቀረቡ

  • ‹‹ማንንም አሿሿሚ አይደለሁም፤ የሥልጣን ጥመኞችን አላገለግልም››Ab Hizkiel

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከሐላፊነት የመልቀቂያ ደብዳቤ ለዐቃቤ መንበሩ ማቅረባቸው ተሰማ፡፡ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ የወሰኑትና ከሐላፊነት የመልቀቂያ ደብዳቤ ያቀረቡት ከጥር 6 – 8 ቀን የቆየው የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንደተጠናቀቀ መኾኑ ተገልጧል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከሐላፊነታቸው እንዲለቁ ለውሳኔ ያበቋቸው ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እንዳሉ የዜናው ምንጮች አስረድተዋል፡፡ የመጀመሪያው÷ ቅዱስ ሲኖዶሱ በዐራተኛው ፓትርያሪክ ላይ ስላለው አቋም፣ ዕርቀ ሰላሙንና የፓትርያሪክ ምርጫውን አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት ያሳለፈው ባለሦሰት ነጥብ ውሳኔና ውሳኔውን ተከትሎ ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠበት መንገድ ነው፡፡

ውሳኔውን አስመልክቶ ዋና ጸሐፊው ያላቸው ልዩነት፣ ‹‹በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት አባቶች ጋራ የተጀመረው የዕርቅና የሰላም ሂደት የጊዜ ገደብ ተሰጥቶት፣ ፍጻሜውን አይተን በውጭ በስደት የሚገኙት አባቶች ወደ አገራቸው ተመልሰው ምርጫውን በሰላም እናካሂድ›› የሚል ነው፡፡ ይህ አቋም የዕርቀ ሰላም ልኡካኑ በተለይም ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ከእርሳቸውም ጋራ ብፁዕ አቡነ ሉቃስም በከፍተኛ ደረጃ የተሟገቱለት እንደነበር ነው የተገለጸው፡፡

በመጨረሻም ‹‹ጥሪ አድርገንና የጊዜ ገደብ ሰጥተን ምላሻቸውን እንጠባበቅ፤ አዎንታዊ መልስ ከተገኘ እሰየኹ፤ የሰላም ጉባኤው ተካሂዶ ዕርቁ ተፈጽሞ አብረን እንመርጣለን፤ ካልተገኘ ደግሞ በመልሱ ቅ/ሲኖዶስ ይነጋገርበት›› በሚል መንፈስ በረቂቅ የቀረበው መግለጫ እንዲታረም ስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢኾንም መግለጫው አድሮ ሲመጣ ከቀድሞው ይዘቱ ብዙ ሳይለወጥና እርማቱን ሳያካትት ነበር የቀረበው፡፡ አካሄዱ ክፉኛ ያስቆጣቸው ብፁዕ ዋና ጸሐፊው÷ ከስብሰባው መጠናቀቅ አንድ ቀን በፊት ስብሰባውን ትተው የወጡ ሲኾን መግለጫው በተሰጠበት ቀንም ‹‹አሁን ባለው የአሠራር ኹኔታ ለመቀጠል ያስቸግረኛል፤ ማንንም አሿሿሚ አይደለሁም፤ የሥልጣን ጥመኞችን አላገለግልም፤›› በማለት በአቋማቸው ከመጽናታቸውም በላይ ከዋና ጸሐፊነት ሓላፊነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸው ታውቋል፡፡

ሌላው ጋዜጠኞች የተጠሩበትና ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠበት መንገድ በሕገ ቤተ  ክርስቲያን ለብፁዕ ዋና ጸሐፊው ከተሰጠው ሥልጣንና ከተለመደው አሠራር መለየቱ ነው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 25 ንኡስ አንቀጽ 3 መሠረት÷ ቅ/ሲኖዶስ የሚሰጠውን ትእዛዝና ውሳኔ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትና ለሚመለከተው ሁሉ የማስተላለፍ ሥልጣንና ተግባር የብፁዕ ዋና ጸሐፊው ነው፡፡ የቅ/ሲኖዶሱን ማኅተምና ልዩ ልዩ ሰነዶች የሚይዙትም ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ናቸው፡፡ በተለመደው አሠራር መሠረት ደግሞ መግለጫ የሚያነቡት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ወይም ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ናቸው፡፡

በትላንትናው መግለጫ ላይ እንደታየው አንባቢው ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ ይህም ብፁዕነታቸው የመግለጫ አርቃቂ ኮሚቴው አባል ስለኾኑ ነው በሚል ቢገለጽም በሦስቱ አርቃቂ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ልዩነት እንደነበር (ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በአንድ ወገን ናቸው)፣ የመግለጫው የጽሑፍ ሥራ ከቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት እና አባላቱ ውጭ የኾኑ ግለሰቦች ጉልሕ ሚና የተጫወቱበት እንደ ኾነ የሚገልጹ መረጃዎች፣ ስሞችን በመጥቀስ ጭምር በመውጣት ላይ ናቸው፡፡

በቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ የፕሮቶኮል ደብዳቤ የወጣው መግለጫ ሌላው ቀርቶ ማኅተም እንኳ ሊኖረው ይገባ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ በሌላ በኩል ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲጠራ ትእዛዝ ያስተላለፉት ለዛሬ፣ ጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም 5፡00 ላይ እንደነበር ጥሪው የደረሳቸው ጋዜጠኞች የተናገሩ ሲኾን በእነብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የተላለፈ ነው በተባለ ትእዛዝ ግን ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠው ትላንት፣ ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም፣ በ9፡00 ነበር፡፡ ‹‹ነገሩ ቀላል መስሎ ቢታይም በአቡነ ጳውሎስ ጊዜ የነበረው የተደገመበት (እርሳቸውም የቅ/ሲኖዶስ ስብሰባ ሳያልቅ ለብቻቸው መግለጫ ለመስጠት ይሞክሩ ነበር) እና ጠቅላላ ሂደቱን ከወዲሁ ለመቆጣጠር የናረ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች መደራጀታቸውን ያሳያል፤›› ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

ሁለተኛው የብፁዕ ዋና ጸሐፊው ከሓላፊነታቸው የመልቀቂያ ምክንያት÷ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሚካሄድበት ወቅትና ከዚያ በፊት ባሉት ቀናት ብፁዕነታቸው ወይም ጽ/ቤቱ ሳያውቋቸው የሚወጡ ደብዳቤዎች መበራከታቸው ነው፡፡ ከደብዳቤዎቹ መካከል÷ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የጻፉት ደብዳቤ አንዱ ነው፡፡

በዚህ ደብዳቤ ዐቃቤ መንበሩ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ከፍተኛ ሓላፊዎች ሥራቸውን እንዳይሠሩ ከፍተኛ ዕንቅፋት እየፈጠሩባቸው በመኾኑ የሚኒስቴሩን እገዛ ጠይቀዋል፡፡ የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች እንደሚያስረዱት÷ ዐቃቤ መንበሩ በዚህ ደብዳቤ ከከሰሷቸው ውስጥ ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ይገኙበታል፡፡ የሁለቱ አባቶች ውዝግብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስብሰባዎች ላይ ጭምር እየተካረረ የመጣ ሲኾን በግልጽ የታወቀው ያለመግባባታቸው መንሥኤ÷ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነት ከተነሡ በኋላ በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ያለቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ዕውቅና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመንፈሳዊ ዘርፍ ም/ሥራ አስኪያጅ ኾነው መሾማቸው ነው፡፡

በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የሚመራው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ማኔጅመንት ኮሚቴ የንቡረ እዱ ሹመት አንድም፣ በቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ያልታየ፤ በሌላም በኩል ‹‹መንፈሳዊ ዘርፍ የሚባል መዋቅር የለንም›› በሚል ለቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ በጻፈው ደብዳቤ የዐቃቤ መንበሩን ርምጃ ተቃውሞታል፡፡ ንቡረ እዱ ለዕርቀ ሰላም ተልእኮ በአሜሪካ ሳሉ በሌለ መዋቅር የተሰጣቸው ይህ ሹመት ከዕርቀ ሰላሙና ከፓትርያሪክ ሹመቱ ጋራ ተያይዞ ‹‹የውስጥ ግዳጆችን ለማስፈጸም እንዲያመቻቸው ነው›› በሚል ሲነገር ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ንቡረ እዱ በአስተዳደር ሕንጻ ውስጥ ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጋራ ሳይኾን በጽርሐ መንበረ ፓትርያሪኩ ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያሪኩ ጋራ በተሰጣቸው ቢሮ እንደሚሠሩ ተገልጧል፡፡ ከብፁዕ ዋና ሥ/አስኪያጁ ጋራ የንቡረ እዱን ሹመት ከተቃወሙት የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት መካከል እንደ አቶ ተስፋዬ ውብሸት (ምክትል ሥራ አስኪያጅ) ያሉት በዐቃቤ መንበሩና በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ጥርስ ውስጥ መግባታቸውም ተነግሯል፡፡

በዐቃቤ መንበሩ ዙሪያ የተሰለፉ ግለሰቦችን በሕገ ወጥ መንገድ የማስቀጠሩንና እስከ መመሪያ ሓላፊነት ድረስ ሹመት የማሰጠቱን ትእዛዝ ብፁዕ ዋና ሥ/አስኪያጁ አለመቀበላቸውም ሌላው የውዝግቡ መንሥኤ ነው ተብሏል፡፡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ራሳቸው በርካታ ቀራቢዎቻቸውን በተለያዩ መምሪያዎች ውስጥ ቦታ በማስያዝ ቢተቹም በዐቃቤ መንበሩ ዙሪያ ካሉት ግለሰቦች ውስጥ እንደ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ሁሉ በወቅታዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ተደራጅተው ከሚፈጽሙት ተግባር ጋራ እንደማይደራረስ ነው የሚነገረው፡፡

ሌላው ብፁዕ ዋና ጸሐፊውን ያሳዘነው ተግባር÷ ዐቃቤ መንበሩ በቀጥታ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የጥበቃ አገልግሎት በመጻፍ ያስተላለፉት ትእዛዝ ነው፡፡ ይህ ትእዛዝ የነገረ መለኰት ምሩቃን ማኅበር ሥራ አመራር አባል የነበረውና ለዕርቀ ሰላሙ ሂደት መሳካት ሌት ተቀን በመሥራት ላይ የሚገኘው ዲ/ን ማንያዘዋል አበበ÷ ከጥር 3 ቀን ጀምሮ ላልታወቀ ጊዜ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ እንዳይገባ ማሳገዳቸው ነው፡፡ ይኸው ደብዳቤ በአድራሻ ለጥበቃ አገልግሎቱ ሲጻፍ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ይኹኑ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ እንኳ እንዲያውቁት አለመደረጉ ነው የተነገረው፡፡ ቁም ነገሩ ግን፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጠው ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ሰጥተው የሚቃተሉ ወገኖች በቀና አስተሳሰብና አሠራር ሳይኾን በባለጊዜዎች ተጽዕኖ በመደፈቅ ላይ እንዳሉ ዐይነተኛ ማሳያ መኾኑ ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ከዋና ጸሐፊነት የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን በጽሑፍ ለዐቃቤ መንበሩ ከማቅረባቸው በፊት በምልዐተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ‹‹እንደበቃቸው›› በቃል ማሳወቃቸው ተነግሯል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 24 ንኡስ አንቀጽ 4 መሠረት የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የአገልግሎት ዘመን ሦስት ዓመት ነው፡፡ በዚሁ ንኡስ አንቀጽ መሠረት አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘም ለአንድ የምርጫ ዘመን እንደገና ሊመረጥ ይችላል፡፡

5 thoughts on “የቅ/ሲኖዶሱን ውሳኔ የተቃወሙት ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አቀረቡ

  1. ምእመን January 19, 2013 at 6:39 am Reply

    ዕንቁ፡- በቤተክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ እያለ መሾም የለበትም የሚል ሕግ አለ ?
    ብጹዕ አቡነሕዝቅኤል ፡- ሕጉ አለ ፡፡ በደርግ አገዛዝ ዘመን አቡነ ቴዎፍሎስ እያሉ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ተሾመዋል፡፡ ሆኖም ፓትርያርክ በዚህ ዓለም እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም ነበር፡፡ ያኔ በሀገሪቷ ላይ በነበረው ችግር ተደርጓል፡፡ ብጹእ አቡነ መርቆርዮስ የእኛ የቤተክርስቲያን አባት ናቸው፡፡ ቤተክርስቲያን አስቀምጣቸዋለች ፤ በጊዜው ባለው ችግር “እኔ አሞኛል” የሚል ነገር ተነሳ፡፡ ታሪክ በመስማት እንጂ በእርግጥ እኔ በጊዜው የለሁም ፤ “ኃላፊነቱን ተቀበሉኝ ብለው ቅዱስ ሲኖዶስን አሳስበዋል” የሚል ነገር ነበር ፤ ይህ አግባብ አልነበረም፡፡
    አሳቸውም በወቅቱ ችግሩን ችለው ሀገራቸው ላይ መቀመጥ ነበረባቸው ፤ በዚያ ምክንያት ሌላ ፓትርያርክ ተሹሟል ፡፡ 20 ዓመት ተጉዘን እዚህ ደርሰናል ፡፡ ከ20 ዓመት በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ እያሉ ሰላም እንዲወርድ ተፈልጎ የእርቀ ሰላም ሂደቱን ጀምረን ነበር፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ እያሉ አንድ እናድርግ ሲባል እኛም ወዲያ ወዲህ ስንል በመሀል ቅዱስነታቸው አረፉ፡፡ ብጹዕ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሀገር ቤት መጥተው እዚህ ጠቅላይ ቤተክህነትም ሆነ የሚፈልጉት ገዳም አስፈላጊው ነገር እየተደረገላቸው እንዲቀመጡ ነበር እኛ ለእርቁ ሰው የላክነው፡፡ ይህ እርቀ ሰላም የተጀመረው ቅዱስ ፓትርያርኩ በህይወት ባሉበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡የተጀመረው ሂደት መቀጠል አለበት ብለን ነው ዛሬም ሰው የላክነው፡፡
    ዕንቁ፡- የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት እስከምን ድረስ እንዲጓዝ ነው የታቀደው ? አሁን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በሕይወት የሉም ፤ ፓትርያርክ እያለ ፓትርያርክ አይሾምም የሚለው ሕገ ቤተክርስቲያን እንዲከበር ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ቀደመ ፓትርያርክነታቸው እንዲመጡ በእናንተ በኩል ሃሳቡ አለ?
    ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡- እዚህ መጥተው ፓትርያርክ ይሁኑ ማለት አይቻልም፡፡ ታሪክ ይፋለሳል አምስተኛ ፓትርያርክ እያልን ኖረን ከ20 ዓመት በኋላ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም፡፡ ይህ አስቸጋሪ ስለሆነ ቀኖናውንም ታሪኩንም የሚጥስ ስለሆነ ነው እንጂ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ቦታቸው እንዳይመጡ የጠላ ማንም የለም፡፡ ሁሉም ሰላሙን ፈልጓል፡፡ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሃገር መጥተው በፈለጉበት ቦታ መቀመጥ ይችላሉ፡፡ ሰላሙ ተመስርቶ በውጭ የሚገኙ አባቶቻችን አዚህ መጥተው የመምረጥም የመመረጥም ዕድል ይኖራቸዋል፡፡

    ዕንቁ፡- በጥቅምቱ ሲኖዶስ ማጠቃለያ ላይ እርስዎ በሰጡት መግለጫ የፓትርያርክነት ጉዳይ አምስት ብሎ ወደ ስድስት እንጂ አራት የለም ብለዋል፡፡ ይህ መግለጫ ቀኖና ቤተክርስቲያንን የጠበቀ ነበር ? የእርቁ ሁኔታ መቀጠል እየተገባው ይህን መናገርዎ ሂደቱ ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ አይኖረውም ?

    ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡- በዚህም ተባለ በዚያ ችግሩን እኛ የፈጠርነው ሳይሆን ተፈጥሮ ያገኝነው ነው፡፡ የእኛም ድርሻ የማስተካከል ነው፡፡ ትኩረታችን በትክክለኛው መንገድ እንዲሄድ ማድረግ ነው፡፡
    ዕንቁ፡- ብጹእ አቡነ መርቆርዮስ እያሉ ሌላ ፓትርያርክ መሾሙ ቀኖናውን አያፋልስም?
    ብጹዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡- ጥለውት ሲሄዱ እኮ ነው አቡነ ጳውሎስ የተሾሙት ፡፡ ያን ጊዜ የነበረው ክፍተት የፈጠረው ነው፡፡
    ታድያ የቱ ነው የአቡነ ሕዝቅኤል አቋም?

  2. 0911124434 January 30, 2013 at 8:52 pm Reply

    ወገኖቼ አዲስ አማኝ ከጳጳ ይበልጣል እንደሚባለው በወቅቱ አልነበርኩም የሚሉት አቡነ ሕዝቅኤል እንኳን በሊቀጵጵስና በክርስትናስ ነበሩ ዎይ ከእሳቸውስ መልካም ነገር ይተበቃል ዎይ አባ ሕዝቅኤል ለመልካቸው በሚመጥን የተሰጣቸው ሀገረ ስብከት እያላቸው አፋቸው እንዲዘጉ በማሰብ አዲስ አህጉረ ስብከቶች ተፈጥረው በአዲስ አበባ ቢሰጣቸውም በአጠቃላይ በአድባራትና ገዳማቱ ያሉትን የተሸሉ የሥራ መደቦች ለሞስሊም መሬት የለውም ለሰማይ ምሶሶ የለውም ተብሎ ወገኖቼ ከነገስታቱ ጀምሮ ተገፉ ስለሆነ እነሱ መቀመት አለባቸው በማለት በዘረኝነት እያመሱት ይገኛሉ ዝረኛና ቸካኝ መሆነቸውም በአጭር ጊዜ አስመስክረዋል እነዚህ አይነት አባት የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊስ መሆን ነበረበት አዝነናል

Leave a comment