ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገብርኤል ዐረፉ

• “የማውቀውን እናገራለኹበሚል ርእስ የሰዱት ግለ ታሪካቸው ለስርጭት ተዘጋጅቷል

• በነገረ መለኰት የማስተርስ እና የፒኤችዲ ዲግሪዎች የሞስኮ እና የፕሪስተን ምሩቅ ነበሩ፤

ሥርዓተ ቀብራቸው፣ ነገ እሑድ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል

***

የሲዳማ ጌዲዮ እና ቡርጂ ዞኖች አህጉረ ስብከትን በሊቀ ጳጳስነት ያገለገሉት ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገብርኤል ዓረፉ፡፡

ብፁዕነታቸው፣ ባለፈው ጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ፣ ከእርግና እና ሕመም ጋራ በተያያዘ ከሓላፊነታቸው ተገልለው ረዳት እንዲመድብላቸው መወሰኑ የሚታወስ ሲኾን፣ ዛሬ ቀትር ገደማ በመንበረ ፓትርያርኩ መኖሪያቸው በተወለዱ በ80 ዓመት ዕድሜአቸው ዓርፈዋል፡፡

የብፁዕነታቸው የሽኝት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት በቋሚ ሲኖዶስ የሚወሰን ሲኾን፣ ነገ እሑድ ሰንበት፣ ኅዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቅዳሴ ውጪ፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተጠቁሟል፡፡

ከካህን አባታቸው ከመምህር ገብረ ሕይወት እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ብርነሽ፣ በወሎ ክፍለ ሀገር በዋግ አውራጃ በ1933 ዓ.ም. የተወለዱት ብፁዕነታቸው፣ የወሎ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ይሥሓቅ ማዕርገ ዲቁናን፤ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከቆሞስ ሊቀ ምርፋቅ ኤርሚያስ ሥርዓተ ምንኵስናን በ1958 ዓ.ም.፤ ሥልጣነ ቅስናን ከወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በ1959 ዓ.ም. ተቀብለዋል፡፡

የቅኔንና የአገባብን ይትበሃል በሚገባ አጠናቀው በመምህርነት የተመረቁት፣ የአቋቋም እና የትርጓሜ መጻሕፍት ዐዋቂው ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፣ በ1962 ዓ.ም. ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ተልከው ከሌኒን ግራድ መንፈሳዊ ኮሌጅ የማስተር ኦቭ ዲቪኒቲ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ውጤት አግኝተዋል፡፡

የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በዚኹ መንፈሳዊ ኮሌጅ ቀጥለውና በሚገባ ፈጽመው በትምህርተ ሥጋዌ(ክሪስቶሎጂ) ዶክትሬታቸውን ተቀብለዋል፡፡ ወደ ሰሜን አሜሪካ ዘልቀውም፣ ከፕሪስተን ዩኒቨርሲቲ የማስተር ኦቭ ቴዎሎጂ ዲግሪ በመጨመር የነገረ መለኰት ዕውቀታቸውን በከፍተኛ ደረጃ አጠናክረዋል፡፡ የዶክትሬት ሥራቸው፥ ሞስኮ እና ኒውዮርክ በሚገኙት የዩኔስኮ የትምህርት ኮሚሽኖች ተመርምሮ ጸድቆላቸዋል፡፡

ትምህርተ ሃይማኖት ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 እንዲሁም ክብረ ቅዱሳን ከተሰኙት መጻሕፍት በተጨማሪ፣ በጋዜጠኞቹ መ/ር ጌታቸው በቀለ እና መ/ር ተስፋዬ ሽብሩ አማካይነት ለረጅም ጊዜ ሲሰንዱ የቆዩት ግለ ታሪካቸው፣ የማውቀውን እናገራለኹ በሚል ርእስ ተዘጋጅቶ እና የኅትመት ሒደቱ ተጠናቅቆ ለሥርጭት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

በአገልግሎት ረገድም፣ በዐዲስ አበባ የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሰባኬ ወንጌል እና የእሑድ ት/ቤት መምህር ኾነው ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል እና በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ት/ቤት፣ ለኮርሰኛ ካህናት በክረምት ወራት ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ካቴድራል፣ የሠርክ ጉባኤን በቀዳሚነት ወጥነው አስፋፍተዋል፡፡

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ሓላፊ ኾነው ተመድበው፣ በልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት የካህናት ማሠልጠኛዎች እንዲከፈቱ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ኾነው በመሾም፣ በልዩ ልዩ ገዳማት የልማት ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የመንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ መጋቤ ካህናት ኾነው ተሹመው ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡

ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል፣ በፊት ስማቸው ዶ/ር አባ ኢያሱ(ጴጥሮስ) ገብሬ ይባሉ የነበረ ሲኾን፤ ጥር 4 ቀን 1972 ዓ.ም. በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ከተሾሙት ሦስት ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ ነበሩ፡፡ በሢመተ ጵጵስናው፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ኤጲስ ቆጶስ በመኾን ነበር ሓዋርያዊ አገልግሎታቸውን የጀመሩት፡፡ በኋላም በኤርትራ፣ በድሬዳዋ፣ በደቡብ ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም፣ በሰሜን አሜሪካ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቀጥለው በመጨረሻም፣ የሲዳማ ቡርጂ እና ጌዲዮ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾን አባታዊ ተልዕኳቸውን በትጋት ፈጽመው በዛሬው ዕለት ከዚኽ ዓለም ድካም ዓርፈዋል፡፡

የብፁዕ አባታችን የድካማቸው በረከት ይድረሰን፡፡

One thought on “ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገብርኤል ዐረፉ

  1. Tesfaw Teshome December 6, 2020 at 6:36 pm Reply

    በረከታቸው ይደርብን :: ተተኪ አባት አያሳጣን

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: