የሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራልን ምዝበራ የሚያጣራው የሀ/ስብከቱ ልኡክ ተቃውሞ ገጠመው፤ “አናምናችሁም፤ ቅድሚያ አማሳኞቹን አንሡ!”/ምእመናን/

sealite mihret and aa dio

የልኡካኑ ቡድኑ ዛሬ ረፋድ ማኅበረ ምእመናኑን በዐውደ ምሕረት ካነጋገረ በኋላ፣ ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ውጭ በርካታ የወርቅ ንዋያተ ቅድሳት የተከማቹበትንና “ሻኪሶ” እየተባለ የሚጠራውን የአስተዳዳሪውን ቢሮ በታሸገበት ኹኔታ ተመልክቶታል፤ምእመናኑ የተጠናከረ አቤቱታ ማቅረብ ከጀመሩ በኋላ የተደናገጡት አማሳኞቹ፣ መመሪያውን በመጣስ የረጅም ጊዜ ሕገ ወጥ የኪራይ ውል ፈጽመዋል፤ በተለይ አስተዳዳሪው፣ የካቴድራሉን ጄኔሬተር፣ የልብሰ ተክህኖ ማጠቢያ ማሽንና የውኃ ፓምፕ እንዳሸሹ ተጠቁሟል፡፡ድርጊቱን ለማስቆም የሞከሩ የጥበቃ አባልም እንደታገዱ ተነግሯል፡፡በድንጋጌው መሠረት፣ የቤተ ክርስቲያንን ቅርስ ወይም ንብረት ካለበት ቦታ ወደ ሌላ ያዛወረ ወይም የሰወረ ወይም የሰረቀና ያሰረቀ ወይም የሸጠና የለወጠ ግለሰብ በወንጀል ይጠየቃል፤ ካህን ከኾነ ከሥልጣነ ክህነቱ ታግዶ ጉዳዩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ አስፈላጊው ቅጣት ይወሰንበታል፡፡ ክህነታቸውም ስለመኖሩ ጥያቄ የተነሣባቸው አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን ግን፣ ከተነሣሁ ወደ ሌላ ተመጣጣኝ ደብር ልዛወርእያሉ ነው፡፡

 • በስብከተ ወንጌል ሓላፊ መ/ሰላም ዳዊት ያሬድ የሚመራ ልኡክ ምእመናኑን አወያየ
 • ምላሹ ለወር ያህል በመዘግየቱ፣ በልኡካኑ ውጤታማነት እምነት እንደሌላቸው ገለጹ
 • ሕገ ወጡን ሰ/ጉባኤ በማስመረጥ፣ ሓላፊውንና የልኡኩን አባል ብርሃኑ ጌጡን ወቀሱ
 • ማጣራቱ ከመካሔዱ በፊት፣የአስተዳደር ሓላፊዎቹ ተነሥተው በሌላ እንዲተኩ ጠየቁ
 • ተቃውሞ ከተጠናከረ በኋላ ዝርፊያና ሕገ ወጥ ውሎች መፈጸማቸው፣ መንሥኤ ነው

†††

 • ከአቤቱታው በኋላ፣ ንብረት እንዳሸሹና ሕገ ወጥ የኪራይ ውል እንደፈጸሙ ተጠቆመ
 • ከመመሪያው ውጭ፣ ለዐሥር ዓመት ሕገ ወጥ የኪራይ ውሎች በሓላፊዎቹ ተፈጸሙ
 • አለቃው፣የካቴድራሉን ጄኔሬተር፣ የልብሰ ተክህኖ ማጠቢያ ማሽንና የውኃ ፓምፕ አሸሸ
 • ሻኪሶእየተባለ በሚጠራው ቢሮው፣ የወርቅ ንዋያተ ቅድሳቱን ሰብስቦ አከማችቷቸዋል
 • “በተደበደበ ምሽት፥ የወርቁን ማኅጠንት፣ጽንሐሕና መስቀል ለመውሰድ ነበር አመጣጡ፤”

†††

 • የድኻው መቀበሪያና የባለጸጋው ፉካ፣ መጦሪያው እና የታሸገው ሰንበት ት/ቤት ተጎበኘ
 • የመጦሪያ ማዕከሉ አረጋውያን፣ ለጅብ ተጥለናል፤ለአደጋ ተጋልጠናል፤” ሲሉ አማረሩ
 • ማኅበረ ምእመናኑ፣ ባወጡት የፈረቃ መርሐ ግብር፣ የካቴድራሉን ጥበቃ አጠናክረዋል
 • አለቃውን ጨምሮ ለጥፋቱ ተጠያቂ የኾኑ በሙሉ ይነሣሉ፤ /የልዩ ጽ/ቤት ምንጮች/
 • አለቃው፣“ወደ አጥቢያ ልዛወር” ቢልም ክ/ከተማ አልያም ሀ/ስብከት ሊመደብ ይችላል

†††

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥር በሚገኘው የደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል፥ ከመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በልማት ሰበብ ከሚፈጸም ምዝበራና የቅርስ ውድመት ጋራ በተያያዘ፣ ማኅበረ ምእመናኑና የሰንበት ት/ቤቱ፣ በጽ/ቤት ሓላፊዎችና ሕጋዊ ውክልና በሌለው ‘ሰበካ ጉባኤ’ ላይ ያቀረቡትን አቤቱታ ሀገረ ስብከቱ ማጣራት ጀመረ፡፡

ከሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና ከቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የተውጣጣ አምስት አባላት ያሉት ልኡክ፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ረፋድ 5፡00 ወደ ካቴድራሉ በማምራት የማጣራት ሥራውን ማኅበረ ምእመናኑን በማነጋገር የጀመረ ሲኾን፣ በሥራ አስኪያጁ ጎይትኦም ያይኑ ጥብቅ መመሪያ ተሰጥቶታል፤ ተብሏል፡፡

በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ዋና ክፍል ሓላፊ መልአከ ሰላም ዳዊት ያሬድ በሚመራው ልኡክ፣ የሰበካ ጉባኤ ማዳራጃ ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ መዘምራን ብርሃኑ ጌጡ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማዳራጃ ዋና ክፍል ቀሲስ አሉላ ለማ፤ የቦሌ ክፍለ ከተማ የሰው ኃይል አስተዳደር ሓላፊ መምህር ዳዊት ጥበቡ እና የክፍለ ከተማው የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ሓላፊ መጋቤ ትፍሥሕት ግርማ ተስፉ በአባልነት መካተታቸው ታውቋል፡፡

ልዩ ሀገረ ስብከቱን በበላይነት ለሚመሩት ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀረበው አቤቱታ ወር ያህል ያስቆጠረ ቢኾንም፣ ተገቢው መፍትሔና ምላሽ ሳይሰጠው በመዘግየቱ የተቆጡት ማኅበረ ምእመናኑና የአካባቢው ወጣቶች፣ አማሳኝ ሓላፊዎችንና ሕገ ወጡን የሰበካ ጉባኤ ተወካይ ባለፈው ዓርብ ጠዋት በማባረር ጽ/ቤቱን ከማሸጋቸውም በላይ በዚያው ምሽት አስተዳዳሪውን አካላዊ ቅጣት መቅጣታቸው ተዘግቧል፡፡

ምእመናኑን፣ “ዱርዬዎችና በጥባጮች” ብሎ በማጥላላትና ጥያቄአቸውን ፖሊቲካዊ መልክ በመስጠት እንዲሁም ከተሳላሚ ባለሥልጣናትና ከፓትርያርኩ ጋራ ልዩ ግንኙነት እንዳለው በማስወራት ለማሸማቀቅ ሲሞክር የቆየው አስተዳዳሪው ከተጎሸመና ግብረ አበሮቹም ከተባረሩ በኋላ ዛሬ የተጀመረው የሀገረ ስብከቱ ማጣራት ከውዝግቡ መካረርና ከማኅበረ ምእመናኑ ቁርጠኝነት አንጻር የሚኖረው ፋይዳ አነጋጋሪ ኾኗል፡፡

አጣሪ ልኡኩ እንደሚመጣ አስቀድመው የሰሙት ማኅበረ ምእመናኑ በከፍተኛ ቁጥር ተሰብስበው የጠበቁት ሲኾን፣ ተወካይ ኮሚቴ እንዲመርጡ ቢጠይቅም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ከቀኑ 5፡00 እስከ 7፡20 በካቴድራሉ ዐውደ ምሕረት ላይ ከአጣሪ ልኡኩ ጋራ በተካሔደው ውይይት፣ አማሳኞቹን ከቦታው ከማንሣትና እንደ አግባቡም በሕግ እንዲጠየቁ ከማድረግ ያነሰ መፍትሔ አንሻም፤” ብለዋል ማኅበረ ምእመናኑ፡፡ እንዲያውም ማጣራቱ ሊቀጥል የሚችለው፣ አስተዳዳሪውን ሩፋኤል የማነ ብርሃን፣ ዋና ጸሐፊው ዕፁብ የማነ ብርሃን፣ ሒሳብ ሹሙ ዘርኣ ቡሩክ ኣብርሃና ተቆጣጣሪው በቅድሚያ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው ለቦታው በሚመጥኑ አባትና ሓላፊዎች ከተተኩ በኋላ ብቻ እንደኾነ አስጠንቅቀዋል፡፡

rufael yemanebirhan kassahun gebrahiwot etsub yemanebir and zerabiruk abreha

ምክንያታቸውን ሲያስረዱም፣ አቤቱታቸውን ለፓትርያርኩ ባቀረቡበት ወቅት በሁለት ቀናት ውስጥ አጣሪ መድበው አስቸኳይ ምላሽ እንደሚሰጧቸው ቃል ቢገቡላቸውም መዘግየቱን፤ ከተቃውሞ እንቅስቃሴያቸው መጠናከር በኋላ የጽ/ቤት ሓላፊዎቹ ከመመሪያው ውጭ ለዐሥር ዓመት የኪራይ ውል መፈጸማቸውንና በተለይ አስተዳዳሪው የካቴድራሉን በርካታ ውድ ንብረቶች ማሸሽ መጀመራቸውን በመንሥኤነት ጠቅሰዋል፡፡

rufael yemanbirhan,abu

ባለፈው ዓርብ የእመቤታችን በዓል ዋዜማ ምሽት በአስተዳዳሪ ላይ የአካል ቅጣት ርምጃ ለመውሰድ የተገደዱት፣ ወደ ቤተ መቅደሱ ሳይኾን ወደ ታሸገው ጽ/ቤት ለመግባት በመፈለጋቸው እንደኾነ ማኅበረ ምእመናኑ ለልኡካኑ ገልጸዋል፡፡ ከቃለ ዐዋዲው የንብረት፣ የንዋያተ ቅድሳትና የቅርሳ ቅርስ አያያዝ ድንጋጌ ውጭ ከወርቅ የተሠሩ ማኅጠንት፣ ጽንሐሕና መስቀሎችን በቢሯቸው አከማችተው መያዛቸውን ጠቅሰው፣ “አመጣጣቸውም እነርሱን ለማሸሽ ነበር፤” ሲሉ ጠቁመዋል – ቢሮው፣ ሻኪሶ ነው የሚባለው፤ የወርቅ ማኅጠንት፣ የወርቅ ጽንሐሕ፣ የወርቅ መስቀል የመሳሰሉት የእርሱ ቢሮ ነው የሚቀመጡት፤” ብለዋል ምእመናኑ፡፡ ቀደም ሲል የካቴድራሉን ጄኔሬተር፣ የካህናት ልብስ ማጠቢያ ማሽኑንና የውኃ ፓምፑን እንዳሸሹና ይህንንም ለመከላከል የሞከረ ጥበቃ ከሥራ መታገዱን በመጠቆም የርምጃቸውን አግባብነት አስረድተዋል፡፡

አጣሪ ልኡኩ፣ በርካታ የወርቅ ንዋያተ ቅድሳት የተከማቹበትንና “ሻኪሶ” እየተባለ የሚጠራውን የአስተዳዳሪውን ቢሮ በታሸገበት ኹኔታ ተመልክቶታል፤ በአስተዳዳሪው የታሸገውን የሰንበት ት/ቤቱን ጽ/ቤትም አይቷል፤ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው መጦሪያ ነው በተባለው ማዕከል የሚገኙ አረጋውያንን ያነጋገረ ሲኾን፣“ለጅብ ተጥለናል፤ ለአደጋ ተጋልጠናል፤” ሲሉ በስማቸው እንደሚነገድ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ አማሳኙ አስተዳደር፣ ሀብታምና ድኻ እያለ በሚከፋፍልበት የቀብር አገልግሎት፦ ድኻው የሚቀበርበትን የወንዝ ዳርና ምልስ አፈር አስጎብኝተናቸዋል፤ ለባለጸጋ የሚሸጠውንም ፉካ አሳይተናቸዋል፤” ብለዋል ምእመናኑ፡፡

በሀገረ ስብከቱ ልኡካን ላይም አመኔታ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይም፣ ሕገ ወጡን የሰበካ ጉባኤ ከቃለ ዐዋዲው አሠራር ውጭ በዝግ አዳራሽ ያለምእመናኑና ያለሰንበት ት/ቤቱ የተሟላ ተሳትፎ አስመርጠዋል ያሏቸውን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ዋና ክፍል ሓላፊውን ሊቀ መዘምራን ብርሃኑ ጌጡን በስም በመጥራት ተችተዋቸዋል፤ “የልኡኩ አባል ኾነው ሊያጣሩ በመምጣትዎ አያፍሩም ወይ? የችግሩ አንዱ መንሥኤ እርስዎ ነዎት፤” ብለዋቸዋል፡፡ ሌላው የልኡኩ አባልና የክፍለ ከተማው የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ ክፍል ሓላፊም ከአስተዳዳሪው ጋራ ባላቸው ልዩ የጥቅም ግንኙነት ከሚተቹት ናቸው፡፡

የአጣሪ ልኡኩ አባላት የእያንዳንዳቸው ማንነት፣ ከዚህ ቀደም ባጣሩባቸው አጥቢያዎች የነበራቸውን ዝንባሌ በሚገባ እንደሚያውቁ ምእመናኑ ተናግረዋል፡፡ ተልእኳቸውን፣ ለቤተ ክርስቲያን መብቶች መከበርና ለጥቅሞቿ መጠበቅ መቆማቸውን እንዲያረጋግጡበት እንጅ፣ ችግሩን ለማድበስበስና የእጅ መንሻ ለማግበስበስ እንዳያውሉት በጥብቅ አስጠንቅቀዋል – የማጣራት ሒደቱ የሚቀጥለው ሌላ አለቃ አምጥታችሁልንና ሓላፊዎቹ በሙሉ ተነሥተው ነው፤ እነርሱን ልትመልሱ ማጣራቱ አያስፈልግም፤ አንቀበለውም፤ ደም መፋሰሱ ይቀጥላል፡፡”

ከአራት ዓመት በፊት ተፈጥሮ የነበረውን ውዝግብ ያጣሩት አካላት ገለልተኛና ለጉዳዩም አግባብነት ያላቸው ባለሞያዎች እንደነበሩ ያወሱት ምእመናኑ፣ በወቅቱ አስተዳደሩ፣ ካቴድራሉንና ምእመኑን ለመምራት የማይችል የአቅምና የሥነ ምግባር ችግር እንዳለበት ያቀረቡት ሪፖርት ሰሚ አግኝቶ ተገቢው ማስተካከያ ቢደረግ ኖሮ የአኹኑን ያህል ምዝበራ፣ ጥፋትና ብክነት አይፈጠርም ብለዋል፤ በቁጭት፡፡ የወቅቱ ችግር ከዚያም የከፋና ዘርፈ ብዙ እንደመኾኑ፣ ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት የሚረዱ ሞያተኞችና የሚመለከታቸው አካላት ተወካዮች ሊካተቱበት ይገባ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ያም ኾኖ፣ “ውጤቱ ምንም ይኹን፣ ይህ ዐይነቱ አማሳኝ አስተዳደር እንዲመራን አንፈልግም፤ በሓላፊነቱ እንዲቀጥልም ሊፈቀድለት አይገባም፤ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በካህናትና በምእመናን ኅብረት የተመሠረተ እንደመኾኑ እኛም ልንደመጥ ያስፈልጋል፤” በማለት አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ በምእመናን በተፈጸመባቸው የአካል ቅጣት ቅዳሜ ንጋት ኮርያ ሆስፒታል ገብተው በሕክምና ላይ የነበሩት አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል፣ ወጥተው ወደ መኖርያ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡ ደብድበውኛል የሚሏቸውን በሰዓቱ በቦታው የሌሉ ግለሰቦችን ስም ጭምር በመጥራት እየወነጀሉ ሲኾን፣ ከካቴድራሉ ከተነሡ ወደ ሌላ ተመጣጣኝ አጥቢያ መዛወር እንደሚፈልጉ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በፓትርያርኩ በኩል ግን፣ ወደ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤቱ አምጥቶ በሓላፊነት የማስቀመጥ ሐሳብ መኖሩ በቅድሚያ ሲጠቆም፣ ሥራ አስኪያጁ ደግሞ ከክፍላተ ከተማ ጽ/ቤቶች ወደ አንዱ ቢዛወር የሚል አማራጭ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡ የኾነው ኾኖ፣ “ከሕዝቡ የመረረ ተቃውሞ በኋላ፣ አስተዳዳሪውን ጨምሮ ለካቴድራሉ ጥፋትና ብክነት ተጠያቂ የኾኑ የጽ/ቤት ሓላፊዎችን ለማንሣት አቋም መያዙን ያሳያል፤” ብለዋል የሀገረ ስብከቱ ምንጮች፡፡

ዛሬ በዐውደ ምሕረት ከማኅበረ ምእመናኑ ጋራ ከተደረገው ውይይት፣ በቅድመ ኹኔታ የተለያየውና ተኣማኒነቱ ሳይቀር ጥያቄ ውስጥ የገባው የሀገረ ስብከቱ ልኡክ፣ ኹኔታውን ለሥራ አስኪያጁ በማስረዳት የማጣራቱ ቀጣይ አካሔድ ይወሰናል፤ ጉዳዩ ለቋሚ ሲኖዶሱ ሲቀርብ፣ የቤተ ክርስቲያንን መብቶችና ጥቅሞች የሚያስከብር፣ ለሕዝብ ሰላምና አንድነት የሚያስብ ኹነኛ እልባት እንደሚያገኝም ይጠበቃል፡፡ ከወቅቱ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት አንዱና ለአስተዳዳሪው ይወግናሉ ከሚባሉት አንዱ ብፁዕ አባ ማርቆስ፣ በሀገረ ስብከታቸው በለመዱት አቤት ባዮችን የማሳፈንና የማስደብደብ ልማድ“ሲኖዶሱ ደብዳቢዎቹን ማውገዝ አለበት፤ ለሾምናቸው አባቶች ከለላ መስጠት አለብን፤” ቢሉም በፓትርያርኩ ተቀባይነት አለማግኘታቸው ጥሩ ምልክት ነው፡፡

Advertisements

2 thoughts on “የሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራልን ምዝበራ የሚያጣራው የሀ/ስብከቱ ልኡክ ተቃውሞ ገጠመው፤ “አናምናችሁም፤ ቅድሚያ አማሳኞቹን አንሡ!”/ምእመናን/

 1. Anonymous January 3, 2018 at 6:18 am Reply

  “በሀገረ ስብከታቸው በለመዱት አቤት ባዮችን የማሳፈንና የማስደብደብ ልማድ፣ “ሲኖዶሱ ደብዳቢዎቹን ማውገዝ አለበት፤ ለሾምናቸው አባቶች ከለላ መስጠት አለብን፤”

  Look at this. As the saying goes, ” The decay of the fish is from is head”.

  The decay of the church administration is from its head at different levels.

  The corruption, nepotism and ungodliness which we experience every day is the result of bad church administration.

  They are not church leaders at all – they missed the main objective of their priesthood. It was to guard the church (church children) and of themselves.

  Now the words of the Bible has come true. They worship money and their bellies. They are there to destroy the church of God and expose the followers to wolves.

  Their priesthood was to serve and protect children of God, church followers.

  Look at what one of the popes says; he is down playing the people, the main mission of the church.

  He seems to forget his mission – serving the church. Now the Holy Synod seems symbolic and they only serve themselves and forget the mission of the church.

  If the Holy Synod is not proactive and win trust in the hearts of the people, each of them will also be chased away by the people. They may think that, because they sit at the top, the fire which started at the bottom will not reach them. But they should realize that the fire which started at the bottom will also reach to them as it consumes all the dead logs.

  I think what we see and hear everyday is really worrying.

  I really don’t know what is going on and where this is leading us to.

  I believe one day God will cleanse His Church.

  However, what is happening in our church is not a new thing. The Bible tells us this to come and God works in His time.

  What we must do is to pray to God to give us peace and protect ourselves from the effects of such evil deeds.

 2. Anonymous January 3, 2018 at 3:10 pm Reply

  ማሙዬ አለመላኩ መልካም ነው እንደው ማሙዬ የተባለን ሌባ መተተኛና ሸረኛ አጣሪ አድርጎ መጀመሪያውኑ መላክ ምን ማለት ነው በሌሎች ደብሮች አጣራለሁ እያለ ካጣራ በላኋ ሪፖርቱን ለአንድና ለሁለት ወራት በእጁ ይዞ ከሁለቱም ወገን ይደራደርበታል የተሻለ ላቀረበው አካል ሪፖርቱን ገልብጦ እውነቱን ሐሰት ሐሰቱን እውነት አድርጎ ያቀርበዋል ሥራ አሥኪያጁም በስመሳዩና በተንኮለኛው ማሙዬ የቀረበውን ሪፖርት ሳያጣራና ሳይመረምር ልክ ከሰማይ እንደወረደ በማስመሰል በፍጥነት ይወስናል በዚህ መሀል የብዙ ንፁሐን አገልጋዮች በሐሰት ይወነጀላል ብዙዎች ከሥራ ይፈናቀላሉ ሥራ አሥኪያጁ ሲጠየቅ ትክክለኛ ሥራ እንደ ሠራ አድርጎ እራሱን እንደ መልአክ በመቁጠር የማስመሰል መግለጫውን ያነበንባል ምክንያቱም በ3 ቦታ ላይ እያስገነባ የለውን ፎቅ ለመጨረስ የገቢ ሚንጩን የሚያመቻቹት እነማሙዬ ስለሆኑ ማሙዬ እከሌ ይባረር እከሌ ይቀጠር ካለ ሥራ አሥኪያጁ ያለ ምንም ማቅማማት ይወስናል አቤት ግፍ አቤት ጭካኔ ጌታ ሆይ እባክህን አሁኑኑ ፍረድ በሐሰት የሰበሰቡት ሐብት ደዌ ይሁንባቸው የወለዱት አይደግ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ መከራን ይብሉ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: