“የዐዲሱ ትውልድ መሪዎችና ተጠሪዎች፥ ቤተ ክርስቲያንንና ሕዝቡን ልንጠብቅና ዋጋም ልንከፍል ይገባል!”-ዋ/ሥ/አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ

 

pat mathias 5th year enthronment anniv

 • በፓትርያርኩ በዓለ ሢመት፥ በኖላዊነትና ኖሎተ አባግዕ ወቅታዊ ሚና መልእክት አስተላለፉ
 • ኖላዊነት፣ የመምሰል ሳይኾን የተግባር ሐዋርያነት ነው፤ ትጋትንና መሥዋዕትነትን ይጠይቃል
 • ኑፋቄ ትውልዱን እየተፈታተነ ባለበት፣ከመሪዎች የሚጠበቀው ተቀዳሚ ሥራ ኖላዊነት ነው
 • የመንበሩ ሥዩማን፣ መንጋውን፥ በይቅር ባይነት፣ በፍቅርና በአንድነት መጠበቅ ይኖርባቸዋል
 • ግጭቶችን መርምሮ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት የወቅቱ የትኩረት አቅጣጫችን ሊኾን ይገባል

†††

 • የካህናት፣ የምእመናንና የወጣቱ አስተዳደራዊ ጥያቄ፣በወቅቱ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል
 • ጎሠኝነትንና ሙስናን መከላከል፤ የቤተ ክርስቲያን ሀብት ሲሳየ ካልኣን እንዳይኾን መጠንቀቅ!
 • ለሥራ አጥ ሊቃውንት፣ካህናትና መነኰሳት፥እንደሞያቸው ሥራ ሰጥቶ ችግራቸውን መቅረፍ፤
 • ሙሐዘ ምሥጢራት፣ነቅዓ ጥበባት የኾኑትን የአብነት ት/ቤቶችና ገዳማት ክፍተት መሙላት፤
 • ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት፤ አስተዳደራችንን ማዘመን፤ዘመኑ ሳይቀድመን ቀድመን መገኘት!

†††

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ስድስተኛው ፓትርያርክ ኾነው የተሠየሙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ትላንት የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.፣ ፭ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን፥ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንዲሁም የገዳማቱና አድባራቱ ሓላፊዎች፣ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አክብረዋል፡፡

“እንኳን ለአምስተኛ ዓመት በዓለ ሢመትዎ በሰላምና በጤና ጠብቆ አደረስዎ፤” ያሏቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ቅዱስነታቸው ስድስተኛ ፓትርያርክ ኾነው ሐዋርያዊውን መንበር ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ እያበረከቱ የሚገኙት ዐበይት ተግባራት፣ “መሠረታዊ እና ዘመን ተሻጋሪ” እንደኾኑ ተናግረዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን መብት ከማስከበር አንጻር፣ በሀገር ውስጥም ኾነ ከሀገር ውጭ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞና የሥራ ግንኙነት፣ “የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም ገጽታ አጉልቶ ያሳየ ተግባር ነው፤” ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን፣ ያላትን የሰው ኃይልና የበጀት አቅም በማቀናጀት መሠረታዊ የዕድገት ለውጥ እንድታስመዘግብ፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ከቅዱስነታቸው በየጊዜው መመሪያ እንደሚሰጥ አያይዘው የጠቀሱት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ “በርቱዕ ልብ የምንቀበለውና ተግባራዊ የምናደርገው ይኾናል፤” በማለት አስታውቀዋል፡፡

ኾኖም መመሪያ መስጠት ብቻ በቂ እንዳልኾነ የጠቆሙት ብፁዕነታቸው፣ ለውጡን ለማስመዝገብና የቤተ ክርስቲያናችንን ዐቢይ ተልእኮ ለመፈጸም፣ ውስጣዊ ልዩነትን አስወግዶ በመግባባትና በአንድነት መሥራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡ በአገልጋዮች ካህናትና ምእመናን እንዲሁም በወጣቶች መካከል የእርስ በርስ መለያየት ቀርቶ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላም፣ ፍቅር፣ መከባበርና መተማመን እንዲሰፍን፤ የማይጠቅመንን ትተን፣ የሚጠቅመንን ይዘን፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነን ለቤተ ክርስቲያናችን ኹለንተናዊ ዕድገት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡

በዓለ ሢመቱ ሲከበር፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከቅንየተ ግብጽ ነጻ ኾና ለጥንታዊነቷ የሚገባትን ክብር እንድትጎናጸፍ፣ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ በዘመናቸው ከነበሩ አባቶች፣ ሊቃውንት፣ መኳንንትና መሣፍንት ጋራ ያደረጉት ጥረት ሳይነሣ አይታለፍም፡፡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በንግግራቸው እንዳመለከቱትም፣ “ፓትርያርካዊ አክሊለ በረከቱን ከነሙሉ መንፈሳዊ መብቱ እንድንረከብ ለ31 ዓመታት ሳይታክቱ የሠሩት ታሪካዊ ውለታ ለዘለዓለም ሲታወስ ይኖራል፡፡”

ከዘመናችን የቤተ ክርስቲያን ፈተና አንጻርም ዛሬ ከመንበሩ ይጠበቃሉ ያሏቸውን ተቀዳሚ ተግባራትንም ብፁዕነታቸው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ ለኖላዊነት ሥራ ትኩረት በመስጠት መንጋውን በፍቅርና በአንድነት መጠበቅ፣ የዐዲሱ ትውልድ መሪዎችና ተጠሪዎች የኾኑ ኖሎተ አባግዕ ኹሉ ተቀዳሚ ተግባር ሊያደርጉት ይገባል፤ ብለዋል ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፡፡

ርእሰ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስተማረን፣ ኖላዊነት፥ የጠፋውን ፈልጎ፣ የራቀውን አቅርቦ፣ የተበተነውን ሰብስቦ፣ ያዘነውን አጽናንቶ፣ መንጋውን በፍቅርና በአንድነት ጠብቆ መክሊቱን ከነትርፉ ማስረከብ ነው፡፡ ይህም፣ በሃይማኖት ምክንያት የሚመጣውን መከራ መስቀል በመቀበል የሚከናወን፣ ታማኝነትንና ትጋትን እንዲሁም መሥዋዕትነትን ጭምር ስለሚጠይቅ፣ እንደ ቀላል ነገር የማይታይ ከባድ ሓላፊነት ነው፡፡

በተለይ ቢጸ ሐሳውያን የሚዘሩት የኑፋቄ ትምህርት ትውልዱን እየተፈታተነ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ከውስጥ ስሕተት፣ ከውጭ ሐሜት ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀን ዘመናትን ካስቆጠረ ደማቅ ታሪኳ ጋራ ለሚቀጥለው ትውልድ ለማሻገር፤ ከመናፍቃን ኅብረት፣ ከኑፋቄ ትምህርት እንድርቅና እንድንጠነቀቅ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ዑቊ እንከ ኢይትረከብ በላዕለ አሐዱ እምኔክሙ ልብ እኵይ፣ ወሕጹጽ ሃይማኖቱ ወኑፉቅ ዘያርሕቅሙ እም እግዚአብሔር ሕያው = ከእናንተ ክፉ ሐሳብ ያለው ሃይማኖቱ የጎደለ ከሕያው እግዚአብሔር የሚያርቃችሁ ተጠራጣሪ አንድም እንኳ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤” በማለት ሐዋርያው ይመክራል፡፡ (ዕብ.3፥12)

ብፁዕነታቸው እንደተናገሩት፣ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳውያን መሪዎች፣ እግዚአብሔር ምእመናንን የሚያይባቸው ዐይኖቹ፣ የወደቁትን የሚያነሣባቸው እጆቹ፣ የባዘኑትን የሚፈልግባቸው እግሮቹ፣ ያዘኑትን የሚያጽናናባቸው አንደበቶቹ ስለኾኑ መንፈሳዊ መግቦቱ እንዳይቋረጥ ለምእመናን ቃለ እግዚአብሔርን በትጋትና በታማኝነት እንዲመግቡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “ለኖሎት ይደልዎሙ ይኩኑ ንቄሃነ ወትጉሃነ… እረኞች ነቅተውና ተግተው ማስተማር ይገባቸዋል፤” ብሏል(ድርሳን ፴፬፥፶፬)

በስንዴው መካከል እንክርዳድ፣ በእምነት መካከል ክሕደት፣ በሰላም መካከል ጠብና ክርክር ከሚዘሩ፣ በእናት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ እብነ ዘለፋ ከሚወረውሩ የተሐድሶ መናፍቃንና የክሕደት ትምህርታቸው የተነሣ በእግዚአብሔር ቤት ጥፋት እየበዛ እንዳይሔድ የዐዲሱ ትውልድ መሪዎችና ተጠሪዎች ኾነን ቤቱን ልንመራ፣ ስለ ሕዝቡ በፊቱ ልንቆም የተጠራን መኾናችንን ሳንዘነጋ ከምንጊዜውም በበለጠ ተጠናክረን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና ሕዝባችንን ልንጠብቅ፣ ዋጋም ልንከፍል ይገባል፡፡

ሕይወታቸውን ስለ መንጋው አሳልፈው ከሰጡት ጥንታውያን አበው መካከል አንዱ የኾነው ቅዱስ አግናጥዮስ፣ “ወእትዌከፍ ሕማመ በእንተ ክብራ ለቤተ ክርስቲያን ወበእንተ ሕይወት ኵሉ ሕዝብ” እያለ ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብርና ስለ ሕዝቡ ኹሉ ሕይወት ዋጋ መክፈል የሚገባ መኾኑን ያስተምራል፡፡ በዚህ ፍኖተ ጽድቅ፣ የቀደሙ አባቶቻችን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸው ካላቸው አርቆ አሳቢነት የተነሣ የምድር ጨው፣ የተራራ ላይ መንደር፣ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ የሚለውን አምላካዊ ጥሪ ሳይዘነጉ መልካም አስተዳደርን መርሕ በማድረግ ለሀገራቸውና ለቤተ ክርስቲያናቸው ዕድገት፣ ለአብነት ት/ቤቶች መጠናከር፣ ለጥንታውያን ገዳማት መስፋፋት ቅድሚያ በመስጠት ዘመን ተሻጋሪ የቅድስና ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንትም፣ እግዚአ መምህራን ክርስቶስ አስበ ፃማችንን ይከፍለናል፤ ብለው ወንበር ዘርግተው፣ ለዐይናቸው ዕንቅልፍ፣ ለጎናቸው ምንጣፍ ሳይሉ ያለዕረፍት አስተምረው ብዙ ተተኪ መምህራንን በማፍራት ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎትን በመስጠት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ኹላችንም የማንዘነጋው አኩሪ ታሪካችን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ ላይ ከሀገር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ ድረስ የአገልግሎት አድማስዋን በማስፋት መንፈሳዊ አገልግሎቷን ለምእመናን እንድታበረክትና ታላቅነቷንም ለዓለም እንድትገልጽ የበቃችበት ቁልፍ ሚና የእኒህ ሊቃውንት ያልተቋረጠ ጥረት ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜም ወቅታዊ የትኩረት አቅጣጫችን ሊኾኑ ይገባሉ ያሏቸውን ጉዳዮች በመዘርዘር አመላክተዋል – የቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ አካል የኾነውን ጠቅላይ ጽ/ቤት በበላይ ሓላፊነት የሚመሩት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፡፡ ከዝርዝሮቹም መካከል፡-

 • በአንዳንድ አህጉረ ስብከት እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እየተነሡ ያሉ ግጭቶችን መነሻቸውን በመመርመር ዘላቂ መፍትሔ በመስጠት ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ፤
 • የምእመናንን፣ የካህናትንና የወጣቶችን አስተዳደራዊ ጥያቄ ተቀብሎ በሕጉ መሠረት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት፤
 • የሰው ልጆችን እየተፈታተነ ያለውን ዘረኝነትንና ሕልያንን ወይም ሙስናን አጥብቀን መከላከልና በአሁኑ ወቅት ሲሳየ ካልአን እየኾነ ያለውን የቤተ ክርስቲያናችን ሀብትና ንብረት በአግባቡ መጠበቅና ማስጠበቅ ይገኙበታል፡፡

የምእመናንን መንፈሳዊ ሕይወት ለመጠበቅ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት፤ ወጣቶችን በሃይማኖት ኮትኩቶና በመንፈሳዊ ሥነ ምግባር አንጾ ለነገ ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ለማድረግ የሰንበት ት/ቤቶችን ማደራጀትና ማጠናከር፤ ተመልካች አጥተው በሥራ አጥነት በየቦታው እየተንከራተቱና እየተንገላቱ ያሉት ሊቃውንት፣ መነኰሳትና ካህናት እንደየሞያቸው ሥራ እንዲያገኙ ማድረግ፤ የኹሉ መገኛ ምንጭ የኾነችው የገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን በቂ አገልግሎት እንድታገኝ፣ ከዚህም ጋራ የቤተ ክርስቲያን የህልውናዋ መገለጫ የኾኑት ጥንታውያን የአብነት ት/ቤቶቻችንና ገዳሞቻችን ሙሐዘ ምሥጢራት፣ ነቅዓ ቅድሳት ኾነው በቀደመ ክብራቸውና ታሪካቸው እንዲቀጥሉ ያለንን አቅም ተጠቅመን ክፍተታችንን ለመሙላት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ በአጠቃላይ አስተዳደራችን ዘመኑን የተከተለና የዋጀ መኾን ስለሚገባው ዘመኑ ሳይቀድመን ቀድመን መገኘት እንደሚገባ ብፁዕነታቸው አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ፣ ሊቀ ኖሎት ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ የመጨረሻውን የምስጋና ቃል ለመስማትና የክብር አክሊልን ለመቀዳጀት፣ እንደ አባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት ብዙ ተግዳሮቶችን ማለፍ ግድ እንደሚል ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ አስረድተዋል፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስን አሠረ ክህነት ተከትሎ የመምሰል ሳይኾን የተግባር ሐዋርያ በመኾን ከእግዚአብሔር የተረከበውን የቤተ ክርስቲያን መጋቢነት(ኖላዊነት) ተግባር በአግባቡ ማከናወን የቻለ፣ “አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ፣ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ፤” የሚለውን አክሊለ ክብር ይጎናጸፋል፡፡

በየጊዜው በፈቃደ እግዚአብሔር ተመርጠው በመንበረ ተክለ ሃይማኖት የተሠየሙ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በየዘመነ ክህነታቸው፥ የጠፋውን ፈልገው፣ የራቀውን አቅርበው፣ የተበተነውን ሰብስበው፣ ያዘነውን አጽናንተው፣ የተሰበረውን ጠግነው፣ የተራበውን መግበው፣ የበደላቸውን ይቅር ብለው መንጋውን በፍቅርና በአንድነት በመጠበቅ ሠርተው ያስረከቡን ነገር እንዳለ ብፁዕነታቸው አዘክረዋል፡፡

ዛሬም፣ ሰላማችን የጸና፣ ሥራችን የተቃና፣ አገልግሎታችን የሠመረ፣ አንድነታችን የጠነከረ እንዲኾን፣ “እግዚኦ አምላክነ ሰላመ ሀበነ = አቤቱ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ሰላምን ስጠን” እያልን ዘወትር ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ዘላቂ ህልውና፣ ስለ ሕዝባችን አንድነት ማስተማር ተግተን መጸለይ እንዳለብንም አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም፣ ሠያሜ ካህናት ልዑል እግዚአብሔር፣ የቅዱስነታቸውን ቀሪ ዘመነ ክህነት የሥራ፣ የጤና፣ የፍቅርና የአንድነት ዘመን እንዲያደርግላቸው፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ካህናትና ምእመናን እንዲሁም በራሳቸው ስም በመመኘት ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡

 

Advertisements

3 thoughts on ““የዐዲሱ ትውልድ መሪዎችና ተጠሪዎች፥ ቤተ ክርስቲያንንና ሕዝቡን ልንጠብቅና ዋጋም ልንከፍል ይገባል!”-ዋ/ሥ/አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ

 1. Amanuel March 5, 2018 at 3:54 am Reply

  ብፁዕ አባታችን አቡነ ዲዮስቆሮስ እናንተን መድሃኒዓለም ያኑርልን !!!

  አንድ እረኛ እረኝነቱ የሚለካው ስለ ቤተክርስቲያን ቅንዓት ሲንኖረውና የተሰጠውን መክሊት በአግባቡ ጠብቆና አትርፎ ይልቁንም እንዲጠብቅ የተሰጡትን አባግዕ ጠብቆ ተንከባክቦ ከተኩላ እና ነጣቂ አስጥሎ የጠፉትንም ፈልጎ ከመንጋው በመቀላቀል አውሬ ነክሷቸው የቆሰሉትንም አክሞ ጤናቸው ዳግም እንዳይታወክ በቅርበት ሲከታተላቸው እውነትም ይሄ የመልካሙን እረኛ ፈለግ የተከተለና አደራውንም የጠበቀ ታማኝ እረኛ መሆኑን በግብሩ አስመስክሯል ማለት ነውና ክብሩ ታላቅ ነው ።

  አሁን እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ሆነና ማንም መንገደኛ እየመጣ ወደ መልካሟ በረት በመዝለቅ መንጋውን የሚያውክ ሆነ እረኛ እንደሌለው ቤቱ ወንበዴዎች እና ነጋዴዎች ነፍሰ ገዳዮችም እንዳሻቸው የሚፋንኑበት ሆነ ፤

  ድሮኮ በዚህች ቤት ለአገልግሎት የሚመረጡትና የሚሾሙት በስነ ምግባራቸው የከበሩ ትህርምተኞች ጭምቶች እና በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ሞገስ የነበራቸው ነበሩ።

  ዛሬ የሆነውን መንገሩ ጉንጭን ማልፋት ነው፤ በግልፅ ቋንቋ ዛሬ ጭምት መሆን የሚያስነቅፍ አመንዝራና ወንበዴ መሆን በኛ ቤት የሚያስከብሩ ሆኑ፤ ለመንጋው የሚራሩ ስለ ቤተክርስቲያን የሚተጉ ይሳደዱባታል የሚዘርፏት አንገተ ደንዳኖች እና ነጣቂ ተኩላዎች እንዳሻቸው በኩራት ይንጎማለሉባታል ይህንን ለእናንተ ለቀናኢያን አባቶቻችን መንገሩ ለቀባሪው ማርዳት እንደሚባለው ይሆናል ፤ታድያ ይህን ብልሽት ከምንጩ ለማድረቅ እና ቤተ ክርስቲያንን ወደቀድሞው ክብሯ ለመመለስ ቁርጠኝነቱ ለምን ጠፋ??? ።

  ይሄ ሁሉ ነገር በቅድስና ስፍራው እየተፈፀመ ሀገርስ እንዴት ከህመሟ ትፈወስ ?
  በገዢዎችም ፊት ቀርቦ ከአጥፊ ድርጊታቸው እዲታቀቡ የሚመክር እና የሚገስፅ በመጥፋቱ ሀገር እየሆነች ያለችውን ነገር ትመለከታላችሁ ።

  ቤተክርስቲያን የመገሰፅ እና የማስታረቅ ሚናዋን እና ሞገሷን ካጣች ሀገር የምትሆነውን በግልፅ እያየን ነው፤ ተወደደም ተጠላም ታመነም ተካደም እንኳንስ የኢትዮጵያ የዓለምም ሰላም ምንጯ ከዚህችው ቤተ ክርስቲያን ነው ።

  ይህንን መዘንጋት መጪውን ጊዜ እንደሚያከብደው አይጠረጠርምና መፍትሄው የጌታ የምህረት ዓይኖቹ እንዲጎበኙን የእናንተ የቀናዒያን አባቶች ትጋት ወሳኝ ነው ።

  ስለዚህ አዎን አባታችን “”የአዲሱ ትውልድ መሪዎች እና ተጠሪዎች ቤተ ክርስቲያንን እና ሕዝቡን ልትጠብቁት እና ዋጋም ልትከፍሉለት ይገባል””

  አምላካችን ሀገራችንን ከጥፋት ሕዝቧንም ከስደት ይጠብቅልን አጥፊዎቿን ያጥፋልን! ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንም በቸርነቱ ይጠብቅልን አሜን!!!!!!!

 2. Anonymous March 5, 2018 at 5:21 am Reply

  ሰውዬው (ጳጳሱ)አስመሳይ ነው የተዘጋጀለትን ሪፖርት ከማንበብ ውጭ የሚያውቀው ነገር የለም ፓትርያርኩ በማን አለብኝ በጉልበት የአዲስ አበባን ሀገረ ስብከት እንደፈለጋቸው ሲጫወቱበት እያየና እየሰማ አይመለከተኝም ከማለት ውጭ ምን አደረገ አሁን ደግሞ ተቆርቋሪ መስሎ ያዘጋጀውን ሳይሆን የተዘጋጀለትን ያነበንባል ይልቅ የወለዳቸውን ልጆች አርፎ ቢያሳድግ ይሻለዋል

 3. […] ልንከፍል ይገባል!”-ዋ/ሥ/አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ haratewahido.wordpress.com/2018/03/04/%e1…… fb.me/UudsQ1cP […]

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: