ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ የብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተመደቡ

  • የሌሎች አምስት የጠቅላይ ጽ/ቤት መምሪያዎች ዋና ሓላፊዎች ዝውውር ተደረገ፤
  • ውጤታማዋ ወ/ሮ ጽጌሬዳ ዓለሙ፣ ወደ በጀት እና ሒሳብ ዋና ሓላፊነት ተመለሱ
  • የሊቃውንት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ መጋቤ ብሉይ ዕዝራ ለገሠ፣ ዋና ሓላፊ ኾኑ፤

***

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ የአምስት መምሪያዎች እና ድርጅቶች ዋና ሓላፊዎች ዝውውር እና ሽግሽግ ያደረገ ሲኾን፣ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ ከሰበካ ጉባኤ ማዳራጃ መምሪያ ወደ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ተዛውረው በዋና ሥራ አስኪያጅነት ተመደቡ፡፡

በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቅራቢነት እና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ የተመደቡት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ ከሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም. አንሥቶ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያን በዋና ሓላፊነት ሲመሩ ቆይተዋል፡፡

lique-maemeran-fantahun-muche (1)

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ

ማደራጃ መምሪያውን፣ “በመልካም ሥነ ምግባር እና በጥሩ ኹኔታ በመምራት” የሥራ ሓላፊነታቸውን እንደተወጡ በምደባ ደብዳቤው ተገልጿል፤ “ለሌሎች ሓላፊዎችም አርኣያ የኾነውን ቅንነታቸውንና የሥራ ትጋታቸውን ከግምት በማስገባት”፣ የብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው እንዲሠሩ መመደባቸውን አስታውቋል፡፡

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁንና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ባልደረቦቻቸው፣ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደርያ ደንብ/ቃለ ዐዋዲ/ ግንዛቤ እንዲጎለብትና ምእመናን የድርሻቸውን እንዲወጡ በየሀገረ ስብከቱ ሰፊ እና ተከታታይ ስምሪቶችን አካሒደዋል፡፡ የምእመናንና የገንዘብ መሰብሰቢያ ቅጾች በአግባቡ እና በጥራት እንዲሞሉ በማድረግ፣ ከመላው አህጉረ ስብከት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚላከው ዓመታዊ የፐርሰንት መዋጮ፣ በእጅግ ከፍተኛ ጭማሬ አሳድገዋል፤ በሐምሌ ወር 2003 ዓ.ም. ከነበረበት 19 ሚሊዮን ብር፣ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም. ወደተመዘገበው 337 ሚሊዮን ብር ነው የተመነደገው፡፡

በየዓመቱ ጥቅምት ወር በሚካሔደው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አጠቃላይ ስብሰባ፣ የውጭ አህጉረ ስብከት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር፣ የፐርሰንት መዋጮም እንዲጀምሩ አበረታታዋል፡፡ በአሰልቺነቱ የሚታወቀው የአጠቃላይ ጉባኤው የስብሰባ ሥነ ሥርዓት፣ አልፎ አልፎም ቢኾን፣ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋራ በተያያዘ ለታየበት አበረታች ውጥን የሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሚና ተጠቃሽ ነው፡፡

የቃለ ዐዋዲው ደንብ በ2009 ዓ.ም. ለአራተኛ ጊዜ ተሻሽሎ እንዲጸድቅና ለየአህጉረ ስብከቱ እንዲሠራጭ ከማድረጋቸውም በላይ፥ በአፋን ኦሮሞ(ግእዝ እና ላቲን ፊደል)፣ በትግርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ እና በባለሞያዎች ተተችቶ፣ ለኅትመት ዝግጁ እንዲኾን አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም፣ የአኃዛዊ መረጃ ክፍሉን እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ድረስ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በማጠናከር፣ መረጃዎችን ለመለዋወጥ እና ወቅቱን የዋጀ ሥራ ለመሥራት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቀዋል፡፡ የመምሪያውን ወጪዎች በመቆጠብ በአንድ ተሽከርካሪ እና ሌሎች ቋሚ ንብረቶች ለማሟላት ተሞክሯል፡፡ የግል ገንዘባቸውንና ደመወዛቸውን እየሰጡ የሰበካ ጉባኤን ካደራጁት እና ካስፋፉት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ቀጥሎ፣ መምሪያውን ለረጅም ዓመታት መርተዋል – ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፡፡

ከማደራጃ መምሪያው በፊት፥ በሕዝብ ግንኙነት፣ ዕቅድ እና ልማት መምሪያ እንዲሁም በትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ በዋና ሓላፊነት ሠርተዋል፡፡ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዋና ዲን ኾነው በሠሩበት ወቅት፣ የቀኑን መደበኛ የሴሚነሪ መርሐ ግብር፣ በማታውም ክፍለ ጊዜ አስጀምረዋል፡፡ ከማኅበረ ቅዱሳን በርዳታ ባስገኟቸው በርካታ ኮምፒዩተሮች፣ ደቀ መዛሙርቱ መሠረታዊ የአጠቃቀም ክሂል እንዲቀስሙ አድርገዋል፤ ግምታቸው ከዘጠና ሺሕ ብር በላይ የኾኑ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን በስጦታ አሰባስበው ቤተ መጻሕፍቱን አደራጅተዋል፤ መንፈሳዊ ኮሌጁ የተወረሰበትን ዳቦ ቤት እና ክበቡን በማስመለስ የራስ አገዝ አቅሙን አጠናክረዋል፡፡

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን፣ በምእመናንና በብዙኀኑ ሕዝብ ዘንድ በስፋት የሚታወቁት፣ የመስቀል ደመራ እና የጥምቀት በዓላት አከባበር መርሐ ግብሮችን፣ እንዲሁም ዐበይት ወቅታዊ ኹነቶችን በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ በመምራት ባላቸው የዐደባባይ ተሳትፎ ነው፤ የውጭ አብያተ ክርስቲያን አባቶች እና ሌሎችም እንግዶች በመንበረ ፓትርያርኩ ሲስተናገዱ፣ መተርጉመ ልሳን ኾነው ያገለግላሉ፡፡

ከልዩ ልዩ ተቋማት ከፍተኛ ሓላፊነት ባሻገር፥ በሕፃናት እና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት፣ በልደታ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር እና ልማት ድርጅት እንዲሁም አኹን በተሾሙበት የብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት የቦርድ አባል ኾነው አገልግለዋል፡፡

ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ፣ በነገረ መለኰት የመጀመሪያ ዲግሪአቸውን በከፍተኛ ማዕርግ ያገኙት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ በገዳመ ኢየሱስ ደብር በምክትል አስተዳዳሪነት ቢመደቡም፣ ብዙም ሳይቆዩ ትምህርታቸውን በኹለተኛ ዲግሪ ለመቀጠል ወደ ኦስትሪያ ቬና አምርተዋል፡፡ በ650 ዓመታት የዩኒቨርሲቲው ታሪክ ውስጥ፣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ተማሪ የነበሩት ሊቀ ማእምራን፣ በሊተርጂካል ቴዎሎጂ የማስተርስ ዲግሪአቸውን በእጅግ ከፍተኛ ማዕርግ በማጠናቀቅ ከተመለሱ በኋላ ነበር፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን ኾነው የተመደቡት፡፡

በዚኹ የነገረ መለኰት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪአቸውን በቬና ዩኒቨርሲቲ ቀጥለው የሴሚናር ሥራቸውን ቢጨርሱም፣ የመመረቂያ ዲዘርቴሽናቸውን ሳያጠናቅቁ ወደ አገር ቤት ተጠርተው፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተመድበው ሠርተዋል፡፡ ‘ትምህርት እስከ ዕድሜ ልክ’ ያሉ የሚመስሉትና ለመማር የማይቦዝኑት ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ፣ አኹን በከፍተኛ የሥራ ሓላፊነት ላይ እያሉም፣ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የንግድ አስተዳደር፣ በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የኦርጋናይዜሽናል ሊደርሺፕ የኹለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ በትውፊታዊው ሥርዐተ ትምህርት፥ ቅኔውን በአስነጋሪነት፣ አቋቋሙንም በቆሜ የዜማ ይትበሃል በመምህርነት ደረጃ ጠንቅቀውታል፡፡

እንግዲህ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ፣ ለተጠቀሱት ዓመታት ያካበቱት ትምህርት እና ልምድ፣ ካለፈው በበለጠ ኹኔታ ተገልጦ የሚታይበት መድረክ፣ ከትላንት ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በዋና ሥራ አስኪያጅነት የተመደቡበት፣ የብዙኀን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ነው፡፡ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የበላይ ሓላፊነት የሚመራው ድርጅቱ፣ የቤተ ክርስቲያናችን ልሳን የኾነውን የኢኦተቤ-ቴቪ(EOTC-Tv.) ጣቢያ ያስተዳድራል፡፡ ድርጅቱ፥ የሥራ አመራር ቦርዱንና የውስጥ አደረጃጀቱን ገምግሞ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት እየጣረ መኾኑን ገልጿል፤ የአማርኛ፣ የአፋን ኦሮሞ እና የትግርኛ ክፍሎች እየራሳቸው ተደራጅተው፣ መርሐ ግብሮችን በመደበኛነት እንዲያሠራጩ አድርጓል፡፡

EOTC Tv. pledge

ሥርጭቱን ከሦስት ዓመት በፊት ሲጀምር፣ በወር እስከ 126ሺሕ ዶላር ለሳተላይት ኩባንያ ይከፍልበት የነበረውን፣ በባለሞያዎች በታገዘ የገበያ ጥናት ወጪውን ቀንሶ፣ ከእያንዳንዱ ወርኃዊ ክፍያ ከሰባት ሺሕ ዶላር በላይ ለማትረፍ ችያለኹ፤ ብሏል፡፡ በማርኬቲንግ ክፍሉ ገቢን ለመጨመር ጥረት እየተደረገ ነው፤ የውጭ እና የአገር ውስጥ አህጉረ ስብከት በአየር ሰዓት መጋራት እንዲሳተፉ ለማድረግ ውሎች እየተፈረሙ መኾኑን አመልክቷል፡፡ በማኅበራዊ ድረ ገጽ(ፌስቡክ እና ዩቲዩብ) በመጠቀመም፣ በአጭር ጊዜ ብዙ ተከታዮችን ማፍራቱንና ለገቢ ማስገኛነት ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መኾኑን አስታውቋል፡፡ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ጋራ ተያይዞ፣ በመንግሥት እና የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተላለፈውን የጸሎት እና ትምህርት ቀጥታ ሥርጭት፣ በጣቢያው ለማስቀጠል የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ለመገንባት፣ ለበጎ አድራጊ ግለሰቦች እና አካላት ሰፊ የቅስቀሳ ጥሪዎችን እያቀረበ ይገኛል፡፡

በትላንትናው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የከፍተኛ ሓላፊዎች ዝውውር፣ የሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ምክትል በመኾን ሲሠሩ የቆዩት መጋቤ ሐዲስ ሐዋዘ ብርሃን ጫኔ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያውን በዋና ሓላፊነት እንዲመሩ በዕድገት መመደባቸው ታውቋል፡፡ የብዙኀን መገናኛ ድርጅቱ ከተቋቋመበት እና የቴሌቪዥን ጣቢያው ሥርጭቱን ከጀመረበት ከሦስት ዓመት በፊት አንሥቶ፣ በዋና ሥራ አስኪያጅነት የመሩት መ/ር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ቀደም ሲል ወደ ተመደቡበት የውጭ ጉዳይ መምሪያው ተዛውረው ይሠራሉ፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ከዓመት በፊት ከበጀት እና ሒሳብ መምሪያ ዋና ሓላፊነት ወደ ቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር እና ልማት ድርጅት ቁጥጥር ክፍል ሓላፊነት ተዛውረው የነበሩት ውጤታማዋ አካውንታንት ወ/ሮ ጽጌሬዳ ዓለሙ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን የበጀት እና ሒሳብ መምሪያ በዋና ሓላፊነት እንዲመሩ ተመልሰው ተመድበዋል፡፡ በሞዴል ላይ ብቻ የተንጠለጠለውንና ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ለደረሰበት አሠራር እና ቁጥጥር የማይመጥነውን ነጠላ የሒሳብ እና መዝገብ አያያዝ፣ ወደ ዘመናዊው የኹለትዮሽ የሒሳብ አመዘጋገብ የቀየሩት፣ ለዚኽም የሚመቹ የተለያዩ የጥሬ ገንዘብ እና የንብረት ገቢ እና ወጪ ሞዴላሞዴሎችንና ሰነዶችን እንዲዘጋጅ ያደረጉት ወ/ሮ ጽጌሬዳ ዓለሙ ናቸው፡፡ ከዋናው መሥሪያ ቤት ባሻገር አብዛኞቹ አህጉረ ስብከት፣ በዐዲሱ የኹለትዮሽ የሒሳብ አመዘጋገብ እንዲሠሩ፣ ሥልጠና እና ድጋፍ በመስጠት መሠረቱን የጣሉት፣ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የመጡት ምስጉኗ ሞያተኛ ወ/ሮ ጽጌሬዳ ዓለሙ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል፣ የበጀት እና ሒሳብ መምሪያው ዋና ሓላፊ የነበሩት የአካውንቲንግ እና የማኔጅመንት ባለሞያው መልአከ ብርሃን ፍሥሓ ጌታነህ፣ ወደ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ ዋና ሓላፊነት ተዛውረዋል፡፡ በቁጥጥር አገልግሎት ዋና ሓላፊነት ለረጅም ጊዜ የሠሩት መምህር ኤርሚያስ ተድላ በጡረታ ተገልለዋል፡፡ የሕግ አገልግሎት መምሪያ ዋና ሓላፊ አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት፣ ወደ ቤቶች እና ሕንፃዎች አስተዳደር እና ልማት ድርጅት ተዛውረው በዋና ሥራ አስኪያጅነት ሲመደቡ፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት የአካውንቲንግ ባለሞያው እና የሕግ ዐዋቂው ሊቀ ትጉሃን ሽመልስ ቸርነት ደግሞ ወደ ሕግ አገልግሎት መምሪያ ዋና ሓላፊነት ተዛውረዋል፡፡ የድርጅቱን ዓመታዊ የኪራይ ገቢ ከ29 ሚሊዮን ወደ 86 ሚሊዮን ብር አሳድገዋል፤ በአሮጌው ቄራ አካባቢ በግንባታ ላይ ያሉትን ኹለት ሕንፃዎች መሠረት በማስጣል ሥራቸውን አስኪደዋል፤ በተመለሱ ቤቶች ርክክብ አፈጻጸም ወቅት፣ የግል ካርታ የወጣባቸውንና ከቤተ ክርስቲያን የተወረሱ አይደሉም በማለት አላግባብ ለመውሰድ የሚደረገውን ሙከራ በማምከን፣ ለቤተ ክርስቲያናች ካርታ የማውጣት ሥራው እንዲፋጠን አድርገዋል፡፡

ከትላንቱ ዝውውር ሦስት ቀናት ቀደም ሲል፣ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ በዕድገት ባደረገው ምደባ፣ የሊቃውንት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ የነበሩትን መጋቤ ብሉይ ዕዝራ ለገሠን፣ የሊቃውንት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ ኾነው እንዲሠሩ ሲሾም፣ የቀድሞው ሰብሳቢ ሊቀ አእላፍ ያዝዓለም ገሰሰ፣ በጡረታ ተገልለው በአባልነት እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡ ሌላውን የሊቃውንት ጉባኤ አባል መጋቤ ምሥጢር ፍሬ ስብሐት ዱባለን፣ የሊቃውንት ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ አድርጎ በዕድገት መድቧቸዋል፡፡

ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከወር በፊት አድርጎት በነበረው ምደባም፣ በዐዲስ መልክ ለተቋቋመው የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት መምሪያ፣ ሊቀ ሥዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስን በዋና ሓላፊነት መሾሙ ይታወሳል፡፡ ሊቀ ሥዩማን ቀድሞ ይመሩት በነበረው የዕቅድ እና ልማት መምሪያም፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ገዳማት እና የአብነት ት/ቤቶች ርዳታ ማስተባበሪያ እና ማደራጃ ዋና ሓላፊ መጋቤ ካህናት አባ ሀብተ ማርያም ዐሥራትን በዝውውር ተክቷል፡፡ በስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ተዘዋዋሪ ሰባኬ ወንጌል የነበሩትን መምህር አባ ለይኩን ግፋ ወሰንን፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ገዳማት እና የአብነት ት/ቤቶች ርዳታ ማስተባበሪያ እና ማደራጃ ዋና ሓላፊነት መድቧቸዋል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: