ለሢመተ ጵጵስና የተመረጡት ቆሞሳት አጭር የሕይወት ታሪክ

አዲስ ስለ ተመረጡት ኤጲስ ቆጶሳት የምርጫ ሒደትና አጭር የሕይወት ታሪክ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት፣ በዜና ቤተ ክርስቲያን መምሪያ የተዘጋጀ ልዩ እትም፤

 •  አዘጋጅ፡- መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ
 • ፎቶ ግራፈር፡- መልአከ ሰላም አባ ኪሮስ ወልደ አብ

ለሢመተ ጵጵስና የተመረጡት ቆሞሳት የምርጫ ሒደት

በግንቦት 2008 ዓ.ም. የተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ዐዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን መርጦ ክፍት በኾኑ አህጉረ ስብከት ለመሾም ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ ጊዜውን መዋጀት የሚችሉ ቆሞሳትን መልምለው የሚያቀርቡ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል የተወሰኑ አባቶችን በኮሚቴነት ሠይሞ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህም መሠረት ኮሚቴው በእጩነት መልምሎ ካቀረባቸው 108 ቆሞሳት መካከል፣ 31 ቆሞሳትን ጨምቆ በማውጣት ለሢመተ ጵጵስና ውድድር ያቀረበ መኾኑ አይዘነጋም።

ስለኾነም ከግንቦት 1 ቀን እስከ ግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ኮሚቴው ለይቶ ካቀረባቸው 31 ቆሞሳት ውስጥ፦ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው፥ በኹለገብ ዕውቀታቸውና በአገልግሎታቸው ያመዝናሉ፤ ጊዜውንም ይዋጃሉ፤ ብሎ ያመነባቸውን 15 ቆሞሳት፦ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፥ ከአድባራትና ከገዳማት፥ ከአብነት ት/ቤቶች፥ ከመንፈሳዊ ኮሌጅ፥ ከውስጥና ከውጭ አህጉረ ስብከት በጥልቀት አጣርቶ እንደገና ጨምቆ በማውጣት ለሢመተ ጵጵስና መርጦአቸዋል።

ለሢመተ ጵጵስና የተመረጡት ቆሞሳትም የሚከተሉት ናቸው፤

ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፤

ቆሞስ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ

 • የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ሥራ አስኪያጅ፤

ከአድባራት አስተዳዳሪዎች፡-

ሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ ዘርዐ ዳዊት ኃይለ ሥላሴ

 • በአዲስ አበባ የመርካቶ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ

መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ወልደ መድኅን ተክለ ብርሃን

 • በአዲስ አበባ የእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ደብር አስተዳዳሪ

መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ኃይሉ

 • የመቀሌ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ደብር፥ የኪዳነ ምሕረት እና የልደታ ለማርያም አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ፤

ከገዳማት እና የአብነት ት/ቤቶች፤

አባ ኃይለ ሚካኤል ወልደ አምላክ

 • በደብረ ሊባኖስ ገዳም የብሉያት እና የሐዲሳት መምህር

ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ዕንቈ ባሕርይ

 • በቅዱስ ላሊበላ ገዳም የብሉያት እና የሐዲሳት መምህር

ከአህጉረ ስብከት፤

ቆሞስ አባ ዮሐንስ ገብረ ሥላሴ

 • የወላይታ፥ ዳውሮ እና ኮንታ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ

ቆሞስ አባ ወልደ ሐና ጸጋው

 • በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሓላፊ

መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ

 • የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ

ከመንፈሳዊ ኮሌጅ፤

መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ ቆሞስ አባ ሳሙኤል ገላነው

 • የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር

ከአሜሪካ፤

ቆሞስ አባ ፊልጶስ አሻግር

 • በአሜሪካ የሚችጋን ደብረ ገነት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ እና በኒውዮርክ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌል ሓላፊ

ከጀርመን፤

ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሓ

 • በጀርመን የሙኒክ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ

መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ

 • በጀርመን የበርሊን ደብረ ገነት ቅዱስ ዐማኑኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ

ከፈረንሳይ፤

መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ዘድንግል ኑርበገን

 • በፓሪስ የፈለገ ሕይወት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ናቸው፡፡

ለእነዚሁ አዲስ ተሿሚ አባቶች፡-

 • በቤተ ክርስቲያን ታሪክ
 • በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ
 • ስለ ሥርዓተ ቡራኬ እና ክህነት አሰጣጥ
 • ስለ ትምህርተ ኖሎት
 • ስለ ቤተ ክርስቲያን ቅርስ አያያዝ
 • ስለ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ
 • ስለ ማኅበራዊ ኑሮ እና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር
 • ስለ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ቃለ ዓዋዲ
 • ስለ ሥራ ፈጠራ እና አስተዳደር

ከሰኔ 19 ቀን እስከ ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ለ15 ቀናት ያህል በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና በታዋቂ ምሁራን ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ሥልጠናውን በጸሎተ ቡራኬ ሲከፍቱ ባስተላለፉት ቃለ በረከት፥ “ራሳችሁንና መንጋውን ጠብቁ” ብሎ ጌታችን በአዘዘው መሠረት፣ የአባቶቻችሁን እምነትና ሥርዓት በመጠበቅ በተሰጣችሁ ሓላፊነት የቤተ ክርስቲያናችሁን መብትና ልዕልና የማስከበር ግዴታ አለባችሁ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕድገትና ብልጽግና የሚጠብቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዚያውም መጠን የከበቧት ዘራፊዎች እና መናፍቃን ጥቂቶች አይደሉምና ያለባችሁን ሓላፊነት በርትታችሁ እንድትወጡ ጊዜው ይፈትናችኋል፤ ይጠይቃችኋል፤ ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኛው ጥቂት ነው” በተባለው መሠረት ብዙ አባቶች በሞተ ሥጋ ከዚህ ዓለም በመለየታቸው ምክንያት ክፍት የሆኑት አህጉረ ስብከት ብዙዎች ናቸው፡፡ በዚያውም ላይ ጊዜው በርትቷል፤ ተወዳዳሪው እየበዛ ሔዷል፡፡ ለሥራ ስትሠማሩ፣ ኹሉንም ታገኙታላችኹ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችሁን ለማሳደግ የልማት ሥራ መሥራት ግዴታችሁ ነው፤ ጊዜው የልማት ጊዜ ነው፤ የሰውን አእምሮ ማልማትም ይጠበቅባችኋል፤ ብለዋል፡፡

በመቀጠልም፣ ምእመናን፥ በሃይማኖት ትምህርት፣ በግብረ ገብነትና በመንፈሳዊነት እንዲጎለብቱ ማድረግ ይጠበቅባችኋል፡፡ እግዚአብሔር ከሚወዱት ሰዎች ጋር ስለኾነ የእግዚአብሔር ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ብዙ መሥራት ስለሚችል እናንተንም አብሮአችሁ ያለው እግዚአብሔር ብዙ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችላችሁ አምናለኹ፡፡ “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋራ እኖራለሁ፤” ብሎ የተናገረ እግዚአብሔር፣ ከእናንተ ጋር እንደሚኖር ጸሎቴም ምኞቴም ነው፤ በማለት ቃለ በረከት አስተላልፈዋል፡፡

እንዲሁም ለነዚሁ ተመራጮች ቆሞሳት፣ ትላንት፣ ሐምሌ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የጸሎተ አስኬማው ሥነ ሥርዓት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ተፈጽሞላቸዋል፡፡

የተሿሚ ቆሞሳት  አጭር የሕይወት ታሪከ

1) ቆሞስ (ዶ/ር) አባ ኃይለ ማርያም መለሰ

ቆሞስ (ዶር) አባ ኃይለ ማርያም መለሰ፣ ከአባታቸው ከሊቀ መዘምር መለስ አየነው ደስታ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ፀሐይ ገብረ አብ፣ በሰሜን ጎንደር ደብረ ሰላም ሎዛ ማርያም አካባቢ በ1961 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • ፊደል፥ ንባብ፥ ዳዊትና ቅዳሴ ከመርጌታ ሙሴ ብፅአጊዮርጊስ ተምረዋል።
 • ቅኔ፥ ከግጨው መንክር ምንዝሮ ተክለ ሃይማኖት፥ ሐዲሳት፥ ከመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ግምጃ ቤት ማርያም ተምረዋል።
 • 1ኛና 2ኛ ከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዐፄ ፋሲል፥ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዳግማይ ደብረ ሊባኖስ አዘዞ ተክለ ሃይማኖት ት/ቤቶች ተምረዋል።
 • ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ በቴዎሎጂ ዲፕሎማ፥
 • ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቴዎሎጂ ዲግሪ፥
 • ከኖርዌይ ስታሻንገር ስፔሻላይዝድ ዪኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪ፥
 • ከፕሪቶርያ ዩኒቨርስቲ በፍልስፍና የፒ.ኤች.ዲ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡

ቋንቋ፡-

 • ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ የኖርዌይ፥ የስዊድንና የዴንማርክ ቋንቋዎችን ይችላሉ።

መዐርገ ክህነት

 • ዲቁና – በ1968 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ እንድርያስ (ቀዳማዊ) በወቅቱ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል፤
 • ምንኵስና – በ1984 ዓ.ም. በታዋቂውና ጥንታዊው ገዳም ጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተቀብለዋል፤
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ (ኤርትራዊ) በወቅቱ የሰሜን ጎንደር ሊቀ ጳጳስ ተቀበለዋል፤
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል በወቅቱ የምዕራብ ሸዋ ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • በሆለታ ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት፥ በሆለታ ገነት ደብረ ኤዶም ቅዱስ ገብርኤል፥ በሆለታ ገነት ደብረ ሣህል መድኃኔ ዓለም፥ በወሊሶ ጻድቁ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናት በአስተዳዳሪነት ሠርተዋል።
 • የወልመራ ወረዳ ቤተ ክህነት ምክትል ሊቀ ካህናት ሆነው በቅንንነት አገልግለዋል።
 • በኖርዌይ ስታሻንገር መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የሕፃናትና ቤተሰብ መምሪያ የቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን መርተዋል።የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የቦርድ አባል፥ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የቦርድ አባል በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
 • በቤተ ክህነት ጠቅላይ ጽ/ቤት ቀደም ሲል በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሓላፊ፤
 • በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመጀመሪያ የሪሰርችና ምርምር ሓላፊና አካዳሚክ ዲን፥ ም/ዋና ዲን በመሆን አገልግሎት ሰጥተዋል፤
 • የቅድስት ልደታ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቦርድ አባል በመሆንም ሠርተዋል።
 • በዓለም አቀፍ ተሳትፎ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል፥ የመላው ኦርየንታል ኦርቶዶስ አብያተ ክርስቲያናትን በመወከል የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመሆን እየተሳተፉ ይገኛሉ።
 • በአሁኑ ጊዜ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው በቅንነት በማገልገል ላይ ናቸው። በትርፍ ጊዜአቸውም በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የድኅረ ምረቃ ደቀ መዛሙርትን እያስተማሩ ይገኛሉ።

«በጎ ነገር የሆነው ሁሉ ያለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ፍጻሜ ሊያገኝ አይችልም» ተብሎ በተጻፈው መሠረት፣ ምንም እንኳን ሁሉም ተመራጮች ቆሞሳት፣ ከዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸው ጋር የድምፅ ብልጫ በማግኘት ሊመረጡ የቻሉት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ መሆኑ ቢታመንበትም ቅሉ፣ ቆሞስ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ ግን ከእጩ ተወዳዳሪያቸው ጋር እኩል ድምፅ አግኝተው እርሳቸው የተመረጡት በዕጣ ስለሆነ፣ በእርሳቸው ምርጫ በይበልጥ እደ መንፈስ ቅዱስ እንዳለበት ለማወቅ ተችሏል።

በአጠቃላይ ቆሞስ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ፣ በተግባር እንደሚስተዋሉት፣ ከመንፈሳውያን አባቶች የሚጠበቀውን ማስተዋልን፥ መረጋጋትንና ትዕግሥትን የተላበሱ ኹለገብ አባት በመኾናቸው የአኹኒቱን ቤተ ክርስቲያን ለመምራት ብቃት ያላቸውና መመረጥ የሚገባቸው ዓለም አቀፍ አባት ናቸው።

2) ሊቀ ሊቃውንት ቆሞስ አባ ዘርዐ ዳዊት ኃይለ ሥላሴ

ሊቀ ሊቃውንት አባ ዘርዐ ዳዊት ኃይለ ሥላሴ፣ ከአባታቸው ከአቶ ኃይለ ሥላሴ ደስታና ከእናታቸው ከወ/ሮ አብረኸት ልጅዓለም በሽሬ አውራጃ በላዕላይ አድያቦ ወረዳ በዓዲ ንግሥቱ አጥቢያ በአቡነ ይባርከነ ቤተ ክርስቲያን (ደብር) በ1953 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • በተወለዱበት ደብር የኔታ ገብረ ሥላሴ ከተባሉት መምህር ከዘወትር ጸሎት እስከ መልክአ ኢየሱስ የቃል ትምህርት የተማሩ ሲሆን፣ በቀን ትምህርታቸውም መዝሙረ ዳዊትን አንብበዋል።
 • 1968 ዓ.ም. በ15 ዓመት ዕድሜያቸው በሽሬ አውራጃ በፅንብላ ወረዳ በሚገኘው ታላቁና ታዋቂው ገዳም ደብረ አባይ ገብተው ቅዳሴ፥ ሰዓታት፥ የቅዱስ ወንጌል እና ጳውሎስ ንባብን አጠናቀዋል።
 • ከዚያ በኋላ በገዳሙ ሥርዓት መሠረት፣ ለ3 ዓመታት ያህል በገዳሙ ረድእ ሆነው እያገለገሉ እያሉ በትርፍ ጊዜያቸው ከየኔታ የኋላእሸት ጉባኤ ት/ቤት ከነበሩት ከታዋቂውና ባሕታዊ ከሆኑት የኔታ ቄሰ ገበዝ ገብረ ሊባኖስ ዘውዴ መዝገበ ቅዳሴ ተምረዋል።
 • በማኅበሩ ፈቃድ ለትምህርት ወደ በጌምድር ስሜን ወይም ራስ ዳሽን ሒደው፣ መጀመሪያ የኔታ ዘፈረ ብርሃን ከተባሉ የቅኔ መምህር እስከ ዋዜማ ደረሱ።
 • በዚያው ሀገር በኪሮስ አውራጃ በማቆላ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ከነበሩት የኔታ ገብረ ዋሕድ ከሚባሉት የቅኔ መምህር ከሁለት ዓመት በላይ ቅኔ ከነአገባቡ ተምረዋል።
 • የኔታ ዕዝራ ከሚባሉ የአቋቋም መምህር አቋቋምን ሞክረው ወደ ደብረ ዐባይ ገዳም ተመልሰው የጀመሩትን የመዝገበ ቅዳሴ ትምህርት በሚገባ ተምረው ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ጎን ለጎንም መዝሙረ ዳዊትን ተምረዋል።
 • በወቅቱ አስተማሪያቸው የነበሩት የኔታ ቄሰ ገበዝ ገብረ ሊባኖስ፥ “ጉባኤውን አንተ ልትረከበው ስለምትችል ልምምድ ማድረግ አለብህ፤” ብለዋቸው፣ በማታም፥ በቀንም አጋዥ መምህር ሆነው አስተምረዋል።
 • በደብረ አባይ በነበሩባቸው ብዙ ዓመታት ከየኔታ ቄሰ ገበዝ ገብረ ሊባኖስ ምሥጢረ ሃይማኖት፥ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፥ ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊትን ተምረዋል።
 • ከብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ የሃይማኖተ አበውን ትርጓሜ ተምረዋል። በመቀሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በመዝገበ ቅዳሴ መምህርነት የሠሩ ሲሆን፣ የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ ከተባሉ መምህር በትርፍ ጊዜያቸው የመጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜን ተምረዋል።
 • በግሪክ ቋንቋ በቲኦሎጂ በዲግሪ ተመርቀዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና – በ1967 ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዘኵሎን አድያማተ ትግራይ ተቀብለዋል።
 • ምንኵስና – በ1975 ዓ.ም. በሥርዓተ ገዳም መሠረት ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • በደብረ አባይ ገዳም ቆይታቸው በዕቃ ቤትነት፥ በሊቀ አርድእትነት፥ በቀዳሽነት፥ በአጣኝነት፥ በሰዓታት ቋሚነት፥ በወዲ መጋቢነት አገልግለዋል።
 • በዚሁ ሥራ ላይ እያሉም ቁም ጸሐፊ ስለነበሩ ብራና እየፋቁ፥ ቀለም እየበጠበጡ ለገዳማቸው፥ ለዋልድባና በአካባቢው ላሉ ገዳማትና አድባራት በርካታ የብራና መጻሕፍትን ጽፈው አበርክተዋል። ለመጥቀስ ያህልም ለደብረ አባይ የመንፈቅ ግጻዌና ጸሎተ ዕጣን፥ ለደብረ በንኮል ለፃዕዳ እንባ ገዳም የብራና ቅዳሴ ጽፈው አበርክተዋል።
 • በማኅበሩ ፈቃድ በአስገዳ ወረዳ የምትገኘው ማይደሙ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ዓመታት መዝገበ ቅዳሴን አስተምረዋል።
 • ወደ ቤተ ማርያም ገዳም ተልከውም አበምኔት በመሆን መዝገበ ቅዳሴንም ጭምር እያስተማሩ ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል።
 • ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ ደብረ አባይን ሊጎበኙ በመጡበት ጊዜ ሲመለሱ ማኅበሩን አስፈቅደው ወደ መቀሌ ይዘዋቸው በመምጣት መቀሌ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሆነው መዝገበ ቅዳሴ እንዲያስተምሩ ፈቀዱላቸው። ከዚያም የብፁዕነታቸው አቡነ ቀሲስ ሆነው እንዲሠሩ ተመድበው አገልግለዋል።
 • በሽሬ አውራጃ ቤተ ክህነት በሽራሮ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ሆነው ቅዳሴ እያስተማሩ በወረዳው ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እየዞሩ እንዲሰብኩ ተመድበው ያገለገሉ ሲሆን ቆይተውም በምፅብላ ወረዳ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት እየተዘዋወሩ አስተምረዋል።
 • በሽሬ አውራጃ የነበራቸውን አገልግሎት ጨርሰው ወደ መቀሌ በመምጣት በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ፈቃድ የመጀመሪያ የሆነውን የእልቅና ሥራቸውን ኮረም አፍላ ወረዳ የደብረ ገነት ኃያሎ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የቅዳሴ መምህር በመሆን አገልግለዋል።
 • ወደ አዲስ አበባ መጥተው በብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ አቅራቢነት ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ጋር ተዋወቁ። ቅዱስነታቸውም እንዲህ ያለ ምስክርነት ያውም በአቡነ መርሐ ክርስቶስ፤ የሚገርም ነው! ብለው አድንቀው በጥቂት ቀናት ቆይታ ወደ ደብረ ዘይት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን እልቅና ሾመው ልከዋቸው ለአንድ ዓመት አገልግለዋል።
 • በናዝሬት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንም ለአንድ ዓመት እንዳገለገሉ የደብረ ዘይት ቅዱስ ሩፋኤል ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ካህናት፥ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የይመለሱልን ጥያቄ በማቅረባቸው እንደገና ወደ ቦታው ተመልሰው ግሪክ ሀገር እስከሄዱበት ጊዜ ድረስ በፍቅርና በስምምነት እንዲሁም ከጥሩ የልማት ሥራ ጋር አገልግሎታቸውን አበርክተዋል። ከደብሩም የምስክር ወረቀት አግኝተው በፍቅር ተሸኝተዋል።
 • በግሪክ ሀገር የሰባት ዓመታት ቆይታቸውም በምክሐ ደናግል ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን፤
 • በ1998 ዓ.ም. የቦሌ መድኃኔ ዓለም ካቴድራል አስተዳዳሪ በመሆን (4 ዓመት)፥
 • በ2003 ዓ.ም. የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን (6 ወር)፥
 • በ2004 ዓ.ም. የማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን (1 ዓመት)፥

ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ እስከአሁን የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በብቃትና በጥራት ሰፊ አገልግሎት የሰጡ አባት ናቸው፡፡

3) መልአከ ብርሃናት ቆሞስ አባ ኄኖክ ተክለ ጊዮርጊስ

መልአከ ብርሃናት አባ ኄኖክ ተክለ ጊዮርጊስ በቀድሞ ከንባታና ሐድያ ዞን ከአባታቸው ከአቶ ግዛው ደምሴና ከእናታቸው ከወ/ሮ በላይነሽ መንገሻ በ1973 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፤

 • ከፊደል ጀምሮ መንፈሳዊና ዘመናዊ ትምህርታቸውን በሆሣዕና ከተማ ተከታትለዋል።
 • የቃል ትምህርትና ጾመ ድጓ ከመምህር ሥልጣኑ ብቸና ወረዳ ዘቦች ኢየሱስ ቀበሌ ተምረዋል።
 • ቅኔ ከየኔታ መርሐ ጽድቅ ደጀን ጊዮርጊስና ከየኔታ አንዳርጋቸው ብቸና ወረዳ ተምረዋል።
 • መዝገበ ቅዳሴ አንቀጽ ከነይትበሀሉና ባሕረ ሐሳብ ከየኔታ ናሁሠናይ ጎንደር ደብረ ኃይል በዓታ ተምረዋል።
 • ቅዳሴ በታላቁ ደብረ አባይ አቡነ ሳሙኤል ገዳም በሚገባ በመከታተል በቅዳሴ መምህርነት ተመርቀዋል።
 • በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሲማሩ ቆይተው በነገረ መለኮት በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ የኮሌጅ ትምህርታቸውን ወደ ዲግሪ ለማሳደግ በዚያው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በዲግሪ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና – ከቀድሞው የሸዋ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በ1981 ዓ.ም.
 • ምንኩስና – ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በምሁር ገዳመ ኢየሱስ በ1991 ዓ.ም.
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በ1992 ዓ.ም.
 • ቁምስና – በ2000 ዓ.ም. ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞችና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሰባኬ ወንጌልነትና በቀዳሽነት አገልግለዋል።
 • በአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ሥር ባሉ አድባራትና ገዳማት እንዲሁም በውጭ ሀገር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በመመደብ በአስተዳዳሪነት በመሥራት፥ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት፥ ልማትን በማልማትና ምእመናን በማስተባበር ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉና ውጤት ያስመዘገቡ አባት ናቸው።
 • ከመስከረም 2000 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር 2003 ዓ.ም. ድረስ በሰሜን ሸዋ ሀገረ ሰብከት የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፥
 • ከጥር 1 ቀን 2003 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. የጅቡቲ ምሥራቀ ፀሓይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፥
 • ከግንቦት 1 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ በሰፈረ ገነት (ጦር ኃይሎች) ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፥
 • ከሐምሌ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ በመካኒሳ ምዕራፈ ጻድቃን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፥

ከነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን በመካኒሳ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል በአስተዳዳሪነት ተመድበው በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተግባራትን ያከናወኑ ሲኾን፤ ከዕድሜአቸው አንጻር ወደፊትም ብዙ የሥራ ውጤት የሚጠበቅባቸው ባለራእይ አባት ናቸው።

4) መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ወልደ መድኅን ተክለ ብርሃን

መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ወልደ መድኅን ተክለ ብርሃን ከአባታቸው ከሊቀመንበር ዘውዴ ተፈራና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጫልቱ ኮርሜ በኢሉና ኢጉ ኩራ ቀ/ገ/ማኅበር በውጫሌ ወረዳ በሰላሌ አውራጃ ልዩ ስሙ ሸቦ ወይም ሮብ ገበያ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በ1963 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • ከግእዝ ፊደል ቆጠራ እስከ ሙሉ ንባብ ከታላቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው ከ1972-1975 ዓ.ም. ከመምህር ኢያሱ አሰፋ ዘንድ ተምረዋል።
 • ውዳሴ ማርያም፥ ምዕራፍና ጾመ ድጓ ከመምህር መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል ከ1975-1978 ዓ.ም. ተምረዋል።
 • ሰዓታትና መዝገበ ቅዳሴ ከመመህር ነቅዐጥበብ ደምሴ በደብረ ሊባኖስ ገዳም በአስተማሪነት ደረጃ ተምረው ተመርቀዋል።
 • ሰምና ወርቅ ሙሉ ቤት ቅኔ ከመምህር ክንፈ ሚካኤል ከ1982-1984 ዓ.ም. ተምረዋል።
 • ሰምና ወርቅ ሙሉ ቤት ቅኔ ከመምህር ክንፈ ገብርኤል ከ1984-1985 ዓ.ም. ተምረዋል።
 • የጎዳና ሙሉ ቤት ቅኔ ከመምህር ምሕረተ ሥላሴ ደሳለኝ ከ1985-1986 ዓ.ም. በመማር አጠናቀዋል።
 • የብሉይ ኪዳን ትርጓሜና የ4ቱ ወንጌላውያን ትርጓሜ፥ ፍትሐ ነገሥትና ሃይማኖተ አበው በአንድምታ ትርጓሜ በመምህር ገብረ ኢየሱስ ስም በተመሠረተው የብሉያትና ሐዲሳት ትምህርት ቤት ተምረዋል። እንዲሁም የሊቃውንት ጉባኤ ቤት በመግባት ከመምህር ጥበቡ አስናቀ ዘንድ ተምረዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና – ከብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በ1982 ዓ.ም.
 • ምንኩስና – በደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ በ2001 ዓ.ም. ነሐሴ 24 ቀን፤
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ በ2002 ዓ.ም. መስከረም 24 ቀን፤
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በ2007 ዓ.ም. ሚያዝያ 21 ቀን ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • ከ1996 ዓ.ም. እስከ የካቲት 11 ቀን 2001 ዓ.ም. በለገጣፎ ምስካበ ቅዱሳን አቡነ ኪሮስ ቤተ ክርስቲያን ሰባኬ ወንጌልና የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መምህር፥
 • የካቲት 12 ቀን 2001 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ በሽንቁሩ ደብረ መድኃኒት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በስብከተ ወንጌልና ቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ መምህር፥
 • ከመስከረም 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በሱሉልታ ደብረ ምሕረት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፥
 • ከጥር 9 ቀን 2005 ዓ.ም. እስከ የካቲት 10 ቀን 2005 ዓ.ም. የቦሌ ለሚ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፥

ከየካቲት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የእንጦጦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል እና ነቢዩ ቅዱስ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን ሰፊ አገልግሎት ያበረከቱ ትጉህና ለተልእኮ የሚፋጠኑ ምሁር አባት ናቸው።

5) መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ኃይሉ

መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ገብረ እግዚአብሔር ኃይሉ ከአባታቸው ከአቶ ኃይሉ ማሩና ከእናታቸው ከወ/ሮ ብርሃን ካሕሳይ በትግራይ ክልል ውቅሮ ክልኤተ አውላዕሎ በ1955 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • የደብረ አባይ ቅዳሴን ከመምህር አባ ገብረ እግዚአብሔር እንዳባገሪማ ገዳም ተምረዋል።
 • ቅኔ ከመምህር ፍስሐ ወልደ ማርያምና ከመምህር ፍስሐ ገብረ ማርያም፤ ቅኔ ከነአገባቡ ከቀኝ ጌታ መጽሔት ደሴ ተምረዋል።
 • አቋቋምና ዜማን ከመምህር ዐይነኩሉ ትግራይ ቀስመዋል።
 • መጻሕፍተ ሐዲሳትን፥ ሊቃውንትን፥ ፍትሐ ነገሥትን፥ ዳዊትን፥ ኢሳይያስን፥ ባሕረ ሐሳብን በሙሉ ከመምህር ገብረ ሕይወት ሰይፈ በደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ተምረዋል አጠናቀዋል።
 • ዘመናዊ ትምህርትም እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን በደሴ ተከታትለዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና – ከአቡነ ዮሐንስ ቀዳማዊ ተቀብለዋል።
 • ምንኵስና – በዘቡል ኪዳነ ምሕረት በ1988 ዓ.ም. ተቀብለዋል።
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ የደቡብ ወሎ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ በ1988 ዓ.ም. ተቀብለዋል።
 • ቁምስና ከብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ በ1995 ዓ.ም. ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • በመጽሐፍ መምህርነት ደሴ 4 ዓመት በመምህርነት አገልግለዋል፤
 • እንዲሁም በመቐለ ለ9 ዓመታት በመጽሐፍ መምህርነት በማገልገል ብዙ ደቀ መዛሙርትን አፍርተዋል።

የመቀሌ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ገዳም፥ የኪዳነ ምሕረትና የልደታ ለማርያም አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ በመሆን በርካታ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተግባራትን ያከናወኑ መንፈሳዊ ምሁር አባት ናቸው።

6) አባ ኃይለ ሚካኤል ወልደ አምላክ

አባ ኃይለ ሚካኤል ወልደ አምላክ ከአቶ ወልደ አምላክ ሁንዴና ከወ/ሮ በላይነሽ በዲየ በሸዋ ክፍለ ሀገር በፍቼ ዞን በሙካጡሪ ወረዳ በበቾ ፋኔሊ ቀበሌ ልዩ ስሙ ደሴ በሚባል ቦታ በ1960 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • በደብረ ሊባኖስ ገዳም ካሉት ትምህርት ቤቶች ታላቅና አንጋፋ ከሆኑ መምህር ገብረ ማርያም ንባብ ቤት በመግባት በትጋት ተምረዋል።
 • በደብረ ጽጌ ገዳም ከመምህር ልዑል ቅዳሴ ትምህርት ቤት ገብተው ግብረ ዲቁና ተምረዋል።
 • ከየኔታ መርዓዊ ዜና ትምህርት ቤት ገብተው ጾመ ድጓና ድጓ ከቃል ትምህርት፥ ከውዳሴ ማርያም ጀምረው እስከ ዐቢይ ምዕራፍ ያለውን አጠናቅቀው ተምረዋል።
 • መምህር ወልደ ገብርኤል ት/ቤት ገብተው ዝማሬና መዋሥዕትን በሚገባ ተምረው ተማሪ እያስቀጸሉ ቆይተዋል።
 • ከአቋቋሙ መምህር ከየኔታ በትረ ማርያም ዘንድ ገብተው ክብረ በዓል፥ መዝሙርና አርባዕት፥ ወርኃ በዓልና መኃትው፥ ስብሐተ ነግህና ኪዳን ሰላም፥ ቅናዋትና አርያም፥ እንደገና ዝማሬና መዋሥዕትን ተምረዋል።
 • ከመምህር ምሕረተ ሥላሴ ቅኔ ትምህርት ቤት ገብተው ቅኔ ተቀኝተዋል።
 • በድጋሚ ከመምህር አምዴ ዘንድ ገብተው ለሁለተኛ ጊዜ ቅኔ ተቀኝተው አገባቡን ቀጽለዋል።
 • በደብረ ሊባኖስ ገዳም በመምህር ገብረ ኢየሱስ ስም በተቋቋመው የብሉያትና የሐዲሳት ትርጓሜ አዳሪ መንፈሳዊ ት/ቤት በብሉይ ክፍል ገብተው ስምንት ዓመት ተምረዋል።
 • በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መልካም ፈቃድ በብሉይ ክፍል ምክትል መምህር ሆነው እያስተማሩ ሐዲስ ተምረዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁን – በደብረ ጽጌ ገዳም ተቀብለዋል።
 • ምንኩስና 1996 ታኅሣሥ 24 ቀን በደብረ ሊባኖስ ገዳም፤
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ ዮሴፍ በ1977 ዓ.ም. ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • በነበሩበት የብሉይ ትምህርት ምክትልነቱን ሥራ ሳይለቁ በፍቼ ሀገረ ስብከት በስብከተ ወንጌልና በትምህርት ክፍል ኃላፊነት አገልግለዋል።
 • ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲያስተምሩ በመታጨታቸው ይህንን የሰሙ የደብረ ሊባኖስ የገዳሙ አባቶችና ተማሪዎች ለገዳሙ አቤቱታ አቅርበው ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ያንጊዜ የገዳሙ ጸባቴ ነበሩና ለቅዱስነታቸው አመልክተው በቅዱስነ ታቸው መልካም ፈቃድ ወደ ገዳሙ ተመልሰው በመምሕራቸው በመምህር ጥበቡ አስናቀ እግር ተተክተው ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ በዋና መምህርነት አስተምረዋል።

በተጨማሪ በገዳሙ ካሉት የአብነት ት/ቤቶች ለተውጣጡ ዲያቆናት፥ ቀሳውስት፥ መነኮሳት፥ መዘምራን ከ300 ላላነሱ ደቀ መዛሙርት፦ ሥነ ፍጥረት፥ አምስቱን አዕማደ ምሥጢር፥ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፥ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስተማር ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረጉ ምሁር እና ግሑስ አባት ናቸው።

7) ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ዕንቈ ባሕርይ

ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ዕንቈባሕርይ ከአባታቸው ከመሪጌታ ዕንቈ ባሕርይ ወልዱና ከእናታቸው ከወ/ሮ አዳኑ ገብሩ በዋግኽምራ ዞን በሰቆጣ ከተማ ዙሪያ ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ከሚባለው ቦታ ሰኔ 3 ቀን 1968 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • ከፊደል ጀምሮ እስከ ጾመ ድጓና ሠለስት ድረስ በአባታቸው በመሪጌታ ዕንቈባሕርይ አስተማሪነት ተምረዋል።
 • ቅኔን ከመምህር ይትባረክ አባተ በጋዝጊብላ ወረዳ ጻድቅ ማርያም በመሄድ ተምረዋል።
 • ለሁለተኛ ጊዜ የቅኔን ትምህርት እስከነአገባቡ በሰቆጣ ወረዳ በሐሙሲት ዙሪያ በአድልባድል ሳሙኤል ከሚገኙት ከመምህር ይትባረክ ተቀኝተዋል።
 • ጾመ ድጓና ምዕራፍ ከመምህር ተስፋው ኤልሳዕ በራያ ቆቦ ወረዳ በመሀጎ ቅድስት ማርያም ተምረዋል።
 • የአቋቋም ትምህርት ከመምህር ሞገስ ካሳዬ በሰቆጣ ወረዳ ወለህ ዝቋልሽመን ሳሙኤል ቀስመዋል።
 • ዝማሬ መዋሥዕትን ከመምህር ነቅዐጥበብ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ሰብከት በእስቴ ወረዳ የማታ ጊዮርጊስ ተከታትለው ካጠናቀቁ በኋላ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ሰብከት በላይ ጋይንት በምትገኘው ዙርአባ አቡነ አረጋዊ ጽርሐ አርያም ገዳም በዝማሬ መዋሥዕት መምህርነት ተመርቀዋል።
 • የድጓ ትምህርትን ከመምህር ክነፈ ርግብ በሰሜን ወሎ ሀገረ ሰብከት በወድልድያ ደብረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል በሚገባ ተከታትለው ካጠናቀቁ በኋላ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ሰብከት በታች ጋይንት በምትገኘው የድጓ ማሳመስከሪያ በሆነችው በቅድስት ቤተ ልሔም በድጓ መምህርነት ተመርቀዋል።
 • በባሕር ዳር ከተማ ጉርድማ ገብርኤል ከሚገኙት የቅኔ መምህር ከመምህር ይትባረክ አካሉ በቅኔ መምህርነት ተመርቀዋል።
 • በብፁዕ አባታችን አቡነ ቄርሎስ ፈቃድ ወደ ታላቁ ገዳም ቅዱስ ላሊበላ በመምጣት ለአራት ዓመት ያህል የሐዲስ ኪዳን አንድምታ ትርጓሜን ትምህርትን አጠናቅቀዋል። በመቀጠልም ለአራት ዓመት ያህል ከብሉይ አንድምታ ትርጓሜ የ8ቱን ብሔረ ኦሪት ትርጓሜ፥ የነገሥትን ትርጓሜ፥ የዳዊትን ትርጓሜና የኢሳይያስ ትርጓሜን ተምረው ተመርቀዋል።
 • ዘመናዊ ትምህርትንም በተመለከተ የ10ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና ወስደዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ሥርዓተ ምንኵስናን በመፈጸም ቅስናንና ተቀብለዋል።
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የሰሜን ወሎና የዋግኽምራ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ የቅዱስ ላሊበላ ገዳም የበላይ ጠባቂ ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • በብፁዕ አባታችን አቡነ ቄርሎስ መልካም ፈቃድ በሰቆጣ ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ለአምስት ዓመት በመምህርነት እያገለገሉ ብዙ ደቀ መዛሙርትን በማስተማር ለቤተ ክርስቲያን አበርክተዋል።

በሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ተመድበው ሲያስተምሩ የነበሩት መምህር አእምሮ ደምሴ ቦታ ሲቀይሩ በብፁዕ አባታችን አቡነ ቄርሎስ መልካም ፈቃድ በታላቁ የላሊበላ ገዳም በሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ ትምህርት በመምህርነት ተመድበው እያስተማሩ የቆዩ መንፈሳዊ ምሁር አባት ናቸው፡፡

8) መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ዮሐንስ ገብረ ሥላሴ

መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ዮሐንስ ገብረ ሥላሴ ከአባታቸው ከቀኝ ጌታ ገብረ ሥላሴና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሽታዬ አስፋው ታኅሣሥ 3 ቀን 1967 ዓ.ም. ወላይታ ሶዶ ደብረ መንክራት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ከሚባለው ቦታ ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • ከፊደል ጀምሮ ንባብ፥ ዳዊት፥ ዜማ፥ ጾመ ድጓ፥ ምዕራፍ፥ አቋቋም፥ ዝማሬ መዋሥዕት ከአባታቸው ከቀኝ ጌታ ገብረ ሥላሴ ተምረዋል።
 • በወቅቱ የገዳሙ የቅዳሴ መምህር ከነበሩት ከአባ ተክለ አብ ቅዳሴና ሰዓታት ቀጽለዋል።
 • ትምህርታቸውን ለማጠናከር ወደ ሰሜኑ ክፍለ ሀገር በመሔድ በምሥራቅ ጎጃም ደብረ ኤልያስ አቋቋም፥ በደብረ ሊባኖስ ገዳም አቋቋምና ዝማሬ መዋሥዕት ተምረዋል።
 • በአዲስ ዓለም ማርያም ገዳም ቅኔ፥ በመርጡለ ማርያም ገዳም ቅኔ፥ በገዳመ አስቄጥስ ቅዳሴና ሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ፥ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ ተምረዋል።
 • ወደ ደብረ ጽጌ ገዳም በመመለስ ቀደም ሲል የጀመሩትን ቅዳሴንና ዝማሬ መዋሥዕትን በሚገባ በመማር ለመምህርነት በቅተዋል።
 • ዘመናዊ ትምህርትን በተመለከተም፣ በተወለዱበት በወላይታ አካባቢ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትግል ፍሬ፥ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጐላ ሶዶ በር፥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሊጋባ በየነ ትምህርት ቤቶች ካጠናቀቁ በኋላ ባገኙት ውጤት ወደ አዋሳ መምህራን ማሠልጠኛ በመግባት በመምህርነት ተመርቀው በወላይታ ዞን ውስጥ በሚገኘው በአበላ ቀበሌ ለተወሰነ ጊዜ ከአገለገሉ በኋላ የትምህርት ውጤታቸውን ከፍ በማድረግ በማሻሻል ወደ ኮሌጅ ገብተው የአስተዳደር ትምህርት በመማር በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ምንኵስና – በገዳመ አስቄጥስ
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ ኤፍሬም
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • የደልቦ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፥
 • የደብረ መንክራት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም አበምኔት፥
 • የደብረ ፀሓይ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በመሆን በሰላምና በፍቅር ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
 • በገዳሙ የመነኰሳዪያትን አንድነት መሥርተው መናንያን ከበአታቸው እንዳይፈናቀሉ የከብት ርባታ፥ የሽመና፥ የዳቦ ማሽን፥ የተለያዩ በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የጓሮ አትክልቶችን ለርእሰ ከተማዋ ሕዝብ ለሽያጭ እንዲያቀርቡ በማድረግ ለገዳሙ ከፍተኛ ገቢ አስገኝተዋል።
 • ከ1ኛ-6ኛ ክፍል ያለው የዘመናዊ ትምህርት ቤት እንዲከፈት አድርገዋል።
 • በየደብሩ የአባቶች መንፈሳዊ ማኅበር፥ የእናቶች መንፈሳዊ ማኅበር አቋቁመዋል። የስብከተ ወንጌል ሥራ እንዲስፋፋ አድርገዋል።
 • በየአጥቢያው፥ በየአካባቢው ቋንቋ በማስተማር የሰበካ ጉባኤ እንዲጠና ከር የስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ ይበልጥ እንዲደራጅ አድርገዋል።
 • በየቦታው ራስ አገዝ ልማት እንዲስፋፋ ብርቱ ጥረት አድርገዋል።
 • ያለአግባብ የተወሰዱ የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታዎች እንዲመለሱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በሰላምና በፍቅር በመነጋገር፥ በመጠየቅና በመከታተል እንዲከበሩ አድርገዋል።
 • የአብነት መምህራንን በማምጣት እንዲያስተምሩና ተተኪ ደቀ መዛ ሙርትን እንዲያፈሩ አድርገዋል።
 • በርካታ የስብከተ ወንጌል ኬላዎች አቋቁመዋል።
 • በገዳማትና አድባራት ያሉ ቅርሶች እንዲጠበቁ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሠርተዋል።
 • ከምንጊዜም በላይ ገቢ ከፍ እንዲልና የገቢው ገንዘብ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል አድርገዋል።
 • ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ወጣቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት ልዩ ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ ስለ ሰንበት ት/ቤት በየደረጃው ያሉ አመራሮች ግንዛቤ እንዲጨብጡና በማንኛውም ነገር ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥረዋል።
 • የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ እንዳይበረዝና እንዳይሸረሸር ክትትል አድርገዋል።
 • ችግሮች ሲፈጠሩ በአስቸኳይ ውለው ሳያድሩ በጥንቃቄ በመመርመር ውሳኔ በመስጠት በሰላምና በፍቅር እንዲፈቱ ጥረዋል።
 • ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለሕፃናት፥ ለነፍሰጡር እናቶች፥ ለአካል ጉዳተኞች፥ ጠዋሪ ቀባሪ ላጡ ወላጅ የሌላቸው ሕፃናት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር አድርገዋል።

በአጠቃላይ ከሚመለከታቸው ከሥራ አጋሮቻቸው ምእመናንና ከማኅ በረ ካህናት፥ ከሰንበት ት/ቤቶች ወጣቶች፥ ከአካባቢው የመንግሥት አካላት ጋር ከቀበሌ እስከ ዞን ለበርካታ ዓመታት በሰላምና በፍቅር በማገልገል ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን፣ ለሀገርና ለወገን የላቀ ድርሻ ያበረከቱና ጊዜውን ለመዋጀት የሚችሉ ኹለት ዓይና አባት በመኾናቸው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ በድምፅ ብልጫ ለሢመተ ጵጵስና መርጧቸዋል።

9) መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ወልደ ሐና ጸጋው

መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ወልደ ሐና ጸጋው፣ ከአባታቸው ከቄስ ጸጋው አማኑና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጥሩ ሐረግ በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ሰብከት በወንበር ማርያም መስከረም 2 ቀን 1949 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • ንባብና መዝሙረ ዳዊትን ከመምህር አይተነው ተክሌ በየስበት ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ተምረዋል።
 • ፀዋትወ ዜማን ከመምህር አምሳሉ ውቤ በደብረ መንክራት ውሽ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተምረዋል።
 • ቅኔ ከነአገባቡና ይትበሃሉ ከመምህር በላይ ፊላታዎስ በማቻከል ወረዳ በደብረ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ተምረዋል።
 • አቋቋም ከመምህር ኃይለ ጽዮን በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት በወንበርማ አውራጃ፥ በሻንዲ ወረዳ በአጢማር ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቀስመዋል።
 • የቅዳሴ ዜማን ከመምህር ገብረ ጻድቅ በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት በቆላ ደጋ ዳሞት ወረዳ በርቀኝ ጽዮን በተባለ ቤተ ክርስቲያን ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል።
 • የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን፥ የውዳሴ ማርያም፥ የቅዳሴ ማርያም፥ የኪዳንና የትምህርተ ኅቡኣት አንድምታ ትርጓሜን በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ ከመምህር ብርሃኑ ወልደ ሥላሴና በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የዐራቱ ጉባኤያት መምህር ከሆኑት ከመልአከ ገነት ገብረ ሥላሴ አወቀ ተምረዋል።
 • ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው፣ የመጻሕፍተ ብሉያትን አንድምታ ትርጓሜ፥ የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ፥ የመጻሕፍተ ሊቃውንትና የመጻሕፍተ መነኮሳት አንድምታ ትርጓሜን የዐራቱ ጉባኤያት ሊቅ ከነበሩት ከመልአከ ገነት ገብረ ሥላሴ አወቀ ተምረው በመምህርነት ተመርቀዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና – ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ በ1963 ዓ.ም. በደብረ ማርቆስ
 • ምንኵስና – በታላቁ የደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም በ1975 ዓ.ም.፤
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በ1977 ዓ.ም. በደብረ ማርቆስ
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ቶማስ በ1990 ዓ.ም. ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • በታላቁ የደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ለ22 ዓመታት በተለያዩ አገልግሎቶች ማለትም፦ በረድእነት፥ በቀዳሽነት፥ በገዳሙ ሒሳብ ሹምነት፥ በገዳሙ ዕቃ ግዥ ክፍል ኃላፊነት፥ በመጋቢነት ገዳሙን አገልግለዋል።
 • በ1995 ዓ.ም. ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ከተመረቁ በኋላ በጅማ ከተማ የደብረ መዊእ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና የፍኖተ ብርሃን ካህናት ማሠልጠኛ የዶግማ መምህር በመሆን አገልግለዋል።
 • የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ሀገረ ስብከት ሰባኬ ወንጌል በመሆን ሠርተዋል።
 • በሐዋሳ ከተማ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪና የካህናት ማሠልጠኛው የዶግማ መምህር በመሆን አገልግለዋል።

በባሕር ዳር ከተማ የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም አስተዳዳሪ ሆነው ሰፊ የልማት ሥራ አከናውነዋል። በአሁኑ ወቅት በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሆነው በማገልገል በተማሩት ትምህርት ያስተማረቻቸውን ቤተ ክርስቲያን በትጋትና በቅንነት በመርዳት ላይ የሚገኙ ምሁር አባት ናቸው።

10) መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ

መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ ከአባታቸው ከአቶ ንጉሤ አሳየ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ዐሥራት አብርሃ በኢሉ አባቦራ ዞን በመቱ ከተማ በ1962 ዓ.ም. ተወለዱ። አባታቸው በአንድ ዓመት ዕድሜያቸው ስለሞቱ፣ እናታቸው ከአምስት ልጆቻቸው ጋር ወደ አሜሪካ ሲሔዱ እርሳቸው ከቤተሰቦቻቸው ጠፍተው አሜሪካን በመተው ወደ መቱ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንና ወደ መቱ ሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ገብተዋል።

ትምህርት፡

 • በመቱ ቅዱስ ገብርኤል ለግብረ ዲቁና የሚያበቃውን ንባብ፥ ውዳሴ ማርያም፥ ዳዊት፥ ሥርዓተ ቅዳሴ ተምረዋል፡፡
 • ከሊቀ ሥልጣናት አባ ገብረ ማርያም ፈለቀ (በኋላ አቡነ ፊልጶስ) መንበረ ጵጵስና በመግባት ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ትርጕም፥ ሦስቱን መጻሕፍተ መነኮሳት፥ የግዕዝ ቋንቋ፥ ሰዓታት፥ መዝገበ ቅዳሴ ከየኔታ ጥበቡ በለጠ እና ከአባ ወልደ ገብርኤል ዜና ተምረዋል።
 • በመቱ ካህናት ማሠልጠኛ በተደጋጋሚ ለ1 ዓመት ኮርስ ወስደዋል።
 • በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የ6 ወር ኮርስ ወስደዋል።
 • ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በነገረ መለኮት (ቲኦሎጂ) ተመርቀዋል።
 • ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመሔድ በአሁኑ ሰዓት በጎላ ሚካኤል የመጻ ሕፍት መምህር ከሆኑት ከአባ ተስፋዬ፡- ሊጦን ኪዳን፥ መስተብቁዕ ለክህነት አገልግሎት የሚያበቁትን ትምህርት ተምረዋል።
 • የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመቱ ቅዱስ ገብርኤል ከ1-6 ተምረዋል።
 • የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን፣ ከ7-8 በአቡነ ጴጥሮስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል።
 • የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከ9-12 በመቱ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረው አጠናቀዋል።
 • በBook keeping፥ በኤኮኖሚክስ፥ በኮሜርሻል ማትስ ተመርቀዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና- ከብፁዕ አቡነ አረጋዊ ተቀብለዋል።
 • ምንኩስና – በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ፣ የመጀመሪያው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መናኝ በመሆን በደብረ ሊባኖስ ገዳም  ተቀብለዋል።
 • ቅስና – በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ተቀብለዋል።
 • ቁምስና – በተወለዱበት በኢሉ አባቦራ ከብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • በመቱ ከተማ በሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሊቀ ዲያቆናት በመሆን አገልግለዋል።
 • በኢሉ አባቦራ፥ በዳሪሙ፥ በሱጴ፥ በአልጌሳቾ የወረዳ ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት፥ ሰባኬ ወንጌል፥ የኢሉ አባቦራ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ ኃላፊ፥ የሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቀሲስ እና ጸሓፊ በመሆን አገልግለዋል።
 • የከፋ፥ የሚዛን፥ የቴፒ ሀገረ ስብከት ምክትል ሥራ አስኪያጅ፥ የስብከተ ወንጌል ኃላፊ፥ የገዳም አበምኔት በመሆን ለ40 ዓመታት የተዘጋውን የአቡነ ሐራ ድንግል ገዳምን አስከፍተው ለአገልግሎት እንዲበቃ አድርገዋል።
 • የመንጃና የሸካ ተወላጅ ኢአማንያን የሆኑትን 327 ሰዎች አጥምቀው የተዋሕዶ ልጆች አድርገዋል። ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ አገልግሎታ ቸውን በማየት መጋቤ አእላፍ ብለዋቸዋል።
 • 87 አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል።
 • በየአድባራቱ የሠርክ ጉባኤ ሰባኬ ወንጌል በመሆን አገልግለዋል።
 • በዚህ ወቅት መኪና ስለሌላቸው በእግርና በፈረስ፥ በአይሱዙ መኪና ከላይ በመጫን እየተንቀሳቀሱ ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል።
 • በጅማ ሀገረ ሰብከት የካህናት ማሠልጠኛ ርእሰ መምህር በመሆን ክፍል በመግባትም የዶግማና ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር መምህር በመሆን አገልግለዋል። የሠርክ ጉባኤ በጅማ በማቋቋም ጉባኤያትን በማዘጋጀት በአጋሮ፥ በደነባ፥ በሊሙ ገነት፥ በሶኮሩ፥ በቶባ ተዘዋውረው ወንጌልን ሰብከዋል። 9 ሙስሊሞችን አጥምቀዋል።
 • የጉጂ ቦረና ሊበን ሀገረ ሰብከት ሥራ አስኪያጅ በመሆን ጳጳስ በሌለበት ሀገረ ስብከተ ሁለቱንም ሥራ ደርበው በመሥራት፦
 • የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት በዘመናዊ መልክ አስገንብተዋል፥
 • መንበረ ጳጵስና በዘመናዊ መልክ አስገንብተዋል፥
 • የጽ/ቤቱንና የመንበረ ጵጵስናውን ሙሉ የቤት ማቴሪያሎች አሟልተዋል።
 • 94 አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል። ከዚህ መሃል 7ቱ ገዳማት ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ በሱማሌ ክልል በሊበን ዞን በፊልቱና ዶልቦ በመደብደብ የቅዱስ ገብርኤልና የመድኃኔ ዓለምን ቤተ ክርስቲያን አሳንጸዋል።
 • በነገሌ ቦረና በደርግ መንግሥት የተወሰደውን 37 ክፍል ዘመናዊ ቤት በብፁዕ አቡነ ሚካኤል የተገነባውን እንዲመለስ በማድረግ ትምህርት ቤት እንዲከፈት አድርገዋል።
 • አዳሪ ትምህርት ቤት በማቋቋም 12 ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች በማሳደግና በማስተማር ከእነዚህ መሃል የኮንሶ ተወላጅ ለቅስና ማዕርግ እንዲበቃ አድርገዋል።
 • በያቤሎ የተወሰደውን ቤት አስመልሰዋል።
 • ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን አስገንብተው የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዲቀጥል አድርገዋል።
 • በደቡብ ኦሞ ጅንካ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ያልነበረው በመሆኑ ዘመናዊ ጽ/ቤት በማስገንባትና የቢሮ ሙሉ ማቴርያል በማሟላት ሀገረ ሰብከቱ ዘመናዊ አሠራር እንዲኖረው አድርገዋል።
 • የሠርክ ጉባኤ በአድባራቱ በማቋቋም ከሥራ አስኪያጅነቱ ሥልጣን ጋር የሠርክ ጉባኤ ሰባኪ በመሆን ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት በዙመራቴ 23 የገለብ ተወላጆችን አጥምቀዋል።
 • 11 አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል። 300 ሄክታር የእርሻ መሬት በመቀበል ሀገረ ስብከቱ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገዋል።
 • በጋምቤላ ሀገረ ስብከት ከክህነት ውጪ ያለ ሊቀ ጳጳስ፥ ሥራ አስኪያጅ፥ ጸሓፊ፥ መዝገብ ቤት፥ ሰባኬ ወንጌል በመሆን ለ11 ዓመታት ሲሠሩ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የሌለው ስለነበር ዘመናዊ ጽ/ቤት አሳነጸዋል። ዘመናዊ መንበረ ጵጵስና አስገንብተዋል። በጽ/ቤቱ በቲኦሎጂ የተመረቁ 13 ሠራተኞችን ቀጥረዋል።
 • ገዳማዊ መዐዛ የማያውቀውን ሀገረ ስብከት 11 ገዳማትን ገድመዋል።
 • የአብነት ት/ቤት በመክፈት የአራት ጉባኤ መምሕራን በመቅጠር፥ የብሄረሰቡ ልጆች እንዲማሩ በማድረግና ትምህርት ቤቱን በአቅም እንዲደራጅ አድርገዋል።
 • ንጉሥ ከነሠራዊቱ(ፕሬዝዳንትን ከነካቢኔ) 7,037 የክልሉን ብሔረሰቦች አጥምቀው የተዋሕዶ ልጆች አድርገዋል፥
 • 53 አብያተ ክርስቲያናትን በጋምቤላ ክልል አሳንጸዋል።
 • በደርግ መንግሥት የተወሰዱ ቤቶችን አስመልሰዋል።
 • 13 ዐጸደ ሕፃናትና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን አሳንጸዋል።
 • 4 ወፍጮ ቤቶች አስተክለዋል። የሚከራይ 64 ቤቶች አሳንጸዋል። በጋምቤላ ከተማ G+3 ዘመናዊ ሕንጻ አስገንብተዋል።
 • ለየአብያተ ክርስቲያናቱ ከ300-600 ሄክታር መሬት ከነካርታው አሰጥተዋል።
 • በእያንዳንዱ አብያተ ክርስቲያናት ቡና፥ ባሕር ዛፍ፥ አቡካዶ፥ ሙዝ፥ ኦቾሎኒ፥ ሩዝ፥ ሰሊጥ እንዲተከልና አብያተ ክርስቲያ ናቱ በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ አድርገዋል።
 • በጋምቤላ ከተማ በጥምቀት በዓል በሦስት ቦታ 41 ታቦታትን በማውጣት ለአምስት ቀናት በዓሉ እንዲከበር፥ 44 ታቦታት በማድረግም የእነ አቡነ ዜና ማርቆስ፥ የእነ አቡነ ሐራ ድንግልን ታቦታት በማምጣት ቅዱሳኑን ለክልሉ ሕዝብ አስተ ዋውቀዋል።
 • ከክልሉ ብሄረሰቦች ዲያቆናትን በማስተማር ገብተው እንዲቀድሱ እንዲሁም በከሣቴ ብርሃንና በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ቤት በማስተማር ለሰባኪነት እንዲበቁ አድርገዋል።
 • ሀገረ ስብከቱ ምንም ዓይነት መኪና ያልነበረው በመሆኑ ያለ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ርዳታ ብር 409,000 (አራት መቶ ዘጠኝ ሺህ ብር) ከቤተሰቦቻቸውና ከንስሐ ልጆቻቸው በማስተባበር ገዝተው አበርክተዋል።
 • በክልሉ በተደጋጋሚ በሚነሣው የጸጥታ ችግር ጥይት በሚተኮስበት ቦታ ሁሉ በመግባት የዛሬው ሰላም በክልሉ እንዲሰፍን ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
 • ሦስት ጊዜ ብፁፅ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ከ18 ጳጳሳት ጋር ወደ ጋምቤላ ጠርተዋል፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስንም ከ8 ጳጳሳት ጋር ወደ ጎደሬና ጋምቤላ ጠርተው አስተናግደዋል።
 • 42 ዲያቆናት በእሳቸው፥ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ተማርከው ለምንኵስና ሕይወት በቅተዋል።
 • በጋምቤላ ክልል ከተማ በጎደሬና በዚታንግ ብፁዕ አቡነ ጳውሎስንና ብፁዕ አቡነ ማትያስን ከ22 ጳጳሳት ጋር ወደ ጋምቤላ በማምጣት ከክልሉ ፕሬዝዳንት አንሥቶ እስከ ካቢኔ አባላት በማስጠመቅ የተዋሕዶ ልጆች አድርገዋል። በተጨማሪም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማታያስ በአንድ ቀን ውስጥ በጋምቤላ 4 አብያተ ክርስቲያናትን እንዲባርኩ አድርገዋል።
 • በጋምቤላ ከተማ 44 ታቦታን በጥምቀት በማውጣት ከፕሬዝዳንቱ እስከ ካቢኔ አባላቱ በጥምቀት በእግራቸው በመሄድ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረዋል። በተጨማሪም በዚህ በዓል ላይ ከተለያዩ ቤተ እምነቶች 120-142 ድረስ ተጠምቀው የተዋሕዶ ልጆች አድርገዋል። ጥምቀት በተከበረ ቁጥር ከ127-147 ሰዎች ያጠምቃሉ።
 • በጀጀቤ ተራራ ላይ በጋምቤላ ከተማ በተራራው ቁንጮ ላይ የአቡነ አረጋዊ ገዳምን ሠርተዋል።
 • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ደቡብ ሱዳን ላይ ቤተ ክርስቲያን ያሠሩ፥ ወንጌልን የሰበኩ፥ ቅዳሴ የቀደሱ፥ ሰበካ ጉባኤን፥ ሰንበት ት/ቤትን ያቋቋሙ ሐዋርያ ናቸው።
 • በዲማ ጫካ በሱርማ ጥይት ተተኩሶባቸው በሐዋርያት ተጋድሎ በማለፍ አቶ ሳዶም የተባለውን የአኝዋክ ብሔረሰብ የቻሞ ቀበሌ ሊቀመንበር አስተምረው ካስመረቁት በኋላ የቅድስት አርሴማ ገዳም በመሥራት ጠበል ከፈለቀ በኋላ ከኤችአይቪ ቫይረስ እንዲፈወስ አድርገዋል። በሰበካ ጉባኤ በምክትል ሊቀ መንበርነት እንዲሠራ አድርገዋል። በተጨማሪም በጋምቤላ ብሔረሰቦች የሰበካ ጉባኤና የሰንበት ትምህርት ቤት እንዲቋቋም አድርገዋል።
 • በጋምቤላ ክልልና በደቡብ ሱዳን ጠረፋማ አካባቢ ለ11 ዓመታት በበረሀ ወንጌል በመስበክ፥ ጸሎት በማድረግ ባደረጉት ጥረት 58 አብያተ ክርስቲያናት አሠርተዋል
 • አባ ተክለ ሃይማኖት ወደ ጋምቤላ ሳይመጡ በሀገረ ስብከቱ የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት 14 ብቻ ነበሩ። የሠሯቸው አብያተ ክርስቲያናት የሕንጻው ሰብሳቢ በመሆን ከ6 ወር እስከ ዓመት ውስጥ በማጠቀቅ አሠርተዋል።
 • በጎደሬና በዲና ወረዳዎች 267 የሚከራዩ ሱቆች አሠርተዋል።
 • በገደሟቸው 13 ገዳማት ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶች ከፍተ ዋል። በተጨማሪም በገዳማቱ ላይ እናትና አባት የሞቱባቸው 24 የክልሉን ብሔር ብሔረሰቦች ልጆች አስተምረዋል።
 • በክልሉ ለልማት 640 ሄክታር መሬት በመቀበል የቡና ልማት፥ የሰሊጥ እርሻና የንብ ርባታ በማቋቋም አብያተ ክርስቲያናትን ከልመና አውጥተዋል
 • በክልሉ 16 ዐጸደ ሕፃናትና አንደኛ ደረጃ ት/ቤት አሠር ተዋል።
 • የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦች ልጆች ለዲቁና፥ ለሰባኪነት እንዲበቁ በማድረግ እንዲቀጠሩ አድርገዋል።
 • በክልሉ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ የይዞታ ካርታ አሠርተዋል።
 • በጋምቤላና በአካባቢው ያደረጉትን የሰላምና የልማት ጥረት የተመለከተው የጋምቤላ ክልል መንግሥት የሰላምና የልማት አምባሳደር ብሎአቸዋል። በተጨማሪም የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስ ቴር የሰላም ጀግና በማለት በሀገር አቀፍ ደረጃ የነሐስ ሜዳልያ ሸልሞአቸዋል።

ብዙ የሰው ኃይል የሚጠይቀውንና እንደ ገቢረ ተኣምራት የሚቆጠረውን ይህን ሰፊ ሐዋርያዊ ተግባር በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻቸውን በማከናወን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ኩራትና መመኪያ የኾኑት እኒህ የሐዋርያት ሐዋርያ አባት፣ ሥራውን ሁሉ ከመመረጣቸው በፊት አስቀድመው ስለሠሩት፣ የተሠሩትን ሥራዎች ከመጎብኘትና ከመባረክ በስተቀር፣ ከእንግዲህ ወዲህ ዐዲስ ሥራ የሚጠብቃቸው አይመስልም፡፡

ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ፣ ነፍሳቸውን ለበጎቻቸው አሳልፈው በመስጠት፣ “ቸር እረኛ ነፍሱን ለበጎች አሳልፎ ይሰጣል” የሚለውን የቅዱስ ወንጌል ቃል በተግባር በመፈጸማቸውና “አንተ በጥቂቱ የታመንክ ታማኝ አገልጋይ በብዙ ላይ እሾማሃለሁና፣ ና ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” ተብሎ እንደተሾመው፣ እንደዚያ ታማኝ አገልጋይ አትርፈው የተሾሙ አባት ናቸው፡፡ ስለዚህም ነው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ሁሉ ሰፊ የኾነ ሐዋርያዊ ተግባራቸውን ከግምት በማስገባትና ለሥራቸው የሚመጥናቸው በማጣት ያለተወዳዳሪ መርጦ ለሢመተ ጵጵስና ያበቃቸው፡፡

11) መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ ቆሞስ አባ ሳሙኤል ገላነው

መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ ቆሞስ አባ ሳሙኤል ገላነው ከአባታቸው ከአቶ ገላነው ማሬና ከእናታቸው ከወ/ሮ ያምሮት ንጋቴ በሰሜን ወሎ በመቄት ወረዳ ልዩ ስሙ አስፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተባለ ቦታ መጋቢት 5 ቀን 1965 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

ከፊደል ገበታ እስከ መዝሙረ ዳዊት ያሉትን የንባብ ክፍሎችን በየ ስልታቸው፥ እንዲሁም የውዳሴ ማርያምን ዜማ በአስፋ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በብህትውና ይኖሩ ከነበሩት ከመልአከ ጽጌ አባ ገብረ እግዚአብሔር ካሳውና በመቄት ወረዳ አንሣውኃ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የድጓ መምህር ከነበሩት ከየኔታ ገላው እውኔ ተምረዋል።

የመዝሙረ ዳዊትን ንባብና የውዳሴ ማርያምን ዜማን በመከለስ መስተጋብዕንና አርባዕትን በደቡብ ጎንደር የደብረ ፀሓይ ጨጨሆ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የድጓ መምህር ከሆኑት ከሊቀ ጠበብት መሪጌታ በላይ ከበደ (የአሁኑ አባ ይባቤ) ተምረዋል።

በደቡብ ጎንደር የደብረ ፀሓይ ጨጨሆ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ከነበሩት ከየኔታ ነቅዐ ጥበብ ከጥቅምት 1981 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ ወር 1982 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ቅኔ ተቀኝተዋል።

ከመስከረም ወር 1983 ዓ.ም. እስከ መስከረም 1984 ዓ.ም. ድረስ ወደ ምዕራብ ጎጃም በመሄድ ጨጎዴ ሀና ከሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው ቅኔ እስከ ሥላሴ ነግረዋል።

ከጥቅምት ወር 1984 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 1984 ዓ.ም. በባሕር ዳር ሽንብጥ ሚካኤል ገዳም ከየኔታ መንግሥቱ በሙሉ ቤት ሁለተኛ ቅኔ ተቀኝተው በተጨማሪም በዚያው ሽንብጥ ሚካኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ለአራት ወራት የሚሰጠውን ኮርስ ተከታትለዋል።

ወደ ሰሜን ጎንደር ደንቢያ በመሄድ ገንበራ ኢየሱስ ከየኔታ ዕንባቆም የአቋቋም ትምህርትን ጀምረው የቁስቋምንና የኅዳር ሰባት ቅዱስ ጊዮርጊስን ክብረ በዓል እንደተማሩ ወደ ሰሜን ወሎ መቄት ወረዳ በመሄድ ደብረ ገነት ዋርካዬ ማርያም ከየኔታ ገብረ መስቀል ዳምጤ ከየካቲት 1985 እስከ የካቲት 1989 ዓ.ም. ድረስ የአቋቋም ትምህርታቸውን ተምረዋል።

ከመስተጋብዕ እስከ ሠለስት ያሉትን የቃል ትምህርት፥ ጾመ ድጓና መዝገብ ቅዳሴ በወልቂጤ ዞን ከሚገኘው ምሑሩ ገዳመ ኢየሱስ ከታኅሣሥ ወር 1992 እስከ ታኅሣሥ 1993 ዓ.ም. ተምረዋል።

የሐዲሳት መጻሕፍት ትርጓሜን የከንባታ፥ ሀድያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ጥረት ወደ ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመግባት ከጥቅምት ወር 1996 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2000 ዓ.ም. ተምረው በከፍተኛ መዐርግ ተመርቀዋል።

የብሉያት መጻሕፍት ትርጓሜንም በዚሁ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከመስከረም 2001 እስከ ሰኔ 21 2006 ዓ.ም. ተምረው በማጠናቀቅ በከፍተኛ መዐርግ ተመርቀዋል።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ኮልፌ ክፍለ ከተማ በሰላም በር አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ከ1997-2002 ዓ.ም. ተከታትለዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አባባ ኮልፌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ2003-2005 ዓ.ም. ተምረው አጠናቀዋል።

በሰው ኃይል አስተዳደር ከሪፍት ቫሊ ኮሌጅ በ2008 ዓ.ም. በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና – ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በየካቲት 1984 ዓ.ም. ተቀብለዋል።
 • ምንኵስናና ቅስና – ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በምድረ ከብድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የአንድነት ገዳም መጋቢት 5 ቀን 1994 ዓ.ም. ተቀብለዋል።
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በጥቅምት 27 ቀን 1997 ዓ.ም. ተቀብለዋል። 

አገልግሎት፡

ከመጋቢት 1989 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 1992 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ወሊሶ ሀገረ ስብከት በደብረ ኃይል ጨፎ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በመሪጌትነት አገልግሎት ሰጥተዋል።

በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ጥያቄ መሠረት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ፈቃድ አግኝተው ለ11 ዓመታት የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜን በተማሩበት ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር በመሆን ከሐምሌ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከጥር ወር 1996 ዓ.ም. ጀምሮ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አካባቢ የሚገኙትን የፌደራል ፖሊስ አባላት የሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናንንና ምእመናትን በማሰባሰብ ቋሚ ትምህርተ ሃይማኖት እንዲያገኙ በማድረግ ሕዝባቸውን በታማኝነትና በእኩልነት እንዲያገለግሉ ትልቅ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ከ51 ያላነሱ ኢአማንያን ወደ ክርስትና ሃይማኖት እንዲገቡና ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ዶግማና ቀኖና አፈንግጠው ለነበሩ ቁጥራቸው ከ80 በላይ ለሆኑ ምእመናንና ምእመናት ወደ ቤታቸው መመለስ ምክንያት ሆነዋል።

በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት በመቄት ወረዳ በሚገኘው ጥንታዊና ታሪካዊ በሆነው በአስፋ ገነት ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተደራጀ የአብነት ትምህርት ቤት መልሶ ለማቋቋም የንስሓ ልጆቻቸውን በማስተባበር ከ500 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

መልሶ ለማቋቋም በታሰበው የአስፋ ገነት ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት የዓመት ወጪዎችን ለመሸፈንና እራሱን እንዲችል ለማድረግ የንስሓ ልጆቻቸውን በማስተባበርና ከማኅበረ ቅዱሳን የ85 ሺህ ብር ድጋፍ በማግኘት በመቄት ወረዳ አግሪት ከተማ ላይ ቦታ በመግዛት፥ ቤት በመሥራትና ትራንስፎርመር በማስተከል ከ500 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ የሦስት ወፍጮ ተከላ ተጠናቆ ገቢ እንዲያስገኝ አድርገዋል።

ከመንግሥት የኢንቨስትመንት ቦታ በመረከብ 800 ሺህ ብር የሚጠይቅ የከብት እርባታና የወተት ልማት ፕሮጀክት ለመተግበር ሙሉ ጥናት ተጠናቆ ወደ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት ላይ ይገኛል። በዚህና በሌሎችም ባደረጉዋቸው የልማት እንቅስቃሴዎች በሰሜን ወሎ ዞንና በመቄት ወረዳ መስተዳድሮች የዋንጫ፥ የሜዳልያና የሰርቲፊኬት ተሸላሚ ለመሆን ችለዋል

የወገንን ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት የንስሓ ልጆቻቸውን በማስተባበር ከእነ ወ/ት ገበያነሽ ገሠሠና ከሌሎች ምእመናን ጋር በመቀናጀት የአቡነ ዜና ማርቆስ የሕፃናትና አረጋውያን መርጃ ማኅበርን አቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ ቆሞስ አባ ሳሙኤል ገላነው፣ የተሟላ ዕውቀት ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ ከምርጫቸው በፊት አገልግሎታቸውና ሥራቸው ስለቀደመ ነው፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሢመተ ጵጵስና ምርጫ ያበቃቸው፡፡

12) ቆሞስ አባ ፊልጶስ አሻግር

ቆሞስ አባ ፊልጶስ አሻግር ከአባታቸው ከአቶ አሻግር ዘገነና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሰፋ ከተማሽ በላይነህ በሰሜን ሸዋ ዞን መርሐቤቴ ወረዳ ነሐሴ 13 ቀን 1964 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • በደለማ ደብረ ሐመልማል ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፊደል፥ ንባብና ግብረ ዲቁና ከመምህር አፈወርቅ ተምረዋል።
 • ዘመናዊውንም ትምህርት በወረዳው ዋና ከተማ በዓለም ከተማ በማጠናቀቅ ወደ ምነናው ዓለም ጉዞአቸውን ጀመሩ።
 • በ1986 ዓ.ም. በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል እና በአካባቢው ለ6 ወራት ከቆዩ በኋላ ወደ ሰሜናዊው የሀገራችን ክፍል ወዳሉት ገዳማት ማለትም እመምዑዝና ጎርጎር ማርያም እንዲሁም አቡነ አሮን በማቅናት ስለ ምነናና ገዳማዊ ሕይወት እየተማሩ ከአበው በረከት ተካፋይ ለመሆን በቅተዋል።
 • 1990 ዓ.ም. ወደ ምሥራቅ ጎጃም አስቄጥስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም በመሔድ የቅኔ ትምህርት ከመምህር ዐሥራት ተምረዋል።
 • ወደ ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም በመምጣት የቅዳሴ ትምህርት ከመምህር ጎሐ ጽባሕ በመማር አስመስክረዋል።
 • ባሕረ ሐሳብንም ከመጋቤ ምስጢር ገ/ሕይወት ፋንታሁን አጥንተዋል።
 • በ1994 ዓ.ም. በብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብተው በመማር በሥነ መለኮት የመጀመሪያ ዲግሪ ያዙ።
 • ከአገልግሎታቸው በተጓዳኝ ትምህርታቸውን በመቀጠል ከኮርሊንስ ዩኒቨርስቲ በሥነ መለኮትና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ የምክር አገልግሎት የትምህርት ዘርፍ የማስትሬት ዲግሪ ተቀብለዋል።
 • ከመስት ዩኒቨርስቲ በሥነ ልቦናና የምክር አገልግሎት ዘርፍ ማስትሬት ዲግሪ አግኝተዋል።
 • ከክራይስት ቸርች ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሰርቲፊኬት በማግኘት የዕውቀት አድማሳቸውን ለማስፋት ችለዋል።
 • ቆሞስ አባ ፊልጶስ አሻግር፣ ከነሐሴ 2004 ዓ.ም. ጀምሮ አሁንም የመማሩን ሒደት በመቀጠል፣ የትምህርተ አበ ነፍስ ጥበባዊ መንገድ በሚል የትምህርት ዘርፍ፣ የቅድመ የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን በማዶና ዩኒቨርስቲ በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

መዐርገ ክህነት

 • ምንኵስና – በሐይቅ ቅዱስ እስጢፋኖስ ወአቡነ ኢየሱስ ሞአ ገዳም ታኅሣሥ 1988 ዓ.ም. በጊዜው ከነበሩት አበምኔት መምህር አምደ ሥላሴ አበጋዝ ተቀብለዋል።ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሊቀ ጳጳስ በ1994 ዓ.ም. ተቀብለዋል።
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል።
 • ዲቁና – ከብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ሊቀ ጳጳስ ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • በቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የቀን መርሐ ግብር አስተባባሪነት ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር አገልግለዋል። ወደ ምዕራቡ ዓለም ሰሜን አሜሪካ በመሔድ ላለፉት አራት ዓመታት በሚቺጋን ደብረ ገነት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነትና የኒውዮርክ ሀገረ ሰብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
 • ቆሞስ አባ ፊልጶስ አሻግር መንፈሳዊውንና ዘመናዊውን ዕውቀት አስተባብረው የያዙ ምሁር ከመሆናቸውም በላይ በሰጡት አገልግሎት የተመሰከረላቸው ስለሆነ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሢመተ ጵጵስና ምርጫ አብቅቷቸዋል፡፡
 • በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፈቃድ በ2002 ዓ.ም. ወደ ኒውዚላንድ ሀገር ተልከው አገልግሎታቸውን በበቂ ሁኔታ የተወጡ ሲሆን፣ ይህንንም የሚያረጋግጥ ከሀገሪቱ መንግሥት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡
 • ወደ ምዕራቡ ዓለም ሰሜን አሜሪካ በመሔድ ላለፉት አራት ዓመታት በሚቺጋን ደብረ ገነት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነትና የኒውዮርክ ሀገረ ሰብከት የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
 • ቆሞስ አባ ፊልጶስ አሻግር መንፈሳዊውንና ዘመናዊውን ዕውቀት አስተባብረው የያዙ ምሁር ከመሆናቸውም በላይ በሰጡት አገልግሎት የተመሰከረላቸው ስለሆነ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለሢመተ ጵጵስና ምርጫ አብቅቷቸዋል፡፡

13) ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሓ

ሊቀ ብርሃናት አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሓ ከአባታቸው ከቄስ ፍሥሓ ገብረ ክርስቶስ (አሁን አባ) እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሸጌ ኃይሉ (አሁን እማሆይ) በምሥራቅ ሸዋ ጀልዱ ወረዳ ልዩ ስሙ ቢቾ ሚካኤል በሚባለው ቦታ በ1966 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • ፊደል፥ ንባብ፥ ግብረ ዲቁና – ከአባታቸው ከቄስ ፍሥሐ ገብረ ክርስቶስ እና ከመሪጌታ መለሰ ገብረ ጻድቅ፥
 • ዜማ – ከመሪጌታ ለይኩን ብርሃኑ፥
 • ቅዳሴ – ከአባ ወ/ጊዮርጊስ (ዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም) እና ከመምህር ኃይለ ሥላሴ (ደብረ አባይ ገዳም)
 • ባሕረ ሐሳብ – ከመምህር ኃይለ ሥላሴ (ደብረ አባይ ገዳም)
 • ቅኔ – ከመጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁና ከመምህር አውላቸው አሁን አባ ተክለ ሃይማኖት (ዝዋይ ሐ/ብ/ቅ/ገብርኤል ገዳም)
 • አቋቋም – ከመምህር ሐረገወይን (ዝዋይ ሐ/ብ/ቅ/ገብርኤል ገዳም)
 • የሐዲሳት ትርጓሜ- (ሰ/ብ/ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ)
 • ነገረ መለኮት – (ቅድስት  ሥላሴ  መንፈሳዊ  ዩኒቨርስቲ  ኮሌጅ) ተምረዋል።

የትምህርት ማስረጃዎች፡-

 • የቅዳሴ መምህርነት ምስክር ወረቀት – ከደብረ አባይ ገዳም 1992 ዓ.ም.
 • የካህናት ሥልጠና ሴሚናር ምስክር ወረቀት – ከዝዋይ ሐ/ብ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ገዳም 1990 ዓ.ም.
 • የሐዲሳት ትርጓሜ መምህርነት ዲፕሎማ – ከሰ/ብ/ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ 1997 ዓ.ም.
 • በነገረ መለኮት ባችለር ዲግሪ – ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ 2003 ዓ.ም. ተቀብለዋል።
 • የጀርመንኛ ቋንቋ ተከታታይ ትምህርት ሰርቲፊኬት – ከMunchner Volkshochschule- ጀርመን 2004 ዓ.ም.
 • የጀርመንኛ ቋንቋ ተከታታይ ትምህርት ሰርቲፊኬት – ከMaximilians University – ጀርመን 2007 ዓ.ም. አግኝተዋል።

ቋንቋ፡-

 • ኦሮምኛ፥ አማርኛ በአፍ መፍቻነት፤
 • ግዕዝ፥ እንግሊዝኛና ጀርመንኛ ለትምህርትና ለሥራ አገልግሎት ይጠቀሙባቸዋል።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና – ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ በ1975 ዓ.ም.
 • ምንኵስና – ከብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተ/ሃይማኖት ገዳም በ1986 ዓ.ም.
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ ቶማስ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተ/ሃይማኖት ገዳም በ1987 ዓ.ም.
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ገብርኤል የኢሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በ1993 ዓም. ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡

 • በቀዳሽነት፥ በማኅሌት፥ በሰባኪነት፥ በቄሰ ገበዝነት ዝዋይ ሐ/ብ/ቅ/ ገብርኤል ገዳም፤
 • በደብር አስተዳዳሪነት በቦጬሳ ቅዱስ ሚካኤል፥ ደ/ሲ/ቅድስት ማርያምና ደ/ገ/ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አብያተ ክርስቲያናት ዝዋይ፤
 • በቅዳሴ፥ በማኅሌትና በስብከተ ወንጌል (የፈቃድ አገልግሎት) መ/ን ቁስቋም ማርያም ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ፤
 • በሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪነት ቦሌ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን፤ አዲስ አበባ
 • በደብር አስተዳዳሪነት በላፍቶ ደ/ኢ መድኃኔ ዓለም፥ ሰሚት መድኃኔ ዓለም፥ ደ/ም ፊልጶስ፥ ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ፥ አየር ጤና ኪዳነ ምሕረት፥ አስኮ ደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት አዲስ አበባ፤
 • በደብር አስተዳዳሪነት በሙኒክ ደ/ብ/ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሙኒክ፥ ጀርመን አስተዳድረዋል።

የነጻ ፈቃድ አገልግሎት፡-

 • ከ1990-2003 ዓ.ም. በኦሮምያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ጀልዱ ወረዳ አካባቢ በተለያዩ አድባራት በሰባኬ ወንጌልነት
 • ከመስከረም 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በደ/ም/ም አውሮፓ ሀገረ ስብከት በልማት መምሪያ ሓላፊነት አገልግለዋል።

ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ገብረ ሕይወት ፍሥሓ፣ የሕይወት ታሪካቸውን እንደሚያስረዳው፣ ዘመናዊውን ትምህርት ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር አስተባብረው የያዙ ምሁር ከመሆናቸውም በላይ፣ በተለይም በማሕሌታዊነታቸው የዘመኑ ያሬድ በመባል ይታወቃሉ፡፡ በዚያም ሆነ በዚህ፣ በትምህርት ብቃታቸውና በውስጥና በውጭ ባበረከቱት ሰፊ አገልግሎት ለሢመተ ጵጵስና ምርጫ ብቁ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

 

14) መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ

መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ ከአባታቸው ከአቶ ተድላ መንግሥቴና ከእናታቸው ከወ/ሮ አታላይ ጌታ መርጡለ ማርያም በተባለው ቦታ በ1960 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • ፊደል፥ ንባብና ፀዋትወ ዜማ – ከሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ዓለሙ (ርእሰ ርዑሳን ደብረ ነገሥት መርጡለ ማርያም ገዳም ወደብር)፥ ከመሪጌታ ምሕረት በለጠ (ጎላ ቅዱስ ጊዮርጊስ)፥
 • ቅኔ ከነአገባቡ – ከመሪጌታ ሀብተ ኢየሱስ ጋርደውና ከመሪጌታ ሐረገ ወይን አሻግሬ (ርእሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም)፥
 • ቅዳሴ – ከመምህር በላይ (ርእሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም) እና ከአባ ግርማ ጽዮን (ደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን፥ አዲስ አበባ)
 • የወንጌል ትርጓሜ – ከመሪጌታ ሐረገወይን አሻግሬ (ርእሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም)
 • የካህናት ሥልጠና የ4 ወራት ሴሚናር – (ሸምብጥ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ፥ ባሕር ዳር)
 • የካህናት ሥልጠና የ6 ወራት ሴሚናር- (ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፥ አዲስ አበባ)
 • የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት – (አብርሃ ወአጽብሐ መለስተኛና 2ኛ ደረጃ፥ ነፋስ ስልክ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች)
 • የሒሳብ መዝገብ አያያዝ – (አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ)
 • የሕዝብ አስተዳደር ትምህርት – (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ)
 • የነገረ መለኮት ተከታታይ ትምህርት – (የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ኮሌጅ፥ ጀርመን)
 • ነገረ መለኮት (ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ) ተምረዋል።

የትምህርት ማስረጃዎች፡-

 • የካህናት ሥልጠና ሴሚናር ሰርቲፊኬት – (ሽምብጥ ቅዱስ ሚካኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ – ባሕር ዳር) 1982 ዓ.ም.
 • የሒሳብ መዝገብ አያያዝ ዲፕሎማ – (ከንግድ ሥራ ኮሌጅ)
 • የካህናት ሥልጠና ሰርቲፊኬት – (ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ) 1991 ዓ.ም. ተቀብለዋል።
 • በሕዝብ አስተዳደር ትምህርት ዲግሪ – (ገና ያልተጠናቀቀ – አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ)
 • በነገረ መለኮት ባችለር ዲግሪ – (ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ኮሌጅ -ጀርመን) አግኝተዋል።

ቋንቋ፡-

 • አማርኛ በአፍ መፍቻነት
 • ግዕዝ፥ እንግሊዝኛና ጀርመንኛ በትምህርትና በሥራ ቋንቋነት ይጠቀማሉ።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና – ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ደብረ ማርቆስ በ1975 ዓ.ም.
 • ምንኵስና – ከርእሰ ርኡሳን ኃይለ ኢየሱስ ገብረ ማርያም – ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም በ1980 ዓ.ም.
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በ1980 ዓ.ም.
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ዘካርያስ – ርእሰ ርኡሳን መርጡለ ማርያም 2002 ዓ.ም. ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • ከ1976-1983 ዓ.ም. በዲቁና እና በቅስና – ርእሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም
 • ከ1984-1986 ዓ.ም. በሰባኬ ወንጌልነት – ግፉዕ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን
 • ከ1987-1989 ዓ.ም. በቅስና በደ/መ ቁስቋም ማርያም፥ በደ/ና ቅዱስ ዮሴፍ፥ በደ/ይ ቅዱስ ያሬድ አብያተ ክርስቲያናት አዲስ አበባ
 • ከ1989-1991 ዓ.ም. በሒሳብ ሹምነት በአቃቂ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን
 • ከ1991-1993 ዓ.ም. በሒሳብ ክፍል ኃላፊነት በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክህነት የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር፤
 • ከ1998-1999 ዓ.ም. በቅስናና በሒሳብ ክፍል ሐላፊነት ከኢያሪኮ የተወረሰው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አሠሪ ኮሚቴ አባልነት፥ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ጽ/ቤትና በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ቤቶችና ሕንጻዎች ኃላፊነት፤
 • 1993-1997 እና ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ በደብር አስተዳዳሪነት በበርሊን ደ/ገ አማኑኤልና ሐምቡርግ ደ/መ ኪዳነ ምሕረት አብያተ ክርስቲያናት ጀርመን አገልግለዋል።

የነጻ ፈቃድ አገልግሎት፡-

 • በበርሊን አካባቢ በሚደረጉ ስብሰባዎችና በዓላት ላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ወክሎ በመገኘት ተሳትፎ በማድረግ ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግንዛቤ በማስጨበጥ፥
 • በምሥራቃዊና ሰሜናዊ ጀርመን ከተሞች ምእመናንን በማስተማር የጽዋዕ ማኅበራትን በማደራጀት ወደ ቤተ ክርስቲያንነት እንዲያድጉ በማድረግ አገልግሎት ሰጥተዋል።

መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል ተድላ፣ በትምህርት ብቃታቸውና በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም በሰጡት ሰፊ አገልግሎት፣ በተለይም በጀርመን ሀገር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የደብረ ገነት ቅዱስ ዐማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን አስተባብረው በመግዛት፣ በዚያ የሚኖሩት ኢትዮጵጵያውያን ምእመናንና ሌሎችም እንዲገለገሉበት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ሓላፊነት የተወጡ ምሁር በመሆናቸው ለሢመተ ጵጵስና ለመመረጥ በቅተዋል፡፡

15) መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ዘድንግል ኑርበገን

መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ዘድንግል ከአባታቸው ከአቶ ኑርበገን ገዳና ከእናታቸው ከወ/ሮ መስቀሌ ገብረ ሚካኤል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በ1964 ዓ.ም. ተወለዱ።

ትምህርት፡-

 • የቃል ትምህርት፥ ግብረ ዲቁና – በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል የካህናት ማሠልጠኛ ገዳም
 • ቅዳሴ፥ ሰዓታት – ከአባ ወልደ ጊዮርጊስ – በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል የካህናት ማሠልጠኛ ገዳም
 • ቅኔ ከነአገባቡ – ከመጋቤ ሐዲስ እሸቱ – በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል የካህናት ማሠልጠኛ ገዳም
 • የካህናት ሥልጠና (ሴሚናሪ) – በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም
 • የነገረ መለኮት የመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር – በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፥ አዲስ አበባ
 • የፈረንሳይኛ ቋንቋ – በአልያንስ ፍራንሴስና ሶርቦን ዩኒቨርስቲ፥ ፈረንሳይ
 • የግሪክኛ ቋንቋ – በግሪክ አገር ተሰሎቄ
 • የነገረ መለኮት የሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር – በቅዱስ ሰርጊዮስ ኦርቶዶክስ ዩኒቨርስቲ፥ ፈረንሳይ
 • የነገረ መለከት የዶክትሬት ዲግሪ መርሐ ግብር እጩ (Candidate) – በቅዱስ ሰርጊዮስ ኦርቶዶክስ ዩኒቨርስቲ፥ ፈረንሳይ

የትምህርት ማስረጃዎች፡-

 • የካህናት ሥልጠና (ሴሚናሪ) ሰርቲፊኬት – ከዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል የካህናት ማሠልጠኛ ገዳም
 • የፈረንሳይኛ ቋንቋ ዲፕሎማ – ከሶርቦን ዩኒቨርስቲ፥ ፈረንሳይ
 • የግሪክኛ ቋንቋ ሰርቲፊኬት ከተሰሎቄ
 • የነገረ መለኮት የባችለር ዲግሪ – ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ- አዲስ አበባ
 • የነገረ መለኮት ማስትሬት ዲግሪ – ከቅዱስ ሰርጊዮስ ኦርቶዶክስ ዩኒቨርስቲ – ፈረንሳይ ተቀብለዋል።

ቋንቋ፡-

 • ጉራጊኛ እና አማርኛ በአፍ መፍቻነት
 • ግዕዝ፥ እንግሊዝኛ፥ ፈረንሳይኛና ግሪክኛ በትምህርት፥ በአገልግሎትና በሥራ ቋንቋነት ይጠቀማሉ።

መዐርገ ክህነት፡-

 • ዲቁና – ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በ1983 ዓ.ም.
 • ምንኵስና – ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በ1986 ዓ.ም.
 • ቅስና – ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በ1986 ዓ.ም.
 • ቁምስና – ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ተቀብለዋል።

አገልግሎት፡-

 • ከ1983-1990 ዓ.ም. በረድእነት፥ በቀዳሽነት፥ በገንዘብ ያዥነት፥ በመጋቢነት፥ በሥልጠና ሰጪነት – በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል የካህናት ማሠልጠኛ ገዳም አገልግለዋል።
 • ከ1996-1999 ዓ.ም. የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን መሥርተው፥ ሰባካ ጉባኤ አደራጅተውና ሰንበት ት/ቤት አቋቁመው በፈረንሳይ፥ ፓሪስ በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል
 • በፈንሳይ ማርሴል ከተማ በመድኃኔ ዓለም ስም በተቋቋመው የጽዋዕ ማኅበር ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን በቅዳሴና በስብከተ ወንጌል ሲያግለግሉ ቆይተዋል። (ወደ ፊት ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚያድግ ማኅበር ነው)
 • በ2000 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከምርምር ሥራ ጋር በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለአንድ ዓመት በመም ሕርነት አገልግለዋል።
 • የምርምር ሥራቸውን ጨርሰው ወደ ፈረንሳይ ከተመለሱ በኋላ የፓሪስ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን መሥርተው፥ ሰበካ ጉባኤ አደራጅተውና የሰንበት ትምህርት ቤት አቋቁመው ከ2001-2009 ዓ.ም. በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል።
 • ከምእመናንና ከሰንበት ት/ቤት ለተውጣጡ አባቶች፥ እናቶችና ወጣቶች በተምሮ ማስተማር መርሐ ግብር ቤተ ክርስቲያንን በሰበካ ጉባኤ፥ በሰንበት ትምህርት ቤትና በስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ማገልገል የሚያስችላቸውን ሥልጠና ለ6 ወራት ሰጥተው በሰርቲፊኬት እንዲመረቁ አድርገዋል።
 • ከ2007-2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብና ደቡብ ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ሰብከት የሰበካ ጉባኤ መምሪያ ሓላፊ በመሆን ሠርተዋል።
 • በፈረንሳይ ሀገር ተወልደው ላደጉ ታዳጊ ወጣቶች ግብረ ዲቁና በማስተማር ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለው ያጠናቀቁ 5 ታዳጊ ወጣቶች የዲቁና ማዕርግ ተቀብለው ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በቅዳሴ እንዲያገለግሉ አድርገዋል።
 • ከ15 እስከ 20 የሚደርሱ በተለያዩ የእምነት ተቋማት ውስጥ የነበሩና እምነት ያልነበራቸውን የውጪ ሀገር ዜጎችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት (አዕማደ ምሥጢር፥ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና) በፈረንሳይኛና በእንግሊዝኛ ከ6 ወራት እስከ 1 ዓመት ለሚደርስ ጊዜ አስተምረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ደንብ መሠረት አጥምቀዋል።
 • በቅዳሴ አገልግሎት ጊዜም በተለይ የቅዳሴ ንባብ ክፍሎችን በፈረንሳይኛ በማንበብ፥ በፈረንሳይኛ ወንጌል በማስተማር የውጪ ሀገር ሰዎች የቅዳሴው ተሳታፊዎች እንዲሆኑ አድርገዋል።
 • በፈርንሳይ ቱር ከተማ በቅዱስ ሚካኤል ስም በተቋቋመው የጽዋዕ ማኅበር ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን በቅዳሴና በስብከተ ወንጌል ሲያገለግሉ ቆይተዋል። (ወደፊት ወደ ቤተክርስቲያን የሚያድግ ማኅበር ነው)
 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፥ ቀኖና፥ ትውፊትና ሥርዓትን የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት በፈረንሳይኛ የብዙኃን መገናኛ(የቴሌቪዥን ፕሮግራም) ላይ በመደበኛ የአየር ሰዓት ከማስተዋወቅ ሥራ በተጨማሪ፣ ከአምስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወኪል በመሆን ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ አሁን ሠርተዋል።

የነጻ ፈቃድ አገልግሎት

በሀገር ውስጥ

 • በዝዋይና አካባቢው ባሉ አድባራት ስብከተ ወንጌል በመስጠትና ቅዳሴ በመቀደስ፥
 • በናዝሬት ደብረ ፀሓይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለሰንበት ትምህርት ቤት ተከታታይ ሥልጠና በመስጠት፥
 • በስብከተ ወንጌል አገልግሎት በአዲስ አበባ አድባራት ሥልጠና በመስጠት።

ከሀገር ውጭ(በአውሮፓ)፡-

 • በቤልጂየም፥ በሆላንድ፥ በስፔይን፥ በስዊዘርላንድ፥ በጀርመን፥ በጣሊያን፥ በሎዘምበርግ፥ በቱርክና በሌሎች ሀገሮች በክብረ በዓላት በመገኘት ሕዝበ ክርስቲያኑን ወንጌል በማስተማርና ቀድሶ በማቍረብ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል።

የድርሰት (የጽሑፍ) ሥራ፡-

 • «በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ» በሚል ርእስ አንድ መንፈሳዊ መጽሐፍ ጽፈው በ1995 ዓ.ም. ለሕዝበ ክርስቲያኑ አበርክተዋል።

ቆሞስ አባ ዘድንግል ኑርበገን፣ ከከፍተኛ ትምህርት ጋር በውጭ ሀገር ቤተ ክርስቲያንን በመመሥረትና በየጽዋዕ ማኅበሩ በመገኘት በዚያ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታቸውን አጽንተው እንዲይዙ ትምህርት በመስጠት፤ የውጭ ዜጎችንም በቋንቋቸው በማስተማር የቤተ ክርስቲያናችን አባላት እንዲሆኑ በማድረግና በክፍለ ዓለማቱ እየተዘዋወሩ በማስተማርና ቀድሶ በማቁረብ እንዲሁም፣ ጉባኤያትን በመሳተፍ በፈጸሙት ዓለም አቀፍ አገልግሎትና መንፈሳዊውንና ዘመናዊውን ዕውቀት አስተባብረው የያዙ ምሁር በመሆናቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠው ለሢመተ ጵጵስና በቅተዋል፡፡

†††

ለበዓለ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት

በካህናት አስተዳደር መምሪያ የተዘጋጀ ያሬዳዊ መዝሙር

ምልጣን

ኃረዮሙ ማትያስ ወጸውኦሙ ለ0ወ5 ኤጲስቆጶሳት

ከመቀስተ ደመና ዘክረምት አክሊለ ክብር አስተቀጸሎሙ

ወወሀቦሙ ሥልጣነ ይፈውሱ ኵሎ ዱያነ

እስመ ለዓለም

ብፁዓን ኤጲስቆጶሳት ገባርያነ ሕይወት

እስመ ሎሙ ይእቴ መንግሥተ ሰማያት

ጥቅመ አዳም ስነ ራእዮሙ ለእለ ድኅኑ

አክሊላቲሆሙ ከመቀስተ ደመና ዘክረምት

ዘግቡር በናርዶስ ዘኢይትከሃል ለጠይቆ

ዘዓይን ኢርእየ ወእዝን ኢሰምዓ ይሁቦሙ

ዓስቦሙ ክርስቶስ አምላኮሙ ለአበዊነ ኤጲስቆጶሳት

ወረብ

ኃረዮሙ ማትያስ ፓትርያርክ ወጸውኦሙ ለ1ወ5 ኤጲስ ቆጶሳት

ከመቀስተ ደመና ዘክረምት አክሊለ ክብር አስተቀጸሎሙ አክሊለ ክብር

ለበዓለ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማእከላውያን መዘምራን የቀረበ ያሬዳዊ ዝማሬ

ጸሎትክሙ ጽንእት

ወረብ

ጸሎትክሙ ጽንእት ሃይማኖትክሙ ርትዕት እንተ በኵለት ረድእ።

ሠናያን ወውርዝዋን በምግባረ ጽድቅ፥ አግአዝያን አንትሙ

እለ መነንክምዎ ለዝንቱ ዓለም ኃላፊ።

 

ሕዝበ ቅዱሳን

መዝሙር

ሕዝብ ቅዱሳን ሕዝብ ቅዱሳን ውሉደ ብርሃን።

አእማደ ቤተ ክርስቲያን አንትሙ አእማደ ቤተ ክርስቲያን።

 

ሰላም ለክሙ፤

መዝሙር

ሰላም ለክሙ ኦ ማኅበራኒሁ ለክርስቶስ፥

እለ ተጋባእክሙ በዛቲ (ዕለት) መካን።

ጳጳሳት፥ ቀሳውስት፥ ወዲያቆናት፥ ሕዝበ ክርስቲያን፥

ጽኑዓን በተዋሕዶ ሃይማኖት ርትዕት።

ለበዓለ ሢመቱ የቀረቡ ቅኔያት

በመጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ

1ኛ ኵልክሙ

የማነ እዴከ ፈኑ ኀበ ውሉድከ፤

በዲበ ርእሶሙ ትንበር ወትግበር ተስካረከ።

እስመ አልብከ ጥሪት በመንግሥተ ሰማይ ቤትከ።

እንበለ አሐቲ ቡራኬ ዘለከ።

ወበውስተ ዓለም በረከትከ፤

ምሉአ ሰማይ ወምድር በኀበ ቆምከ ወኖምከ።

ለዓለም

ዘልፈሂ በቅዳሴከ እንዘ ትዜከር ኪያከ።

ታስቆቁ አቅሌስያ መርዓትከ ወእምከ።

ወብፅዕት ይእቲ በውስተ ዕረፍታ ነፍስከ።

እለይሜህሩ (ይትናገሩ) በልሳን አምጣነ ተወልዱ ህየንቴከ።

ኦ ጳውሎስ ዘኢይመውት ስምከ።

እለ ይሜህሩ በልሳን አምጣነ ተወልዱ ህየንቴከ።

2ኛ መወድስ

እምአርባዕቱ አህጉር አስተጋብኦሙ፤

ወረሰዮሙ አሐደ በሲኖዶሳዊት ጉባኤ።

ዘኢያደሉ ለገጽ ዘመንፈስ ቅዱስ ጽዋኤ።

ለዘኃረዮሙ በ2(በክልኤ) ሱባኤ።

አበዊነ ኅሩያን፤

ቤተ ክርስቲያን ትትሐደስ ወከመ ትግበር ትንሣኤ።

ለዓለም

ስርናየሂ አስተጋብአ በተዋሕዶ መስኤ።

እምድኅረ አንጽሐ ዐውደ እክሉ ወአስተዳለወ ተጋባኤ።

ሲኖዶስ ማእምር ማእምረ ማእምራን መጻኤ።

ወዘኢየአምር ለመርዔቱ ድቃሰ በዝንጋኤ

3ኛ ኵልክሙ

በዘመነ ቅዱስ ማትያስ ለእመ ሀለዉ፤

ምንተ ይብሉ ለኢትዮጵያ ለሕዝባ።

ዘአሰርዎ በቃል ወአፈድፈዱ ማዕቀባ።

ሚካኤል አባ ወገብርኤል አባ።

እስመ ለማትያስ በዘመኑ፤

ነሲአ ጸጋ ለርእሳ ለኢትዮጵያ ተውኅባ።

ለዓለም

ሲኖዶስሂ አመ አውገዘ ለጽሕፍተ ዓረብ ንባባ።

ወአንሥአ ማዕቀበ እለ አንበርዎ እለጉባ።

ዙርአምባ ተሐስየት ወተፈስሐት ዋልድባ።

ወየበበት ጉንዳጉንዲ እስመ ነስአ ወረከባ።

ግእዛነ ርእሶን ስፉሐ እንበለ አሐቲ አፀባ።

ወየበበት ጉንዳጉንዲ እስመ ነስአ ወረከባ።

4ኛ መወድስ

ውሉደ ማትያስ ንሑር መንገለ ቤቶሙ፤

ለነገሥተ ዓለም ሥላሴ፥ ዮም ቅድመ ቅዳሴ።

እስመ በበመንታ ወለደት በቤተ አጋእዝት ሥላሴ።

ሠያሚት እዴሁ ለማትያስ ሙሴ።

ቤተ ክርስቲያን ዘተዋሕዶ፤

ከመ ኢትኩን ግድፍተ በአምሳለ ግዱፍ ምናሴ።

ለዓለም

ኢታፍቅሩሂ ወኢትዕመኑ ዓለመ ሥጋ ፈላሴ።

ዘተጸዋእክሙ ለመከራ ወተደለውክሙ ለሕዳሴ።

አበው አንትሙ ዓለመ ከንቱ ውዳሴ።

እስመ ቀርበ ለሙስና ወሚመ ለድምሳሴ።

5ኛ ኵልክሙ

ማትያስ አንሥእ በትረ ሥልጣንከ፤

ወቤተ መቅደስከ አንጽሕ ከመ እግዚእከ በቅድምና።

በበትረ ሥልጣኑ አንጽሐ ለምኩራበ አይሁድ መካና።

በእደ ረበናት ፍቅረ ንዋይ፤

ወርኩሰት ዘመዱ ለዘመድ ሙስና።

በዐውደ ምሕረት አፀደ ወይና፤

አኮኑ ተገድፈት ቤተ ክርስቲያን ሶስና።

 

ለዓለም

እለቦኡሂ በመቅደስከ በስመ ካህናት በፍና።

ወእለ ተጸውኡ በስምከ ወበስመ ጴጥሮስ ወልደ ዮና።

እንዘ የኃጥኡ ክብረ ወይሰይጡ ሕሊና።

ወለጥዎ በሙስና ለሀብቶሙ ቅድስና።

ለደዌ ሥጋ ሙስና እስመ ኃጣእከ ሆሣዕና፤

ወለጥዎ በሙስና ለሀብቶሙ ቅድስና።

 

Advertisements

2 thoughts on “ለሢመተ ጵጵስና የተመረጡት ቆሞሳት አጭር የሕይወት ታሪክ

 1. Anonymous July 16, 2017 at 5:55 pm Reply

  አባ ብርሀነ መስቀል እንቆ ባህሪ የተወለዱት በ አቡነ ቄርሎስ መልካም ፈቃድ ይሆን ?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: