የቤተ ክርስቲያን በሮች እንዲከፈቱ የተላለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም መዘጋጀቱን የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አስታወቀ

 

FB_IMG_1589804669872

ከአካባቢው የፖሊስ አካላት ጋራ በመነጋገር ለነገ ማክሰኞ፣ ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ክብረ በዓል የተዘጋጀው የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን

  • ውሳኔው፣ ለአህጉረ ስብከት እና ለመንግሥት ሳይዘገይ እንዲሰራጭ ግፊት እያደረገ ነው፤
  • ሀገረ ስብከቱ፣ አንድነቱን ከመንግሥት ጋራ በማወያየት አፈጻጸሙን እንዲያመቻች ጠየቀ፤
  • በአንዳንድ ክፍላተ ከተማ፣ ከፖሊስ አባላት የሚታየው አለመተባበር እንደሚያሳስበው ገለጸ፤
  • ምእመናን በየሰበካቸው፣ ጥንቃቄዎችን በመተግበር ለአስተናጋጆች ታዛዥ እንዲኾኑ አሳሰበ፤

***

  • ከሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እስከ አጥቢያ የተደራጁ፣ 1ሺሕ189 አስተባባሪዎችን አሠልጥኗል፤
  • በ227 አጥቢያዎች፣ ከ30 ሺሕ በላይ የሰንበት ት/ቤት አባላትን በአስተናጋጅነት መድቧል፤
  • ቅዳሴ፣ ክርስትና፣ ጋብቻ፣ ቀብር እና የቢሮ አገልግሎቶች በአግባቡ እንዲፈጸሙ ያደርጋል፤
  • በኹሉም አጥቢያዎች በመመሪያው በተፈቀደው የምእመናን ብዛት ያለአድልዎ ይፈጸማሉ፤

***

የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን መስፋፋት ለመግታት ቋሚ ሲኖዶስ ካሳለፈው የቅድመ ጥንቃቄ ውሳኔ ውጭ፣ በኀይል የተዘጉ የቤተ ክርስቲያን በሮች ተከፍተው መንፈሳዊ አገልግሎቱ በጥንቃቄ እንዲከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈውን ውሳኔ ለማስፈጸም መዘጋጀቱን፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አስታወቀ፡፡

የተቋረጠው መንፈሳዊ አገልግሎት፣ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በተመደቡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አስተናጋጅነት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲከናወን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባው የወሰነውን ለማስፈጸም፥ በሰው ኃይል አደረጃጀት፣ ሥልጠና እና ስምሪት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አንድነቱ አስታውቋል፡፡

FB_IMG_1589804635554

የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤው ውሳኔ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ለአስፈጻሚው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ባለፈው ሳምንት ዓርብ መላኩን እንደሚያውቅ የጠቀሰው አንድነቱ፣ ለተልእኮው መፋጠን ይረዳ ዘንድ በአስቸኳይ ወጪ ኾኖ ለመላው አህጉረ ስብከት እና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲሰራጭ ጠይቋል፡፡ እስከዚያው ድረስ፣ የፖሊስ ጥበቃ በተነሣባቸውና የተዘጉ በሮች በተከፈቱባቸው አጥቢያዎች ሓላፊነቱን በምልዓት ለመወጣት፣ ባልተነሣባቸው ደግሞ ግጭት እንዳይፈጠር እያረጋጋ እንደሚጠብቅ ገልጿል፡፡ በትብብር መሥራትን፣ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በውነት ለሚናፍቁ ምእመናን በአግባቡ እንዲደርስ ማስቻልን ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚጥር አስገንዝቧል፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትም፣ ውሳኔው ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ እንደ ደረሰው፣ የሰንበት ት/ቤት ማደራጃ ዋና ክፍሉንና አንድነቱን፣ ከሚመለከተው የከተማ አስተዳደሩ አካል ጋራ ፈጥኖ በማገናኘት በትብብር የሚፈጸምበትን ኹኔታ እንዲያመቻች ጠይቋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ፣ በየደረጃው የተስፋ ልዑክ ግብረ ኃይሎችን አቋቁሜያለኹ ቢልም፣ በመመሪያው እንደታዘዘው፥ የሞያተኛ ተዋፅኦን ጠብቆ በአግባቡ ከማደራጀት፣ መዋቅራዊ ተዋረዱን አክብሮ መመሪያዎችን በትጋት ከማስፈጸም፣ ወቅታዊ መረጃዎችን በቅልጥፍና ከማስተላለፍ በተፃራሪ፣ አንዳንድ ሓላፊዎች በአዘቦታዊ አመለካከት የሚያሳዩት ግዴለሽነት በአስቸኳይ እንዲታረም አሳስቧል፡፡

“ምን እናግዛችኹ” የሚሉ ወገኖች ቢኖሩም፣ “መሽቷል አልችልም፤ ተልእኮ አለብኝ፤ አንድ ነገር ብኾን ዞር ብሎ የሚያየኝ የለም፤ ምን ይመጣል ተዉኝ እባካችኹ” በሚሉ የክፍላተ ከተማ እና የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ሳቢያ፣ ክፍተቶች በጊዜ እልባት ሳይሰጣቸው እየቀሩ፣ የረባም ሥራ ሳይሠራ ግብረ ኃይሉ ለፍርሰት መዳረሱን አስታውቋል፡፡ አንዳንድ ክንውኖች ቢጠቀሱም፣ በግለሰብ አባላት ትጋት የተሠሩ በመኾናቸው፣ ግብረ ኃይሉን በተልእኮው ለማስቀጠል አለመርዳታቸውን አስረድቷል፡፡

FB_IMG_1589763645124

ይልቁንም መዲናዪቱ፥ የወረርሺኙ ማዕከል በኾነችበትና የማኅበረሰባዊ መዛመት ምልክት እንደሚታይባት እየተነገረ ባለበት ወቅት፣ ባለብዙ ሀብቱ ሀገረ ስብከት፣ አደረግኹት የሚለው ጥረት ጨርሶ አደጋውን እንደማይመጥን ተችቷል፤ በምትኩ፣ በወትሮ ዝግጁነት(pro activeness) የተቃኘ ንቁ እና አብነታዊ የፀረ ኮቪድ-19 አመራር እንዲሰጥ ጠይቋል፤ ዋና ሥራ አስኪያጁ በቅርቡ በሰጡት መግለጫም ዐዲስ የልመና ቋት ከመክፈት አስቀድሞ፣ ያለውን ቅምጥ ሀብት አንቀሳቅሶ የተቸገሩትን የመደጎም እና ጫናቸውን የማቃለል ምግባረ ሠናይ እንዲያስቀድም መክሯል፡፡

Saris Abo

በዝጉ ሰሞን፥ የአንድነቱ አመራሮች፣ ከከተማው ፖሊስ ኮሚሽነር እና ከክፍላተ ከተማ ኮማንደሮች ጋራ መልካም ውይይት ሲያደርጉ መሰንበታቸው ተጠቁሟል፡፡ ይኸውም፣ ቀኖናዊ አገልግሎቱ ሥርዐቱንና የጥንቃቄ ተግባራቱን ጠብቆ በሚፈጸምበት፣ የአጥቢያ ሓላፊዎች ቢሮ ገብተው ሥራቸውን በሚሠሩበት፣ የሰንበት ት/ቤቶችም የኦንላየን ማስተማር አገልግሎታቸውን ከየጽ/ቤቶቻቸው ለማስተባበር በሚችሉበት ኹኔታ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል፡፡ በዚኽም፣ ባልቀረበ ጥያቄ የቤተ ክርስቲያን ደጇን በኃይል መዝጋትን ጨምሮ አገልግሎቷን የሚያስታጉሉና ምእመኗን የሚያስቆጡ ከፍተኛ የኃይል ርምጃዎች እና ማጥላላቶች መፈጸማቸው ታምኖ መታረም እንደሚያስፈልጋቸው መግባባቱ ቢኖርም፣ “ዝጉ ከሚለው በቀር የደረሰን መመሪያ የለም” በሚል እና በሀገረ ስብከቱ ዳተኝነት፣ ጥቃቱ እና ጫናው ሳይቃለል ባደረበት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ የምልዓተ ጉባኤ ውሳኔውን ማሳለፉ ተዘግቧል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶሱን መግለጫ ተከትሎ፣ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያንና የክፍላተ ከተማ ሰንበት ት/ቤቶች አደራጆችንና አስተባባሪዎችን፣ ከትላንት በስቲያ በሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ጠርቶ፣ በውሳኔው አፈጻጸም ላይ መወያየቱን አንድነቱ ገልጿል፡፡ ለምልዓተ ጉባኤው ውሳኔ መሠረት የኾነውና ቀደም ሲል በቋሚ ሲኖዶስ በጸደቀው የፀረ ኮቪድ-19 ቅድመ ጥንቃቄ የውስጥ መመሪያ፣ በዚህም ላይ ተመሥርቶ አንድነቱ ባዘጋጀው የአፈጻጸም ዝርዝር እንዲሁም፣ በዝጉ ሰሞን ያጋጠሙ ችግሮችን በስፋት በማንሣት ለአፈጻጸም ያለውን ተጨባጭ ዐቅም ገምግሞ ዝግጁነቱን ማረጋገጡን አመልክቷል፡፡

400015600222_142011

ትላንት እሑድ ግንቦት 9 ቀን፣ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን

ሥርዐተ ቅዳሴው በተመደቡ ቀዳስያን ልዑካን ብቻ እንዲፈጸም፤ ቆራብያን ምእመናን የፈረቃ ተራ ወጥቶላቸው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲሳተፉ፤ ሌሎች ምእመናንም አካላዊ ርቀትንና ንጽሕናን ጠብቀው እንዲያስቀድሱ፤ ስብሐተ ነግህ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማኅሌት፣ ጸሎተ ፍትሐት የመሳሰሉት ደግሞ ለሥርዐቱ በሚያስፈልገው ቁጥር በውሱን ሊቃውንት በየተራ እንዲፈጸሙ፣ ቋሚ ሲኖዶስ መጋቢት 14 ቀን መወሰኑን አንድነቱ ጠቅሷል፡፡ አገልጋዮች፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና ምእመናን፣ ውሳኔውን የሚፈጽሙበት ጥብቅ የውስጥ መመሪያ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የተስፋ ልዑክ ዐቢይ ግብረ ኃይል ተዘጋጅቶና በቋሚ ሲኖዶሱ ጸድቆ ለኹሉም አህጉረ ስብከት መላኩን አስታውሷል፡፡ አንድነቱም በበኩሉ፥ የአገልግሎቱን ዓይነት፣ ከተገልጋዩ ብዛት እና ጊዜ(በዕለተ ሰንበት እና በወርኃዊ በዓላት) ጋራ በማገናዘብ አስተናጋጆችን በመመደብ እና የምእመናን ፈረቃ(ወንዶች፣ ሴቶች፣ ሕፃናት) በማውጣት የሚስተናገዱበትን አፈጻጸም እና መርሐ ግብር በዝርዝር ማዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

መንፈሳዊ አገልግሎቱ ሳይቋረጥ፣ የምእመናን የምስጢራት ሱታፌ ሳይስተጓጎል፣ ካህናት እና ምእመናን ለበሽታው ሳይጋለጡ፣ በኹሉም አጥቢያዎች ካለአድልዎ ለማከናወን በሚያስችሉ ስልቶች ላይ በውይይቱ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ መቻሉን አስረድቷል፡፡ በይበልጥም፣ ምእመናን በብዛት ሊገኙ የሚችሉባቸው ጊዜያት ላይ ትኩረት በማድረግ፣ ከሰበካው ወጣቶች እና ተስፋ ልዑክ ጋራ ተቀናጅተው አገልግሎቱን እንደሚያሳልጡ አረጋግጧል፡፡ እንደዚኹም ኹሉ በተለይ፥ በጥምቀተ ክርስትና፣ ሥርዐተ ጋብቻ፣ ጸሎተ ቀንዲል፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመታሰቢያ ጸሎት እና የቀብር አገልግሎት ወቅት፣ ከባለጉዳዮቹ ጋራ የሚመጡ ተገልጋዮች ብዛት፣ በአፈጻጸም ዝርዝር ውስጥ በተፈቀደው ቁጥር እና በደብሩ ነባራዊ ኹኔታ ስለሚወሰን፣ ምእመናን ይህን የጥንቃቄ መመሪያ በሚገባ ተረድተው በየዕለቱ ለሚመደቡ የተስፋ ልዑክ ግብረ ኃይሎች እና የሰንበት ት/ቤት አስተናጋጆች በመታዘዝ እንዲተባበሩ አሳስቧል፤ “ራሳቸውንም በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የሚያስተናግዱ፣ የሚታዘዙ ሊኾኑ ይገባል፤” በማለት አማፅኗል፡፡

የሰበካ አስተዳደሩ የጽ/ቤት አገልግሎቶች፣ በሠራተኞች የአገባብ እና የቢሮ አቀማመጥ ጥንቃቄዎች የሚፈጸሙ በመኾኑ፣ ምእመናን፥ የሰበካ ጉባኤ፣ የዐሥራት በኵራት፣ የመብዓ እና ሌሎችም የአገልግሎት ክፍያዎቻቸውን በመደበኛው የሥራ ሰዓት እንደሚፈጽሙ፤ ካህናት ከንሥሓ ልጆቻቸው ጋራ በተናጠል ምክክር እንደሚያደርጉ፤ የሰንበት ት/ቤቶች አመራሮች እና አስፈጻሚ አካላት፥ ለአባሎቻቸው የርቀት(ኦንላየን) ትምህርት እንደሚያስተላለፉ እንዲሁም የአስተናጋጆችን ምደባ ጨምሮ አንገብጋቢ ጉዳዮችን በቢሯቸው በጥንቃቄ እንደሚያከናውኑ፤ የተስፋ ልዑክ ግብረ ኃይሎችም፣ ከወረርሺኙ ጋራ የተያያዙ የመከላከል ተግባራትን እንደሚያስተባብሩ ገልጿል፡፡ ለአፈጻጸም እና ተግባቦት ይረዳ ዘንድም፣ ከላይ ለተዘረዘሩት አካላት ኹሉ የመታወቂያ ካርድ ወይም ልዩ ባጅ እና ይለፍ እንደሚዘጋጅላቸው አንድነቱ ጠቁሟል፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች አንድነቱ፣ ከአመራሩ እስከ ፈጻሚው ድረስ፣ በልዩ ልዩ ዕቅዶች ትግበራ የተፈተኑና ውጤታማነታቸውን ያስመሰከሩ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ አስተባባሪዎች እና መደበኛ አባላት ያሉት በመኾኑ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የተጣለበትን ሓላፊነት እንደማያዳግተው አረጋግጧል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ደረጃ 19፣ በሰባቱ ክፍላተ ከተማ ጽ/ቤቶች 35፣ በአገልግሎት ላይ በሚገኙ 206 አድባራት እና ገዳማት እንዲሁም በምሥረታ ክትትል ላይ በሚገኙ ከ21 በላይ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን 1ሺሕ135፣ በድምሩ 1ሺሕ189 ሥልጡን አደራጆች እና አስተባባሪዎች እንዳሉት ገልጿል፤ በኹሉም አጥቢያዎችም፣ ከ30 ሺሕ በላይ ጠቅላላ መደበኛ አባላት በፈጻሚነት ያሉት በመኾኑ፣ ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ጀምሮ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በየድርሻቸው፣ የኮረና ቫይረስን ዘመነ ወረርሺኝ የሚያሻግር የጋራ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: