የሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል ምእመናን አቤቱታ: በአስቸኳይ ተጣርቶ እንዲቀርብ ቋሚ ሲኖዶሱ አዘዘ

sealite mihret plea yekatit2b

 • የሀ/ስብከቱ፣ መንግሥትና ምእመናን የጋራ ልኡክ ይቋቋማል፤
 • ልኡካኑ፣ በመጪው ማክሰኞ የማጣራት ሥራውን ይጀምራሉ፤
 • ሒደቱን ከጥርጣሬ ነጻ ለማድረግ በምስል ወድምፅ ይቀረጻል፤
 • የሀ/ስብከቱ ሥ/አስኪያጅ፣ በታጎለው ማጣራት ማብራሪያ ሰጠ፤

†††

 • ምእመናን በመቶዎች፣ለ2ኛ ጊዜ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ተሰለፉ፤
 • በማጣራቱ ፋይዳ ላይ ጥያቄ አንሥተዋል፤ አስፈላጊነቱ አወያየ፤
 • የሀገረ ስብከቱን የ“ሁከት ይወገድልኝ” ክሥ፣ ቋሚ ሲኖዶሱም ያየዋል፤
 • አጣሪውን አንቀበልም በማለታችሁ ክሡ ተመሥርቷል፤”/ፓትርያርኩ/
 • ችግሩን እያወቃችሁ ምኑን ነው የምታጣሩት?”/የምእመናኑ ተወካይ/

†††

 • የመንጋውን ድምፅ የማይሰማ እረኛ ከወዴት ነው?
 • “ክርስቲያን የኾነኹሉ ብልሹ አሠራርን ከቤተ ክርስቲያን ለማስወገድ መታገል አለበት፤”
 • “ቤተ ክርስቲያን የአምልኮና የጸሎት ስፍራ እንጅ የመዝናኛና የቅንጦት ቦታ አይደለችም፤”
 • “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፏል፤እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት፤”

/ከዛሬው የማኅበረ ምእመናኑ ኃይለ ቃሎች/
†††

sealite mihret plea yekatit2

በመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሕገ ወጥ አሠራሮች ይዞታውና ሀብቱ በልማት ሰበብ እየጠፋና እየተመዘበረ የአማሳኝ ሓላፊዎችና ግለሰቦች መጠቀሚያ የኾነው የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል በመቶዎች የሚቆጠሩ ምእመናን፣ ዛሬ፣ የካቲት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ለኹለተኛ ጊዜ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ በመትመም፣ ቋሚ ሲኖዶስ ኹነኛ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፤ ቋሚ ሲኖዶሱ በበኩሉ፥ የሀ/ስብከቱ ልኡካን፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲሁም የማኅበረ ምእመናኑ ተወካዮች ያሉበት የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋምና አቤቱታው በአስቸኳይ ተጣርቶ እንዲቀርብለት ትእዛዝ ሰጠ፡፡

የካቴድራሉ የአስተዳደር ሓላፊዎች ባለፈው ታኅሣሥ 20 ቀን በምእመናን ተቃውሞ ከተባረሩ በኋላ ችግሩን ለማጣራት ሀገረ ስብከቱ ልኡካኑን በተደጋጋሚ ቢያሰማራም፣ ከተኣማኒነት አንሥቶ በተቀመጡ ቅድመ ኹኔታዎች ሳቢያ መግባባት ላይ ባለመደረሱ መፍትሔ ሳይሰጠው ዘግይቷል፡፡ “ውሳኔ ሳይሰጠን ከግቢው አንወጣም፤” ያሉት ማኅበረ ምእመናኑ የመረጧቸው ተወካዮች ከቋሚ ሲኖዶሱ ጋራ የተወያዩ ሲኾን፤ ተጠርቶ የተጠየቀው የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑም ስለነበረው ሒደት ማብራሪያ መስጠቱ ታውቋል፡፡

