የ፳፻፲ ዓ.ም በዓለ ልደተ እግዚእ-የኢኦተቤ ቴቪ(EOTC Tv) መደበኛ ሥርጭት ፩ኛ ዓመት፤ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ይጀምራል

 • በስብከተ ወንጌልና በመዝሙራት ይጀምራልየስቱዲዮና የዐውደ ምሕረት ቀረጻዎች ይቀርባሉ
 • የሰው ኃይሉ እስኪሟላ፣ በቋንቋዎቹ ተናጋሪዎች ብፁዓን አባቶችና መደበኛ አገልጋዮች ይታገዛል
 • ጋዜጠኞቹ ሰሎሞን መንግሥቱ የአፋን ኦሮሞን፤ኃይሉ በላይ ደግሞ የትግርኛውን ያስተባብራሉ
 • በሌሎችም ቋንቋዎችም ማሠራጨት የድርጅቱ ዕቅድ ነው፤ የዝግጅት መዋቅሩ ሲሟላ ይስፋፋል
 • የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች መቀበያ አሠራር ተጠንቶ ለቦርዱ ቀርቧል፤ ሲጸድቅ ለማጠናከር ያግዛል
 • ከሰንበት ት/ቤቶችና ከአህጉረ ስብከት የፀረ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ጉባኤያትጋ ለመሥራት ዐቀደ

†††

የቤተ ክርስቲያንን ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ የማሳወቅ፣ እምነቷንና ሥርዐቷን የማስተማር ሚዲያዊ ተልእኮ ያለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሳተላይት ቴሌቭዥን(EOTC Tv)፣ መደበኛ ሥርጭቱን ከጀመረ፣ ነገ ታኅሣሥ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በምናከብረው በዓለ ልደተ እግዚእ አንደኛ ዓመቱ፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

የቴሌቪዥን ጣቢያውን የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት አጭር ዓመታዊ ሪፖርት
 • 24 ሰዓት – 13 መርሐ ግብሮች – ጥቂት ሠራተኞች – መጠነኛ ድግግሞሽ
 • የአየር ሰዓቱን ማጋራት እና መሸጥ ሲጀመር እንደሚስተካከል ይታመናል
 • የገበያ ጥናት መመሪያው ተዘጋጅቷል፤ በቦርድ ጸድቋል፤ወደ ሥራ ይገባል፤
 • በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ማሰራጨት ዕቅዱ ነው፤ መዋቅሩ ሲሟላ ይጀምራል
 • በሞያተኛ ቅጥርና የስርጭት አድማሱን ለማስፋት ድረ ገጹን ያጠናክራል፤
 • በዐዲስ አሠራሮችና ግንባታዎች የተሻለ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ ነው፤

†††

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት በአስተዳደሩም ይኹን በቴክኒኩ አዲስ ቢኾንም፣ ለወደፊቱ በከፍተኛ ደረጃ አድጎ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግል በሚችልበት መንገድ ተዋቅሯል፡፡ ግልጽና ተጠሪነት ያለው የራሱ አስተዳደር በውስጡም ሞያንና ልምድን መሠረት ያደረጉ የሥራ መመሪያዎችና ዋና ክፍሎች ተዋቅረዋል፡፡ ድርጅቱ ካለበት ሰፊ ሥራና ከባድ ሓላፊነት አንጻር በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አባታዊ አመራር ቋሚ ቢሮና የቀረጻ ስቱዲዮ በመኾን የሚያገለግሉ መጠነኛ ክፍሎች በጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ተሰጥቷል፡፡

ድርጅቱ፣ የመጀመሪያውን የቤተ ክርስቲያኒቱን የሳተላይት ቴሌቭዥን የሙከራ ሥርጭት በሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም. በቅዱስነታቸው ጸሎተ ቡራኬ በመጀመር እስከ ታኅሣሥ 2009 ዓ.ም. ካሰራጨ በኋላ መደበኛ ሥርጭቱን በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች ጀምሯል፡፡ በመርሐ ግብር ዝግጅት፣ ቴክኒክና አስተዳደር ሠራተኞችን በከፍተኛ ጥንቃቄና በፈተና በመቅጠር፣ ዕቃዎችን በመግዛት፣ የአስተዳደር መዋቅሩን የሚያጠናክሩ ደንቦች፣ ደረሰኞችና ሥርዐቶች የመሳሰሉትን ድርጅቱን ለማቋቋም አስፈላጊ የኾኑ የመዋቅር፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ የመርሐ ግብር እና የቴክኒክ ሥራዎችን ቀን ከሌሊት በማከናወን ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ትልቅ የሚዲያ ድርጅት እንዲኖራት ተደርጓል፡፡

በሊቃውንት ጉባኤ ቀርበውና ተመርምረው ባለፉ የመርሐ ግብር ዐይነትና ይዘት ዝርዝሮች አማካይነት ይዘቱንና ዐይነቱን የሚያርምና የሚገመግም የኤዲቶሪያል(አርትዖት) ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ከድርጅቱ ዕድሜ አንጻር የሥርጭቱ ጥራትና ይዘት በተቻለ መጠን የተሟላ ነው፡፡

በመርሐ ግብር ዝግጅት በኩል፣ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ሐዋርያዊ መልእክቶች፣ ጉዞዎች፣ አባታዊ አመራሮች ጀምሮ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፣ የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መንፈሳዊ ትምህርቶችና መልእክቶች፣ የልማት፣ የማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎች፤ የቀደሙት አበው ቀረጻዎች ሳይቀሩ ተሰራጭተዋል፡፡ በስብከተ ወንጌል፥ ሐዲሳን ኤጲስ ቆጶሳትን ጨምሮ ኹሉም አበው ሊቃነ ጳጳሳት በሙሉ ስብከቶቻቸው ተሰራጭቷል፤ የበርካታ ሊቃውንት ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥነ ምግባር፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ፣ የዜማ፣ የአቋቋም፣ ሥርዐተ ቅዳሴ፣ ትምህርተ ግእዝ፣ የግእዝ ቅኔያት፣ የወጣቶች እና የሕፃናት መርሐ ግብሮች በሰፊው ተሰራጭቷል፡፡

በቤተሰብ መርሐ ግብር፣ በተምሳሌነት፣ በዐውደ ተዋስኦ፣ ዐውደ ኅትመት፣ በዶክመንተሪ(ዘጋቢ መርሐ ግብሮች)፣ በገዳማትና ሥርዐተ ምንኵስና፣ ወቅታዊና አንገብጋቢ መርሐ ግብሮችን በማስተላለፍ ሰፊ የትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮች ቀርበዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ዓላማ፣ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ መፈጸም በመኾኑ፣ የቤተ ክርስቲያንን ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ በማሰራጨትና ሥርዐቷን በማስተማር፣ ሚዲያዊ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማገዝ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በማስተጋባት፣ የፀረ ተሐድሶ መርሐ ግብሮችን በማስተላለፍ የተወገዙ አካላትን ለኅብረተሰቡ በማሳወቅ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ባሉ አህጉረ ስብከት የሚከናወኑ እንቅስቃሴዎችን በዜና ቤተ ክርስቲያንና በልዩ መርሐ ግብሮች በማቅረብ፣ በሕገ ወጥ ልመና፣ በልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ የዐበይትና ልዩ ልዩ ዓመታዊ ክብረ በዓላትን፣ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎችን በሙሉ በማቅረብ ሰፊ ሥራ ሠርቷል፡፡

ይኹን እንጅ ድርጅቱ፣ አኹን ካለው አቅም አንጻር በርካታ መርሐ ግብሮችን በጥቂት ሠራተኞች በማዘጋጀት ኻያ አራት ሰዓትን ለመሸፈን በሚፈጠረው ችግር መጠነኛ ድግግሞሽ ቢኖርም ወደፊት የአየር ሰዓቱን ማጋራትና መሸጥ ሲጀመር ሙሉ በሙሉ እንደሚስተካከል ይታመናል፡፡ ገቢ ለማግኘትም፣ ከመሠረታዊ ትምህርተ ሃይማኖት፣ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተልእኮና ከድርጅቱ ዓላማ ጋራ በማይቃረን መልኩ የገበያ ጥናት መመሪያ መዘጋጀቱንና በቦርድ ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ፣ ይህን የሚያስፈጽም ባለሞያ እንዲቀጠር በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ለማሰራጨት የድርጅቱ ዕቅድ ውስጥ እንዳለና አስፈላጊው የዝግጅት መዋቅር ሲሟላ እንደሚጀመር፣ የስርጭት አድማሱን ለማስፋት ድረ ገጹን በሰፊው ለማጠናከር ዐቅዷል፡፡ በበጀት ዓመቱ፣ በዐዲስ አሠራሮችና ግንባታዎች በተሻለ ለመሥራት ዐቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

Advertisements

4 thoughts on “የ፳፻፲ ዓ.ም በዓለ ልደተ እግዚእ-የኢኦተቤ ቴቪ(EOTC Tv) መደበኛ ሥርጭት ፩ኛ ዓመት፤ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ይጀምራል

 1. አባ ኢየሱስ ሞዓ January 6, 2018 at 8:22 pm Reply

  በማኅበረ ቅዱሳን ትጽእኖ እንጂ በዚህ ዓመት ዕቅዳቸው ላይ የነበረም አይመስለኝም።በመጀመሩ ግን ደስ ብሎኛል።

 2. Amanuel January 8, 2018 at 10:23 am Reply

  በርካታ መርሃ ግብሮችን በጥቂት ሰራተኞች በማዘጋጀት ኻያ አራት ሰዓትን ለመሸፈን በሚፈጠረው ችግር መጠነኛ ድግግሞሽ ቢኖርም?

  እውነት እንነጋገር ከባለማ ድግግሞሹ አሰልቺ ብቻም ሳይሆን አታካች ነው ።
  ቤተ ክርስቲያኗ እጅግ በርካታ ለሀገርም የሚተርፉ የበቁ ባለሙያዎች እና ለቦታው የሚመጥኑ ልጆች
  እያሏት የሌሏት ግን ይመስል በርካታ ፕሮግራሞችን በአንድ ሰው እንዲያዝ ማድረጉ :-
  ለምሳሌ ቀሲስ ፋሲል የልጆች ፕሮግራም ላይ ፣ ስለወጣቶች ህይወት ፣ስለ ጋብቻ ፣ ስለ ሊቃውንቱ ፣ ኸረ እጅግ በርካታ ስለሆኑ ጉዳዮች አቅራቢ ናቸው ።

  *** የቀሲስን በጎ አገልግሎት ለመንቀፍ አይደለም ይህ የቲቪ ፕሮግራም እንደመሆኑ በመጠኑ መናፈቅም የይገባል ።
  በሁሉ ጉዳይ ሁል ጊዜ እኔ ብቻ ከተባለ እንጃ !
  ደግ አይመስለኝም።
  አንዳንዴም የአወያይነት ሙያው(ጸጋው) ፈፅሞ የሌላቸው ሰዎችም አወያይ ሆነው አይተናል ይህን የምለው እንደማንኛውም ሰው በቴሌ ቪዝን መስኮት ያየሁትን መናገሬ እንጂ ሌላ መስፈርት ኖሮኝ አይደለም ።
  የመፃህፍት ግምገማ ላይም ይኸው አታካች አቀራረብ ይታያል። እናንተየ አገልግሎት አለጸጋ በትግል አይሆንምኮ! !የየራሳችን ጸጋ አለን እና ጸጋችንን እንወቅ ያ ሲሆን ሰሚውም ተመልካቹም በተመስጦ ያያል ይሰማል ይጠቀማልም።
  አለዚያ የቲቪ ፕሮግራሙ ዘመኑን መዋጀት የሚችል ካልሆነ ተመልካችና ሰሚ በማጣት ነበር የሚባል እንዳይሆን እሰጋለሁ! !

  ዜና ቤተ ክርስቲያን ሲነበብም ቤተክርስቲያናዊ ወዝ ቢኖረውና ከ ኢብኮ የዜና አንባቢዎች የተኮረጀው የአቀራረብ ስልት ቢቀየር !

  በዚህ አጋጣሚ ግን ማመስገን ከተገባ ከታላቅ ይቅርታ ጋር ስሟን የዘነጋኋት በአወያይነት ሙያው በሚጠይቀው መሰረት ጥሩ ጥሩ ነገሮችን የምታቀርብልን እህት ምስጋና ይገባታል ።

  ቀሲስ መዝገቡም ክብር ይገባዎታል ቀሲስ ፋሲልም እባክዎ ያስፈልጉናል ግን አንድ በሳል ፕሮግራም ዪያዙልን : መ/ር ኃይሉም በርታ ሌሎቻችሁም በርቱ ድግግሞሹ ቅጥ አጥቷልና ቢስተካከል ። ለምሳሌ በርካታ ሊቃውንት ባሉባት ቤተክርስቲያን አቡነ ማርቆስ የቀረቡበትን ጊዜ ብቻ ብቻ እንኳ ብናሰላ ከ365 የዓመቱ ቀናት ውስጥ በርካታው ሆኖ እናገኘዋለን።

  እና ሁሉ በልክና በአግባቡ ቢሆን ለማለት ያህል ነው! ቸር ይግጠመን! !

 3. Anonymous January 8, 2018 at 1:15 pm Reply

  ባለ ሙያ የጠፋ ይመስል አንድ ፕሮግራም አምስትና ስድስት ጊዜ ይደጋገም ሊያውም እንጨት እንጨት የሚል ፕሮግራም ነው የተሻሉ ሰባኪዎች ባልጠፉበት ምድረ ሰካራምና ጠንቋዮች መድረኩን ተቆጣጥረውታል ወይ 12 ሚልዬን ብር ገደል ገባ ያልታደለ ቤት ያሳዝናል፡፡

 4. ሐዲስ ሐዋርያ January 11, 2018 at 12:14 am Reply

  በእውነቱ የቴሌቪዥን መርሐግብሩ መከፈቱ ሲኖዶሱን እጅግ በጣም የሚያስመሰግነው ነው፡፡ ነገር ግን አስፈላጊውን መርሐ ግብር ለማቅረብ የሰው ኃይል ይዘቱና የቴክኖሎጂ አቅርቦቱ ላይ የታሰበበት አይመስልም፡፡ ለዚህም ይመስላል ድግግሞሹ የበዛበት ፡፡ ይህ ቢስተካከል በምሮግራም አቅራቢዎቹ የሚቀርበው ዝግጅት እጅግ የሚያስመሰግን ነው ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግናቸው የማላልፈው አስፈላጊው ነገር ባልተሟላበት ሁኔታ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚታትሩትን የቴሌቪዥኑ አጠቃላይ ሠራተኞችን ሳላመሰግን አላልፍም እግዚአብሔር ብርታቱን ሰጥቷችሁ በቀጣይ ተደማጭና ተመራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደምታደርጉት ተስፋ አለኝ፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: