ሀ/ስብከቱ: በምእመናን የተባረሩትን የሰዓሊተ ምሕረት አለቃና የጽ/ቤት ሓላፊዎች አገደ፤ ማጣራቱ ይጠበቃል

 • አቤቱታው እስኪጣራ፣በሀ/ስብከቱ የካህናት አስተዳደር እና በቄሰ ገበዙ ይመራል
 • በምእመናኑ ቅድመ ኹኔታዎች መጠናከር፣የማጣራቱ ሒደት ገና አልተጀመረም
 • የተባረሩት እንደማይመለሱ ማረጋገጥና አጣሪውን ዳግመኛ ማዋቀር ይገኝበታል
 • “ከማጣራቱ በፊት የሰበካ ጉባኤ ምርጫ፤” የሚለውም ሌላው ቅድመ ኹኔታ ነው
 • ምእመናኑን በፖሊስ ለማስወጣት፣ሀገረ ስብከቱ ለ2ኛ ጊዜ በደብዳቤ ጠይቆ ነበር

†††

 • ጥቅመኛነት፣ሀ/ስብከቱ እንዳይታመንና ቅድመ ኹኔታ እንዲጠናከር አድርጓል
 • አለቃውን በሪፖርት ነጻ አድርገን እናዛውረዋለን፤”የሚሉ የአጣሪው አባላት አሉ
 • አስተዳደራዊ ሥራው በመስተጓጎሉ፣ማኅበረ ካህናቱ ደመወዝ አልተከፈላቸውም
 • ማጣራቱ ሰኞ ይጀመራል፤በጊዜያዊነት የተመደቡት ሓላፊ ትውውቅ አድርገዋል
 • ተጣርቶ ውሳኔ ተሰጥቶ አስተዳደሩ እስኪመደብ ድረስ የቢሮውን ሥራ ይመራሉ

†††

Copy of sealite mihret cathedral officials banned

በልማት ሰበብ ሕግና አሠራር በዓምባገነንነት እየተጣሰ ከሚፈጸም ምዝበራና የቅርስ ውድመት ጋራ በተያያዘ በማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት አቤቱታ የቀረበባቸው፣ የአዲስ አበባ ደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል አስተዳዳሪ እና ሦስት የጽ/ቤቱ ሓላፊዎች በሀገረ ስብከቱ ታገዱ፡፡

በማኅበረ ምእመናኑ የኃይል ርምጃ በተባረረው የካቴድራሉ አስተዳደር ላይ ለማካሔድ የታሰበው ማጣራት፣ በቅድመ ኹኔታዎች መጠናከር ሳቢያ አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት በአኹኑ ወቅት፣ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ ትላንት ኀሙስ፣ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ችግሩ በግልጽ ተጣርቶ የመጨረሻ እልባት እስኪሰጠው ድረስ፡-

 1. አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣
 2. ዋና ጸሐፊው ሊቀ አእላፍ ዕፁብ የማነ ብርሃን፣
 3. ሒሳብ ሹሙ ሊቀ ትጉሃን ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃ፣
 4. ተቆጣጣሪው ቀሲስ ሳሙኤል ደሳለኝ፣

ከያዙት ሓላፊነት ታግደው እንዲቆዩ መወሰኑን በየስማቸው በላከው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡

“በተፈጠረው ከፍተኛ ችግር ምክንያት” የካቴድራሉ አስተዳደራዊ ሥራ ተስተጓጉሎ እንደሚገኝ በውሳኔው የጠቀሰው ጽ/ቤቱ፣ ተጣርቶ መፍትሔ እስኪሰጠው ድረስ የቢሮ እንቅስቃሴውን እያከናወኑ እንዲቆዩ፣ የሀገረ ስብከቱን የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ሓላፊ መልአከ ገነት አባ ገብረ ሥላሴ ስንሻውን እንደመደበ ገልጿል፡፡

የአማሳኝ ሓላፊዎቹ እገዳ፣ የማኅበረ ምእመናኑን የተቃውሞ ጽናት ተከትሎ ከተለያዩ አካላት በተሰጡ ምክሮችና ከፓትርያርኩ በተላለፈ ቀጥተኛ ትእዛዝ እንደተወሰነና የጊዜያዊ ሓላፊውም ምደባ፣ በሥራ አስኪያጁ ሐሳብ አቅራቢነት እንደተካሔደ ታውቋል፡፡

የእገዳውና ጊዜያዊ ምደባው ውሳኔ፣ በደብዳቤ ከመውጣቱ በፊት መረጃው ቀድሞ የደረሰው የተባረረው የካቴድራሉ አስተዳደር፣ በአለቃው መሪነት ከትላንት በስቲያ ማምሻውን ወደ ፓትርያርኩ ዘንድ ገብቶ  ምልከታውን በማስረዳት አፈጻጸሙን ለማሰናከል ሞክሮ እንደነበርና እንዳልተሳካላት ተገልጿል፡፡

አለቃው ኀሙስ ማምሻውን ሌሎቹን የጽ/ቤት ሓላፊዎች ይዞ ወደ ፓትርያርኩ በመሔድ እገዳውን ለማስቀረት ሞክሮ ነበር፡፡ ይኼ አቋም በየአጥቢያው ከቀጠለ ማንም ወንበዴ እየተነሣ፣ ከዚህ በኋላ አለቃ እየደበደበ ቤተ ክርስቲያን የምትከበርበት ነገር አይኖርም፤ በእኛ ላይ በደረሰው ለአንድ ጊዜ ትምህርት ሊወሰድ ይገባል፤ እኛ ከዚያ ቦታ ከተነሣን ለዱርዬ ልበ ሙሉነት ነው የሚሰጠው፤… ብሎ ለማሳመን ሞክሯል፤ አልተሳካለትም፤ የመነሣታቸው ነገር ወደ ኋላ የማይመለስ ኾኗል፤” ብለዋል ምንጮቹ፡፡

በውሳኔው መሠረት፣ ካቴድራሉ የሚገኝበት የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ወንድወሰን ገብረ ሥላሴ፣ ዛሬ ቅዳሜ፣ ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠዋት ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በማምራት ጊዜያዊ ሓላፊውን ከማኅበረ ካህናቱ ጋራ ማስተዋወቃቸው ተጠቁሟል፡፡

በውዝግቡ ሳቢያ የካህናቱም ደመወዝ እንዳልተከፈለ የተገለጸ ሲኾን፣ ደመወዝ ከማውጣትና ሙዳየ ምጽዋት ከማስቆጠር ጀምሮ ከቄሰ ገበዙ ጋራ በመኾን ሥራውን ማስተባበርና መምራት ይጠበቅባቸዋል፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በመኾን የታሸጉ ቢሮዎችን በማስከፈት ለማጣራቱ ኹኔታዎችን ማመቻቸትም ይኖርባቸዋል፡፡ የማጣራት ሒደቱም፣ በመጪው ሰኞ ጥር 7 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ሀገረ ስብከቱ ቀደም ሲል በመደባቸውና አምስት አባላት ባሉት ልኡካን እንደሚጀመር ተጠቁሟል፡፡

ኾኖም ማኅበረ ምእመናኑ አጠናክረው ባቀረቧቸው ሦስት ቅድመ ኹኔታዎች ሳቢያ የማጣራት ሒደቱ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ተገልጿል፡፡ አጣሪ ልኡኩ ከተለያዩ አካላት ተወጣጥቶ ዳግም ይዋቀርልን፤ ማጣራቱ ከመጀመሩ በፊት አስተዳዳሪ ይመደብልን፤ የሰበካ ጉባኤ ምርጫም ይካሔድልን የሚሉት የቅድመ ኹኔታዎቹ መነሻዎች፣ በሀ/ስብከቱ ከተለመደው የጥቅመኝነት ትስስር አንጻር ሒደቱን ከአሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከልና የተባረረው አማሳኝ አስተዳደር እንደማይመለስ ማረጋገጫ ለመጠየቅ ነው፤ ተብሏል፡፡

የአጣሪ ልኡካኑ አንዳንድ አባላት ዝንባሌ፣ በካቴድራሉና ሌሎች አድባራት ከተደረጉ ማጣራቶች የሚታወቅ በመኾኑ፣ ምእመናኑን፣ ሌሎች አካላት ተጨምረውበት ዳግም ይዋቀርልን፤ እንዲሉ አስገድዷቸዋል፡፡ የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ “ማስረጃውንና ስጡንና መዝኑን፤ በአጭር ቀናት ውስጥ ውጤቱን እናሳያችሁ፤” ቢልም፣ ከልኡካኑ አንዳንዶቹ ከታገደው አስተዳደር ጋራ እንዳላቸው በሚነገረው ልዩ ግንኙነትና በስፋት በሚታወቀው የጥቅመኝነት ዝንባሌያቸው ምክንያት ሀገረ ስብከቱ ተኣማኒነት እንዲያጣ፣ ለቅድመ ኹኔታውም መጠናከርና ለአጠቃላይ ሒደቱ መጓተት በመንሥኤነት ተጠቅሷል፡፡

ባለፈው ሳምንት ዓርብ፣ በመንግሥታዊው የቦሌ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ አወያይነት በተደረሰው መግባባት መሠረት፣ ማጣራቱ በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 30 ቀን ሰኞ እንደሚጀመር ተገልጾ አጣሪው ልኡክ በዕለቱ በካቴድራሉ ቢገኝም፣ የተኣማኒነቱ ጥያቄ በማኅበረ ምእመናኑ ተወካዮች ዳግመኛ ተነሥቷል፡፡

“ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል የተውጣጡ ተወካዮች በአጣሪነት እንዲካተቱ እንፈልጋለን፤” ያሉት ማኅበረ ምእመናኑ፣ አጣሪ ልኡኩ ዳግም እንዲዋቀር ጠይቀዋል፤ ምክንያታቸውን ሲገልጹም፣ “ሀገረ ስብከቱን ስለማናምነው ነው፤” ማለታቸው ተመልክቷል፡፡

የልኡኩ ሰብሳቢ ሊቀ መዘምራን ብርሃኑ ጌጡ፣ ስለ ተልእኳቸው ማኅበረ ምእመናኑን ለማግባባት ቢሞክሩም ባለመሳካቱ፣ “እኛ ችግር የለብንም፤ የሀገረ ስብከቱ መልእክተኞች ነን፤ እኔም በዚህ ዕድሜዬ መዋረድ አልፈልግም፤” በማለት ከካቴድራሉ ተመልሰው ስለቆይታቸው ለሥራ አስኪያጁ አስቸኳይ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ከተባረረው የካቴድራሉ አስተዳደር ለመጠቀም ያሰፈሰፉ አንዳንድ የአጣሪ ልኡክ አባላት በአንጻሩ፣ “እንዴት ሀገረ ስብከቱን አናምንም ይሉናል፤ ተሰደብን፤ ተዋረድን፤” በማለት “ምእመናኑን በኃይል ከካቴድራሉ በማስወጣት ሀገረ ስብከቱ ሥልጣኑን እንዲያስከብር” በማለት ሐሳብ ማቅረባቸው ተገልጿል፡፡

ሥራ አስኪያጁንም በመወትወት፣ ባለፈው ረቡዕ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባጻፉት ደብዳቤ፣ ከታኅሣሥ 20 ቀን ጀምሮ አማሳኙን አስተዳደር በማባረር ካቴድራላቸውን እየጠበቁ ያሉትን ምእመናን በኃይል ለማስወጣት ርምጃ እንዲወሰድ ለኹለተኛ ጊዜ ጠይቀዋል፡፡ ይኹንና ለአመራሩ አደጋ የሚያስከትልና አግባብነትም የሌለው አካሔድ በመኾኑ ሥራ አስኪያጁ እንዲያጤነው ጠንክረው ባሳሰቡት የጽ/ቤቱ ሠራተኞችና የውጭ አካላት ምክር ተፈጻሚ ሳይኾን መቅረቱ ተነግሯል፡፡

ርምጃው እንዲወሰድ የጠየቁት የአጣሪ ልኡኩ አንዳንድ አባላት፣ “በአቤቱታ አቅራቢ ምእመናን ላይ ግልጽ ጥላቻ ያላቸው፣ በጥፋተኝነት የፈረጁና በገለልተኝነት ሊሠሩ የማይችሉ በመኾናቸው መውጣት አለባቸው፤” የሚል ስሞታ እየቀረበባቸውም ይገኛል፡፡ በማጣራት ሪፖርቱ፣ “የተባረረውን አስተዳዳሪ አድነን/ነጻ አድርገን/ በዝውውር እናነሣዋለን፤” እያሉ ሲናገሩ መሰማታቸው፣ ከሒደቱ፣ የምእመናኑን አቤቱታ ለመመለስና የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስከበር ሳይኾን ራሳቸውን ለመጥቀም እንዳሰፈሰፉ በተጨባጭ ያረጋግጣል፡፡

ከውዝግቡ የግል ጥቅም ለማትረፍ ያሰቡበት ሌላም ስልት አላቸው፡፡ በካቴድራሉ በእልቅና ለመመደብ ከቋመጡ አማሳኞች ለመጠቀም ከወዲሁ ድለላቸውን ማጧጧፋቸው ተደርሶበታል፡፡ የማኅበረ ምእመናኑ ተቃውሞ ወደ ኋላ የማይመለስ መኾኑን በማየት፣ በእልቅና ለመመደብ ለሚፈልጉ የሌሎች አድባራት አለቆች፣ ከ300 እስከ 500ሺሕ ብር እንዲያዘጋጁ በየውስኪ ቤቱ እየተደራደሩ እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡ በካቴድራሉና በቅርቡ አስተዳዳሪዎች በማጣራት በተነሡባቸው ሌሎች አድባራት የተተኪ አለቆች ድለላው ተጧጡፏል፤ አጣሪዎቹ በሕዝብ አመኔታ ዕጦት ከታገደው አስተዳደር ያጡትን ጥቅም የሚያካክሡበትና የሚበቀሉበት ነው፤” ብለዋል- በቅርበት የሚከታተሏቸው ታዛቢዎች፡፡  

የኾነው ኾኖ፣ ልዩ ሀገረ ስብከቱን በበላይነት በሚመሩት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ዘንድ፣ በተባረረው የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል አስተዳዳሪ ላይ የተያዘው አቋም፣ “ጥፋት ካለበት ርምጃ ይወሰድበታል፤ ከሌለበት ይቀየራል፤” የሚል እንደኾነ ተሰምቷል፡፡ ይህም፣ በተኣማኒነት ዕጦት ሳቢያ አጣብቂኝ ውስጥ የገባውን የማጣራት ሒደት ለማስቀጠል የሚያበረታታ በመኾኑ፣ ሒደቱ በመጪው ሰኞ ሲጀመር፣ የማኅበረ ምእመናን ተወካዮች ንቁ ተሳትፎና ጥብቅ ክትትል በማድረግ ለተፈላጊው ውጤት እንዲተባበሩና እንዲተጉ ተጠይቋል፡፡

ዘግይቶ እንደተሰማው፣ በጊዜያዊነት የተመደቡት የሀገረ ስብከቱ የካህናት አስተዳደር ዋና ክፍል ሓላፊ መልአከ ገነት አባ ገብረ ሥላሴ ስንሻው፣ ዛሬ ጠዋት በቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አማካይነት ከማኅበረ ካህናቱና በሰዓቱ በካቴድራሉ ጥበቃ ላይ ከሚገኙት ማኅበረ ምእመናን ጋራ ትውውቅ እንዳደረጉና በቀጣይ አሠራሮችና አካሔዶች ላይ እንደተወያዩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የማጣራት ሒደቱን ለማመቻቸት ከሚፈጸሙ ተግባራት መካከል፣ “ሻኪሶ” እየተባለ የሚጠራውና የተባረረው አስተዳዳሪ ቢሮ፣ በታዛቢዎች ፊት እሽጉ ተከፍቶ በጥብቅ ይፈተሽ፤ ንብረቱም ይመዝገብ፤ የሚለው በውይይቱ ከተነሡት ነጥቦች እንደሚገኝበት ተጠቁሟል፡፡

Advertisements

One thought on “ሀ/ስብከቱ: በምእመናን የተባረሩትን የሰዓሊተ ምሕረት አለቃና የጽ/ቤት ሓላፊዎች አገደ፤ ማጣራቱ ይጠበቃል

 1. Anonymous January 15, 2018 at 6:08 am Reply

  Egziabher selamun yawrdlin.

  I hope it will end up peacefully and constructively for the peace and unity of the church and spiritual health of its followers.

  I do appreciate the Patriarch on his stands.

  I am also happy that the police denies the request of the manager of the Addis Ababa Hagere Sibket to use force against church followers. I found it to be a wise and responsible decision / action.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: