የአንድነቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የትውውቅ ጉባኤ አካሔደ፤ “ለቤተ ክርስቲያን ኃይልና ብርታት የኾነ ዐቢይ ጉባኤ ነው፤ በአንድነት ልንተጋ ይገባል”/ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ/

 • ብፁዓን አባቶች፣በስማቸውና አህጉረ ስብከታቸው የእርስ በርስ ትውውቅ አደረጉ
 • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣የትውውቅ ጉባኤውን፣በርእሰ መንበርነት መርተዋል
 • በጥቅምቱ ምልዓተ ጉባኤ፣የአህጉረ ስብከት ክልል እና ምደባ ማስተካከያ ይደረጋል
 • ከውጭ የመጡት አባቶች፣ በተደረገላቸው አቀባበል የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል

†††

 • ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጋራ 16 ብፁዓን አባቶች አብረው መጥተዋል
 • መንበረ ፓትርያርኩንና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትን እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል
 • “አንድነቷን በዓለም አቀፍ ለማጠናከር ትልቅ ዕድል ነው፤”/ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ/
 • “አገርንና ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቅን በአንድነት እንትጋ፤” /ቅዱስ ፓትርያርኩ/

†††

በዕርቀ ሰላም፣ አንድነቱ የተመለሰው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የአባላቱን የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የእርስ በርስ ትውውቅ ጉባኤ ያካሔደ ሲኾን፤ በርእሰ መንበርነት የመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ አገርንና ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቁ በአንድነት መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

FB_IMG_1533056821700

በጉባኤው፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ስማቸውንና የሚመሩትን አህጉረ ስብከት እየጠቀሱ ራሳቸውን አስተዋውቀዋል፡፡ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ጋራ አብረው ከመጡት 21 አጠቃላይ ልኡካን መካከል 16ቱ ቃነ ጳጳሳት ሲኾኑ፣ ሁሉም በትውውቅ ጉባኤው ላይ ተገኝተዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ካሉት ብፁዓን አባቶች 42ቱ መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

ለብዙኃን መገናኛ ክፍት የነበረው የእርስ በርስ ትውውቁ፣ ከፍተኛ የደስታ መንፈስ የታየበት እንደነበር ተገልጿል፤“ሁሉም እየተነሡ ነበር ስማቸውን የሚናገሩት፤ የፍቅርና የመተባበር ድባብ ታይቶበታል፤” ተብሏል፡፡

ከትውውቁ በኋላ ጉባኤው በዝግ ቀጥሎ ሲፈጸም በጋራ ፎቶ የመነሣት መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡ ከውጭ የመጡት አባቶች፣ የቅዱስ ሲኖዶስንና የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት እንዲሁም ጠቅላይ ጽ/ቤቱን፣ በሠራተኞችና በሚዲያ ባለሞያዎች ገላጭነት እየተዘዋወሩ ጎብኝተዋል፡፡

IMG_20180726_131049ከውጭ ከመጡት አንጋፋ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል የአውሮፓና የአፍሪቃ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ የተደረገላቸው አቀባበል ልዩ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልጸው አመስግነዋል፡፡ ከሀገር በወጡበት ወቅት ከነበረው ኹኔታ ጋራ በማነጻጸር፣ በከተማዋም ይኹን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብዙ ለውጦችን መታዘባቸውንና በዚህም መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሎንዶን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም፣ “ወንድሞቻችን፣ ልዩ ፍቅር አሳይታችሁናል፤” በማለት በአቀባበሉና በለውጡ የተሰማቸውን ደስታ፣ በትውውቅ ጉባኤው ላይ አካፍለዋል፡፡

“ይህች ዕለት ስንጠብቃት የነበረች ናት፤ ይህችን ቀን በማየታችን ምንኛ ዕድለኞች ነን፤” ሲሉ በተመለሰው ፍጹም የቤተ ክርስቲያን አንድነት አንክሯቸውን የገለጹት ደግሞ፣ አንጋፋው የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ናቸው፡፡የኒውዮርክና የፍኖተ ሰላም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዘካርያስም፣ “ተበትና የነበረችው ታላቋ ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድነቷ የተመለሰችበት ይህች ቀን ምን ያህል የታደለች ናት፤” ካሉ በኋላ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምልዓት እንድትጠናከር ለማድረግ አንድነቱ ጥሩ ዕድል እንደኾነና በርትተን መሥራት እንደሚገባን አዘክረዋል፡፡

ጉባኤውን በርእሰ መንበርነት የመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በንባብ ባሰሙት መልእክታቸው፣ ይህ ዐቢይ ጉባኤ፣ እግዚአብሔርንና ምእመናን የሚያስደስት፣ ለቤተ ክርስቲያን ኃይልና ብርታት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ “እግዚአብሔር በፈቀደ ከሰበሰበን ዘንድ ልናመሰግነውና አገርንና ቤተ ክርስቲያንን እየጠበቅን ልንተጋ ይገባል፤” ብለዋል፡፡ በመጪው ሳምንት ማክሰኞ፣ ነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ በምንይዘው የጾመ ፍልሰታ ለማርያም ሱባኤ፣ ጸሎትና ምሕላ በማድረግ፣ በአገልግሎቱም በአንድነት በመሳተፍ የበለጠ መበርታት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፣ ቅዱስነታቸው፡፡

የዛሬው የቅዱስ ሲኖዶስ የትውውቅ ጉባኤ ዋና አጀንዳ፣ የእርስ በርስ ትውውቅ ይኹን እንጅ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉት አህጉረ ስብከት ክልልና የአባቶች ምደባ ጉዳይ፣ በመጪው ዓመት ጥቅምት ምልዓተ ጉባኤ እንደሚታይ ተጠቁሟል፡፡ እስከዚያው ድረስ፣ ወደ ውጭ የሚመለሱት ብፁዓን አባቶች ባሉበት እየሠሩ እንዲቆዩ፣ ሱባኤውን በሀገር ቤት ቆይተው ማሳለፍ ለሚፈልጉትም ቦታ እንደሚመቻች ተገልጿል፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፣ሀገረ ስብከት ማለት በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተለይቶ የተከለለና በሊቀ ጳጳስና በኤጲስ ቆጶስ የሚመራ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ክልል ነው፡፡ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ አህጉረ ስብከት፣ በሚገኙባቸው ሀገሮች ሕገጋት መሠረት ዕውቅና አግኝተው አገልግሎታቸውን ያካሒዳሉ፡፡

በሀገር ቤቱ አስተዳደር፣ በ51 ያህል ሊቃነ ጳጳሳትና ጳጳሳት የሚመሩ 53 የሀገር ውስጥና የውጭ አህጉረ ስብከት፤ በውጩም አስተዳደር ደግሞ በ21 ያህል ሊቃነ ጳጳሳትና ጳጳሳት የሚመሩ በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪቃ፣ በካሪቢያን ደሴቶች፣ በአውስትራልያና ኒውዝላንድ ክፍላተ ዓለም የተቋቋሙ አህጉረ ስብከት እንዳሉ ይታወቃል፡፡

 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣በዛሬው የትውውቅ ጉባኤ አልታዩም፡፡ ነገ ቅዳሜ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ በሚሌኒየም አዳራሽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች በተገኙበት ሲኖዶሳዊ ዕርቀ ሰላሙ በብሔራዊ ደረጃ የሚበሠር ሲኾን፣ 30ሺሕ ያህል ካህናትና ምእመናን እንደሚታደሙበት ይጠበቃል፡፡

Advertisements

2 thoughts on “የአንድነቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የትውውቅ ጉባኤ አካሔደ፤ “ለቤተ ክርስቲያን ኃይልና ብርታት የኾነ ዐቢይ ጉባኤ ነው፤ በአንድነት ልንተጋ ይገባል”/ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ/

 1. Amanuel August 4, 2018 at 8:56 am Reply

  ውድ ሐራ ቸር ወሬ ያሰማሽ!!
  ፍቅራቸው እና መተሳሰባቸውን ለማየት ወይንም ለመስማት ጓጉተን ነበር ምክንያቱም ገና ከ Airport ሲገናኙ የሚሆኑትን ነገር ለማየት ቸኩዬ ብጠብቅ ፍቅር ፍቅር የሚል ነገር አጥቼበት ግራ ተጋብቼ ነበር ፈጽሞ ለፍቅር እንግዳ ነበር የሚመስሉት ፤

  አብያችን እና ኢሳያስ ሲገናኙ የፕሮቶኮል ጉዳይ ተረስቶ እንደ ልጅ እየተጓተቱና እየተሳሳቁ ሲታዩ የእነርሱ ሁኔታ የእኛንም ዓይን እንባ እንዲያፈስ አስገድዶት ነበር ፤በዚያ ምክንያት ነበር አባቶች ሲገናኙ ፍቅር እና ትህትናቸውን ለዓለም የሚያሳዩበትን ነገር በጉጉት እየጠበቅሁ የነበርው ፤

  ምን አልባት ያን ለማድረግም አብይ አስፈልጎ ይሆን?እንድልም አስገደደኝ ለማንኛውም በውስጥ መስመር እርስ በርስ መደጋገፉና መተሳሰቡ ከኖረ ይበል የሚያሰኝ ነው ምክንያቱም ሐራችን “ለብዙሃን መገናኛ ክፍት የነበረው የእርስ በርስ ትውውቁ ከፍተኛ የደስታ መንፈስ የታየበት እንደነበር ተገልጿል፤ ሁሉም እየተነሱ ነበር ስማቸውን የሚናገሩት፤ የፍቅር እና የመተባበር ድባብ ታይቶበታል፤ ስትል አስነብባናለችና ።

 2. ስዩም አስፋው August 10, 2018 at 2:53 pm Reply

  ውድ ሐራ እና የሐራ አንባብያን ፣ I found this article, ሰጋቱ በጣም የመያሳሰብ ይመስለኛል , check አርጉት እስኪ https://kiduszetewahido.wordpress.com/

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: