አባቶች መንግሥትን መከሩ፤“አጥፊዎችን ችላ እያለ ሕዝብን ማፋጀት የለበትም፤መጠየቅ መብት ነው፤ በአግባቡ መመለስ ግዴታ ነው”

 • በመንግሥትም በቤተ ክህነትም መልካም አስተዳደር ጠፍቷል
 • መጠየቅ መብት ነው፤ መላሹ በአግባቡ መመለስ ግዴታው ነው
 • ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ ሰላም ድርሻዋን በጸሎት እየተወጣች ነው

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፤ ለኢኦተቤ-ቴቪ እና ኢቢሲ

†††

 • በጎጥ መለያየት ጥሩ አይደለም፤ ጥንቃቄ ይደረግበት ስንል ጮኸናል
 • ሳይስፋፋ መከላከል ያስፈልጋል፤ ሓላፊነቱ ያለበት መንግሥት ነው
 • ቤተ ክርስቲያንን በሚያፈርሱት መንግሥት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል

ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ የሰሜን ምዕ/ሸዋ – ሰላሌ ሊቀ ጳጳስ፤ለአዲስ አድማስ

†††

ሰሞኑን በአገራችን የተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተከሠቱ ጎሠኝነት ተኮር ግጭቶች፣ የአራት ተማሪዎች ሕይወት መጥፋቱን መንግሥት አረጋግጧል፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች መፈናቀልና በመቶዎች ለሚቆጠሩቱ ኅልፈት ምክንያት የኾነው፣ የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች የድንበር ግጭት ዳግም አገርሽቶ በርካቶች ለሞት መዳረጋቸውም ታውቋል፡፡ መንግሥት አጥፊዎችን ለሕግ እንደሚያቀርብ ያስታወቀ ሲኾን፣ በግጭቱ ለሞቱት ዜጎች ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማውና ለቤተ ሰዎቻቸው መጽናናትን እንደሚመኝ ገልጿል፡፡

የመንግሥት ሓላፊነት፣ የሐዘን መግለጫ ማስተላለፍ ብቻ ሳይኾን፣ ሞትም ኾነ ጉዳት በዜጎች ላይ እንዳይደርስ መከላከል ነው፡፡ ብዙዎች፣ ኹኔታው ስጋት ላይ እንደጣላቸውና በአፋጣኝ መፍትሔ ማበጀት ካልተጀመረ ወደ ጥፋት መንገድ ማምራታችን አይቀሬ ነው፤ ሲሉ ያስጠነቅቃሉ፡፡

ስለ ጉዳዩ ኢኦተቤ-ቴቪ እና ኢቢሲ ያነጋገሯቸው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ጥያቄዎች በወቅቱና በአግባቡ ቢመለሱ ችግሩ እዚህ እንደማይደርስ ገልጸዋል፡፡ “መጠየቅ መብት ነው፤ መላሹ አካል በአግባቡ መመለስ ግዴታው ነው፤” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በውስጥም በውጭም ያሉ ወገኖች ለሰላም ሊያደሉ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

የችግሩ መንሥኤ ፖሊቲካዊ ብቻ ሳይኾን የመልካም አስተዳደር ዕጦትም መኾኑን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፣ “የምናየው ኹሉ የሚያስደስት አይደለም፤ በመንግሥትም በቤተ ክህነትም መልካም አስተዳደር ጠፍቷል፤” ማለታቸው ተጠቁሟል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከመጸለይ እንዳላቋረጠችና ስለ ሰላምም ድርሻዋን እየተወጣች እንዳለች ያስታወቁት ቅዱስነታቸው፣ ሌሎችም አካላት ለሰላም መስፈን ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ትላንት ዓርብ፣ ታኅሣሥ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ፣ በወቅታዊ ጉዳይ፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቪዥን(EOTC Tv) እና ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት(EBC) በጽ/ቤታቸው መግለጫ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በዛሬ ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. እትሙ፣ በዐዲሱ ትውልድ አእምሮ ውስጥ የተዘራውን የጎሠኝነት መርዝ እንዴት ማርከስ ይቻላል?” በሚል ጥያቄ መነሻ ካነጋገራቸው አንዱ የኾኑት የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፥ መንግሥት ሀገሪቱን በእኩልነት በመምራትና በማስተዳደር፣ አንድነትን የማጽናት ሓላፊነቱንና ተግባሩን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

“በጎጥ መለያየት ጥሩ አይደለም፤ ጥንቃቄ ይደረግበት ስንል ጮኸናል፤ የፈራነው እየደረሰ ነው፤” በማለት ያወሱት ብፁዕነታቸው፣ “አዝማሚያው ከተስፋፋ ኢትዮጵያ የለችም ማለት ነው፤” ብለዋል፡፡

መንግሥት አጥፊዎችን ችላ እያለ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ፣ ሕዝብን እርስ በርስ የሚያፋጅ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ብፁዕነታቸው መክረዋል፡፡ ከመንግሥት የሚጠበቀው የሐዘን መግለጫ ማስተላለፍና አዝኛለሁ ማለት ብቻ ሳይኾን፤ አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ ሥርዐት ማስያዝ፣ ተጎጅዎችን ደግሞ ቦታ ማስያዝ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትልቁ መሣሪያ ጸሎት ነው፡፡ በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰላም ባለቤት እግዚአብሔርን በምሕላ ጸሎት እየለመነች መኾኑን የጠቀሱት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ “መንግሥት ደግሞ ሀገሪቱን በእኩልነት መምራትና ማስተዳደር አለበት፤” ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንን የሚያፈርሱ ባለሥልጣናት እንዳሉ አያይዘው ያነሡት ብፁዕነታቸው፣ ድርጊቱን በመቃወማቸውና እንዲታረም በመጠየቃቸው በተቃዋሚ ፓርቲ አባልነት መፈረጅ እንደማያዋጣ አስጠንቅቀዋል፤ መንግሥትም ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል-“ይኼ ከፈጣሪ ያጣላናል፤ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው እየኾነ ያለው፤ መንግሥት ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል፡፡”

“ምኞታችን፥ የሀገራችን አንድነት ጸንቶ፣ ልማት ሰፍኖ፣ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ማየት ነው፤” ብለዋል ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፡፡

††††††††††††††††††

ከመንግሥት የሚጠበቀው አዝኛለሁ ብቻ አይደለም

የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህም በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ፈጣሪን በምሕላ ጸሎት እየለመንን ነው፡፡ የእኛ ትልቁ መሣሪያችን ይኼ ነው፡፡ አደራ ተሰጥቶታል የተባለው መንግሥት ደግሞ ሀገሪቱን በእኩልነት መምራትና ማስተዳደር አለበት፡፡ አጥፊዎችን ለሕግ እያቀረበ ሥርዐት ማስያዝ አለበት፡፡ ተጎጅዎቹን ደግሞ ቦታ ቦታ ማስያዝ ይገባዋል፡፡ ዝም ብሎ ከዳር ኹኖ እንደ ማንኛውም ሰው አዝኛለሁ ቢል አይኾንም፡፡ ሓላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ እንደ ሌላ ሀገራት መንግሥታት እርሱም አብሮ የሐዘን መግለጫ ማስተላለፍ አይጠበቅበትም፡፡

ሐዘኑ እንዳይደርስ የመከላከል ሥራ መሥራት ግዴታው ነው፡፡ አንድነትን ማጽናት ሥራው ነው፡፡ ድሮም የተፈራው ይህ ዐይነቱ ግጭት እንዳይመጣ ነበር፡፡ በጎጥ መለያየት ጥሩ አይደለም፤ ጥንቃቄ ይደረግበት ስንል ጮኸናል፡፡ የፈራነው ነው እየደረሰ ያለው፡፡ አኹንም ሳይስፋፋ መከላከል ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ሓላፊነት ያለበት ደግሞ መንግሥት ነው፡፡

አዝማሚያው ከተስፋፋ ኢትዮጵያ የለችም ማለት ነው፡፡ እኔ በ1999 ዓ.ም ስለዚህ ጉዳይ የጻፍኩት መጽሐፍ አለ፡፡ በወቅቱ አስጊ መኾኑን ተናግረናል፡፡ መንግሥት ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ ሥራ መሥራት የለበትም፡፡ አንዳንዶችም ቤተ ክርስቲያናችንን እያፈረሱ ነው፡፡ ይኼ ከፈጣሪ ጋራ ያጣላናል፡፡ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው እየኾነ ያለው፤ እያለቀስን ነው፡፡ መንግሥት ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል፡፡

ይኼን ስንል የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ናቸው እንባላለን፡፡ ይኼ ደግሞ አያዋጣም፡፡ ሀገሪቱ አንድነቷ ጸንቶ፣ ልማት ሰፍኖ፣ ስደተኞች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ማየት ነው፤ ምኞታችን፡፡ ሥልጣን የያዘ አካል ደግሞ በሥነ ሥርዐት መምራት አለበት፡፡ አጥፊዎችን ችላ እያለ፣ ሕዝብን እርስ በርሱ ማፋጀት የለበትም፡፡(ፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ የሰሜን ምዕ/ሸዋ – ሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ለአዲስ አድማስ)

Advertisements

8 thoughts on “አባቶች መንግሥትን መከሩ፤“አጥፊዎችን ችላ እያለ ሕዝብን ማፋጀት የለበትም፤መጠየቅ መብት ነው፤ በአግባቡ መመለስ ግዴታ ነው”

 1. Anonymous December 23, 2017 at 2:10 pm Reply

  ቃለ ሕይት ያሰማልን

 2. Anonymous December 23, 2017 at 2:34 pm Reply

  “የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች” እንደ ተባለው አባ ማትያስ አሁን ስለመልካም አስተዳደርም ሆነ ስለዘረኝነት ለመናገር ድፍረቱን ከየት አመጡት? ከሳቸው በላይ ዘረኛና ብልሹ አስተዳዳሪ አለ ወይ በአሁኑ ሰዓት ኦሮሞውንና አማራውን አገልገይ እያሰቃዩ እና እያስራቡ ትግሬውን እየሰበሰቡ እየሾሙ ያሉት እርሳቸው አይደሉም ወይ በትረ ሙሴ ያዣቸው ትግሬ ፕሮቶኮላቸው ትግሬ እንጀራ አቅራቢያቸው ትግሬ ጋርዳቸው ትግሬ ሥራ አሥኪያጃቸው ትግሬ አንጣፊያቸው ትግሬ አልባሻቸው ትግሬ ኧረ ለመሆኑ እርሳቸው ከትግሬ ውጪ የሚያቀርቡት ሰው አለ ወይ? ብቻ ፍርዱ ከአምላክ እንጠብቃለን አሁን ደግሞ እርሳቸውን ብሎ መንግሥትን መካሪ መፈሪያ ፡፡

  • አማን December 24, 2017 at 6:09 pm Reply

   እውነት ነው ግን እንዲህ እስከ መቼ ?

 3. Anonymous December 23, 2017 at 3:21 pm Reply

  ህወሀት በፖሎቲካው ዘርፍ በጥቡዓኑ በነ ለማ መገርሳና በነ ገዱ አንዳርጋቸው የተነቃበትና ውጥረት ውስጥ መግባቱን ስላወቀ በትግራዋዩ አባ ማትያስ ምክር ሰጪነትና አሸማጋይነት ቤተክርስቲያኗን ተጠቅሞ የተለመደና ያረጀ ሥራውን ከመሥራት እንደ ማይቦዝን ማወቅ አለብን አሁን አባ ማትያስ የሕዝብ ሰቆቃ ገዷቸው ነው መካሪ እና አሳቢ መስለው ብቅ ያሉት ያ ሁሉ የኦሮሞ ተወላጅ ሲጨፈጨፍ የት ነበሩ ምክንያቱም ለሳቸው ሰው ማለት ትግሬ ብቻ ነው ሌላውማ የዶሮ ያህል እንኳን ዋጋ የለውም ትውልድ ሁሉ መንቃት አለብህ “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት”ሲጀመር አባ ማትያስ የትግሬን ቤተ ክርስቲያን እንጂ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን አይወክሉም ለምን ቢባል ቤተ ክርስቲያናችን ዘረኛ ፓትርያርክ የላትም “የወያኔ ኑሮ የታያል ዘንድሮ”

 4. Amanuel December 23, 2017 at 8:57 pm Reply

  እውነት ለመናገር በኢትዮጵያችን የሚታየው የሚሰማው የሚደረገው ሁሉ ነገር ጥሩ አይደለም! ዘረኝነት ጥርስ አውጥታ ዜጎችን በክፉው የነከሰችበት እና መጪውን ጊዜ በምን ይፈጠር ሰቀቀን እንድንጠብቅ ያስገደደችን ወቅት ቢኖር ያሁኑ ጊዜ ነው ።

  ከቤተ ክህነትም ከቤተ የመንግስትም የህዝቡን ልብ የሚያሳርፍ የተስፋ ሕያው ቃላት የነጠፉበት መፍትሄዎች የሚባሉት ነገሮች ራሳቸው ችግር እየሆኑ ያሉበት ቀፋፊ ወቅት!

  ህዝብ በመሪው ላይ ተስፋ ከቆረጠ ከባድ ነገር ነው ። ምን አልባት የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት ገዢዎች የተለያዩ ስልቶችን ሊነድፉ ይችሉ ይሆናል በስልጣን እንቆይበታለን ብለው የዘየዱትንም ስልት እንደየ ወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ በመጠንቀቅና በመቆጣጠር ጊዜ ይገዙበታል ።

  እንዳለመታደል ሆኖ የኛ ያሁኖቹ መሪዎች ተጨቆነ ላሉት ህዝብ መፍትሄ ይሆነዋል ብለው የወጠኑለት ከሌላው ወገኑ ተነጣጥሎ በቋንቋው ድንበር ተበጅቶለት የክልል ባንዲራ ፣የክልል ቲቪ ፣ የክልል ስፖርት ፣የክልል ፖሊስ ወዘተ… በመፍጠር ተዋዶና ተከባብሮ በአንዲት ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ድርና ማግ ሁኖ ተሳስሮ ተዋህዶም ይኖር በነበረ ህዝብ ላይ በጎጠኝነት አቁስለውት የማይሽር ጠባሳን ፈጥረውበት ለዛሬው ምስቅልቅል አበቁት በእውነት እግዚአብሔር ይይላቸው።

  ከቀደመው ስህተት ተመልሶ ይሄን ከባድ እና ምንአልባትም መለኪያ የሌለው ጥፋት ለማከም መጣርም አንድ ነገር ነበር!! መንግስታችን ግን የብዙ አዋቂዎችን ምክር መቀበል እንደ የበታችነት በመቁጠር ለሌላ ጥፋት ወደፊት ከመፍጠን በቀር የኋላውን ስህተት ለማረም ዞሮ የሚያይበት አንገት ያለው አይመስልም በመሆኑም አሁንም ነገሮችን በሰራዊት ብዛት ለመቆጣጠር የመረጠ ይመስላልና ልብ ይስጥልን።

  ሀገሪቱ በቀድሞ ታሪኳ ደሃ ሲበደል ንጉስን የሚመክሩ እና የሚገስፁ ለድሃው እንዲራራ፣ ፍትህ ርትዕን እንዲያደርግ፣ ቀንበር እንዲያለዝብ፣ ከሽንገላና አድር ባይነት የፀዳ ስብዕናን ተላብሰው ገዢዎችን ወደቀናው መንገድ የሚመሩና በሕዝቡም በመሪዎችም በእግዚአብሔርም ፊት ሞገስ የነበራቸው ርቱዓን አባቶች ነበሯት ።
  ዛሬ የሉም ማለቴ አይደለም አሉ አልፎ አልፎ በተነጣጠለ መልኩ የሚጥሏትን አንዲት ተግሳፅ ቃል እንደ ብርቅዬ ነገር ቆጥረን ያችን ጢኒጥ ተግሳፃቸውን ለዓመት ያህል የምናወራላቸው አባቶች አሉን ኸረ እነሱንም አያሳጣን በጥቂቱ ካላመሰገንን ያችኑም ማጣት አለና!!

  በዚህ ህዝቡ አንዳች መልካም ነገር በሚጠብቅበት ወሳኝ ወቅት በንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ ተነቦ በቤተክርስቲያናችን ቲቪ የታየው የሃይማኖት ተቋማት ህብረቱ መግለጫ እንዴት ያበሳጫል! ! ባይደገም ምንኛ መልካም በሆነ እኔ ስለእውነት አፍሬአለሁ አዝኛለሁም።
  ይሄ ሁኔታስ ወዴት ያደርሰን ይሆን? ሀገሬ ፈጣሪ ምህረቱን ይላክልሽ ።

  የተከፋን እና የተቆጣን ወገን ለማለዘብ ቢፈለግ እንዲህ ባልተደረገ ነበር ንቡረዕዱ ከቀሚስና ቆባቸው ውጪ መንፈሳዊ ወዝ በተለየው ስብዕናቸውና በምንም ሊደብቁት በማይችሉት ቀፈታቸው ስክሪኑ ፊት ቀርበው ያነበቡት መግለጫ መሳይ ነገር ዋናውን የጉዳዩን ባለቤት መንግስትን ሳይጠቅስ (አንተም ተው ሳይል) በማለፋና ቃላቱ ሁሉ ከመንግስት ባለስልጣናት አንደበት በየጊዜው በምንሰማቸው የተለመዱ መንግስታዊ ቃላት የታጨቁ በመሆናቸው የሃይማኖት ተቋማት ህብረቱ የአቋም መግለጫ ሳይሆን ንቡረዕዱን የመንግስት ባለስልጣን አስመስሏቸዋልና እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት በእሳቱ ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ ያለፈ ፋይዳው አይታይምና ቢታሰበት! !

  ህዝቡ ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን እና እግዚአብሔርን መፍራቱን መሰረት በማድረግ ከየትኛውም ወገን ለሚነሱ የጎጠኝነት እና የከፋፋይ አጥፊ ድርጊት ራሱን አሳልፎ ከመስጠት መታቀብና ይልቁንም በፀሎት ፈጣሪ የምሕረት ዓይኖቹን እንዲመልስ እንዲራራልንም በፀሎት መትጋት ይጠበቅበታል ደጋጎቹ አባቶቻችን በየሀገረ ስብከታችሁ ሱባዔና ፀሎት ማወጁ ወቅቱ የሚጠይቀው አብይ ጉዳይ ይመስለኛል
  እግዚአብሔር ሀገራችንን እና ደግ ህዝቧን በፍቅር እና በአንድነት ይጠብቅልን!!!

 5. Anonymous December 26, 2017 at 2:14 pm Reply

  እንደ እውነቱ ከሆነ ለዋልጌዎቹና አሽቃባጮቹ የሃይማኖት አባቶች ተብዬዎች መንጌ ቢኖር ጥሩ መድኃኒታቸው ነበር ምን ያድርጉ መንግሥትም ሆነ እነርሱ ከማሽቃበጥ ውጪ ሌላ ምንም ሥራ የላቸውው

 6. Anonymous December 28, 2017 at 9:42 pm Reply

  አባ ማትያስ በቤተ ክህነትም መልካም አስተዳደር ጠፍተዋል የሚሉት የቤተክህነቱን መወቅራዊ አሰራር በማፍረስ ከፕትርክና እስከግብዝና ያለውን ሀላፊነት የጨበጡት እሳቸው አይደሉም ዎይ ተበላሸ የሚሉት ምን ተበላሸ ብቻ ተፀዳዱበት እንጂ::

  አዲስአበባ ሀገረ ስብከትን ከመዋቅር በማውጣት ለሙስናና ለዘረፋ ያደረጉት እሳቸው አይደሉም ዎይ ከህተወጥ ቅጥርና ዝውውር የሚመነተፈው ገንዘብ የአንበሳው ድርሻ የእሰቸው አይደለም ዎይ ከስጋው ጿሚ ነኝ የመረቁ ሌባ የሌቦች አባት አባማትያስ በቤተክህነት መልካም አስተዳደር የጠፋው በእርስዎ ነው ሌባውም ዘራፊውም እርስዎ ነዎት ጉበኛ እርስዎ ነዎት ቀና መልክ እንጂ ቀና ህሊና ያልፈጠረለዎ

  ሰዎች ከስራቸው እየተፈናቀሉ በላያቸው ላይ በፈተና ያላለፋ ከብር 50000 -200000 እየከፈሉ በቢሮ እየተመደቡ ለአዲስ የእልቅና ምደባ ብር 400000 ሺህ ብር ሙዳየሙፅዋት ወደሚዘረፍበት የቦታ ኪራይ ወዳለበት ከሚዛወሩ አለቆችና ፀሀፊዎኔች እስከ 700000 ሺህ ብር የደረሰው በእርስዎና በደደቡ ሌባ ስራ አስኪያጅዎ በአቶ ጎይቶም እኮነው ትንሽ ህሊናና ማሰብ ያልፈጠረበዎ እርስዎ ነዎት;

  ሠራተች በስራቸው እንዳይሰሩ እያፈናቀሉ አቀባዮችዎን አጉራሸችዎን ያለሙያቸው እያስቀመጡ ያሉት ኮሜንት አድራጊዎች በቂ ኢንፎርሜሽን ይኑራችሁ:: ትግሬ ትግሬ የምትሉት ትግሬዎች አነ የማነ እነ ሊቀጠብት ኤልያስ አባርረው በነ አቶ ጎይቶምና አቶ ገብረ ሂወት አልተኩም እንዴ? አነ ፀጋየ አልተባረሩም እንዴ የሳቸው ትግሬ ከመቀሌ ወዲህ አያካትትም አትሳሳቱ ሰውየው አምባገነን ናቸው የቆጠራችኋቸው ሁሉ

  አንዴ በዛሚ ሬድዮ ተጠይቀው ሲመልሱ በትርፍ ሰአትዎ ምን ይሰራሉ ሲባሉ ኤክሰርሳይስ አደርጋለሁ አሉ እስፖርት ከሚሰሩ አይሰግዱም ማፈርያ እርግጥ ለማፈር አእምሮ ያስፈልጋል አሁን ባለቻቸው ሰአት ጉቦአቸውን ይሰብስቡ መብላትካ አይበሉትም

  ጉቦ ባለመስጠታቸው አንድ ሊቀጳጳስ ጨምሮ 321 ወለየዎች ከስራ ተባረዋል 87ጎንደሬዎች ተባረዋል በቁጥር 27 የሚሆኑ ዝርያ የሌላቸው ከስራቸው ከግል ካምፓኒያቸው አዲስበበ ሀገረ ስብከት ተባረዋል ለማን ይነገሩ አትስረቅ ትላለህ አንንተ ትሰርቃለህ ብለዋል መፅሀፋ ደግም አፈለኝ ብለው መንግስት መውቀሳቸው መጠየቅ መብት ነው ካሉ ከስራችን ተባረርን ጉቦተጠይቅን ብለው ለሚጠይቁዋቸው መልስ አይሰጡም

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: