የሰዓሊተ ምሕረት ምእመናንን አቤቱታ ሰኞ ማጣራት ይጀመራል፤የክ/ከተማ ቤተ ክህነቱ ሥ/አስኪያጅና ቄሰ ገበዙ አገልግሎቱን ያስተባብራሉ

 • ማጣራቱ በመጪው ሰኞ ሀገረ ስብከቱ በመደባቸው ልኡካን ይጀመራል
 • ከማንኛውም የጥቅም ትስስር የጸዳ እንዲኾን፣ጥብቅ ክትትል ይደረጋል
 • ከሀ/ስብከቱ ልኡክም ከአቤት ባዮችም ትኩረት የሚደረግባቸው ይኖራሉ
 • አለቃውና የተባረሩቱ፣ ለማጣራቱ ካልኾነ ወደ ቅጽሩ እንዳይገቡ ታገዱ
 • ለበዓለ ልደትም መግባት አይችሉም፤በማጣራቱ ብቻ እየተገኙ ያስረዳሉ
 • በጥበቃ የሰነበቱት ምእመናን፣ “ወደ ቤት ይመለሱ፤” መባሉ አከራከረ

†††

 • “ረብሻ እስኪነሣ ዘግይታችኋል፤”ያለው ፖሊስ ሀገረ ስብከቱን ወቀሰ
 • በአቤቱታ አቀራረብ ቅደም ተከተሉ፣ሥራ አስኪያጁ ቅሬታውን ገለጸ
 • “እያጣራን፣ ጥፋተኞችን ማረሙን እንቀጥላለን፤” /ሥራ አስኪያጁ/
 • አቤት ባዮችን ለማንኳሰስ የሞከረው አጣሪ ልኡክ ተቃውሞ ገጠመው
 • በአለቃው ላይ የተነሡበት፣“ቡድነኞችና ጥቅማቸውን ያጡ ናቸው፤”አለ
 • በቦሌ ክ/ከተማ ሥራ አስፈጻሚ የተመራው ውይይቱ፣ ቀኑን አውሏል

†††

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት እና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ምእመናን፣ በአማሳኙ የካቴድራሉ አስተዳደር ላይ ያቀረቡት አቤቱታ፣ ከመጪው ሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 ቀን ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ ልኡካን መጣራት እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

“የምእመናን ቅሬታዎች በብዛት እየቀረቡ የሚገኙት ሀገረ ስብከቱ ርምጃ መውሰድ በመጀመሩ ነው፤” ያሉት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ጎይትኦም ያይኑ፣ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ከሥራ ሰዓት ውጭም፣ የቀረቡትን በርካታ አቤቱታዎች በመመርመር በአጭር ጊዜ ውሳኔ ለመስጠት ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

ማጣራቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስተዳዳሪውና የተባረሩት የጽ/ቤት ሓላፊዎች፣ ከሥራ ውጭ ኾነው በሒደቱ እየተገኙ የሚጠየቁትን የመመለስና የማስረዳት ተሳትፎ ብቻ እንደሚኖራቸው፤ ዛሬ ታኅሣሥ 27 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ በመንግሥታዊው የቦሌ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ አማካይነት፣ ማኅበረ ምእመናኑ በሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ ከተመራው ልኡክ ጋራ ባካሔዱት ውይይት ስምምነት ተደርሶበታል፡፡

አቤቱታው ባለፈው ኅዳር 26 ቀን ለፓትርያርኩ ቀርቦ ለወር ያህል መፍትሔና ምላሽ ሳይሰጠው ከዘገየ በኋላ፣ የሀገረ ስብከቱ ልኡካን ለማጣራት ያደረጉት ሙከራ፣ ማኅበረ ምእመናኑ ባስቀመጡት ቅድመ ኹኔታ ሳቢያ ውዝግቡ በመካረሩ፣ ትላንት ለክፍለ ከተማው አስተዳደር በቀረበ ጥያቄ መነሻ ነው፣ የዛሬው ውይይት የተካሔደው፡፡

በክፍለ ከተማው መሰብሰቢያ አዳራሽ የተደረገው ይኸው ውይይት፣ ከጠዋቱ 4፡00 ጀምሮ እስከ ቀኑ 10፡00 ውሏል፡፡ ከማኅበረ ምእመናኑ የተውጣጡ ኻያ ተወካዮች፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና አጣሪ ልኡካኑ፣ የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የክፍለ ከተማው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ልኡካን እንዲሁም የመንግሥታዊው የቦሌ ክፍለ ከተማ የሥራ አስፈጻሚ አባላትና የክፍለ ከተማው ፖሊስ ኮማንደር የተገኙበት ሲኾን፤ በሥራ አስፈጻሚው ሰብሳቢ የተመራ ነበር፡፡

ለዓመታት ያወዛገቡ የካቴድራሉ ችግሮች ቁርጥ ያለ መፍትሔ እንደሚሹ የተናገሩት ሰብሳቢው፣ “ተከሣሹ አስተዳደር፥ ሥራውን እየሠራ ይጣራ ወይስ ጊዜያዊ አካል ተተክቶ ማጣራቱ ይካሔድ?” በሚለው ላይ ሀገረ ስብከቱ ተመካክሮ ግልጽ አቅጣጫ ሊቀመጥ እንደሚገባ በማንሣት፣ ለምእመናኑ ቅድመ ኹኔታ ምላሽ የሚያስገኝ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

በጋራ መግባባት በተቀመጠው አቅጣጫና ሥራ አስኪያጁም በሰጡት ማረጋገጫ መሠረት፣ ማጣራቱን በመጪው ሰኞ በመጀመር በአጭር ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት የሚደረግ በመኾኑ ተከሣሾቹ የአስተዳደር ሓላፊዎች በማስረዳት ከመሳተፍ በቀር ወደ ጽ/ቤት ገብተው አይሠሩም፤ ይኹንና ካቴድራሉ ታላቅና ወዲያውም በድምቀት የሚከበረው የልደት በዓል በመኾኑ፣ ከነገ ታኅሣሥ 28 ቀን ጀምሮ አገልግሎቱን እንዲያስተባብሩ የክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ትጉሃን ወንድወሰን ገብረ ሥላሴ ከቄሰ ገበዙ ጋራ እንዲሠሩ፣ የሚፈጠሩ ክፍተቶች ካሉም ለበላይ አካል እንዲያስታውቁ ተመድበዋል፤ ከዚሁም ጋራ በተያያዘና በዓልም በመኾኑ፣ በካቴድራሉ ጥበቃ የሰነበቱ ምእመናን ወደየቤታቸው ተመልሰው ውጤቱን እንዲጠባበቁ በተወካዮቻቸው ይነገራቸው፤ ተብሏል፡፡

መፍትሔና ምላሽ በወቅቱ ባለመሰጠቱ ችግሮች መባባሳቸውን የጠቀሱት የክፍለ ከተማው ፖሊስ ኮማንደር፣ “ተገቢና ትክክለኛ ጥያቄ እስከቀረበ ድረስ ረብሻ እስኪነሣ መጠበቅ አልነበረባችሁም፤” ሲሉ ሀገረ ስብከቱን ወቅሰዋል፡፡ “ምእመኑ መፍትሔ እየጠበቀ እናንተ ገና ለማጣራት ትመጣላችሁ፤ ሀገሪቱ ከምትገኝበት ወቅታዊ ኹኔታና ከሕዝቡ ምሬት አንጻር ዘግይታችኋል፤” ሲሉም አክለዋል፡፡

መ/ር ጎይትኦም ያይኑ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ

የአቤቱታውን አቀራረብ ቅደም ተከተል በመተቸት አስተያየት የሰጠው ሥራ አስኪያጁ ጎይትኦም፣ ለሀገረ ስብከቱ በቀጥታና በአድራሻ ባለመቅረቡና “በቅድሚያ አለቃውን አንሡ፤” በመባሉ ሳቢያ ቶሎ ወደ ማጣራት ለመግባት አለመቻሉ ለመዘግየቱ ምክንያት እንደኾነ አስረድቷል፡፡ ለስድስት ዓመት ሲሰማ የቆየ አቤቱታ ኾኖ ሳለ፣ አስቸኳይ መፍትሔና ምላሽ ይሰጠን በማለት የሚጠየቀው፣ “ሀገረ ስብከቱ በአጥፊዎች ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ ስለጀመረ ነው፤” በማለት ከሰኞ ጀምሮ ከሥራ ሰዓት ውጭም ማጣራቱ እንደሚካሔድ አስታውቋል፡፡

የተለያዩ ጥያቄዎች በዝርዝር የቀረቡበት አቤቱታ እንደመኾኑ፣ የአስተዳደር ሓላፊዎቹ በአካል ተገኝተው የሚጠየቁትን እየመለሱና እያስረዱ ይሳተፋሉ፤ ሒደቱ ሲጠናቀቅ ውሳኔ እንሰጣለን፤ በማስረጃ ጥፋተኛ ኾነው ከተገኙ በሌሎቹ ላይ ሲደረግ እንደነበረው በሀገረ ስብከቱ ደረጃ አስተዳደራዊ ርምጃ እንደሚወሰድ፣ በወንጀል የሚያስጠይቃቸው ከኾነም በሚመለከተው የሕግ አካል እንደሚታይ ገልጧል፡፡ “ጠብቁን፤ ማንም ከሕግ በላይ አይደለም፤ ዛሬም እያጣራን በአጥፊዎች ላይ ርምጃ መውሰዳችንን እንቀጥላለን፤ እናንተም ሕዝቡን አረጋጉ፤” ብሏል፡፡

በቂ ቅስቀሳ ሳይደረግ ያለምእመናንና ያለሰንበት ት/ቤት ተሳትፎ በዝግ አዳራሽ ስለተመረጠው ሰበካ ጉባኤ፣ የሀገረ ስብከቱ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ሓላፊና የአጣሪ ልኡኩ ሰብሳቢ ሊቀ መዘምራን ብርሃኑ ጌጡ፣ ቃለ ዐዋዲውን መሠረት በማድረግ በሰጡት ምላሽ፡- ሰበካ ጉባኤው የሦስት ዓመት የሥራ ዘመን ቢኖረውም፣ ሕዝብ አይወክለኝም ካለና ካልፈለገው ሊነሣ እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

በአንጻሩ፣ አቤት ባይ ምእመናኑን በማንኳሰስ የተባረረውን አስተዳዳሪ ከወዲሁ ነጻ ለማውጣት የቃጣቸው የሀገረ ስብከቱ አጣሪ ልኡክ አባል ስለመኖራቸው በዛሬው ውይይት ከሰጡት ሐሳብ ለመታዘብ ተችሏል፡፡ እንደ አጣሪ ከሚጠበቅባቸው የገለልተኝነት መርሕ በመውጣት አቤት ባዮቹን፣ “የተደራጁ ጥቅመኞችና ቡድነኞች” ብለው ከመፈረጃቸውም በላይ ከውይይቱ በኋላም “ልክ ልካቸውን ነገርናቸው፤” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ እንደ አባባላቸው፣ በአስተዳዳሪው ላይ የተነሡበት አቤት ባዮች፣ “ከፉካ የተባረሩ፤ በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ መኪና አጣቢዎች፣ ጥቅም ለምደው ከሰበካ ጉባኤና ከሰንበት ት/ቤት አባልነት የተባረሩ፣ የደርግ ርዝራዦች ናቸው፤” በማለት ከተባረረው አስተዳዳሪ በቃረሙትና በመከሩት ፍጹም ወገንተኝነታቸው ተጋልጧል፤ ከምእመናኑ ተወካዮችም ተደጋጋሚ ተቃውሞ ገጥሟቸው ተስተውሏል፡፡

ይህም ምእመናኑ፣ በአጣሪ ልኡካኑ ላይ ያነሡትን የተኣማኒት ስጋት የሚያጠናክር እንደኾነ ተገልጿል፡፡ “ሀገረ ስብከቱን ካላመናችሁ መሥራት ይቸግረናል፤” ያለው ሥራ አስኪያጁ በበኩሉ፣ “ማስረጃውን ሰጥታችሁ በተግባር ፈትኑን፤” በማለት ምእመናኑ ለአጣሪ ልኡኩ ዕድል እንዲሰጡ ጠይቋል፤ “እገሌ ጓደኛው ነው፤ ፓትርያርኩን ይዣለሁ፤” በሚል የተጠቆመው የአስተዳዳሪው አነጋገር ሊያሰጋችሁ ይችላል፤ እኛን ግን በተግባር ፈትኑን፤ ዕድሉን ስጡንና በውሳኔአችን መዝኑን፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንሰጣለን፤” ብሏል፡፡ የማጣራት ሒደቱን ከየትኛውም ወገን ተጽዕኖና የጥቅም ትስስር ለመጠበቅ ክትትል እንደሚደረግና ከዝንባሌ አኳያም ልዩ ትኩረት የሚደረግባቸው እንደሚኖሩ ተመልክቷል፡፡ ይህም ኾኖ በተለይ፣ ሕገ ወጡን ሰበካ ጉባኤ እንደ ሕጋዊ ልባስና ማረጋገጫ በመያዝ ከተፈጸሙ ግድፈቶች አኳያ ለኦዲት ፍተሻዎች ባለሞያና ገለልተኛ አካላት በልኡኩ እንዲካተቱ ከቀደመው ተመክሮ የተሰጠው ሐሳብ ሰሚ ያገኘ አይመስልም፡፡ የአቤት ባዮችም ሐሳብ፣ አጣሪው አካል፦ “ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከምእመናንና ከመንግሥት አካላት የተውጣጣ ይኹን፤” የሚል ነበር፡፡”

ማኅበረ ምእመናኑና የሰንበት ት/ቤቱ በጽሑፍ ባቀረቡት አቤቱታ የዘረዘሯቸው ችግሮች በዛሬው ውይይት በተወካዮቻቸው በስፋት ተንጸባርቀዋል፤ “ከአስተዳዳሪው የክህነት ጉዳይ ጀምሮ(ሁለት ትዳር እንዳለው ተጠቁሟል)፣ በአቤቱታው ከሰፈረው ሳይነገር የቀረ ያለ አይመስልም፤” ብለዋል ተሳታፊዎች፡፡ በመድረኩ ከታየው ኹኔታ አንጻር፣ የተባረረውን አስተዳደር መልሶ የማስቀጠል ፍላጎት ይኖራል ብለው እንደማይጠብቁ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በዓልም ስለኾነ ካቴድራሉን በፈረቃ ሲጠብቅ የሰነበተው ምእመን ወደየቤቱ ይግባ፤ መባሉን ግን በጥንቃቄ እንደሚመለከቱት አስታውቀዋል – “መጨረሻውን ሳናይ በጭራሽ!!”

 

Advertisements

6 thoughts on “የሰዓሊተ ምሕረት ምእመናንን አቤቱታ ሰኞ ማጣራት ይጀመራል፤የክ/ከተማ ቤተ ክህነቱ ሥ/አስኪያጅና ቄሰ ገበዙ አገልግሎቱን ያስተባብራሉ

 1. amare getu January 6, 2018 at 5:32 am Reply

  thank you hara zetewahido word press for information you share to
  orthodoxes’

  2018-01-06 3:35 GMT+03:00 ሐራ ዘተዋሕዶ :

  > haratewahido posted: ” ማጣራቱ በመጪው ሰኞ ሀገረ ስብከቱ በመደባቸው ልኡካን ይጀመራል ከማንኛውም የጥቅም
  > ትስስር የጸዳ እንዲኾን፣ጥብቅ ክትትል ይደረጋል ከሀ/ስብከቱ ልኡክም ከአቤት ባዮችም ትኩረት የሚደረግባቸው ይኖራሉ
  > አለቃውና የተባረሩቱ፣ ለማጣራቱ ካልኾነ ወደ ቅጽሩ እንዳይገቡ ታገዱ ለበዓለ ልደትም መግባት አይችሉም፤በማጣራቱ ብቻ
  > እየተገኙ ያስረዳሉ በጥበቃ የሰነበቱት ምእመናን፣ “ወደ ቤት ይመለሱ፤” መባሉ አ”
  >

 2. Anonymous January 6, 2018 at 2:16 pm Reply

  የማጣራቱን ሂደት በገለልተኛ አካል ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ራሱ በሙስና የተጨማለቀ መሆኑ እያታወቀ እንዲያጣራ መደረጉ ይገርማል፡፡ አጣሪ ቡድኑ፣ ፓትርያርኩ የሚፈልጉትን አይነት ሪፖርት ቢያቀርብ እንጂ እውነትን ይሰራል ብሎ ማመኑ ጅልነት ነው፡፡ በእቅድ ያልተመራ አቤቶታና ከስሜት ያልፀዳ ቀናኢነት ውጤቱ ከንቱ ድካም ነው፡፡ አጣሪዎቹ በዚህ አጋጣሚ ከፍተኛ እጅ መንሻ የሚያጋብሱበት ስለሆነ በበሉበት ከመጮህ ውጪ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ ሥራ ይሰራሉ ተብሎ መጠበቅ ማለት፣ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንደ ማለት ነው፡፡

 3. Amanuel January 6, 2018 at 4:30 pm Reply

  : እንግዲህ ስራ አስኪያጁ ጎይቶም “መፍትሄ ባልሰጥ በስራዬ ፈችኑኝ” ብሏልና ፍፃሜውን እናያለን! መቸም ከእባብ እንቁላል ርግብ ባንጠብቅም ለስጋዊ ክብሩም ሲል ወይም ይህን ከማድረግ ውጭ ምንም ምርጫ ስለሌለው የማረጋጋት ርምጃ ሊወስድ ይችላል ።

  ይህ የሆነውና የሚሆነው የምዕመኑ ቆራጥና ጥብዓትን ከተሞላ የቁርጠኝነት ጥያቄ የተነሳ ጉዳዩ ሌላ መልክ እንዳይዝና በሌሎች አካባቢዎችም (አብያተ ክርስቲያናት) እየተፈፀመ ባለው ርካሽ ሰንሰለታዊ ስራቸው የተነሳ ተመሳሳይ ተቃውሞ ቢቀሰቀስ ለመቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል እንጂ ከጎይቶም እና መሰሎቹ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ተብሎ የሚወሰድ አንዳች ነገር እንደማይኖር ይታወቃል ።
  ሰዎቹ ሃይማኖታቸው ብር እንጂ ሌላ አይደለምና የሚጠባበቁት ተስፋ መንግስተ ሰማያት የላቸውም!!

  የሆነው ሆኖ ቤቱን ጥሎ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብር መራር ተጋድሎን እያደረገ ላለውና የፖሊስን ጉሸማና ጡጫ ተተቁሞ ውሎ አዳሩን ስለ ቤተ ክርስቲያን ክብር ዋጋ እየከፈለ ላለው ምዕመን እና አገልጋይ ክብር ይገባዋል ።

  እግዚአብሔር ትውልዳችሁን ይባርክ ይህች ናት የቀደመች የአባቶቻችን የማትነጥፍ ቁርጠኛ የዕምነት መገለጫ ቁርጠኝነት፣ ጭከና ፣ጥብዓትና ፣ ከራስ በላይ ለትውልድ ለምተላለፍ ቅድስት ሃይማኖት ቅድሚያ መስጠት ፤
  ደግሜ እላለሁ እግዚአብሔር ድካማችሁን እና ትጋታችሁን በቸርነቱ ለበረከት ያድርግላችሁ ኮርተንባችኋል!!!

 4. Anonymous January 9, 2018 at 11:37 am Reply

  በሀገረ ስብከቱ ልኡካን”

 5. Anonymous January 9, 2018 at 11:55 am Reply

  “የሀገረ ስብከቱ ልኡካን” እነዚህ እነማን ናቸው? ለመሆኑ ከቤተክህነቱ ጋር የተነካካ ሹመኛ የእምነት እና ትክክለኛና ፍትሀዊ ሥራ ይሰራል ብላችሁ ታምናላችሁ? አለቃ ሩፋኤል ( ወይም በዱሮ ስሙ አቡ) ማለት (ከቤተ ክህነቱ ባለስልጣናት ጋር)ብዙ ኔትወርክ ወይም ግንኙነት ያለው ሰው ነው፡፡ ይህን ጉዳይ የሚያጣራ ኮሚቴ ከቤተክህነት ውጪ ከህዝቡና ከሀገር ሽማግሌዎች መሆን አለበት ይህ ካልሆነ ቤተክህነቱማ አንዱ የስርቆቱ ባለድርሻ አካል ነው በየ አድባራቱ ምን እንደሚሰራ ቀድሞ ያውቃል ሌቦችን አሰልጥኖ እንዲያቀብሉት የሚልከው እርሱ ነው ሲነቃባቸው ደግሞ ከስራቸው ከማገድ ይልቅ እድገት ሰጥቶ ወደሌላ ቦታ እንዲዘርፉ ያዘዋውራቸዋል ችግር ሲፈጠር “አጣሪ ኮሚቴ“ ብሎ የሌቦች ደጋፊዎችን ይልክና ጉዳዩ ተድበስብሶ እንዲቀርና የመጨረሻው ሪፖርት ሌቦቹ እንደፈለጉት እንዲሆን የድርሻውን ጉቦ ይበላና ሪፖርት የሚቀይር ኮሚቴ ነው “የሀገረ ስብከቱ ልኡካን” ማለት ሥራው ይህ ነው፡፡

 6. Anonymous January 10, 2018 at 6:40 am Reply

  “ከአስተዳዳሪው የክህነት ጉዳይ ጀምሮ(ሁለት ትዳር እንዳለው ተጠቁሟል)፣

  ha ha ha … betam yaskal.

  It is nothing surprising.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: