ባሕታዊ ዘበኅድአት ቀናዒ በእንተ ሥርዐት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልስ: ዜና ሕይወት እና ሥራዎች

/የዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት/

~~~~~~~

ሠናየ ገድለ ተጋደልኩ ብድርየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ ዐቀብኩ = ጽኑ ገድልን ተጋደልኹ፤ ሩጫዬንም ጨረስኹ፤ ሃይማኖቴንም ጠበቅኹ።

(፪ኛጢሞ. ፱፥፮)

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልስ: የዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ – ከ፲፱፻፴ ዓ.ም. እስከ ፳፻፲፪ ዓ.ም.

ልደት እና ዕድገት

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ከአባታቸው ከቀኝ አዝማች ከበደ መሸሻ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ እታገኘኹ ዘለለው፣ ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፲፱፻፴ ዓ.ም. በጥንቱ አጠራር በበጌምድር እና ስሜን ጠቅላይ ግዛት በጋይንት አውራጃ ስማዳ ወረዳ ተወለዱ። ብፁዕነታቸው የልጅነት ዕድሜያቸውን ያሳለፉት፥ ለወላጆቻቸው በመታዘዝ፤ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም፣ ፊደል ቆጥረው ከንባብ ጀምረው ዳዊት፣ ጸዋትወ ዜማ እየተማሩ ነበር።

ትምህርት እና አገልግሎት

ከልጅነታቸው ጀምሮ ካህን ኾኖ መኖርን ይመኙ ስለነበር፣ ግብረ ዲቁናን አጠናቀው ክህነተ ዲቁናን፣ የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዘንድ በ፲፱፻፵፬ ዓ.ም. ተቀበሉ፤ በዲቁና እያገለገሉም ቅዳሴ ዜማ እና ቅኔ ተማሩ።

በመቀጠልም፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በተመሠረተው በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም በ፲፱፻፶፩ ዓ.ም. በመግባት፣ ቅኔ ከነአገባቡ ተምረዋል። በመጽሐፈ መነኰሳት እንደታዘዘው፣ በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. በተግባር ቤት ለኹለት ዓመት በአመክሮ ረድዕ በመኾን ካገለገሉ በኋላ፣ ማዕርገ ምንኵስናንና ማዕረገ ቅስናን ከመጀመሪያው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ እጅ በደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ክብረ በዓል ተቀበሉ። በተጨማሪም በዚኹ ገዳም፥ ዜማ ከነባህሉ፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳትንና መጽሐፈ መነኰሳትን ትርጓሜ ተምረዋል።

ብፁዕነታቸው በነበራቸው የዕውቀት ጥማት፣ የቅዳሴ ዜማ ሞያቸውን የበለጠ በማሻሻል ለማስመስከር በነበራቸው ፍላጎት ከገዳሙ ፈቃድ ተሰጥቷቸው፣ ወደ ታላቁ ደብረ ዓባይ አቡነ ሳሙኤል ገዳም ሔደው የቅዳሴ ዜማ ትምህርት በሚገባ አጠናቀዋል፡፡ ከመምህራቸው የኋላእሸት መንገሻ፣ ታኅሣሥ ፫ ቀን ፲፱፻፶፯ ዓ.ም. የመምህርነት ምስክርነት ልብን ከሚመስጥ የአባትነት ምርቃት እና ጸሎት ጋራ ተሰጣቸው። ለጥቂት ወራት በዚያው በደብረ ዓባይ ገዳም በመምህርነት አገልግለዋል። በመቀጠልም፣  ወደ ደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም በመመለስ ከስመ ጥሩው መምህር ልዑል ዘንድ የቅዳሴ መምህር ምክትል ኾነው ያስተምሩ ነበር።

በዚኹ ገዳም ለቅዱስ ተልዕኮ እየተፋጠኑ በማገልገል ላይ ሳሉ ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው፣ በደገኛው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ፈቃድ እና ትእዛዝ፣ በቀዳሲነት እና የቅዳሴ መምህር ኾነው አገልግሎት ሰጥተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ መጋቢት ፯ ቀን ፲፱፻፷፭ ዓ.ም. በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ታላቁ የዴር ሡልጣን ገዳማችን አገልግሎት እንዲሰጡ፣ በግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ እና በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ፈቃድ እና ትእዛዝ፣ ከኹለት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አባቶች ጋራ ተላኩ። የገዳሙ ዋና ጸሐፊ፣ ተቆጣጣሪ፣ ሕፃናትንና ወጣቶችን አስተማሪ እንዲሁም፣ ገዳሙን ለተሳላሚዎች እና ጎብኝዎች በማስጎብኘት፤ ፩ኛ)ዕብራይስጥ፣ ፪ኛ)እንግሊዘኛ፣ ፫ኛ)ፈረንሳይኛ፣ ፬ኛ)ጀርመንኛ፣ ፭ኛ)ዐረብኛ ቋንቋዎች ተሰጥኦ ስለነበራቸው አስተርጓሚ በመኾን ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል። በደብረ ሥልጣን ገዳም ያሳዩት በነበረው ትጋት፣ አበምኔት ኾነው ገዳሙን በሓላፊነት እንዲያስተዳድሩ፣ ጥር ፳፯ ቀን ፲፱፻፷፯ ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ሊቀ ጳጳስ ደብዳቤ ተመድበዋል። 

በዚኹ የገዳሙ ሓላፊነት ላይ እያሉ በትርፍ ጊዜያቸው፣ ቋንቋ እና ዘመናዊ ትምህርት ይከታተሉም ነበር። ይህንኑ የመማር ፍላጎታቸውንና ጥረታቸውን በመገንዘብ በ፲፱፻፷፰ ዓ.ም. የነፃ ትምህርት (ስኮሊርሽፕ) በቤተ ክርስቲያን በመገኘቱ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ፊርማ ወደ ምዕራብ አውሮፓ ተላኩ። 

በምዕራብ አውሮፓ-አየርላንድ የሞራል ቴዎሎጂ፥ የቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ የዓለም ታሪክ እና የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን ተምረው ዲግሪ ካገኙ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ገዳም የተመለሱት ብፁዕነታቸው፣ የዴር ሡልጣን ገዳም ዋና ጸሐፊ እና መምህር በመኾን ለ፲፬ ዓመታት ያህል በቀናነት እና በትጋት የተሰጣቸውን ተልዕኮ የተወጡ ታላቅ አባት ናቸው።

ከዐሥራ ሰባት ዓመታት የውጭ ዓለም ቆይታ በኋላ ጥቅምት ፳፱ ቀን ፲፱፻፹፩ ዓ.ም. ከኢየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ ተጠርተው በመመለስ በነበራቸው የአስተዳደር ችሎታ እና አስተዋይነት፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ልዩ ጸሐፊ ኾነው አገልግለዋል።

ሢመተ ጵጵስና እና ኖላዊነት-በስደት

በፊት ስማቸው መጋቤ ኅሩያን አባ ኃይለ ኢየሱስ ከበደ ይባሉ የነበረ ሲኾን፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ፣ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ ጥቅምት ፲፰ ቀን ፲፱፻፹፫ ዓ.ም. በዕለተ እሑድ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎሬዎስ ተብለው የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ከሌሎች አምስት ኤጲስ ቆጶሳት ጋራ ተሹመዋል። 

ብፁዕነታቸው በዚኹ አገልግሎት ላይ እያሉ በመጣው የመንግሥት ለውጥ፣ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው የፖሊቲካ ኃይል፣ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ቀጥታ ጣልቃ በመግባት፣ በሕጋዊነት እየመሩ እና እያገለገሉ የነበሩት ፓትርያርክ በግፍ ከመንበራቸው ተገፍተው እንዲባረሩ አድርጓል። ብፁዕነታቸውም፣ የጣልቃ ገብነት ድርጊቱ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ እና አግባብ እንዳልኾነ በመቃወማቸው፣ በጊዜውም የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ በመኾናቸው፣ ለህልውናቸው ፈታኝ የኾነ ከፍተኛ ፖሊቲካዊ ጫና ስለደረሰባቸው፣ ከሚወዷት አገራቸው ሳይወዱ በግድ ወጥተው፣ በ፲፱፻፹፬ ዓ.ም. ወርኀ ሚያዝያ የጸሎተ ኀሙስ ዕለት በስደት ወደ እንግሊዝ አገር ገቡ። 

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ በሎንዶን ከተማ ስደተኞችን ትረዳ፣ ታስተምር በነበረችው ርእሰ አድባራት ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመገኘት በመባረክ፣ በማስተማር፣ በጥዑም ድምፃቸው በመቀደስ እና ቡራኬ በመስጠት አገልግሎታቸውን ከአባ አረጋዊ(በኋላ አቡነ ዮሐንስ) እና ሌሎች ካህናት ጋራ በመኾን በየዕለተ ሰንበት አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። ርዕሰ አድባራት ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም የራሷ ቋሚ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ስላልነበራት፣ የብፁዕነታቸው መምጣት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት መልካም ዕድልን ፈጠረ። ቤተ ክርስቲያን ከነበረችበት ጠባብ ክፍል ወደ ተሻለ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን አዛውረው እና ቅዳሴ ቤቱን ፈጽመው ባርከው በማስገባት አገልግሎቷ የተሟላ እንዲኾን አድርገዋል። 

የአገር ቤቱ የፖለቲካ ሙቀት መጨመር፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር ማስከተሉን የተረዱት ብፁዕነታቸው፥ “አመጣጤ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ምእመናንን ለመከፋፈል አይደለ፤ ኹሉንም ነገር ጊዜው ሲርስ እግዚአብሔር ይፈታዋል፤” በማለት በዓታቸውን ዘግተው በጸሎት መኖርን ተያያዙት፡፡ ኾኖም በቅርበት፣ የብፁዕነቸውን ቡራኬ የሚፈልጉ፣ አበክረው አገልግሎት እንዲሰጧቸው በመጠየቃቸው፣ በወርኃ መጋቢት ፲፱፻፹፮ ዓ.ም. የስደተኛው መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን አቋቁመው የቤተ ክርስቲያኑን ኪራይ በጋራ ከምእመናን ጋራ እየከፈሉ፤ ቅዳሴ በመቀደስ፣ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በመፈጸም፣ ወንጌልን በማስተማር፣ ጥምቀተ ክርስትና፣ ሥርዐተ ጋብቻን በመፈጸም ሕሙማንንና ያዘኑትን በማጽናናት አባታዊ ተግባራቸውን ፈጽመዋል።

ብፁዕነታቸው፣ በአሜሪካ ልዩ ልዩ ግዛቶች ሰፊ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሲሰጡ ኖረዋል፤ በተለይም፣ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል፣ የቅዳሴ አገልግሎት በመስጠት እና ልጆችን ለዲቁና በማስተማር ጭምር አገልግሎት ሰጥተዋል፤ እንዲሁም በውጭ በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በመዘዋወር አዲስ አብያተ ክርስቲያን በመባረክ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ብፁዕነታቸው፣ የቤተ ክርስቲያናቸው ህልውና በጽኑ ያሳስባቸው ነበር። ከምንም በላይ እጅግ ጉዳት የደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናትን ለመርዳት ወደ ኋላ የማይሉ አባት ነበሩ። በዚኽም መሠረት፣ በአገር ቤት ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያን የፈጸሟቸው ተግባራት፦

፩ኛ)በአገራችን ተከሥቶ በነበረው ድርቅ በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ለአራት አህጉረ ስብከት፣ ምእመናንን በማስተባበር የርዳታ ገንዘብ ልከዋል።

፪ኛ)ከ፳፻፬ እስከ ፳፻፮ ዓ.ም. ለጣና ገዳም ማንእንዳባ መድኃኔዓለም ቤተ መቅደስ ሙሉ ጥገና እንዲደረግ ገንዘብ በመላክ አሳድሰዋል።

፫ኛ)ከ፳፻፬ እስከ ፳፻፮ ዓ.ም. በስማዳ ወረዳ ቋጢጥ ማኅደረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ገንዘብ በመላክ ሙሉ በሙሉ አዲስ ሕንፃ አሳንፀዋል።

፬ኛ)መጠነኛ ጥገና ያስፈልጋቸው የነበሩ የቋራ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ለዳባት ጽዮን እና ለቢቸመር መዴኃኔዓለም አብያተ ክርስቲያናት ርዳታ ሰጥተዋል።

ብፁዕነታቸው በኖሩበት በምዕራቡ ዓለም ለ፳፱ ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ባለማቋረጥ በማገልገል፣ ጸንተው በመጸለይ እና በማስተማር፣ “የሎንዶን ባሕታዊ” ኾነው አሠረ ምንኵስናቸውን ጠብቀው የኖሩ ናቸው። በጊዜው በቀኖና ጥሰት ምክንያት የተፈጠረው የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አስተዳደር፣ ወደ አንድነቱ እንዲመለስ የዘወትር ጸሎታቸው ነበር። በሚኖሩበት ሎንዶን፣ የምዕመናኑን ሥነ ልቡና ጠንቅቀው በመገምገም የበለጠ ክፍፍል እንዳይፈጠር ኹኔታዎችን በጥንቃቄ የሚያዩ፤ አንድ ቀን ኹሉም ወደ ሌቡናው ሲመለስ በእግዚአብሔር ኃይል ይስተካከላል ብለው ተስፋን ሰንቀው የኖሩ አባት ናቸው።

ሐዋርያዊ አገልግሎት በሲኖዶሳዊ አንድነት

ይህ በእንዲህ እንዲለ፣ ጊዜው ደርሶ አዲስ ተስፋ ብቅ አለ፡፡ በኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ መንግሥት መምጣቱ፣ በተለይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ ይኾን ዘንድ፥ “ግንቡን እናፍርስ፤ ድልድዩን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል፣ ሐምሌ ፳፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ከአነጋገሩ በኋላ ብፁዕነታቸው ከሌሎች ብፁዓን አባቶች ጋራ በመኾን ወደ አገር ቤት በመግባት ታሪካዊው ዕርቀ ሰላም ተፈጸመ። 

ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ በመኾኑ፣ ብፁዕነታቸው፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾን፣ ጥቅምት ፳ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. ተመደቡ። ብፁዕነታቸው፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንደተመለሱ የተለመደ ተግባራቸውን በዐዲሱ ሓላፊነታቸው በማጠናከር ሀገረ ስብከታቸውን ለማደራጀት ጊዜ አላጠፉም፤ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የተከበረ እና አገልግሎቱ የተሟላ ኾኖ ባለማየታቸው፣ በቅድሚያ ሀገረ ስብከቱን ፈቃደኛ ለኾኑ ካህናት የሥራ ሓላፊነት በማከፋፈል፣ ተዘዋውረው በመጎብኘት፣ ያሉባቸውን ችግሮች እና ተግዳሮቶች በጥንቃቄ ማጥናት እና መመሪያ መስጠት ጀመሩ።

በአንዳንዶች ዘንድ፣ የብፁዕነታቸው ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ማስከበራቸው በበጎ አልታየም። ብፁዕነታቸው ግን፣ ይህን በሆደ ሰፊነት እና በአርቆ አስተዋይነት ማሳለፋቸው የሚደንቅ ነው። አባታዊ ምክራቸው፣ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዋ ይከበር በማለታቸው፣ ከአላዋቂዎች ዘንድ ነቀፌታ ቢደርስባቸው እንኳን በጽናት ታግሠው የሚኖሩ፤ የታዘዙትን የሚፈጽሙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ነበሩ። ችግር ባለባቸው አብያተ ክርስቲያናት እየተገኙ፣ ከምዕመናን ጋራ በሚያደርጉት ስብሰባ፥ ሐሳብ በነፃነት እንዲንሸራሸር ለኹሉም ዕድል የሚሰጡ፣ በተለይ ሴት እኅቶቻችን ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚያቀርቡት ሐሳብ ሊደመጡ ይገባል የሚሉና ሚዛናዊ ዲኝነት የሚሰጡ፣ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እና በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ላይ የማይደራደሩ፣ ጽኑ አቋም እና ጠንካራ ሰብእና የነበራቸው አባት ነበሩ።

ብፁዕነታቸው በመጨረሻ፣ ከምእመናን ጋር ባደረጉት አንድ ታላቅ ጉባኤ እንዲህ ብለው ነበር፦

“የቤተ ክርስቲያን ባለቤቷ፣ እርሱ ራሱ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እኛ ደግሞ አገልጋዮች ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሰማይም በምድርም የተሠራች ነች። እኛ ግን እናልፋለን፤ ስለዚህ የኹሉ ማሠሪያ በኾነው ሰላም እና ፍቅር ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ይኖርብናል።”

ብፁዕነታቸው ይመሩት በነበረው ሀገረ ስብከት፣ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ቋሚ ጽ/ቤት መገንባት፣ ለኹሉም ምዕመናን የመረጃ ማዕከል እንዲሁም ለአገልግሎት የሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት እና አገልጋዮች ማረፊያ ጭምር የማደራጀት ታላቅ እና ሰፊ ዕቅድ ነበራቸው። ኾኖም በአገልግሎት ላይ እያሉ፣ ቀደም ሲል በነበረባቸው ሕመም ምክንያት፣ በልዊሽሃም ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. ዕለተ እሑድ በሎንዶን ከተማ ዐርፈዋል። 

ምንጊዜም ቢኾን፣ ጻድቃን ካለፉ በኋላ ስለ ጽድቃቸው ይነገራል፤ እንደሚባለው ኹሉ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም በሕይወት ዘመናቸው፥ ለራሴ ይድላኝ፣ መጓጓዣ አቅርቡልኝ፣ ደመወዝ ቁርጡልኝ የማይሉ፣ አጀብ ይብዛልኝ፣ እዩኝ እዩኝን የማይወዱ፣ ለንዋይ የማይጨነቁ፣ ሰውን በእኩል ዓይን የሚመለከቱ፣ በመጠን መኖርን እንጂ ያልተገባ ነገርንና ቅንጡነትን የሚጸየፉ፤ ይልቁንም ብፁዕነታቸው፥ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይከበር፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይጠበቅ እያሉ መዋዕለ ዘመናቸውን በማይዋዥቅ መንፈሳዊነት የፈጸሙ ደግ እና ቀናዒ የቤተ ክርስቲያን አባት ነበሩ።

የብፁዕነታቸው በረከት ይደርብን፡፡

ነፍሳቸውን ከቅዱሳን ጋራ ይደምርልን፤ አሜን፡፡

Leave a comment