የቅ/ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ በዐበይት ወቅታዊ ጉዳዮች ይወያያል፤ ፓትርያርኩ፣ ብፁዕ አባ አረጋዊን ያለሕጉ በረዳትነት መደቡ፤ምልአተ ጉባኤው ይመረምረዋል

 • በሙስናና ዘረኝነት ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ፤
 • የሲኖዶሳዊው ዕርቀ ሰላም ንግግር ቅድመ ዝግጅት፤
 • የመማክርት ጉባኤ/ሕዝባዊ ሲኖዶስ?/ስለማቋቋም፤
 • የአ/አበባ ሀ/ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ አጀንዳዎች ናቸው፤

†††

ለነገ ማክሰኞ፣ ሐምሌ 3 ቀን 2010 ዓ.ም.የተጠራው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ፣ በቤተ ክርስቲያናችን አንገብጋቢና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገር ተጠቆመ፡፡

ቀደም ሲል በቀረበው ዘገባ፣ አስቸኳይ ስብሰባው የተጠራው፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ ጉዳይ እንደኾነ ቢገለጽም፣ ከዚያም በላይ ትኩረት በሚሹ ሦስት አንገብጋቢና ወቅታዊ አጀንዳዎችም እንደሚነጋገር፣ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባው የተጠራው፣ በቅርብ አካባቢ ያሉና ጥሪ የተደረገላቸው ብፁዓን አባቶች ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት ጋራ በመኾን ባለፈው ሳምንት ዓርብ ባካሔዱት ስብሰባ በተደረሰበት ስምምነት ሲኾን፤ የመነጋገሪያ ነጥቦቹም፡-

 • ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሙስናን/ሌብነትንና ዘረኝነትን በተመለከተ ለሃይማኖት ተቋማት ያስተላለፏቸው መልእክቶች፤
 • ከሐምሌ 12 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ ስለሚካሔደው ሲኖዶሳዊ ዕርቀ ሰላም በመደረግ ላይ ስላለው ቅድመ ዝግጅትና አቀባበል፤
 • ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የኾነ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምሁራን የሚገኙበት የመማክርት ጉባኤ እንዲቋቋም ስለቀረበው ሐሳብ፤
 • የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ለኾነው አዲስ አበባ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚቀርበውን ረዳት ሊቀ ጳጳስ መመደብ የሚሉት ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ፓርላማን ጨምሮ በተለያዩ የብዙኃን መድረኮች ባስተላለፏቸው መልእክቶች፦ የሃይማኖት ተቋማት የሞራል ልዕልና እንዲያሰፍኑ እንጂ የሌብነት ምሽግ መኾን እንደሌለባቸውና እንደማይችሉ በመግለጽ ለሕዝብና ለመንግሥት ምሳሌ እንዲኾኑ አሳስበዋል፡፡ “ከሙስና እና ዘረኝነት ርቃችሁ ድኃ ተበደለ፤ ፍርድ ተጓደለ በሉ”፤ “ከፍተኛ ሌብነት በውስጣቸው አለ፤ ኦዲት አይደረጉም“፤ “በውስጣችሁ የተሰገሰገውን የሌብነት ድር በመበጣጠስ ለመንግሥትም ለሕዝብም የሞራል አስተማሪነታችሁን አሳዩ”፤ “መባውና ዘካው የሕዝብ ሀብት እስከኾነ ድረስ መንግሥት አጠቃቀሙን ይቆጣጠራል” የሚሉና የመሳሰሉት ከመልእክቶቹ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ይኸው መልእክት ዘልቆ የተሰማቸው ብፁዓን አባቶች፣“ለምን ዝም እንላለን? ብዙ ችግሮቸ አሉ፤ በፓርላማ ሳይቀር ሙስና፣ዘረኝነት እየተባለ ነው፤ ተነጋግረን ለምን አንድ ነገር አናደርግም፤” በሚል በቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ ባነሡት ሐሳብ፣ ቤተ ክርስቲያን አቋሟንና ምላሿን በይፋ እንድትገልጽ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መልእክት በፊትና ባሻገር፣በተለይ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ምእመናንና ወጣቶች፣ ሌባ የአጥቢያ አለቆችንና የጽ/ቤት ሓላፊዎችን በማባረርና ቢሮዎችን በማሸግ በሕግ ተጠያቂ እንዲኾኑ፤ የተጠናው የመዋቅርና የአሠራር ለውጥ እንዲዘረጋ እያቀረቧቸው ያሉት አቤቱታዎች፣ ውለው አድረው ያልተፈለገ መልክ ከመያዛቸው በፊት ኹነኛ ምላሽ እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡

“ባይኾን እስከ አኹን ይህን ይህን አድርገናል፤ በቀጣይ ደግሞ አሠራራችንን ፈትሸን አስተዳደራችንን እናስተካክለን ማለት ይገባናል፤” ያሉ ብፁዓን አባቶች፣ እየተነገረ ያለውን ዝም ካልን፣በደፈናው አመንን፣ ተቀበልን ማለት እንዳይኾን አስገንዝበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ጉዳዩ፣“ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን አንገብጋቢ ችግሮች” በሚል እንዲያዝ መግባባት ላይ ተደርሶበታል፡፡

ሲኖዶሳዊው የዕርቀ ሰላም ሒደት ሌላው አጀንዳ ሲኾን፣ልኡካን አባቶች፣ሐምሌ 11 ቀን ወደ ሥፍራው ከማምራታቸው በፊት ሲደረግ የቆየውን ቅድመ ዝግጅት እንደሚገመግም ተጠቅሷል፡፡ የግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ባስቀመጠው መርሖና አቅጣጫ መሠረት፣ በቋሚ ሲኖዶስ የተቋቋመው አካል ያዘጋጀው የልኡካኑ የመነጋገሪያ ነጥብና ውይይቱ የሚመራበት ደንብ የግምገማው አካል ነው፤ተብሏል፤ “ለሚመጡት አባቶች ምን እናድርግ?” የሚለውንም ሊጨምር ይችላል፤ ብለዋል ምንጮቹ፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ አካል የኾነ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምሁራን የሚገኙበት የመማክርት ጉባኤ እንዲቋቋም ሐሳብ መቅረቡን የጠቆሙት ምንጮቹ፣ በነገው አስቸኳይ ስብሰባ ምክክር ሊደረግበት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የ1991 ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ለማሻሻል በ2007 ዓ.ም.በተዘጋጀው ረቂቅ ውስጥ ሐሳቡ ተነሥቶ እንደነበርና በማጽደቁ ሒደት ቀሪ መደረጉን በቅርቡ ግን፣“ሕዝባዊ ሲኖዶስ” በሚል በቀረበ የዶ/ር ዘሪሁን ሙላቱ ጽሑፍ መነሻነት ዳግም መወያያ እንደኾነ ተመልክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ መመደብ፣ የአስቸኳይ ምልአተ ጉባኤው አራተኛ አጀንዳ የነበረ ቢኾንም፣ ፍጹም ሕገ ወጥነት በታየበት አካሔድ፣ ፓትርያርኩ የመረጧቸውን ብፁዕ አባ አረጋዊን፣ በልዩ ጽ/ቤታቸው ባወጡት ደብዳቤ መድበው፣ በዛሬው ዕለት ወደ ሀገረ ስብከቱ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ የቅዱስነታቸው ድርሻ መርጠው ማቅረብ እንጅ መመደቡ የምልአተ ጉባኤው ሥልጣን እንደኾነ፣ባለፈው ዓርብ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ሕጉን ጠቅሰው በተደጋጋሚ ያሳሰቧቸውን በመተላለፍ ነው፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ ወደ ሀገረ ስብከቱ አዳራሽ አጅበው በመውሰድ አቀባበል እንዲደረግላቸው ያዘዙት፡፡

“ጳጳስ በቋሚ ሲኖዶስ አይመደብም፤ ምንም ልዩ ሀገረ ስብከትዎ ቢኾንም ለምልአተ ጉባኤ ማቅረብ ይኖርብዎታል፤ ለሚመደቡትም አባት በምልአተ ጉባኤ ቢኾን ነው የሚሻለው፤” በማለት በተደጋጋሚ ቢመከሩም፣ ትላንት በልዩ ጽ/ቤታቸው ባወጡት ደብዳቤ፣ የውጭ ጉዳይ መምሪያውን ጳጳስ ብፁዕ አባ አረጋዊን ያለሕጉ መድበዋቸዋል፡፡ ከዛሬው የቀትር በኋላ የአቀባበል መርሐ ግብር ቀደም ሲል፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤቱ ምክትል ጸሐፊዎች አንዱን ጠርተው ቃለ ጉባኤ እንዲያዘጋጅ በማድረግ አባላቱን እንዲያስፈርምበትና ምደባው በቋሚ ሲኖዶስ እንደተወሰነ ለማስመሰል ቢሞክሩም፣ በዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተቃውሞ እንዳልተሳካላቸው ተገልጧል፡፡

ለፓትርያርኩ ጥድፊያ የተለያዩ መላምቶች በመሰንዘር ላይ ቢኾንም፣ ሥራ አስኪያጁ መ/ር ይቅርባይ እንዳለ፣ በተደረገላቸው የአቀባበል መርሐ ግብር ላይ፣ “ደላሎች ይውጡ፤ የፈረጅያ ሥር ኑፋቄ ይቁም፤ መናፍቅ የቤተ ክርስቲያንን እንጀራ አይብላ” በማለት ያስተላለፉት ግልጽ መልእክት ደስ እንዳላሰኛቸው ተጠቁሟል፡፡ “የመልእክቱን ቅጅ እንደሰሙ፥ ጉድ ሠራኝ፤ ሥራ ሳይጀምር እንደልብ የሚታዘዘኝ ረዳት ጳጳስ ቶሎ ልሹምበት፤” ማለታቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ምደባቸው ያለሕጉ እንደኾነ ቢያውቁም፣ “ታዝዤ ነው” በሚል ሰበብ የተቀበሉትን ብፁዕ አባ አረጋዊንም ለትዝብት ዳርጓቸዋል፡፡ “ሥራ አስኪያጁ ብቻውን ከኾነ አያሠራንም፤ ይጨርሰናል፤” ሲሉ የሰነበቱት ጥቂት የማይባሉ የአለቃና የጸሐፊ ሌቦችና ደላሎች፣የረዳት ሊቀ ጳጳሱን ምደባ ሲሰሙ ጮቤ ረግጠዋል፤ “ኹለቱን አጣልተን የሥራ አስኪያጁን ስም በማጥፋት ዕድሜውን/ቆይታውን እናሳጥራለን፤” በማለት የተለያዩ ተንኮሎችን ከወዲሁ እየሸረቡ እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡

ያም ኾነ ይህ፣ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅና የማስጠበቅ ተግባርና ሓላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ነገ ማክሰኞ፣ ሐምሌ 3 ቀን ጠዋት 3፡00 ላይ በሚጀምረው አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባው፣ ከላይ በጠቀሱት ዐበይት ወቅታዊ አጀንዳዎችና “በልዩ ሀገረ ስብከት” ሽፋን እየታየ ያለውን የፓትርያርኩን ሕግ ተላላፊነት መርምሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

Advertisements

One thought on “የቅ/ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ በዐበይት ወቅታዊ ጉዳዮች ይወያያል፤ ፓትርያርኩ፣ ብፁዕ አባ አረጋዊን ያለሕጉ በረዳትነት መደቡ፤ምልአተ ጉባኤው ይመረምረዋል

 1. Amanuel July 10, 2018 at 7:22 am Reply

  ሿሚውም ተሿሚውም የቀደመ (የቅርብ) ታሪካቸውን ካስታወስን ብዙም አንደነቅም፤ በተደጋጋሚ እንደምንለው ፓትርያርክ ማትያስ በማን ፈቃድ እና ለምን ዓላማ ተሾሙ? የሚለውን ካልዘነጋን ነጥቡ ላይ እንደርሳለን ። መድገም ካስፈለገም :– ቅድስት ቤተክርስትያናችን ደገኞች ፣ ትጉሃን ፣ ቀናዒያን እና መንፈሳውያን ብጹዓን አባቶችን ያጣች ይመስል ጎጠኛው ሰው አባ ማትያስን ፓትርያርክ ይሆኑ ዘንድ ሊያግባባ እና ሊያሳምን ኢየሩሳሌም ድረስ የሄደው ቡድን ማን ዓላማውን እንደሚያስፈጽምለት በደምብ ስለሚያውቅ ነው ።
  ይሄ መሳሳብ ድንገት የተከሰተም አይደለም። የህወሃት ጉምቱ መሪዎች በሚሰጧቸው መመሪያ መሰረት ሲሰሩ የቆዩትን ነው አሁንም የደገሙት ምክንያቱም ለፓትሪያርክ ማትያስ በወንዜነት እና በዓላማ ከአባ አረጋዊ በላይ ማን ቅርብ አለ? በቅርቡ እንኳ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አመራሮች ሲመጡ ዶግማ እና ቀኖና ጥሰው በሰዓሊተ ምህረት ቤተክርስቲያን ከመናፍቃኑ ጋር በሚስጢር ሲቀባቡ በመገለጣቸው ያላዘነ ኦርቶዶክሳዊ ያለ አይመስለኝም ።

  አሁን ደግሞ ሿሚውም ተሿሚውም የስህተት ታሪካቸውን መድገማቸው እና ራሳቸውን ከቅዱስ ሲኖዶስ በላይ አድርገው መገደራቸው የትዕቢታቸውን ልክ ያሳዩ ይሆናል እንጂ የትም እንደማይደርሱ ቢያንስ ወቅቱ ይመክራቸዋል ።

  በሌላም ካየነው ሌላው ወዳጃቸውን ጎርጎርዮስን ማንሳት ተገቢ ይሆናል ሰውየው እዚህ ብቅ ሲሉ የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ለመምሰል ሲሞክሩ በሃ/ስብከታቸው ግን የሚሰሩት አሻጥር አፍ አውጥቶ ይናገራል።

  ባሁኗ ሰዓት እንኳ የልብ ወዳጃቸው ከሆነውና በቅርቡ ከእስር ከተፈታው ሁከተኛው እና ተንኮል የዘለዓለም ቤቷ ካደረገችው ሰው ጌታቸው ዶኒ ጋር ሆነው ሰላም አግኝታ የነበረችውን የመቂ ቤተክርስቲያንን ለማወክ እውነተኞች አገልጋዮችን እየነቀሉ አረሞቻቸውን መትከል መጀመራቸው የሰዎቹ ጥፋት የማያንቀላፋ ወሆኑን በግልጽ ያሳያል።

  ስለዚህ አባ ማትያስ እንዲህ መሆናቸው ሊገርም ባይገባም በቃዎት መባል ይገባቸዋል ። ሌባም ተቀባይም ያው ሌባ ናቸውና ሿሚውም (አባ ማትያስ) ተሿሚውም (አባ አረጋዊም) የሚሄዱበት መንገድ ወደገደል ነውና ብቻቸውን እንዲገቡበት ማድረጉ ይበጃል ።

  የሰሞኑ ጭምጭምታ እና ሹክሹክታ ደግሞ በቅርቡ ስልጣኔን እለቃለሁ የምትል ነገር አላት አሉ አንቱ ሰው ይህን ነገርዎን መች ነው የሚተውልን የዛሬ ዓመት አካባቢም እለቃለሁ ብለው አጓጉተውን ሰፍ ብለን ስንጠብቅ ጭራሽ አጥብቀው ይዘውት ይኸው ያምሱናል ።
  በእርግጥ ያሁኗ ከቀድሞው ትለያለች አሁን “እርቀ ሰላም ” የሚባል ለእርስዎ ውጋት ለቅድስት ቤተክርስቲያን ደግሞ ከፍታ የሆነ ታላቅ ነገር እየመጣ ነውና በምን የሞራል ብቃት እዚያ እርቅ ላይ ይቆማሉ? ስለዚህ እንደመንቻካ ሰይጣን እለቃለሁ እያሉ መልሰው አይጣበቁብን ባይሆን ምሥዎን ጎይቶም ያይኑ በሚገባ አዘጋጅቶዎልዎታልና በፍጥነት ይልቀቁ ፤ ካህን በሞላበት ሀገር እስካሁን አለመልቀቅዎም ይገርማል! !

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: