አነጋጋሪው የአኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ መዘክር ግንባታ በአዲስ ውል ሊጀመር ነው

Aksum Tsion museum

 • የግንባታ ውሉ እና ወጪው፣ አነጋጋሪ ኾኖ ቆይቷል፤
 • ያለጨረታ የተሰጠና ለተጠያቂነት ያስቸገረ ውል ነበር፤
 • ከ200እስከ 425ሚ.ብር የወጪ መጠን ተጠቅሶ ነበር፤
 • ለተቋረጠው ግንባታ፣ 60 ሚ. ብር መዋሉ ተጠቁሟል፤

†††

 • ለቀሪው ሥራ በእጅ ያለው ከ25 ሚ. ብር አይበልጥም፤
 • በሙዳየ ምጽዋት፣የተፈለገውን ያህል ገንዘብ አልተገኘም፤
 • እንደ አጥቢያዎች ገቢ መጠን “ቁርጥ መዋጮ” ተደለደለ፤
 • መሰል ድጋፎችን የሚሹ ሌሎች መካነ ቅርሶችም ይታዩ፤

†††

(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.)

Aksum Tsion Museum construction

የሕንፃ ግንባታው ለአምስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ መዘክር ግንባታ ዳግም ለማስጀመር፣ የ160 ሚሊዮን ብር አዲስ ውል ተፈረመ፡፡

ጨረታውን በአዲስ መልክ በማውጣት፣ ባለፈው የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ የግንባታው አስተባባሪ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ገሪማ እና አሸናፊ የኾነው ተቋራጭ ድርጅት የስምምነት ውል ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ከድርጅቱ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ተክለ ሃይማኖት አስገዶም ጋራ በመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት አዳራሽ በተከናወነው የፊርማ ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ “የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን በመተማመን ያስጀመሩት ይህ ታሪካዊ ቤተ መዛግብት፣ የኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረት ነው፤” ብለዋል፤ ለፍጻሜውም ኹሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም የቤተ ክርስቲያን አካላት እያንዳንዳቸው ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Aksum Tsion Museum

ቀሪው የሕንፃ ቤተ መዘክሩ ሥራ 160 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅና በኹለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

የአኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ መዘክር ግንባታ፣ በሚያዝያ ወር 2003 ዓ.ም. በቋሚ ሲኖዶስ ተወስኖ በቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ይፋ የተደረገ ቢኾንም፤ እስከዛሬ የግንባታው ወጪና ሒደት አነጋጋሪ ኾኖ መዝለቁ ታውቋል፡፡

በአንድ ወቅት “ዜና ቤተ ክርስቲያን” ጋዜጣ፣ ለግንባታ ፕሮጀክቱ በውጭ ምንዛሬ 8.9 ሚሊዮን ዩሮ እና 25 ሚሊዮን ዶላር፣ በኢትዮጵያ ገንዘብ ደግሞ ከ200 ሚሊዮን እና ከ425 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪዎች እንደሚያስፈልጉ የጠቀሰ ሲኾን፤ የወጪው በሰፊ መጠን መለያየት በፕሮጀክቱ አፈጻጸም ላይ ጥያቄዎችንና ጥርጣሬዎችን ሲያሥነሳ ቆይቷል፡፡

ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት ለቤተ መዘክሩ ግንባታ ርዳታ ለማሰባሰብ፣ በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ፣ ላለፉት 6 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየ ቢኾንም፣ በሙዳየ ምጽዋት የተፈለገውን ያህል ገንዘብ በወቅቱ ማግኘት እንዳልቻለ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ለተቋረጠው ግንባታ ውሏል ከተባለው 60 ሚሊዮን ብር በኋላ፣ እስከ አኹን ተሰብስቦ በእጅ የሚገኘው ገንዘብ ከ25 ሚሊዮን ብር ያልበለጠ እንደኾነ የጠቆሙት ምንጮች፣ ግንባታው ከቆመ አምስት ዓመት ማስቆጠሩን ጠቁመዋል፡፡ “ፀሐይና ዝናም እየተፈራረቀበት ብረቱ እየዛገ፣ ብሎኬቱ እየፈራረሰ ነው፤” ይላሉ ምንጮቹ፡፡

በሌላ በኩል፣ አኵስምን በዓለም ቅርስነት ያሰፈረው ዩኔስኮ፣ “የሙዚየሙ ሕንፃ ዲዛይን መካነ ቅርሱን(ሐውልቱንና የጥንቱን ቤተ ክርስቲያን) የሚሸፍን መኾን የለበትም፤” በማለት ማሻሻያ እንዲደረግበትና ሕንፃ ቤተ መዘክሩን ለማጠናቀቅ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶችም(finishing materials) ከመካነ ቅርሱ መልኮች ጋራ እንዲጣጣሙ ማሳሰቡን ምንጮቹ አክለዋል፡፡

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ትብብር፣ የቤተ መዘክሩ ዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎ ለዩኔስኮ ከተገለጸና ሥራው እንዲቀጥል ከተፈቀደ በኋላ ጨረታው ወጥቶ የግንባታው ውል እንደ አዲስ መፈረሙን አስረድተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የገንዘብ አስተዋፅኦውን የሚያሰባስበው ኮሚቴም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳግመኛ ተዋቅሮ በሥራ አስኪያጅ እንዲመራ ተደርጓል፤ ሙዳየ ምጽዋት ተቀምጦ በየጊዜው ይሰበሰብ የነበረው ርዳታም፣ እንደ አድባራቱ የገቢ አቅም ወደ “ቁርጥ መዋጮ” መዞሩ ታውቋል፡፡

ኾኖም፣ የ“ቁርጥ መዋጮው” ድልድል፣ በሀገረ ስብከቱ ገዳማትና አድባራት ዘንድ አሳታፊና በቂ ውይይት አልተካሔደበትም፤ ያሉት ምንጮቹ፣ ይህም የተፈለገው አስተዋፅኦ እንዳይገኝ ዕንቅፋት እንዳይኾን ስጋታቸውን ገልጸዋል፤ ቀሪ ግንባታውና የማጠናቀቂያው ሥራ(መካኒካልና ኤሌክትሪካል መሣሪያ ወጭው) እስከ አኹን ከወጣው ከዕጥፍ በላይ የሚጠይቅ በመኾኑ፣ የአጥቢያዎቹን አስተዳደር አካላት ታች ድረስ ወርዶ የማወያየትና የማሳመን ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡

የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ መዘክር ግንባታ ከወሰደው ረዥም ጊዜ አኳያ፣ መሰል ድጋፎችን የሚሹ ጥንታውያን ቅዱሳትና ታሪካውያን መካናት በየአህጉረ ስብከቱ እንዳሉ ከግምት እንዲገባ የጠቆሙ አስተያየት ሰጭዎች፤ ቀድሞውንም በቂ ገንዘብ ሳይያዝ በተለጠጠ በጀት ግንባታውን መጀመሩ አግባብነት የሌለው በመኾኑና ለቁጥጥርም ስለሚያዳግት፣ በአሠራሩ የተስተዋለው ለብክነትና ምዝበራ የሚዳርግ ግለሰባዊና ግብታዊ አካሔድ ሊታረም ይገባል፤ ብለዋል፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

ማለቂያ የሌለው ፕሮጀክት??

የርእሰ ገዳማት ወአድባራት አኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ መዘክር፣ ዐፄ ፋሲል በ1627 ዓ.ም ባሠሩት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ዐፄ ኀይለ ሥላሴ በ1957 ዓ.ም ካሠሩትና በመጠኑ ሰፋ ካለው የአኵስም ጽዮን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በስተጀርባ ሰሜናዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ነው እየተገነባ ያለው፡፡ በ4ሺሕ975 ካሬ ሜትር ስፋት ይዞታ ላይ ያረፈ ሲኾን፣ ሦስት ደርቦች/ፎቆች/ ይኖሩታል፡፡ የሕንፃው ዐቅድ በግሪክ ባለሞያዎች የተሠራ፣ ዘመኑ የሚጠይቀው የቴክኖሎጂ ግብአቶች ሁሉ የተሟሉለትና የሕንፃው የላይኛው ክፍል የአኵስም ሐውልቶች ከተጠረቡበት ድንጋይ የሚሠራ ከመኾኑም በላይ በውስጡ የሚቀመጡትን ቅርሶች በዘመናዊ መልኩ ለመጠበቅና ለመከባከብ የሚያገለግል የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ይገጠምለታል፤ ተብሏል፡፡ የዚሁ መካኒካልና ኤሌክትሪካል መሣሪያ ወጭም የሕንፃው ግንባታ ከሚወስደው ገንዘብ በላይ እንደኾነ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፣ በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. እትሙ ዘግቧል፡፡

የግንባታ ፕሮጀክቱ ዓላማ፣ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻና የአርኬዎሎጂ መካን በኾነችው አኵስም፣ ከሦስት ሺሕ ዓመት የሚበልጥ ዕድሜ ያላቸውን ንዋያተ ቅድሳትና ታሪካዊ ቅርሶች ከብልሽትና ብክነት መታደግ፣ ለጉብኝትና ምርምር ምቹ ማድረግ እንደኾነ፣ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፣ በተጠቀሰው እትም ርእሰ አንቀጹ ገልጿል፡፡ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር በተመረጠና ምቹ የከተማዋ ሥፍራ ከ25 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በኾነ ወጪ በመጣደፍ ላይ እንዳለና ሥራውም ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታትን እንደሚወስድ አስታውቋል፡፡

ለአኵስም ጽዮን ያልተዘረጉ እጆች ለማን ይዘረጋሉ?” በሚለው ርእሰ አንቀጹ እንዳሰፈረው፣ በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት መሥዋዕተ ሐዲስ የሚሠዋባቸው ታቦታት ሁሉ መሥዋዕተ ኦሪት ይሠዋባት ከነበረችውና ዛሬም መሥዋዕተ ሐዲስ እየተሠዋባት ያለችው በርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን የምትገኘው የታቦተ ጽዮን ቅጅና ብዜቶች ናቸው፡፡ ይህም ከሆነ ዘንድ የመላ ኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ለታቦተ ጽዮን ዐሥራት ማውጣት ግዴታቸው ነው፤ ብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ የሚጠይቀው ወጪ የቤተ ክርስቲያንን አቅም በእጅጉ የሚፈታተን እንደኾነ ያልሸሸገው ርእሰ አንቀጹ፣ ቅርሶቹ የሀገር ሀብቶች መኾናቸውን ከግምት በማስገባት፣ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለዓባይ ግድብ መዋጮ በነፍስ ወከፍ ካደረገው ርብርብ ባልተናነሰ መልኩ ለአኵስም ጽዮን ሙዚዬም ግንባታ መዋጮም ሊረባረብ ይገባዋል፤ የዓባይ ግድብ የሥጋችን ብርሃን እንደኾነ ኹሉ ታቦተ ጽዮንም የነፍሳችን ብርሃን ናትና፤ በማለትም ተማፅኖ ነበር፡፡

የአኵስም ጽዮን ንብረት የኾኑ ጥንታውያን ንዋያተ ቅድሳትና ቅርሶች በአግባቡ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ የሙዚየሙን መገንባት አስፈላጊነት ብዙዎች ቢያምኑበትም፣ የግንባታው ውል፣ ከሚመለከታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካላት ዕውቅና ውጭ እና ያለጨረታ ለአንድ የሀገር ውስጥ ሕንፃ ተቋራጭ የተሰጠበት ኹኔታ ክፉኛ ይተቻሉ፡፡ የወጪውን መጠን መለያየት በመጥቀስም ትችታቸውን ያጠናክራሉ፡፡

የፕሮጀክቱን መጀመር ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ለግንባታው የሚፈለገው ወጭ አንድ ዓይነት አልያም ተቀራራቢ አኃዛዊ መጠን አይደለም የነበረው፡፡ የቀድሞው ፓትርያርክ በኅዳር 2004 ዓ.ም. የጽዮን ክብረ በዓል ንግግራቸው፣ “200 ሚሊዮን  ብር ያስፈልጋል ተባልኩ፤” ብለዋል፡፡ ስለ አኵስም ጽዮን ውሏቸው የዘገበው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፕሮጀክቱ ወጪ 8.9 ሚሊዮን  ዩሮ እንደኾነ ሲዘግብ፣ ማዕርግ ካህሱ የተባሉ የፕሮጀክቱን አስተባባሪ የጠቀሰው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድረ ገጽ በበኩሉ ሥራው ከ100 ሚሊዮን  ብር በላይ በኾነ ወጭ በመካሔድ ላይ እንደኾነ ዘግቧል፡፡ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በኅዳር ወር እትም ርእሰ አንቀጹ፣ ግንባታው ከ25 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ወጭ እንደሚጠይቅ ሲያመለክት፣ በዚሁ እትም የወጣ ሌላ ጽሑፍ ደግሞ፣ ሙዚየሙን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ይፈጃል ተብሎ የተገመተው ከብር 425 ሚሊዮን  ብር በላይ መኾኑን ያሳያል፡፡ ?

ግልጽነት የጎደለውና ለምዝበራ የተጋለጠው አሠራር፣ ፕሮጀክቱን ለመርዳት ፈልገው በቅድሚያ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንዲወጣ የጠየቁ በጎ አድራጊዎችን ከማራቁም በላይ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ሠራተኞችና የሀገረ ስብከቱን አድባራት በመዋጮ ጫና ያማረረ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ሕንፃው ከመሠረቱ ወጥቶ ግራውንድ ቢኖች በታሰሩበት ደረጃ 35 ሚሊዮን  ብር ተከፍሎ እንደነበር በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. የጽዮን ክብረ በዓል ላይ ሲገለጽ ብዙዎች ጥያቄ አንሥተው ነበር፤ “ዛሬ በቆመበት ኹኔታ ደግሞ 60 ሚሊዮን ብር እንደፈጀ መነገሩስ ማንን ያሳምናል?” የሚሉ ታዛቢዎች፣ “ማለቂያ የሌለው ፕሮጀክት” እንዳይኾን ይሰጋሉ፡፡ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ የግንባታ አስተባባሪ ኮሚቴውን ዳግም በማዋቀር ቁጥጥሩን ለማጥበቅና ሥራውን ለማፋጠን በወሰደው ርምጃ ተስፋ ቢያደርጉም፣ አፋጣኝ ድጋፎችን የሚሹ በርካታ መካነ ቅርሶችና የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉ መኾኑ አብሮ እንዲጤን ያሳስባሉ፡፡

Advertisements

7 thoughts on “አነጋጋሪው የአኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ መዘክር ግንባታ በአዲስ ውል ሊጀመር ነው

 1. […] ← ለቀውሱ መስፋት ካህኑን ተጠያቂ ያደረጉት ፓትርያርኩ፥“የሰላም መስቀል ይዘን ሕዝቡን የሰላም ኃይል ማድረግ እንዴት አቃተን?” ሲሉ ጠየቁ አነጋጋሪው የአኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ መዘክር ግንባታ በአዲ… […]

 2. Anonymous March 11, 2018 at 4:50 pm Reply

  ይገርማል አንባብያን አስተውሉ ጪራተውን የሚያፈራርሙት በፎቶ የሚታዯት ጥቁሩ አረጋውያን ጳጳስ
  በፎቶ እደሚታየው አይናቸውን የጋረዳቸው ናቸው ታዲያ ሆነ ተብሎ ስራው በተሎ እደ ይጠናቀቅ
  ለሙስና አመች ለመለመኛ አመች መፈጠራቸው ነው ያሣዝናል ያክሱም ሙዜም ግን ከነሱው ምንይጠበቃል፣

 3. Anonymous March 12, 2018 at 12:09 am Reply

  ያሳዝናል አንድ ሚልዬን የኦሮሞ ሕዝብ ከቤት ከንብረቱ ተፈናቅሎ በረሃብና በቤት እጦት እየተንገላታ አባ ማትያስ በብዙ ሚልዬን ለቁስ ማጎሪያ ድንጋይ የከምራሉ ምናለ ብሩን ለተፈናቀለው ወገን ቢለግሱ አይ ፕትርክና ያሳዝናል፡፡

 4. Anonymous March 12, 2018 at 12:09 am Reply

  ያሳዝናል አንድ ሚልዬን የኦሮሞ ሕዝብ ከቤት ከንብረቱ ተፈናቅሎ በረሃብና በቤት እጦት እየተንገላታ አባ ማትያስ በብዙ ሚልዬን ለቁሳቁስ ማጎሪያ ድንጋይ የከምራሉ ምናለ ብሩን ለተፈናቀለው ወገን ቢለግሱ አይ ፕትርክና ያሳዝናል፡፡

 5. Anonymous March 12, 2018 at 8:19 pm Reply

  This is good news. But This agreement is not clear enough. and 160million is very small amount of money for the project. Anyways maybe the change the original design and the t type of materials .believe it or not Abune Mattiyas will never finish that project.

 6. Anonymous April 1, 2018 at 11:31 am Reply

  why all you guys not hope good things and do your own responsibility given by God(by the church).

 7. yayeh April 1, 2018 at 11:40 am Reply

  abune matheias are not a political leader bt leader for church assigned by Holly Spirit so why do you blame them for prioritizing conservation and protection of the church’s heritage.
  be practical Christian what have you done for your Oromo brothers displaced from the Ethiopian Somali region

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: