የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ ሥርዐተ ቀብር: ነገ ረፋድ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ይፈጸማል

  • ሥርዓተ ቀብሩ ለወራት የዘገየው፥ ወረርሺኙ ባስከተለው እግዳት የተነሣ ኹኔታዎች እስኪመቻቹ ድረስ ነው፤
  • መንሥኤ ኅልፈታቸው በኮቪድ-19 እንዳልኾነ፣ የሆስፒታል ማረጋገጫ ለቅዱስ ሲኖዶስ እና ለመንግሥት ቀርቧል
  • በምዕራቡ ዓለም አሠረ ምንኵስናቸውን ጠብቀው እና “የሎንዶን ባሕታዊ” ኾነው ለ29 ዓመታት በጽናት ያገለገሉ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ነበሩ፤”/ሀገረ ስብከቱ/

***

ከኹለት ወራት በፊት በሎንዶን ከተማ ያረፉት የዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ ሥርዐተ ቀብር፣ ነገ ቅዳሜ፣ ግንቦት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ገዳም ይፈጸማል፡፡

ሥርዐተ ቀብራቸውን በተመለከተ፣ ቋሚ ሲኖዶስ ዛሬ ባካሔደው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ ኹለት ብፁዓን አባቶችን የመደበ ሲኾን፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በጥቂት የሰው ኃይል እንዲፈጸም መመሪያ ሰጥቷል፤ የሚያስፈልገው ወጪም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እንዲሸፈን አዟል፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ በጉዳዩ ላይ በተወያየበት ወቅት፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ለማስፈጸም ከተቋቋመው የብሔራዊ ግብረ ኃይል አካላት(የጤና ሚኒስቴር፣ ሰላም ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት) ጋራ ምክክር ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡ የብፁዕነታቸውን ሞተ ዕረፍት አስመልክቶ ለተነሣው ጥያቄ፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ ባለፈው ሚያዝያ 29 ቀን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በላከው የሕክምና ማስረጃ ላይ የተመረኮዘ ገለጻ ተደርጓል፡፡

ብፁዕነታቸው በሕክምና ሲረዱ ከነበረበት የሎንዶኑ ሎዊሽሃም ሆስፒታል በተገኘው ማስረጃ፣ ለኅልፈት ያደረሳቸው፥ የቆየባቸው የስኳር ሕመም እና የልብ እክል እንዲሁም በመጨረሻ ያጋጠማቸው ኒሞኒያ እንጂ፣ ከኮሮና ቫይረስ ኹኔታ ጋራ ተያያዥ እንዳልኾነ ዝርዝር ማብራሪያ ቀርቦ ተሰምቷል፡፡ ሥርዐተ ቀብራቸውም፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ድንጋጌዎች እንዲሁም የኮቪድ-19 ቅድመ መከላከል ተግባራትን ጠብቆ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲፈጸም መታዘዙ ተመልክቷል፡፡

በዚኽም መሠረት በተላለፈው ውሳኔ፣ ከወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት መካከል የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል እና የደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኝበት የሰሜን ምዕራብ ሸዋ-ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ በጠቅላላው ከዐሥር ከማይበልጡ ወዳጆች እና የቅርብ ቤተ ሰዎች ጋራ በሥፍራው ተገኝተው፣ ነገ ቅዳሜ ረፋድ ከቅዳሴ ውጭ፣ ሥርዐተ ቀብራቸውን ያስፈጽማሉ፡፡ የአበውን ሥርዐት፣ ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ እና የወረርሺኙ የጥንቃቄ ተግባራት ጋራ በማገናዘብ እንዲያስፈጽሙ መታዘዛቸው ተገልጿል፡፡

ትላንት ማምሻውን ቦሌ አየር ማረፊያ የደረሰውንና ዛሬ እስከ ሠርክ በካርጎ ተርሚናሉ የቆየውን የብፁዕነታቸውን አስከሬን፣ ቀን 11፡30 ገደማ መረከባቸውንና ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት ሰዓትም ሥርዐተ ቀብራቸው ወደሚፈጸምበት ደብረ ሊባኖስ ገዳም በማምራት ላይ እንደኾኑ፣ ጉዳዩን በመከታተል ላይ ከሚገኙ የቅርብ ቤተ ሰዎች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በተወለዱ በ82 ዓመታቸው መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በሎንዶን ከተማ ያረፉት አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ ጥቅምት 18 ቀን 1983 ዓ.ም. በአራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አንብሮተ እድ፣ የልዩ ጽ/ቤት ኤጲስ ቆጶስነት ተሹመው አገልግለዋል፡፡ የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ቅዱስ ፓትርያርኩ በተደረገባቸው ፖሊቲካዊ ግፊት ከመንበራቸው ሲሰደዱ፣ ብፁዕነታቸውም ለህልውናቸው ፈታኝ ኹኔታ ስላጋጠማቸው፣ በሚያዝያ ወር 1984 ዓ.ም. በስደት ወደ እንግሊዝ መግባታቸውን፣ ሀገረ ስብከቱ ለሥርዐተ ቀብሩ ያዘጋጀው ዜና ሕይወታቸው ያስረዳል፡፡

ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲኖዶሳዊ ዕርቀ ሰላም መፈጸሙን ተከትሎ፣ ብፁዕነታቸው፥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾን፣ ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. መሾማቸውን አውስቷል። ጊዜ ሳያጠፉ ሀገረ ስብከቱን በፈቃደኛ ካህናት በማደራጀት፣ አብያተ ክርስቲያን በሕጉ መሠረት አገልግሎታቸው የተሟላ እንዲኾን አባታዊ ጥረት ማድረጋቸውን አስፍሯል፡፡ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ ላይ የነበራቸውን ጽኑ አቋም እና ጠንካራ ሰብእና በልዩነት ጠቅሷል። “የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዋ ይከበር በማለታቸው ከአላዋቂዎች ዘንድ ነቀፌታ ቢደርስባቸው እንኳን፣ በጽናት ታግሠው የሚኖሩ፣ የታዘዙትን የሚፈጽሙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አባት ነበሩ፤” በማለት ቀናዒነታቸውን አዘክሯል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ፣ ለሀገረ ስብከቱ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ቋሚ ጽ/ቤት የመገንባት፣ ለኹሉም ምእመናን የመረጃ ማዕከል እንዲሁም፣ ለአገልግሎት የሚመጡ ሊቃነ ጳጳሳት እና አገልጋዮች ማረፊያ የማደራጀት ታላቅ እና ሰፊ ዕቅድ እንደነበራቸው ጠቅሷል፡፡ ኾኖም፣ ቀደም ሲል በነበረባቸው ሕመም ምክንያት፣ በልዊሽሃም ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ እሑድ መጋቢት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በሎንዶን ከተማ ማረፋቸውን አስታውቋል፡፡

በአጠቃላይ ብፁዕነታቸው፣ በኖሩበት በምዕራቡ ዓለም፣ ለ29 ዓመታት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ባለማቋረጥ በማገልገል፣ ጸንተው በመጸለይ እና በማስተማር፣ “የሎንዶን ባሕታዊ” ኾነው አሠረ ምንኵስናቸውን ጠብቀው ኖረዋል፤ በማለት ሐዋርያዊ ትጋታቸውን በስፋት አትቷል፡፡ የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊን ዜና ሕይወት ሙሉ ይዘት በቀጣይ ጡመራ እናቀርባለን፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: