ቅ/ሲኖዶስ: የተጀመረው ሱባኤ እንዲቀጥል ወሰነ፤ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ፤ መንግሥት ሰላም የማስከበሩንና አገር የመጠበቁን ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቀረበ

Holy Synod Ginbot2011 closing

ከጥቅምት 11 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለ13 ቀናት፣ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲነጋገር የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በሰላም ተጠናቅቆ ዛሬ ከቀትር በኋላ በጸሎት ተዘግቷል፤ ባለ14 ነጥቦች መግለጫም አውጥቷል፡፡

የመግለጫው ዐበይት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡-

 • በዜጎች ሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም፣ ጉዳቱ ጎልቶ እየታየ ያለው በክርስቲያኖች እና በአብያተ ክርስቲያን ላይ ነው፤ እየደረሰ ያለው ስደት እና መከራ ቅዱስ ሲኖዶስን በእጅጉ አሳዝኗል፤ መንግሥት፥ የጥፋት መልእክተኞችን በሕግ እንዲጠይቃቸውና ለሕዝቡም ብርቱ ጥበቃ እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቧል፤
 • በቤተ ክርስቲያናችን የሚከናወነውን መንፈሳዊም ይኹን ማኅበራዊ ተግባራት በአግባቡ ማስተላለፍ እንዲቻል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሕዝብ ግንኙነት፣ በመምሪያ ደረጃ እንዲቋቋም ወስኗል፤
 • በአገራችን የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በቋንቋቸው ማገልገልና ማስተማር እንዲቻል፣ በየአህጉረ ስብከቱ የሚገኙ የአብነት ት/ቤቶችን ማጠናከር፣ ከልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች አገልጋዮችን ማፍራት እንዲቻል፣ ለት/ቤቶቹ ማጠናከርያ የሚኾን ቋሚ በጀት እንዲመደብ፤ በቀጣይም በኹሉም አፍ መፍቻ ቋንቋ በማዕከል ማሠልጠኛ እንዲቋቋም ወስኗል፤
 • የቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ መሪ ዕቅድ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል ወደ ተግባር እየተገባ መኾኑን ጉባኤው ከቀረበው ሪፖርት አዳምጧል፤ በቀጣይ ሥራው ተፋጥኖ እንዲቀጥልና ከካህናትና ከምእመናን ከወጣቱም ጭምር የሚቀርቡ ወቅታዊ አቤቱታዎች፣ በመሪ ዕቅዱ እየተጠኑ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ወስኗል፤
 • በግንቦቱ ርክበ ካህናት በቤተ ክርስቲያናችን የተቋቋመው አገራዊ የሰላም እና ዕርቅ ኮሚቴ፣ የ4 ወራት ሪፖርት ለጉባኤው አቅርቧል፤ ኮሚቴው ያከናወነውን የሰላም ተልእኮ ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎ በቀጣይም ኮሚቴው፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራንና ከወጣቶች የተውጣጡ አባላትን አካቶ የሰላም እና የዕርቅ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ፣ ለዚህም የሚኾን አስፈላጊውን በጀት መድቧል፤
 • በአገራችን በኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋት እና ስደት ላይ በመነጋገር በጣም ለተቸገሩ ወገኖች በጊዜያዊነት የሚደርስ ምግብ እና አልባሳት ለማቅረብ እንዲቻል አስፈላጊው ገንዘብ እንዲመደብ፣ በቀጣይም በክልሉ ይህን ችግር እየተከታተለ ዘለቄታዊ ርዳታ የሚያሰባስብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ወስኗል፤
 • የጌዴኦ እና ቡርጂ ዞኖች እስከ አሁን ድረስ በሲዳማ ሀገረ ስብከት ሥር ኾነው መንፈሳዊውን አገልግሎት ሲያገኙና ሲተዳደሩ የቆዩ ቢኾንም፣ በአሁኑ ጊዜ ራሱን ችሎ ሀገረ ስብከት እንዲኾንላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ራሱን የቻለ ሀገረ ስብከት እንዲኾን ወስኗል፤
 • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት በተመለከተ፣ ከቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ግንኙነት መምሪያ በቀረበ ሪፖርት ላይ ጉባኤው ተነጋግሮ፣ በኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው ጥንታዊ ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል፤
 • በስዊድን አገር ሶደርቴሌ ከተማን ማእከል ያደረገ የቅዱስ አግናጥዮስ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሴሚናሪ በመላው አውሮፓ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን እና አገልጋይ ካህናት፣ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ የአብነት ትምህርት እና ዘመናዊ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነገረ መለኮት ሥልጠና የሚሰጥ ከፍተኛ የትምህርት ማእከል በመኾኑ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ዕውቅና እንዲያገኝ ወስኗል፤ አገልግሎቱን በስፋት እና በብቃት እንዲያከናውን፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የዕውቅና ደብዳቤ እንዲደርሰውም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወስኗል፤
 • የ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ በጀት አስመልክቶ ከሒሳብ እና በጀት መምሪያ በቀረበው ዕቅድ ላይ በመነጋገር የቀረበው በጀት ላይ ማሻሻያ በማድረግ የ2012 ዓ.ም. በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፤
 • በአኹኑ ጊዜ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለው ችግር እንዲያበቃ እግዚአብሔር አምላክ ምሕረቱን እንዲሰጠን የተጀመረው ሱባኤ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡

ጥንታዊት እና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ከጥንት ጀምሮ የአገር ባለውለታ እንደመኾኗ ኹሉ፣ ወደፊትም በአገራችን ኢትዮጵያ በመንግሥት እና በሕዝቡ ትብብር ለአገር አንድነት እና ለዜጎች መብት መከበር፣ ለሰው ልጆች እኩልነት ለሚደረገው አገራዊ ጥረት የበኩሏን አስተዋፅኦ ከማድረግ አትቆጠብም፡፡

ኾኖም፣ ለዚሁ አገራዊ ስኬት ከኹሉም በላይ በዜጎች መካከል መከባበርና ሰላማዊ አንድነት መኖር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መኾኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያምናል፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ኹሉ፣ በአሁኑ ጊዜ ለአገራዊ አንድነታችን ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው መኾኑን አምናችኹ፣ በአንድነት፣ በሰላምና ተከባብሮ በጋራ ለመኖር፣ ለመሥራትም ኾነ ሠርቶ ለመበልጸግ አገራዊ አንድነታችኹን እንድታጠናክሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የአገራችን መንግሥትም፣ የአገር ሰላም፣ የዜጎች ደኅንነትና በሰላም ወጥቶ መግባት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መኾኑን፣ ክቡር የኾነው የሰው ልጅ ሕይወት በምንም መልኩ በከንቱ መጥፋት የሌለበት መኾኑን ተገንዝቦ፣ ሰላምን የማስከበሩን፣ አገር የመጠበቁንና ዜጎች በአገራቸው በእኩልነት ተሳስበው የሚኖሩበትን መንገድ በመቀየስ መንግሥታዊ ሓላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ያሳስባል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: