ሰበር ዜና – ፓትርያርኩ ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ በቃል ጠየቁ፤ ጫና ለማሳደር የታሰበ ስልት መኾኑ ተጠቆመ

  • ከሥልጣን የመገለል ስጋት ባይኖራቸውም፣ተገቢነታቸው ብርቱ ጥያቄ እየተነሣበት ነው
  • በአቅም ማነስ ያጡትን ተቀባይነት ለመመለስ፣ ከአማካሪዎቻቸው ጋራ የወጠኑት ነው፤”
  • ለብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ምክር የሰጡት ምላሽ፣ ብዙዎችን ቢያሳዝንም ሊያግዷቸውም ዛቱ
  • የተወነጀሉት ብፁዕነታቸው፣ በምልአተ ጉባኤ እና በሕግም እንደሚጠይቋቸው ተጠቆመ
  • በሀ/ስብከታቸው ተቀባይነት ያጡት ብፁዕ አባ ማርቆስ፣በቦታቸው ለመተካት እየሠሩ ነው

†††

ታማኝነታቸውና መንፈሳዊ አባትነታቸው ተቀባይነት እያጣ መምጣቱ በብርቱ አሳስቧቸዋል የተባሉት፣ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ “መሥራት አልቻልኩም፤” ሲሉ ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ፣ ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቃል ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ፡፡

ፓትርያርኩ ጥያቄውን ያቀረቡት፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ አውጭና ወሳኝ አካል ከኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ እና ከሥራ አስፈጻሚው የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ አካል ጋራ ያላቸው ግንኙነት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደገባ እየታየ ባለበት ወቅታዊ ኹኔታ ውስጥ ነው፡፡

“መፍትሔ ሊሰጠኝ ይገባል፤” በማለት በሓላፊነታቸው ለመቀጠል እንደተቸገሩ በቃል ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መናገራቸውንና በቅርቡም በጽሑፍ እንደሚያሳውቁ ነው፣ ምንጮች የጠቆሙት፡፡

በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የፓትርያርኩ ሢመትና ርደት ጉዳይ የሚወስነው ቅዱስ ሲኖዶስ ኾኖ ሳለ፣ ጥያቄያቸውን ለባለሥልጣናት ማቅረባቸው፣ በቅዱስ ሲኖዶስና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዘንድ በአስከፊ ኹኔታ እያጡ የመጡትን ተደማጭነትና ተቀባይነት በተጽዕኖ ለመመለስ፣ ከአማካሪዎቻቸው ጋራ የወጠኑት መኾኑን እንደሚያሳይ ተነግሯል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶሱ፣ የመጀመሪያ ዓመታዊ የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ፣ ከነገ በስቲያ፣ ጥቅምት 12 ቀን እንደሚጀመር እያወቁ፣ ከሓላፊነት ለመልቀቅ ጠይቀዋል፤ መባሉ ይህንኑ ጫና የማሳደር ስልታዊነቱን እንደሚያረጋግጥ ነው የተገለጸው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ጋራ በተያያዘ የሚያቀርቡት የእግድ አጀንዳ፣ በቅዱስ ሲኖዶሱ አካላት(ቋሚ ሲኖዶስ እና ምልአተ ጉባኤ) ውድቅ መደረጉ፤ ቡድን ፈጥረው እየመከሩ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሚያስተላልፉት መመሪያ መሸራረፉ ሕመም እንደኾነባቸው ነው የተስተዋለው፡፡

የማኅበሩ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ሥርጭት፣ ከቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔ ውጭ እንዲታገድ ያስተላለፉት መመሪያ ተፈጻሚነት ሲያጣ፣ ከአጠቃላይ ጉባኤው 36ኛ ዓመታዊ ስብሰባ ተሳትፎ እንዲታገድ ወደ ማዘዝ ቢሸጋገሩም፣ እንዳሰቡት ሳይሳካላቸው ቀርቶ፣ በተፃራሪው፣ የማኅበሩ የማዕከልና የአህጉረ ስብከት ሥራዎች በጉልሕ እንዲስተጋቡ ምክንያት ኾኗል፡፡

በአጠቃላይ ጉባኤው መክፈቻ ምሽት፣ የማኅበሩ ተወካዮች እንዳይሳተፉ በማድረጋቸው፣ “የእኛን ሥልጣን ማወቅ አለባቸው፤ ሥልጣናችንን መረዳት አለባቸው፤” በማለት ከእነብፁዕ አባ ሩፋኤል፣ ብፁዕ አባ ማርቆስ እና ብፁዕ አባ ቶማስ ጋራ ውሎውን የገመገሙ ቢኾንም፤ በቀጣዩ ቀን፣ ማኅበሩ ከአህጉረ ስብከት ጋራ በመቀናጀት ያከናወናቸው ተግባራት በድምቀት እየተነገሩ በመዋላቸው፣ በጋራ መግለጫውና ቃለ ጉባኤው ላይ፣ የቴሌቭዥን ሥርጭቱ ሕገ ወጥ እንደኾነና እንዲዘጋ የሚጠይቅ አንቀጽ በጣልቃ እንዲገባ አርቃቂዎቹን አዝዘዋል፡፡ ሐሳቡን የተቃወሙ የአርቃቂ ኮሚቴው ሦስት አባላት፣ “የማኅበር ተላላኪዎች” ተብለው በሰብሳቢው የተዘለፉ ሲኾን፣ ሥርዋጹም በግድ እንዲገባና በድፍረት እንዲነበብ ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ ጉባኤው ያልተነሣ ጉዳይ በቃለ ጉባኤው የውሳኔ ሐሳብ ተብሎ መስፈሩ አግባብነት እንደሌለው ወዲያውኑ ከጉባኤተኛው ተቃውሞ የተሰማበትና በምክትል ሰብሳቢው ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁም ክፉኛ ቢተችም፣ ርእሰ መንበር የኾኑት ፓትርያርኩ ግን ሕገ ወጥነቱን ነው የተከላከሉት፡፡ ስሕተቶችን በፍጥነት እያረሙ፣ የአጠቃላይ ጉባኤውን ሒደት በጥብቅ እየተቆጣጠሩ፣ ማኅበሩን የማስወገዝና ሥልጣናቸውን የማግነን ምክራቸውን ያፈረሱባቸውን ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን፣ የመዝጊያ ንግግር እንዳደርግ ስለ ፈቀዱልኝ አመሰግናለሁ፤” በማለት በማጠቃለያ ቃለ ምዕዳናቸው በአሽሙር መናገራቸውም ተሰብሳቢዎችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡

የቤቱን ፈገግታ ያከሰመው፣ የፓትርያርኩ ክብረ ነክ ንግግር ግን ወዲያው ነበር የተሰማው፡፡ “ተናግሮ አናጋሪ የትላንቱ ሰውዬ” ያሏቸውን ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን በመዝለፍ፣ ለአጠቃላይ ጉባኤውም ለመንበረ ፕትርክናውም ክብር በማይመጥን ንግግር፥ ደጋፊዎቻቸውን ሳይቀር አሳፍረዋል፡፡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በእጅጉ አዝነዋል፤ ቁጣቸውን በግልጽ ያሳዩም ነበሩ፡፡

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፣ ፓትርያርኩ በሚሰጧቸው ሕገ ወጥና ረብሕ የለሽ መመሪያዎች እንዲጠነቀቁ፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን አቅርበው ማነጋገርን እንዲያስቀድሙ ነበር ምሳሌያዊ ምክር የሰጡት፤ ቅዱስ ሲኖዶሱንም ያሳሰቡት፡፡ እንደተለመደው ግን፣ በዚያው ዕለት ማምሻውን፣ በተጠቀሱት ክፉ አማካሪዎች፣ ምሳሌያዊ ምክሩ በአሉታ እየተተነተነ የፓትርያርኩ ቁጣ እንዲጋጋም መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

“አቡነ ፋኑኤል፣ በፈንጅና ጭስ መስለው የተናገሩትን [አማካሪዎቻቸው]ይዘው፣ ቅዱስነትዎ የሚጽፉት ደብዳቤ ከዚህ ግቢ ውጭ የማይሠራና አቅም የሌለው እንደኾነ፤ ምንም ቢጽፉ የትኛውም አካል የማያስፈጽመው ነው፤ ነገር ግን መነጋገርያ እየኾነ ብዙ ሰው እያደናገረ ነው፤ ብለው ተርጉመውላቸዋል፤ ይህም ሕመም ፈጥሮባቸው አድሯል፤”


ነውረኛ ንግግራቸው፣ በአጠቃላይ ጉባኤው ተሳታፊዎች ላይ የፈጠረውን ስሜት ቢያዩም፣ ይብሱኑ፣ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን ከሀገረ ስብከታቸው እንደሚያግዱ ነው የዛቱት፡፡ በሀገረ ስብከታቸው ተቀባይነት ያጡትና የመባረር ዕጣ የሚጠብቃቸው ብፁዕ አባ ማርቆስ፣ “ሀገረ ስብከቱን ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፎ ሰጥቶታል፤” እያሉ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤልን በማሳጣት በቦታቸው ለመተካት የፓትርያርኩን እልክ እየገፋፉ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡ “ምን ሲኖዶስ አለ፤ ሲኖዶስ እኛው ነን፤” በማለት ፓትርያርኩ፣ ሌሎችንም አባቶች እንዲያስተባብሩም እየወተወቱ ናቸው፡፡

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በበኩላቸው፣ ለተሰነዘረባቸው ውንጀላ ፓትርያርኩን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደረጃና በሕግም እንደሚጠይቁ ነው፣ የተጠቆመው፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ርእሰ አበው እንደመኾናቸው መጠን፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው ለቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ አመራር የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እንደተደነገገው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ እያስወሰኑና ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋራ እየተማከሩ መሥራት የሚጠበቅባቸው ቢኾንም፣ ከዚህ ውጭ እየመከሩ የሚከተሉት ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ አካሔድ፣ ታማኝነታቸውና መንፈሳዊ አባትነታቸው በካህናትና በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት እንዲያጣ፤ በባለሥልጣናትም ዘንድ አቅመ ቢስ ተደርገው እንዲናቁ አድርጓቸዋል፡፡ የመንግሥት ሹማምንትን ባገኙ ቁጥር፣ ማኅበሩን ዝጉልኝ የሚለው የዘወትር ውትወታቸው በእጅጉ እንዳስናቃቸውና ተደማጭነት እንዳሳጣቸውም ተጠቁሟል፡፡

በቃል አሳውቀውታል፤ የተባለውና በቀጣይም በጽሑፍ እንደሚያቀርቡ የተጠቆመው ከሓላፊነት የመልቀቅ ጥያቄ መነሻዎች ባለሥልጣናቱን እያነጋገረ ነው፣ ተብሏል፡፡ ከሥልጣን ለመልቀቅ ፍላጎት እንዳላቸው ከማሳየት ይልቅ፣ ከመንግሥት ያጡትን ትኩረት ለመመለስ፤ በዚህም፣ በቀጣዩ ሰኞ በሚጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ጫና ፈጥረው ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም፣ ከእኩይ መካሪዎቻቸው ጋራ የወጠኑት ስልት ሊኾን እንደሚችል ተጠቁሟል፤ “ትቼላችሁ እሔዳለኹ፤” እያሉ ማንገራገራቸው ዐዲስ እንዳልኾነ በማስታወስ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾኖ የተሾመ አባት ከመዓርጉ የሚወርደው፡- ሃይማኖትን የሚያፋልስ፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስነቅፍ ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ፤ በተሾመበት ቀን የፈጸመውን ቃለ መሐላ ካልጠበቀ፤ ታማኝነቱና መንፈሳዊ አባትነቱ ተቀባይነት ያጣ ከኾነና ይህም በተጨባጭ ተረጋግጦ በቅዱስ ሲኖዶስ ሲወሰን እንደኾነ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 33/1(ሀ)፣ (ለ) እና (ሐ) ተደንግጓል፡፡

8 thoughts on “ሰበር ዜና – ፓትርያርኩ ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ በቃል ጠየቁ፤ ጫና ለማሳደር የታሰበ ስልት መኾኑ ተጠቆመ

  1. Amanuel October 20, 2017 at 11:15 am Reply

    “ከመጣሽ ማርያም ታምጣሽ” ይሉት ብሂል የሚጠቀሰው ለእንደዚህ ዓይነቱ ግጥምጥሞሽ ነውና ቅዱስ አባታችን በደስታ ሊያሰክሩን እንዳይሆን ፤ ይህን ነገር አጓጉተውን ከተውት ግን ግፍ ይሆንብዎታል ። ስለ መድሃኒዓለም ብለው መልቀቂያ ማስገባቱን ይግፉበት ። ይህን ካደረጉ እንደእርስዎ ያለ ቆራጥ ተብሎ የሚወደስ የሚኖር አይመስለኝም ። +++++++ ይህን አምነው መልቀቂያ ለማስገባት ማሰብዎ ያስከብርዎታል እንጂ አያስነቅፍዎትም የእርስዎ ትልቁ ክብርም ይኸው ነውና ፤ አደራ ይህን ቅዱስ ሀሳብዎን አይጠፉት ፤ አሁን ደግ መካሪ ሳይጎበኝዎ አልቀረም ፤ እንዲህ ያለውን ብርቱና ቅዱስ ሀሳብ በማሰብዎ እናከብርዎታለን ። እውነት ለመናገር ከዚህ ያለፈ ጥፋት አጥፍተው የዘለዓለም ፀፀት ከሚለበልብዎ እንደ መልካም ታሪክም ሲወሳልዎ ይኖራልና በፈቃድዎ ለቀው ሀሴት ሙሉብን ።ከዚያ በኋላ ግን ስላለፈው ከባድ ጥፋትዎ እግዚኦ እግዚኦ ይበሉ ። በመሾምዎ ባይሰሩላትም በመውረድዎ ውለታ ይዋሉላት ለእርስዎም እረፍት ይሆንልዎታል ። መጥላትም መጠላትም ያደክማልኮ ፤ ምንአልባትም የጥሞና ጊዜ ይሆንልዎታልና አባ ሆይ አሳይተው እንዳይነሱን አደራ ሀሳብዎ ግሩም ነውና ይበርቱበት ይህን ለማድረግ አምላክ ያግዝዎ! !

  2. Sabawi mengesha October 20, 2017 at 2:58 pm Reply

    Wond lihonu newa gena. Lemejemeriya give tiru neger liseru newa.

  3. Amanuel October 20, 2017 at 3:46 pm Reply

    +++ብፁዕ አባታችን አቡነ ፋኑኤል በአንድ ወቅት ለበጋሻው ደሳለኝ ያለአቅሙ ያሸከሙትን የ “መጋቤ ሀዲስነት ስልጣን” በመቃወም ብዙ ተብለው ነበርና አባቴ ሆይ ዛሬ በዚያ አንወቅስዎትም እርስዎንም እንደሚፀፅትዎ አንጠረጥርምና! ! ++++++++++++++ የዚያን ወቅት የነፈሰው ነፋስ እርሱን እርሱን አስብሎት ነበርና ምክንያቱም ልጁም ለማወቅ ሳይሆን ለመታወቅ ብዙ ደክሞ ነበርና እርሱ ራሱን በጉልበት በሾመበት የ “ዲቁና ” ስልጣን ላይ እርስዎም አባታችን ነፋሱን ተከትለው “መጋቤ ሃዲስነቱን” ቢመርቁለት ምድር ጠብባው “ጨረቃ ላይ ቤተክርስቲያን እንሰራለን ” እስከማለት ራዕይ ይታየው እንደነበር መደስኮሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር ።
    +++++++ያለ አቅም የሚሸከሙት ስልጣን እንዲህ ያስዘላብዳልና ልጁ በወቅቱ ከነበረው ጭብጨባ የተነሳ ምድር ብታስጠላውና ጨረቃ ብትናፍቀው አይገርምም እንዲህ ያለ ስጋዊ ሰው ጥጋብ ሲያፋነው ዘለል ብሎ ጨረቃን እንደሚነካ ቢያስብ አንገረምም አሁን እርሱ ስም አጠራሩ የለም የተመኛት ጨረቃ ላይ ለመድረስ ያሰበው ራዕይ ጨንግፎበት 24 ቀበሌ ከምድር ከፍ ያለች ሕንፃ ተከራይቶ የቅጥረኝነቱን ስራ በግልፅ ይሰራል ። + ++++++++++++++++++++++++++++++++++ ብፁዕ አባታችን ዛሬ ስለቅድስት ቤተክርስቲያን ክብር መስራት እንደሚገባ በማሳሰብዎ ዘለፋ ደርሶብዎታል ። ብፁዕ አባታችን ስለቅድስት ቤተክርስቲያን ጥብቅና በመቆምዎ በፓትርያርኩ በደረሰብዎ ዘለፋ ተሰማዎን ??? ++++++++++አባታችን ከእርስዎ አላውቅምና በዚህ መልካም ስራዎ መነቀፍዎ ሊሰማዎና ሊያዝኑ ወደ ክስም ሊገቡ አይገባዎትም ባይ ነኝ ። እርስዎ ለመንጋው ጠባቂ ነዎት እንጂ ከሳሽ አይደሉም። ለክስማ ዘላፊዎ አሉ አይደል? ይታገድ፣ ይነቀል፣ ይወገድ፣ይታገድ፣ ሲሉ ክስ በመፃፍ ጡንቻቸው የዳበረ ፤ መግፋት እንጂ ማፍቀር ውስጣቸው የሌለና ያልታደሉ ፤ እርስዎ ምን በወጣዎ! ዶሴ ይዘው ክስ ፤ ++++++++++++እረኛ ብዙ ስራ አለበት እንደ ሰበ ዓለም በዓለም ፍርድ ቤት በመካሰስ የሚያባክነው ጊዜ የለውም። በጎቹ ከእርሱ የሚጠብቁት ብዙ ጉዳይ አለበት ።+++++++++++++++++ አዎን! እረኛ ሲከሰስ እንጂ ሲከስስ እንዴት ይሆናል? +++የክርስቶስ እንደራሴ ብፁዕ አባታችን፤ የሾመዎ ያለበደሉ ተከስሶ ከዚያም በላይ እስከሞት ለበጎቹ ነፍሱን የሰጠ አይደለምን ??? ዘላፊዎ ቤተክርስቲያንን ያዋረዱ መስሏቸው በየጊዜው ራሳቸው እየተዋረዱ እያዩ ሊፀልዩላቸው ሲገባ በግብራቸው የተከሰሱትን ሰው ምን ቀራቸውና ምናቸውን ይከሷቸዋል??? ++++++++++++++++++++++ብፁዕ አባታችን ይህ ክስ የሚባለው ጉዳይ ለእርስዎ አይመጥንም ። አባቶቻችን ፣ መሪዎቻችን ፣ እረኞቻችን ስለ ቅድስት ቤተክርስቲያን ስለምትከፍሉት ዋጋ ክብር ይገባችኋል ። የእናንተ ፅናት መንጋውን ያፀናል ። +++++እውነት እነጋገር ከተባለ የዓለም ሕይወቷም ሞቷም በእናንተ መዳፍ ላይ ነው ። እግዚአብሔር ይህን ታላቅ ክብር አስጨብጧችኋልና። በፅናታችሁ እንድንፀና በበረከታችሁ እንድንባረክ በፍቅራችሁ እንድንፋቀር በአንድነታችሁ አንድ እንድንሆን እንመኛለንና !!! +++++++++++++ እግዚአብሔር ለቅድስት ቤተክርስቲያን ልዕልናና ክብር የምትተጉትን ብፁዓን አባቶቻችንን በቸርነቱ ያብዛ ይጠብቅልንም!!!!!!!

    • Anonymous October 20, 2017 at 5:22 pm Reply

      የማህበረ ቅዱሳን ዝንቦች ቆፎአችሁ ሲነካ ብቻ ነው በዚህም በዚያም የምትንጫጩት ፓትርያርኩ ከአባትነታቸው ወርደው በተራ የሰው ሀይል አስተዳደር ክፍል ኋላፊነት ሦራ ተሠማርተው በከበረ ፊርማቸው የደብር ፀሀፊና የደብር ሂሣብ ሰራተኛ ሲያዘዋውሩ ነበር መጮህ የነበረባችሁ በወሎ ተወላጅ ተራ ሠራተኛችና አስተዳዳሪዎች በሊቀጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ህዝቅኤል ላይ የፈፀሙት የማባረር ተግባር በታሪክ አይረሳም ያኔ የቤተክርስቲያን ተቆርቛሪዎች ምን ምላሽ ሰጣችሁ በእናንተ ላይ ሲመጡ ግን ያዙኝ ልቀቁኝ አላችሁ ማንም አይሰማችሁም የኛ ፀሎት አንዲት የተከበረች የታፈረች ከተከበረ አባት ጋር ማየት ነው እናንተም እሳቸውም ጠፍታችሁ ማየት ነው

  4. ዮኒ October 20, 2017 at 6:06 pm Reply

    በቃ አባታችን ወደ አገሮ አሜሪካ ይምጡ።

    • Anonymous October 21, 2017 at 3:39 pm Reply

      ዮኒ ልክ አይደለህም ወደ አሜሪክ አትበል ወደ ሀገራቸው አጋሜ ነው እንጂ

  5. […] via ሰበር ዜና – ፓትርያርኩ ከሓላፊነታቸው ለመልቀቅ በቃል ጠየቁ… […]

  6. አዲስዓለም ጌታሁን April 15, 2019 at 1:47 pm Reply

    እግዚአብሄር መልካሙን ነገር ያሰማን የትንቢት መፈፀሚያዎች ሳይሆን የክብሩ መገለጫዎች ያድርገን

Leave a reply to Sabawi mengesha Cancel reply