“ቋሚ ሲኖዶሱ ጉዳዩን በአጀንዳ ይዞ እንደሚነጋገርበትና ከኹሉም አካላት የተውጣጣ አጣሪ ኮሚቴ ይመደባል፤” በሚለው ምላሽ ያልረኩት ምእመናኑና ተወካዮቻቸው፥ “ችግሩን እያወቃችሁ ምኑን ነው የምታጣሩት?”ሲሉ ፋይዳውን ጠይቀዋል፤ የአጣሪዎች አግባብነት፣ ማጣራቱ ስለሚወስደው ጊዜና የአፈጻጸሙ ተኣማኒነት ሊታወቅና ሊረጋገጥ እንደሚገባው አሳስበዋል፤ በተጨማሪም፣ በሀገረ ስብከቱ ስለተመሠረተባቸው ክሥ ጥያቄዎችን እንዳቀረቡ ተጠቅሷል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በሰጠው ማብራሪያ፣አጣሪ ልኡካንን በተደጋጋሚ ቢልክም ምእመናኑ አምነው ለመቀበል አለመፈለጋቸውን ተናግሯል፡፡አስተዳዳሪውን ጨምሮ አራት የጽ/ቤት ሓላፊዎችን ያገደው፣ የማጣራቱን ሒደት ለማመቻቸት እንደነበር ጠቅሶ፣ “የመንግሥት ተወካይ ይኑር፤” በሚል እንደ ቅድመ ኹኔታ የቀረበውንም ተቀብሎ የክፍለ ከተማ ሓላፊዎችን ለማካተት ጥረት ማድረጉን ገልጿል፡፡

አስተዳዳሪው ተገኝቶ ሰነድ ባላቀረበበት፤ በሰነዱም ላይ የእምነት ክሕደት ቃሉን ባልሰጠበት አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ እንደማይቻል የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ሳይጣራ የሚወሰድ ርምጃ እንደሌለና ችግሩ በማጣራት ከተረጋገጠ ደግሞ፣ እስከ ማባረር ሊደርስ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡ “መረጃ ያጠፋል፤ ሰነድ ይደብቃል፤” እንዳይባል አግዶ ለማጣራት እንደተሞከረ ጠቅሰው፣ ከተጣራ በኋላ ማዘዋወር አልያም ማገድ ብቻ ሳይኾን፣ “ማባረርም ይቻላል፤” ብለዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱን የ“ሁከት ይወገድልኝ” ክሥ በተመለከተም፣ “አጣሪውን አንቀበልም በማለታችሁ እንግዲህስ መንፈሳውያን አይደሉም፤ ጥያቄአቸው ሌላ ነው በሚል ነው ወደ ፍ/ቤት የተኬደው፤” በማለት የክሡን አግባብነት ደግፈዋል፡፡ ምእመናኑ በጉልሕ ጽሕፈት ከያዟቸው ኃይለ ቃሎች አንዱ፡- “የመንጋውን ድምፅ የማይሰማ እረኛ ከወዴት ነው?” የሚል መጠየቅ ይገኝበታል፡፡

እስከ ግንቦት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ድረስ የቋሚ ሲኖዶሱ ተለዋጭ አባላት በመኾን ዛሬ ሥራቸውን የጀመሩት ብፁዓን አባቶች በበኩላቸው፣ አማሳኞቹ ከካቴድራሉ እንዲነሡ የተጠየቀውን ርምጃ ለመውሰድና በሕግ ለመጠየቅም ቢኾን፣ አስቀድሞ አቤቱታው መጣራት እንደሚኖርበት አስረድተዋል፤ – “ራሱን አጣሪውንምኮ ለማጋለጥ ያመቻል፤” ሲሉ የሒደቱን አስፈላጊነት አስገንዝበዋል፤ ክሡን በተመለከተም ቋሚ ሲኖዶሱ የሚያውቀው ጉዳይ ባይኖርም እንደሚመለከተው ጠቁመዋል፡፡

በተደረሰበት ስምምነት መሠረት፣ ሀገረ ስብከቱ ከሚመድባቸው ልኡካን በተጨማሪ፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት የክፍለ ከተማው አስተዳደርና ፖሊስ አካላት እንዲሁም ከአቤቱታ አቅራቢ ማኅበረ ምእመናን የተውጣጣ የጋራ አጣሪ ኮሚቴ በአፋጣኝ ይቋቋማል፤ ማጣራቱ በመጪው ማክሰኞ ይጀመራል፤ አስተዳዳሪውና የጽ/ቤት ሓላፊዎቹ ተገኝተው ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣሉ፤ አጠቃላይ ሒደቱም በታመነበት የተመረጠ አካል በቪዲዮ ተቀርፆና ሪፖርቱም ተጠናቅሮ የጋራ መተማመን ከተደረሰበት በኋላ ለቋሚ ሲኖዶሱ ቀርቦ ውሳኔ ያገኛል፡፡

His Grace Abune Sawiros with SM faithfuls

ዛሬ ከጧቱ ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርኩ ተገኝተውና “ለወራት ካቴድራሉን እየጠበቅን ቆይተናል፤ ኹነኛ መፍትሔ በአፋጣኝ እንዲሰጠን እንፈልጋለን፤ ውሳኔ ሳትሰጡን ከግቢው አንወጣም፤” ብለው እስከ ተሲዓት የቆዩትን ከ600 ያላነሱ ማኅበረ ምእመናን፣ ከጽ/ቤት ሠራተኞቻቸው ጋራ ወጥተው ያነጋገሩት ዋና ጸሐፊው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ናቸው – “ክርስቲያን የኾነ ኹሉ ብልሹ አሠራርን ከቤተ ክርስቲያን ለማስወገድ መታገል አለበት፤” ይላል፣ ወቅታዊው የማኅበረ ምእመናኑ ኃይለ ቃል፡፡

Advertisements

One thought on “የሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል ምእመናን አቤቱታ: በአስቸኳይ ተጣርቶ እንዲቀርብ ቋሚ ሲኖዶሱ አዘዘ

 1. Anonymous February 9, 2018 at 7:44 pm Reply

  በጣም ይገርማል ፓትርያርኩ ግን ጤነኛ ናቸው?እኔ ግን አይመስለኝም የሂትለርን ባሕርይ ተላብሶ ሀገረ ስብከት የገባው ጨካኙና መናፍቁ ዘረኛውና አረመኔው ጎይቶም የተባለው ሥራ አሥኪያጃቸው ስንቱን ንፁሕ አስተዳዳሪ በቂም በቀል እያፈናቀለ ቦታውን በሃራጅ ሲቸበችብና ብዙኃኑን ለረሃብና ለስደት ሲዳርግ እየተመለከቱ ትንፍሽ ያላሉት አባ ማትያስ የሰአሊተ ምሕረቱ ዋልጌውና ክህነት አልባው አስተዳዳሪ ደብሩን የግሉ ድርጅት አድርጎ ሲጫወትበትና ይህን ሁሉ የቤተ ክርስቲያን መንጋ ሲያሳዝንና ሲያስለቅስ እየተመለከቱ ለባለጌውና ውዳሴ ማርያም እንኳን ለማይደግመውና ለአንድ ዱርዬ አስተዳዳሪ ወግነው መቆማቸውን ስመለከት ውስጤ እጅግ ያዝናል
  ይህ ሁሉ በደል በማንም ሳይሆን በመንግሥት የተፈጸመብን ነው ምክንያቱም አባ ማትያስን ፓትርያርክ አድርጎ የሾመው እራሱ መንገሥት ስለሆነ ነው
  በአባ ማትያስ ምርጫ ሰዓት መርጫውን በከፍተኛ ሁኔታ የመራው የመንግሥት የደህንነት አካል ነው እያንዳንዱ መራጭ ቀደም ብሎ በየ ሀገረ ስብከቱ በደህንነት አካላት በተሰጠው መመሪያ መሠረት ነው ሰውዬውን የመረጠው ከመራጮቹ መካከል እኔው አራሴ አንዱ መራጭ በመሆኔ የምርጫውን ሂደት ጠንቅቄ አውቀዋለሁ እናም ውጤቱም አሁን የምናየውን አስከተለ፡፡እኚህ ሰውዬ መኝታ ክፍላቸው ሊዘጋባቸውና ቤተክርስቲያኗ በእንደራሴ ሊቀ ጳጳስ መመራት አለባት ሲኖዶሱስ ቢሆን የት ደረሰ ድሮ አባ ጳውሎስ ላይ ዘራፍ ሲል የሚውለው አስመሳይ ሁሉ የት ደረሰ ብቻ ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ወጥቷል ለማንኛውም ሰው ከመጫረሱ በፊት አንድ ነገር በሏቸው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: