ምእመናን በብዙ የተንገላቱበት የምሥ/ጎጃም ሀ/ስብከት አቤቱታ: ሳይጣራ የተዘጋበት ውሳኔ ሕግንና አሠራርን የጣሰ ነው

east gojjam dio report

 • ልኡካኑ፣ ምንም ዐይነት የማጣራት ሥራ ሳያከናውኑ ፋይሉ እንዲዘጋ ተወሰነ
 • የቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤትን በመጋፋትና የስብሰባ ሥነ ሥርዐቱን በመጣስ የተወሰነ ነው
 • በፓትርያርኩ ጫናና በብፁዕ አባ ማርቆስ ውትወታ፣ በአጀንዳነት ቀርቦ ተወስኗል

†††

 • የቋሚ ሲኖዶሱን አጀንዳ የማቅረብ ሓላፊነት የጽ/ቤቱና የብፁዕ ዋና ጸሐፊው ነው
 • ሊቀ ጳጳሱም፣“ስለጉዳያቸው በሚታይበት ስብሰባ በአባልነት መገኘት አይችሉም፤”
 • እንዲወጡ ሲጠየቁ እምቢተኛ ከመኾናቸውም በላይ የተቃወሟቸውን ተሳድበዋል፤

†††

 • አካሔዱንና ውሳኔውን የተቃወሙት ዋና ጸሐፊውና ዋና ሥራ አስኪያጁ አልፈረሙም
 • ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ሌላ የተጠናከረ ቡድን ልከው ለማጣራት እየተዘጋጁ ነበር
 • ለሒደቱ መሰናከል ምእመናኑ ቢወቀሱም፣መነሻው በአጣሪው አባል የታየ አድልዎ ነው

†††

በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና በማኅበረ ምእመናኑ መካከል ተፈጥሮ የቆየው ውዝግብ ተጣርቶ መፍትሔ እንዲሰጠው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ቢወስንም፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና አሠራርን በጣሰ አካሔድ ፋይሉ እንዲዘጋ ተወሰነ፡፡

የምልአተ ጉባኤው ውሳኔ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት በኩል የደረሰው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ የማኅበረ ካህናቱንና የማኅበረ ምእመናኑን አቤቱታ እንዲያጠና ባለፈው ኅዳር 3 ቀን ወደ ሥፍራው የላከው ቡድን፣ ምንም ዓይነት ማጣራት እንዳላከናወነ በገለጸበት ኹኔታ፣ በሊቀ ጳጳሱ ውትወታና በፓትርያርኩ ተጽዕኖ በተላለፈ ውሳኔ ፋይሉ እንዲዘጋ መደረጉ ተገልጿል፡፡

ሦስት አባላት ያሉት አጣሪ ልኡክ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ መመሪያ በመቀበል ወደ ደብረ ማርቆስ ቢያቀናም፣ ከአቤቱታ አቅራቢ ምእመናን ጋራ በተፈጠረ አለመግባባት አንዳችም የማጣራት ሥራ ሳያከናውን ነበር የተመለሰው፡፡ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱም ባቀረበው ሪፖርት፣ ተልእኳችን ሳይሳካ በመቅረቱ በእጅጉ አዝነናል፤ከማለትና ያልተሳካበትን ምክንያት ከማብራራት በቀር በአጀንዳነት አንሥቶ ውሳኔ ለመስጠት የሚያበቃ ማስረጃና የመፍትሔ ሐሳብ አልጠቆመም፡፡

thJYRCQPD6ይህም ኾኖ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ውሳኔ ተግባራዊነት ለሚከታተለውና ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አባ ማርቆስ በተለዋጭ አባልነት ለሚገኙበት ቋሚ ሲኖዶስ ሪፖርቱ እንዲቀርብ በሰብሳቢነት የሚመሩት ፓትርያርኩ በቃል ያዝዛሉ፤ የትእዛዙም መነሻ፣ “አጣሪ ልኡካኑ ያቀረቡት ሪፖርት ለቋሚ ሲኖዶስ ይቅረብልኝ፤” የሚለው የብፁዕ አባ ማርቆስ ጥያቄና ውትወታ ነበር፡፡

ጥያቄውን ለመጀመሪያ ጊዜ ባነሡበት የቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ ቀን፣ “እነርሱ እንደፈለጉት ማድረግ ስላልቻሉ ወደ አዳራሽ አንገባም፤ አንፈልግም ብለዋል፤” በማለት አቤቱታ አቅራቢዎችን የከሠሡት ሊቀ ጳጳሱ፣ “ዛሬውኑ ውሳኔ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ፤” ሲሉ አመልክተዋል፤ ቪዲዮም እንዲታይ ጠይቀዋል፡፡ 

የሀገረ ስብከቱ ፍትሕ ፈላጊ ማኅበረ ምእመናን አዲስ አበባ ድረስ ለበርካታ ጊዜ እየተመላለሱ የተንገላቱበት ጉዳይ መኾኑን የጠቀሱት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ የኹለቱም ወገኖች ተሟልቶ ባልቀረበበት ኹኔታ በአጀንዳነት ሊያዝ እንደማይገባው በማስረዳት በቀዳሚነትና በቀጥታ ተቃውመዋል፤ ቪዲዮውም፣ ከሊቀ ጳጳሱና ከሀገረ ስብከቱ በኩል ያለውን እንጅ የሕዝቡን እውነት የማይገልጽ በመኾኑ መታየት እንደማይችል ቢናገሩም፣ በፓትርያርኩ ትእዛዝ እንዲታይ ተደርጓል፡፡

በቪሲዲው የሚታየው፣ በደብረ ማርቆስ ሲኒማ አዳራሽ አጣሪ ቡድኑና የዞኑ አስተዳደር ተወካዮች፣ በሊቀ ጳጳሱ በኩል ለተጠሩት ወገኖች መግለጫ ሲሰጡና የማጣራቱን ጅምር ነው፡፡ ከታየ በኋላ፣ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው፣ “እንግዲህ በዚህ እንዴት ብለን ነው የምንነጋገረው?” ሲሉ መጠየቃቸውን አላቋረጡም፡፡ በዚህም በብፁዕ አባ ማርቆስ፣ ስድብና ኃይለ ቃል ማስተናገዳቸው ተጠቁሟል፡፡

በዕለቱ የቋሚ ሲኖዶሱ ቋሚ አባል ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ ያልነበሩ ሲኾን፣ ከተለዋጭ አባላት አንዱ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ዘግይተው ተገኝተዋል፡፡ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው እና በብፁዕ አባ ማርቆስ ሙግት መሀል የደረሱት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ ጉዳዩ ከተገለጸላቸውና ከተረዱ በኋላ በቀጥታ የጠየቁት፣ ብፁዕ አባ ማርቆስ ከስብሰባው እንዲወጡ ነበር፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 19 ቁጥር 7 መሠረት፣ “አንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ስለራሱ ጉዳይ በሚታይበት ስብሰባ ላይ በአባልነት መገኘት አይችልም፤” የሚለውን ጠቅሰው፣ “ባለጉዳዩን አስቀምጠን ነው ወይ የምንነጋገረው፤ ይውጡ እንጅ፤” ሲሉ የስብሰባው ሥነ ሥርዐት እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡

ፓትርያርኩም ፈጥነው፣“አይ፣ ሌላ አካል የለም፤ የእርሳቸው ብቻ ስለታየ ነው፤” ሲሉ ሊሸፍኑላቸው ሞክረዋል፡፡ በሀገረ ስብከታቸው ብቻ ሳይኾን በቦርድ ሰብሳቢነት በሚመሩት የቤተ ክርስቲያናችን ቴሌቪዥን የብዙኃን መገናኛ ድርጅት ቦርድ አሠራሮችን እንዳሻቸው እየጣሱ መጠቀሚያ ያደረጉት ብፁዕ አባ ማርቆስም፣ “አልወጣም” በሚል እምቢተኝነት ሕግ አፍራሽነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከበዓለ ልደት በፊት የታየው የዕለቱ ስብሰባ በዚሁ ቢጠናቀቅም፣ ከበዓለ ጥምቀት በኋላ ሥራውን በቀጠለው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ የአጣሪ ቡድኑን 3 ገጽ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በቃል ታዝዘዋል፡፡

አጣሪ ልኡካኑ፣ ምንም ዐይነት የማጣራት ሥራ እንዳላከናወኑ ከሚገልጽ አጭር ማስታወሻ ጋራ የቡድኑን 3 ገጽ ሪፖርት ያቀረቡት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁም፣ ፓትርያርኩ አመራር እንዲሰጡበት ጠይቀዋል፡፡ ሪፖርቱ ከታየ በኋላ የአጣሪ ቡድኑ አባልና በማጣራቱ ቅድመ ዝግጅት ወቅት አቤቱታ የቀረበባቸውን ሊቀ ጳጳስ በዐውደ ምሕረት እያሞካሸ ሕዝብን በማስቆጣት መሰናከል ፈጥሯል የተባለው መጋቤ ሃይማኖት አብርሃም ገረመው ማብራሪያ መስጠቱም አልቀረም፡፡

በምልአተ ጉባኤው የተወሰነው ችግሩ ተጣርቶ መፍትሔ እንዲሰጠው በመኾኑና ሪፖርቱም የተልእኮውን አለመሳካት በመግለጹ፣ ሌላ የተጠናከረ አጣሪ ቡድን መላክ እንዳለበት ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሐሳብ ተሰንዝሯል፤ ብፁዕ ዋና ጸሐፊውም፣ “ተበደልኩ ብሎ አዲስ አበባ ድረስ ስንቴ የተመላለሰ አካል ጩኸትና ልቅሶ ሳንሰማ እንዴት ተብሎ ነው ውሳኔ የሚሰጠው፤” በማለት ሌላ አጣሪ ቡድን እንዲላክ የቀረበውን ሐሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ከርእሰ መንበሩ የተሰጣቸው ምላሽ ግን፣ “ከእነዚህ በላይ ማን ትልቅ ሰው ይሔዳል፤ እነዚያ መሰብሰብ አልፈልጉም፤ ልኡኩም ያየው ነገር የለም፤ በቃ አልቋልኮ፤” የሚል ነበር፡፡

ወዲያውም ቃለ ጉባኤው እንዲነበብ አዝዘዋል፡፡ የቋሚ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት የቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት እንደመኾኑ፣ አጀንዳ አዘጋጅቶ የማቅረብ፣ ቃለ ጉባኤ የመያዝና እንዲያዝ የማድረጉ ሓላፊነት የዋና ጸሐፊው ነውና ይህንንም ጥሰት ብፁዕ ዋና ጸሐፊው ተቃውመዋል – “ባልተያዘና ባልጸደቀ አጀንዳ ምን ተደረገና ነው የሚነበበው፤” ሲሉ፤ ቃለ ጉባኤ ጸሐፊውን ገሥጸዋል፡፡ ብፁዕ አባ ማርቆስም እንደተለመደው፣ “ሳዊሮስ ናቸው እንዴ አዛዡ፣ ቅዱስነትዎ ዝም ይላሉ እንዴ፤ እርስዎ ይዘዙ እንጅ” እያሉ ሸንቁጠዋል፡፡ በፓትርያርኩ ትእዛዝ ቃለ ጉባኤው ከተነበበ በኋላ አስተያየት ሲጠየቁ፣ ብፁዕ ዋና ጸሐፊው፣ “እጄን አላስገባም፤ አልፈርምም፤” ብለዋል፤ “እርስዎ ሳይፈርሙ እኛ መፈረም አንችልም፤” ቢሏቸውም“አላምንበትም፤ አላደርገውም፤” በማለት እስከ መጨረሻው በአቋማቸው ጸንተዋል፡፡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁም፣ ጉዳዩ በተነሣበት በበቀደሙ ስብስባ እንዳልነበሩ ገልጸው አልፈረሙም፡፡

ይህን ጊዜ፣ ሕጉንና አሠራሩን አክብረው ማስከበር ያለባቸው ርእሰ መንበሩ፣ ደፍረው ለማስደፈር በሚመስል መልኩ፣ “አምጡ እኔ እፈርማለሁ፤” ብለው ፈርመዋል፤ በማስከተልም በስብሰባው ሥነ ሥርዐት መሠረት፣ መገኘትም ድምፅ መስጠትም የማይገባቸው ባለጉዳዩ ብፁዕ አባ ማርቆስ ፈርመዋል፤ ከእርሳቸውም በኋላ የወቅቱ የቋሚ ሲኖዶሱ ተለዋጭ አባላት የነበሩት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ እና ብፁዕ አቡነ ሰላማ ደግፈው ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

በዚህ ቀን፣ በቀደመው ስብሰባ፣ ሥነ ሥርዐቱን ለማስከበር የተሟገቱት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ አልነበሩም፡፡ በመኾኑም በፓትርያርኩ ተጽዕኖና በብፁዕ አባ ማርቆስ ውትወታ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት የማያውቀው አጀንዳና ውሳኔ፣ በአብላጫ ድምፅ(ከሰባቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በአራቱ ተደግፎ)፣ ማኅበረ ምእመናን በብዙ የተንገላቱበት የአቤቱታቸው ፋይል ሕግንና አሠራን በጣሰ አኳኋን እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡

የብፁዕ አባ ማርቆስ፣ የቋሚ ሲኖዶስ ተለዋጭ አባልነት ጥር 30 ቀን አብቅቷል፤ ባልተጣራ ችግር ያ ሁሉ ጥድፊያና ማሸማቀቅም፣ የሦስት ወር የቋሚ ሲኖዶስ አባልነት ጊዜያቸው ከማብቃቱ በፊት ጉዳዩን ለራሳቸው በማድላት ለማዘጋት ነበር፡፡ የሊቀ ጳጳሱ ዋነኛ ፍላጎት ጉዳዩን ለማዘጋት ብቻ አልነበረም፤“በቀረበው ሪፖርት ብቻ ንጹሕ ናቸው እንዲባሉም ነበር፤” ይላሉ ታዛቢዎች፡፡

ፋይሉን ለጊዜው ቢያዘጉትም ግና፣ ከትላንት በስቲያ የካቲት 1 ቀን በተተኪ ተለዋጭ አባላት ሥራውን በጀመረው ቋሚ ሲኖዶስ አልያም በመጪው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ዳግመኛ መታየቱ እንደማይቀር የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ የምልአተ ጉባኤውንና የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔና ትእዛዝ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ለሚመለከታቸው ሁሉ የማስተላለፍ፣ አፈጻጸሙንም የመከታተል ሓላፊነቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ነውና የሕገ ወጥ ውሳኔው ተግባራዊነት አጠያያቂ ኾኖ ይቆያል፤ ፓትርያርኩ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል ካልሸኙት በቀር፡፡

አጣሪ ቡድኑ፣ ኅዳር 11 ቀን ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ባቀረበው ሪፖርቱ፣ ለማንም ወግኖ እንዳልቆመ ገልጾ የማጣራቱም ዓላማ፣ “እውነቱን ፈልጎ በማውጣት የመፍትሔ ሐሳብ ከተጨባጭ ማስረጃ ጋራ ለውሳኔ አሰጣጥ በሚያመች መልኩ ለውሳኔ ሰጭው አካል ማቅረብ” እንደነበረ አስታውቋል፡፡ ኅዳር 4 እና 5 ቀን በደብረ ማርቆስ ከተማ በነበረው ቆይታ፥ ከዞኑ አስተዳደር፣ የጸጥታና ፍትሕ፣ የፖሊስ መምሪያ እና የከንቲባ ጽ/ቤቶች ተወካዮች ጋራ የማጣራቱ ሒደት በምን እንዴትና መቼ መኾን እንዳለበት መክሯል፡፡ በ370 ማኅበረ ምእመናን ፊርማ ተደግፎ ከቀረበው አቤቱታም የሚታወቁ አንድ ምእመን ስም በመለየት ጥሪ እንዲተላለፍ አድርጓል፡፡ በጥሪው መሠረት፣ የተመረጡት ግለሰብ መቶ የአቤቱታ አቅራቢ ምእመናንን፣ የሀገረ ስብከቱም ሥራ አስኪያጅ መቶ ምእመናንን፣ ከንቲባው ደግሞ ከየቀበሌው የተውጣጡ ኃምሳ ሽምግሌዎችን ይዘው በደብረ ማርቆስ ሲኒማ አዳራሽ እንዲገኙ ስምምነት ተደርሷል፡፡

ኾኖም ጥሪው ዘግይቶ እንደደረሳቸውና ተፈላጊውን የምእመናን ቁጥር አሟልተው ለመምጣት በበነጋው እንዲቀጠርላቸው አቤቱታ አቅራቢዎች በጠየቁት መሠረት፣ ተፈቅዶላቸው ለኅዳር 5 ቀን ከጠዋቱ 2፡00 በደብረ ማርቆስ ሲኒማ አዳራሽ ቀጠሮ እንደተያዘ ጠቅሷል፡፡ የመንግሥት ተወካዮች ባሉበት የተደረሰበት ሌላው የጋራ ስምምነትም፣ “ልኡካኑ ይዘውት ከመጡትና በደብዳቤ ከተገለጸው ቪዲዮ ካሜራ ውጭ ሞባይልና መቅረጸ ድምፅ ሁለቱም ወገን ይዞ አይገባም፤” የሚል እንደነበር አውስቷል፡፡

ይኹንና በተባለው ቀንና ሰዓት፣ አቤቱታ አቅራቢ ወገኖች ከጋራ ስምምነቱ ውጭ፣ “ቪዲዮ ካሜራ ይዘን እንግባ፤ በፕሮጀክተር የምናሳየው መረጃ ስላለን ይፈቀድልን፤” የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበው በመከልከላቸው ለመግባት ፈቃደኞች እንዳልኾኑ ገልጿል፤ “ተገቢ ያልኾነ ጩኸት በማሰማታቸው በዞኑና በከተማው ፖሊስ ወደየመጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል፤” በማለትም አክሏል፡፡ የመንግሥት አካላትም ወደ አዳራሹ ተመልሰው ከአጣሪ ቡድኑ ጋራ ስብሰባው ሊቀጥል እንደማይችል ለሊቀ ጳጳሱና ለተገኘው ሕዝብ መግለጫ በመስጠት ስብሰባው ያለውጤት መዘጋቱን አስታውቋል፡፡

ከዚያም በኋላ ውይይቱ የሚቀጥልበት ኹኔታ ይፈጠር ይኾናል በሚል ተስፋ ቡድኑ ባረፈበት ሆቴል ቆይቶ ቢከታተልም ተለዋጭ ሐሳብ እንደሌለ በከተማው ከንቲባ ስለተገለጸለት ወደ አዲስ አበባ መመለሱን ጠቅሷል፡፡“ተልእኳችን ሳይሳካ በመቅረቱ በእጅጉ አዝነን የተመለስን መኾኑን እየገለጽን የማጣራቱ ጅምር ምን እንደሚመስል እስከደረስንበት ድረስ የተቀረፀውን የምስልና የድምፅ ቅጅ ሲዲ አያይዘን ያቀረብን መኾኑን ስንገልጽ በአክብሮት ነው፤” ብሏል በሪፖርቱ ማጠቃለያ፡፡

አጣሪ ልኡካኑ፣ ለሒደቱ መሰናከል ምእመናኑን ይውቀሱ እንጅ አስተያየታቸውን የሰጡ አቤቱታ አቅራቢዎች በበኩላቸው በመንሥኤነት የሚጠቅሱት፣ የቡድኑ አባል መጋቤ ሃይማኖት አብርሃም ገረመው የታየባቸውን የገለልተኝነት ጉድለት ነው፡፡ በዋዜማው ምሽት በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሲያስተምሩ፣ ሕዝብ የጠላቸውንና ከሀገረ ስብከቱ እንዲነሡ ጥያቄ ያቀረበባቸውን ሊቀ ጳጳስ ሲያሞካሹ ይሰማሉ፤ ይህንም የምእመናኑ ተወካዮች ሲሰሙ በማጣራቱ ሒደት ተኣማኒነት ላይ ጥያቄ እንዲያነሡ አስገደዳቸው፤ “ተፈትሻችሁ ትገባላችሁ፤ ሞባይል አይፈቀድም ሲሉ ሁሉም ተስማምቶ ነበር፤ የተጠቀሱት የቡድኑ አባል በዋዜማው የገለልተኝነት ጥያቄ ከተነሣባቸው በኋላ ግን በተመዘገበና ሓላፊነት በተወሰደበት መልኩ መረጃ መያዝ እንዳለብን አምንበት፡፡ የእነርሱ መከልከል አግባብ አልነበረም፡፡ ማስረጃችንን ማቅረብ ካልቻልን፣ እጃችን ላይ የሚቀር ዶክመንትም ከሌለ መግባት አያስፈልግንም ብለን ወሰንን፤” ይላሉ ተወካዮቹ፡፡

አንድ ካሜራ ይዘን እንድንገባ ይፈቀድልን ብሎ ሕዝቡ ጠየቀ፤ የጠየቀበትም ምክንያት ከአጣሪ ኮሚቴዎች መካከል መጋቤ ሃይማኖት አብርሃም ገረመው የተባለው ልኡክ በዋዜማው በቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሲያስተምር ሊቀ ጳጳሱን ሲያሞካሽ ነበር ያመሸው፡፡ በዚህም የተነሣ ሰዉ ጥርጣሬ ስላደረበት፣ ለራሳችን በማስረጃነት የምናስቀረው አንድ ቪዲዮ ካሜራ ይዘን መግባት አለብን ብሎ ጠየቀ፤ በተጨማሪም በማጣራቱ የምናቀርባቸውን ማስረጃዎች በፕሮጀክተር እናቀርብ ብሎም ጠይቆ ነበር፡፡ ኹለቱንም አይቻልም ብለው ከለከሉ፡፡


እውነታው ይህ ኾኖ ሳለ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩም ኾኑ ብፁዕ አባ ማርቆስ ማኅበረ ቅዱሳንን ከመክሠሥ አልታቀቡም፡፡ ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ አካሔዱን ተቃውመው በቃለ ጉባኤው ላይ ባለማፈረማቸው፣ “እንዲያው አንድ ማኅበር መሀላችን ገብቶ ይበጥብጠን እንዴ፤” ብለዋል ብፁዕ አባ ማርቆስ፡፡ ፓትርያርኩም እርሳቸውን ተከትለው፣ “ይኼ ሁሉ የማኅበሩ ጫና እንደኾነ እናውቃለን፤ እየሰማንም ነው፤ እዚህ ውስጥም ደጋፊዎች እንዳላችሁ እናውቃለን፤” እያሉ ደጋግመው በግልጽ ተናግረዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ፣ የማኅበሩን ደንባዊ አገልግሎት ከማሰናከል እንዲታቀቡ ቢያስጠነቅቃቸውም አሁንም ያልታረሙት ፓትርያርኩ፣ በተለይ የማኅበሩ ዘጋቢዎች የመንበረ ፓትርያርኩን መግለጫዎች ገብተው እንዳይዘግቡ ያስተላለፉትን ክልከላ አላነሡም፤ ይህን አያያዛቸውን ሊጠቀሙበት የዶለቱት እነኃይሌ ኣብርሃ፣ ሠናይ ባያብልና የመሳሰሉት ሌባና ዋልጌ አለቆች የሚመሩት የአዲስ አበባ አድባራት አማሳኞች ቡድን፣ በየሰበካው የተጋጋለውን የምእመናኑን የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ ለማዳፈን ሊያማከሯቸው እየተዘጋጁ ይገኛሉ፡፡

ከፓትርያርኩ ፈቃድ የተቀበሉ የሚመስሉት እነብፁዕ አባ ማርቆስ፣ ብፁዕ አባ ቶማስ እና ብፁዕ አባ ሩፋኤልም በየአህጉረ ስብከታቸው፣ “ማኅበሩን በሲኖዶስ አውግዘናል፤” በሚል ሐሳዊነት፣ በማኅበሩና አባላቱ ላይ ዘመቻቸውን አጧጡፈዋል፤ በጋምቤላ ከተማ እና በአዊ ዞን አህጉረ ስብከት የማኅበሩን ጽ/ቤቶችና የግቢ ጉባኤ ሱቅ እስከ ማሸግና አባላቱንም እስከ ማሳሰር ደርሰዋል፡፡

ይህ ሁሉ ግን፣ የምሥራቅ ጎጃም ካህናት፣ ምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤቶችና ግቢ ጉባኤያት፣ መሠረታዊና ዘርፈ ብዙ ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ ችግሮች ያሉበት የብፁዕ አባ ማርቆስ አስተዳደር እያደረሰባቸው ካለውና በጥብዓት ከተቋቋሙት በደል የማይበልጥ በመኾኑ፣ የፀረ ኑፋቄና የፀረ ሙስና ንቅናቄውን በእጅጉ ቢያጠናክረው እንጅ አያዳክመውም፤ሕግንና አሠራርን እየጣሱ አገልግሎቱንና ንቅናቄውን በማዳፈን የግል ጥቅማቸውን ያለተጠያቂነት ለማካበት ለሚመኙ አማሳኞችም ከዕብነ አድማስ ጋራ እንደመላተም ይኾንባቸዋል፡፡

Advertisements

6 thoughts on “ምእመናን በብዙ የተንገላቱበት የምሥ/ጎጃም ሀ/ስብከት አቤቱታ: ሳይጣራ የተዘጋበት ውሳኔ ሕግንና አሠራርን የጣሰ ነው

 1. Amanuel February 12, 2018 at 12:55 pm Reply

  በእርግና ዘመን እንደአባ ማትያስ እና ማርቆስ ከመሆን ይሰውረን እንጂ ምን ይባላል? ስለእነኚህ ሰዎች ብዙ ተብሏልና የውሾን ነገር …ብለን እንተው ብንልም የማያንቀላፋው ጥፋታቸው መልስ እንድንሰጣቸው ይቀሰቅሰናል።

  ስዎቹ እንዲህ ግራ ግራውን ለመሮጥ መምረጣቸው በርግጥ አያስገርምም፤
  ለማይረባ አይምሮም ተላልፎ መሰጠትም በእነርሱ አልተጀመረምና አንገረምም፤ አርአያዎቻቸው እነ አርዮስ እና እነንስጥሮስ እንኳ ነገሮችን ጠየም አድርገው እባብነታቸውን እንዳንነቃባቸው ብዙ ይጥሩ ነበር ።

  እነኚህ ግን ውጊያቸው ሁሉ ግልጥልጥ ያለ እና እንዲያውም ነውራቸውን እንደክብር በመቁጠር ከእውነት ጋር በግልጥ እየተላተሙ መገደራቸው ያስገርማል ። ዳሩ ምን ያድርጉ ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች ይባልም የለ!!

  ማፈር የሚገባቸው ደፈሩና መድፈር የሚገባቸው አፍረው እንዲህ ሊሆን ቻለ!በዚህ ዘመን የእውነት ምሥክር መሆን ምንኛ ክብር ነው፤

  የሐዋርያ ግብሩ እውነትን መሥክሮ ሊሄድ እና ከክርስቶስ ጋር ለመኖር መናፈቅ መሆኑን ከቀድሞዎቹ ተምረናል ።
  ዛሬም የምንማርባቸው አሉ፤ ያማ ባይሆን የአጥፊዎቹ ግብር እንዲህ ተገልጦ ባላየን ነበር ።
  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ልሄድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ ሲል ወደዚያ መሄጃ መንገዱ የምቾት መኪና አልያም ቆንጆ ሰረገላ እንዳልሆነም ጠንቅቆ ያውቅ ነበር።ሞት እና መከራም ወደሚናፍቀው ወደርሱ (ወደ ክርስቶስ)ለመሄድ እቅፋት ሳይሆኑ መንገዶቹ እንደሆኑ በደምብ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር ።

  እንደ አባ ማትያስ እና ማርቆስ ቤተክርስቲያንን አላሳደደም፤ ይልቁንም ስለቤተ ክርስቲያን ተሰደደ እንጂ ፤ ከእነ ኔሮን ጋር በፍቅርም አልቀለጠም ቅድስት ቤተክርስቲያንንም ያገለገላት በሾመው በመንፈስ ቅዱስ እንጂ በእነርሱም ፈቃድ አልነበረም ፤ እነርሱ ለቤተ ክርስቲያን ጠንቅ ነበሩ እንጂ ለአገልግሎቷ መፍትሄዎች አልነበሩምና!!

  “የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ የሚለው ቃል ምንኛ የተወደደ ነው!!!”

  አባ ማትያስ ወማርቆስ አረጋዊ ወ ሰላማ ትምክህታችሁን ባትነግሩንም እናውቃለን፤ አንድ ነገር ግን እናውቃለን ምን አልባት ወደክርስቶስ ለመሄድ ናፍቆቱ አይኖራችሁ ይሆናል ግድ የለም እውነትን መሥክራችሁና ስለ እውነት ኖራችሁ ለማለፍ ድፍረት እና የእውነት መንፈስ ባይገኝባችሁም የምትሰሩት ጂም የምትዘሉት ገመድ እድሜን እንደማይቀጥልላችሁ ግን ጠንቅቀን እናውቃለን፤
  ስለቤተክርስቲያን መቀበል የሚገባውን መከራ እና ሞት ብትሰቀቁም በተርታ ሰው ደምብ በስኳር በግፊቱ እና በተለያዩ ደዌያት ጥሪው እዲደርሳችሁ እናምናለ ።
  እንግዲህ የቱ እንደሚሻላችሁ እኛ አንመርጥላችሁም!!!
  ግን አንድ ነገር እንመኛለን የጌታ እጅ ከብዳባችሁ እናንተን ሞት ነጥቋችሁ እኛም ፀፀቱ በገደለን!!!!!!!
  የቤተ ክርስቲያን አምላክ ፍርዳችሁን ያሳየን አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን !!!
  ይቆየን …

 2. Gebresilassie Shitahun February 13, 2018 at 1:23 am Reply

  አንድ ሰው ለማንኛውም ነገር ራሱን ፈላጭ ቆራጭ አድርጎ የሚቆጥር ከሆነ በጣም ከባድ ነው። ፈረንጆች “If you only have a hammer, you tend to see every problem as a nail.” እንደሚሉት በእጃችን ያለው ሥጋዊ ነገር ብቻ ከሆነ የምንሠራው ሥራ መንፈሳዊ ሊሆን አይችልም። መካሪዎቻችን ሥጋውያን ከሆኑ፤ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ከየት ይመጣ ይሆን? ባልንጀሮቻችን መንፈሳዊነትን በገንዘብ ልክ ቀደው ሚሰፉት ከሆነ፤ በመንፈሳዊ ገንዘብ ልክ ማሰብ ከወዴት ይመጣ ይሆን? ዛሬ ቁጭ ብለን የሰቀልነው ነገርስ ነገ ቆመን ለማውረድ ይቻል ይሆን? እኔ ግን እነደ አባቶቼ “እንደ ወዳጆቹ ሐዋርያት በአንድ ልብ መካሪ በአንድ ቃልም ተናጋሪ የደርገን ዘንድ የሰአሊተ ምኅረት የድንግል ማርያም ምልጃ እና ጥበቃ አይለየን።” ባይ ነኝ

 3. Anonymous February 17, 2018 at 2:38 am Reply

  አባ ማትያስም በስተ እርጅና ቤተክርስቲያንን ከሚያምሱ እንደ አቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኘ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ይልቀቁ ስልጣንን በገዛ ፈቃድ መልቀቅ ብስለትም አስተዋይነትም ነው ያለ በለዚያ ዝም ብሎ ስልጣን ላይ ተቀምጦ እንደ አሮጌ ውሻ መንገታገት መጨረሻ ዋጋ ያስከፍላል እነጎይቶም ከሆኑ የዘራረፉትን ይዘው አፈትልከው ከማምለጥ ውጭ አያዋጡም

 4. Anonymous February 22, 2018 at 6:55 am Reply

  አይ ሐራዎች! “የሕገ ቤተ ክርስቲያን አሠራር ተጣሰ” ነው ያላችሁት? ምነው ትላንት ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ በቋሚ ሲኖዶሱ እና ምንም በማያውቁት ፓትርያርክ አሰራር ይግባኝ ብለው ሲጮሁ እንዳልሰማ ሆናችሁ የ”ቀሲስ” ደጀኔንና፣ የ”ቀሲስ” ያሬድን ለተወገዘ መሪጌታ ያሳዩትን ቲፎዞነት ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ በዘገባችሁ በቀናት ውስጥ እናንተን የሚቆረቁር የአሠራር ጥሰት መከሰቱ የሚገርም ነው።

 5. Anonymous March 14, 2018 at 7:34 am Reply

  ጊዜ ለኩሉ
  ውድ ሐሳዊ አባቶቻችን አባ ማትያስ ወማርቆስ አረጋዊ ወ ሰላማ የምትገርሙ ናችሁ!!!!
  ቤተ-ክርስቲያን መንፈሳዊ መሪ ስታደርጋችሁ እናንተ የዘር ሹመት፣ የገንዘብ ምዝበራ፣የተሐድሶ ምንፍቅና .. የምታራምዱ ሥጋዊ ጳጳስ ሆናችሁ፡፡ ከብዙ ውሸታም አንድ እውነት ተናጋሪ አባት በእግዚአብሔር ዘንድ ከፍከፍ ያለ ነው፣ ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ኩላሊት የሚመረምር አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር በሰማይ ቤት ይመስክርላችሁ ፣ እናክብራቸሃለን እንወድሃችለን፡፡
  በአሁኑ ወቅት አባ ማርቆስ በምስ/ ጎጃም ምእመናን ላይ ርምጃቸው እውነተኛ ምእመናንን በስውር መደብደብ (ማስደብደብ) ጀምረዋል፡፡ ወንድማችን ዲ/ን ጌታቸው ደጀን ወረዳ የሚያገለግል ሲሆን ከአገልጎሎት በኋላ በመኪና አፍነው የራባ ጫካ ደብድበው ከሄዱ በኋላ ሕይወቱ ሳያልፍ ከ2 ቀን በኋላ ተገኝቷል፣ አሁን በደ/ማ ሆስፒታል ይገኛል፡፡
  አምበር ወረዳ እራሳቸው የቤ/ያን አስተዳዳሪ አድርገው የሾሟቸውን አባት አባ በትረ ማርምን ስለ እውነተኛዋ ስላስተማሩ ቡትቲያም በማለት በመሳደብ ክህነትን የሚያቃልሉ፤
  በተለያዩ ሰ/ት/ቤቶች ፤ግቢ ጉባዔያት አዳራሾች እንዲዘጉ እያደረጉ የእውነት ሳይሆን የሰይጣን አባት ሆነዋል፡፡
  የሁሉ አምላክ እግዚአብሔር መፍትሔ እስከሚያመጣ ጊዜ ለኩሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡

 6. Anonymous March 14, 2018 at 7:35 am Reply

  ጊዜ ለኩሉ
  ውድ ሐሳዊ አባቶቻችን አባ ማትያስ ወማርቆስ አረጋዊ ወ ሰላማ የምትገርሙ ናችሁ፡፡
  ቤተ-ክርስቲያን መንፈሳዊ መሪ ስታደርጋችሁ እናንተ የዘር ሹመት፣ የገንዘብ ምዝበራ፣የተሐድሶ ምንፍቅና .. የምታራምዱ ሥጋዊ ጳጳስ ሆናችሁ፡፡ ከብዙ ውሸታም አንድ እውነት ተናጋሪ አባት በእግዚአብሔር ዘንድ ከፍከፍ ያለ ነው፣ ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እና ዋና ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ኩላሊት የሚመረምር አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር በሰማይ ቤት ይመስክርላችሁ ፣ እናክብራቸሃለን እንወድሃችለን፡፡
  በአሁኑ ወቅት አባ ማርቆስ በምስ/ ጎጃም ምእመናን ላይ ርምጃቸው እውነተኛ ምእመናንን በስውር መደብደብ (ማስደብደብ) ጀምረዋል፡፡ ወንድማችን ዲ/ን ጌታቸው ደጀን ወረዳ የሚያገለግል ሲሆን ከአገልጎሎት በኋላ በመኪና አፍነው የራባ ጫካ ደብድበው ከሄዱ በኋላ ሕይወቱ ሳያልፍ ከ2 ቀን በኋላ ተገኝቷል፣ አሁን በደ/ማ ሆስፒታል ይገኛል፡፡
  አምበር ወረዳ እራሳቸው የቤ/ያን አስተዳዳሪ አድርገው የሾሟቸውን አባት አባ በትረ ማርምን ስለ እውነተኛዋ ስላስተማሩ ቡትቲያም በማለት በመሳደብ ክህነትን የሚያቃልሉ፤
  በተለያዩ ሰ/ት/ቤቶች ፤ግቢ ጉባዔያት አዳራሾች እንዲዘጉ እያደረጉ የእውነት ሳይሆን የሰይጣን አባት ሆነዋል፡፡
  የሁሉ አምላክ እግዚአብሔር መፍትሔ እስከሚያመጣ ጊዜ ለኩሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: