“የቱሪዝም አባት” ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ ሥርዓተ ቀብር፣ ነገ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በብሔራዊ ክብር ይፈጸማል

  • 50 ዓመት የቆየውንና ታዋቂውን13 ወር ጸጋ”(“13 Months of Sunshine”) የሚለውን አገራዊ የቱሪዝም መለዮ የፈጠሩ ናቸው፤
  • የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን(ETO) በማቋቋምና በመምራት የተፈጥሮና ባህላዊ ጸጋዎቻችንን ለዓለም ለማስተዋወቅ በትጋት የሠሩየኢትዮጵያ ቱሪዝም አባትናቸው፤
  • ከኢፌዴሪ መንግሥት የእውቅና የወርቅ ፒን ተበርክቶላቸዋል፤ 2008 ..የበጎ ሰው ሽልማትአግኝተዋል፤ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲም የእውቅና ሽልማት ሰጥቷቸዋል፤

†††

(አዲስ አድማስ፤ ዓለማየሁ አንበሴ፣ ቅዳሜ፣ ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)

“የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት” በመባል የሚታወቁት የአቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ ነገ እሑድ፣ ነሐሴ ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.፣ ከቀኑ በ5 ሰዓት፣ በዐዲስ አበባ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በብሔራዊ ክብር እንደሚፈጸም ተገለጸ፡፡

በሕክምና ሲረዱ በቆዩበት ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል፣ ባለፈው ረቡዕ፣ በ90 ዓመታቸው ሕይወታቸው ያለፈው አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰን፣ መንግሥት በታላቅ ክብር ለመሸኘት የተለያዩ ዝግጅቶች እያደረገ እንደ ኾነ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቶ ገዛኸኝ አባተ አስታውቀዋል፡፡

በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ፥ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ገዛኽኝ፣ “ሥነ ሥርዓቱ ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ በብሔራዊ ደረጃ ይከናወናል፤” ብለዋል፡፡

ባለፈው ዓመት፣ “ምድረ ቀደምት”(Land of Origins) የሚል ብሔራዊ የቱሪዝም መለዮ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት፣ ላለፉት ኃምሳ ዓመታት ሲያገለግል የቆየውንና በመላው ዓለም የሚታወቀውን፣ “የ13 ወር ጸጋ”(“13 months of Sunshine”) የሚል አገራዊ የቱሪዝም መለያ የፈጠሩት አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ ነበሩ፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የውጭ ሀገር ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ፣ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ቀርበው፣ ስለ ቱሪዝም ድርጅት አስፈላጊነት በማስረዳት ባገኙት ፈቃድ፣ የዛሬ 54 ዓመት(በ1955 ዓ.ም.)፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን(ETO) አቋቁመዋል – አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ፡፡

የሀገሪቱን ባህላዊ ታሪካዊ ገጽታዎች የሚያሳዩ የተለያዩ ፎቶግራፎችን በፖስት ካርድ መልክ በማሠራትም፣ የኢትዮጵያን የተፈጥሮና ባህላዊ ጸጋዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ በትጋት የሠሩ “የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት” ናቸው፡፡ በራሳቸው ተነሣሽነት ወደተለያዩ ሀገራት በመጓዝ፣ ለአገር ጎብኝዎች ኢትዮጵያን ያስተዋውቁ የነበሩት አቶ ሀብተ ሥላሴ፣ የኢትዮጵያን ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን በማቋቋም፣ ቱሪስቶች የአገሪቱን ባህላዊ መገለጫዎች በቀላሉ እንዲያገኙ ዕድሉን አመቻችተዋል፡፡

የአገሪቱን የቱሪዝም መዳረሻዎችና አቅጣጫዎች የሚያመላክቱ የመጀመሪያዎቹን ፍኖተ ካርታም ማዘጋጀታቸው ይነገርላቸዋል፡፡ እኒህ ታላቅ የአገር ባለውለታ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የእውቅና የወርቅ ፒን የተበረከተላቸው ሲኾን፤ የ2008 ዓ.ም. “የበጎ ሰው ሽልማት” አግኝተዋል፤ ዩኒቲ ዩኒቨርስቲም በቅርቡ የእውቅና ሽልማት ሰጥቷቸዋል፡፡

የዕድሜ ባለጸጋው አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ፣ ባደረባቸው ሕመም በታይላንድ ሲታከሙ ቆይተው ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲኾን፤ በደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እያደረጉ በነበረበት ወቅት፣ ባለፈው ረቡዕ፣ በ90 ዓመት ዕድሜያቸው ከዚኽ ዓለም በሞተ ዕረፍት ተለይተዋል፡፡

********************

አእአ በ1927 በዐዲስ አበባ የተወለዱትና ልዩ የተግባቦት ጸጋ የታደሉት አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ፣ ከዲፕሎማት ቤተሰብ የተገኙና ገና በልጅነታቸው በታላላቅ የውጭ ከተሞች ለመኖር ዕድሉን በማግኘታቸው፣ ስምንት የውጭ ቋንቋዎችን ለማወቅና አቀላጥፈው ለመናገር መልካም አጋጣሚ ኾኗቸዋል፡፡ ቅድመ ኮሌጅ በተፈሪ መኰንን ት/ቤት፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውንም በኦሃዮ ኦበርሊን ኮሌጅ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነትና ሥነ መንግሥት ተምረው ተመርቀዋል፡፡ ሥራቸውን በጀመሩበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፕረስ ጉዳዮች ሓላፊ በነበሩበት ወቅት፣ በሞያዊ ብቃታቸው በዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችና በውጭ እንግዶች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ነበራቸው፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የሥራ ሚኒስትር ከነበሩት ራስ ሥዩም መንገሻ ጋራ፣ እ.አ.አ. በ1960 በጀርመን የተካሔደውን የንግድ ኤክስፖ ተሳትፈው ሲመለሱ፣ ቱሪዝም ለአውሮፓ ሀገሮች ያስገኘውን ታላቅ ፋይዳ በመረዳት ለንጉሠ ነገሥቱ በቀረበ ሐሳብ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን እንዲያቋቁሙና በሓላፊነት እንዲመሩ ተደርገዋል፡፡ በአመራራቸውም፣ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስሕቦች(የዓባይ ፏፏቴን፣ ላሊበላን፣ ጎንደርን፣ ጥንታዊ ዜና መዋዕሎችንና ድርሳናትን) በማስተዋወቅ፤ የቀረጥ ነጻ ሽያጭ ሱቆችን ሐሳብ በማስተዋወቅና በማስፋፋት የመሳሰሉ ሌሎች በርካታ ጥረቶችን በግላቸውም በማድረግ ለሴክተሩ ዕድገት ታላቅና አስደናቂ ትጋት አሳይተዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ በቀድሞ መንግሥት ለስምንት ታስረው ቢቆዩም፣ ለአገሪቱ ቱሪዝም መጎልበት ጉልሕ አስተዋፅኦ እንዳላቸው በመገንዘብ ከእስር ተለቀው፣ በደርጉ የቱሪዝም ሚኒስትር ፍሥሓ ገዳ ሥር ዘርፉን ዳግም በመቀየስና በማደራጀት እንዲያንሠራራና እንዲነቃቃ የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በዚህም፣ ርእሰ ብሔሩ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ለስምንት ዓመት መታሰራቸው እጅግ ስሕተት እንደነበር በመግለጽ ይቅርታ ጠይቀዋቸዋል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስትሩ የሰሜን ኮርያ አምባሳደር ኾነው መሾማቸውን ተከትሎ በጡረታ ቢገለሉም፣ በየአጋጣሚው ቱሪዝሙን ለማሳደግና ለማስፋፋት የሚያስችሉ የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሣት ሚናቸውን ቀጥለው ቆይተዋል፡፡ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ሕብረ ብዙ ሀብቶች እንዳሉንና በአግባቡ ብንጠቀምባቸው፣ የውጭ ቱሪስቶችን ቁጥር ያለጥርጥር ለማብዛት እንደሚያስችሉን ይናገሩ ነበር፡፡

“የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት” አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ፣ የራስ መስፍን ልጅ ከኾኑት የቀድሞ ባለቤታቸው ወ/ሮ ሙሉ መስፍን፥ ሦስት ልጆች አፍርተዋል፤ አራት የልጅ ልጆችንም ለማየት በቅተዋል፡፡( http://www.thereporterethiopia.com/)

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: