በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ: ሌብነትና የሌብነት ድር መንግሥት ርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጠነቀቁ

PM Abiy Ahmed on corruption

  • አንዱ በሌላው ጣልቃ እንደማይገባ በሕገ መንግሥቱ የሰፈረው ድንጋጌ ባላንስ ያስፈልገዋል
  • መባው እና ዘካው የሕዝብ ሀብት እስከኾነ ድረስ መንግሥት የመቆጣጠር ርምጃ ይወስዳል፤
  • ሃይማኖትም፣በሹመኞች አስተሳሰብ ላይ የሚፈጥረው ጫና ስላለ ግንኙነቱ ዜሮ አይደለም፤
  • የተሰገሰገባቸውን የሌብነት ድር በመበጣጠስ ለመንግሥትና ለሕዝብ ምሳሌ ሊኾኑ ይገባል

†††

  • ዘርፎ መክበርን የሚያወግዝ፣ሌብነትን የሚጠየፍ ባህል ሳናዳብር ሌባን ማጥፋት አንችልም፤
  • ሌብነትን፥ሙስና ማለት ማሽሞንሞን ነው፤የአገር መዘዝ፣የዕድገት ጠንቅና ካንሰር ነው፤
  • ሥራቸው የሞራል ልዕልና መፍጠር ነው፤የሌብነት ምሽግ መኾን አይችሉም፤ የለባቸውም
  • ግልጽነትንና ተጠያቂነት በማስፈን፤ትውልዱን በሥነ ምግባር በመቅረፅ መንግሥትን ያግዙ፤

†††

(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም.)

የሃይማኖት ተቋማት፣ በውስጣቸው የተሰገሰገውን የሌብነት ድር በመበጣጠስ የሞራል አስተማሪነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከእንግዲህ መንግሥታቸው በተቋማቱ ውስጥ የሚፈጸምን ዘረፋና ሌብነት በቸልታ እንደማያልፈው አስጠነቀቁ፡፡

“ሃይማኖት በመንግሥት፣ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም፤” የሚለው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ትክክለኛ መርሕ ቢኾንም፣ የሃይማኖት ተቋማት የሚሰበስቡት መባ እና ዘካ የሕዝብ ሀብት እስከኾነ ድረስ መንግሥት አጠቃቀሙን የመቆጣጠር ርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

pm abiy ahmed on corruption7

የሃይማኖት ተቋማት ገንዘብ የሕዝብ ሀብት እንደኾነና በየትኛውም ዓለም ኦዲት እንደሚደረጉ የጠቀሱት ዶ/ር ዐቢይ፣ትንሽ የሌብነት ምልክት ካዩ ፈቃዳቸውን እስከመቀማት እንደሚደርሱ አስረድተዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ከመሬት ጀምሮ ለመንግሥት ለሚያቀርቡት ጥያቄ ባለሥልጣናቱ በእኩልነት ምላሽ መስጠት የሚገባቸውን ያህል፣ በአጸፌታው የመንግሥት ጥያቄ “ምከሩ፤ ገሥጹ፤ ሰላም አምጡ” በማለት ብቻ እንደማይወሰንና እንደማይቀጥል አስረድተዋል፡፡ “በዕለት ተዕለት የሃይማኖት ሥራ መንግሥት አይገባም፤ በመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ሃይማኖት አይገባም፤ ግን ደግሞ ቀይ መሥመርና ድንበራችን ኹሌ የቆመና የማይገናኝ አይደለም፤” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አጠቃላይ መርሑ ትክክል ቢኾንም ዘወትር እንደማይሠራና ሚዛን እንደሚያስፈልገው አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፣“የሃይማኖት ተቋማት ዋነኛ ሥራቸው፣የሞራል ልዕልና መፍጠር ነው፤ የሌብነት ምሽግ መኾን አይችሉም፤የለባቸውም፤ አላግባብ መባ እየሰበሰቡ ምን ላይ እንዳዋሉት የማይታወቅ ከኾነ ከእነርሱ የሚጠበቀው የሞራል ልዕልና ይጠፋና የሚያስተምሩትም ምእመን ሌባ ይኾናል፤”በማለት በውስጣቸው የተሰገሰገውን የሌብነት ድር በመበጣጠስ እንዲሁም ሃይማኖት በጥበብና በዕውቀት በባለሥልጣናት ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በመጠቀም፣መንግሥትን በተግባር ለማስተማር ቀዳሚውን ድርሻ እንዲወስዱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ባለፈው ረቡዕ፣ በሼራተን አዲስ የተካሔደውን 4ኛውን ሀገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ጠቅላላ ጉባኤ በከፈቱበት ወቅት“የተደራጀ ሌብነት፥ አምስተኛ መንግሥት እንደኾነ” የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማትን ከተደራጁ ሌቦች ለመከላከልና ለማጠናከር የሚደረገው ትግል በመንግሥት ብቻ ከዳር የማይደርስ በመኾኑ፣ ግብግቡ የጋራ ጥረትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሲቪል ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ ዘርፎ መክበርንና ሰርቆ አለማፈርን የሚያበረታታውን ባህልና አስተሳሰብ፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በሚያሰፍን አሠራር እያወገዙና እያጋለጡ በምሳሌነት በመዋጋት ለሕዝቡ የተግባር ትምህርት እንዲሰጡ ጠይቀዋል – እስኪ ምሳሌ ኾናችሁ ተገኙ፤ ምሳሌ ኾናችሁም ታገሉ፤ የሠራችሁትንም ለትምህርት እንዲኾን ለሕዝብ አሳዩ፡፡

PM Abiy Ahmed on corruption8በሀገራችን እየታየ ያለውን፣ በመጥፎ ሥነ ምግባር፣ በማጭበርበርና በሌብነት ላይ የተመሠረተ እጅግ አደገኛ አዝማሚያና ውድድር በማረም ረገድ ባህላችን ቁልፍ መከላከያ መኾኑን ያመለከቱት ዶ/ር ዐቢይ፣ ዘረፋን የሚያወግዝ፣ ሌብነትን የሚጠየፍ ባህል ሳናዳብር ሌቦችን ማጥፋት እንደማንችል አስረድተዋል፡፡ ሌብነትን፣“ሙስና፣ ብልሹነት ወይም የጨዋነት ጉድለት” እያሉ የሚያሽሞነሙኑት ሳይኾን፤የሞራል ዝቅጠት፣ አገር አጥፊ መዘዝና የዕድገት ጠንቅ በመኾኑ፣“ይህን አደገኛ ካንሰር ለማጥፋት ሁላችን የምንችለውን እናድርግ፤ የምንችለውን እንሥራ፤”ሲሉ የትብብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከ97 በመቶ ያላነሰው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኛና ሃይማኖተኝነት እንዳለው ቢነገርም፣ በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ጥናት መሠረት፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ የተደራጀ ሌብነት ብዙም የለባቸውም በተባሉት የዓለማችን 10 ሀገራት ውስጥ ብቻ ሳይኾን፣ ከአፍሪቃም 10 የተሻሉ የሚባሉ ሀገራትም መካከል የለችበትም፡፡ ይህ ብቻ ሳይኾን፣ ከ10ሩ ዝቅተኛ የአፍሪቃ ሀገሮች ውስጥም የለንበትም፡፡ በጣም ያሳፍራል፤ሲሉ ኹኔታውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚሁ ከቀጠለ፣ ከዐሥሩ አስጊ አገሮች ተርታ እንደምንሰለፍ ስለሚጠቁም የተቀናጀ ዘመቻና ትግል አስፈላጊ መኾኑን ለሀገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች አሳስበዋል፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

ጠቅ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በጋምቤላ ጉብኝት ባደረጉበት ግንቦት 19 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋራ ሲወያዩበሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ስለሚፈጸመው ሌብነትና ስለተሰገሰገባቸው የሌብነት ድር ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መንግሥታቸውን ያለውን አቋም አስመልክቶ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል

...እኩልነት ይከበር፤ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ሃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም፤ የሚለው አጠቃላይ መርሕ ትክክል ነው፤ግን ደግሞ ኹሌ አይሠራም፤ባላንስ ያስፈልገዋል፡፡ እኚህ ሰውዬ[የክልሉ ፕሬዝዳንት ጋቱሉዋክ ቱት] ቀን ቀን ፕሬዝዳንት ናቸው፤ ሃይማኖት አላቸው፤ እሑድ እሑድ ወይም ዓርብ ዓርብ ወደሚያምኑበት የእምነት ተቋም ሲመጡ የእምነት አገልጋዩ በሐሳብ ይጫናቸዋል፤ይቀርፃቸዋል፡፡ ሌብነት ጥሩ ነው የሚል ከኾነም ሌባ ይኾናሉ፤ሌብነት መጥፎ ነው የሚል ከኾነም ሌብነትን ይጠየፋሉ፡፡ ሃይማኖት በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ በጥበብና በእውቀት የሚፈጥረው ጫና አለ፤ ዜሮ አይደለም ግንኙነቱ፡፡

በሌላ መንገድ፣ በሁሉም ዓለም እንዳለው መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት የሚሰበስቡት መባ/ዘካ/ በትክክል ሥራ ላይ ስለመዋሉ መቆጣጠር አለበት፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ዋነኛ ሥራቸው፣ የሞራል ልዕልና መፍጠር ነው፡፡ የሌብነት ምሽግ መኾን አይችሉም፤ የለባቸውም፡፡ አላግባብ መባ እየሰበሰቡ ምን ላይ እንዳዋሉት የማይታወቅ ከኾነ ከእነርሱ የሚጠበቀው የሞራል ልዕልና ይጠፋና የሚያስተምሩትም ምእመን ሌባ ይኾናል፡፡ በየትኛውም ዓለም የሃይማኖት ተቋማት ኦዲት ይደረጋሉ፡፡ ያስገባው የሕዝብ ሀብት ስለኾነ፡፡ ብዙዎቹ ሀብታም ሀገሮች የሃይማኖት ተቋማትን ታክስ አያስከፍሉም፤ነገር ግን ይቆጣጠራሉ፡፡ሲቆጣጠሩ፣ ትንሽ የሌብነት ምልክት ካዩ ላይሰንስ ይቀማሉ፡፡

PM Abiy Ahmed in Gambella0

እኛ ጋራ የሃይማኖት ተቋማት መሬት ሲፈልጉ መንግሥት፣የኾነ የኾነ ሲቸግራቸው መንግሥት በሌላ ጊዜ አትግቡብን፤ መንግሥትም አንዳንድ ጉዳይ ሲኖረው የሃይማኖት አባቶችን ተጠቅሞ ምከሩ ገሥጹ ሰላም አምጡ የሚል፤ በሰላም ጊዜ ዘወር ብሎ የማያያቸው፤ እንደዚህ አይሠራም፡፡ በሕግ በዕለት ተዕለት የሃይማኖት ሥራ መንግሥት አይገባም፡፡ በመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ሃይማኖት አይገባም፤ ግን ደግሞ ቀይ መሥመርና ድንበራችን ኹሌ የቆመና የማይገናኝ አይደለም፡፡ አንዳችን በአንዳችን ውስጥ አለን፡፡በሚያገናኘን ጉዳይ ተገናኝተን ተባብረን መሥራት፤ በማይመለከተን ጉዳይ ደግሞ እጃችንን መሰብሰብ፤ ለምን? የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ የራሱን ሥራ በወጉ ሳይሠራ፣ ከተማውን ሳያጸዳ የሃይማኖት ተቋማትን ሊቆጣጠር ቢፈልግ ኪሳራ ነው፡፡ መጀመሪያ ሥራውን መሥራት፤ የሃይማኖት ተቋማት፣ በግቢያችሁ ምእመኖቻችሁ ላይ ማድረግ የሚገባችሁን ሳታደርጉ ከንቲባውን ብትወቅሱ እናንተም እንዲሁ ማለት ነው፡፡

መጀመሪያ እያንዳንዱ ዜጋና ቡድን ሓላፊነቱን ከወሰደ በኋላ እንደ ሀገር የምንወስደውን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ይኼ በሚኾንበት ሰዓት ያን ቀን ክቡር ፕሬዝዳንት ሃይማኖት የላቸውም፡፡ኹሉም የሃይማኖት ተቋም ሁሉም የጋምቤላ ዜጋ ለእርሳቸው ዜጋ ነው፡፡ ሁሉንም በእኩል ዐይን ማየትና መገልገል ሕገ መንግሥታዊ ግዴታቸው ነው፡፡ለእምነት ተቋማቸው የሚያዳሉ ከኾነ እርሳቸው የሃይማኖት ተቋም መሪ እንጅ የሕዝብ መሪ መኾን አይችሉም፡፡ የሕዝብ መሪ ስንኾን ሁሉን በእኩል ማየት፣ በእኩል ማቀፍ፣ በእኩል ማስተዳደር ይጠይቃል፡፡ እርሱን ደግሞ እንደሚያደርጉ፣ የተነሣውን ጥያቄ እምነት አለኝ፤ እኔም እከታተላለኹ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: