በጅማ ዩኒቨርስቲ የኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች መብት መረገጥ ተባብሷል፤ የትምህርትና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴሮች የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያውን ማስከበር ተስኗቸዋል

jimma University

ጅማ ዩኒቨርስቲ

 • በአለባበስ እና በአመጋገብ በክርስቲያንና በሙስሊም ተማሪዎች መካከል አድልዎ ይፈጸማል
 • በተማሪዎች ዲኑ ማንአለብኝነት ተማሪዎች የፍልሰታ ለማርያምን ጾም ለመጾም ተቸግረዋል
 • የጅማ የማኅበረ ቅዱሳን ማዕከል ምእመኑን በማስተባበር ለተማሪዎቹ ድጋፍ እያደረገ ነው
 • ቅ/ሲኖዶስ ሃይማኖታዊ መብታቸውን የሚያስከብር አቋም እንዲወስድ ተማሪዎቹ ጠይቀዋል
 • ‹‹ኦርቶዶክሳዊ ሥርዐተ እምነትን በማንአለብኝነት ለይቶ የመጋፋት አካሔዱ፣ አኹን በደረሰበት ደረጃ አሳሳቢ የሃይማኖታዊ ነፃነት መረገጥ እንጂ የመብል ጉዳይና የአንድ ዩኒቨርስቲ ችግር ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡›› /ተማሪዎቹ/

(ኢትዮ – ምኅዳር፤ ቅፅ ፪ ቁጥር ፷፤ ረቡዕ፣ ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)

Jimma University logoበጅማ ዩኒቨርስቲ የተለያዩ ካምፓሶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ተማሪዎች በሥርዐተ እምነታቸው የተደነገጉ የዐዋጅ አጽማዋትን በመጾም ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ለመወጣት መቸገራቸውንና የትምህርት ተቋማት የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያውን* በአድሏዊነት በሚያስፈጽሙ ሓላፊዎች ምክንያት በእምነት ነፃነታቸው ላይ የሚደርሰው መረገጥ ተባብሶ መቀጠሉን ለኢትዮ – ምኅዳር ገለጹ፡፡

በጅማ ዩኒቨርስቲ በዋናው ግቢ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲኹም በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ካምፓሶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ የክረምት፣ የፔዳጎጂና የሕክምና ሳይንስ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ለኢትዮ – ምኅዳር እንደተናገሩት÷ በየዓመቱ ከነሐሴ ፩ – ፲፮ ቀን በሚቆየው የፍልሰታ ለማርያም መታሰቢያ ጾም ‹‹የጾም ምግብ አይዘጋጅም›› በመባሉ በሥርዓተ እምነታቸው ላይ አድልዎና ጫና እየተደረገባቸው እንዳለ ገልጸዋል፡፡

የፍልሰታ ለማርያም ጾም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሰባት ዓመት ዕድሜ በላይ የሚገኙ ምእመናንዋ እንዲጾሟቸው ካዘዘቻቸው የሕግ/የዐዋጅ/ አጽዋም አንዱ እንደኾነ የሚጠቅሱት ተማሪዎቹ፣ መዋዕለ ጾሙ ከተጀመረበት ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ከምግብ ቤቱ የሚያገኙት አንድ ዳቦ ብቻ እንደኾነና እርሱም ለኹሉም ጿሚ ተማሪዎች ሳይዳረስ እንደሚያልቅ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመዋዕለ ጾሙ ተማሪው ወደ ካፊቴሪያው ገብቶ የሚቀርብለት ሥጋ በመኾኑ ሊመገበው አይችልም፤ ዳቦውም አይዳርስም፤ ቶሎ ያልቃል፤›› ብለዋል ተማሪዎቹ፡፡

ቀደም ሲል በአጽዋማት ወቅት የጿሚ ተማሪዎችን ዝርዝር ለተማሪዎች ዲኑ በማሳወቅ በብዛታቸው ልክ ምግቡ ተዘጋጅቶ ይስተናገዱ እንደነበር ተማሪዎቹ አውስተው፣ ጾመ ፍልሰታ ባለፈው ሳምንት ኃሙስ ከመግባቱ አንድ ሳምንት በፊትና ጾሙ በገባበት ዕለት እንደተለመደው ለዲኑ ቢሮ ብናሳውቅም፣ ዲኑ አቶ እውነቱ ኃይሉ፣ ‹‹በዚኽ ጉዳይ እኛ ጋራ እንዳትደርሱ፤ ማመቻቸት አይቻልም›› የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡ Continue reading

ልጆችም ወላጆችም የሚተባበሩበት የፍልሰታ ለማርያም መታሰቢያ ጾምና በዓል

(አለቃ አያሌው ታምሩ)

 • በኢትዮጵያ እመቤታችንን መውደድ በልማድ እንደ ተረት በማይታይ ዓይነት ኹኔታ ተስፋፍቶ የኖረ አይደለም፡፡ ወንድም ሴትም ቢኾኑ እንዳላቸው የእምነት መጠን በእመቤታችን ስም ጸሎት ጸልየው፣ ስእለት ተስለው፣ ምጽዋት አድርገው፣ ዝክርዋን ዘክረው፣ ስምዋን ጠርተው፣ በአማላጅነትዋ ተማፅነው ዐሳባቸው እየተፈጸመላቸው፣ የጎደለው እየሞላላቸው፣ የጠመመው እየተቃናላቸው፣ ድውያን ፈውስ በማግኘት፣ ሠራተኞች ለሥራቸው የተቃና መንገድ በማግኘት፣ መምህራን በሚያስተምሩበት፣ ቅዱሳን ገድላቸውን በሚፈጽሙበት ጊዜና ምክንያት ኹሉ የእመቤታችንን ረድኤት እያገኙ ስለሔዱና ዛሬም ያው ያልተቋረጠ ስለኾነ ነው፡፡
 • ከቀደሙ ሰዎች ታሪክ ከእስራኤል መሳፍንት አንዱ ለኾነው የዮፍታሔ ልጅ መታሰቢያ ልጆች ወይም ደናግል በየዓመቱ በዓል ሲያከብሩ እንደነበረ ተነግሯል፡፡ (መጽ. መሳ.፲፩፥፵፡፡) እንዲህ ከኾነ ዘንድ ኢትዮጵያውያት ቆነጃጅትና ሕፃናት፥ ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች የእናታችንን፥ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን መታሰቢያ በየዓመቱ ሲያከብሩ የበለጠ ነገር ፈጽመዋል ማለት ነው፡፡

  *                 *                 *

መሠረተ ቃል፡-

 • ‹‹ተንሥአ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፡፡›› ‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ
  ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት፡፡›› (መዝ.፻፴፩፥፰)
 • ‹‹ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይት ርግብየ ውስተ ጽላሎት ኰኵሕ ቅሩበ
  ጥቅም፡፡›› ‹‹አቅራቢያዬ መልካማ ርግቤ ተነሽ ነዪ በግንቡ አጠገብ ወዳለው ወደ ዋሻው
  ጥላ፡፡›› (መኃ.፪፥፲-፲፬)

ቅዱስ እግዚአብሔር ሰው ለመኾን፥ የሰው ልጅ ለመባል ባሰበው የመጀመሪያው የተስፋው መንገድ የምትገኘው፥ ለእናትነት የመረጣት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ኢትዮጵያ በእመቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያን ትሠራለች፤ ልብዋንም በረድኤትዋ ላይ አሳርፋ በቤተ ክርስቲያንዋ ውስጥ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት፥ ጸሎት፥ ምጽዋት፥ ስግደት ታቀርባለች፡፡ በእመቤታችን አማላጅነትም ትማልዳለች፡፡ እንዲኹም የማይጠፋ ስም ተሰጥቷታልና በመዝሙር ፵፬ ፥ ፲፪ – ፲፮ በተጻፈው መሠረት ወላጆች ከነልጆቻቸው ተሰብስበው የእመቤታችንን የልደትዋን፥ ጌታን ለመውለድ ብሥራት የመቀበልዋን፥ የመውለድዋን፥ የዕረፍትዋን፥ የትንሣኤዋን፥ የዕርገትዋን በዓል ያከብራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከፍ ብሎ የሚታየው በብዛት ልጆች ተሳትፎ የሚያደርጉበት የፍልሰታ ጾምና በዓል ነው፡፡ ፍልሰታ የሚለው ቃል የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን፣ ኋላም በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ቃል ነው፡፡

filseta lemariam

የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን በወለደችበት፣ ስብሐተ መላእክትን በሰማችበት፣ ባየችበት የልደት ወራት አካባቢ በ፷፬ኛ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ከዚኽ ዓለም በሞት ተለይታ ወደ ሰማይ ስትወጣ በሰማይም በምድርም ለሰውም ለመላእክትም ከልጅዋ፣ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰጣት ጸጋና ክብር ተገልጧል፡፡ ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በሰማይ በፍጹም ደስታ አስተርእዮ ኾኗል፡፡ በመጀመሪያ ዐብረዋት የኖሩት ልጆችዋ ቅዱሳን ሐዋርያት በሥጋ ያሉት ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰብስበው፣ ከዚኽ ዓለም የተለዩት በአካለ ነፍስ ተገኝተው የዕረፍቷን ጊዜ እየተጠባበቁ ሳሉ፤ እመቤታችን፤ ‹‹ማዕጠንት አምጡ፤ በጸሎትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥሩት፤›› አለቻቸው፡፡ እነርሱም ትእዛዟን በመፈጸም ላይ ሳሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ በክብር፥ በጌትነት ተገለጠ፡፡ እናቱንም፤ ‹‹የተወደድሽ እናቴ ሆይ! ዛሬ ድካምና ሕማም ወደሌለበት ወደ ዘለዓለም መንግሥት ላሳርግሽ መጥቻለኹ፤ ወደ እኔ ነዪ፤›› እያለ ሲያነጋግራት ቅድስት ነፍስዋ ከክቡር ሥጋዋ በልጅዋ ሥልጣን ተለየች፤ ልጅዋም በክብር ተቀበላት፡፡ በዚኽ ጊዜም ነቢዩ ዳዊት፤ ‹‹ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤›› እያለ ያመሰግናት ነበር፡፡ ቅዱሳን መላእክት፥ ነቢያት፥ ሐዋርያት፥ ጻድቃን፥ ሰማዕታት በዚያው ከበው ቆመው፤ ‹‹ጸጋን የተመላሽ ሆይ! እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነውና ደስ ይበልሽ፤›› እያሉ ያመሰግኗት ነበር፡፡ በዚኽ ዓይነት ጸጋና ክብር በልጇ ሥልጣን፥ በልጇ ቸርነት ወደ መንግሥተ ሰማያት አሳርገዋታል፤ ‹‹እቴ ሙሽራዬ ከሊባኖስ ከእኔ ጋራ ነዪ፤›› የሚለው ተፈጽሞላታል፡፡ ሥጋዋንም ቅዱሳን ሐዋርያት ለጊዜው ጌቴሴማኒ በተባለ ቦታ አሳርፈውታል፡፡ በሦስተኛው ቀን ግን መላእክት ከዚያ አፍልሰው በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኑረውታል፡፡ ከመቃብር እስከ ተነሣችበትና ፍጹም ዕርገት እስካገኘችበት እስከ ነሐሴ ፲፮ ቀን ለኹለት መቶ አምስት ቀኖች በዚያው ቆይቷል፡፡ በዕለተ ዕረፍቷ ብዙ ተኣምራት ተደርገዋል፡፡ ለድውያን የፈውስ ጸጋ ታድሏል÷ ስሟን ለሚጠሩ ኹሉ ፍጹም በረከት ተሰጥቷል፡፡ የፈውስ ጸጋ ከደረሳቸው አንዱ ታውፋንያ ወይም ሶፎንያስ የሚባለው አይሁዳዊ ነው፡፡

Continue reading

ከፍተኛ ምዝበራ የተፈጸመበት የድሬዳዋ ቅ/ገብርኤል ሕንፃ ሥራ ኦዲት ሪፖርት ይፋ ኾነ፤ የደብሩ አለቃ ከሪፖርቱ አስቀድሞ ያለሊቀ ጳጳሱ ስምምነት በፓትርያርኩ ትእዛዝ ተነሡ!

 • እስከ ልዩ ጽ/ቤት የተዘረጋው የአማሳኞች ሰንሰለት ለአለቃው መነሣት ተጠያቂ ኾኗል
 • ምእመናን፣ በተነሡት አለቃ ምትክ የሚደረግ ምደባን እንደማይቀበሉ አስጠንቅቀዋል
 • ፓትርያርኩ ለክብረ በዓል ወደ ቁሉቢ ሲያልፉ ለማነጋገር ዝግጅት እየተደረገ ነው
 • የኦዲት ሪፖርቱ የድሬዳዋ አገልጋዮች ና ምእመናን በአንድነት እንዲሰለፉ አድርጓል
 • ‹‹የአለቃው መነሣት ሙስናን ለሚዋጉ ሌሎች አስተዳዳሪዎች ዋስትና የሚያሳጣ ነው፡፡››
 • ‹‹ፓትርያርኩ በቋሚ ሲኖዶስ የተወሰነውን ስለማይቀበሉና መፍትሔ ማምጣት ስላልተቻለ ሕዝቡ ራሱ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲጠብቅ ብፁዓን አባቶች ነግረውናል፡፡››

/የተሟጋች ምእመናን ቡድን/

*            *           *

 • ከአምስት ሚልዮን በላይ ብር ከውል ውጭ መከፈሉ በኦዲት ምርመራው ተረጋግጧል
 • በ2.9 ሚልዮን ብር ለማገባደድ የታቀደው ኮንትራት ዋጋ ከ10 ሚልዮን በላይ ብር ደርሷል
 • የምእመናን የወርቅ ስጦታዎች በልክ ተሽጠው ገቢ ስለመኾናቸው ለማረጋገጥ አልተቻለም
 • የሕ/አሠሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ ገንዘብ ተቀባይም ወጪ ጠያቂና አጽዳቂም ኾነው ፈርመዋል
 • የሰብሳቢውን የሥልጣን ምንጭና ሕጋዊነት የሚገልጽ ሰነድ ወይም ቃለ ጉባኤ አልተገኘም
 • ውጭ ሔጃለኹ ያሉት ተቋራጩ አ/አ ተቀምጠው ውሏቸውን በጠቅ/ቤ/ክህነት አድርገዋል
 • ደብሩ÷ ኮሚቴውን፣ ተቋራጩንና የግንባታ ተቆጣጣሪውን በሕግ እጠይቃለኹ ብሏል

(ኢትዮ ምኅዳር፤ ቅጽ 02 ቁጥር 77፤ ረቡዕ፣ ሐምሌ 16 ቀን 2006 ዓ.ም.)

???????????????????????????????

 

በድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ከታቀደለት ጊዜ በላይ በመጓተቱ እያወዛገበ በሚገኘው የሳባ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ግንባታ፣ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው ለሕንፃ ሥራ ተቋራጩ በተለያየ መልክ የከፈለው ከአምስት ሚልዮን በላይ ብር ከውል ስምምነት ውጭ የተፈጸመ እንደኾነ በሕንፃ ሥራው ሒሳብ ላይ የተካሔደው የገለልተኛ ኦዲተሮች ምርመራ አረጋገጠ፡፡

Dire Dawa Saba Saint Gabriel Church Audit Report by Habtewold Menkir and Co. Authoried Auditor

በደብሩ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ የገቢና ወጪ መግለጫዎች ላይ ሀብተ ወልድ መንክርና ጓዶቹ በተሰኘ የተፈቀደለት ኦዲተር በተደረገ የሒሳብ ምርመራ÷ ኮሚቴው ሪል የሕንፃ ሥራ ለተሰኘ ተቋራጭ ለሕንፃ ግንባታ በሚል የፈጸማቸው ከፍተኛ ክፍያዎች፣ ኮሚቴው ከተቋራጩ ጋራ የገባውን የውስን ኮንትራት ውል ስምምነት በሚቃረንና በውሉ ለግንባታው መጠናቀቅ ከተያዘው ቀነ ገደብ ውጭ የተሻሻለ የማሟያ ስምምነት ከመፈራረም በፊት ያለአግባብ የተከናወኑ እንደኾኑ ከኦዲተሮቹ ሪፖርት ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በኦዲት ሪፖርቱ እንደሰፈረው፣ የቤተ ክርስቲያኑን ሕንፃ በብር 2‚984‚562.51 እና በ730 ቀናት ገንብቶ ለማስረከብ ኮሚቴውና ተቋራጩ መስከረም 19 ቀን 1998 ዓ.ም. በተስማሙበት የውስን ኮንትራት ውል መሠረት ምንም ዓይነት ቅድመ ክፍያ እንደማይጠየቅ ቢገለጽም ለኮንትራክተሩ ከውል ውጭ ቅድመ ክፍያ ሲፈጸምለት ቆይቷል፡፡

እስከ 2004 ዓ.ም. የካቲት መጨረሻ ድረስ ለኮንትራክተሩ በተለያየ መልክ የተከፈለው 5‚565‚470.76 ያኽል ገንዘብ፣ በውስን ውል(Fixed contract) ሕንፃውን ለመሥራት ከተስማማበት ዋጋ ውጭና በዚያው ዓመት የካቲት 28 ቀን የተሻሻለ የሟሟያ ስምምነት ከመፈራረም በፊት የተፈጸመ ክፍያ ነው ያለው ሪፖርቱ፣ ‹‹ይህም ክፍያ የተጨማሪ የማሟያ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ሊፈጸም አይገባም ነበር፤›› ብሏል፡፡

የስምምነት ውሉን ከመቃረን በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኮንስትራክሽን ሕጉን በሚፃረር አኳኋን ተፈጽሟል በተባለው ክፍያ እስከ የካቲት 28 ቀን 2004 ዓ.ም. ድረስ የግንባታ ወጪው ወደ 7‚784‚985.22 ከፍ ማለቱን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ ‹‹ይህ ከግምት ከገባ ኹለተኛ ተጫራች ያቀረበው ብር 3‚700‚770.15 ወይም ሦስተኛ ተጫራች ያስገባው ብር 4‚351‚881.05 ዋጋ በምናይበት ጊዜ ኹለተኛ ተጫራች ወይም ሦስተኛ ተጫራች ሊያሸንፉ የሚችሉበት ዕድሉ እንደነበረ›› ገልጧል፡፡ ይህም ለፕሮጀክቱ የጨረታ ወድድር በወጣበት ወቅት የሥራ ተቋራጩ ‹‹ከሌሎች የተሻለ ጥቅም አግኝቷል›› ሊያሰኝ እንደሚችል አመልክቷል፡፡ Continue reading

ቋሚ ሲኖዶስ: ፓትርያርኩ ከአማሳኞችና ከአፅራረ ሃይማኖት ባለሥልጣናት ጋራ ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው!

 • አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብስባ ለመጥራት ታቅዶ ነበር
 • በተሳሳተ አካሔዳቸው ከቀጠሉ ቋሚ ሲኖዶሱ አብሯቸው አይሠራም
 • በአ/አበባ የአድባራት አለቆች ዝውውር ስሕተት መሥራታቸውን አምነዋል
 • ‹‹የኔ ቃልና የነሱ ቃል በዓላማ አንድ ስለኾነ፣ የሚያመጡት ሐሳብ ስለሚመቸኝ ነው፡፡››

         /ፓትርያርኩ በሰብሳቢነት የሚመሩትንና አብረው የሚወስኑበትን የቋሚ ሲኖዶስ መመሪያዎች ከአማሳኞች ጋራ እየመከሩ ስለሚገለብጡበት አካሔድ በቋሚ ሲኖዶስ ለተጠየቁት የመለሱት/

/ምንጭ፡- ፋክት፤ ቅጽ ፪ ቁጥር ፶፭፤ ፳፻፮ ዓ.ም./

patriarchate officeበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግን የመተርጎምና የማስፈጸም መብት ያለው ቋሚ ሲኖዶስ÷ ውሳኔዬን አክብረው አላስከበሩልኝም፤ ጠብቀው አላስጠበቁኝም ላላቸው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተገለጸ፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ ፓትርያርኩን ያስጠነቀቀው፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ሳምንታዊ ስብሰባውን ባካሔደበት ወቅት ነው፡፡ የቤተ ክህነቱ የፋክት ምንጮች እንደተናገሩት፣ የማስጠንቀቂያው መንሥኤ÷ አቡነ ማትያስ ምክራቸውን ለሥልጣነ ፕትርክናቸው አይመጥኑም ከተባሉ አማሳኝ ግለሰቦች እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ ክብርና ነፃነት በመጋፋት ከሚወቀሱ አፅራረ ሃይማኖት አካላት ጋራ በማድረግ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔና ልዕልና የሚፃረር ተግባር በየጊዜው መፈጸማቸው የቅዱስ ሲኖዶሱን አባላት ክፉኛ በማሳሰቡ ነው፡፡

 • ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የኾነው ቋሚ ሲኖዶስ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እየተወሰኑ የሚተላለፉ መመሪያዎችን ተግባራዊነት እንዲከታተል ካለበት ሓላፊነትና አሠራር ጋራ የማይጣጣሙ የፓትርያርኩ የአፈጻጸም አካሔዶችና አቋሞች መበራከታቸው፤
 • ቋሚ ሲኖዶሱ ሳይወስንና የመንበረ ፓትርያርኩ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሳያውቀው የጽ/ቤት ሓላፊያቸውን አቶ ታምሩ አበበን ያለሞያቸው ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአካዳሚክ ምክትል ዲን አድርገው በማዘዋወር፣ በቦታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ነፃነት ከሚዳፈሩ ባለሥልጣናት ጋራ በሙሉ አቅማቸው በመሥራት የሚታወቁትን የአማሳኞች አለቃ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃን መተካታቸው
 • ከፍተኛ ገቢና የአገልግሎት አቅም ባላቸው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት የአማሳኞችን የምዝበራ ሰንሰለት እያጋለጡ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በመዋጋት፣ ካህኑንና ምእመኑን አንድ አድርጎ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቱ አጋር በመኾን የተመሰገኑ አለቆች፣ ፓትርያርኩ ከአማሳኞች ጋራ እየመከሩ በሚያስተላልፉት ቀጥተኛ ትእዛዝ ከሓላፊነታቸው መነሣታቸው
 • አገልጋዩ እና ምእመኑ በአንድነት የውጤታማና ምስጉን አስተዳዳሪዎችን ያለአግባብ ከሓላፊነት መነሣት በተመለከተ ያቀረባቸው ጥያቄዎች፣ በቋሚ ሲኖዶሱ መመሪያ መሠረት አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ ተገቢ ምላሽ ሳይሰጥባቸው የፓትርያርኩ የዝውውር ውሳኔ ተፈጻሚ መኾኑና የመሳሰሉት ጉዳዮች፤

የቋሚ ሲኖዶሱ አባላት ከፓትርያርኩ ጋራ በከፍተኛ ደረጃ የተጠያየቁባቸውና ፓትርያርኩን ያስጠነቀቁባቸው ዐበይት ነጥቦች እንደነበሩ ምንጮቹ አስታውቀዋል፡፡ Continue reading

የቅ/ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማስተርስ መርሐ ግብር የመጀመሪያዎቹን ደቀ መዛሙርት አስመረቀ

 • በ፲፱፻፹፯ ዓ.ም. ዳግመኛ ከተከፈተ ወዲህ የተመረቁት ደቀ መዛሙርት ብዛት 2175 ደርሷል
 • የተቋማዊ ነፃነት ዕጦትና የበጀት እጥረት ‹‹ጥናትና ምርምር ላይ እንዳላተኩር አድርጎኛል፡፡››
 • መሠረቱ የወጣው ሕንፃ ሥራ እንዲቆም በጀቱም እንዲመለስ የተላለፈው ትእዛዝ አወዛግቧል
 • ወደ ዩኒቪርስቲ ደረጃ የማሸጋገሩ ሒደት በግንባታ ላይ የሚገኘውን ሕንፃ መጠናቀቅ ይጠብቃል
 • ‹‹ከዛሬው ደስታችኹ የሚበልጥ ደስታ ከፊታችኹ ስለተዘጋጀ ደስታችኹ ዕጥፍ ድርብ ነው፡፡›› /ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ/

***

 • መስተጋድላን አኃውና አኃት ደቀ መዛሙርት በእጅግ ከፍተኛና ከፍተኛ ማዕርጎች ተመርቀዋል
 • የሴት ደቀ መዛሙርት ብዛት እና ውጤታማነት ‹‹አገልግሎቱን የተሟላ ያደርገዋል›› ተብሏል
 • ምሩቃኑ ነገ በጠቅ/ቤ/ክህነቱ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ የአገልግሎት ምደባ ዕጣ ያወጣሉ
 • በየገጠሩ ሊቃውንቱ እየተገፉ ያልተማሩት በንዋይ ብዛት የሚንደላቀቁበት ኹኔታ በቅኔዎች ተተችቷል
 • ‹‹ግእዝ የኛ ብቻ ስላልኾነ በተቋማት ኹሉ ይሰጥ፤ ዲፕሎማውም ወደ ዲግሪ ይደግ፡፡››/ምሩቃን/

***

graduates in M.TH and B.TH of HTTC of the class 2014

በቴዎሎጂ የመጀመሪያዎቹ የማስተርስ ዲግሪ ተመራቂ ደቀ መዛሙርት

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴዎሎጂ የማስተርስ ዲግሪ (Masters Degree in Systematic Theology) መርሐ ግብር ያሠለጠናቸውን 25 ደቀ መዛሙርት፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሔደው ሥነ ሥርዓት አስመረቀ፡፡

ኮሌጁ በ፳፻፭ ዓ.ም. የጀመረው የኹለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ቀዳሚ ዕጩ ደቀ መዛሙርትን ለምረቃ ማብቃቱ፣ የዘንድሮውን የምረቃ በዓል የተለየ እንደሚያደርገው አካዳሚክ ምክትል ዲኑ መ/ር ግርማ ባቱ ተናግረዋል፡፡

ምረቃው ‹‹የመጀመሪያና ታሪካዊ አጋጣሚ›› ከመኾኑ ባሻገር በተለያዩ መርሐ ግብሮች የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ደቀ መዛሙርትን ቀጣይ የትምህርት ዕድገት ለማረጋገጥ ኮሌጁ በማድረግ ላይ የሚገኘው ዝግጅት አካልም እንደኾነ አካዳሚክ ምክትል ዲኑ አስታውቀዋል፡፡

ከነባራዊ ኹኔታዎች ግምገማና ከሚጠበቅበት አንጻር፣ ኮሌጁን ብዙኃን ተስፋ ወደሚያደርጉት ቀጣይ ደረጃ ለማድረስ ስለሚካሔደው ዝግጅት በንግግራቸው የዘረዘሩት አካዳሚ ምክትል ዲኑ፣ ለአንድ ግዙፍ የትምህርት ተቋም የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ግብአቶችን ያሟላ ሕንፃ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኘው ሕንፃ÷ የመማሪያና የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍትና የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንደሚያካትትና የተቋሙ ቀጣይ ዕቅዶችም ከሕንፃው መጠናቀቅ ጋራ የተያያዘ እንደኾነ አካዳሚክ ምክትል ዲኑ አመልክተዋል፡፡ ግንባታው የሚከናወነው በአስቸጋሪ የበጀት እጥረት ውስጥ መኾኑን የጠቆሙት መ/ር ግርማ፣ ለፍጻሜውም የበጎ አድራጊ አካላትን እገዛ ጠይቀዋል፡፡

His Grace Abune Timothewos

ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ

ተቋማዊ ነፃነት በዲኑ ንግግር የተጠቆመ ሌላው ችግር ነው፡፡ ነፃነቱ ከምን አኳያ እንደኾነ የተብራራ ነገር ባይኖርም፣ ኮሌጁ ‹‹በሙሉ አቅሙ ጥናትና ምርምር ላይ እንዳያተኩር አድርጎታል፤›› ብለዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን ከአገሪቱ አንጋፋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አንዱ የኾነው ኮሌጁ በቴዎሎጂ የማስተርስ ዲግሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስመረቅ መብቃቱ ‹‹ትልቅ ስኬት ነው፤›› ያሉት የኮሌጁ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የዲኑን ጥቆማ በማጠናከር ባስተላለፉት መልእክት÷ የተቋማዊ ነፃነት ጥያቄው፣ የኮሌጁን ኹለ ገብ ሕንፃ በማስተዳደር የኪራይ ገቢውን ለራስ አገዝ ልማታዊ ፕሮግራሞች መጠቀምን በሚመለከት በኮሌጁ አስተዳደርና በጠቅ/ቤተ ክህነት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት የሚጠቅስ እንደኾነ በንግግራቸው አጠይቀዋል፡፡

ከኮሌጁ ቀጣይ ፕሮግራሞች መካከል በዋናነት የተቀመጠው፣ ‹‹ኮሌጁን ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት ነው፤›› ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ለዚኽም እንዲረዳ የረጅምና የአጭር ጊዜ ዕቅዶች ተነድፈው መተግበራቸውንና በመተግበር ላይ እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ብፁዕነታቸው ገለጻ፣ የኮሌጁ ኹለ ገብ ሕንፃ ግንባታ ከረጅም ጊዜ ዕቅዶቹ አንዱ ነው፡፡ ከሕንፃው የኪራይ አገልግሎት ከሚሰበሰበው ገቢም የራስ አገዝ ልማታዊ ፕሮግራሞችን በመንደፍ ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ለሚደረገው ሽግግር አቅም እየተፈጠረ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ Continue reading

ሰበር ዜና – የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የተፃረረው የፓትርያርኩ የአድባራት አለቆች ዝውውር ቁጣ ቀሰቀሰ፤ አዲሱ የደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል አስተዳዳሪ በሕዝቡ ተቃውሞ አቀባበል ሳይደረግላቸው ተመለሱ

 • ቋሚ ሲኖዶሱ የካህናቱንና ምእመናኑን አቤቱታ በመቀበልና የፓትርያርኩ ጥያቄ እንዲጣራ በማዘዝ፣ በሓላፊነታቸው እንዲቀጥሉ የወሰነላቸው ውጤታማው የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ፣ ውሳኔውን የሚፃረር የዝውውር ደብዳቤ በአባ ማትያስ ትእዛዝ ተጽፎባቸዋል፡፡
 • የፓትርያርኩን አግባብነት የሌለው ትእዛዝ በመቃወም የደብሩን ሀብት ከአማሳኞች ሰንሰለታዊ ምዝበራ ለመከላከል እንዲሁም የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ በማስከበር የደብሩን ሰላም ለማስጠበቅ መንፈሳዊነት በተሞላው አኳኋን የሚንቀሳቀሱ የአጥቢያው ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን በኃይል ለማስፈራራት ሙከራ እየተደረገ ስለመኾኑ ተመልክቷል፡፡
 • የአጥቢያው ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን፡- ውጤታማው አስተዳዳሪ አግባብነት በሌለው የፓትርያርኩ ትእዛዝ መነሣታቸውን በመቃወም ስላቀረቡት አቤቱታ፣ ለቦሌ ክ/ከተማ ካራማራ ንኡስ ፖሊስ ጣቢያ ተገኝተው ለክፍለ ከተማው አዛዥና ለጸጥታ ሰዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
 • ጥያቄአቸው÷ በሕጋዊ ውሳኔ ተመድበው በሰላማዊ መንገድ እየመሯቸው የሚገኙት ውጤታማው አስተዳዳሪ ስለተነሡበት የፓትርያርኩ ትእዛዝ በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ እንዲሰጣቸው መኾኑን አመልካቾቹ ገልጸዋል፡፡
 • ፀረ – የአማሳኞች ሰንሰለታዊ ምዝበራ የኾነውን ሰላማዊ እንቅስቃሴአቸውን ግለሰባዊና ፖለቲካዊ በማስመሰል ከመንግሥት ለማጋጨትና የኃይል ርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚደረግ ግፊት እንዳለ የጠቀሱት የደብሩ ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን÷ ‹‹ወደ ፖሊቲካ ይቀይሩብናል፤ እኛ ግን ፖሊቲከኞች አይደለንም›› ብለዋል፡፡
 • የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በሚፃረረው የፓትርያርኩ ትእዛዝ ከሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ተዛውረው በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን የተመደቡት አለቃ፣ ‹‹ወደ ደብሩ መሔድ የሚገባቸው ከሰበካ ጉባኤው አስተዳደር ጋራ አስቀድመው ከተነጋገሩና ከተግባቡ ብቻ እንደኾነ›› በትላንት ዕለት ከፖሊስ ተነግሯቸው እንደነበር ተገልጧል፡፡፡

*                   *                  *

 • የአጥቢያው ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን የደብሩን ሰላምና ሀብት ከአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለት ለመጠበቅና የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ ለማስከበር የሚያደርጉት የተቀናጀ ጥረት÷ ከቋሚ ሲኖዶሱ፣ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጰሳት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎችና ከሌሎችም አጥቢያዎች ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገለት ነው፡፡
 • ውጤታማና የብዙኃን ተቀባይነት ያላቸውን አለቆች፣ በጥቅመኝነት በታወረው የአማሳኞች ምክር ማዘዋወርን የመረጡት አባ ማትያስ፣ ቋሚ ሲኖዶሱ ያልተቀበለውን የዝውውር አቋማቸውን በባለሥልጣናት ጉልበት እና በአማሳኞች ተንኰል ለማስፈጸም መንቀሳቅሳቸውን ቀጥለዋል፡፡
 • ፓትርያርኩ÷ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርገው ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋራ እየተወያዩ ከመሥራት ይልቅ ‹‹አለቆችን በራሴ ፍላጎት ብቻ የማዘዋወር ሥልጣን ከሌለኝ ፓትርያርክነቴ ምንድን ነው?›› ሲሉ ለባለሥልጣናት አቤቱታ ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡
 • ለአቋማቸው ተቀባይነት አለማግኘትና ላስከተለው ከፍተኛ ተቃውሞ ማኅበረ ቅዱሳንን ተጠያቂ ለማድረግ በአማሳኞች አመቻችነት ከሚገናኟቸው ባለሥልጣናት ጋራ መክረዋል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ እና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊ ኾነው አላሠራ አሉኝ፤›› በሚል በማኅበሩ ላይ ጫናቸውን ለማጠናከርም እየተዘጋጁ ነው ተብሏል፡፡

*                   *                  *

St. Urael parish head row02በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ዛሬ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ከእሑድ ሰንበት ጸሎተ ቅዳሴ መጠናቀቅ በኋላ የደብሩ ካህናት፣ ሠራተኞች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና በርካታ ምእመናን ውጤታማው የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ ወደ ሌላ ደብር መዛወራቸውን በተመለከተ ተቃውሟቸውን ሰላማዊነት በተሞላው አኳኋን ሲያሰሙ ውለዋል፡፡

በተቃውሞው እንደተገለጸው÷ ከሐምሌ ወር ፳፻፫ ዓ.ም. ጀምሮ ካህናትና ምእመናን በአንድ ቃል በሚመሰክሩለት የተሟላ ክህነታዊ አገልግሎትና ብቃት ያለው አስተዳደራዊ ክህሎት ደብሩን የመሩትና በብዙ ሚልዮን የሚቆጠር ፋይናንሳዊ ሀብቱን ከአማሳኞች የምዝበራ ሰንሰለት ጠብቀው ከፍተኛ የልማት አቅም በመፍጠር መልአከ ብርሃናት ቀሲስ ክብሩ ገብረ ጻድቅ እስከ ዛሬ ከታዩት አለቆች ኹሉ ይልቅ ውጤታማ ኾነዋል፡፡

ውጤታማው አስተዳዳሪ፣ ከሰበካ ጉባኤው ጋራ በመተባበር÷ በስብከተ ወንጌል፣ በመልካም አስተዳደር እና በልማት መስኮች ያሳዩት የአገልግሎት ፍሬ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ጭምር መረጋገጡን በተቃውሞው ተመልክቷል፡፡

ውጤታማው አስተዳዳሪ ዓመት ሳይሞላቸው ለደብሩ በፈጠሩት ከፍተኛ አቅም የያዟቸውን ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ ዕድል ሊሰጣቸው የሚገባ እንጂ የአጥቢያውን ሀብት እንደለመዱት ለመቀራመት ባሰፈሰፉና በፓትርያርኩ ዙሪያ በተሰለፉ አማሳኞች ምክር ሊነሡ እንደማይገባ በብርቱ ተጠይቋል፡፡ Continue reading

ፓትርያርኩ ከጥቂት አማሳኞች ምክር ይልቅ የብዙኃኑን ካህናትና ምእመናን ድምፅ ሰምተው ተገቢ ምላሽ እንዲሰጡ ተጠየቁ፤ ‹‹አለዚያ ውሳኔዎ ደብሩ በአንድ ዓመት ያገኘውን ሰላም ያውከዋል፤ እኛም ልጅ እርስዎም አባት አይኾኑንም››

St.Urael church bld complex

የደብረ ጽጌ ቅ/ዑራኤል ቤተ ክርስቲያንና ኹለገብ ሕንፃ

 

ቋሚ ሲኖዶስ ዛሬ በጉዳዩ ላይ እንደሚወያይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ትላንት ጥዋት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ለተሰለፉ ከአንድ ሺሕ ለማያንሱ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት፣ የካህናት፣ የሰንበት ት/ቤትና የምእመናን ተወካዮች አስታውቀዋል፤ የዛሬው የቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ የካህናቱንና ምእመናኑን ቀጣይ ርምጃ ይወስናል፡፡

 

 

 • ፓትርያርኩ በጥቂት አማሳኞች ምክር ላይ የተመሠረተ የሙስና ክሣቸውን በማስረጃ አስደግፈው እንዲገልጹላቸው የተማፀኗቸውን፤ ለአቤቱታ በሕዝብ ማመላሻ አውቶቡሶች፣ ታክሲዎችና የቤት መኪናዎች ተጓጉዞ የመጣውን ምእመንም በአባታዊ መልእክት እንዲያሰናብቱ የጠየቋቸውን አምስት ተወካዮች በግቢ ጥበቃ፣ በፖሊስና በጸጥታ ኃይል ለማስወጣት ትእዛዝ ሰጥተው ነበር፡
 • ፓትርያርኩ የደብሩን አስተዳዳሪ በሙሰኛነት በመክሠሥ የጠቀሱት ምክንያት፣ ሀገረ ስብከቱ የአስተዳዳሪውን ውጤታማ አመራር በመመስከር ካቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ጋራ መለያየቱና መፃረሩ፣ ጉዳዩ በርግጥም ቅን መነሻ የሌለውና በጥቅም ትስስር ላይ የተመሠረተ መኾኑን አጋልጧል፡፡
 • በፓትርያርኩ እንደ ሙስና የተጠቀሱት የገንዘብ ወጪዎች÷ በሀገረ ስብከቱ የታዘዙ፣ የሰበካ ጉባኤው ውሳኔ ዐርፎባቸው በሕጋዊ ሰነዶች የተደገፉና ፓትርያርኩም በቀጥታ የሚያውቋቸው እንደኾኑ ተመልክቷል፤ የፓትርያርኩን የቢሮ ዕቃዎች ለማሟላት ከደብሩ ወጪ የተደረገው አራት መቶ ሺሕ ብር ይገኝበታል፡፡
 • ከደብሩ ከ22 ሚልዮን ብር በመመዝበር የተጠረጠሩ አማሳኞች ተጋልጠው ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረጋቸውን ያስታወሱት የምእመናን ተወካዮቹ፣ ክሡ በአሳማኝ ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ከኾነ አስተዳዳሪው ከሓላፊነታቸው መነሣት ብቻ ሳይኾን በሕግ የማይጠየቁበት ምክንያት እንደሌለ ገልጸዋል፤ አካሔዱም በደብሩ ልማደኛ አማሳኞችና በሙስና ከተጨማለቁ በኋላ ያለተጠያቂነት በሚዘዋወሩ ሌሎች አለቆች ላይም ተፈጻሚ እንዲኾን ጠይቀዋል፡፡
 • ‹‹አለቃው ቅዱስ ናቸው ብለን አይደለም፤ ሊያጠፉ ይችላሉ፤ እስከ አኹን ከተመደቡት ግን እንደ እርሳቸው ያሉ አላየንም፤ ቆጠራው በይፋ ነው፤ የገባና የወጣውን ማንም በይፋ ያውቀዋል፤ ገቢው ኻያ ሚልዮን ብር ደርሷል፤ አገልግሎቱ ሥርዓት ይዟል፤ አገልጋዩ ቦታውን አግኝቷል፤ ሰዓታት ቆመው፣ ኪዳን አድርሰው፣ ቀድሰውና አቊርበው፣ ካህኑን ከምእመኑ አስማምተው ሕዝቡን አንድ አድርገው የሚመሩ እንደ እርሳቸው አይተንም አናውቅ፡፡››
 • ‹‹እስከ አኹን ገንዘባችን ተዘርፏል፤ እስከ አኹን ዑራኤል ተሽጧል፤ ከአኹን በኋላ አንድ ሌባ እዚያች ደጅ አይደርሳትም፤ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያናችኹን አጥራችኹ ጠብቁ፡፡›› /የአካባቢውን ወጣቶች ያበረታቱ የአጥቢያው ተሰላፊ እናቶች/
Follow

Get every new post delivered to your Inbox.

Join 10,928 other followers