በሰዓሊተ ምሕረት ምእመናን ቁጣ የተቀጡት የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሆስፒታል ናቸው፤“በዕለተ ቀኗ የእጁን ሰጠችው”/ምእመናን/

 • ፖሊስ ሓላፊነት እንደማይወስድ እያስጠነቀቀው በትዕቢት ለመግባት ሞክሯል
 • ግብረ ገብ የለሽነቱ፣ ነውረኛነቱና ተሳዳቢነቱ፣የእጁን ነው፤ሲያንሰውአሰኝቷል
 • በፓትርያርኩ የታዘዘው ሥ/አስኪያጁ፥ግባ ማለቱ ሕዝብን መናቅና ግትርነት ነው
 • የተባረሩ የጽ/ቤት ሓላፊዎች፣ሰኞ ቢሮ እንገባለንእያሉ ውዝግቡን እያባባሱ ነው
 • “ባለድርሻዎችን ያሳተፈ ውይይት እንጅ ሕዝብ ምን ያመጣል ማለቱ አያዋጣም!”

†††

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ሓላፊዎች በደል በተቆጡና ምላሽ በተነፈጋቸው የአጥቢያው ምእመናን ርምጃ፣ ጽ/ቤቱ፣ ከትላንት በስቲያ ዓርብ ጠዋት ከታሸገ በኋላ ምሽቱን፣ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በማምራት ካልገባሁ ያሉት ዋና አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን ክፉኛ ተደብድበው ሆስፒታል መግባታቸው ተገለጸ፡፡

በወቅቱ በሥፍራው የነበረውን ኹኔታ ያስረዱት ምእመናኑ፣ “አኹን አዋጩ አካሔድ፡- ከኹሉም ባለድርሻ አካላት ጋራ ቶሎ ብሎ ወደ ውይይት መግባት ነው፤” ይላሉ፡፡ “ንቀትና ግትርነት አያዋጣም፤” ሲሉ አስተዳዳሪውንና የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ ተችተዋል፤ በበላይነት የሚመሩት ፓትርያርኩ፣ ምእመኑንና የሰንበት ት/ቤቱን ያሳተፈ፤ ሕግንና አሠራርን የጠበቀ መፍትሔ በአስቸኳይ ካልሰጡ ውዝግቡ ሊባባስ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፤ በቋሚ ሲኖዶሱም በኩል ጥረት እንዲደረግ ተማፅነዋል፡፡

Melake Birhan Rufael Yemane Birhan

ከቅዳሜ ንጋት ጀምሮ በኮርያ ሆስፒታል በሕክምና ላይ የሚገኙት መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 20 ቀን ጧት 3፡00፣ ማኅበረ ምእመናኑና የአካባቢው ወጣቶች የካቴድራሉን ጽ/ቤት የማሸግ ርምጃ በወሰዱበት ወቅት አስተዳዳሪው በቅጽሩ አልነበረም፡፡ ቀን ላይ ከሥራ አስኪያጁ ጎይትኦም ጋራ ተደዋውሎ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሔደ፡፡ ፖሊሶች ደግሞ፣ “ሕዝብ ማሸግ ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን የበላይ አካልን አማክረን በፍርድ ቤት ትእዛዝ ነው የምናስከፍተው እንጅ በአንተ ትእዛዝ አናስከፍትም፤” አሉት፡፡ “ለዱርዬ ነው የምታግዙት፤” ብሎ ያነጋገሩትን ፖሊሶች ተሳድቦ ነው ከጣቢያው የወጣው፤ ከፖሊስ ጋራም ተጣልቷል፡፡

ከዚያ ተመልሶ ልግባ ወይ ብሎ ለሥራ አስኪያጁ ጎይትኦም በድጋሚ ደወለለት፡፡ እርሱም፦ “ቢሮው ታሽጓል፤ እንማከራለን፤ ቤተ መቅደሱ ግን አልታሸገምና ከፈለግህ ሔደህ ማገልገል ትችላለህ፤” አለው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ወደ ፖሊስ ደወለ፤ “ነገ ማርያም ስለኾነች ልግባ ወይ ብሎ?” ሲጠይቅ፣ “ግባም አትግባም ማለት አንችልም፤ ሓላፊነትም አንወስድም፤” አሉት፡፡

ማታ አምስት ሰዓት ላይ ወደ ካቴድራሉ ብቻውን መጣ፡፡ ቅጽሩ በማኅበረ ምእመናኑ ጥበቃ ሥር ስለነበር ወደ ውስጥ እንደዘለቀ ከመግቢያው አካባቢ ወጣቶቹ አስቆሙት፡፡ የደወል ቤቱን ገንጥለው ገብተው ለረጅም ደቂቃ ተደወለ፤ የአካባቢው ሰው በሙሉ ግልብጥ ብሎ መጣ፤ መብራቱን አጥፍተውት ምንም አይታይም ነበር፤ “ወዴት ነው የምትገባው?” ሲሉት፣ “ላገለግልም ላስገልግልም” ብሎ መለሰላቸው፡፡ “እስከ ዛሬ ያገለገልኸው ይበቃሃል፤” በማለት እንዲመለስ እያነጋገሩት እያለ ከኋላው በኮብልስቶን ጀርባውን ተመቶ ተዘረረ፤ ራሱን ስቶ ወደቀ፡፡ ከአንገቱ በላይ ደኅና ነው፤ ጀርባው ግን በጎማ መሰል ዱላ ተገርፏል፤ ተቀጥቅጧል፤ ተረጋግጧል፤ አሁን ውኃ ቋጥሯል፤ ቆሳስሏል፡፡

ወዲያው የተወሰደው ወደ ፖሊስ ሆስፒታል ነበር፡፡ ሲቪል አናክምም፤ ብለው መለሱት፡፡ ቤተ ዛታ ሆስፒታል ወሰዱት፡፡ ቆዳው አብጧል፤ ምኒልክ ይሻላል፤ ብለው ወደዚያው ወሰዱት፤ ምኒልክም፣ “ውኃ የቋጠረ ነገር ነው፤ ልንረዳው የምንችለው ነገር የለም፤ ለኤክስሬይም ለምንም አያመችም፤” አሉ፤ ንጋት 11፡00 ግድም ወደ ኮርያ ሆስፒታል ተወስዶ እዚያ ገባ፤ የሕክምና ርዳታ እየተደረገለት ራሱን ዐወቀ፤ ነቃ፡፡ ተደብድቦ እንደነበር ለመጡት ጠያቂዎቹ ተናገረ፡፡ ወዳጆቹ እየሔዱ እየጠየቁት ነው፤ ፓትርያርኩም ዛሬ እንደሚጠይቁት ይጠበቃል፡፡

ከሰብአዊ ርኅራኄ አንጻር ጉዳቱ የሚያሳዝን ኾኖ ሳለ በዓምባገነንቱ፣ በግብረ ገብ የለሽነቱ፣ በነውረኛነቱና ተሳዳቢነቱ፣ በርካታ ካህናትና ምእመናን፥ “እመቤታችን በዕለተ ቀኗ የእጁን፥ የሥራውን ሰጠችው፤ ሲያንሰው ነው፤” እያሉ ፍትሐ እግዚአብሔር እንደኾነ እየተናገሩ ነው ያሉት፡፡ እንዲያውም ነቃ ሲባል የተናደዱም አሉ፡፡ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች ሳይቀሩ፣ “ይበለው፤ በዕለተ ቀኗ እርሷ ነች የቀጣችው” እያሉ ነው፡፡

የካቴድራሉን ዋና ጸሐፊ እና ሒሳብ ሹሙን ጨምሮ አንዳንድ የጽ/ቤት ሓላፊዎች በበኩላቸው በእልክ፣ “ለዱርዬ አንበገርም፤ ሰኞ ቢሮ ከፍተን እንገባለን፤” እያሉ እየፈከሩና እየዛቱ ናቸው፤ እልክ ተጋብተዋል፡፡ አብዛኛው አገልጋይና ምእመን ግን፣ ቅጣቱን ከቁንጥጫ በመቁጠር በወጣቶች ርምጃ ደስታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ፣ “በጣም ብዙ አባቶችን አስለቅሷል፤ በድሏል፤ ካቴድራሉን መጫወቻ አድርጎታል፤ ጽ/ቤቱ ታሽጎ ፖሊስም ሓላፊነት አንወስድም እያለው በትዕቢት ለመግባት በመሞከሩ አዝኖበታል፤” ይላሉ፡፡

እርሱም እንግዲህ በቅዠትም ይኹን አይታወቅም፣ አንድ ጊዜ፣ “የጎይቶም ወዳጅ ስለኾንኩ የጎይቶም ጠላቶች ናቸው ያስደበደቡኝ፤” ይላል፤ መለስ ብሎ ደግሞ፣ “ስለሰደብኋቸው ራሳቸው ፖሊሶቹ ይኾናሉ ያስደበደቡኝ፤” ይላል፤ “እነዘካርያስና ኃይሌ ናቸው፤” እያለም ለጠያቂዎቹ ኹሉ እንዲሁ ይለፈልፋል፤ ብቻ እየቃዠ ነው፡፡

rufael yemanebirhan kassahun gebrahiwot etsub yemanebir and zerabiruk abreha

ማኅበረ ምእመናኑ እና የሰንበት ት/ቤቱ፣ አቤቱታቸውን ለፓትርያርኩ ባቀረቡ ማግሥት ጥቂት ደጋፊዎቹ ወደ ፓትርያርኩ ሔደው፣ “እርሱ ምንም አላጠፋም፤ ይነሣ የሚሉት የአካባቢው ዱርዬዎችና በጥባጮች ናቸው እንጅ ትክክለኛ አይደሉም፤” ብለው ሊያስተባብሉለት ሞክረዋል፡፡ ሤረኞቹ የጽ/ቤት ሓላፊዎች፣ “ከሰኞ ጀምሮ ቢሮ እንገባለን” እያሉ የሚያሰሙት ዛቻ ሲታይ፣ ፓትርያርኩ የሚሉት ባይታወቅም ቶሎ መፍትሔ ካልተሰጠ የከፋ ውጤት ይከተላል፤ ምእመኑን እልክ እያጋቡት ነው፡፡

የኹኔታውን አሳሳቢነት ከግምት በማስገባት፣ ቋሚ ሲኖዶሱ በመጪው ሳምንት ረቡዕ ወይ ዓርብ ጉዳዩን ተነጋግሮ ሊወስንበት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሳምንት አንዳች መፍትሔ ካልተሰጠ አልያም አማሳኙ የአስተዳደር አካል እንዲመለስ ከተወሰነ ውዝግቡን ማባባስ ነው፡፡ ድብደባው እኮየችግሩ በወቅቱ አለመፈታት ምን ያህል ምሬት እንደፈጠረ የሚያሳይ ነው፡፡

በአስተዳደር ሓላፊዎች ለውጥ ብቻ የዓመታት ችግሩ ተዘፍዝፎና ተሸፍኖ ነው የቆየው፡፡ ቀድሞ ከሰንበቴ ማኅበራት ጋራ በተገናኘ ነበር፤ አሁን የአካባቢው ወጣትና የሰንበት ት/ቤቱ ጥያቄዎች ተጨምረውበት እንኳ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ጥቂት ጥቅመኞችን ይዞ ሕግንና አሠራርን እየጣሱ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አካል የኾነውን ምእመን፣ “የት ትደርሳለህ? ምን ታመጣለህ?” ማለቱ፣ በድህነቱ፣ “ከአንድ ጧፍ የማያልፍ” እያሉ እየዘለፉና እያንቋሸሹ ለባለጸጋው ማድላቱ ውሎ አድሮ የዚህ ዐይነቱን አደጋ ነው የሚጋብዘው፡፡

አኹን አዋጩ አካሔድ፡- ከኹሉም ባለድርሻ አካላት ጋራ ቶሎ ብሎ ወደ ውይይት መግባት ነው፤ ምን እናድርግ፤ ማለት ነው የሚሻለው፤ እንደ ማኅበረ ምእመናኑ ጥያቄ፣ የአስተዳደር አካላቱና በሕዝብ ሳይመረጡ ራሳቸውን የሰበካ ጉባኤና የልማት ኮሚቴ አድርገው የሾሙ ግለሰቦች ከቦታው መነሣት አለባቸው፡፡ ንቀትና ግትርነት አያዋጣም፤ ከጠላህ ሕዝብ ጋራ ተናንቀህ እንዴትና ምን ትሠራለህ? የሚተካውም አስተዳደር ምን ዐይነት ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፤ ችግሮቹን ለይቶ ወደ ተግባር ለመግባት ማኅበረ ምእመናኑንና የሰንበት ት/ቤቱን እያሳተፉና ሕግን አክብሮ መሥራት ግድ ነው፡፡ የተዘረፈም ነገር ስላለ ጉዳዩ የምር አያያዝ ይጠይቃል፡፡ ከምእመኑም፣ “ለምን የግል ጥቅም አላገኘንም፤” የሚሉ ያደፈጡ ሰዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ የሰንበት ት/ቤቱና የምእመኑ እንቅስቃሴ መጠቀሚያ እንዳይኾን፤ ቦታውን እንዳይዙት ተለይተው ጥንቃቄ ሊደረግባቸው፣ በዐይነ ቁራኛ ሊጠበቁ ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ በቋሚ ሲኖዶሱ ጥረት ካልኾነ፣ ሥራ አስኪያጁም ይኹኑ ፓትርያርኩ ጨክነው ተገቢ ርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ አይታመንም፡፡ ሥራ አስኪያጁ ተናዷል ይባላል፤ ሕዝቡ ምን እንደሚያመጣ አያለሁ፤ ይላል፤ ይኼ ሊከተል እንደሚችል አይረዳም እንዴ? ሕዝብ ምን ያመጣል፤ ከማለት ይልቅ ለምን መልስ አይሰጥም፡፡ ሕዝቡ ያመጣውማ ታየ፤ ገርፎና ረግጦ ከማባረር የዘለለ ምን ያድርግ? አስተዳዳሪውን “መቅደስ አልተዘጋብህም፤ ሔደህ እደር” ማለቱ ተገቢ አይደለም፡፡ ነገሩን እንዲያበርድ እንዲያረጋጋ ነው ማዘዝ የነበረበት፡፡ በብጥብጥ ጊዜ ቢቀድስ ቢባርክ ማን ይሰማዋል፡፡ ሒድ ምን ያመጣሉ፤ ማለቱ ምእመኑን መናቅ ነው፡፡ “ሒድ፤ መቅደሱ አልታሸገብህም፤” ከሚለው “ቆይ፤ አብርድ” ማለት ነበረበት፡፡ በመሀል ሰውዬው ተደበደበ፡፡

sealite mihret cathedral

አስተዳዳሪው፥ ፓትርያርኩ በእጄ ናቸው፤ይላል፤ ሰንበት ት/ቤቱን ያሸገውና የሥራ አመራሩን ያገደው በፓትርያርኩ ትእዛዝ እንደኾነ ይናገራል፤ በዚህም ምክንያት ሥራ አስኪያጁ ፈርቶታል፤ በመሀል ሕዝቡ አዳማጭ አላገኘም ነበርና ምላሹ አስከፊ ኾነ፡፡ በዋዜማው ቤተ ክርስቲያኑ ሳይከፈት አምሽቶ ነበር፤ ካህናቱ እንዳትከፍቱ ተብለናል፤ ብለው ነበር፤ ሕዝቡ ያባረረው ግን የአስተዳደር በደል ያደረሱትን የጽ/ቤት ሓላፊዎችንና የሰበካ ጉባኤውን እንጅ ካህናቱን ባለመኾኑ ታኅሣሥ 21 የእመቤታችን በዓል አገልግሎቱ ሳይታጎል ተከናወኗል፡፡ አስተዳዳሪውን ግን እናቶች እንዳሉት፣ “እመቤታችን በዕለተ ቀኗ ቀሠፈችው፡፡” (የማኅበረ ምእመናኑ የቃል አስረጅዎች)

 

Advertisements

6 thoughts on “በሰዓሊተ ምሕረት ምእመናን ቁጣ የተቀጡት የካቴድራሉ አስተዳዳሪ ሆስፒታል ናቸው፤“በዕለተ ቀኗ የእጁን ሰጠችው”/ምእመናን/

 1. Anonymous December 31, 2017 at 9:21 pm Reply

  የሀገረ ስብከት ሠራተኞች እራሳቸው ከእታች እስከ ላይ ዘረኞች ሌቦች ወንበዴዎች አይደሉ እንዴ ምድረ ዘረኛ

 2. Amanuel January 1, 2018 at 8:51 am Reply

  +++++++እስመ ለቀጣፊ ይደልዎ ጥፊ +++++++
  የተባለው ሸግዬ ቃል ይፈፀም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ!!

  እግዚአብሔር ቀናኢያን ወጣቶችን ይባርክ ሰውየው ያጋብስበት ከርስ እና ሽንፍላ እንጂ በጎ ምክር ይሰማበት ጆሮ የለውም እና +++ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው +++ ይሉትን ክቡር ሀገርኛ ብሒል በመተላለፉ ይኸው ለዚህ በቅቷልና እንኳን ለዚህ አበቃህ ከማለት ውጪ ለርሱ የምናባክነው ቃላት አይኖረንም!

  ቀድሞም በየቦታው ባሉ አማሳኞች ላይ እንዲህ ያለ ጥሩ ጉሸማ ቢደረግ ኖሮ እዚህ ባልደረሱም ነበር ።
  በእርግጥ አንዳንድ ቦታ ለምሳሌ መርካቶ ተክልዬ ደ/ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል እና የመሳሰሉት ቦታዎች በአማሳኞችና አፅራረ ቤተክርስቲያን ላይ ጅራፉ በስሱ አርፎባቸዋል። ያሁኑ ግን ግርፋቱ ከፍ ያለ ይመስላልና ጥሩ ነው ግን እንኳን አልሞተ፤
  ቤተ ክርስቲያን የሚቀኑላት እንዲህ ዓይነት ልጆች እንዳሏት ሳያውቅማ እንኳን አልሞተ፤ ማን ያውቃል ለበርካታ ልማት የሚሆንና ያጋበሰውን የቤተ ክርስቲያኗን ሃብት ተረከቡኝ ከዚህ በኋላ ዓለም ለኔ ከንቱ ናት ይልም ይሆናል ።

  እርሱና መሰሎቹ የሚፈሩት እግዚአብሔርን ሳይሆን ጅራፉን ስለሆነ በሚፈሩት ቋንቋ ማናገሩ ደግሞ ተመራጭ ነው አለዚያ ቅጥ ያጣ ብልግናቸውን በምንም ማረም የሚቻል አይመስልም ።
  +++የክብር ባለቤት ጌታችን ክርስቶስ +++ በውጭ ያሉትን እየመከረ እያስተማረ እየገሰፀም ወደመቅደሱ ሲመጣ በመቅደሱ ሲሸጡና ሲነግዱ የነበሩትን እንደ ሰዓሊተ ምህረት አስተዳዳሪ ዓይነቱን ወንበዴዎች ወንበር እየገለበጠ በጅራፍም እየገረፈ ነበር ከመቅደስ ያባረራቸው ሕይወት በሆነው ቃሉም +++ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት +++ሲል የገሰፃቸው!!!

  ታድያን ዛሬ የሰዓሊተ ምህረት ወጣቶች የሰሩት ግሩም ሥራ ያንን ያስታውሰናልና ተባረኩ ኑሩልን እድሜ ይስጣችሁ ከማለት ውጭ ምን ይባላል???

  +++++++እስመ ለቀጣፊ ይደልዎ ጥፊ +++++++
  እግዚአብሔር ለቅድስት ቤተክርስቲያን ክብር የሚጋደሉ ቀናኢያንን ያብዛልን ይጠብቅልንም! !

 3. Anonymous January 1, 2018 at 11:11 am Reply

  “ጌታ ቤተ መቅደሱን ያጸዳውኮ በትምህርትም በጅራፍም ነው” ያለ ማን ነበር?

 4. chris January 1, 2018 at 11:48 am Reply

  በእውነት ካባማትያስ እና ከጎይቶም ዳኝነት መጠበቅ የማይሆን ነው ምክንያቱም ሁለቱም ግብረበላወች ናቸው ቅዱስ ሲኖደስም አያገባውም ተብሎአል፤ በፓትርያርኩ፡፡ ስለቤተክርስቲያንዋ ደንታም የለውም፡፡ ባጠቃላይ ቤ.ክ መሪ የላትም፤ ሌባ ብቻ ነው ያለው፤ ምዕመናን፣ ሐይማኖታችንን እንጠብቅ! ከሳሊተምህረት ምዕመናን ጎን እንቁም፤ እብረን ድምፃችንን እናሰማ፡፡

 5. Anonymous January 2, 2018 at 5:51 am Reply

  Amen!

 6. Anonymous January 2, 2018 at 8:47 am Reply

  What a pity!!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: