ጸሎተኛው እና ተኀራሚው ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ ዐረፉ

ሥርዐተ ቀብራቸው፥ነገ ሰኔ 5፣በ8 ሰዓት በሐዋሳ ደ/ምሕረት ቅ/ገብርኤል ገዳምይፈጸማል
• ከመሠረት እስከ ፍጻሜ፣ካህናትንና ምእመናንን እያስተባበሩ ያሠሩት መታወቂያቸው ነው
ለሦስት ዐሥርት ዓመታት፣ የተሾሙበትን የሲዳሞ ሀገረ ስብከት አረጋግተው መርተዋል
• በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ጸሎተ ፍትሐት ሲደረግ አድሯል፤

†††

his grace abune bertelomewos

የቀድሞው የሲዳሞ ሀገረ ስብከት እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ(ከጥቅምት 4 ቀን 1919 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም.)

የተሾሙበትን የሲዳሞ ሀገረ ስብከት፣ለሦስት ዐሥርት ዓመታት ያህል አረጋግተው በመምራት የሚታወቁት ጸሎተኛውና ተኀራሚው ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ ሊቀ ጳጳስ፣ትላንት እሑድ፣ ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት፣12:00 ገደማ፣በዕርግና በቆዩበት የመንበረ ፓትርያርክ መኖርያቸው ዐርፈዋል፡፡

አስከሬናቸው፣ወደ መንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ሲደረግ አድሯል፤ በዛሬው ዕለትም፣ ሥርዐተ ቀብራቸው ወደሚፈጸምበት ወደ ሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም፣ከቀኑ 5:00 ላይ አሸኛኘት እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

የሐዋሳ ከተማ መታወቂያ የኾነውን ታላቁ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን፣ ከመሠረቱ እስከ ፍጻሜው፣ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ያሠሩት ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ ሲኾኑ፤ሥርዐተ ቀብራቸውም፣ ሰበካ ጉባኤው በቃላቸው መሠረት ባሠራላቸው መቃብር ቤት፣ ነገ፣ ሰኔ 5 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ከቀኑ በ8፡00፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን በተገኙበት እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡

የሲዳሞ ሀገረ ስብከት(በቀድሞው አጠራር)፣ ብፁዕ አቡነ በርቶሎሜዎስ ሊቀ ጳጳስ፣ በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ከሌሎች 12 አባቶች ጋራ፣ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ጵጵስና የተሾሙበትና በፈቃዳቸው እስከለቀቁበት 2000 ዓ.ም. ድረስ ለ30 ዓመታት ገደማ አረጋግተው የመሩት ነው፡፡ ከመሠረቱ እስከ ፍጻሜው ያሣነፁትን የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራን ካስፈጸሙ በኋላ፣በዕርግናቸው ሳቢያ “ሓላፊነቱ ይበቃኛል” ብለው አመልክተው በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ማረፊያቸው ከመጡ በኋላ፣ ለተወሰነ ጊዜ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ሓላፊ ኾነው አገልግለዋል፡፡

“በንግግር ቁጥብ ግን በሳል ነበሩ፤” የሚሉት ወዳጃቸው፣ በስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር፣ቁጭ ብለው በጥሞና የማዳመጥ በመጨረሻም፣ “ይህ አይባልም፤ ይህን አርሙ፤” እያሉ የመምከር በጎ ልምድ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ፡፡ ብሕታውናዊ ግብር ጎልቶ የሚታይባቸው ብፁዕነታቸው፣ ጸሎተኛና ከመብልዓ ሥጋ የተቆጠቡ ጸዋሚና ተኃራሚ ነበሩ፡፡ በየዓመቱ በጾመ ፍልሰታ ለማርያም፣ የውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ በማሰማት፣ በሐዋሳ ምእመናን ዘንድ በእጅጉ ይታወቃሉ፤ “ሲዳሞን ሲመሩ፣ያለምንም ኮሽታና ውዝግብ ነበር የቆዩት ማለት ይቻላል፤”ይላሉ የሚያውቋቸው፡፡

በፊት ስማቸው አባ ፍሥሓ ጽዮን ይባሉ የነበሩት ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ፣ በሞያቸው የሐዲሳት መምህር ሲኾኑ፤ ከ1960 እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ፣ በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትን፣ ፍትሐ ነገሥትንና ትርጓሜ ዳዊትን ወንበር ዘርግተው አስተምረዋል፡፡ ከዚሁም ጎን ለጎን በገዳሙ ከነበሩት መምህር ወልደ ማርያም፥ መጻሕፍተ ሢራክን፣ መጻሕፍተ ሰሎሞንን፣ መጻሕፍተ መነኰሳትን ተምረዋል፡፡

ወደ አዲስ አበባ ከመጡበት 1960 ዓ.ም. በፊት፣ በበጌምድር/ጎንደር/ ደብረ ታቦር መካነ ኢየሱስ፣ ከመምህር ገብረ ኢየሱስ፥ ቅኔ ከነአገባቡ፣ ቅዳሴ ማርያምና ውዳሴ ማርያም፣ ኪዳንና ትምህርተ ኅቡአት፣ አቡሻህር፣ ትርጓሜ ሓዲሳትን፣ ትርጓሜ ዳዊትን፣ ትርጓሜ ፍትሐ ነገሥትን በሚገባ ከመማራቸውም በላይ የመምህራቸው ምክትል ኾነው በወንበራቸው ገብተው አስተምረዋል፡፡

በልጅነታቸው፣ ከዳዊት ደገማ እስከ ጸዋትወ ዜማ፣ ከመምህር ኤልሳዕ በመቀጠልም የደብረ ዓባይ ቅዳሴን፣ የደብረ ዘመዳ(ጀመዶ) ማርያም የቅዳሴ መምህር ከነበሩት መምህር መልከጼዴቅ ተምረዋል፡፡ የትውልድ ቦታቸውም፣ በቀድሞው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት፣ ላስታ አውራጃ፣ ግዳን ወረዳ የምትገኘው ይህችው የደብረ ዘመዳ/ጀመዶ/ ማርያም ስትኾን፤ ከአባታቸው አቶ ጌታሁን ወልዱ፣ ከእናታቸው ወ/ሮ እርጎዬ ቀኜ፣ ጥቅምት 4 ቀን 1919 ዓ.ም. መወለዳቸውን፣ ለሥርዐተ ቀብሩ በተዘጋጀው ዜና ሕይወታቸው ተገልጿል፡፡

በዕርግናቸው ከመደበኛ ሥራ ከተገለሉበት የመንበረ ፓትርያርኩ ማረፊያቸው፣ በጡረታ ሲረዱ የቆዩት አረጋዊው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ፣ በተወለዱ በ91 ዓመት ዕድሜያቸው በሞተ ዕረፍት ተለይተውናል፡፡

አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር፣ የብፁዕ አባታችንን ነፍስ ከማኅበረ ቅዱሳን ይደምርልን፡፡ የድካማቸው በረከት ይድረሰን፡፡ አሜን፡፡

Advertisements

One thought on “ጸሎተኛው እና ተኀራሚው ብፁዕ አቡነ በርተሎሜዎስ ዐረፉ

  1. Anonymous June 11, 2018 at 6:05 am Reply

    RIP

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: