የቅ/ሥላሴ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ትምህርት አቆሙ፤ “መቋረጥ የሌለባቸው አገልግሎቶች ተቋርጠዋል”

 • የተከሠቱ አለመረጋጋቶች ያሳስቡናል፤ሰላምንና ፍቅርን ለሕዝቡ የምንሰብክበት ወቅት ነው
 • በአንጋፋና ወደ ዩኒቨርስቲ በሚሸጋገር ኮሌጅ፥ሊሟሉ የሚገቡ አገልግሎቶች ተቋርጠውብናል
 • የውኃ ጦት እና የጽዳት መጓደል በአፋጣኝ ይፈታ፤የተማሪው ጤና አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል
 • የጽሕፈት መሣሪያ፣የንጽሕና መጠበቂያና የደንብ ልብስ አለመሟላት ለተጽዕኖ እያጋለጠ ነው
 • ደቀ መዛሙርት በትምህርት ላይ እንዳያተኩሩና ለመናፍቃኑ ማባበያዎች በር የሚከፍት ነው

†††

 • የቀሩ ኮርሶች፣ የስም ለውጥና የሰዓት ቅነሳ፤ከመንፈሳዊና ሴኩላር ኮሌጆች ጋራ አይጣጣምም
 • Sophomore English,Mathematics, Pedagogy,Antiquity፤ በሙሉ ከቀሩት ኮርሶች ናቸው
 • የፈተና ጥያቄ መደጋገም እያዳከመ ነው፤“ለዐዲስ ጥያቄዎች ዝግጅት የፈተና ኮሚቴ ይዋቀር”
 • የመምህራን ብቃት ይገምገም፤የትምህርት ነጻነት ይጠበቅ፤“አሸማቃቂ ንግግሮች ይታረሙ!”
 • ለደረጃ ተማሪዎች ማበረታቻ የለም፤በግቢ ቀርተው ይሳተፉ፤ስኮላርሽፕ ፕሮግራም ይመቻች

†††

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተዳደር፣ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማቋረጡን የተቃወሙና የተቋሙን አንጋፋነትና ቀጣይ ዕድገት የማይመጥኑ ዘርፈ ብዙ አስተዳደራዊና አካዳሚያዊ ችግሮች እንዲፈቱላቸው የጠየቁት ደቀ መዛሙርት ትምህርት ለማቆም ወሰኑ፡፡

ደቀ መዛሙርቱ፣ ዛሬ ዓርብ፣ ታኅሣሥ 13 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ከጠዋቱ የጸሎት መርሐ ግብር ጋራ በማያያዝ፣ በተማሪዎች መማክርቱ መሪነት በጸሎት ቤት ባካሔዱት ስብሰባ፥ በመንፈሳዊና ሰላማዊ አካሔድ ለኮሌጁ አስተዳደር ያቀረቧቸው የመብት ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው ትምህርት ለማቆም መገደዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

“እስከ አሁን የተከተልነው አካሔድ ውጤት አልባ በመኾኑ፣ ዛሬ ትምህርት ለማቆም ለደረስንበት ውሳኔ መነሻ ኹኗል፤” ያሉት ደቀ መዛሙርቱ፣ የኮሌጁ አስተዳደር የጉዳዩን አሳሳቢነት በማጤን ተገቢውን ተግባራዊ ምላሽ በአስቸኳይ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ተቀዳሚ ተግባራቸው ትምህርት እንደኾነና ለማቆምም የተገደዱት የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት በመቃወምና መብታቸውን ለማስከበር እንደኾነ ያስረዱት ደቀ መዛሙርቱ፣ “ከምንም ዐይነት የፖሊቲካ አጀንዳዎች ጋራ የተገናኘ አለመኾኑን ለመግለጽ እንወዳለን፤” ብለዋል፡፡

ከምረቃ በኋላ በየአህጉረ ስብከቱ በዕጣ ሲመደቡ የሚከፈላቸው 900 ብር ደመወዝ፣ የቤተ ክርስቲያንን አቅምና የኑሮውን ኹኔታ በማገናዘብ ተጠንቶ እንዲሻሻል የተወሰነና መመሪያም የተሰጠበት ቢኾንም፤ በሚመለከታቸው አካላት ተግባራዊ አለመደረጉን አውስተዋል፡፡ ዋናውን የስብከተ ወንጌል ሥራቸውንና በሚመደቡባቸው ሌሎችም ዘርፎች ሓላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት፣ ከዓመታት በፊት ተወስኖ ሲሠራበት የቆየው የደመወዝ ክፍያ ሊጤን እንደሚገባው ደቀ መዛሙርቱ አሳስበዋል፡፡

አያይዘውም፣ በአሁኑ ወቅት፣ በሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተከሠቱ አለመረጋጋቶች እንደሚያሳስቧቸውና እንደሚያስጨንቋቸው አውስተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖና አክብረው የሚማሩ የእናት ቤተ ክርስቲያን ልጆችና የመንግሥተ እግዚአብሔር ሰባክያነ ወንጌል እንደመኾናቸው፣ የመንጋውንና የሕዝቡን አንድነት ለመጠበቅ በየዐውደ ምሕረቱ ሰላምንና ፍቅርን፣ አንድነትንና አብሮ መኖርን መስበክ የሚገባቸው ወቅትና ጊዜ መኾኑን እንደሚገነዘቡም ገልጸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን፣ በሦስቱም መንፈሳውያን ኮሌጆች የሚማሩትን ደቀ መዛሙርት፣ የገንዘብ አቅሟ በሚፈቅደው መጠን “ምግብንና የመሳሰለውን አዘጋጅታ”፣ የሚያስተምሩ መምህራንና ሠራተኞችንም መድባ አስተምራ እንደምታስመርቅ፣ በ36ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ ተጠቅሷል፡፡ ከምረቃም በኋላ ወደ የአህጉረ ስብከቱ በመላክ ምእመናንን እንዲያስተምሩና በተለያየ የሥራ መስክ እንዲሠሩ ማድረጓን የሚገልጸው የጋራ መግለጫው፣ “በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሌለ” ልምድ መኾኑን በመግለጽ ያደንቃል፤ የተመደበው ወርኃዊ ደመወዝም፣ “በመጠኑም ቢኾን አቅሟን ግምት ውስጥ ያስገባ ነው፤” ይላል፡፡

HTTC strike1

ብዛታቸው 132 ያህል በሚኾኑ የኮሌጁ መደበኛ ደቀ መዛሙርት ፊርማ ተደግፎ፣ በአድራሻ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የተጻፈውና በግልባጭም የቋሚ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና ልዩ ልዩ መንግሥታዊ አካላት እንዲያውቁት የተደረገው ደብዳቤ ግን፣ ይህን የሚያስተባብልና ከሪፖርትም የዘለለ እውነታነት እንደሌለው ነው የሚቃወመው፡፡

ለአጠቃላይ ጉባኤው በቀረበው ሪፖርት፣ ለመደበኛ ደቀ መዛሙርት፥ የመማሪያ ደብተሮች፣ እስክቢርቶ፣ የንጽሕና መጠበቂያ፣ የደንብ ልብስ እንደሚያሟላ የተገለጸውን በማስተባበል፣ በተግባር የሚደረግልን ነገር እንደሌለ በአጽንዖት ለመግለጽ እንወዳለን፤” ብለዋል ደቀ መዛሙርቱ፡፡

ሶፍት፣ ሳሙና፣ ደብተር፣ እስክቢርቶ፣ የደንብ ልብስ(ቀሚስ) እንዲሁም የክረምት ቀለብና የትራንስፖርት ገንዘብ የመሳሰሉት አስፈላጊ አገልግሎቶች፣ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በከፊል፣ በ2010 ዓ.ም. ደግሞ ሙሉ በሙሉ መቋረጣቸውን ጠቁመዋል፡፡ ይህንኑም ኮሌጁ፣ የ2009 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ሲጠናቀቅ ለክረምት አገልግሎት በተላኩበት ደብዳቤ እንዳስታወቃቸውና ከመኝታ፣ ምግብና ሕክምና በስተቀር ሌላ አገልግሎት እንደማይሰጥ እንደገለጸላቸው ደቀ መዛሙርቱ ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቶቹ አስፈላጊና በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚያስችሉ በመኾናቸው ውሳኔው በእጅጉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ ይበልጡኑ፣ ቤተ ክርስቲያንን ተስፋ አድርገው የመጡና ምንም የሌላቸው ደቀ መዛሙርት በመኖራቸው፣ ለመናፍቃን ማባበያ በር እንደሚከፍትና ለሌሎችም አሉታዊ ተጽዕኖዎች ስለሚዳርግ ውሳኔው በአስቸኳይ እንዲስተካከል አመልክተዋል፡፡

“የጤናችንም ጉዳይ አሳሳቢ ኹኔታ ላይ ይገኛል፤” ያሉት ደቀ መዛሙርቱ፣ የጤና መታወኩ መንሥኤዎች፦ የውኃ በተደጋጋሚ መጥፋት፣ የመጸዳጃ ቤቱና የግቢው አጠቃላይ ጽዳት መጓደል፣ መጸዳጃ ቤቱና የምግብ ቤቱ መቀራረቡ እንደኾነ በመዘርዘር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በመኖርያ ሕንጻ፣ በጸሎት ቤትና በምግብ አዳራሽ መንፈሳዊ ተቋምነቱን የሚገልጽ ሥነ ሥርዐት የተላበሰ ድባብ ቢኖርም፤ አንጋፋውና ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማደግ በሒደት ላይ የሚገኘው ኮሌጁ ሊያተኩርባቸውና መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉድለቶች በደቀ መዛሙርቱ አቤቱታ ተመልክተዋል፡፡ የጉድለቶቹ መሟላት፣ ከሌሎቹ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳውያን ኮሌጆችና ከሴኩላር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንጻር መታየት ያለበትና ደረጃውን ለመጠበቅም(ለመመጣጠን) ወሳኝ እንደኾነ ተገልጿል፡፡

የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት፤ የፈተና አወጣጥ ችግሮች፤ የአካዳሚያዊ ነጻነትና የመምህራን ብቃት ማነስ፤ መቅረት ሳይኖርባቸው እንዲቀሩ የተደረጉ፣ የስም ለውጥና የሰዓት ቅነሳ የተደረገባቸው ኮርሶች፤ የደረጃና ተሸላሚ ተማሪዎች ማበረታቻ አለመኖር፤ የተማሪዎች መማክርትን ተሳትፎ ያገለለና “ፍርሃትን የዘራ ነው” የተባለው ተማሪዎችን የማሰናበት ጉዳዮች፣ መፍትሔና አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው በደቀ መዛሙርቱ ተጠይቋል፡፡

“ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎቻችን እንደ ወትሮው ሁሉ አፋጣኝ ምላሽ ባገኙበት ቅጽበት ትምህርታችንን የምንጀምር መኾናችንን እንገልጻለን፤” ብለዋል ደቀ መዛሙርቱ፡፡

የኮሌጁ የደቀ መዛሙርት መማክርት ኅብረት እና መማክርቱን በማገዝ ጥያቄዎቹ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ በዛሬው ዕለት የተወከለው ዐሥር አባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴ በጽሑፍ ያቀረባቸውና በ132 መደበኛ ደቀ መዛሙርት ፊርማ የተደገፈውን አቤቱታ ዝርዝር ይዘት ይመልከቱ

Advertisements

One thought on “የቅ/ሥላሴ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ትምህርት አቆሙ፤ “መቋረጥ የሌለባቸው አገልግሎቶች ተቋርጠዋል”

 1. Anonymous January 3, 2018 at 10:06 am Reply

  በእውነት የሰአሊተ ምህረት ወጣቶች የወሠዱት እርምጃ በጣም ያስደሥታል ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ከጎናችሁ ነን ቤ፡ክርስቲያንዋ መሪ የላትም ፓትርያሪኩም ሌቦችን በማደራጀት እያዘረፋትነወ ጎይቶምም በሣሊተ ምህረቱ አለቃ ኮንዶ ሚኒየም የተገዛለት በመሆኑ ህዝቡ ምን ያመጣል እያለ ነው ስለዚህ ሁላችን ለእምነታችን ቆመነ ሌቦችን ከቤተ ክህነቱ ከሀገረ ሥብከቱ እስከ አጥቢያ ያሉት ማባረር ያስፈልጋል በተለይ 1ጎቶምን 2ንቡረእድ ኤልያስን ሌሎች ደላሎችንም ጨምሮ መዋጋት ያስፈልጋል

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: