ቅዱስ ሲኖዶስ: ለሰላም እና አንድነት ዐቢይ ኮሚቴ ዐሥር ሚሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ፈቀደ፤ ለቤተ ክርስቲያን መብትና ክብር አስጠባቂው – “ጴጥሮሳውያን የካህናትና ወጣቶች ኅብረት” ውጤታማ እንቅስቃሴ ይኹንታ ሰጠ!

  • ዐቢይ ኮሚቴው፣ ከተለያዩ አካላት በተውጣጡ አካላትና አባላት በቀጣይነት ይጠናከራል፤
  • የካህናትና ወጣቶች ኅብረቱ ተጠሪነት ለዐቢይ ኮሚቴው ኾኖ እንዲቀጥል ይኹንታ አገኘ
  • የኦሮሚያ አህጉረ ስብከት ካህናት እና ምእመናን ኅብረትም፣ ዐቢይ ኮሚቴውን ያግዛል

***

73108746_732445340607253_5028854134598533120_n

በሕዝብ አንድነትና ሰላም እንዲሁም በምእመናን ደኅንነትና መብቶች መጠበቅ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ፣ ባለፈው ዓመት ግንቦት የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ የተቋቋመው፣ የሀገራዊ ሰላም እና አንድነት ዐቢይ ኮሚቴ የአፈጻጸም ሪፖርቱንና የወቅታዊ ጉዳዮች ዳሰሳዊ ጥናቱን ለምልአተ ጉባኤው አቀረበ፡፡

በሪፖርቱ እንደተገለጸው፣ ዐቢይ ኮሚቴው፣ ከ53ቱም አህጉረ ስብከት ለተውጣጡ ልኡካን፣ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ሰላምና ለሕዝብ አንድነት መጠበቅ ያላትን ድርሻና የሚጠበቅባትን አስተዋፅኦ፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ጨምሮ በግጭት መንሥኤዎችና አፈታት ዙሪያ ክህሎትን የሚያዳብሩ ሥልጠናዎችን በጠቅላይ ጽ/ቤት እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰጥቷል፡፡

ከውጭ ኹኔታዎች አንጻር፣ ለቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አንድነት ስጋት ስለኾኑ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግልጽ እና ኅቡእ ኀይሎች አሰላለፍ፣ ተግዳሮቱን በአስተሳሰብና ተግባር የመመከት ስትራተጂና ዝግጅት ላይ፣ በባለሞያዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት አድርጓል፡፡

የዐቢይ ኮሚቴው ያለፉት አራት ወራት እንቅስቃሴ በዋናነት በሥልጠና ላይ ያተኮረ ሲኾን፤ ይኸውም፡-

  • ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር አጋማሽ፣ ከ53ቱም አህጉረ ስብከት ከእያንዳንዳቸው ለተውጣጡ አምስት አምስት ልኡካን፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የኹሉም አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሰባክያነ ወንጌል በአጠቃላይ ለ800 ተሳታፊዎች፣ የኹለት ቀናት ውጤታማ ሥልጠና በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በየዘርፉ ባለሞያዎች ተሰጥቷል፤
  • ከአዲስ አበባ በመቶ ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ለሚገኙ የኦሮሚያ አህጉረ ስብከት(ምሥራቅ ሸዋ፣ ፍቼ-ሰላሌ፣ አምቦ እና ግንደበረት) ለተውጣጡ 400 ምሁራንና ሰባክያነ ወንጌል፣ የአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ጥቅምት 9 ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል፤
  • ለመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 38ኛው ዓመታዊ ስብሰባ ከተገኙ 15 የኦሮሚያ ክልል አህጉረ ስብከት ልኡካን ጋራ፣ በወቅታዊ ኹኔታዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሒዷል፤
  • በሀገራዊ ሰላም እና አንድነት እንዲሁም በወቅታዊ ችግሮችና የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ላይ ያተኮረ የሥልጠና ማኑዋል በባለሞያዎች ተዘጋጅቶ የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሰጥቷል፤ ለኦሮሚያ ክልል 15 አህጉረ ስብከት እና ለደቡብ ክልል ሐዋሳ ቅድሚያ በመስጠት፣ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ የተውጣጡ 25 ልኡካን፣ ጥቅምት 10 ቀን የተሰጠውን የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሳትፈው በየዞኖቹ ስምሪት አድርገዋል፤ እስከ አጥቢያ ድረስ ለሚዘልቀው ሥልጠና ማስፈጸሚያ፣ በየወረዳዎቹ አካውንት በእያንዳንዳቸው 133ሺሕ ብር በጀት ገቢ አድርጓል፤
  • ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጥቃትንና ችግሮችን በተመለከተ፣ ለመንግሥት እና ለሚመለከታቸው አካላት የተጻፉ ደብዳቤዎችንና የጽሑፍ ሰነዶችን አዘጋጅቷል፡፡

ይህንኑ የዐቢይ ኮሚቴውን የሥራ አፈጻጸም የገመገመው ምልአተ ጉባኤው፣ በ68 ከፍተኛ ድጋፍና በኹለት የትችት ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል፤ ከወቅቱ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን የሰላምና የደኅንነት ተግዳሮት አኳያ፣ ብቁና ውጤታማ እንቅስቃሴ ለማድረግ ያስችለው ዘንድ፣ ራሱን በተጨማሪ የሰው ኀይል እንዲያጠናክር መመሪያ ሰጥቶታል፤ ለተከታዮቹ ስድስት ወራት በበጀት ደግፎ ያቀረበውን ዝርዝር ዕቅድ ከመረመረ በኋላም፣ ከጠየቀው የኻያ ሚሊዮን ብር በጀት ውስጥ ዐሥር ሚሊዮኑን ፈቅዶለታል፡፡

የዐሥር ሚሊዮን ብር በጀቱ፣ በግንቦቱ ጉባኤ ተመድቦለት ከነበረው 7 ሚሊዮን ብር በጀት ተጨማሪ እንደኾነ ተጠቁሟል፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ወጪ ተደርጎ የተፈቀደ ሲኾን፣ የዐቢይ ኮሚቴው የሥራ አፈጻጸም በቋሚ ሲኖዶሱ እየተገመገመ በቀጣይነት ድጋፍ እንደሚደረግለት በውሳኔው ተጠቁሟል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶሱ መመሪያ መሠረት፣ በእምነት አቋማቸውና በተግባር ቁርጠኝነታቸው የታመነባቸውን ምእመናን በሥራ አስፈጻሚነት መርጦ ለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቅርቦ እያጸደቀ ራሱን በማጠናከር እንደሚንቀሳቀስ ዐቢይ ኮሚቴው አስታውቋል፤ “አሁንም የምናተኩረው በሰው ላይ ማለትም በሥልጠና እና ስብከተ ወንጌል ላይ ይኾናል፤ ሀገራዊ ኮሚቴ እንደመኾኑ፣ ችግርና ስጋት ያለባቸውን የሀገራችንን ክፍሎች ኹሉ በመሸፈን ግጭትንና ጥቃትን ለመከላከል እንቀሳቀሳለን፤” ብለዋል አንድ የዐቢይ ኮሚቴው አባል፡፡


በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ሰብሳቢነት፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን፣ ብፁዕ አቡነ ኄኖክን፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤልንና ብፁዕ አቡነ ሩፋኤልን ከሦስት የመምሪያ ዋና ሓላፊዎች ጋራ የያዘው የሀገራዊ ሰላምና አንድነት ዐቢይ ኮሚቴው፣ ዘጠኝ ጠቅላላ አባላትን በማካተት ነው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባለፈው ዓመት የተቋቋመው፡፡

በሌላ በኩል፣ ካለፈው ዓመት ግንቦት የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ መጠናቀቅ ማግሥት፣ ለቤተ ክርስቲያን ፍትሕን ለማረጋገጥና ለቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄዎች ምላሽ ለማሰጠት መንቀሳቀስ የጀመረው የዐሥር መንፈሳውያን ማኅበራት ኅብረት፣ የዐቢይ ኮሚቴው ንኡስ አካልና አባል ኹኖ የዕቅበተ ቤተ ክርስቲያን ተግባሩን ይቀጥል ዘንድ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ይኹንታ አግኝቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ይኹንታውን የሰጠው፣ ኅብረቱ፣ ካለፈው ዓመት ሰኔ ጀምሮ ለአምስት ወራት በአዲስ አበባ እና በአህጉረ ስብከት ያደረጋቸው፣ የቤተ ክርስቲያንን መብትና የምእመናንን ደኅንነት የማስጠበቅ ውጤታማ እንቅስቃሴዎቹ፣ በዐቢይ ኮሚቴው ሪፖርት አማካይነት ለምልአተ ጉባኤው ቀርቦ ከተሰማ በኋላ ነው፡፡

Mahiberat Hibret Meglecha Ginbot2011

የቤተ ክርስቲያን መብት እና ክብር አስጠባቂ – የሰማዕቱ ቅዱስ ጴጥሮስ የካህናት እና ወጣቶች ኅብረት ኮሚቴ በሚል መጠሪያ በቀረበው ስያሜውና ተጋድሎው ይኹንታውን ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤው ማግኘቱ ታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ኅብረቱ፣ በዐቢይ ኮሚቴው ሥር ንኡስ ኮሚቴ ኾኖ፣ መብቱ ተጠብቆ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም፣ ለተጎዱት አብያተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ካሳ እንዲሰጥና በቀጣይም መንግሥት ተከታታይ የጥቃት ዒላማ ለኾነችው ቤተ ክርስቲያናችን የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጥ ግፊት ማድረግ፣ የኅብረቱ ተቀዳሚ ዓላማዎች ናቸው፡፡


ቅዱስ ሲኖዶሱ ባለፈው ዓመት ግንቦት፣ ለመንግሥት ላቀረባቸው ለእነዚህ ጥያቄዎች በወቅቱ ተገቢው ምላሽ በመነፈጉ፣ በምልአተ ጉባኤው መጠናቀቅ ማግሥት ኅብረቱ በይፋ ወጥቶ ባስተላለፈው ጥሪ፣ ምልአተ ምእመናን ከዳር ዳር ተነሣስተው አለኝታነታቸውን አሳይተዋል፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት እስከ ክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ድረስ የተዘጉ በሮችን በግርማዊነት በማስከፈት ለቤተ ክርስቲያን ደኅንነትና መብት መጠበቅ ምልክት የኾኑ ጅምር ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች፣ በአብዛኛው ሃይማኖታዊ መልክ ይዘው በምእመናንና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አሠቃቂ ጥቃቶች፣ በዐቢይ ኮሚቴው ሥር የተዋቀረውን የኅብረቱን ጥያቄዎች ትክክለኝነትና አግባብነት የሚያረጋግጡ ናቸው፤ በጥቃቱ የተገደሉና የተጎዱ ምእመናን እነማን እንደኾኑና የጥቃቱ ዝርዝር አፈጻጸም በውል የሰነደ ሲኾን፣ ሌላ ዙር ጥቃትን አስቀድሞ ከመግታት፣ ፍትሕን ከማስገኘት ጀምሮ ለጉዳዩ አንዳች መልክና እልባት በሚሰጥበት ኹኔታ ላይ ንቁህና ትጉህ ዘኢይነውም ኾኖ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡


በተያያዘ ዜና፣ ጥቃቱ ያለማቋረጥ እየተፈጸመ ካለበት ከኦሮሚያ ክልል አህጉረ ስብከት የተውጣጡ ካህናትና ምእመናን ኅብረት ተወካዮች፣ በማስረጃ አስደግፈው ያቀረቡትና በክልሉ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚገኝበትን ተጨባጭ ወቅታዊ ይዞታ የሚያትት ጥናታዊ ሪፖርት ለምልአተ ጉባኤው አቅርበዋል፡፡

ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ እና ለቅሠጣ ዓላማ፣ አንዳንድ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን በማሳጣት በስፋት ሲለፍፉ ከቆዩት በተለየ፣ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችን፣ ስጋቶችንና ዕድሎችን በወጉ በመተንተን፣ ሊደረግ የሚገባውን ስትራቴጂያዊ ዝግጅትና አገልግሎት የጠቆመ ልከኛ ምክረ ሐሳብ የቀረበበት ጥናታዊ ሪፖርቱ፣ የምልአተ ጉባኤውን ብዙኀን አባላት ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቷል፡፡


በጥናታዊ ሪፖርቱ መነሻነት ምልአተ ጉባኤው ባደረገው ውይይትም፣ የኦሮሚያ ክልል ካህናትና ምእመናን ኅብረትም፣ የሀገራዊ ሰላምና አንድነት ዐቢይ ኮሚቴው አካል ኾኖ በአጋርነት እንዲሠራ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ይኹንታውን መስጠቱ ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: