ቤተ ክርስቲያን የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎቿን ለማልማት ዕቅድ መንደፏን አስታወቀች

  • በአ/አበባ ሀ/ስብከት በስሟ የሚገኙ 38 ይዞታዎችን ያቀፈ ዕቅድ ነው፤
  • የሌሎች 40 ማክበሪያዎችን ይዞታ ለማረጋገጥ ምላሽ እየጠበቀች ነው፤
  • የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ባለቤትነቷን የሚያረጋግጥ ካርታ ጠይቃለች
  • ከዕሴቷ ጋራ የማይቃረኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር ዐቅዳለች፡፡

***

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ጃንሜዳን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችን ለማልማት ዕቅድ የነደፈች ሲኾን፣ የጃንሜዳ ባለቤትነቷን የሚያረጋግጥ  ካርታ እንዲሰጣት ጠይቃለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የካርታ እና የይዞታ ጉዳይን የሚከታተለው እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ የሚመራው ኮሚቴ፣ ሰሞኑን  ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋራ ባደረገው ውይይት፣ ቤተ ክርስቲያን በስሟ የሚገኙ 38 የባሕረ ጥምቀት ቦታዎችን በተለያየ መልኩ የማልማት ዕቅድ እንዳላት ማስታወቁን፣ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የመረጃ ክፍል ሓላፊ ላዕከ ሰላም ግርማ ተክሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያዎች፣ በመንግሥትም በግል ባለሀብቶችም እየተቀነሱ በመወሰድ ላይ እንዳሉና ይኸውም ቦታዎቹ፣ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ለጥምቀት በዓል ማክበሪያነት አገልግለው ከዚያ በኋላ ሳይሠራባቸው መክረማቸውን በመመልከት እንደኾነ የሚጠቅሱት ላዕከ ሰላም ግርማ፣ ይህ ኹኔታ ያሳሰባት ቤተ ክርስቲያን፣ ቦታዎቹን የማልማት  ዕቅድ መንደፏን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት 78 ጠቅላላ የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያዎች ውስጥ፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በተረከበችባቸው 38ቱ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ላይ፣ ከእምነቱ ዕሴት ጋራ የማይቃረኑ የማኅበራዊ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር መታቀዱን ነው ላዕከ ሰላም ግርማ ያስረዱት፡፡ በተቀሩትም ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደተገኘባቸው ወደ ልማት እንዲገቡ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል፡፡

በቦታዎቹ ላይ ሊተገበሩ ከታቀዱት የማኅበራዊ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል፥ ቤተ መጻሕፍት፣ የመናፈሻ ውስጥ ክፍት የማንበቢያ ቦታዎች፣ ከሥርዓተ እምነቱ ጋራ የማይቃረኑ የመዝናኛ እና የመናፈሻ አገልግሎት መስጫዎች እና አረንጓዴ ልማት የማከናወን ዕቅዶች እንደሚገኙበት ሓላፊው አብራርተዋል፡፡

የቦታዎቹ ሃይማኖታዊ ክብር ተጠብቆ ማኅበራዊ ግልጋሎትን በሰፊው እንዲሰጡ ዕቅድ መነደፉን፣ ይህም፣ ከአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ ጋራ የተስማማ የአረጋውያን፣ የወጣቶች እና የልዩ ልዩብረተሰብ ክፍሎች የመንፈስ ማደሻ ቦታዎች እንዲኾኑ ያደርጋል፤ በዚኽም ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን ለማስገኘት ምቹ ኹኔታ ይፈጥራል፤ የቦታዎቹንም ቅርስነት ጠብቆ ለማቆየት ያስችላል፤ ያሉት ላዕከ ሰላም ግርማ፣ በዚኽ ረገድ ከውጭ አገር ተመሳሳይ የዐደባባይ የሃይማኖት በዓላት ማክበሪያ ሥፍራዎች አጠባበቅ ልምድ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

በአኹኑ ወቅት በስፖርት ኮሚሽን ባለቤትነት ሥር የሚገኘውና በዓለ ጥምቀት በብሔራዊ ደረጃ የሚከበርበት ታሪካዊው የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት፣ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስ ኾኖ ሲመዘገብ፣ በዋናነት የተጠቀሰ የበዓሉ ማክበሪያ ቦታ እንደመኾኑ፣ ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነቷን የሚያረጋግጥ ካርታ እንዲሰጣት ጥያቄ አቅርባ ምላሽ እየጠበቀች እንደምትገኝ ጠቁመዋል፤ ምላሹ እንደተገኘም፣ ቦታውን በተለያየ መልኩ ለማልማት ቤተ ክርስቲያን ዕቅድ መንደፏን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡

የጃንሜዳ ባለቤትነት ለቤተ ክርስቲያን ቢደረግም፣ ወትሮ የነበረውን የስፖርት  ማዘውተሪያነት ከሌሎች የማኅበራዊ ልማት ሥራዎች ጋራ አቀናጅቶ እንዲሰጥ ይደረጋል፤ ተብሏል፡፡ (አዲስ አድማስ፤ ጥር ፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም.) 

በሌላ በኩል፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 78 የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያዎች ውስጥ 40ዎቹ፥ ለአረንጓዴ ልማት(ግሪን ኤሪያ) በሚል በተያዙ፣ የስፖርት ኮሚሽን የይዞታ ካርታ ባወጣባቸው፣ በግለሰብ አርሶ አደሮች ይዞታዎች፣ በዐደባባዮች መሀል ላይ እና በጋዝ ማደያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ ከእኒህም ውስጥ፣ የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያነታቸው  በሕጋዊ ካርታ እንዲረጋገጥ ላለፉት 14 ዓመታት ሲጠይቁ ቢቆዩም፣ ምላሽ ያልተሰጣቸው አድባራት እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ፣ ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብር እና መብት አስጠባቂ ኅብረት፣ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ፣ ከምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና በምክትል ከንቲባ ማዕርግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣን ጥራር ዓባይ ጋራ ተወያይቷል፡፡

የኅብረቱ ተወካዮች፣ ችግሩንና መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ አማራጮችን በዝርዝር ያስረዱ ሲኾን፣ ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል የተባሉ መመሪያዎችንም አንሥተዋል፡፡ ምክትል ከንቲባዋም፣ በተጠቀሱት የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች የሚገኙ አድባራት፣ ለአኹኑ በዓሉን የሚያከብሩበት መንገድ በጊዜያዊነት እንዲመቻችና ከበዓሉ በኋላ በኹለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ከሚመለከታቸው ባለሞያዎች ጋራ ጉዳዩን መርምረው ኹነኛ እልባት እንደሚሰጡ ለተወካዮቹ አስታውቀዋል፡፡ በመኾኑም፣ የዘንድሮውን በዓለ ጥምቀት ከሌሎች አድባራት ጋራ ተደርበው ለማክበር የሚችሉበት ኹኔታ፣ ከየአድባራቱ ሓላፊዎች ጋራ በመመካከር መመቻቸቱ ተገልጿል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: