4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ ወደ ሀገራቸው ቅድስት ኢትዮጵያ ተመለሱ

IMG_20180731_145733

  • “አቤቱ፣ ወደ ጥንተ መንበራቸው መልሰህ ስላሳየህን እናመሰግንሃለን፤”

/ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/

†††

  • “ቅዱስነታቸው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የመጀመሪያውን የድልድዩን ጡብ አስቀመጡ፤”
  • “ለአንድነቷ ድጋፋችንን ለጠየቀችው የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ሓላፊነት አለብን፤”

/ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ/

†††

ዛሬ፣ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ቅዱስነታቸው ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከሰላም ልኡካኑና ከብፁዓን አባቶች ጋራ ሲደርሱ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአብያተ እምነት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶችና መንፈሳውያን ማኅበራት ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

የአሜሪካ ጉብኝታቸውን በማጠናቀቅ አብረዋቸው የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በሰጡት መግለጫ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አቀባበል ያደረጉትን ሁሉንም አካላት አመስግነዋል፡፡

“ግንቡን በማፍረስ ድልድዩን ለመገንባት” ባለመው የአሜሪካ ጉብኝታቸው፣ በሲኖዶሳዊ ዕርቀ ሰላም ዛሬ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ “የመጀመሪያውን ጡብ አስቀምጠዋል፤ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ጥረትና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፤” ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን አንድ መኾኗ፣ ደስታውና ክብሩ ለኢትዮጵያውያን ኹሉ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

በአኃት የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለው የመለያየት ችግርም ተፈቶ አንድነቷን ለመመለስ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ልጆቿ ከተሰበሰቡና የሃይማኖት ተቋማቷ ከተጠናከሩ መጻኢ ጊዜዋ ብሩህ እንደኾነም ዶ/ር ዐቢይ ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከአየር ማረፊያው መርሐ ግብር በኋላ ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያመሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በካቴድራሉ ሲደርሱ ካህናትና ምእመናን በእልልታና በዝማሬ ተቀብለዋቸዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ ወደ ሀገራቸው በመመለሳቸው ደስታቸውን የገለጹትና እግዚአብሔርን ያመሰገኑት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በካቴድራሉ ካህናት እየተከናወነ ያለውን የመርሐ ግብር መክፈቻ ጸሎተ ወንጌል እየመሩ በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

“አቤቱ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክን፣ ወደ ጥንተ መንበራቸው መልሰህ ስላሳየህን እናሰግንሃለን፤” በማለት ምስጋና አቅርበዋል ቅዱስነታቸው፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: