ጠቅላይ ሚኒስትሩ: ሊቁ መሪጌታ እንደሥራቸው አግማሴ ከእስር የሚፈቱበትን አመራር እንዲሰጡ ፓትርያርኩ ጠየቁ

pat abune mathias request to pm abiy

  • በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ አላግባብ ለሚደርሰው ችግር አስረጅ ናቸው
  • ሊቁን መሪጌታ መፍታት፣ የቤተ ክርስቲያንን ቅርስ መጠበቅና መታደግ ነው
  • ሞያቸውን ለትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላቸዋል፤ /ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ/
  • 24 ዓመት በእስር ቤት ማሳለፋቸው ከፍተኛ ችግር ነው፤ /ፓትርያርኩ/

†††

pat request to endeserachew release

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የዜጎች መብት መጠበቅን ተቀዳሚ አጀንዳቸው በማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በታላቅ አድናቆት እንደምትመለከተው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የገለጸች ሲኾን፤ ላለፉት 24 ዓመታት ታስረው የሚገኙት የተክሌ አቋቋም ሊቁ መሪጌታ እንደሥራቸው አግማሴ እንዲፈቱ የሚያስችል አመራር ለሚመለከተው አካል እንዲሰጥላት ጠየቀች፡፡

 

958778802በሀገራችን ተከማችቶ የቆየውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየቦታው እየተዘዋወሩ የሚሰጡት አመራር፣ ከበጎቹ አንዲቱ እንድትነካ ከማይፈልግ መልካም እረኛ ጋራ ያመሳሰሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ ከ1986 ዓ.ም. ሐምሌ 12 ቀን ጀምሮ ላለፉት 24 ዓመታት ደብዛቸው ጠፍቶ በእስር ቤት የቆዩትና በሕይወት የመኖራቸው ዜና በቅርቡ የተሰማው ሊቁ መሪጌታ እንደሥራቸው አግማሴ ከእስር የሚፈቱበትን አመራር ለሚመለከተው አካል እንዲያስተላልፉ፣ በቤተ ክርስቲያን ስም አሳስበዋቸዋል፡፡

በመሪጌታ እንደሥራቸው አግማሴ በድንገት ታፍነው ከመወሰዳቸው በፊት፣በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በተለያዩ የሓላፊነት ቦታዎች ላይ በማገልገል ላይ የነበሩ የድጓ፣ የተክሌ አቋቋምና የቅኔ መምህር እንደነበሩ ቅዱስነታቸው በደብዳቤአቸው ያስታወሱ ሲኾን፤“ከግንዛቤ ጉድለትም ይኹን በሌላ ምክንያት” በቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን በደል እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡

ሊቁ፣ በሕይወት የመኖርና ያለመኖራቸው ጉዳይ ሳይታወቅ 24 ዓመታትን በእስር ቤት ማሳለፋቸውን፣ “ከፍተኛ ችግር” በማለት ነው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የገለጹት፡፡የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ስለጉዳዩ ያስታወቁበትን 2 ገጽ ደብዳቤ በአባሪነት ያያዘው ይኸው የቅዱስ ፓትርያርኩ ጥያቄ፣ ያለው ዝርዝር ኹኔታ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታይቶ፣ መሪጌታ እንደሥራቸው አግማሴ ከእርስ ቤት እንዲወጡ/እንዲፈቱ የሚያስችል አመራር ለሚመለከተው ክፍል እንዲተላለፍ በቤተ ክርስቲያን ስም አሳስቧል፡፡

his-grace-abune-elsaቀደም ሲል፣ ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ፣ ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን ቅርስ፤ የቤተ ክርስቲያናችን ኮከብ፤ ታላቁ ሊቅ፤በማለት የገለጿቸው መሪጌታ እንደሥራቸው አግማሴ፣ የታሰሩበት ቦታ ተጣርቶ ከእስር ይፈቱ ዘንድ ፓትርያርኩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ይጠይቁ ዘንድ ግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፉላቸው ደብዳቤ አመልክተዋል፡፡ ከእስር ተፈትተው ቀሪ ዘመናቸውን ከቤተሰዎቻቸው ጋራ በመኾን አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉ፥ ታላቁ ሊቅ ሞያቸውን ለትውልድ እንዲያስተላልፉ ከማስቻሉም ባሻገር ለተክሌ አቋቋምና ለሌሎች የምስክር ቤቶች ማደግና መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው፣ብፁዕነታቸው አስረድተዋል፡፡

ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ባደረሱት ደብዳቤ፣ በየቦታው እየተዘዋወሩ ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ የቆዩ ወገኖቻችን እየተፈቱ ከቤተሰዎቻቸው ጋራ እንዲገናኙ ማድረጋቸው፣ የሀገርን ሰላም ከማረጋገጡም በላይ ኢትዮጵያ ወደፊት ብሩህ ተስፋ እንዳላት ያሳያል፤ ብለዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዕንቁ የኾኑትን መሪጌታ እንደሥራቸው አግማሴን መፍታትም፣ ቅርስን መጠበቅና መታደግ እንዲሁም ጥንታዊትና ታሪካዊት የኾነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ማጠናከር በመኾኑ፣ የታሰሩበት ቦታ ተጣርቶ እንዲፈቱ ጠይቀዋቸዋል፡፡

የሊቁ መሪጌታ እንደሥራቸው አግማሴ መኰንንን ከእስር መፈታት በመጠየቅ ባለፈው ቅዳሜ፣ የበየነ መረብ ዘመቻ የተደረገ ሲኾን፣ አኹንም በተለያየ መልክ ቀጥሎ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት በፋርጣ ወረዳ ሥር በሚገኘው በደብረ ሰላም ሰላምኮ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የተወለዱት መሪጌታ እንደሥራቸው፣ በቅድስት ቤተ ልሔም ድጓን፤ በደብረ ታቦር ኢየሱስ ደግሞ የተክሌን አቋቋም አስመስክረዋል፡፡

“እግዚአብሔር ከማያልቅበት ሀብቱ አብዝቶ አምልቶ የሰጣቸው፣ ይህ ቀረህ የማይባሉ ታላቅ መንፈሳዊ ሊቅ፣ የተክሌውን አቋቋም ሲዘሙ የሰውን ልቡና የሚመስጡ እና ሰማያዊ መልአክ የሚመስሉ ዓለም የሚያውቃቸው ታላቅ ምሁር ናቸው፤” ሲሉ መስክረውላቸዋል ብፁዕነታቸው – ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በታታሪነትና በቅንነት በማገልገል ላይ ሳሉ በድንገት ታፍነው ለ24 ዓመታት በእስር ደብዛቸው እንዲጠፋ በመደረጉ፣ ቤተ ሰዎቻቸውን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝብን እያሳዘነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

ንቦችን በዜማው ያወረዱ ታላቁ የተክሌ አቋቋም ሊቅ መምህር እንደሥራቸው አግማሴ መኰነን አጭር የሕይወት ታሪክ

ከአባታቸው ከአቶ አግማሴ መኰነን ከእናታቸው ወ/ሮ ሙሉነሽ ዓይናለም፣ በ1939ዓ.ም. ሚያዚያ 23 ቀን በደብረ ታቦር ልዩ ስሙ ሰላምኮ በተባለ ቦታ ተወለዱ፡፡ በዚህም የተነሳ አምኃ ጊዮርጊስ ተባሉ፡፡

በወላጆቻቸውና በዘመድ አዝማዶቻቸው በጣም ብርቅና ድንቅ የኾኑ ልጅ ነበሩ፡፡ እኒህ ምሁር ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በአካባቢያቸው ከነበሩ መምህር አባ ባያፈርስ፣ ከመርሻ ዓለሙ ጋር ከፊደል እስከ ፆመ ድጓ ተምረዋል፡፡ ፀዋትዎ ዜማ፥ ከአለቃ ማኅተም ጌጠየ ተምረዋል፤ ቅኔ፥ ወረታ አካባቢ ከሚገኙት መሪጌታ ጌቴ ተምረዋል፡፡ አሁንም ሁለተኛ ቅኔ፥ ከመምህር ጥበቡ ተምረዋል፡፡ የተክሌ አቋቋም፥ ከአለቃ ማኅተም ጌጤ ተምረዋል፡፡ ይህን ካወቁ በኋላ እንደገና ድጓ ቤት አዛወር ኪዳነ ምሕረት አዋቂ ከኾኑት ትልቅ መምህርት መሪጌታ ጀንበር ገብተው ካወቁ በኋላ፣ ከታች ጋይንት ወረዳ በኢትዮጵያ ብቸኛዋ የድጓ ምስክር ቅድስት ቤተ ልሔም ገብተው፣ የድጓ ምስክራቸውን ከምሕርት ጥበቡ አስመስከረው የድጓ መምህር ኹነዋል፡፡

ሊቁ መምህር እንደሥራቸው ድጓን አስመስክረው ከተመረቁ በኋላ በደብረ ታቦር ኢየሱስ የተክሌ አቋቋም ምስክር ከኾኑት ከአለቃ ቀለመ ወርቅ ይማም ጥሩ አድርገው ተምረው አስመስክረዋል፡፡ መምህር እንደሥራቸው ቃለ እግዚአብሔርን በማሕሌት በሚዘምሩበት ጊዜ ከልሳናቸው ጣፋጭነት የተነሳ የሰሚውን ልቡና ይማርኩ ነበር፡፡ በቅድስት ቤተ ልሔም በዐቢይ ጾም ዝማሜ ይሰጥ የነበረው ለመምህር እንደሥራቸው ነበር፡፡ መምህር እንደሥራቸው ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጸሎተ ሃይማኖትን በዝማሜ በሚዘምሩበት ጊዜ ንብ ከእጃቸው ላይ ያርፍባቸው ነበር፡፡

ወደ ጎንደርም ከመጡ በኋላ በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ለማንም የማይሰጠው የተክሌ ዝማሜ ለመምህር እንደሥራቸው ይሰጥ ነበር፡፡ ጎንደርም በነበሩበት ጊዜ የሐዋርያ ጳውሎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሥራ አስኪያጅ፣ የካህናት የታሪክ፣ የሒሳብና የዜማ መምህር በመኾን ሰፊ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡ በዓለማዊውም ሥራቸው ደግሞ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ዋና የአስተዳዳር ክፍል ኾነው አገልግለዋል፡፡

እነኾ በምእመኑ እንደተናፈቁ፤ በጳጳሳቱ፣ በሊቃውንቱ፣ በካህናቱ እንደ ተደነቁ እንቆቅልሽ ኹነው ጠፉ፡፡

ሐምሌ 12 ቀን 1986 ዓ.ም. 11፡35 አካባቢ ሲሠራበት ከነበረው ኪቢአድ ቢሮ ከሥራ ቆይቶ ሲመለስ በህወሓት/ኢሕአዴግ/ ተላላኪዎች በመኪና ታፍኖ ተወሰደ፡፡ በወቅቱ ከእርሱ ጋር ሌሎች የታፈኑ ሰዎች የነበሩ ሲኾን፣ በጎንደር ራስ ግንበ ተብሎ ከሚጠራበት ቦታ ሥር በሚገኘው ማሠቃያ ቦታ ከሌሎች ታሳሪዎች ጋር እንዲሠቃይ ተፈረደበት፡፡ የታሰረበት ምክንያት ምን እንደኾነ ሲጠይቅ፣ በወቅቱ የቆሰለ የደርግ አመራር አሳክመሃልየሚል ምላሽ ተሰጠው፡፡ እርሱም ታዲያ ማሳከም ምንድነው ጥፋቱ፤ ሰው ካጠፋ ለምን በሕግ አይጠየቅም፤” በማለት ምላሽ ሰጠ፡፡ አሳሪዎቹም፣ ሥልጣን እንስጥህ፤ ሕዝቡም ካህናቱም ይቀበሉሃል፤” በማለት ድለላ አቀረቡለት፡፡ እርሱም፣ኢትዮጵያን ከሚከፋፍል ቡድን ኅብረት የለኝምብትፈልጉ ግደሉኝ፤” አለ፡፡ ብዙ ሥቃይ አበዙበት፡፡

ከሦስት ቀናት በኋላ ቤተሰቦቹ ጭንቀት ውስጥ ስለወደቁ፣ “የእስር ቤቱ ጠባቂ ያውቀው ስለነበር፣ማታ ማታ የታሰረበትን ሰንሰለት እያላላለት፤በቆራጣ ወረቀት መታሰሩንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንደተገደሉ፣ከእርሱ ላይ ሲደርስ ግድያ አቁሙ የሚል ትእዛዝ መድረሱን ጠቅሶ መልእክት በእስር ቤት ጠባቂው በኩል ላከ፡፡ በወቅቱም ባለቤታቸውና ትልቅ ልጁ ለማስፈታት ጥረትም ቢያደርጉ የሚሰማቸው አካል ዐጡ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የት እንደተወሰደ ሳይታወቅ እንቆቅልሽ ኾኖ ቀረ፡፡ ኾኖም ከ24 ዓመታት በኋላ በሕይወት እንደሚገኝ ተነገረ፡፡ አምኃ ጊዮርጊስ ዛሬም በትግራይ ከሚገኙ እስር ቤቶች በአንደኛው ውስጥ ይገኛል፡፡

በደብረ ታቦር አሁን ድረስ የእንደሥራቸው ዜማ” እየተባለ በተክሌ ዝማሜ ውስጥ ይገኛል፡፡ ለዚህም አሁን በቦታው ያሉት መምህር ምስክር ናቸው፡፡ መቋሚያ ይዞ ሲዘም እንኳን ሰውን ንቦችንም ይመስጣል፡፡ ድምፁ ልዩ ነው፡፡ መቋሚያ አጣጣሉ ልዩ ነው፡፡ ከበሮ አመታቱ ልዩ ነው፡፡

መምህር እንደሥራቸው፣ የተክሌ አቋቋሙ ዜማ ከጊዜ በኋላ ቢጠፋ ወይም እኔ አንድ ነገር ብኾን ብለው 9 ካሴት የሚኾን ዝማሜ በካሴት ቀርፀው አስቀምጠዋል፡፡

ስለ መምህር እንደሥራቸው፥ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ – የሊቃውንት ጉባዔ ሰብሳቢ/በወቅቱ ጓደኛ የነበሩ/፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ – የሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ – በወቅቱ የጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በኋላ ፓትርያርክ፣ ክቡር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኰነን የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባዔ መምህር የነበሩት አሁን በሕይወተ ሥጋ የሌሉት፣ ክቡሩ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ ሐዲስ የጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም የአራቱ ጉባዔ መምህር፣ መልአከ መታቦር ኃይለ ኢየሱስ የደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና በጎንደር የሚገኙ ታላላቅ ሊቃውንት ቢያነሱም አይጠግቡም፡፡ ያለቅሳሉ፤ያነባሉ፤ይቆጫሉ፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን የማዳከምና የማጥፋት አንዱ የአገዛዙ ዘዴ፣ ብርቅዬ ሊቃውንትን በዚህ መንገድ ድምፃቸውን በማጥፋት ተስፋ ለማስቆረጥ መጣሩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ ማኅበረ ቅዱሳን በአንድ ወቅት ደብረ ታቦር ኢየሱስ ላይ በነበረው የቴሌቪዝን መርሐ ግብር፣ የመምህር እንደሥራቸው ስም ከዜማ ጋር ተያይዞ በሰፊው ይነሣ ነበር፡፡

የአገዛዙ አፋኞች፣ የቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ሊቅ የነበሩትን አፍነው ድምፃቸውን ለ24 ዓመታት አጥፍተዋል፡፡ዛሬም በህወሓት እስር ቤት ውስጥ መከራ እየተቀበሉ ይገኛሉ፡፡ የእርሳቸው መመለስ በቤተ ክርስቲያናቸውን የአብነት ትምህርት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል፡፡ መምህር እንደሥራቸው 2 ሴት ልጆችና 7 ወንድ ልጆች አሏቸው፡፡ ባለቤታቸውም ንግሥት ተፈራ ይመር ይባላሉ፡፡

የልጆቻቸው ስም፡- ትርሲት፣ ጥሩዓለም፣ ኪዳኔ፣ ቢራራ፣ ቶማስ፣ ሐሤት፣ በፈቃዱ፣ አናሲሞስ እና በርናባስ እንደሥራቸው ይባላሉ፡፡

ልዩ ልዩ ያስመሰከሩባቸው የትምህርት ዓይነቶች(የቅኔና የተክሌ አቋቋም የአገልግሎት ምስክር ወረቀት)

ታስረው ለቤተሰቦቻቸው የላኩላቸው መልእክት

 

ምንጭ፡- ቤተሰቦቻቸው ለጡመራ መድረኩ የላኩት

Advertisements

One thought on “ጠቅላይ ሚኒስትሩ: ሊቁ መሪጌታ እንደሥራቸው አግማሴ ከእስር የሚፈቱበትን አመራር እንዲሰጡ ፓትርያርኩ ጠየቁ

  1. Hailu June 13, 2018 at 10:45 pm Reply

    Egziabhere yasfetachew. Talaqe semaetenet new.. Yedoqltianos zeroch betechrstianen 40 amet aseqayat. Egzeabeher feraje new lehulum endeseraw yekeflewal.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: