ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅነት እና ዋና ጸሐፊነት የውድድር ማስታወቂያ ወጣ

  • በተለይ በሥራ አመራር ወይም በሰው ሀብት አስተዳደርየመጀመሪያ ዲግሪዎችን ይጠይቃል፤
  • በአስተዳደር እና በፋይናንስ የሥራ መስኮች ቢያንስ የ5 ዓመታት የሥራ ልምድ ያስፈልጋል፤
  • ለዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚወዳደሩ፥የአመራር ሐሳባቸውን በጽሑፍ መግለጽ ይጠበቅባቸዋል፤

***

  • የሃይማኖት ሕጸጽ የሌለባቸው፣ ጎጠኝነትን የሚጠየፉና በሙስና የማይጠረጠሩ ይወዳደሩ
  • አመልካቾች እስከ ኅዳር 21 ቀን ድረስ በቢሮ ቁጥር 303 ማስረጃቸውን ማቅረብ አለባቸው፤
  • ብቁ አገልጋይ በመሾም የሥራውን መንገድ አስተካክሎ ለመጀመር የወጣ ማስታወቂያ ነው

***

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደ ሌሎቹ አህጉረ ስብከት ኹሉ ራሱን ችሎ በሊቀ ጳጳስ እንዲመራ በቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑን ተከትሎ፣ ለጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ዋና ጸሐፊ በውድድር ለመመደብ ሀገረ ስብከቱ ማስታወቂያ አወጣ፡፡

የውድድሩ ዓላማ፣ ለቦታው የሚመጥን ብቁ አገልጋይ በማግኘት እና በመሾም የሥራውን መንገድ አስተካክሎ ለመጀመር እንዲቻል መኾኑን በማስታወቂያው ያስገነዘበው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፣ መስፈርቶቹን የሚያሟሉ አመልካቾች በውድድሩ እንዲሳተፉ አስታውቋል፡፡

በትምህርት ዝግጅት ረገድ አመልካቾች፣ ከአብነት ትምህርቶች ቢያንስ በአንዱ ምስክር ያላቸው፣ በነገረ መለኰት እና በዘመናዊው የማኅበራዊ ሳይንስ መስክ በተለይም በአስተዳደር፣ በሥራ አመራር ወይም በሰው ሀብት አመራር የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖራቸው እንደሚገባ በማስታወቂያው ተገልጿል፡፡ የሥራ ልምድን በተመለከተ፣ በአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት በአስተዳደር እና በፋይናንስ መስኮች ለአምስት ዓመት እና ከዚያ በላይ መሥራትን እንደሚጠይቅ ተመልክቷል፡፡

ለዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚወዳደሩ አመልካቾች፣ ሀገረ ስብከቱን እንደምን ለመምራት እንደሚፈልጉ ከሦስት ገጽ ባላነሰ እና ባልበለጠ ጽሑፍ ዐሳባቸውን ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲኾን፣ ለሚመደቡበት ሓላፊነት በሚፈለገው ኹኔታ በራሳቸው ፕሮጀክት ቀርጸው የማቅረብ እንዲሁም የግጭት አፈታት ስልትን በመጠቀም ችግሮችን ፈትቶ የማስተካከል ችሎታ እና ልምድ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡

ሥልጣነ ክህነት ያላቸው እና በክህነታዊ አገልግሎትም(በቅዳሴ፣ በማሕሌት፣ በሰዓታት እና በስብከተ ወንጌል) በበቂ ኹኔታ ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሃይማኖት ሕጸጽ የሌለባቸው፣ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባራቸው፥ ጎሠኝነትንና ጎጠኝነትን የሚጠየፉ፣ በሙስና የማይጠረጠሩ፣ በአድመኝነትና በአሳዳሚነት የማይታወቁ፣ በወንጀል ጉዳይ ተከሠው በፍርድ ቤት ያልተወሰነባቸው መኾን ይኖርባቸዋል፡፡

የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያሟሉ አመልካቾች፣ ከዛሬ ኅዳር 16 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማስረጃዎቻቸውን፣ በቢሮ ቁጥር 303 በአካል በመቅረብ እንዲያመለክቱ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 53 ንኡስ አንቀጽ 8 መሠረት፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ በትምህርት ችሎታው እና በሥራ ልምዱ ብቁ የኾነ ሰው መርጠው ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በማቅረብ እንዲሾም እንደሚያደርጉ የተደነገገ ሲኾን፣ ዕጩዎችን የመምረጫ መሳፍርትም በዚኹ ድንጋጌ ከፊደል ተ.ቁ(ሀ) እስከ (መ) በዝርዝር ሰፍረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን አጠቃላይ የአሠራር ሥርዓት ገምግሞ በማስተካከል ላይ የሚገኘው የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ አስተዳደር፣ የጽ/ቤቱን ጊዜ አላግባብ የሚሻማውንና ለብልሽት የዳረገውን የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ዐዲስ የሥራ ቅጥር፣ ዕድገት፣ ዝውውር ፈላጊዎች እና የደመወዝ ጭማሬ ጥያቄ ዎችን ጨምሮ ላልተወሰነ ጊዜ እንደማያስተናግድ ቀደም ሲል አስታውቋል፡፡

በምትኩ፣ የጽ/ቤቱን አመራር ከወዲሁ አስተካክሎ ተፈላጊውን ተቋማዊ ማሻሻያ ለማምጣት፣ ለከፍተኛ ምደባዎች(ሹመቶች) መስፈርት አዘጋጅቶ በዚኽ መልኩ የውድድር ማስታወቂያ በማውጣት የጀመረው ግልጽ እና ለተጠያቂነት የሚያመች አካሔድ፣ በሌሎችም አሠራሮች ሊበረታታ እና ሊጠናከር የሚገባው ነው፡፡ በመኾኑም፣ በሞያቸው አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚፈቅዱ እና የሚችሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ኹሉ በተግባር በመሳተፍ ሊደግፏቸው እና ሊያግዟቸው ይገባል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: