ቅ/ሲኖዶስ ጸሎተ ምሕላው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰበ፤“የረብሻው መነሻ ሥር የሰደደ ሙስና ነው፤”/ፓትርያርኩ ለኢኦተቤ ቴቪ/

holy-synod

 • የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን፣ ከምልአተ ጉባኤው ጋራ ተነጋገረ
 • በሀገራዊ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን ድርሻዋን እንድታጠናክር ጠየቀ
 • በውስጥና በውጭ መከፋፈል እንዲወገድ ተጽዕኖ ትፍጠር፤ /ቡድኑ/
 • “ለሰላም የሚደረገውን ጥረት ትደግፋለች፤ ከጎናችሁ ነን፤” /ቅዱስ ሲኖዶሱ/
 • ለዕርቀ ሰላም ጥረቱ፣ ሦስት ብፁዓን አባቶችን በልኡክነት ሠየመ

†††

ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ዛሬ ሰኞ፣ የካቲት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሔደው አስቸኳይ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ፣ ሀገራችን ከገባችበት ቀውስ ጋራ በተያያዘ በመዋዕለ ጾሙ የሚካሔደው ጸሎተ ምሕላ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰበ፤ በውጭ ከሚገኙ አባቶች ጋራ የተስተጓጎለውን የዕርቀ ሰላም ሒደት በተሻለ አያያዝ ለማስቀጠል በተጀመረው ዓለም አቀፍ ጥረት የሚሳተፉ ሦስት ብፁዓን አባቶችን በልኡክነት ሠየመ፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን አምስተኛ ዓመት በዓለ ሢመተ ፓትርያርክ ምክንያት በማድረግ የተሰበሰቡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ዛሬ ከቀትር በፊት ባካሔዱት አስቸኳይ ምልአተ ጉባኤ፣ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ስለሚገኘው የሀገራችን ወቅታዊ ኹኔታና እጅግ አሳሳቢ ስለኾነው መጻእያቷ በመነጋገር፣ በመላው አድባራትና ገዳማት የሱባዔው ጸሎተ ምሕላ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ይህም በየብዙኃን መገናኛው በስፋት እንዲገለጽ አዝዟል፡፡

በምልአተ ጉባኤው ላይ እንደተገኘ የተገለጸው፣ የእነሻለቃ አትሌት ኃይለ ገብረ ሥላሴ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን፣ ቤተ ክርስቲያን ሀገራችን ለተዘፈቀችበት ቀውስ ትኩረት እንድትሰጥ፣ ከጥንታዊና ታሪካዊ ብሔራዊ ሚናዋን የሚመጥን ጠንካራ ጥረትና ግፊት እንድታደርግም መማፀኑ ተጠቁሟል፡፡

የቡድኑን ጥያቄ በአዎንታ በመቀበል በስፋት የመከረው ምልአተ ጉባኤው፣ ለሰላም የሚደረገውን ጥረት ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደምትደግፍና በየትኛውም አህጉረ ስብከት የሚገኙ ብፁዓን አባቶችም ከጎኑ በመቆም እገዛ እንደሚያደርጉ ተገልጾለታል፡፡ ወቅቱ የሱባዔ ከመኾኑ አኳያ ግን ጸሎተ ምሕላው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ ላይ የተወሰነ ምላሽ ነው የተሰጠው፡፡

ኾኖም፣ አስጊ ኾኖ የሚታየው የመከፋፈል አደጋ ተወግዶ የሀገር ሰላም እንዲመለስና የሕዝብ አንድነት እንዲጠበቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተጽዕኖ ትፍጠር፤ ድርሻዋም የተጠናከረ ይኹን፤ በማለት የጠየቀው ቡድኑ የበለጠ ተግባራዊ ተሳትፎና እንቅስቃሴ ሽቶ እንደነበርና በምላሹ አለመርካቱ ነው የተመለከተው፡፡

በተያያዘ ዜና፣ በጥቅምቱ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔ መሠረት፣ በውጭ ከሚገኙ ብፁዓን አባቶች ጋራ ተጀምሮ የተስተጓጎለውን የዕርቀ ሰላም ሒደት በተሻለ አያያዝ ለማስቀጠል በእነዶ/ር ንጉሡ ለገሰ ዓለም አቀፍ አስታራቂ ኮሚቴ አነሣሽነት በተወጠነው ጥረት የሚሳተፉ ሦስት ብፁዓን አባቶችን፣ ምልአተ ጉባኤው በልኡክነት ሠይሟል፡፡

ተነጋጋሪ ልኡካኑ፦ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ-ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም መኾናቸው ታውቋል፡፡

ልዩነቱ አስተዳደራዊ መልክ ይዞ ቢከሠትም፣ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሒደት በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱና መዋቅራዊ አንድነቱ ባለመመለሱ ወደ ቀኖናዊ ልዩነት ሊሰፋና ሊከፋ የሚችልባቸው ዕድሎች ከስጋት(ምልክት) በላይ ኾነው እንደሚታዩ፣ የዓለም አቀፍ አስታራቂ ኮሚቴው ልኡካን በጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ቀርበው አስረድተዋል፡፡

የዕርቀ ሰላም ሒደቱን በተሻለ አያያዝ በአፋጣኝ በማስቀጠል የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማረጋገጥ እንድንነሣሣ አስገድዶናል፤ ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፍ አስታራቂ ኮሚቴውን፣ በቅንነትና በበጎ ፈቃድ በማቋቋም ስለአካሔዱ ሲመካከሩበት እንደቆዩና በውጩ ሲኖዶስም ጠንካራ ፍላጎት ያላቸው አባቶች እንዳሉ መረዳታቸው እንዳበረታታቸው መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል፣ የአምስተኛ ዓመት በዓለ ሢመተ ፕትርክናቸውን በማስመልከት ከኢኦተቤ ቴቪ ጋራ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፓትርያርኩ፣ ለሀገራችን ወቅታዊ ቀውስ መንሥኤው ሥር የሰደደው ሙስና እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

scan0030

ችግሩ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን የሀገሩ ጣጣ፣ የሀገሩ ችግር ነው፤ ሙስና በፊትም በዓለምም ያለ ነው፤ የአፍሪቃ መሪዎች ተሰብስበው ትልቁ አጀንዳ እርሱ ነበር፡፡ ሙስና(corruption) እየተባለ ትልቅ አጀንዳ ነበር፡፡ ገንዘባችንን በትክክል ብንሰበስብ ከፈረንጆች ልመና፣ ስጦታ ወይም ብድር እንድን ነበር፤ ገንዘባችን እየተመዘበረ ነው ያለው፤ ብለው በየዓመቱ ይህን ያህል በቢሊዮን የሚቆጠር እንከስራለን ብለው በዚህ ነው የዋሉት፤ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ “ሙስና፣ ሥር የሰደደ መጥፎ፣ መጥፎ ነገር ነው ያለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለረብሻውም መነሻ የሚኾነው እርሱ ነው፡፡ “ሙስና በዝቷል፤ አገር ተጎድቷል፤” እየተባለ ነው መነሻ እየኾነ ያለው፡፡”

ሰው ምናለ ያልተሰጠውን ከመውሰድ የተሰጠውን በሥነ ሥርዐት ቢመገብ፣ ቢበላ፤ ሥርዐት ያለው ደመወዝ እያገኘ እንደገና ደግሞ በአጭር ጊዜ ለመበልጸግና ያልታዘዘልንን ሀብት ለመብላት… በእውነቱ ይህን እንዲጠነቀቅበት ነው፡፡ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ምን እናድርግ ብለው የንሥሓ ጥምቀት ለመጠመቅ የሔዱ ሰዎች፣ በሕግ የተሰጣችሁ ደመወዛችሁ ይብቃችሁ ነበር፤ ያላቸው፡፡ ያልተሰጣችሁን ሰውን አትበዝብዙ፤ ሰውን አትጉዱ፤ የታዘዘላችሁን ተመገቡ፡፡

እና ይኼ ሀገርን የጎዳ፣ ወገንን የጎዳ መቼም ያልታወቀ ጉዳት በሀገርና በወገን ላይ እየተካሔደ ያለው ነው፡፡ ይኼን ጸያፍ የኾነ ነገር ቤተ ክርስቲያን በደንብ ነው የምታወግዘው፡፡ በየጊዜው እናስተምርበታለን… ግን ያው በመጠኑ ትንሽ ትንሽ ለውጥ ቢታይም ችግሩ አለ፤ ችግሩ ግን እስከ አሁን ድረስም አለ፤ ወደፊት ምናልባት ትውልዱ ይቀርፈው ይኾናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

Advertisements

3 thoughts on “ቅ/ሲኖዶስ ጸሎተ ምሕላው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰበ፤“የረብሻው መነሻ ሥር የሰደደ ሙስና ነው፤”/ፓትርያርኩ ለኢኦተቤ ቴቪ/

 1. Anonymous March 5, 2018 at 6:00 pm Reply

  ሐራዎች አትቸኩሉ የምትዘግቡ ከኾነ አጣርታችኹ ዘግቡ ጉባኤው ላይ የተገኘው ስሙ የ.ኦ.ተ.ቤ.ክ.ኹለተኛ ዙር የሰላምና አንድነት ጉባኤ የሚባለው የዋናው ጉባኤ ተወካዮች ከአውሮፓና የኢትዮጵያው ቅርንጫፍ ሥራ አስፈጻሚ ነው እንጂ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን አይደለም እባካችኹ ያልተጣራና አፍራሽ ነገር አትዘግቡ ለመስማት የፈጠንክ ለመናገር የዘገየህ ኹን እንዲል ፡፡

 2. ያየህይራድ ኢሳኮር March 5, 2018 at 6:11 pm Reply

  ካላፋጠጠው አያራ ይባላል።ይህ የወያኔዎች ስብስብ ሲኖዶስ ተብዬ ሁሌ ባለቀ ሰዓት የተፃፈለትን ማንበብ ይወዳል።የቀድሞው ፓትሪያርክ እንዴት እንደተባረሩ እያወቁና እሳቸውም ሿሚያቸውን አቡነ ተክለሃይማኖትን ሲሳደቡ ከርመው ዛሬ ደርሶ የሰላም አባት ለመምስል ይሞክራሉ።ኢትዮጵያ ዛሬ የሚያስፈልጋት ከሃይማኖት እስከ ፖለቲካው ስር ነቀል ለውጥና ይቅር መባባል ነው።ሰኞን ቢያባብሉት ማክሰኞ ላይሆን።

 3. አባ ፋኑኤል March 6, 2018 at 12:02 am Reply

  እንዴት ተሾፈ ጎበዝ?ምህላ የሚያደጉትና የሚያውጁት በተሽቆጠቆጠ ልብሰ ዽዽስና የወርቅ መስቀል ተደርተው የቀረቡት ካድሬው ትግሬው አባ ማትያስ ትእዛዝ ከቶ ለልማድ ካልሆነ በቀር ዋጋየለውም ከንቱ ነው;;ደግሞስ ችግራችን ሙስና ነውን?አባማትያስ ?ችግሩ የወያኔው አፓርታይድ ሒትለራዊ ትግሬ ወያኔ አገዛዝ እንጂ?መቼ ይሆን ለጨበጡት መስቀል ተገዝተው እውነተን የሚናገሩት?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: