የተወገዘው አሰግድ ሣህሉ: ከ6 ሚ.ብር በላይ በኾነ የዐሥራት ገንዘብ ምዝበራ የክሥ አቤቱታ ቀረበበት፤ በ‘ቃለ ዐዋዲ’ የቴቪ ጣቢያ ስያሜ የሕግ ክትትል ይደረጋል

 • ሱዳናውያን የኮፕት ምእመናን፣ለቤተ ክርስቲያናችን የሰጡት የዐሥራት ገንዘብ ነው
 • እነ ኢዮብ ይመርና ኳየሮቹ፣ ለመቀራመት ቢጠይቁትም ባለመፍቀዱ ተለይተውታል
 • በኹለት ተባባሪዎቹ ስም፣ በግል ባንክ የተቀመጠ 3 ሚሊየን ብርም መኖሩ ተጠቆመ
 • በኑፋቄው ያማለላቸውና ኦንሊ አሰግድ ከሚባሉት ባለትዳር ሴቶች መካከል ናቸው
 • ጥቆማውን ተከትሎ፣ እርሱና አንዲቱ ተባባሪው ከሀገር እንዳይወጡ መታገዱ ተነገረ
 • ፈውስስም ባዕለጸጎችን እየቀሠጠና እያማገጠ ትዳር ማፍረስን ልማዱ አድርጓል፤

†††

 • የመዘበረውን ዐሥራት፣ቃለ ዐዋዲለተባለው ጣቢያው እያዋለው መኾኑ ተጠቁሟል
 • እነአእመረ አሸብርን የቀጠረው ባለሀብት ቀድሞ ቢረዳውም፣በጥቂቱ ነው ተብሏል
 • “ጸጋዬ ሮቶ ነው የረዳኝ፤ እያለ ቢያስወራም ለሽፋንና የብሩን ምንጭ ለመሰወር ነው”
 • የሕግ አገልግሎት መምሪያ፣የቴቪ ጣቢያውን ስያሜ በማስለወጥ እንዲያስከብር ታዟል
 • ክትትል ተደርጎበት ለሕግ እንዲቀርብ፣ /ሲኖዶስ በውግዘቱ መመሪያ አስተላልፎ ነበር
 • 6.2 .ብር ምዝበራ የክሥ አቤቱታው ቀርቦ ወራትን ቢያስቆጥርም፣ እየተጓተተ ነው

†††

በዐሥራት ገንዘብ ምዝበራ የክሥ አቤቱታ የቀረበባቸው አቶ አሰግድ ሣህሉ እና ወ/ሮ ሰላማዊት የማነ

በተከራየው አዳራሽ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም፣ ሙዳዬ ምጽዋት በማስቀመጥና ከግለሰብ ዐሥራት በመሰብሰብ፣ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ለግል ጥቅሙ አውሏል፤ በሚል በተጠረጠረው ግለሰብ ላይ ቤተ ክርስቲያን የክሥ አቤቱታ አቀረበች፡፡

ከ6 ሚሊዮን በላይ ብር ምዝበራ የተጠረጠረው አሰግድ ሣህሉ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ባደረገው የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ፣ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት እና ሥርዓተ እምነት አፋልሶ ለምእመናን ኑፋቄ በማስተማሩ ተወግዞ መለየቱ ታውቋል፡፡

የውግዘቱ ውሳኔ በተላለፈበት የቅዱስ ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤ ላይ እንደተገለጸው፤ ግለሰቡ በቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ ደረሰኝ ብቻ ሊከፈል የሚገባውን የዐሥራት ገንዘብ፣ በተለያዩ ጊዜያት ከግለሰቦች እየሰበሰበ ለግል ጥቅሙ ያውላል፤ በሚል የተጠረጠረ ሲኾን፤ በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ አማካይነት፣ ጉዳዩን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማመልከቷንና በግለሰቡ ላይም ምርመራ እንዲጀመር በተደጋጋሚ እያሳሰበች መኾኗን ለመረዳት ተችሏል፡፡

ግለሰቡ የተጠረጠረበት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የዐሥራት ገንዘብ፣ የኮፕት ኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ከኾኑ ሱዳናውያን ምእመናን የተገኘ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ 5M የተባለ ቤተሰባዊ ስያሜን በያዘ ድርጅታቸው አማካይነት፣ በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በነበራቸው የአስጎብኚና ጉዞ ቢዝነስ እንዲሁም፣ በለገጣፎ 43ሺሕ መሬት ይዞታ ላይ ጀምረውት በነበረው የሪል እስቴት እንቅስቃሴ ከሚያገኙት ገቢ ዐሥራት እያሰቡ፣ ወ/ሮ ሰላማዊት የማነ በተባለች ኢትዮጵያዊት ወኪል ሠራተኛቸው አማካይነት፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲደርስላቸው በተለያየ ጊዜ በአደራ የሰጡት እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ማርቆስ ፊላታዎስ የሚባሉት የቤተሰቡ ሓላፊ፥ በቅድሚያ፣ ለአኵስም ጽዮን ሙዝየም ማሠሪያ ቃል የገቡትን 100 ሺሕ ብር፤ በመቀጠልም፣ ለጐንደር አቡን ቤት ገብርኤል የአብነት ት/ቤት እህል ግዥ(በኋላ ለጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን ማእከል የፍራሽና ብርድ ልብስ ግዥ የታሰበ) 50 ሺሕ ብር፤ በመጨረሻም በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አዳራሽ እንዲሠራ 6 ሚሊዮን ብር ሰጥተው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ይኹንና ገንዘቡን እንድታደርስ አደራ የተጣለባት የድርጅቱ ወኪል ሠራተኛ ወ/ሮ ሰላማዊት፣ ለቤተ ክርስቲያን ገቢ ከማድረግ ይልቅ፣ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ለኾነና ምንም ዕውቅና ለሌለው ለአሰግድ ሣህሉ ስታስተላልፍ ቆይታለች፡፡ ይህን በተመለከተ ጥቆማ የደረሰው የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ሙዝየም አሠሪ ኮሚቴም፣ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጻፈው ደብዳቤ ጉዳዩን በማስታወቅ በሕግ አግባብ እንዲጣራለት ጠይቋል፡፡

ውጉዙ አሰግድ ሣህሉ፣ በስም ከተጠቀሰው ቤተሰብ በተለያዩ ጊዜያት ለቤተ ክርስቲያን ገቢ መደረግ የነበረበትን የዐሥራት ገንዘብ በወ/ሮ ሰላማዊት የማነ በኩል ይቀበል እንደነበርና በድምሩ 6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ገደማ ያለአግባብ እንደወሰደ ኮሚቴው በደብዳቤው አስታውቋል፡፡ “ከልጅቷ ጋራ ካለው የጠበቀ ግንኙነት የተነሣ፣ እኔ ለወንጌል አገልግሎት ልውሰድውና ተገልግዬበት ወደፊት እመልሳለሁ፤ በማለት አዳራሽ ለራሱ ለማስገንባት እንዳሳመናት፤ ለዚህም እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበር በጥቆማው ለማወቅ ተችሏል፤ብሏል፣ ኮሚቴው፡፡

የባለኮከብ ሆቴልና የራድዮ ጣቢያ ባለቤት እንደኾኑ የተነገረላቸውና በአሁኑ ወቅት በካርቱም የሚኖሩት በጎ አድራጊዎቹ፣ የእኅት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በመኾናቸው፣ ዐሥራታቸው፥ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ለተሳሳተ ዓላማ እንዲውል እንደማይፈቅዱ ኮሚቴው ገልጾ፣ ለታሰበለት ዓላማ ሳይውል ለአሰግድ ሣህሉና “ቃለ ዐዋዲ” በሚል ላቋቋመው ሕገ ወጥ ድርጅቱ አላግባብ ተላልፎ መሰጠቱ በሕግ እንዲጣራለት ፓትርያርኩን ጠይቋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም፣ የኮሚቴውን ጥያቄ መነሻ በማድረግ፣ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር መጀመሪያ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጻፉት ደብዳቤ የክሥ አቤቱታ ማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡ በግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ፣ በአሰግድ ሣህሉ ላይ የቀረበው ጥናትና ማስረጃም፣ ከምእመናን ዐሥራት እየሰበሰበ ለግል ጥቅሙ የማዋሉን ሕገ ወጥ ድርጊት ያካተተ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ምልአተ ጉባኤው በውሳኔው፣ አሰግድ ሣህሉን በኑፋቄው አውግዞ የለየ ሲኾን፤ ስለ ዐሥራት ገንዘብ ምዝበራውም፣ በጥናቱ እንደተገለጸው፣ አስፈላጊው ክትትል ተደርጎና በማስረጃ ተደግፎ ወደ ሕግ እንዲቀርብ መመሪያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

መመሪያው መሠረት፣ ሦስት ልኡካን ተሠይመው ጉዳዩን በመከታተል ላይ ሲኾኑ፤ ለምርመራው የሚያስፈልጉ መረጃዎች ተሟልተው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንደተላኩ ተገልጿል፡፡ ይኹንና፣ የክሥ አቤቱታው ቀርቦ ወራትን ቢያስቆጥርም ሒደቱ እየተጓተተ ይገኛል፡፡“ለተጨማሪ የፖሊስ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠን ብንቆይም፣ የሕግ ሒደቱ የሚጠበቅበትን ርምጃ አላሳየም፤” ሲሉ የኮሚቴው ምንጮች ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የፖሊስ ምንጮች በበኩላቸው፣ የክሥ አቤቱታውና ተያያዥ ጥቆማዎች መቅረባቸውን ተከትሎ፣ አሰግድ ሣህሉና የምዝበራ ተባባሪው ሰላማዊት የማነ ተጠርተው እንደተጠየቁና ከሀገር እንዳይወጡም መታገዳቸውን በመጥቀስ ቅሬታውን ያስተባብላሉ፡፡

በሌላ በኩል፣ የምርመራው ሒደት መጓተቱ እየተገለጸ ባለበት ኹኔታ፣ ውጉዙ አሰግድ ሣህሉ የመዘበረውን ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የዐሥራት ብር፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ዳግም ለጀመረውና ‘ቃለ ዐዋዲ’ እያለ ለሚጠራው የቴሌቭዥን ጣቢያው ወጪ እያጠፋው እንዳለ ተጠቁሟል፡፡ የገንዘቡን ምንጭ ለመሰወርም፣ “ጸጋዬ ሮቶ ነው የረዳኝ፤” እያለ ሲያስወራ ቢሰነብትም፣ ለሽፋን እንደኾነ ተጋልጧል፡፡

በስም የጠቀሰው ባለሀብት(ጸጋዬ ደበበ)፣ ቀደም ሲል፥ የቴሌቭዥን ጣቢያውን፣ የአዳራሽና የቀበናውን ቤቱን ኪራይ ክፍያ በብዙ መቶ ሺሕዎች እያወጣ ሲሸፍንለት እንደነበር ርግጥ ቢኾንም፤ ኑፋቄው በስፋት መጋለጡንና ውግዘቱ ይፋ መኾኑን ተከትሎ ድጋፉን እንዳቋረጠበት ታውቋል፡፡ ድጋፉ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቦታ በመያዝ ከሚደረጉ የኑፋቄ እንቅስቃሴዎች ጋራ የተያያዘ መኾኑን የተናገሩ ምንጮች፣ “አሁን አሰግድ ለሚመራው የቴሌቭዥን ጣቢያ ያደረገለት እገዛ ካለም ጥቂት ወይም ምንም ነው፤” ብለዋል፡፡

ባለሀብቱ፣ “ፍኖተ ጽድቅ” በሚል የሰየመውንና የቀረፃ ስቱዲዮው በዐዲስ አበባ ጀርመን ዐደባባይ(መካኒሳ የመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ አቅራቢያ) የሚገኘውን የቴሌቭዥን ጣቢያ ለመክፈት እየተንቀሳቀሰ ሲኾን፤ ሰሎሞን ንጉሤን ጨምሮ በቅርቡ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ የለቀቁትን አእመረ አሸብርን፣ ኢዮብ ይመርንና ያሬድ ክብረትን በቦርድ አመራርነት፤ መኳንንት ተገኝን፣ ያለው ጸጋዬንና ሽመልስን(የቀድሞ አባ ነኝ ባዩ ሰላማ) በስታፍነት፤ ዘርፌ ከበደንና ‘7ቱ ዘማርያን’ ተብዬዎቹን(ሰሎሞን አቡበከር፣ አሸናፊ አበበ፣ ሐና መርዓዊ፣ ትርኃስ ኃይለ ሥላሴ፣ አማረ፣ ዘመናይና ዮርዳኖስ) በኳየርነት በማደራጀት እያረባረበ ይገኛል፡፡

አሰግድ ተወግዞ በመለየቱ፣ የቀድሞዎቹ የኑፋቄ አጋሮቹ በብዛት እየሸሹት ለባለሀብቱ ማደርን መርጠዋል፤ ከልክ ያለፈ ፍቅረ ንዋዩም ያራቃቸው እንዳሉ ታውቋል፡፡ ከግብረ ሰዶማዊነት ጋራ በተያያዘ ከሌላው ውጉዝ፥ አሸናፊ መኰንን ጋራ በብሎግ ሳይቀር በተወነጃጀሉበት ወቅት(ራሱም ቅሉ በዚሁ እኩይ ግብር ስለሚታማ)፣ ሰልፋቸውን ከእርሱ ያደረጉት እነኢዮብ ይመር፣ መኳንንት ተገኝና አበበ ታዬ፥ ከመዘበረው 6 ሚሊዮን የዐሥራት ብር እንዲያካፍላቸው ቢጠይቁትም አሻፈረኝ በማለቱ እንደተለዩት ቀራቢዎቻቸው ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ኢዮብ ይመር፣ ብሩን ለመቀራመት ብቻ ሳይኾን፣ “መልከኛ ናት፤” የተባለች እኅቱን ለማግኘት ጎምጅቶ፣ “ተግቶ ያገለግለው፣ ይላላከውም ነበር፤” ብለዋል፡፡

አሰግድ፥ እኅቱን፣ 6 ሚሊዮኑን የዐሥራት ገንዘብ፣ በአደራ ከተቀበለችው ወ/ሮ ሰላማዊት የማነ ጋራ በማስተዋወቅና በቤቴል ደብረ ኢዮር ቅዱስ ሚካኤል ሰበካ በሚገኘው G+2 መኖርያዋም ቤተኛ እንድትኾን በማትጋት፣ በዐይነ ቁራኛ ያስጠብቀው እንደነበር ተነግሯል፡፡ በሦስት ጆንያዎች ታስሮ በመኖርያዋ ለአንድ ወር ገደማ የቆየውን ገንዘብ አሳልፋ ከሰጠችው በኋላ ግን፣ እኅቱም እግሯን ማሳጠሯ ተገልጿል፡፡

የገንዘቡ በአሰግድ መወሰድ፣ ለወ/ሮ ሰላማዊት ትዳር መፍረስ ምክንያት እንደኾነና ከዐሥራ አንድ ወራት የቤተሰብ ጭቅጭና ከሦስት ወራት የፍርድ ቤት ውዝግብ በኋላ በፍቺ እንደተጠናቀቀ ታውቋል፡፡ ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ከማምራቱ አስቀድሞ፣ ውዝግቡን ለመፍታትና ትዳሩን ከመበተን ለመታደግ ለተቀመጡ ሽማግሌዎች፣ በአደራ ስትቀበል የቆየችውን የዐሥራት ገንዘብ፣ ለአሰግድ ‘የወንጌል አገልግሎት’ ብላ እንደሰጠች ማመኗን ለመረዳት ተችሏል፡፡

መቶ ሺሕ ብሩን፣ ለአኵስም ጽዮን ማርያም ሙዝየም አሠሪ ኮሚቴ ለመስጠት በተዘጋጀሁበት ሰዓት፣ የአሰግድም ማኅበር የቤተ ክርስቲያን አካል ነው፤ ብዬ ስላመንኩና እርሱም “ይበሉብሻል፤ ድንጋይ ከሚታነፅበት ሰውን እናንፅበት፤” ስላለኝ ሰጥቸዋለሁ፣ ብላለች፡፡ 50 ሺሕ ብሩም፣ ለጎንደር አቡን ቤት ገብርኤል የአብነት ት/ቤት እህል መግዣ እንዲደርስ ተፈልጎ ከአሰግድ ጋራ ሔጄ የነበረ ቢኾንም፣ ተቃውሞ ስለገጠመን ወደ አዲስ አበባ ተመለስን፤ ለጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ ማእከል የፍራሽና ብርድ ልብስ መግዣ እንዲኾን ወስነን ለማእከሉ ሥራ አስኪያጅ ደውለን ነግረን ነበር፤ በመሀሉ ግን አሰግድ፣ “ይህንንም ይሸጡብሻል” በማለት ለወንጌል አገልግሎት ወስዶታል፡፡ 6 ሚሊዮኑን የዐሥራት ብር፣ ማርኮ(በጎ አድራጊው)፣ ለቤተ ክርስቲያን አዳራሽ ማሠሪያ ብሎ ከሰጠኝ በኋላ፣ ከሽያጭ የተገኘ ነውና ቀሪ ተከፋይ ገንዘብ ስላለኝ እሰጣለሁ፣ ብሎ መልሶ ወሰደው፤ ብላ ለሽማግሌዎች ለመካድ ሞክራለች፡፡ የማይመስል ኾኖ ስላገኙት አልተቀበሏትም፡፡ በመኾኑም፣ በድምሩ 6 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር የዐሥራት ገንዘብ፣ ከታቀደለት ዓላማ ውጭ ለኑፋቄና ለግል ጥቅሙ አውሏል፤ እያዋለውም ይገኛል፡፡


ይኼስ፣ በቤተሰብ ውስጥ በተነሣ አለመግባባት በአጋጣሚ የታወቀና ባለፉት ኹለት ዓመታት ብቻ የኾነ ነው፡፡ ወ/ሮ ሰላማዊት ለማርኮ ድርጅት ለሰባት ዓመታት ያህል ስትሠራ የቆየች ናት፡፡ በመኾኑም፣ በቀሪዎቹ አምስት ዓመታትም በተመሳሳይ ኹኔታ የአሠሪዎቿን የዐሥራት ገንዘብ ስትቀበል እንደቆየች መገመት አያዳግትም፡፡ ለዚህም ማሳያው፣ ቀደም ሲል በጎ አድራጊ አሠሪዎቿ ሰጡኝ በምትለው ገንዘብ፣ የቀርሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን እያሠራሁ ነው፤ ብላ ስትናገር እንደነበር መሰማቷ ነው፡፡

በተጨማሪም፣ በብርሃን ባንክ ለገሃር ቅርንጫፍ፣ በእርሷና በሌላዋ የአሰግድ ምርኮኛ የባለሀብት ሚስት፣ “ለአሰግድ የወንጌል አገልግሎት” ብለው ያስቀመጡት 3 ሚሊዮን ብር መኖሩ መጠቆሙ ነው፡፡ ምንጩ የማይታወቀው ይኸው ተቀማጭ፣ ከምዝበራው አቤቱታ ጋራ በተያያዘ ለፖሊስ የተሰጠው መረጃ አካልም እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም በላይ፣ ወ/ሮ ሰላማዊት በዓለም ባንክ የሚገኘውን ሌላውን ቪላ ቤቷን ያሠራችበትና ቤተ ዘመዶቿን በሀብት ያንበሸበሸችበት ገንዘብ ምንጭም አጠያያቂ መኾኑ አልቀረም፡፡

በነገራችን ላይ፣ እኒህ ኹለት ሴቶች፣ ኦንሊ አሰግድ’ ከሚባሉትና በአሰግድ ኑፋቄና ‘የቅባ ቅዱስ ፈውስ’ ከደነዘዙት ባለትዳሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከባለትዳሮቹ፣ የሀብት ምንጭ የኾነውን ወገን(ሚስትን ወይም ባልን) እየለየ በመጠጋት መቀሠጥና ማማገጥ፣ ትዳሩንም ማፍረስ የምዝበራው ስልት አድርጎታል፡፡

በሰበካ ጉባኤ በተደራጀው የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደርያ ደንብ(ቃለ ዓዋዲ) ድንጋጌ መሠረት፣ እያንዳንዱ ካህንና ምእመን፥ ዐሥራት፣ በኩራትና የአባልነት ክፍያ የመክፈል ክርስቲያናዊ ግዴታ ያለበት ሲኾን፣ ማናቸውም የሰበካው ገንዘብና ንብረት ገቢም መሰብሰብ ያለበት ቤተ ክርስቲያኒቱ በሓላፊነት አሳትማ በምታወጣው ሕጋዊ ደረሰኝ /ካርኒ/ ብቻ ነው፡፡ ደንቡ በሥራ ላይ እንዳይውል በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚቃወሙ ካህናትከክህነታቸው፣ ምእመናን – ከአባልነታቸው እንደሚሰረዙ በቃለ ዓዋዲው ተደንግጓል፡፡

“ቃለ ዓዋዲ” የሚለው ስያሜም፣ እንደ መንግሥት የ“ነጋሪት” ጋዜጣ፣ በትእዛዝ ዐዋጅ ቁጥር 83/65፣ የቤተ ክርስቲያናችን ሰበካ መንፈሳዊ አስተዳደር ጉባኤ መተዳደርያ ደንብ የሚጠራበት በመኾኑ፣ የግለሰብ ማኅበር/ድርጅት ሊጠራበት እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ከዚሁ ጋራ በተያያዘ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎት መምሪያ፣ ስያሜውን በማስለወጥ እንዲያስከብር ሰሞኑን እንደታዘዘ ታውቋል፤ የሕግ አስተያየት በማቅረብም የሕግ ክትትሉን እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡

አሰግድ ሣህሉ፣ ያለአጥቢያው በሰንበት ት/ቤት አባልነት ሾልኮ በመግባት፣ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አገልግሎት ሲያውክ የኖረ ነው፡፡ ለስውር ተልእኮው፣ የተለያዩ ክፍተቶችንና አመች ናቸው ያላቸውን ጊዜያት በመጠቀም ያልተቋረጠ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ‘ቃለ ዐዋዲ’ በማለት የሰየመውን ቴሌቭዥን ጣቢያም የከፈተው በዚሁ አኳኋን ሲኾን፤ ቀደም ሲል ተወግዞ ከተለየው ግርማ በቀለ፣ የአንድ ዓመት ሥልጠና በመውሰድ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡ “የእውነት ቃል አገልግሎት” የተሰኘውንና በልደታ ኮንዶሚኒየም የሚገኘውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ድርጅት የሚመራው ግርማ በቀለ፣ ቤተ ክርስቲያናችንን ለመበቀል አተኩሮ የሚንቀሳቀስ ሲኾን፤ ከአሰግድ በተጨማሪ እነያሬድ ዮሐንስን፣ በጋሻው ደሳለኝንና በሪሁን ወንደወሰንን ለሦስት ወራት ማሠልጠኑ ታውቋል፡፡

ከሥልጠናው በኋላ እነበጋሻው ደሳለኝ ወደ ሐዋሳ በማምራት፣ “የጥንቷ ኦርቶዶክስ ሚሽን” በማለት በ‘ልሳንና ፈውስ’ ኑፋቄአቸውን በግልጥ ሲያካሒዱ፤ አሰግድም የቴሌቭዥን ጣቢያውን በመክፈት የግርማ በቀለን ስብከት እንደ በቀቀን ማስተጋባቱን ተያይዞታል፡፡ ጣቢያውን በ‘ቃለ ዐዋዲ’ ስም ቢሰይምም፣ የተመዘገበው ግን፣ ከመንግሥት የሚኒስትሪ ፈቃድ ከወሰዱ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጅ ድርጅቶች በአንዳቸው ሳይኾን እንደማይቀር እየተገለጸ ይገኛል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን አካላትና መዋቅሮች ላይ አተኩረው የሚሠሩ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን ኃይሎች፣ ላቋቋሟቸው ማኅበራት የሚሰጧቸው ስሞች፣ ከቤተ ክርስቲያናችን ስያሜዎችና ከጤናማ ማኅበራት መጠሪያዎች ጋራ ሊገጣጠሙ ይችሉ ይኾናል፡፡ ይህም ደኅናውን ስያሜ ለራሳቸው በመጠቀም የስውር ዓላማቸውንና ግብራቸውን ክፋት ለመሸፈን የሚያደርጉት ጥረት ነውና በቀጣይነት ሊጋለጡ ያስፈልጋል፡፡ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ የሕግ አገልግሎትም፣ በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት በአፋጣኝ ተንቀሳቅሶ የቃለ ዐዋዲ ስያሜን ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችንን የአእምሮና የንብረት ሀብቶች ቆጥሮና ዘርዝሮ በማስመዝገብ የባለቤትነት መብቷን ማስጠበቅ ግን መሠረታዊና ዘላቂ መፍትሔው ይኾናል፡፡

መነሻ ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ፣ ፲፫ኛ ዓመት ቁጥር ፮፻፳፱፤ ረቡዕ፣ መስከረም ፲፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም.

Advertisements

3 thoughts on “የተወገዘው አሰግድ ሣህሉ: ከ6 ሚ.ብር በላይ በኾነ የዐሥራት ገንዘብ ምዝበራ የክሥ አቤቱታ ቀረበበት፤ በ‘ቃለ ዐዋዲ’ የቴቪ ጣቢያ ስያሜ የሕግ ክትትል ይደረጋል

 1. Selomon Teka September 29, 2017 at 10:47 am Reply

  ዑቁዎሙ ለገበርተ እኪት – – – ፊል 3:2

 2. Anonymous September 29, 2017 at 10:53 am Reply

  The legal department of the EOTC has to be strong and work hard to preserve the rights and dignity of the Church in its entirety. The printing and distribution of all sorts of Church books and icons and the production and distribution of “newaye kidsat” has to be through the Church units and affiliated associations.

  The Church by no means should allow others to use its properties, names and symbols. We see some protestant associations who use our Church identities such as the Kebero, Mekuamia, Tsenasil and even the way we dress our netela.

  The big mistake is the failure of the Church leaders not to legally protect the identity of the Church and prevent others legally not to use any of its properties, symbols and artifacts.

  I hope the legal action against the defects will teach others.

 3. Amanuel September 29, 2017 at 11:07 am Reply

  በለው!!! ‘ሀጢአታችን በመስቀል ተውጧል’ እያለ ደናግላንን ባለትዳሮችን ፈት ሴቶችን በተቃራኒው በጣፋጭ ቃላት እየሸነጋገለ “ሃጢአትን ሲያስውጣቸውና እንደጡትም እያጠባና መራርነቷን ዘንግተው ቅልጥ ባለች ሴሰኝነት ውስጥ የዘፈቃቸውና ሃራ እንዳለችውም ” ኦንሊ አሰግድ ” የሚሉ ቅምጥል ኮረዶች ባለቤት እና “አነካኪው” በሚል የሚታወቀው ጩሉሌው ሰውአሰግድ ሳህሉ አስራት ሰብሳቢም ሆኖ ነበር? ጉድ ነው መቸም በንስሃ መመለስ እና የበደለውን መካስ ለርሱ የማይታሰብ ነውና የሰረቀውን ማስመለሱ ግን አግባብ ነውና ጉዳዩን በደምብ መከታተል ይገባል ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: