“የሐምሌ 11 የዋሽንግተን የአባቶች ዕርቀ ሰላም ሒደት፣ ፍጹም የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚመለስበት እንዲኾን ትጉና ጸልዩ”/የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ/

EOTC Holy Synod reconciliation Meg Ham2010

  • 4ኛውፓትርያርክ መንበሩን ለቀው ከአገር ከወጡ በኋላ ለ26 ዓመት አዝነናል፤
  • ቅዱስ ሲኖዶስ፣የሰላሙን በር ክፍት አድርጎ የሰላም ጥሪ እያስተላለፈ ቆይቷል፤
  • ከችግሩ መነሻና ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ፣ለ4 ጊዜ ልኡክ መድቦ አሜሪካ ልኳል፤
  • 3 አባቶችን የሠየመበት የአሁኑ ጥረት፣ሒደቱ እልባት የሚያገኝበት ይኾናል፤
  • የምእመናን የሰላም ጥማትና የቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ጥረት መቋጫ ያገኛል፤

†††

  • በውጤቱ፦ ፓትርያርኩና በውጭ አገር ያሉ አባቶች ወደ አገር ቤት ይገባሉ
  • ፍጹም የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ አንድነት፣ የሚመለስበት ይኾናል
  • ሃይማኖትንና ቀኖናን የሚመለከቱ ጉዳዮች፣በቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ ብቻ ይወሰናሉ፤
  • ሁሉ በጸሎት ይትጋ እንጅ፣መግለጫ መስጠት ያለበት የተፈቀደለት ብቻ ነው
  • የቅዱስ ሲኖዶሱን ውክልና ይዘው ለሚጓዙ ልኡካን አባቶች ስኬት እንተባበር

†††

የፊታችን ሐምሌ 11 ቀን ጀምሮ፣ በዋሽንግተን ዲሲ የሚከናወነው የአባቶች ዕርቀ ሰላም፣የዓመታት ሒደቱ መቋጫ አግኝቶ በውጭ ያሉት አባቶች ወደ አገር ቤት የሚገቡበትና ፍጹም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የሚመለስበት እንዲኾን፣ መላው ካህናትና ምእመናን በጸሎት እንዲተጉ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አሳሰበ፤ የልኡካን አባቶች ጉዞም የተቃና እንዲኾን ሁሉም ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪ አቀረበ፡፡

EOTC Holy Synod Hamle2010 Megየምልአተ ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ዛሬ ረቡዕ፣ ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ፣ ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለብዙኃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ፣ ከሐምሌ 11 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በውጭ ከሚገኙበት አባቶች ጋራ የሚካሔደው ዕርቀ ሰላም፣የምእመናን ልጆቻችን የሰላም ጥማትና የዘወትር ጸሎት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ የዕለት ከዕለት ጥረት ሰላማዊ መቋጫ አግኝቶ ፍጹም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የሚመለስበት እንዲኾን፣ መላው ካህናትና ምእመናን በጸሎት እንዲተጉ ምልዓተ ጉባኤው አሳስቧል፡፡

የዕርቀ ሰላም ሒደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ፣በራሱ ተነሣሽነት ከካህናትና ምእመናን የተውጣጣው የሰላም ኮሚቴ በጥቅምት 2010 ዓ.ም. ያቀረበውን ጥያቄ ተቀብሎ ሦስት ብፁዓን አባቶችን መሠየሙን የጠቀሰው ምልዓተ ጉባኤው፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውክልና ይዘው ወደ አሜሪካ እንደሚጓዙ ገልጾ፣ተልእኳቸው የተቃናና የተሳካ ኾኖ ችግሩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሁሉም ተባብሮ እንዲሠራ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

EOTC Holy Synod Hamle2010 Meg4

4ኛውን ፓትርያርክና የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትን እንዲሁም በኹለቱም በኩል የተላለፈውን ቃለ ውግዘት ጨምሮ ሊነሡ ስለሚችሉ ጉዳዮች በተመለከተ፣ በትላንትና ውሎው፣ በቋሚ ሲኖዶሱ የቀረቡለትን ባለአምስት ነጥቦች አጀንዳዎች የመከረበት ምልአተ ጉባኤው፣ መግባባት ሲደረስባቸው ዕርቀ ሰላሙ ተፈጻሚ እንደሚኾን ጠቁሟል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይዛው ስለቆየችው ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ጉዳይ በውይይቱ የሚነሣ ካለ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ብቻ እንደሚታይ አስታውቋል፡፡

የዕርቀ ሰላም ጥረቱ፣4ኛው ፓትርያርክ መንበራቸውን በመልቀቅ ከተወሰኑ አባቶች ጋራ ከአገር ከወጡበት ጀምሮ ላለፉት 26 ዓመታት ሲደከምበት የቆየ እንጅ፣ አሁን የተፈጠረ አለመኾኑን መግለጫው አውስቷል፡፡ ስለ ሒደቱም፣ በግለሰቦች የሚሰጡ መግለጫዎች አግባብነት እንደሌላቸውና ያለምንም መሰናክል ለውጤት ይበቃ ዘንድ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከሰጠው አካል በስተቀር መግለጫ መስጠት ጠቃሚ አለመኾኑን አበክሮ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል፣ የአገራችንን ወቅታዊ ኹኔታ በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ፣ በ“አዲስ መንፈስ” እየሔደች እንዳለች የገለጸው ምልዓተ ጉባኤው፣“የሕዝቡን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ ውጤታማ እየኾነ መጥቷል፤” ብሏል፡፡

አያይዞም፣ የዘመናት አንድነትና ቤተሰባዊነት የነበራቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች፣ወደ ፍጹም ሰላም እንዲመጡ እየተከናወነ ያለውን ጅምር ቤተ ክርስቲያን በእጅጉ እንደምትደግፈው አረጋግጧል፤ለመጨረሻውም ግብ የበኩሏን አስተዋፅኦ እንደምታደርግ ምልዓተ ጉባኤው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

eotc holy synod hamle2010 meg7

በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃ ለማድረግ እና ሰላምንና አንድነትን ማምጣት እንዲቻል በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተሰጠ መግለጫ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ለ2000 ዓመታት አንድነቷን፣ ዶግማዋንና ቀኖናዋን ጠብቃ የቆየች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በተለያዩ ዘመናት የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ቢፈራረቁባትም ፈተናዎቹን በመቋቋም፣ እምነቷን በማጽናት፣ ቀኖናዋንና ትውፊቷን በመጠበቅ፣ ተከታዮቿን በመምከርና በማስተማር ሀገርን ሰላም እያደረገች ኖራለች፡፡

ኾኖም በ1984 ዓ.ም. የነበሩት 4ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ከተወሰኑ አባቶች ጋራ ከአገር በመውጣታቸው ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችን ለ26 ዓመታት ተከታዮቿ ምእመናን እያዘኑ በከፍተኛ የሰላም ዕጦት ውስጥ አሳልፋለች፡፡

ይህ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የጠፋውን ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ ከችግሩ መፈጠር መነሻ ማግሥት እና ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስ በአራት የተለያዩ የስብሰባ ጊዜያት ዕርቀ ሰላሙን ለማምጣት ሊቃነ ጳጳሳትን መድቦ አሜሪካ ድረስ በመላክ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በዓመት ኹለት ጊዜያት በሚያደርጋቸው ጉባኤያት የሰላሙ በር ክፍት መኾኑን በመግለጽ የሰላም ጥሪ ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡

ይህ የምእመናን ልጆቻችን የሰላም ጥማትና የዘወትር ጸሎት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ የዕለት ከዕለት የሰላም ጥረት ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ሰላሙ መቋጫ ወደሚያገኝበት ደረጃ እንዲደርስ፣ የ2010 የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤን ተከትሎ በራሱ ተነሣሽነት ከካህናትና ምእመናን የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ ያቀረበውን የዕርቀ ሰላም ጥያቄ በአዎንታ ተቀብሎት ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የዕርቀ ሰላም ሒደት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ሠይሟል፡፡

በዚሁ መሠረት፣ ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአባቶች መካከል የሚካሔደው የዕርቀ ሰላም ሒደት ፍጻሜ የሚያገኝበት፣ በውጭ አገር የሚገኙ አባቶች ወደ አገር ቤት የሚገቡበት፣ ፍጹም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የሚመለስበት እንዲኾን፣ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ካህናትና ምእመናን በጸሎት እንድትተጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ መንፈስ እየሔደችበት ያለው የሕዝቡን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ ውጤታማ እየኾነ መጥቷል፡፡

ከዚሁ ጋራ ለዘመናት አንድነትና ቤተሰባዊነት የነበራቸው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝቦች ወደ ፍጹም ሰላም እንዲመጡ እየተከናወነ ያለው ጅምር፣ ቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ የምትደግፈውና ለመጨረሻውም ግብ የበኩሏን አስተዋፅኦ የምታደርግበት ይኾናል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በአኹኑ ጊዜ በውስጧ የሚገኙ ችግሮቿን ከጥንት ጀምሮ ይዛው በቆየችው ትዕግሥትና የሰላም ሒደት በቀኖናዋ መሠረት የምትፈታው ሲኾን፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን በብቃት የምታከናውንበት አቅጣጫ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቀምጧል፡፡

በቀጣይ ወቅቱንና ዘመኑን በዋጀ መልኩ፣ መልካም አስተዳደርን በቤተ ክርስቲያናችን ካለፈው በበለጠ ማስፈን እንዲቻል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች ሊፈታ ያስችላል፤በሚል በባለሞያዎች የተዘጋጀውን መሪ ዕቅድና ከአሁን በፊት የተጠኑ ጥናቶች በተግባር ማዋል እንዲቻል፣ ጥናቶቹ ለ2011 ዓ.ም. የጥቅምት ምልዓተ ጉባኤ ዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ኾኖ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

አሁን በቤተ ክርስቲያናችን አባቶች መካከል የተጀመረው ዕርቀ ሰላም ያለምንም መሰናክል ለውጤት ይበቃ ዘንድ፣ ዕርቀ ሰላሙን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከሰጠው አካል በስተቀር መግለጫ መስጠት ጠቃሚ አለመኾኑን ምልዓተ ጉባኤው አበክሮ ያሳስባል፡፡

በዕርቀ ሰላሙ ሒደት በሚደረገው ማንኛውም ውይይት የነበረውንና ቤተ ክርስቲያናችን ይዛው የቆየችውን ቀኖና በተመለከተ፣ ውይይቱም ኾነ እይታው በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ብቻ የሚታይ ይኾናል፡፡

አሁን ለተጀመረው የዕርቀ ሰላምና አንድነት መገኘት፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን ውክልና ይዘው ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ብፁዓን አባቶች፣ ጉዟቸው የተቃናና የተሳካ ኾኖ ችግሩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሁላችንም ተባብረን እንድንሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለአገራችንና ለሕዝባችን ሰላሙን ይስጥልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: